ተሻለ መንግሥቱ

የክርስትና እምነት ተከታይ የሆናችሁ የድረ ገጽ ታዳሚዎች እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ። ለጊዜው መድረሳችሁ ብቻ ይበቃል - አደረሳችሁ ላይ ለወትሮው ይገባ የነበረው ‹በሰላም› የሚለው ቅጥያ ለአሁኑ ይቅር። እየተዋወቅን ለደንብ ሙሌት ብቻ በቃላት አንጫወትም፤ እነሱም ይታዘባሉ።

 


ኮምፒውተሬ አልከፍትልኝ አለኝ እንጂ ትናንት ማታ ኢንተርኔት ስዳብስ ርዕሱን ብቻ ያየሁት የዶክተር ኃይሉ አርአያ ጽሑፍ በጣም ማርኮኛል። ሌላ ቦታም ቢሆን ከፍቼ አነበዋለሁ። ለአሁኑ ግን እኔም እርሳቸው ባነሱት ጉዳይ ዙሪያ ለመጻፍ በቋፍ ላይ ስለነበርኩ ወደዚያው ላምራ። በነገራችን ላይ ታዲያ ‹ካላነበብከው እንዴት አወቅኸው?› ለምትሉኝ ርዕሱ በሀተታው ላይ የሚስተናገደውን ዝርዝር ሃሳብ ጠቋሚ በመሆኑ ነው ለማለት እፈልጋለሁ። እንጂ እንደቢትወደድ መሀመድ ሁሴን አላሙዲን ያላነበበውን የበረከት ስምዖንን መጽሐፍ በምረቃው ዕለት ‹ለትውልድ ቅርስ የሚሆን፣ ብዙ የተለፋበት፣ ሃቅን ብቻ የተመረኮዘና እውነትን የተንተራሰ፣ ከግልብ ጭንቅላት ማንንም ለማስደሰት ወይ ለማስከፋት ያልወጣ ግሩም መጽሐፍ ጽፏል› ብሎ - በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ እንዳለ ተቆጥሮ - በራሱም በጸሐፊውም በግዑዙ መጽሐፍም ላይ እንዳላገጠው ዓይነት እኔም በድጋሚ ታሪክ ለመሥራት አስቤ እንዳልሆነ መግለጽ እወዳለሁ።


እውነት ነው - ዶክተር ኃይሉ እንዳሉት የመንግሥትም የልማድም የገበያም በጥቅሉ የሁሉም ባርያ ሆነናል። አለበለዚያማ በዚህ ሰሞኑን ባሳለፍነው የ2004ዓ.ም የፋሲካ በዓል የታዘብነውን የመሰለ ለሚያልፍ ቀን በቀላሉ የማያልፍ ሥጋዊና ኀሊናዊ ዕዳዎችን አናተርፍም ነበር። እጅግ በሚያሳዝን ሂደት ውስጥ እንደምንገኝ ታዝቤያለሁ። በዓሉን ተመርኩዞ የታየው የገበያ ግርግርና የዋጋ ግሽበት በሀገራችን ታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ እሚያውቅ አይመስለኝም። ሁኔታው በእጅጉ ያሳስባል፤ ያስደነግጣል፤ ያስፈራልም። አስተውሎ ለታዘበ የምፅዓት ቀን የመጣ ነው እሚመስል። ሁሉም ፈጣሪን ረስቶ ለሥጋው ብቻ ሲራወጥ ስትመለከቱ ‹በርግጥ ይሄ የመጨረሻ ዘመን የሚባለው ትንቢት ደርሶ ይሆን እንዴ?› ብላችሁ ከምር ልትጨነቁ ትችላላችሁ። ለአንዲት ቀን የቂጣ በዓል (የፋሲካ ነባር ትርጉም ነው) ሲባል ክርስቶስን - ዋናውን የበዓሉን ማዕከል - ዘንግቶ እንዲህ ለሆድ ብቻ አቅልን ስቶ መራወጥ እሚያሳየን አንድ ትልቅ ነገር ቢኖር ካህናቱም ሃይማኖት ዐዋቂዎችም መጻሕፍቱም በሕዝቡ ውስጥ የሠሩት ሃይማታዊ ሥራ እምብዝም እንደሆነ ነው። በሌላም በኩል ሃይማኖትና ባህል መነጣጠል በማይችሉበት ሁኔታ መዋሃዳቸውን እንረዳለን። አንዳንዱ ሰው ገንዘብ ያለው መሆኑን ለማሳየት ይመስላል ሁሉም ነገር አይቅረኝ ከሚል የሚያጋፍረው - ቅርጫውንም ዶሮውንም በግና ፍየሉንም። የሚገርመው ግን ገንዘቡ ከየት ይመጣል? በዜጎች ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ይህ ዓይነቱ ቅጥ ያጣ ልዩነት እንዴት ሊከሰት ቻለ? ምን እየሆንን ነው? ወዴትስ እያመራን ነው? ገንዘቡን የሚነኳኮት የማሽላ እንጀራ እያደረገ ያለ ማን ወይም ምንድን ነው? የማኀበረሰቡ አጠቃላይ ሕይወት ወደዚህ የተመሰቃቀለ ደረጃ እስኪወርድ መንግሥት ምን እያደረገ ነበር? በዚህ መመሰቃቀልስ መንግሥትም ሆነ ሌላ አካል እሚጠቀመው ምንድን ነው? ይህን ከመንግሥትም፣ ከቅን አሳቢና ጤናማ ኀሊና ካለው ሕጋዊ ነጋዴም፣ ምናልባትም ከእግዜሩም እጅ አፈትልኮ የወጣና ወደሰይጣን ግዛትም የተሸጎጠ እሚመስለውን ይህን የኢትዮጵያ ጉዳይ ከእንግዲህ ሊያስተካክል የሚቃጣና እሚሳካለትም ምን ዓይነት ሰብኣዊ ፍጡር ይሆን። ምንድነው የተዞረብን በውነቱ?


