ከአባኪያ

እንደመግቢያ እንደመነሻ

ይሄንን ጽሁፍ እየጻፍኩ እያለ ጓደኞቼ የላኩልኝን በቻይና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ለማቋቋም ሲሞክር ስለታሰረ ሰውና እየተመላለሰች ስለምትጠይቀው እህቱ የሚያትት ጽሑፍ ሳነብ፣ የሚማርክና ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ሃሳብ አገኘሁበትና እዚህች መጣጥፍ ላይ ሻጥ ላደርጋት አሰብኩ። ያው የቻይና መንግሥት ክስም እንደ ኢህአዴግ መንግሥት ክሶች ተመሳሳይ ነው። መንግሥት ለመገልበጥ ወይም ለመጣል አሲራችኋል አይነት ነገር። የጽሑፉ አቅራቢ ሴት፣ በዚህ ክስ የታሰረ ሕመምተኛ እስረኛ ወንድሟ በሕክምና አመክሮ ካገር ሊወጣ እንደሚችል የተሰጣትን ምክር ይዛ ምን እንደሚያስብ ብትጠይቀው፣ “I will not leave China unless my freedom of return is guaranteed” (ወደቻይና የመመለስ መብቴ ካልተረጋገጠልኝ በስተቀር አገሬን ለቅቄ አልሄድም) አላት።

 

ይሄንን አይነት አገሬን ጥዬ አልሄድም ጀግንነት ኢትዮጵያ እነ ራስ አበበ አረጋይ፣ እነ በላይ ዘለቀ ጋር ብቻ ይመስለኝ ነበር። ይሄ አገሬን ጥዬ አልሄድም ጀግንነት ኢትዮጵያ ሲያበቃ፣ ሁሉም ቦታ ያበቃ መስሎኝ ነበር። ለካ ቻይናም ጀግና አለ። እንደ ጸሐፊዋ አገላለጽ፣ እስረኛ ወንድሟ በታይናሚን አደባባይ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት ወጣቶች ከተጨፈጨፉ በኋላ ወደ ውጭ የተሰደዱ ተቃዋሚ ቻይናዊያን ባለባቸው የተለያየ ችግር የተነሳ ፖለቲካዊ ስኬታማነታቸው ይቀንሳል ብሎ ያምናል። “Once they leave Chinese soil, their role is very limited” በራሱ አገላለጽም “አንዴ የቻይናን መሬት ከለቀቁ በኋላ ቻይናዊያን ተቃዋሚዎች ያላቸው ፖለቲካዊ ሚና አናሳ ይሆናል” ይቀጭጫል። ይመናመናል። ጽሁፉን እንዳለ ብታነቡት እመክራለሁ (LETTER FROM BEIJING፤ ENEMY OF THE STATE፣ The complicated life of an idealist, By Jianying Zha)

 

በስሱ ነካክቼ ማለፍ ይሆንብኛል እንጂ፣ በዚህ ሰሞን በለስ ቀንቶኝ የፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለማሪያምን መጽሐፍም ሳነብ ምን ያህል ወደ አገር ቤት ለመመለስ የነበራቸውን ጉጉትና በኋላም አጼ ኃይለሥላሴ ከአካባቢያቸው ገለል ሊያደርጓቸው አስበው ወደ ውጭ በመልዕክተኝነት ሊልኳቸው ሲነሱ፣ የጣልያን ጦርነት ኢትዮጵያን ሊበላ ሲያንዣብብ፣ ምን ያህል ከኢትዮጵያ ላለመውጣት፣ (ልብ አድርጉ ላለመውጣት ነው) ያደርጉ የነበረውን ጥረት ተመልክቼ ተደንቄ ነበር። ስለግንቦት ሰባት ብቻ አይደለም ከኢትዮጵያ ውጪ ስለሚደረግ ኢትዮጵያን ነፃ የማውጣት ፖለቲካዊ ትግል ሳስብ የሚነሳብኝ ጥያቄ ይኸው ቻይናዊው እስረኛ ያነሳው ነው። ከኢትዮጵያ ምድር ከኢትዮጵያ ህዝብ በአካል የራቀ ትግል እንደምን ተጨባጭ ድል ማምጣት ይቻለዋል? ግንቦት ሰባትና ግንቦት ሰባታዊያን ይሄንን ጥያቄ ፊት ለፊት መግጠም አለባቸው።

 

