አደራ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፖለቲካውን በዚህ ሰሞን ገታ ያድርግልን!!!!!!

ኤፍሬም እሸቴ

ዛሬ ሐሙስ ረዥም ቀን እንደሚሆንብን እገምታለኹ። መች ነግቶ የኢትዮጵያንና የቡርኪናፋሶን ጨዋታ ባየን የሚለው የብዝዎቻችን ሐሳብ ነው። ብሔራዊ ቡድናችን ከዛምቢያ ጋር ባሳየው “ደረጃውን የጠበቀ እግር ኳስ” (World Class football") ምክንያት የዓለምን ዓይን ስቧል። ስለዚህ የሚጠበቅበትም እንደዚያው ደረጃው ከፍ ብሏል።

 

የሚቀጥሉት ሁለት ጨዋታዎች ታሪካዊና ወሳኝ የሚሆኑት ለሚቀጥለው ምድብ ለማለፍ ብቻ ሳይሆን የተፈጠረው በጎ አመለካከት (good impression) እንዲቀጥል ስለሚረዳ፤ ተጨዋቾቹም ከአገራቸው ወጥተው በሌላው የፕሮፌሽናል ዓለም መቀላቀል እንዲችሉ ለማስቻልም ነው። ትልቁ ጥያቄ የትኛው ጨዋታ ለቡድናችን ከባድ ይሆናል የሚለውም ነው።

 

በእኔ ግምት ከናይጄሪያ ይልቅ የቡርኪናፋሶ ቡድን ሊከብደን ይችላል። ምክንያቱም ቡርኪናፋሶ እንደኛው “ዝቅተኛ ግምት የሚሰጠው”፣ ቢያሸንፍ የሚደንቅ፣ ቢሸነፍ ግን “ይገባዋል” የሚባል ዓይነት ስለሆነ። ናይጄሪያ በእግር ኳሱ ካላት ታሪክ፣ ከተጫዋጮቿ ዝነኝነትና ፕሮፌሽናልነት ወዘተ ወዘተ አንጻር ጫናው ይበዛባታል። ከቡርኪናፋሶ ጋር ባደረገችው ጨዋታ የተበሳጩ የአገሪቱ የስፖርት ባለሥልጣናት ጣልቃ ገብተው “የሚቀጥሉትን ጨዋታዎች ማሸነፍ አለባችሁ” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ እንዳስተላለፉ ተዘግቧል። ጫናው ይቀጥላል።

 

Adane Girma አዳነ ግርማቡርኪናፋሶን ማሸነፍ ለሚቀጥለው ዙር ማለፊያ ትኬት መቁረጥ ነው። ከናይጄሪያ ጋር የሚኖረውንም ጨዋታ የተደላደለ ያደርግልናል። ስለዚህ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለው ናይጄሪያን ቀድሞ ከማሸነፍ አይተናነስም። በቀደም ባየነው የኢትዮጵያ ቡድን አቋም እንኳን ቡርኪናፋሶን የሌላውንም ዓለም መርጥ ቡድን መቋቋም የሚችል አቅምና ችሎታ እንዳለን ግልጽ ነው። ጥያቄው ይደግሙታል ወይ ነው። እምነቴ እንደሚደግሙት ነው።

 

ሌላ አንድ ሥጋት ደግሞ አደብ ገዝቶና አንገቱን ደፍቶ የነበረው ፖለቲካው ድንገት ብቅ እንዳይልና ጨዋታው ላይ ጥላውን እንዳያጠላ ነው። ለብዙ ጊዜ ስነገር እንደነበረው የኢትዮጵያን ሕዳሴ ለዓለም እናሳየለን የሚሉ አማተር ፖለቲከኞች ቡድናችንን የሐሳባቸው ማንጸባረቂያ ለማድረግና ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው እየተገለጸ ነው። እነርሱ ይህንን ሲያድረጉ በደቡብ አፍሪካ ያለው ሌላው ተቃዋሚ ቡድን ደግሞ ምላሹን ለመስጠት “ተዘጋጅቼያለሁ” ብሏል። እንደተባለው “ጎል የሚያገባ ተጫዋች ሁሉ ከሥር የሚለብሰውን የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶ ያለበትን ካናቴራ እየገለጠ እንዲያሳይ” የሚደረግ ከሆነ ተቃዋሚው ደግሞ ያንን ለመቃወም በሚያደርገው ምላሽ ኢትዮጵያን ስም ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ሜዳ የሆነውን የስፖርት ቦታ የጦርነት አውድማ እንዳናስመስለው፣ በቴሌቪዥን መስኮት በዓለም ፊት ራሳችንን እንዳናስገምት እፈራለኹ።

 

Adane Girma, አዳነ ግርማአደራ!!! “እርሟን ብታፈላ - አተላ” እነዲል ተረታችን በስንት መከራና ትጋት እዚህ የደረሰውን ቡድናችንን ጨዋታ ሳያንሰው በተበላሸው ፖለቲካችን ምክንያት ጫና ውስጥ አስገብተን ችግር እንዳንፈጥርበት። በነገራችን ላይ፣ ኢትዮጵያውን በስቴዲየሙ የምንፈጥረው ማንኛውም ከስፖርቱ ዲሲፕሊን የወጣ ድርጊት ቡድናችን በቀጣይ የሚኖሩትን ጨዋታዎች በባዶ ስቴዲየም እንዲያደርግ ሊያስቀጣው የሚችል እንደሆነ ተነግሯል። ይኼንን ደግሞ “አፍቃሬ መለስ” ወይም “ተቃዋሜ-መለስ” የሆነውም ኢትዮጵያዊ የሚፈልገው አይመስለኝም። ስለዚህ ስፖርቱ እስኪጠናቀቅ ፖቲካውን ከሜዳው ገለል እናድርገው። የተለያየ የፖለቲካ አቋም ቢኖረንም በአንድነት ቡድናችንን ከመደገፍ ወደ ኋላ አንበል። 12ኛው ተሰላፊ የተባለው ደጋፊ የማይቋረጥ ድጋፍ በመስጠት አጋርነቱን ይግለጽ። አደራ!!!!!! በባንዲራው!!

 

ኤፍሬም እሸቴ

www.adebabay.com

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!