ነጻነት ዘገዬ

በሰሞነኛ ሀገራዊ የፖለቲካ ትኩሳትና ያን ተከትሎ ሊከሰት ይችላል ብዬ በጉጉት በምጠብቀው የማይቀር የለውጥ ማዕበል ምክንያት ስሜን የምቀይርበት ዘመን እየባተ እንደሆነ ይሰማኛል። ”ነጻነት ዘገዬ” በሚለው ስሜ የዘለቅሁበት የዓመታት ብሶትም አንገሽግሾኛል። ሲያላዝን የሚኖር ውሻ ብቻ ነው፤ እኔ ደግሞ ሰው ነኝና ከእንግዲህ የማዘንና የመከራ ዘመኔ ወደ ታሪክነት መለወጥ ይገባዋል። እናም ”ወርቁ ሞላ” ወደሚል አዲስ የብዕር ስም እንድሻገር በሀገርም በውጪም ያላችሁ ወገኖች ለጋራ የተሻለ ኅልውና ተረባረቡ።

 

ጥሩ ዜና ነው። አቶ መለስ ማረፉ ጥሩ ነው። ሰው ሲደክመው ማረፉ ያለና የነበረም ነው። በተለይ አቶ መለስ የማያዳግም ታላቅ ዕረፍት ያስፈልገው ነበር፤ ብዙ ደክሟል፤ አልሳካ ብሎት እንጂ የሚወዳት ብቸኛ ሀገሩን ኢትዮጵያንና የሚወደንን ኢትዮጵያውያንን በቀን ሦስት ጊዜ ከማብላት ጀምሮ የጠፈር ቱሪስቶች እንድንሆንለት ለማስቻል ብዙ ጥሯል። በዚህ መልኩ እንዲያርፍም ብዙዎቻችን ላለፉት በርካታ ዓመታት ስንጸልይለት ቆይተናል። ይሄውና ጸሎታችን ሠምሮ ዐረፈ መባልን መስማት ከጀመርን አምስተኛ ቀናችን ሆነ። እግዜር እንዴት ተብሎ ነው የሚመረቅ? ብቻ ስሙ የተባረከ ይሁን። ከተመስገን ሌላ ምን ይባላል? ለዘላለሙ የተመሰገነ ይሁን።

 

አንድ የደስታ አጋጣሚ ሌላ የሀዘን አጋጣሚ ሊፈጥር እንደሚችል መረዳት ግን ይህችን ወርቃማ ጊዜና ዕድል በከንቱ እንዳናባክናት ልብ እንድንል ያደርገናል። በመሠረቱ በሊቀ ሣጥናኤል አቶ መለስ ዜና ዕረፍት ብዙም መደሰት ተገቢ አይመስለኝም። ማረፉ የሚያስከትለውን ሀገራዊ በረከት በማጤን ከጉዳቱ ጥቅሙ ይበልጣል ብለን እንጽናና እና ዜና ዕረፍቱን በደስታ እንቀበል እንደሆን እንጂ በሰው ሞት መደሰት ሞራላዊም ሆነ ሃይማኖታዊ አይደለም። ፈጣሪ አዘዘው፤ የታዘዘውን ፈጸመ፤ ና ሲለው ሄደ። የመለስ ጥፋት የመላላክ እንጂ የራሱ አይመስለኝም። ”እግዜር ሲቆጣ ሽመል አይቆርጥም ያደርጋል እንጂ ነገር እንዳይጥም” እንላለን። ጥፋት አለብን። ጥፋቱ አሁንም ድረስ አለብን። ከጥፋት እንመለስ። ያኔ ከጫፍ የጀመረው አብዮት እስከታች ይወርዳል። ሳናስበው ከላይ የወረደ ቡራኬ እያየን ነው፤ ይጨርሰው። (በነገራችን ላይ የወያኔ አሻንጉሊት ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሴትዮ ለምን ጥቁር ልብስ ለበሰች? ገና በይፋ ሳይታወጅ? አዜብስ ለምን የጠቋቆረ ልብስ ለበሰች? ለምንስ የአንገት ሐብሏን አወለቀች? አለወትሮው አንገቷ ለምን ባዶ ሆነ? አንደበት ቢለጎም ድርጊትና ስሜት ያሳብቃሉ!)