ከራሴው ልጀምር። ጥሩ ደመወዝ አለኝ። እርግጥ ነው የቃላት ትርጓሜም እየተቀየረ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅት የ‹ጥሩ ደመወዝ›ንም ፍቺ በቀላሉ መረዳት ይከብዳል። በወር መቶ ብር ጥሩ ደመወዝ የነበረ መሆኑን የሚረዳና በዚያም ጥሩ ደመወዝ ቤተሰብን በሚገባ እያስተዳደረ ተርፎ በሚጠራቀም ገንዘብ አሁን በሚሊዮኖች ሊሸጥ የሚችል ማለፊያ መኖሪያ ቤት መሥራት እንደሚቻል ለሚያስታውስ ሰው የኔ የአሁኑ የብር አምስት ሺህ ደመወዝ ለቤት ኪራይና ከደረጃ በታች ለሆነ ወርሃዊ የምግብ ፍጆታ ብቻ እንደሚውል ሲገነዘብ በጥቂት አሠርት ዓመታት ውስጥ በሀገራችን ላይ የወረደው መቅሰፍትና የፈጣሪ ቁጣ ምን ያህል ከባድ ፈተና ውስጥ እንደከተተን ይገነዘባል። እንዴ - እርግማኑ የሚከሽፍበትን መንገድ በጋራ እናፈላልግ እንጂ ምንድነው ጉዱ ጎበዝ! ደግሜ ልጠይቅ - ወዴት እየሄድን ነው? እንደማኀበረሰብ ጭልጥ ብለን እንጥፋ? - ዥው ወዳለ ገደል ዐይናችን እያዬ እንግባ? ...


ዶሮ እንደማልገዛ ባለቤቴን በግድ አሳመንኩ። ለምን ብትሉ ዶሮዋ ከነኮተቷ በአነስተኛ ግምት 400 ብር ትገባለች፤ ጉልበቱ በነጻ ሂሳብ ተይዞላት የስንት ብር ነጭና ቀይ ሽንኩት - ቅቤ- ዘይት- በርበሬ - ቅመማ ቅመም - ማገዶ - አጃቢ ዕንቁላል እንደምትፈጅ አስሉት። ለመነሻነት ሥጋ ያለው ትልቅ ዶሮ ባማካይ ብር 180 ነበር ሲሸጥ የዋለው የቀዳም ሥዑር ዕለት። ለማስታወስ ያህል በእኔ ዕድሜ አንድ ዶሮ ከአሥራ አምስት ሣንቲም እስከ ስሙኒ ይገዛ ነበር፤ ዕንቁላል የብር ባማካይ አንድ መቶ። በዚህች ዕድሜየ ነገሮች ሁሉ እንዳልነበሩ ሆነው ተለዋውጠው በተረት ልኑር? በአንድሺህ ዓመትም ሊታይ በሚሰቀጥጥ ክፉ ለውጥ ኑሮው እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደህዋ ይምጠቅ? ገና እኮ ስድስት አሥሮችን እንኳን በቅጡ አልደፈንኩም! ምን ዓይነት ዘመን መጣብን? ፍቅርንም፣ መተዛዘንንም፣ መተሳሰብንም፣ ሃይማኖትንም፣ ወንድማማችነትንም፣ እህትማማችነትንም … ሁሉንም ገደል የከተተ ዘመን ይምጣብን? ኧረ እግዚኦ እንበል!


