ተድላ ሀይሉ

ሰላም ውድ አንባብያን። ሠሞኑን አንድ ጽሑፍ በአቶ ተስፋዬ ገብረአብ ተደርሶ በኢንተርኔት በየድረ-ገፆቹ ተበትኗል። የዚህ ጽሑፍ ትክክለኝነት ወይም ተዓማኒነት ሣይጣራ ልክ እንደ ቆላ ሠደድ እሣት በብዙ የኢትዮጵያውያን ድረ -ገፆች ላይ ተበትኗል። ነገር ግን 'ታሪክም' ይሁን 'ድርሠት' ሆን ተብሎ የሚታወቅ ሃቅን ለማስካድ የሚጻፍ ከሆነ አንባብያንን ማሣሣት ብቻ ሣይሆን በትውልድ ውስጥ የማያስፈልግ ውዝግብን ይተክላል።

 

 

ለመሆኑ አቶ ተስፋዬ ገብረአብ ይህንን ዓይነት ድርሠት ለመጻፍ ያነሣሣው ምክንያት ምን ይሆን ? ወያኔን በሚያገለግልበት ዘመን' ነፍጠኛ አማራን ለማጥፋት' የተሠጠውን ተልዕኮ በሚገባ ፈፅሟል - ማኅበረሰቡ የፈቀደለትን ያህል የጥላቻ መርዙ ሠርቶለታል። ዛሬ ደግሞ የሻቢያ የፕሮፓጋንዳ ሠራተኛ ሆኖ ተጨፍጭፎ አላልቅለት ያለውን የ 'አማራ ሕዝብ' ዳግም ለማዋረድና ለማንጓጠጥ ከአቅሙ በላይ ታሪክ አዋቂ ሆኖ እየተንጠራራ ይገኛል። በጽሑፉ የሥም ማጥፋት ዒላማ ሆነው የቀረቡት ዳግማዊ አፄ ምኒልክና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ናቸው።

 

እስኪ የእርሱን ጽሑፍ ዋና ዋና ነጥቦችን እየመዘዝኩ ሥህተቶቹን ላመልክት። የጽሑፉ ርዕስ "የንጉሠ -ነገሥቱ እናት" ይላል። ንጉሠ -ነገሥቱ ልጅ እያሱ (እያሱ አባ -ጤና ) መሆናቸው ነው። በታሪክ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ልጅ እያሱ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ኑዛዜ መሠረት ሕጋዊ ወራሽ ነበሩ። ነገር ግን ሥርዓተ -ንግሥና ፈፅመው 'ንጉሠ -ነገሥት' የሚለውን ሹመት አልተቀቡም የመመሪያ ሥህተት። ታሪኩ የሚያጠነጥነው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሁለተኛ ልጅ (ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ) ትውልድ ላይ ነው። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሕጋዊ መንገድ ያገቧቸው ሚስቶች የሚከተሉት ናቸው፦

 

1 ...ወይዘሮ አልጣሽ ቴዎድሮስ (የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ልጅ) በ 1856 ዓ .ም. ተጋቡ። በተከታዩ ዓመት በ 1857 ዓ.ም የያኔው ሣህለማርያም (የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዓለማዊ ሥም) በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በእሥር ከተጋዙበት ከመቅደላ አምባ ጠፍተው ሲያመልጡ ባለቤታቸውን ወይዘሮ አልጣሽን ትተው ሄዱ።

 

2 ...ከመቅደላ አምባ አምልጠው ሸዋ እንደመጡ በዚያው ዓመት በ1857 ዓ.ም ወይዘሮ ባፈና ጌታቸውን (የመረሃ-ቤቴ ተወላጅና ባላባት) አገቡ። ወይዘሮ ባፈና በንጉሡ ላይ የፖለቲካ ሤራ ሲዶልቱ በመገኘታቸው ከ 7ዓመታት ጋብቻ በኋላ በ 1874 ዓ.ም ተፋቱ።

 

