ያሬድ አይቼህ

የደርግን ወታደራዊ መንግስት ለማስወገድ በተደረገው ትግል የብዙዎች ህይወት ተሰውቷል። ከቀይ ሽብር ጀምሮ ኢህአዴግ አዲስ አበባን እስከተቆጣጠረበት ቀን ድረስ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የህይወት፣ የአካል፣ የንብረት፣ የእድሜና የስነልቦና መስዋዕትነት ከፍለዋል። ሆኖም ግን መስዋዕትነት መክፈል አንድ ጊዜ ሆኖ የሚያልፍ ክስተት አይደለም - መዘዝም አለው።

 

 

ከመዘዞቹ ውስጥ ግልጽ ሆኖ የምናየው ከአካል መስዋዕትነት የተነሳ በሰዎች አካል ላይ የሚደርሰውን ጉድለት ነው። ነገር ግን መስዋዕትነት አካላዊ ከሆነው በተጨማሪ ሌሎች ጥልቅ የሆኑ መዘዞች አሉት። ከነዚህ መዘዞች አንዱ የመስዋዕትነት ወጥመድ ብዬ የምጠራው ነው።

 

መስዋዕትነት መክፈል እንደማንኛውም ክፍያ ዋጋ ወይም ተመን አለው። አነድ ሰው ጊዜውን መስዋዕት ካደረገ፣ ለዚያ ለከፈለው የጊዜ ዋጋ የሚጠብቀው ምላሽ አለ። ለምሳሌ ሃማኖተኛ ሰዎች ለሚያደርጉት መልካም ስራ ከአምላካቸው የሚጠብቁት ሽልማት ወይም ስጦታ ይኖራል። ሌሎች ደግሞ ከሚያደርጉት ግብረ-ሰናይ ድርጊት የተነሳ ለመንፈሳቸው የሚያገኙት እርካታ ለመስዋዕትነታቸው እንደ ክፍያ ወይም ምላሽ ይቆጥሩታል።

 

በአገራችን ዘመናዊ የፓለቲካ ታሪክ ብዙ መስዋዕትነት ከከፈሉት የፓለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ግንባር ቀደም ናቸው። ግምቱ ቢለያይም በቀይሽብር ከ100,000 እስከ 200,000 ኢትዮጵያውያን የኢህአፓ አባል ወይም ተባባሪ በሚል ሰበብ በግፍ ተጨፍጭፈዋል። ከደርግ ጋር በነበረው የትጥቅ ትግል የህወሓት 60,000 ታጋዮች እደተሰዉ ፓርቲው ገልጿል። ለሁሉም ሰማዕታት ዘላለማዊ ክብር ይገባቸዋል!

 

መስዋዕትነትና ስሜት

መስዋዕትነት የባለቤትነትና የይገባኛል ስሜት ይፈጥራል። ይህ ስሜት ምክንያታዊ ከሆነው የሰው አስተሳሰብ በላይ እጅግ በጣም ግዙፍ ነው። ከመስዋዕትነት የተነሳ የሚፈጠረው የባለቤትነት ስሜት ለብዙዎች ቋሚ የእድሜ ልክ ሸክም ሆኖ ይኖራል። የደማ፣ ጓዱን ከጎኑ ያጣ ሰው እድሜ ልኩት ለዚያ መስዋዕትነት ተገቢ የሆነውን ዋጋ ለማግኘት የትግል እሳቱ ቋሚ ሆኖ ይነዳል። ይህንን መረዳት የሚችሉት የደሙ ብቻ ናቸው፤ ወገናቸውን ያጡ ብቻ ናቸው። ያልደሙ ግን አይገባቸውም።

 

ሆኖም ግን ይህ የባለቤትነትና የይገባኛል ስሜት ሁልጊዜ አወንታዊ ገጽታ ብቻ አያንጸባርቅም። ከዚህ ስሜት የተነሳ የማያባራ የበቀል፣ የማን አለብኝነትና የትዕቢት፣ እንዲሁም የእብሪተኝነት፣ የአስተሳሰብ ጭፍንትነትና ፋሽስትነት ይፈጠራሉ። ከከፈሉት መስዋዕትነት የተነሳ “እኛ ነን ትግን የምናቅ!” “ያ የኛ ትውልድ ብቻ ነው አብዮተኛ!” “እኛ ነን ጦርነት መስራት የምናቅ!” “ታግለን ነው ስልጣን የያዝነው፤ አንለቅም!” የሚሉ ወገኖቾቻን በሁሉም የፓለቲካ ጎራች አሉ።