ትችት፣ ድጋፍ፣ ምናልባትም ነቀፋ፤ ግን እንደወገን

መቼም ድርጅት ሲቋቋም ሊተች፣ ልምድ እንደሚጠቁመው ሊነቀፍ፣ ሊወረፍ እንዲሁም ሰዎች ሊሉ የሚችሉትን ሁሉ መቆጣጠር አንችልምና ሊዘለፍ ተዘጋጅቶ መሆን አለበት። እንደዚያ ባይሆን ጥሩ ነበር። ግን እንደዚያ ነው። በተለይ በፖለቲካችን ውስጥ ከገንቢ አስተያየቶች ይልቅ፣ አነታራኪ ርዕሶች ዕድሜያቸው በሚረዝምበት ወቅት እንደመወለዱ፣ እንዲሁም ራሱ ግንቦት ሰባት ከረጅምና አሰልቺ እንካሰላንቲያ በኋላ እንደመመስረቱ፣ ባንድ በኩል ለሚሰነዘሩበት ማናቸውም ፖለቲካዊ አፍ እላፊዎች፣ መርዛማ ጉንተላዎችና አልባሌ ክሶች በሌላ በኩል ለገንቢና ቅን ሂሶች መሰናዳት አለበት። ጠላት ተነስቶ ይሄንን ድርጅት በእግሩ መሄድ ከመጀመሩ በፊት እየዳኸ እያለ ሳይተረክከው፣ እንደ ትግሉ አጋር፣ እንደ ደጋፊ ተቺ፣ አንዳንድ አስተያየቶችን መለገስ ከጀልኩ። እንደ ወዳጅ ተቺ መሆኑ ነው ታዲያ። እንደ ባለጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ችግር በፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ብቻ እንዲመከርበትና እነሱው መፍትሄ አንጪ፣ አታጋይ ሆነው እንዲታዩና ሌሎቻችን ደግሞ የሞቀ ኑሮ ላይ ቁጭ ብለን፣ እነሱን የምንተች፣ የምናፋጥጥ እንድንሆን አልፈልግም።

 

ማንም አፋጣጭ፣ ምንም ተፋጣጭ የለም። አንዱ ጠያቂ ሌላው ተጠያቂ መሆን የለበትም። ካፋጠጥንም ጠላቶቻችንን፡ ከተጠያየቅንም እርስ በእርሳችን ነው መሆን ያለበት። ስለዚህ እነዚህን የማለዳ ትችቶች/አስተያየቶች በግንቦት ሰባት የፍትህ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ላይ መሰንዘር ሻትኩ። አስተያየቶቹ ሁሉ ከድርጅቱ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ላይ ምንም የሚቀንሱት ነገር የለም። ግንቦት ሰባት አስፈላጊ፣ ይወለድ ዘንድ የግድና ብዙዎቻችን በጉጉት የምንጠብቀውና የምንመለከተው ነበር። ነውም። የግንቦት ሰባት ልደት ወቅታዊ ነው። አስተያየቶቹ ከዚያ መለስ ናቸው።

 

ስለሥልጣን፣ ከሥጋው እጾማለሁ አይነት ነገር

ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ሳስብ ዘወትርም የሚገርመኝ፣ ግራ የሚያጋባኝ በመጨረሻም የሚያበሽቀኝ የፖለቲካ ባህል የሥልጣን ጥማት ሳይሆን የሥልጣን ወይም ከሥልጣን ሽሸት ነው። ሥልጣን ለመያዝ የሚታገሉ ድርጅቶች ሁሉ፣ ዕድሜ ልካቸውን ሥልጣን ለመያዝ እየተቧቀሱ፣ የለም ለሥልጣን አይደለም የምታገለው የሚሉት ፈሊጥ አላቸው። ይሄ ከመሪዎቹ ነው። የዚህ ባህል ሌላው ጎኑ፣ ሌላው ህዝባዊ ቅጥል፣ እከሌ ሥልጣን ወዳድ ነው የሚባል ነገር ነው። ታዲያ ሥልጣንና ሥልጣን የሚሸከመውን ባንፈልግማ ምን ሥልጣን ከያዙና ሥልጣንን እንዳሻቸው ከሚመነዘሩ ኃይሎች ጋር አሟገተን?! ብዙ ሐተታ ሳናበዛለት የፖለቲካ ትግል ሁሉ እኛ ወይም ሌሎች እኛ የምንፈልጋቸው ኃይሎች ሥልጣን እንዲይዙ የምናደርገው ትግል ነው። ሥልጣን ይይዝ ዘንድ ድንገት የሚወለድ፣ ከሰማይ ዱብ የሚል ልዑል ወይም ልዕልት የሉም። ያ ዘመን አለፈ።

