ይኸነው አንተሁነኝ

የወያኔ ፓርላማ ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ ራሱ ያጸደቀውን የይስሙላ ሕገ-መንግሥት በመጣስ ሁለት ተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሮችንና የውጭ ጉዳይ ሚንስትርን ጨምሮ ሌሎች ጥቂት ሚንስትሮችን በመሾም ቀሪው ባለበት እንደሚረግጥ ከኃይለማሪያም ደሳለኝ የቀረበለትን ተቀብሎ አጽድቋል።

 

 

ይህን የህወሓቶች ጊዜ የወሰደ፣ ጥንቃቄ የተሞላበትና የተጠና ሹመት በተመለከተ ገና ያኔ የዘረኛው መለስ ዜናዊ ግብኣተ መሬት ይቅርና በወያኔዎችና የቅርብ ዘመዶች በሚስጥር የተያዘው ገሃድ ሞቱ በይፋ ሳይገለጽ፤ የነበረከት የለቅሶ ሀገር አቀፍ ወጥ ሙሾና ረገዳ ተደርሶ ሳይመረቅ፤ ዘማሪያን በመዝሙራቸው፣ ደራሲያን በግጥሞቻቸው፣ ዘፋኞች በዘፈኖቻቸውና ተዋኒያንም በትእይንታቸው ”ባለ ራዕዩ መሪ” እያሉ ከመዘባረቃቸው በፊት፤ አዜብ መስፍን የምርጫ ቅስቀሳ እንደሆነ ባሳበቀባት ንግግሯ ”የመለስ ራዕይ እስካልተበረዘና እስካልተከለሰ ድረስ ... ወዘተ ወዘተ ከማለቷ እጅግ በፊትና የጠቅላዩን መሞት ያወቁ ሁሉም ወያኔዎች በድብቅ እህህ በሚሉበት ወቅት ሳይቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ ካንድ በላይ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ሊኖር እንደሚችል ያውቅ ነበር።

 

አንዳንድ ልበ ብርሃን የማሕበረሰባችን አባላት ያህን ጉዳይ እንዲያውም ሲበዛ ወደ ሗላ ጎትተው ጨካኙ መለስ ከመታመሙ በፊት ከሚቀጥለው ሀገር አቀፍ ምርጫ በሗላ ሊተገብራቸው ካሰባቸው የተነቃቁ የወያኔ አባላትን ማደንዘዣ እና በወያኔ ውስጥ እየታየ ያለውን የህወሓት የበላይነት ይብቃ ማጉረምረም ማስተንፈሻ ዘዴዎች ውስጥ እንዳንዱ የሚጠቅሱት አልጠፉም፤ የሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሮችን ሹመት ጉዳይ፤ ጨካኙ መለስ በጨካኙ ሞት ተወሰደና እስከ ዛሬ ተጓተተ እንጅ።

 

የሕዝብ ዓይን ያየውን በዚህ መልኩ ይናገር እንጅ እንዲህ እንዳሁኑ ህግ ተጥሶ በጠራራ ፀሐይ ያለ ምንም ማስተባበያ ሹመቱ ያሰጣል ብሎ አልጠበቀም ነበር። ይልቅስ ከዚያ በፊት የወያኔ ማለዘቢያ ንግግሮችና ማስታረቂያ ወይም ግራማጋቢያ መመሪያዎች ካልሆነም ሁሉ በጄ ሁሉ በደጄ የሆነው ወያኔ የግል ንብረቱ በሆነው ፓርላማ አማካኝነት አንቀጽ 75ን ሞረድ የደርጋታል የሚል ግምት ነበር፤ በነበር ቀረ እንጅ። ከዚህ ይልቅ በጊዜው የተመረጠው የሕዝብን ከመሬት ጠብ የማይል ንግግር፤ ”የነቶኔ ሃሳብ ነው፣ ያሸባሪዎች መላምት ነው፣ እንትና እና እንትና የሚባሉ ንቅናቄዎች በዚህ መልኩ ያሻቸውን ቢያወሩ እኛ ግን ከባለራዕዩ ራእዮች ጋር ሳንበረዝና ሳንከለስ ቀጥለናል” እየተባለ እንደተለመደው በሕዝብ ላይ ተሾፈ። ዛሬ የሆነው ግን የህዝብ አይን ያየውና የተናገረው ሆነ።

 

