ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

በሀገሬ ሳለሁ፥ ለዓመታት ከለፋሁበት የትምህርት ገበታዬ ተፈናቅዬ፣ ያለፍርድ ቤት ማዘዣ ወረቀት ተይዜ ከአንዴም ሁለቴ ለእስር የተዳረግኩ፣ በሞትና በህይወት መካከል የተገረፍኩና የተደበደብኩ፣ በመጨረሻም ሀገሬን ለቅቄ በባዕድ ምድር ያለ አንዳች ረዳትና የህይወት ዋስትና በእንግድነት እንድኖር የተገደድኩ ስዘርፍ፣ ሳምጽና የሰው ሚስት ሳማግጥ ተገኝቼ ወይም ተደርሶብኝ ሳይሆን ሕገ መንግስታዊ (አንቀጽ 29) መብቴን በመጠቀም ጸረ-ቤተ ክርስቲያን፣ ጸረ ሀገርና ጸረ ትውልድ በሆነው ድብቅ አጀንዳ ያለው ማህበር ላይ “ማህበረ ቅዱሳን ወይስ ማህበረ ሰይጣን?” በማለት በበርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ሰነዶችና ደብዳቤዎች የተደገፈ ከጻፍኩት መጽሐፍ የተነሳ ነበር። የታሪኩ አንዳኛ ምዕራፍ መሆኑ ነው!

 

ሁለተኛውሳ? ማለታችሁ አይቀርም። የሁለተኛው ነገርማ ደግሞ የከፋ የሚያደርገው ሰሞኑ ለንባብ ከበቁ ጽሑፎች ተያይዞ ከወደ “ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች”፣ “የነጻነትና የፍትሕ ታጋዮች”፣ “ዲሞክራቶችና ነጻ አውጪዎቻች” ሰፈር እየታየ፣ እየተሰማና እየተንጸባረቀ ያለው እውነታ መሆኑ ነው። ሰው ሃሳቡን ገለጸ ተብሎ ሃሳቡን ሳይሆን ዕድሜውን ለማሳጠርና ዘመኑን ለማጨናገፍ የሚታየው የሚሰማውና የሚወርደው መብረቅና ነጎድጓ እንዲሁም ከጥቂቶች የሚወረወረው ጦርና ፍላጻም ከጽሑፉ አዘጋጅ አልፎ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የድረ ገጾች ባለቤቶችን ጭምር እያዳረሰና እያጠቃ መምጣቱ ይባስ ጉዳዩ አሳሳቢ አድርጎታል። ስቀለው! ስቀለው! ባይ ቁጥርም ተበራክተዋል። ቁምነገሩ ሰው ሃሳቡን ገለጸ ተብሎ እንዲህ ያለ ልቅነት ምን አመጣው የሚል ነው? ሌላው ቢቀር ሕግ ባለበት ሀገር በርስትህና በሚስትህ የተገኘ ሰው እንኳን ቢሆን እንዲህ አታንጓጥጠውና ጉዳዩ ፍጹም ሌላ መልክ ይዞ የከፋ አደጋ ከማድረሱ በፊት ለመመካከር ያክል እንዲህ ያለ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ግድ ብለዋል።

 

እንግዲህ “ሁላችን” እንደምናውቀው የሰው ልጆች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በተመልከተ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 19 ቀዳሚ ተጠቃሽ ለመሆኑ የምንስተው አይመስለኝም። የዛሬ ማወያያ ርእሳችንም ከዚህ አንቀጽ በመነሳት ይሆናል።

 

አንቀጽ፡ 19 “እያንዳንዱ ሰው የሐሳብና ሐሳቡን የመግለጽ መብት አለው።

ይህም መብት ያለጣልቃ ገብነት በሐሳብ የመጽናትንና ዜናን ወይም

ሐሳቦችን ያላንዳች የድንበር ገደብ የማግኘትን የመቀበልንና ወይም የማካፈልን ነጻነትም ይጨምራል።”

 

የሚል ሲሆን በዚህ አንቀጽ ውስጥ የተመላከቱ ነጥቦችም በጥቂቱ የተመለከትን እንደሆን፣ “እያንዳንዱ ሰው የሐሳብና ሐሳቡን የመግለጽ መብት አለው“ እንዲል በዋናነት አንድ ሰው የሌላውን ወገን ሃሳብ የመቀበል፣ የማስተናገድ፣ የማስተጋባት፣ የማንጸባረቅና የማመን በአንጻሩ ደግሞ መስሎ ያልታየውን ሃሳብን በሃሳብ የመቃወምና ያለመቀበል በተጨማሪም የራሱን ሃሳብ በማንኛውም ዓይነት መንገድ በቃልም ሆነ በጽሑፍ የመግለጽ መብት እንዳለው የሚያትት አንቀጽ ነው። ልብ ይበሉ! “መብት አለው” እንዲል ይህ ዓይነቱ መብት ደግሞ በሕግ የተጠበቀ ነው። ሲሞቀን የምቆፈቅፈው ሲበርደን ቁልቁሊት የምንደፋውም አይደለም። በሌላ አገላለጽ የሰውን ሃሳብ፣ በሃሳብ የመቃወም መብት እንደተጠበቀ ሆኖ በአንድም በሌላም መልኩ የሰውን በነጻነት ሃሳብን የመግለጽ መብት ተከትሎ የሰውን መብት መግሰስ ግን በሕግ እንደሚያስጠይቅ ነው። አክሎም “ይህም መብት ያለጣልቃ ገብነት … የመቀበልንና ወይም የማካፈልን ነጻነትም ይጨምራል” እንዲል ይህን ነጻነት በመጋፋት ሕጋዊ ነጻነቱን ተጠቅሞ ሃሳቡን በሚገልጽ ግለሰብም ላይ ማንኛውም ዓይነት ጫና ለማሳደር ሙከራ ማድረግ፣ ይህ በል እንዲህ ግን አትበል፣ ይህን ጻፍ እንዲህ ግን አትጻፍ በማለት ሃሳቡን በነጻነት በሚገልጽ ግለሰብ ትክሻ ላይ መንጠላጠል ጸረ-ሰብዓዊ ነጻነት ከመሆኑ በላይ ጋጠ-ወጥነት ለመሆኑ ምንም አያጠያይቅም።

