ግርማ ካሣ

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዙሪያ ለአንባቢያ ያቀረብኳቸው ሁለት መጣጥፍት ከፍተኛ የአንባቢያን አስተያየቶችን እንደጫሩ ለማየት ችያለሁ። የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ኤሜሎች በብዛት የደረሱኝ ሲሆን፣ በአቡጊዳ ድህረ ገጽ ላይ የቀረቡ አሰትያየቶች ከወትሮ እጅግ የበዙ ነበሩ።

በጽሑፌ ቅር የተሰኙ፣ ለምን ቅር እንደተሰኙ በአግባቡ ለመግለጽ ያልቻሉ፣ ያቀረብኳቸውን ነጥቦች ትክክል እንዳልሆኑ ለማሳመን የራሳቸውን መከራከሪያ ያላቀረቡ፣ ሃሳቤን በነጻ የመግለጽ ዴሞክራሲያዊ መብቴን እንዲሁ በደፈናው ተጋፍተው የስድብ ውርዥብኝ ያወረዱብኝም ጥቂቶች አይደሉም።

የስድብ ፖለቲካ የትም አያደርሰንም!

ከቀረቡልኝ አስተያየቶች መካከል በአንድ በኩል ያሳቀኝን፣ በሌላ በኩል ግን ያሳዘነኝ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ በአቡጊዳ የለጠፈውን አስተያየት ከዚህ በታች አቅርቤዋለሁ። የሁለት ወያኔዎች ወግ በሚል ነበር አስተያየቱ የተሰጠው።

–ሰማህ!
..ምኑን?
–አንድ ግርማ ካሳ የተባለ ሰው በኢንተርነት ብርሃኑ ነጋን ደህና አድርጎ አገባለት
..እንዴት እባክህ?
– “ሰላማዊ ትግል አይሰራም እያለ ይዘባርቃል፤ በሶስት አመት ግንቦት7 የፈየደው ነገር የለም …ምናምን” እያለ…
..ወግ አይቀር– ”ምን ይዞ ጉዞ አለ” አማራ ሲተርት–ደርግን ለመጣል ስንት አመት እንደወሰደብን አያውቅም ማለት ነው? እንዲሁ እርስ በርስ ሲበላሉ አይደለም ሶስት አመት አይደለም ሰላሳ አመት የትም አያደርሳቸው
–ይልኩንስ እኔ የደወልኩልህ ነገሩ ወዲህ ነው
..እንዴት ማለት!
–እነዚህ ተቃዋሚ ተብዬዎች ተስፋ ሲቆርጡና ወደ እኛ ጠጋ ጠጋ ማለት ሲፈልጉ፣ የራሳቸውን ሰውና ግሩፕ በአደባባይ ድባቅ ማግባትን ይመርጣሉ–የግርማ ካሳም ጽሁፍ ይዘት ይህን ይመስላል–ሰለሞን ተካልኝን ታስታውሰው የለ?
..i understand perfectly! ይህን ካልክሰ የጌታ ክርስቶስ ልደት የሚከበርበት ቀን ደርስዋል–የገና ስቶጣ መሆኑ ነው! አሃሃሃ!!!
–ስለሆነም እንዲህ አይነቱ ወላዋይ በጣም ይጠቅመናል–በዚያ ላይ ቦታ ቢሰጠውና ትንሽ ብር ብናስታቅፈው ግንቦት ሰባትን ገትሮ ይይዝልናል ብዬ አምናለሁ
..እርግጠኛ ነህ? ይህ ሰው ለመንበርከክ ተዘጋጅቷዋል?
–እንዴታ! ፈርቶ ነው እንጂ ልቡ ከእኛ ጋር ሳይሆን አይቀርም። እንዲያውም ወያኔ በሩን ከከፈተልን ለመወያየት ዝግጁ ነን ብሎ በብእሩ አሰፍርዋል።
..ታዲያ ምን ትጠብቃለሀ! አስገባዋ! በሩ ክፍት ነው በለው–እንደተለመደው የተራረፈንን እንወረወርለታለን!!”