 

የሆነ ሰው ወይንም የሆኑ ሰዎች ሥልጣን መያዝ አለባቸው። ሥልጣንን በሎተሪ ካላደረግነው በስተቀር ደግሞ ሰዎች ሥልጣንን ለመያዝ መፎካከር፣ መወዳደር፣ መደርደር አለባቸው። በሎተሪም ቢሆን እንኳን ቀድሞውንም ሎተሪው ውስጥ ማን ይግባ የሚለው መወሰን አለበት። ስለዚህ ሥልጣን ለመያዝ መታገል መብት ነው። ነውር አይደለም። ነውሩ ሥልጣን ሕጋዊ ወይም ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ለመያዝ መታገል ነው። ከዚህ አንጻር ሥልጣን ለመያዝ እየተሯሯጥንና ሥልጣን ይዘን የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት እንችላለን ብለን እየፎከርን፣ የምንታገለው ለሥልጣን አይደለም የሚለው ድብብቆሽ፣ በተጨማሪም ሥልጣን ለመያዝ የሚታገሉ ሰዎችን እንደ ሥልጣን ወዳድ አድርገን የምንስላቸው ነገር አይዋጥልኝም። አግባብም አይደለም።

 

እነሆ ምሳሌ፣ ቅንጅት የታገለው ለሥልጣን ነው። ኢህአፓ የታገለው ለሥልጣን ነው። ኦባማም የሚታገለው ለሥልጣን ነው። ክርስቶስ ራሱ በምድር ሳለ ከፍተኛው ትንቅንቁ በምድር ላይ ሥልጣን ከነበረው ኃይል ጋር፣ የተሰቀለውም ለሥልጣን ይመስለኛል። በሰይጣን ላይ ለመሰልጠን። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ የተለየ ቅዱስ ተልዕኮ የላቸውም። ሥልጣን ይዞ ሌላ በጉልበት ሥልጣን የያዘ ኃይል ያበላሸውን የኢትዮያን ታሪክ መቀየር ነው አጀንዳቸው። ይህም ነውር አይደለም። ቅንጅት ደግሞ የሰዎች እንጂ የመላዕክት ሕብረት አይደለም። ስለዚህ ከአንጋፋው ፕ/ር መስፍን እስከ ወጣቱ መስፍን አማን፣ ከየዋኋ ብርቱካን ሚደቅሳ እስከ አኩራፊው ኢንጂንየር ኃይሉ፣ ከአንደበተ ርትዑ ብርሃኑ ነጋ እስከ ጥጋበኛው ስብኃት ነጋ፣ … ሁሉም የታገሉት የሚታገሉትም ለሥልጣን ነው። ይሄ ከግንቦት ጋር ምን አያያዘው?

 

ወደ ግንቦት ሰባት ስንመለከት

ወደ ግንቦት ሰባት ስንመጣ ነጥቤ እንዲህ ነው። ምናልባት ይሄንን ጽሑፍ ከማውጣቴ በፊት እንዲተችልኝ የሰጣሁት ወዳጄ፣ እንዳለው ፀጉር መሰንጠቅ ይሆናል። ግን “ዓላማችን ሥልጣን ለመያዝ ሳይሆን” ይላል ግንቦት ሰባት እንደ ግብ ያስቀመጠው መግለጫ፣ በሀገራችን ፖለቲካ ያገባናል ከሚሉ ሁሉም ኃይሎች ጋር በመተባበር የመንግሥት ሥልጣን የሚያዝበትን ዲሞክራሲያዊ የሆነ የፖለቲካ ሥልጣን አያያዝ ሂደት ማስጀመር። ቀድሞውንም ሥልጣን ካልተያዘ፣ ይሄንን ማድረግ አይቻልም። እነዚህ የተባሉት ኃይሎች ሥልጣን ተጋርተው ካልያዙ እንደምን ባለ ተዓምር ነው የሥልጣን አያያዝ ሂደቱን የሚጀምሩት? ሥልጣን ሸሽተን ሥልጣንንም ሽተን አንዘልቀውም። የምንታገለው ከተመረጥንና ህዝብ ከወደደን ሥልጣን ለመያዝ መሆኑ መሰመር አለበት። ያለበለዚያ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነው። ሌላው ሐተታ ሁሉ ማጣፈጫ ወይም ማዳበሪያ ነው። ከሥልጣን አንጻር የግንቦት ሰባትን ሽሽት አልወደድኩትም።