 

ፈረንጆች surgical operation የሚሉት ንዑስ ሐረግ አላቸው። በሁለት መንገድ ይጠቀሙበታል - በሕክምናውና በወታደራዊው ዘርፎች። የሕክምናውን ሁሉም ያውቀዋል። በወታደራዊው ዘርፍ ሰርጂካል ኦፐሬሽን ሲሉ ልክ እስራኤል እንደምታደርገው አንድን ሞት የሚገባውን ሰው ወይም መውደም አለበት የተባለን ዒላማ በልዩ ሥልት በአካባቢው የሚገኝ ሌላ ሰውና ነገር ሳይጎዳ ለይቶና አነጣጥሮ በማጥቃት ዓላማን ማሳካት ማለት ነው። ይህ ዓይነቱ የማጥቃት ሥልት ከብዙ ወታደራዊ ኪሣራና ወጭ ይታደጋል። ትልቅ አደጋንም ይሠውራል።

 

በኢትዮጵያ እግዚአብሔር ይሁን ወይም ገና ወደፊት የሚታወቅ ሥውር ኃይል - ልዩ ቴክኖሎጂም በመጠቀም - (መጠርጠር ነው) ባደረገው ሰርጂካል ኦፐሬሽን ይህ መፃጉዕ ሰውዬ የማይቀር ዓለማዊ ሒሳቡን አግኝቷል፤ የነፍሱን እዚያው ያወራርድ። ባልተጠበቀው ሁኔታ የተወነባበዱት ወያኔዎች ቤታቸውን እስኪያስተካክሉና የተዝረከረከውን ነገር ሁሉ እስኪያጸዳዱ ቢደብቁትም እውነቱ እውነት መሆኑን ከጥርጣሬ በላይ እየተረዳን መጥተናል፤ መቼም ዱብ ዕዳ ነው የሆነባቸው፤ የሆነብንም። ከእንግዲህ የመለስ ፀሐይ ጠልቃለች፤ ከእንግዲህ እኛም ካወቅንበት የወያኔ ፀሐይ ባጠቃላይ ጠልቃለች። የኛ ፀሐይ እንድትወጣ ግን ገና ብዙ ልፋት ይጠብቀናል፤ የነጻነት ጎሕ አሁን ነው መቅደድ የጀመረው። በመጀመሪያ በተበጣጠቀ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው የተቃዋሚ ጎራ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ማዕከል መሰባሰብና በአፋጣኝ መነጋገር ብቻ ሳይሆን ወደ ተግባራዊ እርምጃ መግባት ያስፈልገዋል፤ ይህች ዕድል የጋለች ብረት እንደማለት ነች። ካልተጠቀሙባት ብረቱ እንደገና ይጠጥርና ለመቼውም ሊያስቸግር ይችላል። የተቃዋሚው ጎራ እንደ እስካሁኑ ገና ባልተገኘ ሥልጣን የሚቆራቆስና የሚሻኮት ከሆነ ይህችም ዕድል እንደስካሁኖቹ ታመልጣለች። ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ።

 

እኔ በበኩሌ እንደሚከተለው እራገማለሁ፤

ከእንግዲህም ሆነ አሁን በዘርና በጎሣ እንዲሁም በሃይማኖት የሚደራጅ ጥቁር ውሻ ይውለድ፤ ዘር አይውጣለት። ከእንግዲህም ሆነ አሁን የሕዝብን ስቃይ ለግል ጥቅሙና ለሥልጣን ፍላጎቱ ማርኪያ የሚያውል ጥቁር ውሻ ይውለድ፤ ዘር አይውጣለት። ከእንግዲህ ከሕዝብ ሰቆቃና ችግር በፊት የራሱን የሥልጣን ሱስና የሀብት ማከማቸት ቁሣዊ አራራ የሚያስቀድም ዜጋ ጥቁር ውሻ ይውለድ፤ ዘር አይውጣለት። ከእንግዲህ ወደ ጤናማ አስተሳሰቡ ተመልሶ ይህን በቁሙ የሞተ ሕዝብ ለማዳን የማይሠራ ዜጋ፣ ይህችን በውርደት መንገድ እየነጎደች ያለች ሀገር ለማንሳት የማይተጋ ዜጋ ጥቁር ውሻ ይውለድ፤ ዘር አይውጣለት። ከእንግዲህና አሁን በንግድ ሰበብ ሕዝቡን እስከመቅኒው ድረስ የሚግጥ ዜጋ ጥቁር ውሻ ይውለድ …። ከአሁን በኋላ አንተ ትግሬ አንቺ አማራ አንተ ኦሮሞ እሱ ጉራጌ እነሱ ከምባታ … በሚል የዘረኝነት ወያኔያዊ ልክፍት ተጠምዶ ወገንን ከወገን የሚለይ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጥቁር ውሻ ይውለድ። ከአሁን በኋላ የተቀበረን እየቆፈረ ባለፈ በደልና ጥፋት ቋሚን የሚወቅስ ሰው ጥቁር ውሻ ይውለድ። ከአሁን በኋላ ከኢትዮጵያዊነት የጋራ መገለጫ በፊት በነገዱና በጎሣው ወይም በሃይማኖቱና በቋንቋው ሰውን እየለዬና እያንጓለለ ሥራ የሚቀጥር ወይ የሚያስቀጥር፣ ከ‘meritocracy’ ይልቅ ማንኛውንም ዓይነት ያልተገባ ‘discrimination’ የሚያራምድ ጥቁር ውሻ ይውለድ፣ ዘር አይውጣለት። ይህን እርግማን እግዚአብሔር እንዲቀበለው የምትደግፉኝ ጸልዩ።

