ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም Mengistu HaileMariamአቶ መለስ ዜናዊ Meles Zenawiበሕግ አምላክ (ከስዊድን)

ሰው ሆኖ መኖር፣ ኖሮ - ኖሮ መሞት አይቀርም። ቢሆንም ገና በህይወት ያለ ሰውን ቢሞት ኖሮስ ብሎ የቀብር ስነሥርዓቱን መግለጽ በባህላችን አልተለመደም። ስለዚህም በርዕስ ምርጫዬ ኮሎኔል መንግሥቱ ቤተሰቦቻውም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው እንደማይቀየሙኝ ተስፋ አደርጋለሁ። በርካታ ሰዎች በምስል አቅርቦትና በድምፅ ቀርፃ ያዩትንና የሰሙትን አስመልክቶ የአቶ መለስ ዜናዊ የቀብር ስነሥርዓት እፁብ ድንቅና ወደርየለሽ ነው ይላሉ። እኔ ግን ወደርየለሽ የሚለውን አባባል አልጋራቸውም። ምክንያቱም ...

 

ምክንያቱም የአቶ መለስ የቀብር አሸኛኘትና አፈጻጸም ወደር የማይገኝለት ነው ሊባል የሚችለው ከየትኛው መሪ የቀብር ስነሥርዓት ጋር ተወዳድሮ ነው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ አባባሉን ኢተዓማኒ ያደርገዋልና። ለዚህም ነው የሞቱት ኮሎኔል መንግሥቱ ቢሆኑ ኖሮስ ምን ዓይነት ትዕይንተ ሕዝብ ይታይ ነበር? የሚለውን ግምታዊ አስተሳሰብ በዓይነ ህሊና ለማሳየት የምሞክረው።

 

በቅድሚያ ግን የአቶ መለስ ዜናዊ እልፈተ ህይወትን ምክንያት በማድረግ ወያኔ (ኢህአዲግ) ለዓለም ሕዝብ ሊያሳይ የፈለገው ትዕይንተ ሕዝብ አሁንም የሕዝብ ንቀትን አመላካች ክንውን መሆኑን ማስመር እፈልጋለሁ። ህወሓትና አጫፋሪዎቹ አባቱን በድንገት እንዳጣ ህጻን ልጅ ”አባቴ! አባቴ!” ብለው እያለቀሱ የሸኙትን ያህል በውስጣዊ ሳቅ የተሰናበቱትም ያንኑ ያህል በርካቶች ናቸው። በለቅሶም በሳቅም ያልኩበት ምክንያት አለኝ። ሁሉንም ነገር አንተ እንዳልክ፣ ካንተ ወዲያ ለኢትዮጵያ፣ ካንተ ወዲያ ለእኩልነትና ለነፃነት ተሟጋች፣ የለም እያሉ በጨለምተኝነት ”አምላኪ መለስ” የነበሩት ቀቢፀ ተስፈኞች አዎ በእጅጉ አዝነዋል። እናም ከልብ አልቅሰው ተሰናብተዋል።

 

አንድነት፣ እኩልነት፣ ነፃ ምርጫ፣ ... ወዘተ የሚባለውን ስንክሳር ተዉትና በማናቸውም ሲስተም ገብታችሁ መዝረፍ ትችላላችሁ ተብለው አንድ ሺህ ብር ቆጥረው የማያውቁት ቢልዮን ብር በባንክ፣ ሚልዮን የኪስ ገንዘብ የያዙት አግበስባሾችም በእጅጉ አዝነዋል፣ እናም በደንብና በሥርዓት አልቅሰዋል። እነዚህኞቹ ዕንባ አይደለም ቢቻል ደምም ቢያለቅሱ አይወጣላቸውም። ስለዚህም ምርር፣ ስቅስቅ ብለው አልቅሰዋል። ከትግሬ መወለድ ልዩ ፍጥረትና ልዩ ክብር እንዳለው በአደባባይ ላይ በትዕቢትና በትምክኽተኛነት በመነገሩ የትናንቱን ኑሯቸውን ምንም ባይለውጠውም በትግሬነታቸው ብቻ ዘራፍ ሲሉ የነበሩትም ከሌሎች እኩል አልቅሰው ቀብረዋል። እነዚህኞቹ ደግሞ ምንም አላገኙ፤ ምንም አላጡ፣ ነገር ግን መለስ በመሞታቸው ሁሉም ጣቱን የሚቀስርባቸው እየመሰላቸው በሥነልቡና ፍርሃት ተሸማቀው በዕንባ ሲራጩ ተስተውለዋል። በአንፃሩም መሬቱ ይቅለላቸውና አቶ መለስ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሀገራዊ ጥቅም ይልቅ ግማሽ ልባቸው ወደ ኤርትራ፣ ግማሽ ልባቸው ወደ ትግራይ፣ የሥልጣን ልባቸው ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ተከፋፍሎ ሚዛናዊ ዳኝነታቸው ተዛብቶባቸዋል። ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያዊነት ደብዛን ለማጥፋት በፈፀሙት ብሔራዊ ስህተቶች አንጀቱ ሲቃጠል የነበረው፤ ነገር ግን ውጣና ቅበር የተባለው ህዝብም በእውን እያለቀሰ ከማለት በውስጡ እየሳቀ ሸኛቸው ቢባል ከእውነታው የራቀ አይሆንም። ምክንያቱም ሰው እንዲያለቅስም እንዲስቅም የሚያነሳሳው ኑሮው ነውና።