 

ከታሪክና ካካባቢ ተጽዕኖ አፈትልኮ መውጣት አዳጋች ነው። ይሁን እንጂ፣ የምንፈልገው የፖለቲካ ፓርቲ ከሌሎች ይሄን ያህል ካደከሙንና አየሩን ሁሉ ከሞሉት ድርጅቶች በተወሰነም መልኩ ቢሆን የተለየ ነገር ሊያቀርብልን እንጠብቃለን። ይሄ አዲስ ነገር በዚህ ስለሥልጣን ባላቸው ሃሳብ ብቻ ይመዘናል ማለቴ አይደለም። ግን ከሥልጣን ጋር በተያያዘ የሚደረግ ድብብቆሽ መወገድ አለበት። የሥልጣን አያያዝንም ለመቀየር ሥልጣን መያዝ ያስፈልጋል። የግንቦት ሰባት ግብ ከዚህ አንጻር ግልጽ አይደለም ወይንም ያ የኢትዮጵያ ድብብቆሽ ሽታ አለበት።

 

የህዝብ ተሳተፎ መፍጠር፣ ነፃ ፍርድ ቤት ማቋቋም፣ ነፃ ምርጫ ቦርድ ማዋቀር፣ … እነዚህ ሁሉ ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ያስፈልጋል። ኢህአዴግ እነዚህን ሁሉ የነሳን ሥልጣን ስለያዘ ነው። ሥልጣንም ይሁን የሥልጣን አያያዝ መንገድ፣ በሥልጣን ነው የሚቀየረው እንጂ፤ በጸሎት አይደለም። ስለ ሥልጣን አያያዝ ሂደትና የህዝብን የሥልጣን ባለቤት ስለማድረግ የተገለጸው በሙሉ መልካም ሆኖ ሳለ፤ “ዓላማችን ሥልጣን ለመያዝ ሳይሆን” የሚለው ኃይለቃል፣ ያ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህል ውስጥ የተሰነቀረን አጉል በሽታ ያሳያል።

 

ለሥልጣን እየታገልን፤ የምንታገለው ለሥልጣን አይደለም የሚባል ነገር የለም። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ትግላችን ለሥልጣን ነው። ያ ደግሞ የማንም መብት ነው። እንኳንስ ግንቦት ሰባትን ያበረከቱልንና የበኩላቸውን የተወጡና እየተወጡ ያሉ ልጆች። አንዳንዶቹ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶች የሚመነጩት ከዚህ ስለሥልጣን ካለን አስተሳሰብ ከመሆኑም ባሻገር፣ የሥልጣን ሽኩቻዎቹ ድብቅ ከመሆናቸው የተነሳ፤ ያ ሥልጣንን እንደነውር የማየት ባህል ይቆም ዘንድ ሥልጣን በይፋ መነሳት አለበት።

 

ስለስልት፣ ዘርፈ-ብዙ ችግርና ሁሉን አቀፍ ስልት

ከሌለው ነገር የሚጀምር ጉዞ አይመቸኝም። ጥሩም አይደለም። ግንቦት ሰባት እና “ትግላችን ቀኖናዊ በሆነ መንገድ የሚከተለው የትግል ስልት የለውም” ይላል ስለንቅናቄው የትግል ስልትና መርኆች የሚያትተው መርኀ ግብር ክፍል። ግን ደግሞ “ንቅናቄያችን የሚከተለው የትግል መስመር ሁሉን-አቀፍ ነው” ይላል የንቅናቄውን መመስረት የሚያበስረው ባለ ሁለት ገጹ መግለጫ። ቤተክህነት ነው ያደግኩት። ግን “ቀኖናዊ በሆነ መንገድ” ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም። የፖለቲካ ፓርቲ መርኀ ግብር በተቻለ መጠን ግልጽና ከግልጹ ነገር የሚጀምር ቢሆን መልካም ነው። ይሄንን ግልጽ ያልሆነና ድርጅቱ ካለው ሳይሆን ከሌለው ነገር የሚጀምር ዓረፍተ ነገር ፊት ለፊት መቀርቀር አሉታዊ ተጽዕኖ አለው።