በመጀመሪያ ላነሳ የምፈልገው ነጥብ ቢኖር ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ እኛ የኢትዮጵያዊያን (በተለይም በውጭ አገር ያለን) ያሉንን ልዩነቶች አቻችለን፣ እንደ ጨዋ፣ በሰለጠነ መልኩ መነጋገር አለመቻላችን ነው። ከኛ የተለየ አስተያየት አንድ ሰው ስለሰጠ፣ እኛ የምንደግፈውን ድርጅት አንድ ሰው ስለተቃወመ፣ ያንን ሰው እንደ ጠላት የማየት ዝንባሌ አለን። ማንም ዜጋ ሃሳቡን በነጻነት የመግልጽ መብት ያለው ይመስለኛል። ሰዎች ከፈለጉ የኢሕአዴግ ደጋፊ የመሆን ሙሉ መብት አላቸው። ኢሕአዴግን ስለደገፉ የሚሰደቡበት ምንም ምክንያት የለም። ይልቅስ የሰለጠነው ፖለቲካ የምንቃወማቸውን መስደብና ማዋረድ ሳይሆን የምንቃወማቸውን አሳምነን ወደ እኛ ማምጣት ነው። ፈረንጆች the power of persuasion ይሉታል።

የተቃዋሚ ድህረ ገጾች ተሃድሶ ያስፈልጋቸዋል

ሌላው ላነሳ የምፈልገው ነጥብ የተቃዋሚ ድህረ ገጾችን በተመለከተ ነው። ከጥቂት ወራት በፊት ኢትዮጵሜዲያ «ግርማ ካሳ የወያኔ ፕሮፖጋንዲስት ነው» ሲል ክስ ማቅረቡ ይታወቃል። የዶ/ር ብርሃኑ ነጋን የኢሳት ቃለ መጠይቅ ኢካዴፍ፣ አዲስ ድምጽ፣ ኢትዮሜዲያ እና ቋጠሮ ድህረ ገጾች አውጥተውት አይቻለሁ። ዶ/ር ብርሃኑ በኢሳት ለሰጡት ቃለ መጠይቅ ያሉኝን አስተያየቶች፣ እነዚህን ድህረ ገጾች ጨምሮ፣ ለበርካታ ሜዲያ ግሩፖች ልኪያለሁ። ነገር ግን ከአቡጊዳና ከኢትዮጵያ ዛሬ በስተቀር እንደ ኢትዮሜዲያ ያሉ ታዋቂ ድህረ ገጾች አስተያየቴን ሊያስተናግዱ ፍቃደኛ አልሆኑም። በሌላ አባባል ነጻ የሃሳቦች መሸራሸርን እያገዱ ነው ማለት ነው። በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አቶ መለስንና ድርጅታቸውን መቃወም እንደማይቻል፣ በነዚህ ድህረ ገጾችም እንደነዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ያሉ የተቃዋሚ መሪዎችን ለሚናገሩትና ለሚሰሩት ስራ ተጠያቂ ማድረግ አይቻልም።

ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ነጻ ብሎጎች በሽ በሽ በሆነበት ዘመን፣ ሃሳብን ለሕዝብ ማሰራጨት ከመቼውም የበለጠ ቀላል እንደሆነ ሁላችንም የምንዘነጋው አይመስለኝም። እንደ ኢትዮጵያዊ ሃሳባችንን በነጻ እንዳንገልጽ፣ እነዚህ ድህረ ገጾች፣ እገዳ ቢያደርጉም፣ ሃሳብችንን ከመግልጽ ለአገራችን ያለንን አስተዋጾ ከማድረግ የሚከለክለን ምንም ነገር እንደሌለ መቼም የሚታወቅ ይመስለኛል።

ነገር ግን ይህን የምጽፈው እነዚህ ለዲሞክራሲ ቆመናል የሚሉ ድህረ ገጾች እራሳቸውን እንዲመረምሩ ነው። ለዲሞክራሲ መቆም የሚጀመረው ከራስ ነው። እኛ የማናደርገውን ነገር ሌሎች እንዲያደርጉ መጠበቅ የለብንም። እኛ ሳንሱር እያደረግን፣ ከኛ የተለያ አስተያየት ያላቸውን ዜጎች ወያኔ ሆዳም ብለን እየሰደብን፣ እኛ መስማት የምንፈልገውን አስተያየቶች ብቻ እያስተናገድን፣ ለዴሞክራሲ ቆመናል ማለቱ ትንሽ የሚያሰኬድ አይመስለኝም።