በግ ወይም ፍየል እንደማልገዛ ከፊትም ታውቃለችና አናስበውም። በቤቴ የባህል እሥረኛነት እንዲወገድ ብዙ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ - በትንሹ ሃያ አንደኛ ዓመቴ። ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ ሊሆን እንደማይገባው እንዳብዛኛው ሰው በቲየሪ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ማሳየት ስለምፈልግ ሳልወድ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ቤተሰቤን የ‹መጨቆን› ጠባይ ብዙውን ጊዜ ይታይብኛል። እናም አንድ ወዳጄ በግድ ያህል ባስመዘገበኝ ቅርጫ ብቻ ፀናሁ - ለያውም በይሉኝታ ተሸንፌ። ለግማሽ መደብ ብር 500 ከፈልኩ። ሥጋው መጣ። ስመዝነው ጨጓራና ለድመት የመጣው ሳምባ ሳይጨመሩ ነገር ግን ከነግድንግድ አጥንቶቹ 6 ኪሎ ሆነ። በኪሎ ሲተነተን አንድ ኪሎ በስንት መጣ ማለት ነው? 83.3333…ብር! በቅርጫ ለአንድ ኪሎ ይህን ያህል ከወጣ በሉካንዳ ቤት አስቡት። ታዲያ ይሄ መኖር ነው በቁም መሞት? ከናካቴው ቢቀርስ? ሣር ጎዝጉዞ፣ እጣን ጨስ አድርጎ፣ ቢወደድም የአሥር ብርም ብትሆን ሁለት ፍሬ ቡናን አፍልቶ፣ ከተገኘም በሽሮና በቅምጫና ጠላ በዓልን ቢያሳልፉት ምን ይላል? የምን የባህል እሥረኛ መሆን ነው? የተወረወረ ጦር እስኪያልፍ ጎንበስ ቢባል ምን ክፋት አለው? በእልህና በቁጪት በሚመስል አኳኋን ጥሪትን መከስከስ ምን ይባላል? ማንንስ ይጠቅማል? …


ብዙ ሰው ለዚህና ለመሰል ዓመታዊ ክብረ በዓላት ባለ በሌለው ሲሟሟት ይታያል። የዕድራችን ጡርንባ ነፊ - እውነቴን ነው እምላችሁ - አንዳች ያህል ዶሮ ገዝቶ ተሸክሞ ወደቤቱ ሲሄድ አይቸዋለሁ። ይህ ሰው ለእግሩ ጫማና ለሰውነቱ ከተጣጣፈ በውሀ እጦትም ከተማረረ አሮጌ ልባሽ በስቀር የለውም፤ ያጣ የነጣ ድሃ ነው፤ በደንብ ነው እምናውቀው። በበዓል ቀናት ብቻ ነው የማናውቀው። እናም ለዚያች ቀን ሀብታም ነው። የርሱና የኔ ቢጤ የባህል አሥረኞች እጅግ ብዙ ነን። እናም እላለሁ - ኢትዮጵያውን እንደቻይናዎቹ የባህል አብዮት ያስፈልገናል። ሀገር ልትለወጥ እምትችለው ማይምነት ሲጠፋና አመለካከትና አስተሳሰብ ሲለወጥ ነው። በቀድሞ በሬ እያረሱ የ21ውን መቶ ክፍለ ዘመን ሕይወት በአግባቡ መምራ አይቻልም፤ ዓለምም እየተለወጠች ናት። በዚያ ላይ የተጫነብን መንግሥታዊ ቀምበር ለዜጎቹ የሚያስብና የሚቆረቆር ሳይሆን ራሱም እንደመጋጃ በልተው እማይጠግቡ ዓሣማ ዜጎች የተሰገሰጉበት መዥገራዊ ተቋም ነው። እናም ለዜጎች መቆርቆዝና መደህየት የሚጠየቅ መንግሥታዊ ተቋም ስለሌለን እኛው ለኛው እየተሳሰብን ብንኖር ጥቂቱ እየተንደላቀቀ በቅንጦት አይቸገርም - ብዙኃኑም በኑሮ ውድነት እየተሰቃዬ የመከራ ሕይወት አይገፋም። በተለይም በሃይማኖት ስም ሃይማኖቱ ሳይገባን በከንቱ አምልኮተ እግዚኣብሔርን አናበላሽ። ተራረዱ ሳይሆን ተረዳዱ ተፋቀሩም ማለቱን እናስታውስ።