 

ሰዎች ዘለው ከሚያዩትና ከሚጠብቁት ነገር ለዚያውም የለንም ብሎ መጀመር በራሱ መልካም አይደለም። ጎበዝ ብዙ ያለን ነገር አለና ካለን ነገር እንጀምር። ቀኖናዊ የትግል ስልት ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም። ማብራሪያ ይፈልጋል።

 

የሀገራችንን ተጨባጭና የተለየ ሁኔታ ከግምት የሚያስገባ ሁለገብ የሆነ የትግል ስልት ቀኖናዊ የትግል ስልት አይደለም ማለት ነው? ትግልን ቀኖናዊ የሆነ ያልሆነ ብሎ የመደበ ማነው? ሠላማዊ እና የትጥቅ ትግል እንደማለት ነው፣ ቀኖናዊ? ይሄ ከኛ ጋር መሆናችሁን አሳውቁ ያለበለዚያም ከጠላት ጋር ናችሁ አይነት ሁለትዮሽ ክፍፍል ለቡሽም ያልበጀ አካሄድ ነውና፣ እሱን መቀበል የለብንም። ቢሊዮኖችን የያዘች ዓለምን በሁለት ብቻ ስልት ከፋፍሎ ማስቀመጥ አግባብ አይደለም።

 

አያሌ ስልት እንዳንከተል የሚያግደን ማነው? ዘርፈ ብዙ የትግል ስልትን የትግል ስልት አይደለም ብሎ የበየነ ጠቢብ ማነው? አንደኛ ነገር፣ ግንቦት ሰባት ስልት አለው። ሁለተኛ ነገር፣ ስልት የሌለው ድርጅት ድርጅት አይደለም። በእውኑ ብድግ ብለን ለውጥ አመጣለሁ ብሎ የሚዳክረውን ባራክ ኦባማን ቀኖናዊ ስልት የለህም ልንለው ይቻለናልን? ያን የማለት ያህል ነው።

 

ከድርጅቶች ጋር አብሮ ስለመስራት፣ እና ሌሎችም

አንደኛ ከዚህ አንጻር የግንቦት 7 ዓላማ ተራማጅ ነው። ምን አይነት ኢትዮጵያ የሚለው ካልሆነ በስተቀር፣ በኢትዮጵያ ኢትዮጵያነት ላይ መደራደር የለብንም። መቼም የኢትዮጵያ ጉዳይ የአንድነት ኃይሎች ጉዳይ ብቻ አይደለም። የተገንጣዮችም ጭምር ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ኃይሎችም መሆኑን ከዚህ ቀደም ጽፌያለሁ። እኛ ባንፈልግም እነ ግብጽ፣ እናሜሪካ፣ ዐረቦቹም መምጣታቸው አይቀርም።

 

ለውይይት ዕድል እስከሰጡና፣ አንዳችን የአንዳችንን ዕጣ ፈንታ የምንወስን መሆኑን እስካመኑ ድረስ ከሁሉም ጉዳይ አለን ከሚሉና ጉዳያቸውን ምክንያታዊና አሳማኝ በሆነ መንገድ ከሚያሳዩ ኃይሎች ጋር መሥራት የግድ ነው። ይሁን እንጂ ይኸው ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ እንኳን እስከ ቅንጅት ድረስ የተፈጠሩ ሕብረቶች፣ ግንባሮች፣ ትብብሮች፣ … እየተፈረካከሱ ምን ያህል አንጀታችንን እንዳደበኑት፣ ተስፋችንን እንዳመከኑትና ሌላ ሕብረት እንኩዋን መፍጠር እስከማይቻልና ነገ አይገናኙም እስክንል ድረስ እየተጣሉ ኖረናል። ተመልክተናል። ስለዚህ በተቻለ መጠን በመርኅ ደረጃ ከሌሎች ጋር መሥራት ቢታመንበትምና የግድ ቢሆንም፣ እንደዚያ ያለ ሰፊ ቃል ኪዳን ውስጥ ለመግባት ግን አለመጣደፍ ነው።

 