በጣም የሚገርመው ደግሞ እነዚህ ስድብና ወገዛ የሚያበዙ ወገኖች እነርሱን አገር ወዳድ ሌሎቻችን ኢትዮጵያ ለማፍረስ የተነሳን የኢትዮጵያ ጠላቶች፣ እነርሱን ታጋይ፣ ሌሎቻችንን ለሰላምና ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል ለመጉዳት የተሰማራን አድርገው ማቅረባቸው ነው።

እውነት እንነጋገር ከተባለ፣ በተቃዋሚው ጎራ የሚታየው ይህ አይነት ያለመቻቻልና የመሰዳደብ ፖለቲካ ነው ከምንም በላይ ትግሉን እየጎዳው ያለው። የተማሩ ዜጎች፣ ለአገራቸው አስተዋጾ ማድረግ የሚፈልጉ፣ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው እንጭጭ በሆኑ ላላመሰድ ሲሉ፣ በራቸውን ዘግተው ከትግሉ የሸሹ ብዙ ናቸው። እንግዲህ ይህ የዜጎች ከትግሉ መሸሽ ነው ትግሉን ክፉኛ የሚጎዳው። ነጻ፣ ዲሞክራሲያዊ ውይይቶችን ማድረግ እንደውም የበለጠ እንድንግባባ የሚያደርግ ትግሉንመ የሚጠቅም ነው። የሚያሳዝነው በርካታ የሜዲያ ወገኖቻችን ይህን መረዳት አለመቻላቸው ነው።

ሁላችንም ቆም ብለን በረጋ መንፈስ ማሰብ ያለብን ይመስለኛል። አቶ መለስ ላይ መጀመሪያ ከማነጣጠር በፊት እራሳችን ላይ ማነጣጠር አለብን። በተቃዋሚ ወገን ነን የምንል ሁሉ፣ ስር ነቀል የአስተሳሰብ ለውጦች ማድርግ ይኖርብናል። ከጥላቻ፣ ከእልህ፣ ከስድብ ፖለቲካ ወጥተን ዜጎችን የማቀራረብ፣ በኢሕአዴግ ካምፕ ያሉትን ሳይቀር ወደ ዴሞክራሲው ካምፕ የማምጣት፣ የሚያዋጣና የሰለጠ ፖለቲካ ማራምድ መጀመር ይኖርበናል።

የኦነግ ውሳኔ ኢትዮጵያዊነት ማሸነፉን ያሳል!

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በኢሳት ቴሌቭዥን በቀረቡበት ጊዜ ከተጠየቋቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ከኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር ጋር ድርጅታቸው ግንቦት ሰባት ስላለው ግንኙነት ነው። ሁሉም የተቃዋሚ ኃይሎች ኦነግን ጨምሮ፣ በአንድ ላይ መሰባሰብ እንዳለባቸው ዶክተሩ ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ከኦነግ አንጃዎች ጋር በሙሉ እየተነጋገሩ የኦነግ አንጃዎችንም ለማስማማት እየሞከሩ እንደሆነም ሳይጠቁሙ አላለፉም።

ከጥቂት ቀናት በፊት በጀኔራል ገልቺ የሚመራው የኦነግ ቡድን የኢትዮጵያን አንድነት ተቀብሎ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት ለመታገል መወሰኑን ይፋ አድርጓል። በአንጻሩም ደግሞ በዳዎድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ ቡድን ባወጣው መግለጫ «የኦሮሞ ጥያቄ ከሌላው ሕዝብ ጥያቄ የተለየ ነው» በሚል ዘረኛና ከፋፋይ ምክንያት የነጄነራል ገልቺን ቡድን ሲያወግዝ የግንቦት 7 ድርጅትን « የኦነግን ለመድ የለበሱ ጥቂቶች » ሲል ከሷል።

አብዛኛው የኦነግ አባላትን ያቅፋል የሚባለው የጀነራል ገልቺ ቡድን በይፋ ኢትዮጵያዊነትን ማወጁ በርግጥ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ሊያስደስት የሚገባ ትልቅ ዜና ነው። ይህን ስል ኦነግ ትልቅ ነገር ያመጣል በሚል አይደለም። ኦነግ ኤርትራ ወይንም አሜሪካ ተቀምጦ፣ ትግሉን በአገር ቤት በሪሞት ኮንትሮል ሊመራ አይችልም። ኦነግ ምናልባት ከግንቦት ሰባትና ሌሎች ድርጅቶች ጋር በውጭ አገር አንድ ትልቅ ኢትዮጵያዊ ስብስብ ቢፈጥርም፣ ትግሉ አገር ቤት ነውና፣ በአገር ቤት ያሉ ድርጅቶች ጋር እስካላበረ ወይንም አገር ውስጥ ገብቶ እስካልታገለ ድረስ ብዙም የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።