3 ...ሚያዝያ 21 ቀን 1875 ዓ.ም እቴጌ ጣይቱ ብጡልን (የስሜኑ ገዢ ራስ ብጡል ኃይለማርያም ልጅ) አግብተው እስከ ዕለተ - ሞታቸው ታኅሣሥ 3 ቀን 1906 ዓ .ም አብረው ኖሩ። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሕጋዊ ጋብቻ ካገቧቸው ሦሥት ሚስቶች መካከል ከወይዘሮ ባፈና ጌታቸው አንድ ልጅ ብቻ ወልደው ነበር። ያም ልጅ በጨቅላነቱ አርፏል። ከጋብቻ ውጭ የወለዷቸው ልጆ፦

 

1 ...በ 1859 ዓ.ም ወይዘሮ ሸዋረጋን ከወይዘሮ ደስታ ወለዱ።

 

2 ...በ 1865 ዓ.ም አቤቶ አስፋወሰንን (የወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ታናሽ ወንድም፡ የአንድ እናት ልጆች ናቸው) ወለዱ። አቤቶ አስፋወሰን በ14 ዓመታቸው በ 1879 ዓ.ም በሕመም ሞቱ።

 

3 …በ1868 ዓ.ም ንግሥተ-ነገሥታት ዘውዲቱን፤ ከወይዘሮ አበቺ ወለዱ። ለታሪኩ መንስዔ የሆኑት ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ፦

 

1 ...ከ1884 ዓ.ም. በፊት የራስ ጎበና ዳጨን ልጅ ደጃዝማጅ ወዳጆ ጎበናን አግብተው አቤቶ ወሰንሰገድ ወዳጆን ወልደዋል።

 

2 ...የወሎውን ገዢ ራስ ሚካኤልን በ 1884 ዓ.ም አግብተው ሁለት ልጆችን ወልደዋል፦ አቤቱ እያሱ ሚካኤልን በጥር 25 ቀን 1888 ዓ.ም እንዲህም ወይዘሮ ዘነበወርቅ ሚካኤልን። ተስፋዬ ገብረአብ እቴጌ ጣይቱ ከወይዘሮ ሸዋረጋ እናት ከወይዘሮ ደስታ ጋር የነበራቸውን ዕውቂያ እንዲህ አቅርቦታል፦

 

"ንጉሰ ነገስቱ ከዚያን ቀን ምሮ ከዚህች ውብ የወሎ ኮረዳ ጋር የፍቅር ግንኙነት ነበራቸው። በመካከሉ ደስላ ፀነሰች። ማርገዟም ይታወቅ ጀመር። ሆኖም ፍርሃት ይዟት ለንጉሱ ሳትናገር ቀረች። በቤተመንግስቱ ዙሪያ የደስላ ማርገዝ በሹክሹክታ ይወራ ጀመር። ከአጤ ምኒልክ ልጅ መውለድ የሚመኙ ሁሉ፣ ደስላ ከንጉሱ በማርገዟ በቅናት ጦፈዋል። እቴጌ ጣይቱ በወቅቱ ይህን ሁሉ ዝርዝር ቢያውቁም፣ አንዳች ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር አልነበራቸውም። ደስላ ማርገዟን ለንጉሱ ከመንገሯ በፊትም አጤ ምኒልክ ወደ ሰሜን ዘመቱ። ከዘመቻ ሲመለሱ ደስላ ቤመንግስት ውስጥ አልነበረችም።

 

…ርግጥ ነው፣ ደስላ ከቤተመንግስት ከተባረረች በሁዋላ አጤ ምኒልክን ፍለጋ ወደ ሰሜን ተጉዛ ነበር። በጉዞዋ ላይ ግን ወለደች። ህፃኗ የንጉሱ መሆኗን መናገር አደጋ ይኖረዋል ብላ ሰጋች። የጣይቱ ሰዎች ይህን ከሰሙ ከነልጇ እንዳያስገድሏት መፍራቷ አልቀረም። ስለሆነም፣ ለራሷም ሆነ ለልጇ ህይወት ስትል ንጉሱን በአካል እስክታገኝ ምስጢሯን በሆዷ መያዝ መረጠች። የምትጠጋበት ወገን ስላልነበራትም እን ራ ጋጋሪ ሆና ማገልገል እጣ ክፍሏ ለመሆን በቃ። እንዳለመችው ግን አልሆነም። ታመመችና ህይወቷ አለፈ። "

