ዳኛቸው ቢያድግልኝ

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ሀገርኛ በሆነ መንገድ ከውስጥ በፈለቁ ጠላቶች ጉልበት የማፈራረስና ከካርታ የማጥፋት ሂደት ሴራ የተፈለገውን ያህል ውጤት ባያመጣም ሀገሪቱን ግን የሁዋልዮሽ እየጎተተ እንደሚገኝ ይታወቃል። ስለምን ብለው እኒሁ የኢትዮጵያ ልጆች እናታቸውን ለመግደል ሀገራቸውን ለማፈራረስ ተነሱ? ፍጻሜያቸውስ ምን ሊሆን ነው? የሚለው ጥያቄ ሁሉንም ሰው የሚያሳስብና የሚገርምም ነው።

 

የፈለገውን ያህል ሚስጥራዊ ስራ ይሰራ፣ ምንም አይነት የጉልበት ጫና ይደረግ የፈለገውን ያህል የገንዘብና የመሳርያ ክምችት ይኑር ለውጥን ለቅጽበት ማገድ እንጂ ማቆም ከቶውኑም አይቻልም። አገር ለማፈራረስ ተነሱ የሚባሉትና ሀገር በማፈራረስ ከበሩ በሚባሉት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። ይልቁንም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ቆርጦ ሊታገል የሚገባው ጎጠኛነት መሰረት ያደረገ ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ አውጆ ሀገር እያፈረሰ ያለውን የትግራይ ተገንጣይ ድርጅት ‘ጅሃዳዊ’ እርምጃን ሊሆን ይገባል።

 

ሰሞኑን ከተለያዩ ዜናዎች ላይ የተለቃቀሙ የፊልም ቅንጫቢዎችን አስፈሪ በሚመስል ሙዚቃ በማጀብ አንድና ሁለት አረፍተ ነገር ከታሳሪዎች ድምጽ በመቀነጫጨብ ለማጅ የሰራው ፊልም ውሸት በማይታክተው ኢቲቪ ለእይታ ቀርቦ ተመልክተናል። ይህንን “ተጨፈኑልኝ ላታላችሁ” ድርሰት ተመልክቶ የሳቀ እንጂ የተሳቀቀ ይኖራል ብሎ የሚያምን የለም። የትግራይ ተገንጣይ ቡድን አሸባሪዎች በየጊዜው ቁልቁል የወረደ ነገር የሚያደርጉት መካከላቸው የነበሩ ጥቂት ሻል የሚሉ ሰዎች እንኳን አብረዋቸው ባለመኖራቸው መሆኑ በግልጽ እየታየ መጥቷል። እንደሁልጊዜውም የአምባገነን መንግስት ራሱን በልቶ የሚሞት ነውና፣ እራሳቸው አሸባሪዎቹ አሮጌ ሽፍቶች ሬሳ ሳጥን ውስጥ ሆነው የሰሩቱን ፊልም ማየት የሀገር ጉዳይ ግድ አስብሎን እንጂ የምርጫ ነገር ሆኖ አልነበረም። ጥንቆላና መተት በማሳየት ፊልም መስራት የጀመሩት የናይጄርያ ኖሊውዶች እንኳን እንዲህ ያለ ነገር አላደረጉም። ፍርድ ቤት ያለ ጉዳይ ውሀ አላነሳ ሲል በጉልበት ውሸት የሚጋተው የሀገራችን ሕዝብ ግን በጣም ያሳዝናል።

 

አሁን ካሳዩንም ጅሃዳዊ አረካት ሆነ አኬልዳማ ከሚለው ፊልማቸው አንጻር ቀደም ብለው የትግራይን ሕዝብ ሀውዜን ላይ በአውሮፕላን እንዲጨፈጨፍ ያደረጉትና ለእይታ ያቀረቡት ፊልማቸው እጅግ የተሻለ ነው። ምናልባት ያለቀው የትግራይ ገበያተኛና አውሮፕላኑ ሁሉም እውነተኛ በመሆናቸው ሊሆን ይችላል። ባለቁት የሀውዜን ሰዎች ምክንያት ደግሞ በሺህ የሚቆጠር ወዶ ገብና በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ዝቀውበታልና ተዋጥቶላቸዋል። ሌላው ገና ለሕዝብ እይታ ያልቀረበው አሪፍ ፊልማቸው ማለትም በመቶ ሺህ የሚገመቱ የትግራይ ረሀብተኞችን እንደ መንጋ ነድተው በማገት ጥቂት ጆንያ ማሽላና በሺህ የሚቆጠር ኩንታል አሸዋ ከምረው ለትግራይ ረህብተኞ ማሽላ እንግዛ ብለው ከውጭ ድርጅቶች በሚልየን የሚቆጠር ገንዘብ እነመለስና ስብሃት ሙልጭ አድርገው ያጋዙት የሚያስደንቅ ጭካኔ የተሞላበት ፊልም ይወጣው ነበር። ምስጋና ለገብረመድህን አርአያ ይሁንና ከዚህ መረጃ የምንረዳው ሕዝብ በማስጨፍጨፍ፣ በረሀብ በመፍጀት የፖለቲካ ትርፍ ማግኘትና የትግራይ መንግስት ለማቋቋም የሚደረግ አሸባሪነት የራሳቸው የከሳሾቹ ተግባር መሆኑን ነው። ያ ነው እነሱ የሚሉትን አይነት ጅሃድ እንጂ መብታችን ይከበር ማለት አይደለም። ሰሞኑን አንድ እብሪተኛ ከእንግሊዝ አበበ ገላውን መጣሁልህ ደምህን እጠጣዋለሁ ብሎ ሲያቅራራ የሰማነው አይነት ነው አሸባሪ ድርጊት የሚባለው። የሚያሳዝነው ግን ከገዛ አብራኩ በወጡ ክፉዎች ለግማሽ ምዕተ አመት መጫወቻ ሆኖ የኖረው የትግራይ ገበሬ ነው። ይሁን እንጂ