ነገር ግን ፖለቲካውን ነው ማየት ያለብን። የኦነግ ኢትዮጵያዊንትን መቀበል፣ በምርጫ ዘጠና ሰባት ሕዝቡ ኢትዮጵያዊነትን በመምረጡ የተመታው፣ በመድረክ ምስረታ የተዘረረው የሕወሃት/ኢሕአዴግ የዘር ፖለቲካ፣ የበለጠ ድባቅ እንደገባ ነው ያሳየው። ኢትዮጵያውያን በዘር በሃይማኖት እንደማይከፋፈሉ በድጋሚ እንዲረጋገጥ ነው ያደረገው። ለ19 አመታት በሕዝብ ጫና ላይ በጉልበት የተዘረጋው የአቶ መለስ ዜናዊ የኋላቀር ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ መሸነፉን፣ ኢትዮጵያዊነትም ማየሉን ነው ያወጀው።

በኦነግ የአቋም ለውጥ የግንቦት ሰባት ሚና

እነጀኔራል ገልቺ ከአራት አመታት በፊት ከነዳዎድ ኢብሳ ሲለዩ፣ በይፋ አልወጡም እንጂ፣ ውስጥ ውስጡን፣ «ኢትዮጵያዊያን ነን፤ ከተቀሩት ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ጋር አብረን መስራት አለብን» ይሉ እንደነበረ፣ ከነዳዎድ ኢብሳ ጋር የተለያዩበት ዋናው ምክንያትም ይሄ እንደነበረ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሲናገሩ ሰምቻለሁ።

ለዚህም ነው እነጄነራል ገልቺ ወደ ኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ኦነግ እንዲመጡ ሲያደርጉ፣ ግንቦት ስባት አስተዋጽኦ አደረገ ብዬ የማላምነው። ነገር ግን እነጀነራል ገልቺ፣ በውስጥ የሚያራምዱትን አቋም በይፋ እንዲያወጡ በማድረጉ አንጻር፣ ግንቦት ሰባት ጉልህ ሚና የተጫወተ ይመስለኛል። ለዚህም መመስገን አለባቸው ባይ ነኝ። ትልቅ ነገር ነው ያደረጉት።

ከግንቦት ሰባት አብዛኞቹ የአመራር አባላት ጋር ትውውቅ አለኝ። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ቅንጅትን ወክለው በቺካጎ ባደረጉት ስብሰባ፣ የስብሰባው ሞደሬተር ነበርኩኝ። ቃሊት እሥር ቤት ታስረው በነበረ ጊዜ የተሸጠውን ትምህርት ሰጪ መጽሃፋቸውን፣ በቺካጎ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲከፋፋል ያደረኩት እኔ ነኝ። ስለሰላማዊ ትግል ይናገሩት የነበረው ሁሉ፣ ልብን የሚስብና የሚማርክ ነበር። ትዝ ይለኛል አንድ ቀን ያሉት፣ «እነርሱ (ኢሕአዴጎች) መሳሪያ አላቸው። ሊገድሉን ይችላሉ። እኛም የራሳችን ሽጉጥ አለን፤ ፍቅር የሚባል» ነበር ያሉት።

ዶ/ር ብርሃኑ የሰላማዊ ትግል መሪ በነበሩት ጊዜ በጥቂት አመታት ውስጥ ትልቅ አስተዋጾ ያደረጉ ሰው ናቸው። በብዙዎች ዘንድ ዶ/ር ብርሃኑ አሁን ያላቸው ፍቅርና ከበሬታ፣ በግንቦት ሰባት መሪነታቸው ያገኙት ሳይሆን በቅንጅት መሪነታቸው፣ በሰላማዊ ትግል ባስመዘገቡት ውጤት፣ ያገኙት ነው። የግንቦት ሰባት የሌለ የትጥቅ ትግል ያታረፈላቸው ነገር ቢኖር፣ እንደ እኛ ካሉ ከብዙ ደጋፊዎቻቸው ጋር መጋጨትን ነው።

