አዜብ መስፍን Azeb Mesfinከበደ ኃይሌ

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ የሃውልት፤ የመኖሪያ ቤቶችና የመቃብር ሥፍራዎች የማፍረስ ዘመቻ ስለመካሄዱትና ተዛምዶ ስላላቸው ክስተቶች የታዘብኩትን ጽፌ ለማስነበብ ነው። የቀደሞዋ ቀዳማዊት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከቤተ-መንግሥት እንዲለቅቁ ተጠይቀው በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያላስረከቡበት ምክንያትም ለማነፃፀር እሞክራለሁ።

 

 

የቀደሞዋ ቀዳማዊት ወ/ሮ አዜብ ከባለቤታቸው (አቶ መለስ ዜናዊ) ጋር የኖሩበትን ነጻ የመንግስት መኖሪያ (ቤተ-መንግሥት) ቤት እንዲለቅቁ ተጠይቀው በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያላሰረከቡበት ምክንያት የተመረጠላቸው ቤት ለደህንነታቸው አመቺ ባለመሆኑ፤ ቤቱን ቢለቅቁ ሃዘኑ ስለሚጫናቸው፤ ዕቃቸውን ለማዘጋጀት ጊዜ ስለሚፈጅባቸው፤ ከፍተኛ የመንግስት በጀት የያዘ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሃላፊ ስለሆኑና አሁንም በፓርቲው ውስጥ ባላቸው ተሳትፎ ቤት መልቀቁን በማዘግየታቸው የሥልጣን ሸግግሩን ስመ-ጥሩ ሂደት እያጎድፉት ነው። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ ጉዳዩን እንዲፋጠን ያላደረጉት የሹመታቸውን ህልውና ይፈታተነው ይሆናል ብለው ስላዩት ግፊት አላደረጉም ወዘተ … በማለት በብዙኀን መድረክ ተተችቶበታል። አሁን ደግሞ ታሪካዊ ሃውልቶች ያሉበት ሥፍራ ይፈለጋል ስለተባለ በሰፊው ቢወሳ ሊያስደንቀን የሚገባ አይመስለኝም። ምክንያቱም የመኖሪያ ቤቶች፤ የመቃብርና የሃውልት ሥፍራዎች ማፍረስና መሰል ለሕዝብ ግልጋሎት የሚሰጡ ተወዳጅ ነገሮችን በመንሳት ዘመቻ ማካሄድ የምዕራባዊያን ገዢ መደብ የሚጠቀሙበት የሕዝብ ትብብር መንሻና ውዥንብር ማካሄጃ ስልት ነው።

 

ይህን ጉዳይ ስመለከተው በኢትዮጵያ ቀን አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም. አካባቢ ውስጥ የመንግስት ቤት ተከራተው በግላቸው እያስጠገኑ፤ በፈረቃ በሚሰጣቸው መብራትና ውሃ እየተገለገሉና ኪራይ በወቅቱ እየከፈሉ ለአመታት ያህል ከመንግስት ተከራይተው የኖሩበትን የመኖሪያ ቤት የቤት ውሉን የፈረሙት ተከራዎች በቤት ውስጥ አይኖሩምበትም፤ ቤቱ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ኢትዮጵያውያን ይሰጣል፤ ቤቱን አከራይታችኋል ወዘተ … የሚል ምክንያት እየተሰጣቸው በተወሰነ ቀን ውስጥ ቤቱን ለቅቃችሁ ለመንግስት እንድስታረክቡ፤ ባታስረክቡ ቤቱ ይታሸጋል፤ ብሎም ዕቃችሁ ከቤት ወጥቶ ከመጣሉም በላይ የወጣበት የሰራተኛ ክፍያ ሂሳብ እንድትከፍሉ ትደረጋላችሁ የሚል ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ሲደርሳቸው ለክልሉ የቀጠናው ፖሊስና ለክፍለ ከተማው ጽ/ቤቶች እንድያውቁት ሲደረግ ህዝቡ ተደናግጦ በከተማው ውስጥ ትርምስ ተፈጥሮ ነበር። በተራው ህዝብ ላይ የመጣው የቤት ልቀቁ ጣጣ በመንግስት ቤት ለሚኖሩ የኢሕአዴግ አባሎችም ደብዳቤው በስህተት ተጽፎ ደርሷቸው ስለነበር እኛ በሜዳ የታገልነው ይህ በደል እንዲደርስብን አይደለም በማለት በኪራይ ቤት አስተዳዳሪዎችና በጸሐፊዎቻቸው ላይ ሲፎከርባቸው እንደነበር አስታውሳለሁ።

 

