ግርማ ካሣ ከቺካጎ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.) ሰኔ 13 ቀን 2000 ዓ.ም.

 

ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት፣ ስለ ኤድስ ለመነጋገር በተጠራ ስብሰባ ላይ፣ አንዲት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑ የሕክምና ባለሞያ የተናገሩት አንድ አባባል ነበር። ያኔ ቀሳፊው የኤድስ በሽታ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ገድሎ፣ የሰው ልጆች ቀንደኛ ጠላት ከተባሉት ውስጥ ከመጀመሪያዎቹ መከከል የተመደበበት ጊዜ ነበር። ይህ በሽታ ከየት እንደመጣና እንዴት ሊስፋፋ እንደቻለ ሃሳብ የሚሰጡ በርካቶች ነበሩ። ታዲያ እኝህ ሴት የትኩረት አቅጣጫው ወዴት ሊሆን እንደሚገባ ለማስረዳት የአንድ ነብርን ምሳሌ አቀረቡ።

በሻሸመኔ አካባቢ፣ “ድንበር የለሽ ሐኪሞች” የተሰኘው ድርጅት በሚያንቀሳቅሰው የእርዳት መስጪያ ማእከል፣አንዲት እናት ልጇን ስታጥብ

ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት፣ ስለ ኤድስ ለመነጋገር በተጠራ ስብሰባ ላይ፣ አንዲት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑ የሕክምና ባለሞያ የተናገሩት አንድ አባባል ነበር። ያኔ ቀሳፊው የኤድስ በሽታ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ገድሎ፣ የሰው ልጆች ቀንደኛ ጠላት ከተባሉት ውስጥ ከመጀመሪያዎቹ መከከል የተመደበበት ጊዜ ነበር። ይህ በሽታ ከየት እንደመጣና እንዴት ሊስፋፋ እንደቻለ ሃሳብ የሚሰጡ በርካቶች ነበሩ። ታዲያ እኝህ ሴት የትኩረት አቅጣጫው ወዴት ሊሆን እንደሚገባ ለማስረዳት የአንድ ነብርን ምሳሌ አቀረቡ።

 

“ሰዎች ተሰብሰበው ባሉበት በአንዲት ቤት ውስጥ ድንገት መስኮቱን ሰብሮ አንድ ነብር ቢመጣ ምንድን ነው የምናደረግው?” ሲሉ በመጠየቅ ነበር ሴትየዋ ንግግራቸውን የጀመሩት። “እንዴት ማምለጥ ወይንም ነብሩን መግደል እንደሚቻል ነው እንጂ ቅድሚያ የምንሰጠው፣ ነብሩ እንዴትና በየት በኩል አድርጎ ከጫካ እንደወጣ አይነጋገሩም” ብለው ካስረዱ በኋላ ነበር ጊዜው ይህንን ቀሳፊ የኤድስ በሽታ የበለጠ ሰዎችን እንዳያጠፋ እንዴት መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ ላይ ውይይቱና ንግግሩ እንዲያተኩር ለጉባዔው ተሳታፊዎች ያሳሰቡት።

 

ይህንን ምሳሌ የጠቀስኩት ያለ ምክንያት አይደልም። ያኔ ነብሩ የተመሰለው በኤድስ በሽታ ነበር። አሁን ያንን ነብር በረሃብ እመስለዋለሁ።

 

በተለያዩ የሀገር ቤትና የውጭ የመገናኛ ብዙኀን እንደሰማነው ኢትዮጵያውያን በምግብ እጦት እያለቁ ናቸው። በደቡብና በምስራቅ ኢትዮጵያ ረሃብ ገብቷል። በተቀረው የአገራችን ክፍልም በኑሮ ውድነት ምክንያት በቀን ሦስቴ የሚበላው ኢትዮጵያዊ ከ5 በመቶ ይበልጣል ብዬ አላስብም። አንድ ኩንታል ጤፍ 1300 ብር በገባበት ሁኔታ የምግብ እጦት አንደኛውና ቀንደኛው የአገራችን ጠላት እንደሆነ ማየት እንችላለን።

 