 

ይህንን አገላለፅ ስናነብ የሚከተለውን ጥያቄ ለመጠየቅ እንገደዳለን፦ ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ የተወለዱበትን ዘመን (1859 ዓ.ም) እና እቴጌ ጣይቱ ብጡል ከጎንደር ወደ ሸዋ መጥተው ዳግማዊ አፄ ምኒልክን ያገቡበትን ጊዜ (1875 ዓ.ም) የ 16 ዓመታት ልዩነት ስናነፃፅር 'እቴጌ ጣይቱ በሌሉበት እንዴት የ 7 ወራት ነፍሰጡር የነበሩትን የወይዘሮ ሸዋረጋን እናት ከቤተ -መንግሥት ሊያባርሩ ይችላሉ?' ደግሞም ስለ ወይዘሮ ሸዋረጋ በእቴጌ ጣይቱ የመገኘት ዜና ሲተነትን፦

 

"* * * እነሆ ! ሸዋረጋ እና ባልዋ ከሃረርጌ ወደ አዲስአበባ ጉዞ ጀመሩ። አንዲት መጠጊያ ያጣች ወላጅ አልባ ሴት ያገባ የመሰለው ወታደር ከንጉሰ ነገስቱ ሴት ልጅ ጋር ጋብቻ መፈፀሙን ማመን ቸግሮታል። ህይወት እድል ናት። እድል እያዋከበ ወስዶ የንጉስ ልጅ ባል አድርጎታል። በዚህ ምክንያትም ከንግዲህ ህይወቱ ይለወጣል። በርግጥም ሹመት እንደሚያገኝ አምኖአል። የልእልት ባል እንደመሆኑ ተራ ሰው ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። ቢያንስ ደጃዝማችነት ማግኘት እንደሚገባው ሳያሰላስል አልቀረም። የንስሃ አባቱ የመከሩትና የነገሩትም ይህንኑ ነው፣

 

“እድለኛ ነህ። ከንግዲህ ኑሮህ ይለወጣል። ሚስትህን ወደ ንጉሱ ውሰዳት። የእሳቸው ልጅ ነች…” ባላገሩ ወታደር ይህንኑ ጣፋጭ ህልም እያኘከ፣ ሸዋረጋ ምኒልክን ይዞ ከመናገሻዋ ከተማ አዲስአበባ ገባ። * * * እቴጌ ጣይቱ በጥሞና ካዳመጡ በሁዋላ፣ “አስገቧቸው” ሲሉ አሽከራቸውን አዘዙ። የተጎሳቀሉ ባልና ሚስት ባላገሮች ከንግስቲቱ እልፍኝ ገብተው ለጥ ብለው እጅ ነሱ። እቴጌ ጣይቱ ልጅቱን አተኩረው መረመሯት። የእናቷን ቁንጅና ይዛ መወለዷን ሳያስተውሉ አልቀሩም። ፈገግ ስትል ፀሃይ ብልጭ ያለ ይመስላል። አይኖቿ የአባቷን እንደሚመስሉም ታዝበዋል። እናቷ ከቤተመንግስቱ ስትባረር ይህች ልጅ የ 7 ወር ፅንስ እንደነበረች ያስታውሳሉ። የተፈፀመውን ዝርዝር ነገር ሁሉ ያስታውሳሉ። አሁን ግን ፀፀት ቢጤ ልባቸውን ጫር ሳያደርገው አልቀረም። ...በዚያው ሰሞን አጤ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ እንደተለመደው እያወጉ ሳለ፣ “ያቺ ይወዷት የነበረች ገረድ ትዝ ትሎታለች ?” ሲሉ ይጠይቃሉ። “የትኛዋ ?” “ወደ ሰሜን በዘመቱ ጊዜ እዚህ ትተዋት የሄዱት። ከዘመቻ ሲመለሱ እንኳ ‘የት ሄደች?’ ብለው ጠይቀው ነበር። ልናገኛት ስላልቻልን ግን ልናመጣልዎ አልቻልንም”"

 