ግንቦት ሰባት ከኦነግ ጋር ባደረጋቸው የመናገገርና የመወያየት እንቅስቃሴዎች ውጤት ሲያመጣ፣ ያደረጋቸው የሰላማዊ እንቅስቃሴ መሆናቸውን አንርሳ። የግንቦት ስባት መሪዎች የሰላማዊ ትግል መሳሪያ የሆኑትን፣ መጻፍ፣ መናገር፣ ማግባባት የመሳሰሉትን መጠቀም ይችሉበታል። ለምሳሌ ተመልከቱ «የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ከተመሰረተ በየሳምንቱ የሚያወጣቸው ጋዜጣዎች ወደ ቁጥር 189 ደርሷል። ( ከ189 ሳምንታት ወይንም ሶስት አመት ከሰባት ወራት በፊት የተጀመረ)

ስለ ጦርነት የማውራት፣ እንዲሁ በባዶ የመፎከር ፖለቲካ አያምርባቸው። አይችሉበትም። መቼም ሁላችንም የምናስታወሰው ነው። ሲመሰርቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወያኔ ያበቃለታል ብለው አምስት መቶ ብሮች ከደጋፊዎቻቸው ሲሰበስቡ ነበር። ያ ሳይሆን ሲቀር ደጋፊዎቻቸው “ምንድን ነው እየተሰራ ያለው ?” ብለው መጠይቅ ሲጀምሩ ወደ አስመራ ሄዱ። ከአርበኞች ግንባር ጋር አንዳንድ ነገር ለማድረግ አስበው፣ መንቀሳቀስ ጀመሩ። ሻእቢያ የአርበኞች ግንባር መሪዎችን ወስዶ አሰረ። በዚያም በኩል ያለው ነገር ከሸበፈባቸው። “የትጥቅ ትግል፣ ሁለ ገብ ትግል ወዘተረፈ ” የሚሉት ነገር በጭራሽ ሳያዋጣላቸው ቀር። አልሰራላቸውም። በዚያ ረድፍ ያመጡትም ሆነ ያስመዘገቡት አንዲት ውጤት የለም። አንዲት ቀበሌ አልተቆጣጠሩም፣ አንድ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለስልጣን አልገደሉም። ዜሮ!! ባዶ!!!!

ግንቦት ሰባት ያስመዘገበው ትልቅ ውጤት ቢኖር የጠመንጃን ሳይሆን የማሳመንን፣ የቃላትን ኃይል በመጠቅም ያስመዘገበው ውጤት ነው። ወደዚህ በችሎታቸው ውጤት ሊያመጡበት ወደ ሚችሉበት ትግል ተመልሰው እንዲመጡ ነው ጥሪ የማቀርብላቸው። የግንቦት ሰባቱን ዶ/ር ብርሃኑን አንፈልግም። የቅንጅቱን ዶ/ር ብርሃኑ ይመለሱልን ነው የምንለው።

ትብብር ስለመፍጠር

ትብብርን ለመፍጠር በስፋት እንደሚንቀሳቀሱ የግንቦት ሰባት መሪዎች ይናገራሉ። ይህንን ጥረታቸው ልቃወም አልችልም። በተለይም በውጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሊያሰባስበው በሚችል፣ በአንድ ትልቅ ኃይል ስር መሰባሰቡ ትልቅ ጥቅም ነው የሚኖረው። በአውሮፓ ሕብረት፣ በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንትና ኮንግረስ ተሰሚነት እንዲኖረንና በዲፕሎማሲው አንጻር ከፍተኛ ተጽእኖ ማድረግ እንድንችል፣ አንድ ድምጽ ሊኖረን ይገባል። ለዚህም የሁላችንም መተባበር አስፈላጊ ነው። በአሁኑ ወቅት አንድ ድምጽ የለንም። በዚህም ምክንያት በተጠናጥል የምናደርጋቸው የተለያዩ ጥረቶች ውጤት ሊያመጡልን አልቻሉም።

