ያቺን የማትረሳ ቆንጆ ልጅ የተዋወቅሁዋት አስመራ ላይ ሲሆን፣ ከካቴድሪያል ወደ ቲራቮሎ በሚጓዘው ታክሲ ላይ ተሳፍሬ ነበር። ልጅቱ ፒኮክ የተባለችውን ወፍ ነበር የምትመስለው። ታክሲው ላይ ከሁዋላ አብረን ነበር የተቀመጥነው። “ላናግራት ወይስ ይቅርብኝ?” እያልኩ ሁለት ልብ ሆኜ እያመነታሁ ቆየሁ። እኔ ደጋግሜ ባያትም፣ እሷ አንድ ጊዜ እንኳ ዘወር ብላ አላየችኝም። ከሞባይል ቴሌፎኗ ጋር ተመስጣ እየተጫወተች ነበር።

(መቸም እንዲህ ያለ ነገር የገጠመኝ ደብረዘይት ላይ ቢሆን ለኔ ቀላል ነበር፣

“ጭሷ! ሞባይልሽ ጭስ ናት!” ብዬ እጀምር ነበር።

ወይም ደግሞ፣ “ነፍሷ! ሞባይልሽ ነፍስ አላት!” በተባለ።

“አመስግናለሁ” ካለች ደግሞ፣

“አንቺም እንደ ሞባይልሽ ጭስ ነሽ! የልቤን ልንገርሽ? አንቺ ማለት የ2008 ኖኪያ ማለት ነሽ” በሚል አድናቆትና ቀልድ በመንደርደር ወደ ቁምነገሩ መግባት በተቻለ።

በርግጥ የደብረዘይት የለከፋ መንገድ ይሄ ብቻ ነው ማለት አይቻልም።

“ስሚ አንቺ ብጣሻም! ባለካሜራውን ሞባይል ብትይዢ ብርቅ መሰለሽ?” ብሎ ማብሰሉን የሚጀምርም ይኖራል።

አሁን እንኳ ባለካሜራው ብርቅ አይደለም። አንድ ሰሞን ግን ሪፖርተር ጋዜጣ፣ “ባለካሜራው ሞባይል ስልክ ከአንድ ግለሰብ ላይ ተሰረቀ” ብሎ ዘግቧል። እንግዲህ በእነ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ዘመን፣ “ፍቅረኛዬ ሰአት ያሰረች ናት” ተብሎ እንደሚፎከረው ማለት ነው – አምላክ ነፍሱን በገነት አፀድ ውስጥ ያሳርፋት!…)

እዚህ አገር ግን እንግዳ እንደመሆኔ ኤርትራውያን ሴቶችን እንዴት ማነጋገር እንደሚገባ አላውቅም ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ ትግርኛ ይቸግረኛል። በዚያን ጊዜ ጥቂት ትግርኛ ስናገር ወደ ተራራ እንደሮጠ ሰው ከላይ እስከ ታች ድካም ይሰማኝ ነበር። አሁን እንኳ አቀላጥፌ ከመናገር ባሻገር፣ መፃፍና፣ ማንበብም ጀምሬያለሁ።

የሆነው ሆኖ ከዚህች ጠጉሯን እንደ ጉድ ከለቀቀች ፒኮክ ጋር በምን ዘዴ መነጋገር እንዳለብኝ እያሰላሰልኩ ሳለ፣ ሞባይል ስልኳ መጥራት ጀመረ። የስልኳ የጥሪ ድምፅ የቴዲ አፍሮ፣ “ዳህላክ ላይ ልስራ ቤቴን” የሚለው ነበር።

ፒኮክ ለስልኩ ጥሪ ምላሽ ስትሰጥ ዘፈኑ ተቋረጠ፣

“እየመጣሁ ነው። ሲኒማ ሮማ ደርሻለሁ” ስትል ምላሽ ሰጠች።

አሁን የወሬ ርእስ አገኘሁ፣

“አምቼ ነሽ እንዴ?” ስል በትግርኛ ጠየቅሁዋት።

“አይደለሁም” አለችና የሞቀ ሳቅ ሳቀች።

አቀማመጤን አስተካከልኩና ጨዋታዬን ቀጠልኩ፣

“ስልክሽ ላይ የዘፈነውን ድምፃዊ ታውቂዋለሽ?”

ሳቀች። ስትስቅ እንደጉድ ታምራለች። ወይ መከራ!

በጥያቄዬ የተገረመች መስላ፣

“ቴዲን የማያውቅ ማን አለ?” አለች።

በዚያን ጊዜ ቴዲ እስር ቤት ስለነበር ይህንኑ ጠየቅሁዋት፣

“መታሰሩን ሰምተሻል?”

“እውይ! አዎ ሰምቻለሁ። ምናድርጎ ነው ግን ያሰሩት?”

“ለምን እንዳሰሩት አልሰማሽም?”

“ዕንዲዒ! አሰሩት ሲሉ ብቻ ሰማሁ”

“አማርኛ ትሰሚያለሽ?” ስል ጠየቅሁዋት።

“አልሰማም። ብሰማ ደስ ይለኝ ነበር። የቴዲ ዘፈን ምን እንደሚል እሰማው ነበር…”

“የዘፈኑን ትርጉም አታውቂውም ማለት ነዋ!?”

“አውቀዋለሁ!” አለች በእርግጠኛነት፣ “….የአክስቴ ልጅ አምቼ ናት። ትርጉሙን ነግራኛለች”

“ምን ብላ ነገረችሽ?”

ፒኮክ በተፈጥሮ ሊፒስቲክ የተቀቡ ከንፈሮቿን ላሰቻቸውና ለወግ ራሷን አመቻቸች። ከማውራቷ በፊት ግን እንደገና በረጅሙ ሳቀች። እና እንዲህ አለች፣

“…የቴዲ ፍቅረኛ ኤርትራዊት ነበረች ምሽ? ከዚያ ወያኔ ከአገር አባረራት ምሽ? ሃርማዛት ተባዒሶም ይብል ድማ! ከዚያም ቴዲ ‘ከፍቅረኛዬ ተለይቼ ከምቀር ዳህላክ ላይ ቤት ሰርቼ አብረን እንኖራለን’ ብሎ ዘፈነላት። ቴዲ የፍቅር ሰው ነው አይደለም? ልክ ነኝ ምሽ?”

“ልክ ነሽ” እንድላት ጓጉታ በሚለማመጡ አይኖቿ እያየችኝ ሳቀች።

አህ! ታክሲው እኔ ከምወርድበት ቦታ ደርሶ ቆመ። እኔ ወረድኩ። ፒኮክ ወደ ቲራቮሎ መንገዷን ቀጠለች። ከታክሲ ከወረድኩ በሁዋላ፣ እዚያው እወረድኩበት ቦታ ዝም ብዬ ቆምኩ። ታክሲው መንገዱን ሲቀጥል፣ ፒኮክ በታክሲው የጀርባ መስታወት በኩል አንገቷን ጠምዝዛ ስታየኝ አየሁዋት። “ቻዎ!” ለማለት እጄን ብድግ አደረግሁ። ፈገግ ሳት አልቀረችም….

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