እርግጥ ነው ብዙው ሰው በድህነት ይንገላታ እንጂ በአንዳንድ ግልጽ ምክንያቶች ከበቂ በላይ ገንዘብ እሚያገኙ ወገኖች ኑሮውን እየሰቀሉት እንዳሉ መገንዘብ ይቻላል። እንደሚመስለኝ እነዚህን ዓይነቶቹ የዕውቀትና የማስተዋል ችግር እንጂ የገንዘብ ችግር የሌለባቸው በሆዳቸውና በኪሣቸው የሚያስቡ ሰዎች የድሃ ወገናቸውን የመግዛት አቅም እያጤኑ ቢገበያዩ ኑሮው ይህን ያህል ባልተሰቀለ ነበር። ለምሳሌ የበግ ዋጋ ሲጠይቁ ‹7 ሺህ› ከተባሉ ሳያቅማሙ ይገዛሉ፤ በሌሎችና በድሆች በግ ገዢዎች ላይ እሚያሳድሩት ተፅዕኖ ግን አይታያቸውም። አሁን አሁን ጨቅላ በግ/ፍየል ካልሆነ ደህና በግ/ፍየል ከ1500 ብር በታች አይታሰብም( አምስት ብር የተገዛ በግ ቆዳው በሰባት ብር እየተሸጠ ሥጋ ለመብላት ማነቃቂያ እንዳልተከፈለና የበጉና የቆዳው ዋጋ እኩል እየሆነ ሥጋ በነጻም እንዳልተበላ ሁሉ)። ያለው የሌለውን ማየት ካልቻለ ግንኙነታችን ጥሩ አይሆንም፡ የጎሪጥ እንተያይና ለመጎዳዳት አመቺ ሁኔታን መጠበቅ ሊከሰት ይችላል - ከዚያ ይሠውረን እንጂ። ከዚህ አኳያ ሲታይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ አብዛኛው ባለገንዘብና ባለሀብት እንደገንዘብ የማግኛ ሥልቱ ሁሉ ደንቆሮና ደደብ በመሆኑ እርሱን ከተመቸው ለሌላ አያስብም፤ አንዳንዱ አእምሮው በሞራና በስብ የታሸገ በመሆኑ እንኳን ለድርጊቱ ለአነጋገሩም አይጨነቅም - ለድፌና ዘርፍጤ ነው። እንጂ እኔ መግዛት ስለቻልኩ ብቻ ብር እየመዘረጥኩ ያሻኝን በተጠየቅሁት ዋጋ ዐይኔን ሳላሽ መግዛቴ በሌሎች ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ካላመዛዘንኩ በዚይም ላይ ‹ከሌለው እዚህ ምናባቱ ሊያደርግ ይመጣል? ድሃ!› እያልኩ በወገኔ ላይ የምሳለቅ ከሆነ በርግጥም ሆዳም ብቻ ሳልሆን አነሳሴን የረሳሁ ደንቆሮ ማይም ነኝ። ከዚህ አለመተሳሰብ በመነሳትም ነው የዱሮው የ40 ብር ድልብ በሬ ሸኖ አካባቢ በሚገኝ ሐሙስ ገበያ በቀደም ዕለት 40ሺህ ብር የተሸጠው። በሀገራችን የኑሮ ውድድሩ ተጧጡፏል። ያንተ የተጣራ ወርሃዊ ደመወዝ በትልቅ ግምት ብር 857 ሆኖ (ጥሩ ተከፋይ ሆነህ!) አንተን ጨምሮ ለስድስት ቤተሰብህ በወር ለጤፍ ብቻ ማውጣት እሚጠበቅብህ ነጭ ማኛ ይሁንልኝ ካልክ ይህችው ብር እንዳለች ጤፉ ብቻ ይዟት ይሄዳል - በግማሽ ኩንታል ሂሳብ። ከዚህ የበለጠ ዕንቆቅልሽ ያለበት ሌላ ሀገር ይኖራል ታዲያ? ሰው ግን እንዴት እዬኖረ ነው? ስታዩት ሕይወት እንደዱሮው ናት - ሰው እስከጣሪያ ይስቃል፤ይጫወታል፤ ይጠጣል - ያጣጣል፤ ይኖራል - ያኗኑራል፤ ይቀላለዳል፤ ይወፍራል፤ ይዋለዳል፤ ይበላል፤ ይተኛል፤ ይነሳል፤ ሕይወት ዑደቷን እንደቀጠለች ናት። ግን እንዴት የሚለው ጥያቄ ሊመለስልኝ ያልቻለ ከባድ ጥያቄ ሆኖብኛል - ለእኔ።