«እንዴት እንሰባሰብ ?» የሚለው ጥያቄ ተከትሎ የሚመጣ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። ትብብርን ለመፍጠር ከሚያስፈልጉት አበይት ነጥቦች መካከል ዋናው ቅንነት ነው። ብዙዎች በውጭ አገር የሚደረገውን ፖለቲካ እንደ ኑሯችን ያደረግን አለን። በመሆኑም ጥቅማችን ከተነካ፣ ምንም ለአገር ይጠቀም፣ ትብብሩ እንዳይሳካ ችግር ከመፍጠር ወደ ኋላ አንልም፡፡

ሌሎቻችን ደግሞ ዝና እንፈልጋለን። መምራት እንጂ መመራት፣ ማዘዝ እንጂ መታዘዝ አንወድም። በየመድረኩ የአንቱታ የክብር ቦታ እንፈልጋለን። እኛ ካልመራነው በቀር ምንም አይነት ትብብር አንደግፍም።

ነገር ግን ሁላችንም ከጥቅማችን እና ከዝናችን ይልቅ አገራችንን ካስቀደምን፣ በቅንነት ከተነጋገረን፣ ያሉንን ልዩነቶች ማናጠብበት ምንም ምክንያት ያለ አይመስለኝም። ቅንነት ካለ እንከባበራለን። እንቻቻላለን። አንሰዳደብም።

ሁለተኛ እንድንሰባሰብ የሚያደርገን ነገር፣ ከፊታችን የተቀመጠ፣ ልንደርስበትና ተግባራዊ ልናደርገው የምንችለው የተጨበጠ አላማ ወይንም ግብ ነው። ትብብር ስንፈጥር ለምን እንደምንተባበር ማወቁ አስፈላጊ ነው። የት እንደምንሄድ ሳናወቅ ጉዞ አንጀምርምና።

አንዳንዶቻችን ወያኔን ለማስወገድ ነው መጓዝ ያለብን እንላለን። በአገራችን ሰው መግደል፣ ሰው ማሰር፣ ግፍ መፈጸም እኮ የተጀመረው በወያኔ አይደለም። ከዚያ በፊት ነው። ወያኔም ብትሄድ፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣው በሌላ መልኩ ሊቀጥል ይችላል።

በመሆኑም ወያኔን ማስወገድ የሚለው አላማ የሚያሰባስብ አላማ አይመስለኝም። ነገር ግን፣ «አንዲት ኢትዮጵያን ማቆየት፣ በአገራችን ሰላም፣ ዲሞክራሲ የሕግ የበላይነትን ማስፈን፣ ሕዝባችንን ከድህነት ማውጣት ..» የሚሉ የተቀደሱ አላማዎች ይዘን ብንወጣ ግን ሁላችንም በቀላሉ ልንስማማ እንችላለን።

ሶስተኛ አስፈላጊ ነጥብ፣ «ወደ ዘረጋናቸው ግቦች ለመድረስ የትኛውን መንገድ ነው መያዝ ያለብን ? » በሚለው ጥያቄ ላይ ስምምነት ላይ መድረሱ ነው። እንዲሁ በደፈናው «ይሄ ያዋጣል፣ ያ አያዋጣም» በሚል ሳይሆን በቅንነት፣ ሁሉን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በማመዛዘን፣ ተነጋግረን ተወያይተን፣ ከስሜት፣ ከጥላቻና ከእልህ በጸዳ መልኩ፣ የሚበጀንን መንገድ በጋራ መርጠን፣ በዚያ መሰረትም በአንድነት መሰማራት እንችላለን።

ሁለት በጋራ ልናደርጋቸው የምንችላቸውን ምሳሌዎች ልጥቀስ፡

• የግንቦት ሰባት ድርጅት፣ የአንድነት ድጋፍ ማህበራት፣ ሕብረት፣ ኢሕአፓዎች፣ ሶሊዳሪቲ ንቅናቄ፣ ማርች ፎር ፍሪደም፣ በቃ፣ አድቮከሲ ኢትዮጵያ፣ ኦነግ …የመሳሰሉ በውጭ አገር ያሉ ድርጅቶች፣ አንድ በተቀናጀ መልኩ፣ ውጤት የሚያመጣ የዲፕሎማሲ ሥራ የሚሰራ፣ በዚያ ረገድን በውጭ የሚደረገውን የዲፕሎማሲ ትግል የሚመራ አካል ማቋቋም ይችላሉ።