 

የባለቤትነትና የይገባኛል ወጥመድ

ከህወሓት መሰረታዊ ችግሮች ውስጥ አንዱ ከመስዋዕትነት የተነሳ ድርጅቱ እና ደጋፊዎቹ ወገኖቻችን የገቡበት የባለቤትነትና የይገባኛል ወጥመድ ነው። ይሄ ወጥመድ ህወሓትን ጭንጋፍ ድርጅት አድጎታል። ወደፊት መራመድ የማይችል፣ ራሱን ማደስም ሆነ መታደግ የማይችል፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ አደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባና መውጫ ቀዳዳ እንዲያጣ ዳርጎታል። እዚህ ጋር አንድ ግልጽ ማረግ ያለብኝ ጉዳይ ቢኖር የትግራይ ወጣቾች፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በህወሓት ውስጥ ታቅፈው ላደረጉት ትግልና ክቡር መስዋዕትነት ወደር የለለው አክብሮትና ምስጋና እንዳለኝ ነው። ዘላለማዊ ክብር ይገባቸዋል!

 

ሆኖም ግን ህወሓት ሚዛናዊ፣ ፍትሃዊ፣ ሰብዓዊና ተሸጋጋሪ የሆነ የመንግስት ስርዓት የመፍጠር አቅም የሌለው ድርጅት እንደሆነ ባለፉት 21 ዓመታት በግልፅ ታይቷል። በድርጅቱ ታጋዮች የተከፈለው የህይወት፣ የአካል፣ የቁሳቁስ፣ የእድሜ እና የስነልቦና መስዋዕትነት አሁን ያለውን ድርጅት እውርና ደንቆሮ ያደረጉት ይመስለኛል። በተለይ ደግሞ የ”አናሳ ትግሬ መንግስት” የሚል አደገኛ የሆነ የጥላቻና የበቀል ስሜት በሌሎች ኢትዮጵያውያን ውስጥ እንዲጸነስ፤ የትግራይ ህዝብ በደርግ አስተዳደር የደረሰበት ስቃይ አይበቃ ይመስል አሁን ከህወሓት የተነሳ እንደ ባዕድና ጥገኛ-ህዋስ ተደርጎ እንዲታይ የህወሓት የባለቤትነትና የይገባኛል ስሜት የፈጠራቸው በጣም አሳሳቢ ጉዳዩች ናቸው።

 

የመስዋዕትነት ወጥመድ ውስጥ የገባው ህወሓት የራሱን ህልውና መጠበቅ የሚያስችለው ነገር ቢኖር ትዕቢት ድንፋታና እብሪት ሳይሆን የሰከነ ከባለቤትነትና ከይገባኛል አሉታዊ ስሜት ተጽዕኖ ነጻ የሆነ፣ የበሰለ መፍትሄ ለአገራችን የፓለቲካ ቀውስ መፍጠር ሲችል ብቻ ነው። ለአገራችን ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት፣ ሚዛናዊ፣ ፍትሃዊ፣ ሰብዓዊና ተሸጋጋሪ የሆነ የመንግስት ስርዓት ለማምጣት የሚያስችለን ሌላ ድርጅት ደምቶ፣ ቆስሎና ሞቶ ስልጣን ሲይዝ አይደለም። በትጥቅ ትግሉ ውስጥ ያ-ል-ተሳተፉ የህወሓት አባላት ከመስዋዕትነት ወጥመድ ራሳቸውን የማዳን አቅማቸው የላቀ ስለሆነ በድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የማድረግ ሃላፊነታቸው ከመቸውም ጊዜ በላይ ዛሬ የላቀ ነው። ህወሓቶች ሆይ! ራሳችሁን ከገባችሁበት ወጥመድ ካላዳናችሁ፣ አቶ መለስ ዜናዊ አንድ ጊዜ ፓርላማ ውስጥ ተበሳጭተው እንዳሉት፣ “ፈረንጅ አያድናችሁም፣ አበሻ አያድናችሁም!”

 

ክብር ለሰማዕታት!


ያሬድ አይቼህ

 

ጁላይ 18, 2012 (እኤአ)

ፀሐፊውን ለማግኘት በዚህ ይጻፉ፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!