ኤፍሬም እሸቴ: ብትስማማ ነው እንጂ የሚያስደምመው ባለመስማማትህ ምን ይደንቃል?
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
ጥብቅ ማሳሰቢያ:- ጽሑፉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመደገፍ የተጻፈ ጽሑፍ አይደለም። ጽሑፉ ኤፍሬም እሽቴ የተባለው አንድ "የማህበረ ቅዱሳን" የስራ አመራር አባል ግለሰብ “ጠ/ሚኒስትሩ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን በተናገሩት አልስማማም” ሲል ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ በጻፈው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን አስተምህሮ የማይወክል ዝርው ይዘት ያለው ጥሬ ጽሑፍ አስቸኳይ እርምት እንዲደረግበትና በክርስትና ስም በአንባቢያን ላይ የፈጠረውን ብዥታ ግምት ውስጥ በማስገባት የተጣራ ምስል ለመስጠት ኩልል ቅልብጭ ባለ መልኩ የተዘጀ ጽሑፍ ነው።
"ማህበረ ቅዱሳን" የቤተ-ክርስቲያን የቆሎ ት/ቤት ያልቀመሰ፣ የዜማ፣ የቅኔ፣ የመጽህፍት ትርጓሜያት፣ የቅዳሴ፣ የአቡሻክር … ወዘተ ባህር ያልዳሰሰ የቤተ-ክርስቲያን ጥንተ ታሪክ ያልመረመረ፣ ጥምጥም ያለው ጥቁር ጎማሳ፣ ሆኖ እያለ እምነበሃን የማያውቅ ዲያቆን፣ አሀዱ አብን የማያውቅ ቄስ፣ አአትብ ገጽየን የማያውቅ ክርስቲያን፣ የሴቶችና የወንዶችን መግቢያ በር በቅጡ የማያውቅ፣ ሱቅ ከፍቶ ቄስ ቀጥሮና አቁሞ ስለ ነገደ ቄስ የሆነ የሚመስለው ጠባቂ ነኝ የሚል አጽራረ ቤተ-ክርስቲያን ጿሚ መሳይ አጋሰስ፣ የማይሰግድ አሰጋጅ፣ ለማስተማር የማይበቃ አቃቤ መቃብር ባለ ዲግሪ፣ አስራት የማይከፍል በዝባዥና አስከፋይ፣ የማይቀድስ አስቀዳሽ፣ ያልተለወጠ ለዋጭ አስመሳይ የጎበዝ ጥርቅም ማኅበር ነው ሲባልኮ ተራ ውንጀላ ወይንም ደግሞ ክስ ሳይሆን ምስክርነታች ጭብጥ ላይ የተመሰረተ እውነት ነው።
ይህች ጦማር የቀድሞ የማህበሩ አውራ ቂስ ኤፍሬም እሸቴ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በዕለተ ማክሰኞ ሚያዚያ 9/2004 ዓ.ም በፓርላማቸው ተገኝተው ያደረጉትን ንግግር ተከክትሎ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ እግረ መንገዳቸውን ያነሱትን እና በኢትዮጵያ ውስጥ አለውን “አክራሪነት” በክርስቲያኑ በኩል “ይወክልልናል” ብለው የጠቀሱትን ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ እኔም እንደ አንድ አባል የማምንበት አቀርባለኹ። ማኅበሩ በኃላፊዎቹ በኩል የሚሰጠው መልስ እንደተጠበቀ ሆኖ ለሁለት አሥር ዓመታት አባል የሆንኩበት እና መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በመስጠት በሁሉም ዘንድ የተመሰከረለት ማኅበር “አክራሪ” አለመሆኑን በግሌ ለመመስከር እገደዳለኹ።” ሲል ባልዋለበትና ባላለፈበት የቅድሳት መጻህፍት ቃል ዓውዱን ባላገናዘበ አኳኃን ምክርን ለማጨለም ባደረገው ሙከራ የተፋለሰውን የክርስትና አስተምሮና በማን አለብኝነት መንፈስ የፈጠረውን እጅግ ግዙፍ የሆነ ስህተት ኩልል ባለ መልኩ ያስቃኛናለች። መልካም ንባብ!
