ዳኮታ የጥናት ማዕከል

ቁጥራቸው ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜና ሁኔታ ውስጥ የሚያስቡት ተመሳሳይ ወይ ተዛማጅ ሀሳብ። ፍላጎትን ማስማማት። የሌሎችን ሀሳብና ፍላጎት በቶሎ ከመረዳት ጋር ወደሚታይ ተግባር የመቀየር ችሎታ መናበብ ይባላል። መናበብ ጥበብ ነው።

 

 

እንደማንኛውም ጥበብ በነገሮች ላይ ያለንን እውቀት፤ ተጨባጭ እውነታዎችንና ሀሳብችንን (imagination) በመጠቀም በጋራ የምንደርስበት ውሳኔ። የምናከናውነው ድርጊት ነው። ምንአልባት ይህን ጥበብ ልዩ የሚያደርገው ሁሌም ከአንድ በላይ ቁጥር ባላቸው ስዎች የሚከወን ወይ የሚሰራ መሆኑ ነው። ያም ሆኖ እንደማንኛውም ጥበብ ልናሳድገው፤ ልናረቀውና ልናወሳስበው የሚቻለን ነው።

 

የመናበብ ጥበቡ በቡድን እስፖርት ውስጥ ከጥሩ ወይ ከመጥፎ ውጤት ጋር አብዝቶ ሲነሳ እንሰማለን። በዛው ልክ ግን ብዙ ቁጥር ባላቸው ሰዎች የተደረጉ ቢሆንም በቂ መገናኛ፤ ጥልቅ ውይይት፤ በጋራ ማቀድ ባልነበረበት ጊዜና ሁኔታ ውስጥ የሰው ልጆች ለእኩልነትና ለነፃነት በጋራ ባደረጓቸው ትግሎች ውስጥ ጥበቡ ስለነበረው አስተዋፆ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በአለም ላይም ጎልቶ ሲነሳም ሲፃፍበትም እስከዚህ አይታይም።

 

ወደኛ ጉዳይ ስንመጣ። ለምን መብታችንን ማስከበር፤ ከብራችንን ማስመለስና፤ ነፃነታችንን ማወጅ አቃተን? አይነት ጥያቄዎች ኢትዮጵያዊያን ደጋግመን የምናነሳቸው ናቸው። ለነዚህ ጥያቄዎች የተለመዱትና አብዛኛዎቻችን የተስማማንበት የሚመስሉት መልሶች “ፈሪዎች ስለሆንን”። “ስላልተደራጀን”። ”ከማሸነፍ በሗላ የሚለው ግልፅ ሆኖ ስላልታየን በሌላ አገላለፅ የባሰ እንዳይመጣ”። እንዲሁ ደግሞ “ትግሉ በአንድ እዝ ስር እየተመራ ስላልሆነ”። ” አስተማማኝ ህዝብን መድረሻ ሜዲያ ስለሌለን” የመሳሰሉት ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው።

 

አስፈሪ በሆነ ጭቆና ስር የሚያኖረን የብዙ ምክንያቶች ድምር ውጤት ስለሆነ ከላይ የተዘረዘሩትን አይነት ምክንያቶች በጭቆና ስራ ለመኖራችን የሚኖራቸው ድርሻ አሌ የማይባል ነው። ያም ሆኖ ምክንያቶችን አንድ በአንድ እያነሳን ሁላችንም ብንመረምራቸው አይከፋም። ምን አልባት የበዙት ምክንያቶች ላይ ግኝታችን ያልጠበቅነው ይሆናል የሚል ግምት አለን። “መሪዎች እንጂ መሪ የለንም” የመሳሰሉት በቂ ምክንያቶች የመሆናቸውን ያህል በተደጋጋሚ ምክንያት ሲደረጉ ስለሰማናቸው ምክንያት አድርገን የተቀበልናችው የሚመስሉም በብዛት አሉበት። ከዚሁ ጋር አስከዚሀም ወይ እስከጭራሹ ምክንያት አድርገን የማናነሳቸው ችግሮችም አሉብን። አንዱና ዋንኛው ችግራችን “መጠባበቅ” ነው።

 

