የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ፎቶግራፎችና ፖስተሮች ይነሱ! - ሪፖርተር ጋዜጣ(ሪፖርተር ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ)

የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሲያርፉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ሠርቷል። በጋራ አዝኗል፣ አልቅሷል፣ ሸኝቷል። ዓለምም ተገርሟል። ተደንቋል።

 

ሕዝብ ጨዋ መሆኑን አስመስክሯል። ማንም ሳያስገድደውና ማንም ሳይገፋው ከልብ ያደረገው ሽኝት ነውና።

 

ሐዘኑንና ሽኝቱን በከፍተኛ ደረጃ ለማድመቅም እጅግ በጣም በርካታና ትላልቅ ፎቶግራፎችና ፖስተሮች በከተማው በርካታ ሥፍራዎች ተሰቅለዋል። የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፎቶግራፍ ያልተሰቀለበት ጎዳና በአዲስ አበባ የለም ማለት ይቻላል። በሁሉም ሥፍራ አለ።

 

የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ፎቶግራፎችና ፖስተሮች ይነሱ! - ሪፖርተር ጋዜጣአሁን ግን ይብቃ! ፎቶግራፎቹና ፖስተሮቹ ይነሱ እንላለን። ሊያስተላልፉት የሚገባቸውን መልዕክት አስተላልፈዋል። ከአሁን በኋላ ግን በክብር እንደተሰቀሉ በክብር ይነሱ። ፖስተሮቹ ዝናብ፣ ንፋስና ፀሐይ እስኪያወርዳቸው፣ እስኪቀዳድዳቸውና እስኪጥላቸው መጠበቅ የለበትም። ዘላዓለማዊ ፖስተሮች ተደርገውም መወሰድ የለባቸውም። የተሰጣቸውን መልዕክት ፈጽመዋል። ከአሁን በኋላ እንደተሰቀሉ ማቆየት ማቆሸሽና ትርጉሙን ማሳጣት ነው።

 

በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ሕልፈት ከልብ ያዘነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፎቶግራፎቹና ከፖስተሮቹ በላይ ልባዊ ሐዘኑን በበቂ አስተላልፏል። ከልብ ስለታዘነ እስካሁን ድረስ ተሰቅለው የቆዩበት ጊዜ በቂ ነው። በፖስተሮቹና በፎቶግራፎቹ መሰቀል ለመነገድ፣ ለማስመሰልና ለማጭበርበር የሚፈልግ ሰው ካለም በቃህ ሊባል ይገባል። በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስም አትነግድ፣ አታጭበርብር፣ አታታል ሊባል ይገባዋል።

 

ስለሆነም ሕዝብም ሐዘኑን በአክብሮት ከልብ ስለገለጸ፣ አጭበርባሪም ሊያጭበረብር ሊፈቀድት ስለማይገባ ፖስተሮቹ በአግባቡ ተነስተው ይቀመጡ። ቤተሰብም በየሄደበት ሁሉ ፎቶግራፎቹን እያየ በየቦታው ሐዘኑ ሊቀሰቀስበት አይገባም። ንፋስ፣ ፀሐይና ዝናብ ሲያበላሻቸው ማየት የሚፈልግ ቤተሰብና ወዳጅም አይኖርም፤ የለም። የተሠራውን አዎንታዊ ሥራ ከልብ የሚያስተውልና የሚያደንቅ ወገን አርዓያነቱን ተከትሎ ለተግባራዊነቱ ይረባረብ። ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ የጀመሩዋቸው በርካታ አዎንታዊ ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉ ሁሉም ከልብ በተግባር ይጣር።

 

ትልቁን የዓባይ ግድብ ግንባታን ማጠናቀቅ፣ የባቡር መስመሮችን መዘርጋት፣ የስኳር ፋብሪካዎችን ማስፋፋት፣ ሕዝብን ከድህነት ማላቀቅ፣ ኢትዮጵያን ወደ መካከለኛ የገቢ ደረጃ ማሳደግ፣ ወዘተ የመሳሰሉት ራዕዮች በተግባር እንዲውሉ የሚያምን ሁሉ ከልብ ተግባር ላይ ያውል፤ ይታገል።

 

ፖስተሮችንና ፎቶግራፎችን የመለጠፍና የመስቀል እንቅስቃሴ ግን ይብቃ።

 

በነገራችን ላይ በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የክቡር አቶ መለስ “ፋውንዴሽን” እንዲቋቋም ወስኗል። አፅድቋል። ለምን ተቋቋመ ባንልም፣ ፋውንዴሽን ለማቋቋም ግን የግድ ፓርላማው ማወጅ አይጠበቅበትም። በቤተሰብ፣ በወዳጆች፣ በደጋፊዎችና በፖለቲካ ፓርቲዎች ፋውንዴሽኑ ሊቋቋም ይችል ነበር። በሕግ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ በፍላጎትና በእምነትም ማቋቋም ይቻላል።

 

ዋናው ቁም ነገር ግን ከፋውንዴሽን በላይ በተግባር መሥራት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አዎንታዊና ጠንካራ ጎን ለይቶ በማጥናትና አዎንታዊውን አስተሳሰብ ይበልጥ አጠናክሮ ሥራ ላይ ማዋል ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። በተገኘው አዎንታዊ ተግባር ላይ ተጨማሪ አዎንታዊ ውጤት ለማስመዝገብ ልንረባረብ ይገባል ብሎ የሚያምን ወገን ሊንቀሳቀስ ይገባዋል።

 

በተግባር የማይደገፍ የፎቶና የፖስተር መለጣጠፍ መንፈስ ግን ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። ሒደቱም በጊዜ ወሰን ውስጥ ሊከናወን ይገባል። በመሆኑም የዚህ ዓይነቱን ጨዋታ አቁመን ተግባር ላይ እናተኩር። ፖስተሮቹ ይነሱ። ፎቶዎች ይነሱ። እየተቀዳደዱና እየቆሸሹ ናቸው። መልዕክታቸውንም በበቂ መጠን አስተላልፈዋል። ወቅቱ ከፖስተር ሰቀላ ወደ ተግባራዊ ዕርምጃ የሚገሰገስበትና የምንመዘንበት ነው።

 

ቃላትም ትርጉም ይኑራቸው። በቃላት ድርደራ ብቻ “ራዕይ” እና “ሌጋሲ” እያልን እየለፈለፍን በተግባር ግን ራዕዩንና ሌጋሲውን የሚፃረር ሥራ የምንሠራ ከሆነ ያስተዛዝባል። የእሳቸውን ስምና ሥራ መነገጃና መደለያ የምናደርገው ከሆነ ከሞራል አንፃር ያስወቅሰናል ብቻ ሳይሆን በታሪክም እንጠየቅበታለን።

 

ወደ ፊት እንይ፤ ወደ ፊት እንገስግስ። በስፋት ይታዩ የነበሩ ደካማ ጎኖችን እንዳንደግማቸው፣ የተፈጠሩ አዎንታዊ ሁኔታዎችና ዕርምጃዎች ወደኋላ እንዳይመለሱ፣ አሁንም ተግባር ተግባር ተግባር እንላለን።

 

የቃላት ድርደራዎች ይበቃሉ። ፖስተሮቹና ፎቶግራፎቹ ይነሱ፤ ይውረዱ። በክብር እንደተሰቀሉ በክብር ይውረዱ።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!