ግለሰቡ ምንም እንኳን ራሱ እንደ አንድ ተራ የማህበሩ አባል አድርጎ ለመቅረብ ቢሞክርም ለረጅም ዓመታት በማህበሩ የስራ አመራር አባል: በማህበሩ የተለያዩ የሃላፊነት ቦታችም ሲሰራ የቆየ: አሁንም ቢሆን ከቤተ-ክርስቲያን ጫንቃ ያልወረደ: በቤተ-ክርስቲያን የምጽዋት ገንዘብ ኑሮውን ያደላደለ በዋናነት ከተጣያቂነት የማያመልጡ የማህበሩ ልሂቃን መካከል ለመሆኑ የማህበሩ ስም በተነሳ ቁጥር ይህን እውነታ ሳያውቅ የሚቀር ያለ አይመስለኝም። ግለሰቡ ወደ አሜሪካ እንዴት መጣ አሁንስ የማህበሩን ተልዕኮ ከማከናወን አንጻር ምን እየሰራ ይገኛል የሚሉትና ሌሎች ተጓዳኝ ጥያቄዎች በቅርብ በስፋት የምንመለከተው ይሆናል። ለጊዜው ግን የተነሳንበትን ዋና ርእስ እንጠበጥባለን።
“በመጀመሪያ “አንድ ሃይማኖት” የሚለው መሠረታዊ ሐሳብ ለብዙ ውይይቶች በር የሚከፍት ትልቅ ጉዳይ ነው። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚያስተምረን እና የጥምቀት አክባሪ ክርስቲያኖች በቲ-ሸርቶቻቸው ላይ አትመውት በፎቶግራፍ የተመለከትኩት ኃይለ ቃል ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ምዕራፍ 4 ቁጥር 5 ላይ የጻፈው “አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት” የሚለው ሐዋርያዊ ቃል ነው። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል እንጂ የጥምቀት አክባሪዎቹ የፈለሰፉት አይደለም። የትኛውም ክርስቲያን “አንድ ሃይማኖት” ቢል የሐዋርያውን ቃል መጥቀሱ እንጂ ሌላ እምነት ላላቸው ኢትዮጵያውያን ጥላቻ አለው ማለት አይደለም። የጥምቀት አክባሪ ወጣቶች ቲ-ሸርቶች ላይ የተጻፈውን የሐዋርያውን ቃል የምረዳው በዚህ መንፈስ ነው።” (ውድ አንባቢ: የዚህ ጽሐፍ ዋና ዓላማ የኤፌሶን መልዕክት መንፈሱን በሚገባ መተንተን: መመስከር ነው)።
ይህ ሰው ሌላው ቢቀር የተጠቀሰውን ቃል ፊደላትን ከማንበብና ከማነብነብ ባልዘለለ መልእክቱን በሚገባ አለመረዳቱና አለማወቁ ብቻ ሳይሆን የፈጠረውን ስህተትና ያፋለሰውን አስተምህሮ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን ሊቃውንት ጨምሮ አባባሉን ሌሎች እንደሚጋሩት ሃፍረት ሳይሰማው እንዲህ ሲል መግለጽ ነው “በዚህ የሐዋርያው ቃል ውስጥ ያለው “አንድ ሃይማኖት” የሚለው አገላለጽ የሚናገረው ስለ ክርስትና ሃይማኖት ነው። ሌሎች እምነቶች የሉም፣ መኖርም የለባቸው የሚል የጨፍላቂነት ትምህርት አለመሆኑን ሊቃውንቱ አምልተው አስፍተው ሲያስተምሩ ኖረዋል፤ እያስተማሩም ነው። አሁን ደርሶ የሚለወጥ ነገር የለም።” እዚህ ላይ ሊቃውንት የሚላቸው በሰው የእአምሮ ንብረት ስርቆት ላይ የተሰማሩ እንደነ ዳንኤል ክብረት የመሳሰሉ በጠራራ ጸሐይ ፎቶግራፍ የሚያነሱ ከሆነ እስማማለሁ።
በዚህ ሳይገታም (ጽሑፉ የሚያጠነጥነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር እስከ ሆነ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጎንተሉ ነው) በትልቁ ከቃሉ ጋር ፈጽመው የማይታወቁ ራሱ አቶ ኤፍሬም ጨምሮ ማህበሩና አባላቱ እያሉ በተጨማሪም አራት ገጽ ያስጻፈበት ምክንያት ፊደል እንደቆጠረ እንደማንኛው ሰው መልእክቱ ሲያነበው (ኤፌ. 4:5 ለማለት ነው) ነገር ቆስቋሽ ሰላም ነሺ የአመጽ ቋንቋ ሆኖም ስለተሰማው ጳውሎስ ወይንም ደግሞ እግዚአብሔርን ላለማሳፈር “አንድ ሃይማኖት የሚለው አገላለጽ ከሃይማኖት ጋር በማይተዋወቁ ሰዎች ዓይን ከተመለከትነው መቻቻልን ለማስተናገድ ፈቃደኝነት የጎደለው አገላለጽ ሊመስል ይችላል።” በማለት አጉል ጥብቅና በመቆም ለመገንባትና ለማጣጣም በሚያደርገውና ባደረገው ሙከራ ቃሉን ማፋለሱ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማሰደቡ ስመለከት አገላለጹ በቀላሉ የአብዬን ለምዬ አስብሎኛል።