አሁንም እርግጥ ነው - ገንዘብ የማግኛ መንገዶች በርካታ ናቸው። ከውጪ ልጁ ወይ ዘመድ ወዳጅ እሚልክለት ሰው አለ። ሴት ልጁን ዐረብ ሀገር ለመከራና ለሰቀቀን ሕይወት ዳርጎ የምትልክለትን ጥሪት ለቁም ነገር ማዋል ሲገባው ለበዓልና ለመሳሰለው እሚምነሸነሽበት አለ። ወንድ ልጁን ደቡብ አፍሪካና ቦትስዋና ልኮ በሚላክለት ገንዘብም እንዲሁ። ከአሜሪካና ከሌላው ዓለምም በብዛት ይጎርፋል። ይህ ዓይነቱ የዲያስፖራ ገንዘብ ኑሮን እየሰቀለ ሰው ባቅሙ እንዳይኖር የበኩሉን አስተዋፅዖ እያደረገ ነው። አይላክ እያልኩ አይደለም - ወገንን ለመጨቆኛ አይዋል ግን እላለሁ። ነጋዴ ደግሞ ሸቀጡ ከተገዛለት ምን ገደደው? አንተ በርሃብና በችግር ብትጠገረር ምን ጨነቀው? ማን ለማን ሊያስብ? የ‹ተርን ኦቨር›ን ነገር እሚያውቅ ነጋዴ ደግሞ ከስንት አንድ ነው። አብዛኛው ዋጋ ይቆልልና አሥርም ሰው ይግዛው አሥራ አምስት እነዚያን ሀብታም ደንበኞቹን ሱቁን ዝምብ እየወረረው አፉን ከፍቶ ይጠብቃል እንጂ በመጠነኛ ትርፍ መቶና ሁለት መቶ ከዚያም በላይ ደንበኞችን በአንዴ በማስተናገድ ቀስ ብሎና ተያይቶ ማደግን አያውቅም። ኢትዮጵያዊነት ከስግብግብነት ጋር ሲዛመድ ማየት የዘማናችን ክፉ ዕጣ ፋንታ የሆነ መሰለኝ። ይህም ያሳዝናል። አብዛኛው ሰው ከየኅሊናው ጋር ተጣልቶ ከፈጣሪም ተኮራርፎ የገንዘብ ጣዖት አምላኪ ሆኗል - እገሌ ከገሌ ሳይባል።


በሙስና ገንዘብ እሚያጋብስ ሰው ሞልቷል። ለዚህ ዓይነቱ ሰው የኑሮ መወደድ አይገባውም፤ የደመወዙን መኖርም ከጉዳይ አይጥፍም። ያ ለስም ነው። ደመወዙን በጓደኞቹ ግፊት በስንትና ስንት ልመና እሚወስድም አለ - ሰው እንዳይታዘበውና በሙስና ‹እንዳይጠረጠር›ባቸው አስበውለት። ሙስና ሀገራችንን እንደነቀዝ ቦርቡሮ ጨርሷታል። ከላይ እስከታች ነቅዘናል - ማስተካከል በሚያስቸግር ሁኔታ። ያልተለፋበት ገንዘብ ደግሞ አወጣጡ እንዳገባቡ ነው - እየተመዘረጠ። ይህም አንዱ ጠንቃችን ነው ለኑሮው ማሻቀብ።


