አማኑኤል ዘሰላም

“ESAT is tasked to produce accurate and balanced news and information” ይላል የኢሳት ኤዲቶሪያል ፖሊሲ። ኢሳትን የሚያዳምጠው ሰው ጥቂት እንደማይሆን አስባለሁ። እስቲ በኢሳት የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን እንመዝናቸው። ምን ያህል ሚዛናዊ፣ በእውነት ላይ የተመሰረተ፣ የሁሉን ወገኖች አስተያየት ያንጸባረቀ ዜናና ትንታኔ ይቀርባል? ምን ያህል በአገራችን ኢትዮጵያ መቀራረብ፣ ፍቅር፣ አንድነት እንዲሰፍን ይረዳል?

 

በቅርቡ ኢሳት አንድ ዘገባ አወጣ። “የFBI መርማሪዎች፣ አበበ ገላውን ለመግደል የታቀደን ሴራ አከሸፉ። በሴራው የተሳተፉ የሕወሓት ሰላዮች ምርመራ እየተደረገባቸው ነው” ሲል፣ በቦስተን፣ አቶ አበበ ገላው ላይ፣ የግድያ ሙከራ ለማድረግ እንደታሰበ እና ኤፍ.ቢ.አይ. ሙከራውን/ሴራውን/ዕቅዱን እንዳከሸፈው ነበር ኢሳት የገለጸው።

 

ዜናውን ተከትሎ ብዙዎቻችን፣ ነፍጥ የያዘ ግለሰብ በስብሰባው ተገኝቶ ለመግደል ሙከራ ያደረገ ነበር የመሰለን። በዜናውም በጣም አዘንን። ድርጊቱን ፈጸሙ የተባሉ፣ ነዋሪነታቸው ቦስተን የሆኑ፣ ጉሽ አበራ የተሰኙ ኢትዮጵያዊ ፎቶግራፍ በኢሳት ድረገጽ ላይ ተለጠፈ። እኝህ ሰው እንደ ነፍሰ ገዳይ ተቆጠሩ። አገር ሁሉ አወቃቸው። እርግማንና ስደብ ወረደባቸው። ስማቸው ጠፋ። የፖለቲካ ጥገኝነት እንደጠየቁ፣ አቶ አበበ ገላውን እንዲገድሉ በገዢው ፓርቲ እንደተላኩ፣ እንደ ኢሳት አባባል የሕወሓት ሰላይ እንደሆኑ፣ ቤታቸው እንደተበረበረ፣ እንደታሰሩም የሚገልጹ ዘገባዎችን በስፋት አነበብን፣ ሰማን።

 

የአቶ መለስ አፍቃሪ እንደመሆናቸው፣ አቶ ጉሽ፣ በአቶ አበበ ገላው ላይ ንዴት ሊኖርባቸው ይችላል። በዚህም ምክንያት “አቶ አበበን መግደል ነበር” የሚል ስሜታዊ አስተያየቶችን በፌስ ቡክ ላይ ሳይለጥፉ እንዳልቀረ አስባለሁ። (በነገራችን ላይ በተለያዩ ጊዜያት በጻፍኳቸው ጽሁፎች ተናደው የተለያዩ የማስፈራራትና የዛቻ ኢሜሎች፣ እኔም ብዙ ጊዜ ደርሶኛል)።

 

የአቶ ጉሽን ስሜታዊና መነገር የሌለበትን አስተያየት (አቶ ጉሽ እራሳቸው እንደተናገሩ ያመኑት)፣ ማንነታቸው ይፋ ያልወጣ፣ አንድ ወይንም በርካታ ግለሰቦች፣ ይቀዱና ለFBI ይልካሉ መሰለኝ። ማናቸውንም አይነት ማስፈራራትና ዛቻ፣ እንደ ትንሽ ነገር የማይቆጥረው FBI፣ ሁኔታውን ለመከታተል፣ መስሪያ ቤታቸው ድረስ በመምጣት፣ አቶ ጉሽን ለአሥራ አምስት ደቂቃ የሚያህል አነጋገረ።

 

ነገሮች በተሟሟቁበት ወቅት፣ ለአሥርተ አመታት ሕዝብን በታማኝነት ያገለገለው የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጣቢያ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ዘገባ አቀረበ። አቶ አበበ ገላውንና አቶ ጉሽ አበራን አወያየ። እውነትን ሚዛናዊነት ባለው ሁኔታ መዘገብ ማለት ይሄ ነው። ከFBI ባለስልጣናት፣ በጉዳዩ ላይ የተላከ ደብዳቤ ተነበበ። የግድያ ሙከራ ተፈጸመባቸው የተባሉት፣ አቶ አበበ ገላው የአየር ሰዓት ተሰጣቸው። ምንም አይነት የግድያ ሙከራ እንዳልተፈጸመባቸው ግልጽ አደረጉ። “ሴራ ነው እንጂ የግድያ ሙከራ አልተደረገም” ሲሉ ግን በኢሳት የተዘገበው ዜና ለመመከት ሞከሩ። FBI የግድያ ሙከራ ለመደረጉና፣ ሴራ ለመጠንሰሱ የሚያሳዩ አንዳች አሳማኝ መረጃ እንዳላገኘ፣ በጉዳዩም የከሰሰው ማንም ሰው እንደሌለ፣ ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጣቢያ አሳወቀ። እደግማለሁ እንደ FBI ገለጻ፣ ማናቸውም አይነት የግድያ ሙከራ አልተደረገም።