ውድ አንባቢ:- እንግዲህ እስከ አሁን ድረስ ያለነው መግቢያ ላይ ለመሆናችን ለመግለጽ እወዳለሁ ወደ ሚቀጥለው የጽሑፉ ዋና ክፍልና ዓላማ ስንሸጋገርም ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው እንዲሁ ህይወት የሆነውንና ህይወትን የሚሰጥ የመልእክቱ መንፈስ እናገኘው ዘንድ በታላቅ እርጋታና ማስተዋል ጽሑፉን እናነበው ዘንድ በድጋሜ በወንድማዊ መንፈስ በትህትና እጠይቃለሁ።
“እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤
እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።
በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤
ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።” ኤፌ. 4: 5
ጳውሎስ እንዲህ ያለ መንፈስ ያለው የአማኞች ህብረትንና አንድነትን የሚያጠነክር መልእክት ሲጽፍ ለመጀመሪያ ጊዜው አይደለም። የአማኞች በቁጥር መበራከትና ከተለያየ ልማድና ወግ መምጣታት ተከትሎ ይፈጠርው የነበረውን ችግር በማስመልከት ጳውሎስ በርካታ ገንቢ መልእክቶችን ጽፈዋል። ለምሳሌ የተመለከትን እንደሆነ በኤፌሶን ከተማ ሳለ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈውን አንደኛ መልእክቱ ለርእሳችን ተጠቃሽ ማጣቀሻ ነው።
የቆሮንቶስ ቤተ-ክርስቲያን ከተከሰቱ በርካታ ችግሮች መካከል ትልቁና ዋነኛ ችግር በእግዚአብሔር ቃል ካለማደግና ካለመብሰል ቃሉንም በሚገባ ካለማጥናት የተነሳ "እኔ የጳውሎስ ነኝ" "እኔ የኬፋ ነኝ" እያሉ ለአራት ተከፍለው ጎራ ለይተው እርስ በርሳቸው መቧቀሳቸው ነበር። ይህንን የሰማ ጳውሎስ "ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ ሃሳብም ተባብራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችሃላሁ። ወንድሞቼ ሆይ በእናንተ ክርክር እንዳለ ስለ እናንተ የቀሎዔ ቤተ ሰቦች አስታውቀውኛል። ይህንም እላለሁ እያንዳንዳችሁ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፥ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፥ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ስለ እናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን? …" (1ኛ ቆሮ. 1: 10) እያለ ይቀጥላል።