የመ መሪያው ሥህተት እንዳለ ሆኖ ይህ ደግሞ ሌላ ሥህተት ተጨምሮበታል። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እቴጌ ጣይቱን ካገቡ በኋላ ብቻቸውን ወደሰሜን ኢትዮጵያ ዘመቻ አላደረጉም። ታዲያ በምን ሥሌት እቴጌ ጣይቱ 'እርስዎ ወደ ሰሜን በዘመቱ ጊዜ ...' ብለው ለንጉሡ ሊነግሩ ይችላሉ ? ከዚህ ሌላ ትልቅ የታሪክ መፋለስ (ሆን ተብሎም ሊሆን ይችላል ) ያዘለው ጉዳይ የወይዘሮ ሸዋረገድ ወላጅ እናት ወይዘሮ ደስታ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሁለት ልጆችን በ 6 ዓመታት ልዩነት ወልደዋል (በመ መሪያ በ1859 ዓ.ም ወይዘሮ ሸዋረጋን ከዚያም በ1865 ዓ.ም አቤቶ አስፋወሰንን)። በአቶ ተስፋዬ ገብረአብ አገላለጽ ወይዘሮ ደስታ (ደስላ ) የሞቱት ወሎ ውስጥ ወይዘሮ ሸዋረጋ የ 7 ዓመት ልጅ ሣሉ ነው።

 

ይህ ማለት የሁለተኛው ልጃቸው የአቤቶ አስፋወሰንን እናት አይደሉም ማለት ይሆናል። ነገር ግን የወይዘሮ ሸዋረጋና የአቤቶ አስፋወሰን እናት ወይዘሮ ደስታ (ደስላ) መሆናቸው በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። ከዚህ የባሠው ጉድ ደግሞ እኒህ ሁለት ልጆች ሲወለዱ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ዳግማዊ አፄ ምኒልክን አላገቡም። ታዲያ ለዚህ ሁሉ የቤተመንግሥት ሤራ እርሣቸው በሌሉበት ተጠያቂ የሚሆኑት እንዴት ነው? ከሁሉም የሚገርመው የወይዘሮ ደስታ (ደስላ) ልጅ ወይዘሮ ሸዋረጋ ስሟ "ሸዋረጋ " መሆኑን ስሟን ያወጡላትን አባቷን ገና በአካል ሣታገኛቸው ታውቅ ነበር?

 

"አንድ ቀን ከባልዋ ጋር ሲጨዋወቱ፣ “ሸዋ! ምንድነው ይሄ አንገትሽ ላይ ያለው ድግምት?” ሲል እንደ ዋዛ ይጠይቃታል። “ምንም” ትላለች። “አለምክንያትማ አላንጠለጠልሽውም?” መልስ ሳትሰጥ ዝም ትላለች፣ ባሏ ጠረጠረ። መስተፋቅር ሊሆን ይችላል ብሎ ስለገመተ ወደ ንስሃ አባቱ ሄዶ ሚስቱ አንገት ላይ ስለታሰረው ድግምት ይናዘዛል። ቄሱ ሚስትየውን ለማነጋገር ይፈቅዱና ባልየው በሌለበት እለት ወደቤት በመምጣት ሸዋረጋን ያነጋግሯት መር። “እንዲያው ይሄ አንገትሽ ላይ ያሰርሽው ምን ይሆን ?” ሸዋረጋ በልቧ የያዘችው ምስጢር ቢሆንባትም፣ ቄስ ጠይቆ መልስ መስጠት ግዴታ ነውና እናቷ ከመሞቷ በፊት የነገረቻትም ምስጢር ተነፈሰች፣ "

 

ተስፋዬ ገብረአብ ጥንትም ዛሬም ሆነ ለወደፊት ሌላም ሌላም የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያጠፋ የሃሰት ታሪክ ይጽፋል። ነገር ግን እንደ እርሱ ያሉ ፀረ -ኢትዮጵያ የሆኑ ሃሰተኞች የሚለቀልቁትን ሁሉ እንዳለ በየድረ -ገፁ ከመለጠፍ በፊት ግራ -ቀኙን እያጣሩ ቢሆን ይመረጣል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!