 

ማንም ሰው በሕግ ወንጀለኛ ተብሎ እስኪወሰንበት ድረስ ጥፋተኛ አይደለም። አቶ ጉሽ አበራ በፌስቡክ የጻፉት ተገቢ ያልሆነና መታረም ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ፤ በፌስቡክ በጻፉት፣ እጅግ በጣም የከፋና የተጋነነ ወንጀል የሰሩ ይመስል፣ በርሳቸው ላይ ሳይጣራ፣ መረጃ ሳይኖር፣ በኢሳት አዝማችነት ውርዥብኝ ደረሰባቸው። ያወቀም ያላወቀም ኢሳት ባናፈሰው ንፋስ እየተወሰደ አላስፈላጊ ነገሮች መናገር ጀመረ። ይህ በጣም አሳዛኝ ነው። ስህተትም ነው። በኢሳት ኢዴቶሪያል ፖሊሲ ቃል የተገባው ሚዛናዊነትስ የት አለ? ለምንስ ኢሳት አቶ ጉሽ አበራን አስቀድሞ ሳያነጋገርና ሳይጠይቅ፣ ሳያጣራም እርሳቸውን ይከሳል? በዘፈቀደ፣ ያለመረጃ የዜጎች ስም እንዲጠፋ ማድረግ፣ ሊያስጠይቅ አይገባምን? ነውር አይደለምን? ለተፈጸመውም ስህተት፣ አቶ ጉሽ አበራ እና የኢሳት አድማጮቹ የኢሳትን “ይቅርታ አደርጉልን፤ ተሳስተን ነበር” መልዕክት ቢጠብቁ ተገቢ አይደለምን? አንድ በሉ!

 

ኢሳት “ብዙ የሕወሓት ሰላዮች” በምርመራ ላይ እንዳሉ ነበር የገለጸው ነው። ኢሕአዴግ የድርጅቱን የፖለቲካ ሥራ የሚሰሩ፣ ለአባይ ግንባታ መዋጮ እንዲሰበሰብ፣ በዳያስፖራው ዘንድ ኢሕአዴግ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚረዱ፣ የሚያሰማራቸው አባላት ይኖሩታል። ይሄ ደግሞ የሚጠበቅና ማንንም ሊያስገርም የሚገባ አይመስለኝም። ነገር ግን ኢሕአዴግ ሰውን ለማስገደል፣ አህማዲኒጃድ እንዳደረገው፣ ወዳጅ በሆነችው በአሜሪካ፣ የግድያ ስኳድ (ቡድን) አሰማርቶ፣ ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት ያበላሻል ብሎ ማሰብ፣ ኢሕአዴግን አለማወቅ ነው። ይቅርታ ይደረግልኝና፣ ኢሕአዴግ በውጭ ሆነው በባዶ የሚጮኹትን ንቋቸዋል። ቦታም አይሰጣቸው። ምንም ማድረግ እንደማይችሉ፣ መተባበር እንዳቃታቸው፣ የአለም አቀፉ ማህበረሰብን ጆሮ ያላገኙ መሆናቸውን ጠንቅቆ ያውቃል።

 

ኢሳት “የሕወሓት ሰላዮች” ሲል፣ ምን መረጃ ይዞ እንደዚያ እንዳለ አይገባኝም። የኢሳት ባልደረቦች ለኢሕአዴግ ጥላቻ ስላላቸው ብቻ ፈጥረው ያወሩት እንጂ ኢሕአዴግ ሰላይ ስለመላኩ፣ የላካቸውም ሰላዮች የግድያ ሴራ እየፈጸሙ ስለመሆናቸው ምንም መረጃ የላቸውም። አለን የሚሉ ከሆነ ደግሞ እስከአሁን ለሕዝብ የገለጹት ነገር የለም። “ሰላዮች” ብለው ሲሉም፣ ያውም በስህተትና በችኮላ፣ አቶ ጉሽን ብቻ ነው እንጂ የጠቆሙት ሌሎችን አልዘረዘሩም። ሁለት በሉ!