 

በሌላ መልኩ የአቶ መለስ ተለዋዋጭ ባህሪም ከአንድ መንግሥትና ፓርቲ መሪነት ወደ ሁለንተናነት እየተለወጠ በመምጣቱ ሁሉንም ነገር እርሳቸውና እርሳቸው ብቻ የሚያቅዱና የሚወስኑ በመሆናቸው ከአመራር ውጪ ሆኖ በጀሌነት አብሯቸው የነበረው ባለሥልጣን ሳይቀር ላይ ላዩን በጥቁር ልብስ ተዠብኖ ቢታይም ውስጡ ግን ”አብዝቶት ነበር ይበቃዋል!” በሚል በአዲስ ተስፋ ተሰናብቷቸዋል። ወጣም ወረደ አቶ መለስ ዜናዊ አስከሬናቸው ከቤተ መንግሥት በክብር ወጥቶ በሕዝባዊ አጀብ የተቀበሩ የዘመናችን መሪ በመሆናቸው በዚህ ዕድለኛ ናቸው። በዚህ ምክንያትም ቀብራቸው ዕፁብ ድንቅ በሚባል ታላቅ ትዕይንተ ሕዝብ ተፈጽሟል። ነገር ግን የርሳቸውን ሥርዓተ ቀብር ወደር የማይገኝለት ለማለት ለሌላ መሪ የተደረገውን ወይንም ሊደረግ የሚችለውን ሥርዓት መቃኘት ንፅፅሩን ሚዛናዊ ያደርገዋል። ለዚህም ነው የሞቱት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ቢሆኑስ ኖሮ? ያልኩት። ለመሆኑ እኒህ ሰው በበትረ ሥልጣናቸው ላይ እያሉ ቢሞቱ ኖሮ ደርግ (ኢሠፓ) ምን ምን በማለት አጅቦና አዝኖ ቀብራቸውን ያስፈጽም ነበር?

 

”ውድ ጓድ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣

የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ፣

የኢህዲሪ ፕሬዘዳንትና የአብዮታዊ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣

 • • ሲወርድ ሲዋረድ የቆየውን የኢትዮጵያን አንድነትና ዳር ድንበር አስከብሮ ለማቆየት በየማዕዘኑ ከተነሱ ጠላቶች ጋር የተደረገውን ፍልሚያ የመሩ የጦር መሪያችን፣
 • • በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲፈጠሩና ህዝቡ እንዲነቃ፣ እንዲደራጅና እንዲታጠቅ ያስቻሉ አሻግሮ ተመልካች፣
 • በገባርና በጢሰኛ መካከል ተንሰራፍቶ የነበረውን ኋላ ቀር ግንኙነት በጥሰው መሬት ለአራሹ ያደረጉ የድሃው ገበሬ አባት፣
 • የሶማሊያ ተስፋፊ ጦርነትን “እናት ሀገርህ ተደፍራለች! ተነስ፣ ታጠቅ፣ ዝመት፣ ...” በሚል ብሔራዊ ጥሪ ሕዝባዊ ሠራዊትና መደበኛ ጦር በማዝመት ድል መትተው የሀገር ክብርና ዳር ድንበርን ያስከበሩ የጦር አዝማችና መሪያችን፣
 • የውበት ፈርጣችን የሆኑትና በአንድነትና በፍቅር ተሳስረው የሚኖሩ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች እንዲታወቁ፣ እንዲጠኑና መብታቸውም እንዲከበር የሚያስችል የብሔረሰቦች ኢንስቲትዩትን ያቋቋሙ የእኩልነት በር ከፋች፣
 • በሕዝብ የመኖሪያ አቅራቢያዎች የመሠረታዊ ሸቀጦች ማከፋፈያንና የፍትሕ አካላትን (ፍርድ ሸንጎ) አቋቁመው የነጋዴ ብዝበዛንና የፍርድ ቤት ውጣውረድን ያስቆሙ ተቆርቋሪ ዜጋ፣
 • መኃይምነትን በማጥፋት ዘመቻ ዓለም አቀፍ አድናቆትን ያተረፉ አስተማሪያችን፣
 • ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን፣ የመገናኛ አውታሮችንና አስተዳደራዊ ልማቶችን በሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት በአቻነት ያስፋፉ የልማት መሐንዲሳችን፣
 • የኢትዮጵያን ታሪካዊና ዙርያ ክብ ጠላቶች ለመመከት የሚያስችልና ምዕራባውያንን በከፍተኛ ስጋት ላይ የጣለ የመከላከያ ኃይል የገነቡ የዘመናችን አፄ ቴዎድሮስ፣ … ወዘተ … ወዘተ …"