 

በኢትዮሚዲያ ድረ ገፅ ከቀረበ አንድ የእንግሊዝኛ ዘገባ የተረዳሁት አሳሳቢ ችግር አለብን። ይሄውም የመለስን ማረፍ ተከትሎ ሊከሰት ስለሚችል ሁኔታ ነው። የመለስ ማረፍ ብቻውን ሊያዘናጋን እንደማይገባውና እንደማይችልም በዚህ ዘገባ ተገንዝቤያለሁ። የነብር ዐይን ወደ ፍየል የፍየል ዐይን ወደ ቅጠል ይባላል። እኛ በመለስ ሞትና በሀገር መገላገል ላይ ስናተኩር የሀገሪቱ ታሪካዊና ጥቅማዊ ጠላቶች ምን እየሠሩ እንደሆነ መገመት እንዳያቅተን መጠንቀቅ ይኖርብናል። እርግጥ ነው መለስ ትልቁ ሞጄሌ ነበር፤ ትልቅ ሞጄሌ ከነሰንኮፉ እንደተገላገልን ልንቆጥር እንችላለን፤ ግን ብዙ ሞጄሌዎች ከነሰንኮፋቸው አሉ። በአምባገነናዊ ሥርዓቶች ዋናው ቁንጮ ሲገረሰስ እንደተናጋሪ ዕቃ የሚቆጠሩት በሥሩ ያሉት ተከታዮች የሚገቡበት እንደሚያጡና እንደሚደነጋገጡ ግልጽ ነው። ከኛው ታሪክ ብናይ አፄው ሲወርዱ ሁሉም ነገር ተንኮታኮተ፤ መንግሥቱ ሲወርድ ሁሉም ነገር ተንኮታኮተ፣ አሁንም መለስ ሲሞት - ስብሃት ለአፉ ያህል ምንም ችግር እንደማይኖር እንደወያኔያዊ የመወሻከት ልማዱ ይዘላብድ እንጂ - ሁሉም ነገር ይንኮታኮታል። እመኑኝ ተቃዋሚም ባይኖር (ካለንም እሰዬው ነው) እርስ በርሳቸው ይባላሉ፤ በዚያም ሳቢያ ውስጣዊ አብዮት ይፈነዳል፤ በዚያውም ”በንነው ይጠፋሉ” የተባለው ትንቢት እውን ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። በመጥፎ ምግባር የበሸቀጡ፣ በሃይማኖት የበከቱ፣ ከባህልና ወጋችን ያፈነገጡ፣ … በመሆናቸው ቀሪዎቹ ወያኔዎች ከእንግዲህ የሚያገግሙበት ሁኔታ ጨርሶውን የለም - አሁንም ልድገመው ተቃዋሚ እንኳን ባይኖር። የማይምር በትር ታዞባቸዋል ባይ ነኝ።

 

ፈጣሪ ፍጡሩን ጥሎ አይጥልም። ተቃዋሚዎች ለራሳችሁ ስትሉ ተባበሩና ይህን ዕድል ተጠቀሙ። የሩቅ ተኩስ ያንጀትን አያደርስም። ከአሥራ ምናምን ሺህ ማይሎች ርቀት ላይ በሚተኮሱ ስሜታዊ ቃላትና የአቋም መግለጫዎች እንዲሁም ጋዜጣዊ ሀተታዎች የጠላትን የተደበቀ ገመና ማጋለጥ ይቻል ይሆናል እንጂ ዝምቡን እሺ ማለትና የጭረት ያህልም ብትሆን ማቁሰል አይቻልም። አሁን ያለን የጠላት መንጋ ደግሞ ለቋንቋ ደንታ የለውም፤ ስትሳደብ ውለህ ብታድር፤ በሥነ ጽሑፍ ርቃቆትህ እንደነ ሼክስፒርና ሎሬት ጸጋዬ ስትቀኝ ውለህ ብታድር በልፋትህ ይስቅብሃል እንጂ ጉዳዩ አይደለም። ነገሩ የመጻፍ ሳይሆን የመተኮስና ዒላማን የመምታት ነው። በሀሰትና በዕብለት ተጠንስሶ ያደገና ለአካለ መጠን የደረሰ ወያኔያዊ ውድብ(ድርጅት) በስድብና በዘለፋ እንደጢስ በንኖ ይጠፋል ማለት ቀልድ ነው። አየነው። በጩኸት ብዛት ወያኔ አንድ ኢንች እንኳን ወደኋሊት መሄድ ቢችል ኖሮ ባለፉት 21 ዓመታት ውስጥ እኔ ብቻየን በጮኽሁት ብቻ ቀይ ባሕርን አልፎ ሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ በገባ ነበር። የማይሆን አይሆንም፤ አንልፋ። ወደተግባር እንግባ። ወደተግባር የሚያስገባን ኃይል ይኑር፤ ጩኸታችን በቲዮሪ ብቻ ሳይሆን በተግባር ይደገፍ። ጉዳዩ ቀድሞ መገኘት ነው እንጂ በርግማንና በስድብ የሚጠፋ ጠላት የለም። ስድብና ነቀፋ የአምባገነኖች የደንብ ልብስ ነው። የሚገርማቸው ይልቁንስ ስለነሱ መልካም ነገር ቢነገርላቸው ነው።