ዛሬ ህዝባችንን ያንገበገበው ወያኔ የራሱን ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 75ን በመጣስ ሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር መሾሙ አይደለም፤ምክንያቱም ህግ መጣስ ለወያኔ የዕለት ተዕለት ተግባሩ ስለሆነ፤ ከዚያ ይልቅ መተካካት በሚል ሰበብ የህወሓት የበላይነት እንደገና መንገሱ እንጅ። ኃይለማሪያም ደሳለኝ አሁን በዋናነት ካቀረበው ሹመት ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ሁለቱ በህወሓት ከመያዛቸው አንጻር ሲታይ ሰውየው በራሱ ላይ የቅርብ አለቃና ተከታታይ በመተካካት ስም ለማስቀመጥ እንደተገደደ ያሳይል። የብሄርን ተዋጽኦ ለማሟላት በሚል ከሌሎች ብሄሮች የተሰየሙትም ቢሆኑ ወይም ቀድመው የደነዘዙ አልያም በህወሓት ሰዎች እንዳሻ የሚሽከረከሩና ቦታው ስም እንዲሰጠው ብቻ ሹመቱ የተሰጣቸው ናቸው።

 

ይችን ”መተካካት” የምትባል ቃልና ውጤቷን በደንብ ያስተዋሉ አንዳንድ ሰዎች እጅግ ወደ ሗላ ተመልሰው የወያኔን የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን በማስታወስ በጊዜው ወያኔዎች ” በሁሉም መልኩ ቅድሚያ በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች” በሚል ሰበብ የቀበሌ ቴሌቪዥንና የእድር ድስትና ማንኪያ ሳይቀር ወደ ትግራይ ማጓጓዛቸው አይረሳም፤ ምንም እንኳ የትግራይ ሕዝብ ከዚህ ዝርፊያ ስም እንጅ ምንም ያልደረሰውና ተጠቃሚ እንዳልነበር የሚታወቅ ቢሆንም።

 

ወያኔ በየጊዜው በሚያወጣቸው እንደመተካካት ያሉ ዘዴዎች በሽፋን ህወሓቶች ያሻቸውን ሲያደርጉና የፈለጉትንም ሲከውኑ ኖረዋል። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ቅድሚያ በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች በሚል ሰበብ ከትንሽ እስከ ትልቅ ጥሬ እቃ፣ የሰው ኃይል፣ የኢንቨስትመንት አቅም፣ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች ግንባታዎችን ወደ ትግራይ በማዞር ትልቅ የሙስና መረብ ገንብተውበታል፤ ጥቂት የማይባሉትም ከታጋይነት ይልቅ ባንድ ጊዜ ወደ ታዋቂ ነጋዴነት እና ኢነቨስተርነት ተቀይረውበታል። የትግራይ ሰፊ ሕዝብ ግን ልክ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ”ሽህ ቢታለብ ያው በገሌ ...” አለች የምትባለውን የድመቷን ተረት እየተረተ የስቃይ ዘመኑን ይገፋል።

 

እንዲህ እንደዛሬው የያኔው የወያኔ ፓርላማም ያችኑ የተለመደች ”ቅድሚያ በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች” የምትለዋን ነጠላ ዜማ በማዜም ከፍ ያለ በጀት ለክልሉ በመመደብ ሙሰኛ ወያኔዎችን አበረታቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በጊዜው የነበሩት ጥቂጥ የህትመት ውጤቶች፤ በእርግጥ ቁጥራቸው ካዛሬው ይበልጥ ነበር፤ ”ትግራይ እስክትለማ ሌላው ሀገር ይድማ” የሚል ጽሁፍ በማስነበባቸው ብዙ መተረማመስ እንደተፈጠረና ከፍ ዝቅ እንደተደረጉ አይዘነጋም።

 

ሌላው እንደ መተካካት ያለና በሀገራችን ጉድ የታየበትና ታምር የተሰራበት አሁንም እየተሰራበት ያለ ደግሞ ”መድብለ ፓርቲና አውራ ፓርቲ” የሚለው ነው። ወያኔ በሀገራችን መድብለ ፓርቲ ስርአትን እስፍኛለሁ በማለቱ ከዓለም ዙሪያ ከሚጎርፍለት የዲፕሎማሲ ችሮታ በተጨማሪ የትምህርትና የአቅም ግንባታ እገዛ፣ የአቅርቦትና የቴክኖሎጅ ሽግግር እርዳታ እንዲሁም በገንዘብ አገሪቱ አይታው የማታውቀውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እርዳታ በየዓመቱ ወያኔ ሲያፍስ ቆይቷል፤ ምንም እንኳ አንቱ የተባሉ ዓለማቀፍ ተቋማት የሚበዛው የአይነትም ሆነ የገንዘብ እገዛ በወያኔ ባለስልጣናት አማካኝነት ተዘርፎ በውጭ ባንኮች በግል ሃብትነት የተቀመጠ መሆኑን ያጋለጡ ቢሆንም። ይሁንና ይህን ሁሉ ችሮታና ጥቅማጥቅም ያስገኘው መድብለ ፓርቲ ተሽከርክሮና ለዘብ ብሎ ”የአውራ ፓርቲ ስርአት” በመባል አውራ ነኝ ባዩ ወያኔ ህወሓት ተቃዋሚ ነን የሚሉትን ፓርቲዎች ይቅርና የኔ ናቸው በሚላቸውም በብአዴን፣ በደህዴን እና በኦህዴድም ላይ አውራ ሆኖ ባውራ ፓርቲ ስም እገዛውንም፣ የትምህርት እድሉንም፣ ስልጣኑንም፣ ኢንቨስትመንቱንም፣ ንግዱንም፣ ሙስናውንም፣ የመንግሥትም ሆነ መንግሳታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንም፣ እድሩንም፣ ፎረሙንም፣ ማህበሩንም፣ እቁቡንም ጠቅልሎ ይዞ ያሻውን እያደረገ ቀጥሏል።