ኢትዮጵያውያን በየጊዜው እርስ በርስ ብንጣላም አንድ ቤተሰብ ነን። ኢትዮጵያ ሀገራችንም ቤታችን ናት። ታዲያ በቤታችን ነብሩ-ረሃብ ሲገባ፣ አንዳንዶቻችንንም ሲገድል የሌሎቻችን መልስ ምንድን ነው መሆን ያለበት? “ረሃቡ እንዴት ሊመጣ ቻለ? ረሃቡን የፈጠረው እገሌ ነው” እያልን አሁን የምንወቃቀስበት ጊዜው ነውን? ወይንስ “መወቃቀሱን ለሌላ ጊዜ እንደርስበታለን፤ አሁን ነብሩን እንግደል” ብለን ነው መነሳት ያለብን?

 

እርግጥ ነው አለመተማመን በመካከላችን አለ። እርግጥ ነው ህዝባችንና ወገናችንን እንዳንረዳ የተደቀኑ አንዳንድ እንቅፋቶች ይኖራሉ። ነገር ግን እንቅፋቶችን አልፈን ለህዝባችን በዚህ ወቅት መድረስ ይኖርብናል። ፈረንጆች እስከመቼ እያጎረሱን እንኖራለን? የፈረንጅ እርዳታ ድርጅቶች እኛን ለማዳን ሲሯሯጡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከኛ የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት እንዴት ይሳነናል? በአዲስ አበባ ካለው አገዛዝ ጋር ባለን ችግር ምክንያትስ ስለምን በምግብ እጦት እየተጠበሱ ያሉ ሕፃናት ይቀጣሉ?

 

ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣

 

ዝነኛው ጥላሁን ገሰሰ ከሰላሳ ዓመታት በፊት በወሎ ድርቅ የተጎዱትን በማሰብ የዘፈነውን ዘፈን ማስታወስ እፈልጋለሁኝ።

 

“ዋይ ዋይ ዋይ ሲሉ፣

የረሀብን ጉንፋን ሲስሉ

እያዘነኩኝ በዓይኔ አይቼ

ምን ላድርግ አለፍኳቸው ትቼ

 

ወይ እማማ ወይ አባባ

ብለው ሲሉኝ ሆዴ ባባ

አስጨነቀኝ ጭንቀታቸው

ምንስ ሆኜ ምን ላርጋቸው

 

ሳያቸው ዓይኔ አፍጥጦ

ተለየኝ ልቤ ደንግጦ

ተብረከረከ ጉልበቴ

ምን ላደርግ ዋ ድህነቴ

 

በረሃብ ስቃይ ቸነፈር

ግማሹ ጎኔ ሲቸገር

ክው ብሎ ደርቆ አፋቸው

የእግዜር ውሃ ሲጠማቸው

 

በዱር አምባ የፈሰሱ

ለአቅም አዳም ያልደርሱ

ሁሉም ሕፃን ልጆች ናቸው

ምንስ ሆኜ ምን ላርጋቸው

 

ተዓምር ነው የአምላክ ሥራ

መቼ ያልቃል ብናወራ

አንዱን ጎርፍ አጥለቅልቆት

ሌላው ያልቃ በድርቀት

 

በዚህ ከንቱ ድልል ዓለም

መቼም ጠገብኩ የሚል የለም

የተገኘውን እንስጣቸው

ቸርነቱን አንንሳቸው”

 

(ለማዳመጥ ከዚህ በታች የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ! ካልሠራልዎ ደግሞ እዚህ ላይ ይጫኑ!)