የቤት ልቀቁ ማስጠንቀቂያው በመኖሪያ ቤቶች ጉዳይ ላይ ሳይቆም በመቃብር ቦታ ላይ ሙታን የቀበሩ ግለሰቦችም እንዲሁ አካባቢው ለመንገድ ስለሚፈለግ መቃብሮች ይፈርሳሉና በስፍራው የቀብር ቦታ ያላችሁ በተወሰነ ቀን ውስጥ አስከሬኑን አንስታችሁ ሌላ ቦታ ወስዳችሁ ቅበሩ ተብሎ በይፋ ሲነገር፤ ያላወጡት መቃብሩ በላያቸው ላይ እንዲፈርስ ተደርጎ አጽማቸውን በማዳበሪያ ከረጢት ውስጥ እየተደረገ ለቋሚ ዘመዶቻቸው እንዲሸጥ በማድረግ ህዝቡን በእንባ አራጭተውት ነበር። እንዲሁም ለታሪክ ሊጠበቁ የሚችሉ ቤቶችም በመኖሪ ቦቶች ሳቢያ እንዳይፈርሱ እያለ የኢት.ቅርሳቅርስ ድርጅት ሲወተውት ችላ በማለት የተወሰደውን ወገናዊነት የተሞላውና ህገ ወጥ የሥራ የአፈጻጸም በአገር ውስጥ እንደሚካሄድ ለማያውቁ ግለሰቦች ለማስነበብ ነው።

 

የቤታቸው መፍረስ/የልቀቁ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው ግለሰቦች ህጋዊ ነዋሪ መሆናቸውን ለማሳወቅና ምትክ የመኖሪያ ቤት ይሰጠን በማለት በኪራይ ቤት ቀጠና ጽሕፈት ቤቶችና የቀጠናው ዋናው አስተዳደርው ቢሮ እየተሰባሰቡ አቤቱታ በማቅረብ እላይ ታች ሲሉ በወቅቱ ያለቀቁትን የነዋሪዎች መኖሪያ ቤት ታሸጎባቸው እቃቸውን ገንዘብ ከፍለው እንዲያወጡ፤ ተከራዮቹ በሌሉበት ቤታቸው ተሰብሮ እቃቸው በፖሊስ ውጭ ተወርብሮባቸው ነበር። ወይዘሮ አዜብ ግን ቤቱን ሲለቅቁ የሚገቡበት ምትክ ቤት ተዘጋጅቶላቸውና ዕቃቸው በክብር ተዘጋጅቶ በውዴታ እንዲለቅቁ ተጠየቁ እንጂ እንደሌላው ተከራይ ነዋሪ ህዝብ ተገድደው አልወጡም።

 

ተከራዮቹ በግዳጅ ሲፈናቀሉ ካሳ ተከፍሎአቸዋል ለማለት እንዲያስችል ከንብረታቸው ዋጋ በታች ግምት እየተሰጡ ርካሽ የኪራይ ቤት ዋጋ በሚገኝበት የመኖሪያ አካባቢ ሲሄዱ ግማሹም ከርቀቱ የተነሳ ከስራቸው ተፈናቀለዋል። የዕለት መታዳደሪያ ገቢ አጥተዋል። ዘመድ ቤት እንዲዳበሉ ተገድደዋል። ቤተሰባቸውን በትነው የባሰበትም የሜዳ ተዳዳሪ ሆነዋል። በኢህአዴግ አባል በሆኑት ላይ የተላለፈው ውሳኔ ባፈነገጡት አባሎች ላይ ሲጸና ሌሎቹ አልተነኩም። የተለቀቁት ቤቶችም ቤት ለሌላቸው የፖለቲካ አባሎች እንዲሰጥ ተደርጓል።

 

የእንኝህን ነዋሪ ህዝቦች የደረሰባቸውን እንግልት በተመለከተ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰፊው ጽፈው ሲያወጡ ለዚያን ወቅት የመጻፍ መብታቸው ተጠብቆላቸው ነበር። በየአካባቢው የሚገኘው ሥራ አጥ ዕቃ ጫኝ ወዛደሮች፤ የካሚዮን ባለቤቶች፤ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ባልደረቦች ወገን መግዣና የገቢ ምንጭ ማፍሪያ ሆኖም ነበር።

 