 

የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ባልደረቦች፣ ከደርግ ዘመን ጀምሮ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲያገለግሉ የነበሩ፣ የተከበሩ የተወደዱ ወገኖቻችን ናቸው። ስራቸውን ጠንቅቅው የሚያውቁ፣ የጋዜጠኝነት ፕሮፌሽናሊዝም የተላባሱ ባለሞያዎች ናቸው። ከFBI የተላከላቸውን ደብዳቤ ለአንባቢያን ማቅረባቸው እንደ ነውር ተቆጥሮ፣ ሊያስወቅሳቸውና ሊያሰድባቸው በቅቷል። በተለይም ጋዜጠኛ አበበ ገላውን ጨምሮ ለዲሞክራሲና ለጋዜጠኖች ነፃነት እንቆማለን የሚሉ ወገኖች፣ በጋዜጠኛ ሄኖክ ሰማእግዚአብሔር ላይ ያነጣጠሩት ክስ አስገራሚ ነው። እነዚህ ወገኖች በሚሰብኩት የማይኖሩ፣ እነርሱ ሲናገሩና አስተያየት ሲሰጡ እንጂ፣ ከነርሱ የተለያ አስተያየት ያለውን በተለይም እነርሱን ቻሌንጅ የሚያደርግን ሰው የማይታገሱ መሆናቸውን ነው እያሳዩን ያሉት።

 

ጋዜጠኛም ሆነ ማንም፣ ከኛ የተለየ አመለካከት ካለው፣ የኛን ሃሳብ ውድቅ ካደረገ፣ ወይንም ለመቀበል ካዳገተው መብቱ መሆኑን መረዳት አለብን። ቢቻል ሃሳቦቻችን ተቀባይነት እንዲኖራቸው የበለጠ መረጃዎች በማስቀመጥና አቀራረባችንን በመቀየር ለማሳመን እንሞክር። አለበለዚያም ላለመስማማት ተስማምተን (agree to disagree) መከባበር ይጠበቅብናል። እንጂ የሃሳብ ልዩነቶች አበሳጭተውን፣ በስሜታዊነት ወደ ግለሰብ ጠብ ወይንም ስድብና ክስ ማምራት የለብንም። ሦስት በሉ!

 

በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት ከቅንጅት መሪዎች ጋር ለሁለት አመት በቃሊቲ ማቀዋል። ከባድና ፈታኝ በሆነበት ሁኔታ፣ የግል ጋዜጣ ኤዲተር ሆነው በአገር ቤት ለበርካታ አመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ አገልግለዋል። እርሳቸው የሚያዘጋጁት ጋዜጣ አዲስ ድምጽ፣ ኢ.ኤም.ኤፍ.፣ አቡጊዳ፣ ኢትዮሜዲያ በመሳሰሉ ድረ ገጾች በነፃ ይወጣ ስለነበረ፣ በአገራችን ያለውን ሁኔት በቅርበት እንድንከታተል ረድቶናል። የፓልቶክ ክፍሎችም ይህን ጋዜጣ በየሳምንቱ ያነቡ ነበር። ይህ ጋዜጣ “አውራምባ ታይምስ” ጋዜጣ ነው። ዋና አዘጋጁም አቶ ዳዊት ከበደ ናቸው።

 

ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ፣ ከጥቂት ወራት በፊት አቶ ያሬድ ጥበቡን፣ በቅርቡ ደግሞ አቶ ጉሽ አበራን ቃለ መጠይቅ በማድረጋቸው “ወያኔ” ናቸው እየተባሉ ነው። በተለይም “አባ መላ” የሚባሉ ኢትዮጵያዊ የሚመሩት፣ የሲቪሊቲ ፓልቶክ ክፍል፣ እንግዳ ሆነው በመቅረባቸው፣ ብዙዎችን አስቀይመዋል። ለምን? “አባ መላ” የኢሕአዴግ ደጋፊ በመሆናቸው!!! በዳያስፖራ አለን ከሚሉ ተቃዋሚዎች አመለካከት የተለየ አመለካከት ካላቸው፣ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ከሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጋር ጋዜጠኛ ዳዊት መነጋገራቸው ወንጀል ሆኖ እያስከሰሳቸው ነው። አራት በሉ!