ደመወዝተኛ ገቢውን በራሱ አይጨምርም/አይቀንስም። ነጋዴውና በግል ሥራ ተዳዳሪው ግን የሸቀጥም ይሁን የአገልግሎት ዋጋውን በኑሮ ውድነቱ እያስታከከ ያስተካክላል፤ ለምሳሌ የአምስት ብር የቀድሞ ግምበኛ ዛሬ ከ150 ብር በታች አታገኙትም - ረዳቱን ከ50 በታች ወይ ንክች! ቫት ቢታወጅ ግብር ቢጨምር ምንም ቢሆን ምን ያን ሸክም እሚችለው ተጠቃሚ ደንበኛ እንጂ ነጋዴው አይደለም። ይሄ ቫት እሚሉት ድምባዣም የድምባዣሞች መመሪያ ደግሞ ፍጹም ዕውር ነው - ዕውር በፍካሬያዊ ፍቺው። ሕጉን ከመፍራት የተነሣ ከሰው የተረፈውን የሆቴል ፍርፋሪ ለውሻ ሲያኮናትሩ ቫት እሚጨምሩ ታዝቤያለሁ። ለሻይና ቡና አሁን ምን ቫት ያስፈልጋል? ልብ አድርጉ እንግዲህ ይህ ቅጥ ያጣ ግብርም በበኩሉ ኑሮውን አጡዞታል። ነጋዴውም ምን ቸገረው? እንዲያውም በሰበቡ ከቫቱ ሌላም ይጨምራል።


የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው መጨመርና ድጎማው መነሳቱ ሌላው የኑሮ ውድነቱ መንስኤ ነው። ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የትራንስፖርት አገልግሎት ወሳኝ ነው። አሁን እሱም እሳት ሆንዋል። በአምስት ብር ሸጠጥ እምንልበት የውሎ ጉዞ ዛሬ በመንግሥት የዋሊያ ወይም የግል ሀገር አቋራጭ አውቶቡስ 147ብር ደርሷል፤ በግል ሚኒባስ ከሆነ ደግሞ ባማካይ 200 ብር። የዋጋ ነገር አይነሳ - የሁሉም ነገር ዋጋ እጅግ ያስደነግጣል፤ ለመስማትም ይዘገንናል። የሚዘገንነው ግን በዋጋው መብዛት ብቻ እንዳይመስላችሁ - ከገቢያን ጋር ሊጣጣም አለመቻሉ ነው፤ ሻል ያለውን ደመወዝም አትመልከቱ። አብዛኛው በተለይ የመንግሥትና የግል ድርጅት ተቀጣሪ ሠራተኛ ደመወዙ ለሦስት ቀናትም እማይበቃው ነው። የኑሮ ግሽበቱ ደግሞ በመቶኛ ሳይሆን በዕጥፍ ነው እሚሰላው። ለምሳሌ እኔ ቤት ስሠራ በ31 ብር የገዛሁት ባለ12 ቁጥር የአርማታ ብረት(ፌሮ) ሰሞኑን ጠይቄ 267 መሆኑን ተረድቻለሁ፤ የ44 ብሩ የያኔው ስሚንቶ ደግሞ በጣም ወረደ ተብሎ 255 ብር በኩንታል። ሰውም ሆነ ዕቃ ለመጓጓዝ ዋጋው ሰማይ ሆንዋል። በዚህ ሰበብ ዕቃዎች ዋጋቸው አይቀመስም። ቤት መሥራት አይታሰብም - ከተጠቀሱት የጎን ገቢዎች ተቋዳሽ ካልሆንክ በስተቀር። እናስ የማንኛው ጎን ነው ይህን ኑሮ እሚችል?


ቤቱን እየሸነቆረ ሱቅና ግሮሠሪ እሚያደርግም መጠነኛ ገቢ ያገኛል። ቤቱ አመቺ ሥፍራ ላይ እሚገኝ ሰው በዚህ ይጠቀማል። ጥሩ ነው ። ይጠቀም። ወያኔ ግን አይለቀውም፣ በቃፊሮቹ ሲደርስበት በመብራትና በውሃ በስልክና በግብር ናላውን ያዞረዋል፡ ያኔ የሱን ናላ መዞር ወደተጠቃሚው ያዞራል። በዚህም ምክንያት ኑሮ ሽቅብ ትጉናለች። እንዲህ እንዲህ እያልን እንደነገሩ በሕይወት አለን። እነሱም ይጭኑናል እኛም እንደጋማ ከብት ልክክ አድርገን እንጫናለን። አለን - መኖር ከተባለ። ቢበቃኝስ? ኤዲያ - በደም ምድር የመፈጠር ጣጣ ያለው አባዜ! ለማንኛውም የአሁኑ በዓል ከሚቀጥለው ይሻላል - ቢሆንም ለሚቀጥለው በዓል በሰላም ያድርሰን። መድረሱ በራሱ ዋጋ ካለው።


ተሻለ መንግሥቱ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!