 

የወያኔ ህግ አልበኝነትና ኃይ ባይ ማጣት በመተካካት ሰበብ በሚፈጸም ህግወጥነት እና ቅድሚያ ለተጎዱ አካባቢዎች በሚል የሃብት ሽግግር ብቻ የሚቆም አልሆነም። ይህን ሁሉ ካደረገና ሁሉንም ነገር ዝብርቅርቁን ካወጣም በሗላ ቢሆን ሀገሪቱን የሚመራት ማን መሆኑ ለመለየት እስከሚቸግር ድረስ የሟቹ የጎጠኛው መለስ ዜናዊ የተለያዩ ፎቶ ግራፎች የሀገሪቱን ህንጻዎች እስከ ዛሬም ድረስ ሸፍነው መታየታቸውና ስሙም ለሀገሩም ሆነ ለሕዝቡ መልካም እንዳደረገ መሪ በወያኔ ጋዜጦች፣ ራዲዮዎችና ቴሌቪዥኖች ክህዝባችን ህሊና እንዳይጠፋ ይመስላል ጠዋት ማታ እንደ ፈረንጅ ቅመም በየዜናው አላግባብ እየተደነጎረ ከመገኘቱም በተጨማሪ፤ የባስ ብሎ የወያኔ ቃል አቀባይ አንባሳደር ዲና ሙፍቲ ከቪኦኤ የእንግሊዝኛው ክፍል ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ”በፓርላማ የመለስ መቀመጫ ቦታ ክፍት ነው ለምንድን ነው” ተብሎ ለተጠየቀው ጥጣቄ ሲመልስ ”ለባራዕዩ መሪያችን ክብር ለመስጠት ነው” ማለቱ ዘላለማዊ መሪ ተብለው በልጃቸውና በልጅ ልጃቸው ዘመን ሰይቀር ሰሜን ኮሪያን እየመሩ እንደሚገኙት የሰሜን ኮሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኪም ኢል ሱንግ እኛስ አገር ”ለባለ ራዕዩ መሪ ክብር ለመስጠት” በሚል ስበብ አሁንም ሀገራችን በሙት እየተመራች ስላለመሆኗ ምን ማረጋገጫ አለ። መቼም ኃይለማሪም ደሳለኝስ የት ሄደና ብላችሁ ስድስት ወር እንዳታስቁኝ።

 

ይህን ሁሉ ጉድና መከራ፣ ስቃይና ግፍ፣ ህግ አልበኝነትና የወያኔን ሁሉ የኔና በኔ ባይነትን ተሸክሞ እየተጓዘ ያለው የሀገራችን ሕዝብ በቃኝ ብሎ በመነሳት በወያኔ የግፍና የከፋፍለህ ግዛ አገዛዝ ላይ ማሳየት የጀመረውን በብሔርም ሆነ በኃይማኖት አነድነትን የማጠናከርና ከሁሉም ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር እያደረገ ያለውንም ሁሉን አቀፍ ትብብር በከፍተኛ ሁኔታ በመቀጠልና ወያኔን የማስወገድ ብቃቱን ለዓለም የበለጠ አጠናክሮ በማሳየት ከሌሎች አህጉር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ሆነ ሀገሮች እገዛን ሊያገኝ ይችላል። ከዚህ ውጭ ግን ”ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም” እንደሚባለው እጅን አጣጥፎ በመቀመጥ ለራስ ችግርና መከራ ዓለም አቀፍ እገዛንም ሆነ መለኮታዊ መፍትሄን መጠበቅ የሕዝባችንን ስቃይ የበለጠ ከማስፋቱም በላይ ሀገራችንንም ከዓለም ካርታ ላይ ሊያስፍቃት ይችላል። ስለዚህም የህን ትሪካዊ ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ጊዜው ዛሬ ነው፤ አሁን።

ይኸነው አንተሁነኝ

ታህሳስ 1 ቀን 2012

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