 

በኢሳት ፕሮፖጋንዳ አዝማችነት፣ በዳያስፖራ ስር የሰደደው ፖለቲካ፣ ምን ያህል የተበላሸና የቆሸሸ መሆኑን የሚያሳዩ ሌሎች ብዙ ምሳሌዎችን መዘርዘር ይቻላል።

 

እንደሚገባኝ፣ መሰረታዊ የሆነ የአስተሳሰብ ተሃድሶ መኖር እንዳለበት አስባለሁ። የዳያስፖራው ፖለቲካ ትልቅ ለውጥ ያስፈልገዋል። እንደ ኢሳት ያሉ፣ በኢዲቶሪያል ፖሊሲያቸው ቃል የገቡትን ጠብቀው፣ እራሳቸውን በማሻሻል፣ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ማስፋፊያና የሌሎች መሳሪያ ሳይሆኑ፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሠለጠነ፣ ዲሞክራስያዊ ሜዲያዎች ሊሆኑ ይገባል። አለበለዚያ እነርሱን እያዳመጥን፣ በገንዘብ እየረዳን፣ ሕዝባችንንና አገራችንን የሚጎዳ፣ የጥላቻ መንፈስ በመካከላችን እንዲሰፍን መፍቀድ፣ እራሳችንንም በዚህ ቁሻሻ ፖለቲካ ማጨማለቅ የለብንም።

 

ምን አለ የመወጋገዝና የመካሰስ ፖለቲካ ተወግዶ የመወቃቀስና የመተራረም ፖለቲክ ቢሰፍን?! የፖለቲካ ልዩነቶች ይኖሩናል። አንዳችን የምንደግፈውን ድርጅት ሌሎች ሊቃወሙት ይችላሉ። በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ሲቻል እንዲሁ በባዶ ጦር መማዘዝ ምን ይበጃል? አንድ ነገር መርሳት የለብንም። አገራችን ኢትዮጵያ ድሃ ናት። ብዙ የምንሰራው ሥራ አለ። ገና ረጅም መንገድ እንደ ሕዝብ መጓዝ አለብን። አሁን ባለው አይነት ሁኔታ፣ በዚህ በጥልቻ ድባብ ውስጥ ግን መቀጠል አንችልም። ፖለቲካችን መሰረታዊ የሆነ ተሃድሶ ያስፈልገዋል። አራት ነጥብ።

 

እንደ ኢሳት፣ ኢካዴፍ ያሉ ወገኖች ቆም ብለው እንዲያስቡ በአክብሮት እጠይቃለሁ። የሚዘግቡትን፣ የሚናገሩትን ይመርምሩ እላለሁ። የሚያፈርስ፣ የሚያራርቅ ሳይሆን አንድ የሚያደርግ፣ የሚያሰባስብ፣ የሚያስተምር ዘገባ ያቅርቡ። ኢሕአዴግን መቃወማቸውን ይቀጥሉ። ኢሕአዴግ የሚሰራቸውን ስህተቶች ያጋልጡ። ነገር ግን በስሜታዊነትና በጥላቻ ሳይሆን በሠለጠነ መንገድ ያድርጉት። ኢሕአዴግን እንደሚቃወሙትም ሁሉ፣ ኢሕአዴግ ለሚያደርጋቸውም መልካም ተግባራት እውቅና ይስጡ።

 

መቼም ኢሕአዴግ ምንም የሰራው ሥራ የለም ብሎ የሚከራከር፣ ወይንም የሚያምን ሰው ይኖራል ብዬ አላስብም። ምንም እንኳን በመልካም አስተዳደር፣ በሰብዓዊ መብት መከበርና በዲሞክራሲ ግንባታ አንጻር፣ በዘጠና ሰባት ከነበረው በጣም ያሽቆለቆለ ሁኔታ ላይ ብንገኝም፣ በልማቱ አንጻር አስደሳች ውጤት እየተመዘገቡ ነው። ግልገል ጊቤን፣ በለስ፣ ተከዜ፣ አባይ የመሳሰሉ ግድቦችን፣ ሊሰሩ የታሰቡ የባቡር ሃዲዶችን፣ መንገዶችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የጤና ጣቢያዎችን የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። የሚታዩ፣ የተጨበጡ ለውጦች በአገራችን እየታዩ ነው። ይሄ መደገፍ፣ መበረታታ አለበት።

 

በውጭ ግንኙነት አንጻር በሶማሊያና በሱዳን ኢትዮጵያ የተጫወተችውና እየተጫወተችው ያለው ሚና እንደ ኢትዮጵያዊ የሚያኮራ ነው። ለዚህም ኢሕአዴግ ሊመሰገን ይገባዋል።

 

ኢሕአዴግ ስላከናወናቸው መልካም ተግባራት መዘገብ፣ ከአሁን ለአሁን “ኢሕአዴግ መጥቀም ነው” በሚል ኢሳቶች እውነትን መደበቅ የለባቸው። የኢሕአዴግን መልካም ተግባራት ለመዘገብ መድፈርና መቻል አለባቸው። በኢዲቶሪያል ፖሊሲያቸው የሁሉን አመለካከቶች እናስተናግዳለን አይደለም እንዴ የሚለው? አዲስ ነገር አይደለም የምጠይቀው። ፖሊሲያቸው ላይ ያለውን በተግባር ያውሉት ነው የምለው።

አማኑኤል ዘሰላም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