እነኝህ ነዋሪዎች ሃላፊነታቸውን እየተወጡ እየኖሩ ከቤት ውጡ ሲባሉ እንኳን ቤት የመመምረጥ እድል ሊሰጣቸው ቀርቶ የሚከራይ ቤት ፈልገው ለመግባት በቂ ጊዜ ሳይሰጣቸው ልጆቻቸውን ወልደው ካሳደጉበት ቀየ የተበተኑ ሰዎች አቤቱታቸውን የሚሰማ ጠፍቶ ሲያለቅሱና ሲባዝኑ ይታዩ ነበር። በቀጠናው ጽሕፈት ቤት ግጥር ግቢ የአቤቱታ አቅራቢ በብዛት ተሰባስበው ሲታዩ አስፈቅዳችሁ ሰላማዊ ሰልፍ ውጡ እንጂ ካለፈቃድ በብዛት መሰባሰብ አትችሉም ወይም ጠበቃ አቁማችሁ ክስ መስርቱ ተብለዋል። በአንደኛ ደረጃ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ከህዝብ ደህንነት ጽህፈት ቤት ፈቃድ ለማውጣት ጊዜ ይወስዳል። በሁለተኛ ደረጃ የዜግነት መብቱን የሚያስከብር አስተዳዳሪ ቢኖረው ኖሮ ጉዳያቸው ተሰምቶ በምትኩ ቤት በተሰጣቸው ወይም እንደ ወይዘሮ አዜብ ቤት አግኝተው በፈቃዳቸው እስከሚለቅቁ ጊዜው እንዲራዘም በተደረገ። በሶስተኛ ደረጃ ለጠበቃ የሚከፍሉት የገንዘብ አቅም ቢኖራቸው ከቀጠናው ጽሕፈት ሰራተኞች ጋር በመጨቃጨቅ ጊዜያቸውን ከማጥፋት ቤት ተከራይተው መውጣት በቀለላቸው ነበር።

 

በተጨማሪም ለወላጆቻቸው ቤት የተከራዩ በውጭ አገር የሚኖሩ ልጆቻቸው ወላጆቻቸውን ለመርዳትና ቤቱን ለማዳን በአስቸካይ ከውጭ አገር የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ከወላጆቻቸው ጋር ሄደው ውሉን አድሱልን ብለው ሲጠይቁ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ አጽፉ ወይም ከቀጠና ጽሕፈት ቤቶች የተላለፈውን ውሳኔ ለመሻር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማዘዣ አምጡ እያሉ የከተማ ኪራይ ቤት አስተዳዳሪ ኃላፊዎች ከቤት ውጣ በተባለው ሕዝብ ላይ ሲመጻደቁና ሲያፌዙበት ነበር። በዚህ አጋጣሚ አንድ ከውጭ መጥቶ የወላጆቹን መበሳጨት የተመለከተና የተማረረ ግለሰብ ሁለተኛ አገር አለኝ ብዬ ወደ እዚች አገር አልመለስም ብሎ በባልስልጣን ፊት ተናገረ ተብሎ ከቅጥር ግቢው በዘበኛ ተባሯል።

 

ቤት ልቀቁ ብሎ መጠየቅ ወ/ሮ አዜብን ሊያስገርማቸው አይገባም። የመቃብር ሥፍራዎች ማፍረስና አሁን ደግሞ ቦታው ለልማት ይፈለጋል በማለት ሃውልቶችን ለማፍረስ መነሳት ከአገሩ ርቆ ለሚኖር ወገን አዲስ ይሁንበት ይሆናል እንጂ የኢትዮጵያን ሕዝብ አያስደንቀውም። ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ የወ/ሮ አዜብ ባለቤት በአመራር ላይ ሳሉ በሕዝብ ላይ የፈጸሙት አንዱ በደል እንደሆነና፤ የባለቤታቸው የቀብር ቦታም እንዲሁ ጊዜውን ጠብቆ መፍረሱ የማይቀር ስለሆነ ወይዘሮ አዜብ ከወዲሁ ሊያውቁት ይገባል። ይሁንና ሕዝቡ በሰላም ከሚኖርበት ቤት የምትክ ቤት ሳይሰጠው አላግባብ ከመኖሪያ ቤትህ በድንገት ውጣ ብሎ ህዝብ ማስገደድ፤ የመቃብር ስፍራዎች፤ የመኖሪያ ቤቶችና ሃውልቶች ለመንገድና ለመንግስት ስራ ጉዳይ ይፈለጋሉ በማለት ንብረት ማፍርስ የሕዝብ መብትና የአገር ቅርሳቅርስ ማውደም የአገር ወዳዱን ህዝብ አዕምሮ እንደሚረብሽ፤ እንደሚያሳዝን፤ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆንን የሚያስጠላ ኢ-ሰብዓዊነት ድርጊት መሆኑ ገሃድ ነው። ስለሆነም ወ/ሮ አዜብ ከዚህ ገጠመኝ ትምህርት ስላገኙበት፤ ባላቸው ሥልጣንና ተሰሚነት ይህ ዓይነቱን ሕገወጥ የስራ አፈጻጸም ያዘሉ መመሪያዎች እንዲሻሻሉ፤ ባለስልጣኖችም ጉዳዮችን እያመዛዘኑ እንዲወስኑና ወደፊት ከተመሳሳይ ድርጊትም እንዲቆጠቡ የአገር ሃብት እንዲጠበቁ፤ የህዝብ አቤቱታ ሰሚ፤ የአገር ሃብትና ዳር ድንበር ጠባቂ ሆነው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!