 

 

አሁንም በብዛት እየረገፉ ያሉት ሕፃናት ናቸው። ምንም ነገር ይሆን እነዚህን ሕፃናት እንዳንረዳ እጆቻችንን ሊይዝ የሚችል ምክንያት ሊኖር አይገባም። ይህ በሀገራችን የተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ከፖለቲካ በላይ የሆነ በመኖርና ባለመኖር ላይ ያነጣጠረ አንገብጋቢ ቀውስ ነው።

 

በሀገር ቤት ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በፓርላማ ውስጥ ብሶት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ለምርጫና ለፖለቲካ ሥልጣን የሚሯሯጡትን ያህል አገር በቀል ከሆኑ የሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተጎዳው ወገናችን የሚያንሰራራበትን መንገድ በአስቸኳይ መቀየስ ይኖርባቸዋል።

 

እንዲሁም በውጭ አገር ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማኅበራት፣ አገዛዙን ከመኮነን ያለፈ ተጨባጭ ሥራ በጋራ የሚሠሩበት ጊዜው አሁን ነው። ወገኖቻችን ከዲሞክራሲ በፊት ዳቦ ነው የሚፈልጉት።

 

ለወገኖቻችን እርዳታ ገንዘብ ቢሰበሰብ፣ በአገዛዙ እጅ ሳያልፍ በቀጥታ ለተጎዱት እንዲደርስ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይቻላል። በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ ያሉ በርካታ ዓለም አቀፍና ሀገር በቀል ሰብዓዊ ድርጅቶች አሉ። በእነርሱ በኩል መርዳት የሚቻልበትን ፕሮቶኮል በውጭ ያሉ ድርጅቶች እራሳቸው ሊያመቻቹት ይችላሉ። ከእኛ የሚያስፈልገው ለመርዳት መነሳሳት ብቻ ነው።

 

“እኛ የምናደርገው እርዳታ ብዙም ለውጥ ሊያመጣ አይችልም” የሚሉ አንዳንዶች አይጠፉም። እንዲህ አይነቱ አባባል ነው ወደ ኋላ ያስቀረን። የ”አንችልም!” መንፈስ የድሆች ድሃና ለማኞች አድርጎናል። እንዴት አድርገን ነው የማንችለው? ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊ በውጭ ሀገር ይኖር የለም እንዴ? እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዓመት 500 ዶላር ቢመድብ (የአንድ መኪና አራቱን ጎማና ፍሬን መቀየሪያ ዋጋ) ግማሽ ቢሊዮን ዶላር አይደርስምን? ግምሻ ቢሊዮን ዶላር በአሁኑ ወቅት የከፋውን አደጋ ቢያንስ ቢያንስ በመላው ኢትዮጵያ ለዚህ ዓመት ማቃለል አይችልምን? እግዚአብሔር ቸር ልቦና ይስጠን! - አሜን!

 

በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ የዓመቱ የኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ውድድር ይከናወናል። በዚህ ውድድር ከሃያ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። የዚህ ስፖርት ውድድር አዘጋጅ የሆነው ፌዴሬሽን የተደራጀ አካል እንደመሆኑ መጠን ከአቅሙ በላይ በሆነ ችግር በረሃብ የተጠቃውን ወገናችንን ለማዳን የተደራጀ ሥራ ሊሠራ ይችላል ብዬ አምናለሁ። ለምሳሌ በምግብ እጦት ክፉኛ የተመቱ የተወሰኑ መንደሮችን በኃላፊነት ወስዶ በዚያ አካባቢ የሚደረጉትን የሰብዓዊ እርዳታዎችን መደገፍ ይችላል። ይህንን ያደርግ ዘንድ ከተለያዩ ወገኖች ጥሪ እየቀረበለት ነው። ፌዴሬሽኑ ለዚህ ወገን ለወገን ለሚያደርገው እርዳታ የመጀመሪያው ፈር ቀዳጅ መሆን ይጠበቅበታል። ይህንንም አጋጣሚ በመጠቀም በውድድሩ ስፍራ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያንን ለሰብዓዊ እርዳታ በማነሳሳት ታላቅ ሥራ ለመሥራት የኢትዮጵያዊነት አደራውን ይወጣል የሚል እምነት አለኝ።

 

ከታሰበበት የማይቻል ነገር የለም። በሚሊዮን የምንቆጠር ኢትዮጵያውያን በውጭ ሀገር እየኖርን ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ሲያልቁ ዝም ብሎ ማየት ወይንም ፈረንጆች እሰኪያድንዋቸው መጠበቅ ትልቅ የሞራል ውድቀት ነው። ከዚህ የሞራል ውድቀት እንድን ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳን! - አሜን!

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!