 

እየተባለ አሁን አቶ መለስን ለመሰናበትና ለመቅበር በደብዳቤ ጋጋታ ከወጣው የስም እዝንተኛ በእጅጉ የላቀ ትዕይንተ ሕዝብ በታየ ነበር። ለዚህ ነው ወደር የማይገኝለት የቀበር ስነሥርዓት ለማለት ከማን ጋር ተነፃፅሮ በማለት የጠየቅሁት።

 

አቶ መለስ ዜናዊ እንደማናቸውም ሰው በአንድ የታሪክ አጋጣሚ የሀገር መሪነት ሥልጣን ጨብጠዋል። እንደማንኛውም መሪም ጠንካራና ደካማ ጎኖች ታይተውባቸዋል። በመሪነት ዘመናቸው አፍላ ምዕራፍ ላይ በመደራጀት መብት፣ በነፃ ፕሬስ፣ በነፃ መሰብሰብና በመሳሰሉት በተለይም በ1997 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 2005) ቅድመ ምርጫ ወቅት ተስፋ ሰጭና በጎ ጅምሮች ቢታዩም ውለው አድረው ብሔራዊ ኃላፊነት በጎደለው ትዕቢት የፈፀሟቸው የታሪክ ጠባሳዎች እጅግ በርካቶች ናቸው። እናም እንደዚህ ማለት ይቻላል፣

 

አቶ መለስ ዜናዊ፣

የኢፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣

የኢህዲግ ሊቀመንበርና የጦሩ የበላይ አዛዥ፣

 • የቆየውን የኢትዮጵያውያን አብሮነትና ብሔራዊ ስሜት በጎሣ ፖለቲካ ተክተው በተጋድሎ አንድነቷ ተጠብቆ የቆየችው ሀገር እንድትበጣጠስና ለእርስ በርስ ጦርነትም እንድትመቻች፣ የመከፋፈልና የመፈራረስ የመሰረት ድንጋይ የሆነውን ሕገ መንግሥት አውጥተው ያፀደቁ ናቸው።
 • የኢትዮጵያን የባህር ወደብ ለሻዕቢያ እጅ መንሻ ከመስጠት አልፎ መጠነ ሰፊ የሀገሪቱ አካል ተቆርሶ ለኤርትራ እንዲሰጥ በጥፋት የስምምነት ፊርማቸው ያጸደቁ መሪ ናቸው።
 • በህይወት መስዋዕትነት ተከብሮ የቆየውን የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ለሱዳን ምንደኞች በመስጠት የክልሉን ገብሬ ያፈናቀሉና ብሔራዊ ክብር ያሳጡ ግድየለሽ ናቸው።
 • ትጥቅ አልባ ተቃዋሚ ሠልፈኞችን በቅልብ ጦራቸው ያስረሸኑና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ተለጣፊ ስም በመስጠት በእስር እንዲሰቃዩ አመራር የሰጡ የሰብዓዊ መብት ረጋጭ አምባገነን ናቸው።
 • ዛሬ በሚታየው የሰለጠነ ፖለቲካ ሥርዓት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸውን አማራጭ ለህዝብ አቅርቦ በማስወሰን ፈንታ የተቃዋሚዎችን ጽ/ቤት በመዝጋት፣ መሪዎችን በመግደልና በማሰር የሕዝብ ድምጽን በገሀድ በመዝረፍ ሥልጣንን በብቸኝነት ይዘው ዲሞክራሲን ያፈኑ የስም መሪ ናቸው።
 • ለውጤት የማይነሳሳ ትውልድ እንዲፈጠር የሚያደርግ የትምህርት ፖሊሲ በማውጣትና የሥራ ዕድል ባለመፍጠር ተስፋ የቆረጠና ችግር መፍታት የማይችል ትውልድ እንዲበራከት ያደረጉ ምሁር አምካኝ መሪ ናቸው።
 • ለዘመናት የብዙኀን ተቆርቋሪ ዜጎች ጥያቄ የነበረው የመሬት ላራሹ ጥያቄ ተቀልብሶ የገጠር መሬት ለህወሓት/ኢህአዲግ የፖለቲካ መሣሪያነት እንዲውል ለማድረግ በመንግሥት ቁጥጥር ስር አውለው ገበሬውን ማዕከል አድርገናል በሚሉት ፍልስፍና የኢትዮጵያ ገበሬን የመሬት ባለቤትነት ያሳጡና ኑሮውን እያፈናቀሉ ለድንበር ዘለል ከበርቴዎች የሸጡት ናቸው።
 • በኦሮሞ፣ በኦጋዴን፣ በጋምቤላና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች በተወርዋሪ ጦራቸው በአንድ ብሔረሰብ አባላት ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ያካሄዱና በዘር ማጥፋት ወንጀል መጠየቅ የነበረባቸው ወንጀለኛ ናቸው።