• በአገር ቤት ያሉ በከባድና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እየታገሉ ያሉትን የሲቪክ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በገንዘብና በሞራል መደገፍ እንችላለን። በየቦታው ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንዲያደርጉ፣ ጋዜጣዎችን በስፋት እንዲያሳትሙና እንዲያሰራጩ፣በየወረዳው ጽ/ቤቶችን እንዲከፍቱ በማድረግ አንጻር ትቅል ሚና ልንጫወት እንችላለን።

• የታሰሩ ወገኖቻችን ቤተሰቦችን መርዳት፣ ለጠበቃዎቻቸውና ለተለያዩ ጉዳዮች የሚያስፈልጉትን ወጪዎች መሸፈን የመሳሰሉ ቁልፍ ተግባራትን መፈጸም የሚከብደን አይመስለኝም።

እነዚህን እንደምሳሌ የዘረዘርኳቸውን ተግባራት ከማድረግ ውጭ፣ ሌላ «ሊሰሩ የሚችሉና በመላ ምት ሳይሆን በተጨባጭ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ ተግባራት አሉ የሚሉ ወገ»ኖች ካሉ፣ ሃሳባቸውን ጠረቤዛ ላይ ያስቀምጡ። እንየው እናጥናው። እስከተመካከርንበትና እስከተነጋገርበትን ድረስ፣ ካመንበት፣ አብረን የማንሰለፍበት ምክንያት ይኖራል ብዬ አላስብም።

በአራተኛነት የማስቀምተጠው «ለመለያየቶቻችን ምክንያት የሚሆኑትን ኮንትሮቨርሻልና ከፋፋይ የሆኑ ነገሮችን ከኛ ማራቅ» የሚለውን ነው።

ኦነግ ኢትዮጵያዊነትን በመቀበሉ ከብዙ የአንድነት ኃይሎች ጋር አብሮ የመስራት በሩን በእጅጉ ከፍቶለታል። የመገንጠል ጥያቄን እያነሳ፣ ኢትዮጵያዊነትን እያረከሰ፣ ከሕውሃት/ኢሕአዴግ የባሰ እንጂ ያልተሻለ ዘረኛ ፖለቲካን እያራመደ ከኦነግ ጋር ትብብር መፍጠር የሚቸግር ነበር ።

በአሁኑ ጊዜ ከግንቦት ሰባትም ሆነ ከኦነግ ጋር አብሮ ለመስራት ትልቅ እንቅፋት ይሆናል ብዬ የማስበው አንድ ትልቅ ጉዳይ አለ። እርሱም ከሻእቢያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ነው። ጽ/ቤቶቻቸው አስመራ እስከሆነ ድረስ፣ ከኢሳያስ አፈወርቂ ተጽእኖ ነጻ ናቸው ማለት አይቻልም። ሻእቢያ ኢትዮጵያውያን እንድትከፋፈል ያደረገ ቡድን ነው። በሻእቢያ ምክንያት መከፋፈላችንን መቀጠል የለበትም። ከሻእቢያ ጋር ሆነን የትም መግፋት በጭራሽ አንችልም። የተከበሩ አባቴ አቶ ሮቤል አባቢያ በጥሩ ሁኔታ አስቀምጥውታል።

“Ethiopians should at least strongly suspect that Isaias Afeworqui and Meles Zenawi are still buddies ”keeping their tents apart but their hearts together” as the old adage goes. These two despotic rulers must be dethroned by their respective oppressed peoples for the sake of regional stability, tranquility, democracy and prosperity.” ነበር የጻፉት አቶ ሮቤል።

በመሆኑም ከሻእቢያ ጋር የተቃቀፉ ኃይላት እጃቸውን እንዲሰበሰቡ፣ ለኢትዮጵያውያን መሰባሰባና አንድነት ሲሉ ከሻእቢያ እንዲለዩ የግድ ነው። አፍቃሪ ሻእቢያ የሆኑ ድርጅቶች አቋማቸውን በአስቸኳይ የማያስተካክሉ ከሆነ፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ወደ አንድ የጋራ አቋም በነዚህ ድርጅቶች ላይ መድረስ ያለብን ይመስለኛል። ይህ በኢትዮጵያ ለውጥ ላማምጣት የሚደረገው ትግል ጨዋታ አይደለም።

ለሁላችንም ባለንበት ቦታ ቸር ይግጠመን!


ግርማ ካሣ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!