በምሳሌ ኢትዬጵያዊያን ለልጆችን ያለን ፍቅርና መቆርቆር ከሌሎች ጋር ሲተያይ የሚበዛ እንጂ የሚያንስ ሊሆን አይችልም። አይደለምም። ልጆቻችን ከጉያችን እየተወስዱ ሲጋዙ “በሬሳዬ” ላይ ማለቱን ወላጆች ሳናስበው ቀርተን ወይ ፈርተን የተውነው አይደለም። ይህን ግፍ ለመቋቋም የጋራ እንቢተኛነትን፤ በህብረት ሆኖ “በሬሳዬ ላይ” ማለትን የሚሻ መሆኑን አሳምረን አውቀናል። ታዲያ አስቸጋሪ የሆነብን በግላችን ልንወስድ የሰብንው እርምጃ ወይ የእንቢተኛነት ተግባር ላይ ያገሬውን ስሜትና አቋም ማወቅ አለመቻላችን ነው።

 

እየኖርን ያለነው ባፈና ስር ነው። እየኖርንበት ያለው አፈና ደግሞ በይዘቱም በአይነቱም ለየት ያለና ጠንካራም ነው። ከዚህ አፈናና ጭቆና ለመላቀቅ ያሉንን አማራጮች ላይ በህብረት ለመወያየት፤ በጋራ ለማቀድ፤ በጋራ ተግባራዊ ለማድረግ አፈናው አላስቻለንም። ወይ አሜኔታችንን ማግኘት የቻለ መሪ ተፈጥሮ መመራት አልቻልንም። ይህ ሁኔታ በይበልጥም በሚጨፈጭፉንና ግፍ በሚፈጸምብን በነዛ ግዚያት ላይ እራሳችንን ለመከላከልም ሆነ ግፉን ለማስቆም የሚያስችለን ጉልበት አሳጥቶናል።

 

ጥቃት የሚፈፀምብን በጅምላ ስለሆነ ለመከላከል በጋራ የምናደርገው እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው። ሁላችንም የተሳተፍንበት ሲሆን ከደህንነት አኳያም በጣም ተመራጭ ነበር። በጋራ እንድ እርምጃ እንዳንወስድ ያደረገን ምን ማድረግ እንዳለብን በተናጠል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሳናስብበት ቀርተን አይደለም። ስለምንጠባበቅ ነው።

 

ከላይ እንዳየነው መጠባበቅን ያመጣው ዋናው ምክንያት አፈናው ነው። በአፈናው ምክንያት በህብረት ሆነን ያሉንን አማራጮች መርምረን፤ ተወያይተንና ውሳኔ አድርገን በጋራ መንቀሳቀስ አልቻልንም። እዚህ ላይ ነው የመናበብ ጥበብ የሚያስፈልገን። ሁላችንም የምንሳተፍበትና ድርሻ የምናደርግበት ትግል የግድ የሚል መሆኑ ላይ ከተስማማን እላይ ችግሮች ብለን ለዘረዘርናቸው ለበዙት ምክንያቶችም ሆነ ላለብን የመጠባበቅ ችግር ጥበብ ላይ መረቀቅ ፍቱህን መድሀኒት ነው።

 

ለመናበብ የሚያስፈልገው ሞልቶ የፈሰሰና እስከአጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ግፉ፤ አድሎና፤ መናቅ ኢትዮጵአዊያን እየኖርንበት ያለ እውነታ ነው። ይሀን እውነታ ለመቀየር ያለው የበዛ ፍላጎት፤ ጉዳዩ ላይ በመብሰልሰል የምናጠፋው ሰፊ ጊዜና ቁጭት ሁላችንም በአንዴ አንድ አይነት ሀሳብን ለማሰብነ ለመተግበር ያስችለናል የሚል እምነት አለን። ባጠቃላይ ጥበቡን ካሳደግነው ጠንካራ መታገያ መሳርያ ለማድረግ እየኖርንበት ያለነው ነባራዊ እውነታ የተመቸ ነው።

 

እንደተናቀ እየተረገጠና አድሎ እየተደረገበት እንዳለ ህዝብ። ለነፃነታችን የምናደርገው ትግል ላይ አሸናፊ የሚያደርጉን ተግባራት ላይ ተገናኝተን እንዳንመከር በጋራ እንዳናቅድና ተባብረን እንዳንነሳ መጠነ ሰፊ በሆነ አፈና ውስጥ መኖር ግድ ለሆነብን ኢትዮጵያዊያን እስከዛሬ ለነጻነት በአደረግናቸው ትግሎች ውስጥ ጥበቡን ስንገለገልበት የነበረም ሆነ አልሆነ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የተጫነብንን አፈና ሰብረን ነፃነታችንን ለማወጅ ጥበብ ሊኖርን የግድ ይላል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!