የቆሮንቶስ ሰዎች በክርስቶስ ስም በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ መሰባሰባቸው ሲያበቁ ኑሮአቸው ግን ፈጽሞ የምስራች (ወንጌል) ካልሰሙት አህዛብ በማይተናነስ ድርጊት ተጠምደው ወደ ቀድሞ ኑሮአቸው በመመልስ/ተመልሰው ልምምዳቸውን ሲገፉበት መሆናቸው ሲሰማ የሰማውንም ሁሉ እውነት መሆኑን ሲያረጋግጥ የጻፈው መልእክት የቆሙበት ስፍራ ለማመላከት ነበር። ከዚህ የጳውሎስ መልእክት አንድ ትልቅ ቁምነገር ለመረዳት የሚቻለው ሰው ሲባል በእግዚአብሔር መንፈስ ካልተነካ በስተቀር በሃሳብም ሆነ በቃል አንድ ብሎ ነገር ፈጽሞ የማይታሰብ ነው የሚለውን አንድምታ እንደተጠበቀ ሆኖ የእግዚአብሔር መንፈስ የተቀበሉ: ብዙ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች የተገለጡባቸው: በአንድ ንግግር በአንድ ልብ በአንድ ሃሳብና ቃል ህብረታቸው ከማንም በላይ ያጠናክሩ ዘንድ የሚጠበቅባቸው የቆሮንቶስ ሰዎች በአንጻራዊ ገጽታ ሆነው ሲያገኛቸው በሌላ አነጋገር የተቀበላችሁት መንፈስ እኮ እንዲህ ለመነታረክ: ለመለያየት: ለመናቆር እርስ በርሳችሁም ለመናካስ ሳይሆን የተቀበላችሁት መንፈስ የተበተነውን የሚሰበስብ/አንድ የሚያደርግ: ልዩነትን በወንድማዊ ፍቅርና በመቻቻል የሚያጠብ: በጸብ ፈንታ ሰላምን ፍጹም መዋደድን የሚሰጥ: እግዚአብሔርን የሚያከብርና የሚያነግስ ነው ታድያ ይህ መንፈስ የትገባ? ምን ዋጠው? ወይስ የተቀበላችሁትን አታውቁምን? ለመሆኑ እንዲህ ያለ ግርግርና ኢ-ክርስቲያናዊ ምግባር ከማን የተማራችሁ ነው? ይህ ሁሉ ወከባ ምን ለመሆን: የትስ ለመድረስ ይሆን? ምክንያታችሁ ማወቅ እፈልጋለሁ። ሰው ሲያምን ከስጋ ደዌ ከመንፈስ አባዜ ይፈወሳል እንጅ እንዲህ ያለ ነገርስ ትክክል አይደለም። አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ 12:13) በማለት ወደ ልቦናቸው ይመለሱ ዘንድ የሚያሳስብ ነው።
አሁን በዚህ መንፈስ ወደ ኤፈሶን መልእክት ተመልሰን እንመጣለን። የኤፌሶን መልእክት የተጻፈው በተመሳሳይ ጸሐፊ በሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲሆን መልእክቱ የተጻፈበት ምክንያትም እንደ እንዳንዶቹ በሚገጥማቸው ችግሮችና መሰናክሎች የተነሳ ሳይሆን በመጽሐፉ ምዕራፍ አንድና ሁለት በተገለጸው መሰረት መልእክቱ የተጻፈበት ምክንያት በኤፌሶን የምትገኘውን ቤተ-ክርስቲያን ምእመናንና አባላት (ሌሎች) በዘመን ፍጻሜ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ አሳብ ይረዱና ያውቁ ዘንድ: አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ጠንክረው የክርስቶስ ፍቅር ለማስተዋልና ለማወቅ ይበረቱ ዘንድ እንዲሁም በእግዚአብሔር ጸጋ ዕለት ዕለት ወደ ምልዓት ያድጉ ዘንድ የተጻፈ መልእክት ነው።
እንግዲህ ጳውሎስ "አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት” ሲል በጌታ በማያምኑ: ሃይማኖትም በሌላቸው: በልተጠመቁ ወገኖች/አካላት ላይ ጣቱ እየቀሰረ ሳይሆን ያለው "አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት” ማለቱ የኤፌሶን ምእመናን በተጠሩበት መጠራት እንደሚገባ በሚገባ እንዲመላለሱ ቀደም ሲሉ ጌታ አምነው በእውቀት ለተጠመቁ ምእመናን በክርስቶስ የያዛችሁትን መንገዳችሁን አጽንታችሁ ያዙ: በትእግስት በየዋሃትና በፍቅርም እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ: ተዋደዱ ምንም የሚያጨቃጭቃችሁ: የሚያነታርካችሁና እርስ በርሳችሁ የሚያናክሳችሁ ነገር አይኑር የሁላችሁም ጌታ አንድ ጌታ ነው! ሃይማኖታችሁም እውነት መንገድም ህይወትም የሆነ ኢየሱስ አንድ ነው! ሁላችሁም የተጠመቃችሁት ጥምቀት እንዲት ጥምቀት ናት! ይኸውም:
-
ግሪኩም አይሁዱም አንድ የሚያደርግ:
-
ባሪያው ከጭዋው የሚያስተካክል:
-
ሴቱም ከውንዱ እኩል የሚያደርግ (በእመነት)
-
ክርስቶስን የሚያለብስ:
-
ከክርስቶስ ጋር ሕብረት በሚፈጥር:
-
ለምስክርነት የሚያበቃ ጥምቀት ነውና እንግዲህ ይህን መንፈሳችሁን ጠብቁ! በማለት የኤፌሶን ምእመናን
-
ፍቅር አጥብቀው እንዲይዙ:
-
መቻቻል እንዲለማመዱ:
-
በሕብረት/አንድነት የሚገኘውን በረከት ተካፋዮች እንዲሆኑ:
-
ወንድማማችነት እንዲያጣጥሙ:
-
ስለ የክርስትና ህይወት ትርጉም እንዲያውቁ:
-
በጥምቀት ስለተፈጸሙት ስርዓት እንዲያስቡ:
-
ከሁሉም በላይ ደግሞ በጌታ ስም ማመን ምን ማለት እንደሆነ እንዲያውቁ ጸጥ ረጭ ባለ በዝግታ መንፈስ የሚነበብ/የሚደመጥ: ተነቦም/ተሰምቶ ወደ ልብ ስለሚወርድና በልብም ስለሚጠበቅ ከሃጢአት: ከጥፋት: ከአመጽ ስለ ሚያተርፍ የተበተነውን ስለሚሰበስብ ህያው ቃል ላከላቸው (መከራቸው) እንጂ የኤፌሶን ምእመናን "አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት!" የሚል መፎክር ይዘው በኤፌሶን ጎዳናዎች አቧራ እንዲያስነሱ አይደለም! እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባ ነጥብ ቢኖር አቶ ኤፍሬም እንሳሰበውና እንደተረጎመው "ጥምቀት! ጥምቀት!" እየተባለ የሚጮክ ዝሩው ቃል ሳይሆን ጥምቀት ተብሎ የተጠቀሰውን የውሃ ጥምቀት የሚያመላክት ለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። አንድም እንዲት ማለቱ ይህችንም ጥምቀት አንዳዶቻችሁ በውሃ ሌሎቻችሁ በወተት አልተጠመቃችሁም እንዲል ነው።
-
በሰላም ማሰሪያ: የሚለው ትህትና: የዋህነት: ፍቅር ሁነኛ የአንድ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምን ክርስቲያን መታወቂያዎች ናቸው። “የማህበረ ቅዱሳን” አባላት ክርስቲያን ናቸው ለማለት በራሱ ቀድመውኑ በክርስቶስ ብቸኛ አዳኝነት ሲያምኑ አይደለም ወይ? እንዲሁም በሌላ ስፍራ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና” እንዲል ኢየሱስን የለበሰ ኢየሱን ይመስላል!! የሀገሬ ሰው "ከአህያ ጋር የዋለ ኰርማ ሕላ (እንደ አህያ መጮህ) ባይማር ምን ይለምዳል" እንደሚለው እንደ "ማህበረ ቅዱሳንና” አባላቶቹ ያሉት ከቃሉ ጋር ምንም ዓይነት ግኑኝነትና ሕብረት የሌለው ደግሞ ጋንጩር መምሰሉ ሊደንቀን አይገባም።
መቼም በዚህ ሁሉ ሐተታ ጳውሎስ “አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት” በማለት የጻፈው መልእክትና "ማህበር ቅዱሳንና” አባላቱ ደግሞ በፊናቸው ባልገባቸው “አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት” ማለትና ምን እንደሆነ ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ የተቀረውን ደግሞ አንድ በአንድ ተለቅመው ለንባብ እስኪበቁ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረት ሰላማና ፍቅር ከሁላችን ጋር ይሁን።
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
Email: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
April 26, 2012
United states of America