በተቻለ መጠንም ዋንኛው የተቃዋሚዎች ቃል ኪዳን መሆን ያለበት፣ አሁን ሥልጣን ላይ ባለው ኃይል ኢ-ዲሞክራሲያዊነትና አጥፊነት ከተማመኑ ባሻገር ማናቸውም ድርጅቶች ያንን ስርዓት በመዋጋቱ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ነው። ይሄ “ሀ” በ”ለ” ላይ፣ “ለ” ደግሞ በ”መ” ላይ፣ “መ” ደግሞ በ”ሰ” ላይ የሚወረውሩት ነገር ይቅር ማለቴ ነው። በዚህ ሰዓት ዋነኛው የስምምነት ነጥብ፣ ዐብዩ የትብብር ጉዳይ መሆን ያለበት ሁሉም የራሱን ሥራ እንዲሠራና አንዱ ሌላውን የሚጠልፍበትን ነገር እንዲያበቃ፣ አንዱ ሌላውን በምንም መልኩ እንዳያጠቃ ነው። ሌላው ትብብር እንኩዋን ቀስ ብሎ እያደር ይምጣ።

 

ሁለተኛ በኢትዮጵያ ውስጥ የአንድነት ጉዳይ ሲነሳ የሚያስደነግጣቸው፣ የሚያንቀጠቅጣቸው ኃይሎች ብዙ ናቸው። አንድነት ሲባል በነሱ አጠራር “የድሮው አማራና አማርኛ” የነገሠበት አንድነት ተመልሶ መጥቶ የሚያንቃቸው፣ የሚጫንባቸው፤ ምናልባትም እንደነሱ አስተያየት በተወሰነ መልኩ እኔም እጋራዋለሁ፣ ኢህአዴግ የሰጣቸውን በቋንቋ የመጠቀምና ዲሞክራሲያዊ ባይሆንም በራሳቸው ሰዎች የመተዳደር መብት የሚነጥቃቸው የሚመስላቸው ብዙ ኃይሎች አሉ። ከዚህ አንጻር ግንቦት ሰባት አንድነት የሚለውን ቃል በሚጠቀምበት ቦታ ሁሉ ጥንቃቄን ሊያሳይ ይገባል። በሌላ አነጋገር ኢህአዴግ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው ወይም መጥፎ መንግሥት ነው ማለት፤ ኢህአዴግን የሚወዱትና የሚደግፉት፣ በኢህአዴግ ሕይወታቸው በመልካም የተለወጠ ሰዎችና ቡድኖች የሉም ማለት አይደለም። አንዳንድ ግዜ በራሳችን ተቃውሞ ብቻ መታወር የለብንም። ኢህአዴግን ከልባቸው የሚደግፉ፣ ስህተቶች ቢኖሩበትም፣ እነኝህ የኢህአዴግ ስህተቶች ከሌላ እሱን ሊተካ ከሚጥር ኃይል ግን ገዝፈው የማያስፈሩዋቸው ብዙ ቡድኖች አሉ። ይሄ የአንድነት ጉዳይ እንዳይጨፈልቃቸው ሰግተው ከኢህአዴግ ጉያ ስር የሚጠለሉ ኃይሎችን፣ ኢህአዴግ እንደ ማስፈራሪያ መሣሪያ እንዳይጠቀምባቸውና ለዚያም ዱላ ማቀበል እንዳይሆን ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባል።

 

ስለንቅናቄው የእርቅና የመቻቻል እሴቶች የሚናገረው ክፍል ላይ ለምሳሌ ንቅናቄው “ብንወድቅም ብንነሳም በአንድነት ብቻ እንደሆነ” ያምናል የሚለው ዓረፍተ ነገር ለኔ ቢጤ የአንድነት ኃይሎች ያስደስት ይሆናል። ይሄ አንድነት ማለት እነሱንና የነሱ የሆነውን ለመዋጥ እንደመጣ ፖለቲካዊ ዘንዶ አድርገው ለሚያስቡ ኃይሎች ግን ያስፈራል። ከዚያ አይነት አስፈሪና ጠንካራ ዓረፍተ ነገሮች መታቀብ መልካም ነው። በሌላ አነጋገር፣ ኢህአዴግ ጥቂትም ቢሆን የሰጣቸው ነገር ካለ፣ ያንን የሚነጥቅ አካሄድ እንዳየቀየስ ጥንቃቄ መውሰድ ተገቢ ነው። በዚያ በሰጣቸው ላይ ነው መካብ ያለበት። ለምሳሌ፣ የኦሮሞ ክልል ገብቼ ከዚህ በኋላ አማርኛን የመማሪያ ቋንቋ አደርጋለሁ ብሎ ነገር የማይታሰብ ነው። የዚያ አካባቢ ህዝብ ይቀየርልን ካላለ በስተቀር። በዚህ ረገድ የሥራ ቋንቋቸው እንግሊዘኛ የሆነው የካናዳ ክልሎችና ፈረንሣይኛ የሚነገርባት ክቤክ ፖለቲካዊ ሕልውና ጥሩ ምሳሌ ነው።