 

አሁን እንግዲህ ይህን ትንታኔ ይዘን የአንድ ግለሰብ ሃሳብን/ጽሑፍ ተከትለው ወደ ሚሰጡት “አስተያየቶችና” ወደ ሚሰነዘሩት የተቃውሞ ቃላቶች የተመለስን እንደሆነ በበኩሌ ብዙ ከማለት በመቆጠብ ከተባለ ዘንዳ “ዲሞክራሲን ያያችሁ?” ማለት አሁን ነው ለማለት እወዳለሁ። ምንነው ቢሉ?

 

  • ከዚህ በላይ ፍትሕን ማሳጣት፣
  • ከዚህ በላይ ጸረ-ዲሞክራሲ እንቅስቃሴ፣
  • ከዚህ በላይ አንባገነናዊ አስተሳሰብ፣
  • ከዚህ በላይ የዜጎችን ነጻነት መጋፋት፣
  • ከዚህ በላይ ሰብዓዊ መብትን መርገጥ፣
  • ከዚህ በላይ የዜጎች ድምጽ ማፈን፣
  • ከዚህ በላይ ዳግም የባርነት ቀንበር መጫን፣
  • ከዚህ በላይ የዜጋ ሃሳብን በነጻነት የመግልጽ መብት ከመከልከል ገደብ ከማኖርና ድንበር ከማበጀት በላይ ወንጀል የለምና። “ሁለተኛ ግፌ ጫንቃዬን ተገርፌ ልብሴን መገፈፌ!” ለማለት የደፈርኩበት ምክንያትም ከዚህ የማይካድ ተጨባጭ ገጽታችን የተነሳ ነው።

 

ስለ ፍትሕ፣ ነጻነትና ዲሞክራሲ መቆም ማለት ፍትሃዊ አመላካከት ያላቸውን ዜጎች በተራ ቃላት ማሳደድ፣ መመንጠር፣ መልቀምና ማጥፋት ከሆነ የተያያዝነው አገርን የማልማትና ትውልድን የማዳን ስራ ሳይሆን በአንጻሩ ራርሳችንን የመግደል ከፍተኛ ወንጀል ላይ መሰማራታችንን መሆኑ ልናሰምርበት ይገባል። በነገራችን ላይ የዚህ ሁሉ ግርግር ምንጭ ሌላ ምንም ሳይሆን መሰረቱ በተበላሸ ፖለቲካ ለመቆማችን የሚያሳይ ሁነኛ ምሳሌ ለመሆኑ ለመጥቀስ እወዳለሁ። በተረፈ ግን ያገናኘን ሀገርና ሕዝብ እስከሆነ ድረስ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ስለ ሀገሬ ሀገራዊ፣ ሃይማኖታዊና ማህበረሰብአዊ ጉዳዮች ከራሴ አልፌ ሕዝብን ይጠቅማል ያንጻል ሀገርንም ይበጃል ያቀናል የምለውን ከቅዱሳት መጻሕፍት የተማርኩትን ያለመከልከልና ያለገደብ ያለምንም ተጽእኖም የመጻፍ፣ የመናገር፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና የማንሸራሸር ተፈሮአዊ፣ ሕጋዊና ሞራላዊ መብት አለኝ። ስራዎቼንም በተመለከተ እንደማንኛውም ንጹሕ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኢትዮጵያዊ ራዕይ ባላቸውና በኢትዮጵያ አንድነት በሚያምኑ ድረ ገጽች ላይ አቅሜ በፈቀደው በመሳተፍ ረገድ ባለ ሙሉ መብት መሆኔን ስገልጽ በአክብሮት ነው።

 

እዚህ ላይ አንባቢያን እንደ ግለስብ የአንድን ሰው ጽሑፍ የማንበብና ያለማበብ ባለሙሉ መብቶች ሆነን ሳለን ልዩነትን የማስተናገድ ግዴታ ባለባቸው መገናኛ ብዙሐን ላይ ጫና ለመፍጠርና የፈላጭ ቆራጭነት የመጫወት ሚና ለማሳየት የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ፍጹም ኢ-ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ መሆኑን ተገንዝበን ከአንዲህ ዓይነቱ የሀገርንና የትውልድን ዕድገት የሚያጨናግፍ ተግባር እንድንታቀብ በአክብሮት እጠይቃለሁ። አሁንም ቢሆን ጽሑፌን ከማገባደዴ ቤፊት በድጋሜ ለማለት የምፈልገው ነጥብ ቢኖር ያገናኘን ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ ሆነ ድረስ ማንም የነጻነት ሰጪ ናነሺ ሊኖር እንደማይችል አውቀን ያዋጣኛል ብለን በተያያዝነውና በያዝነው አቋም እንግፋበት እላለሁ።


ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

May 6, 2012

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