 

አቶ መለስ ዜናዊ እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ እጅግ በርካታ ብሔራዊ ጥፋቶች ፈጽመው አልፈዋል። መሬት ይቅለላቸው እንጂ በፌደራልና በክልል ሥልጣን ስም፣ በዲሞክራሲና በነፃ ምርጫ ስም፣ በነፃ ፕሬስና በብዙኀን ፓርቲ ስም በአጠቃላይ በማይተገበር ሕገ መንግሥት ስም ጥቂቶች ብዙኀኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ በዘር ከፋፍለው ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን አፍነው የዲሞክራሲያዊ ግንባታውን ቀልብሰውታል።

 

አገራዊ - አገራዊ፣ ብሔራዊ - ብሔራዊ የሚሸተው የአብሮነት መዓዛ ተበርዞና ጠፍቶ ክልላዊ - ክልላዊ እንዲሸትና በአንድ ሀገር ሕዝቦች መካከል የነበረውን የአብሮነት ታሪክና ባህል በጎሣ ፖለቲካ መርዘውታል።

 

አቶ መለስ ዜናዊ ታላቅ ክብርና ሞገስ ያለው የኢትዮጵያዊነት ካባ አልሻም ብለው በትግሬነት ሰደርያቸው የተመፃደቁና ራሳቸውን ከብሔራዊ ክብር ወደ መንደር ያወረዱ፣ ቂም በቀል ከደም ሥራቸው ጋር የተሳሰረ፣ ጥላቻ፣ ፍርሃትና ተጠራጣሪነት ተደራርበው ዕረፍት ስላሳጧቸው ለዕልፈት በቅተዋል።

 

የሞተን አልቅሶ ወይም ሸኝቶ መቅበር ቀጣይ ነባራዊ ክንውን ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከማንም በላቀ ምንም ያስከፋንና የበደለን ቢሆንም ሰው ከሞተ በኋላ ክብር እንሰጠዋለን። ይህም በጎ ባህል ነው!

 

የአቶ መለስ ዜናዊ የቀብር ፋይዳም ይኸው የባህል ጉዳይ ነው። በዚህ ላይ ይፋዊ የሆነ የውጡና ቅበሩ ትዕዛዝም በነቂስ ተሰራጭቷል። ሰው ናቸው ኖረዋል፣ ሰው ናቸው ሞተዋል፣ ሰው ናቸው ሲሞቱ ተቀብረዋል፣ ሌላ ታሪክ የላቸውም። ታሪክን የሚሠራ ሕዝብ እንጂ ግለሰቦች አይደሉም። እናም የወደቀው የሀገራችንና የአንድነታችንን ታሪክ ለማቅናትና መልሶ ለመገንባት ተቃዋሚውም ሆነ ገዥው ፓርቲ በአብሮነት በጋራ ለመሥራት ግዜው የግድ ይላል።


በሕግ አምላክ (ከስዊድን)

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!