 

እንደ መደምደሚያ፤ መደምደሚያ ካለው

“ግንቦት ሰባትን ከቶም አንረሳውም” ይላል የመግለጫው የመጨረሻ ዓረፍተ ነገር። ሰው አንድም የመከራውን ዕለት ሌላም መልካም ነገር ያገኘበትንና የድሉን ቀን አይረሳም። ግንቦት ሰባትን ካለመርሳት መርሳቱ ይከብዳል። እንደምን ግንቦት ሰባትን እንረሳለን። እኛም አንረሳውም ኢህአዴግም አይረሳውም። ይሄ የግንቦት ሰባት አባዜም ይመስለኛል ሌላ ግንቦት ሰባት ሊያመጣ የሚሽት ድርጅት የወለደው። ዓላማው፣ አቀራረቡ፣ ስብጥሩ፣ ታይሚንጉም መልካም ነው። ጉዞው ግን አቀበት ነው። አባላትን መመልመሉ፣ አባላትን ማሰለፉ፣ ህዝቡን ማንቃቱ፣ ከምንም በላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ባለበት መድረሱ፣ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ከጎን ማሰለፉ፣ ሌሎች ድርጅቶችን ማስተባበር ባይቻል፤ እንዳይናደፉ፣ እንዳይተናኮሉና እንዳይደነግጡ ኒውትራላይዝ ማድረጉ ቀላል አይደለም። ኢህአዴግ ብቻ አይደለም የዚህን ድርጅት መወለድ በጥርጣሬና በክፉ ዓይን ሊመለከተው የሚችል። ሌሎች በግልም በቡድንም የተነካካችኋቸው ድርጅቶችም ጭምር እንጂ። ስለዚህ ለሁሉም በየፈርጃቸው መሰናዳቱ ይታሰብበት።

 

በምንም መልኩ ግን ከኢትዮጵያ እየራቅን በሄድን ቁጥር ያ ቻይናዊ እስረኛ እንዳለው፣ ፖለቲካዊ ሚናችን እየኮሰመነ፣ እየቀጨጨ፣ እየሳሳ ይሄዳል። ፖለቲካ በትርጓሜ ስለአካባቢና በአካባቢ ስለሚኖሩ ህዝቦች ነው። በኢትዮጵያ ጉዳይ ፖለቲካ ማለት ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ነው። ከኢትዮጵያ ከራቅን አከተመ ባንልም ፖለቲካችን እየመነመነ፣ ከተጨባጩ ነገር እየራቀ ይሄዳል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ባይሆንልን፤ ኤርትራም ቢሆን መሞከር ነው። በፖለቲካ ውስጥ ደግሞ ሁሉም ነገር ይለዋወጣል። በነበሩበት የሚቀጥሉ አንዳችም ነገሮች የሉም። ግንቦት ሰባት ብዙ ነገሮችን ከለዋወጠና የግንቦት ሰባት ለውጥ ተጽዕኖ በኢትዮጵያ ብቻ ካልተወሰነ፤ የኤርትራ ጉዳይ በሰፊውና በትልቁ ቢፈተሽ መልካም ነው። ማለቴ ከኢትዮጵያ ውጪ ስለኢትዮጵያ የሚደረጉ ትግሎች፣ ኤርትራን ማሰብ አለባቸው። አውቃለሁ አይዋጥልንም። ኤርትራንም ከኢትዮጵያም ወጥተን፣ ከኤርትራም ሸሽተን፣ ከአሜሪካ አውሮፓ አይሆንልንም። ኢህአዴግን መደብደብ ካለብን ሲሆን ሲሆን ከዚያው ከኢትዮጵያ ነበር። ከኢትዮጵያ ካልሆነ ግን ከዚያው ከጎረቤት አገር ነው። ግንቦት የዚህ የኤርትራን ነገር ደፍሮ ሊገባበት ይገባል። ከኤርትራ ጋር እንተባበር ማለቴ ነው።

 

አባኪያ ነኝ። አባኪያ

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!