 

ወደኢትዮሚዲያ ሥጋት ልመልሳችሁ። አሁንና ከ93 ዓ.ም. ወዲህ ህወሓትን እየመሩ ያሉት እውነተኞቹ የትግራይ ተወላጆች ሳይሆኑ ኤርትራውያን ናቸው። በመሠረቱ በበኩሌ የየትኛውም ክልል ተወላጅ ቢሆኑ ሃሳቡ አይበላኝም። ከኬንያ ሄዶ አሜሪካንን እያስተዳደረ የሚገኘው የዓለማችን ዜጋ የተወሰኑ የጥራት መሥፈርቶችን በማለፉ እንጂ እንደኤርትራውያኑ ሠርጎ ገቦች በሕግ አልባነት የጫካ ሕግ እየተመራ አይደለም። እነዚህኞቹ ግን በአንጻራዊ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ደግ የሚያስቡትን የትግራይ ትግሬዎች በቂምና በበቀል መንጥረው በማባረር ሁሉንም በእነሱ ቁጥጥር አድርገዋል። ይህ አደገኛ አካሄድ ግዘፍ እየነሳ ሄዶ በአሁኑ ወቅት አጠቃላዩ የሀገራችን ሕልውና በኤርትራውያኑ መዳፍ ሥር ያለ ይመስላል። ይህ የፈጠጠ እውነት አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ላይ ተገሽሮ እየተንጎማለለ እኛና ተቃዋሚዎች በመለስ ሞትና በማያስማሙን ጉዳዮች ዙሪያ ብቻ መተብተባችን ደግ አይደለም ብቻ ሳይሆን አንዳች ነገር የተዞረብን ነው የምንመስለው። እንደገና የመፈጠር ያህል ልንለውጥ ይገባናል። እነ ንዋይ ገ/አብ፣ ሳሞራ የኑስ፣ ብርሃኔ ገ/ክርስቶስ፣ በረከት ስምዖን … ሁሉም በአሁኑ ወቅት ያሉት የወያኔ ባለሥልጣናት ኤርትራውያን መሆናቸው የአጋጣሚ ነገር ሳይሆን መለስ ቀደም ካለ ጊዜ ጀምሮ ለሚያደላላት የቀድሞ ክፍለ ሀገራችን ኤርትራ ያለውን አድልዖና አመኔታ እንዲሁም የመሀል ሀገሩን ሰው (የትግራይን ትግሬ ጭምር) ምን ያህል እንዳንጓለለን ያመለክታል። የመለስ ማረፍ የምዕራፍ አንድ መዝጊያ ነው፤ ከባዱና ምዕራፍ ሁለት መቀጠል አለበት። እነዚህን በመለስ ጥላ ሥር መሽገው የነበሩ ውሉደ አጋንንት መመንጠር የሚቻለው ልዩ ሥልት በመንደፍ ነውና ይህ ነገር ይዋል ደር የሚባል አይደለም። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በተቃዋሚው ጎራ ታውጆ የ24 ሰዓት ሥራ መሠራት አለበት። ኋላ እንዳይቆጨን!

 

አሁን ለወሬ ብዙ ጊዜ ልንሰዋ አያስፈልግም። ስንፈራው የነበረውን ጦርነት ግማሹን ያህል እግዜር ወይም ያላወቅነው ሌላ ኃይል ተዋግቶልናል። የሚቀረው ድሉን መሰብሰብ ብቻ ነው። ድሉን መሰብሰብ የምንችለው ደግሞ እንደእስከዛሬው በወሬና ዛሬ ተገንብቶ ነገ በሚፈርስ ጉባኤና ስብስብ ምሥረታ በመጠመድ ሳይሆን በተግባራዊ እንቅስቃሴ ነው። ሲያጎርሱት የማያላምጥ የሞተ ብቻ ነው። ልዩ ኃይል ልዩ ጉርሻ አጉርሶናልና እንጠቀምበት። ሦርያውያን ይህን መሰል ዕድል ቢያገኙ ምንኛ በታደሉ?

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!