 

ለምን በስሙ ግፍ እንደሚሰፍሩለት የሚጠይቅ ብዙም አልተገኘም?

ስለ እስልምና ኃይማኖት ተከታዮች የተነገረው ሁሉ እውነት ከሆነ ደግሞ አልሻባብም ይሁን አልቃይዳ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲገቡ አሰራራቸውን ቀይረዋል ማለት ነው። ምክንያቱም ጥቂት ፌዴራሎች በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በቆመጥ እየደበደቡ ሲያሰቃዩ አንድም ፈንጂ አልፈነዳም፣ አንድም ፖሊስ አልተጎዳም። ስለ አሸባሪዎች እንዲህ ያለ ነገር የምንሰማው በኢትዮጵያ ብቻ ከሆነ አልቃይዳ ሰላማዊ ትግል ውስጥ ገብቷል ማለት ነው።

 

ሙስሊሞቹ ቱርክ ሄዱ፣ ግብጽ ደርሰው ተመለሱ፣ ክላሽንኮቭ ገዙ፣ ጁስ ቤት ከፈቱ ተብሎ የተነገረው አስቂኝን ፊልም ሲመለከቱ ወደሁዋላ መለስ ብሎ ታሪክ መቃኘትም ያስፈልጋል። ኢትዮጵያን የማፍረስ ራዕይ ይዞ የተነሳው መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ጋር ጦርነት በምታደርግበት ወቅት እሱ የሶማሌ ፓስፖርት ይዞ የሚዘዋወር ሰው እንደነበረ ማስታወሱ ሳይጠቅም አይቀርም። የጫካ ትግልን ለመማር ከአረብ ሀገሮች ስልጠና የወሰዱና በነርሱም እየታገዙ ኢትዮጵያን የወጉት የዛሬው የፊልም ደራሲዎች መሆናቸውን የማያውቅ ያለ አይመስለንም።

 

እስላማዊ መንግሥት ሊያቋቁሙ ነው ብሎ የሚከሰው የትግራይ መንግስትን ያቋቋመው ጎጠኛ ቡድን ግን ኤርትራና ትግራይን ለይቶ ቆርጦ ከአረብ ሀገራት ጋር አቆራኝቶ እኛ አረቦች ነን ማለቱን አዎሮፓና ሰሜን አሜሪካ በወቅቱ ይተናነቁዋቸው የነበሩ ሁሉ የሚያስታውሱት እውነት ነው። ያን ዘመን የቱ ትግራይ የትኛው ኤርትራ ተበሎ በማይለይበት ወቅት በየመኖርያ ቤቱ ተሰቅሎ የነበረው የካርታ ስዕል በአእምሮው ውስጥ የተቀረጸ ሁሉ ማን ኢትዮጵያን ለማጥፋት ይታገል እንደነበር አይዘነጋውም።

 

ሕዝብን ከሕዝብ በማጣላት ገላጋይ ሆኖ ተደላድሎ ለመኖር ሲባል ቤተክርስትያን ወይም መስጊድ ያቃጥል የነበረው ማን እንደሆነ ለሚያውቅ ሕዝብ፤ ከተማ ውስጥ ደግሞ ታክሲ ውስጥ ፈንጂ እያጠመደ አሸባሪዎች ለማለት ሲሞክር የተጋለጠው ማን እንደሆን ለሚያውቅ ሕዝብ፤ ይልቁንም ድልድይ በማፍረስ፣ ባንክ በመዝረፍ፣ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመተባበር ወንጀል ሲሰራ የኖረ ድርጅት ማን እንደነበር ላልረሳ ሕዝብ የዚህ አይነት ፊልም መስራቱ የሚያስታውሰው የወያኔን ክፋት እንጂ የሞስሊሞቹን ጥፋት አይደለም። በተለይ አባቱ እስላም እናቱ ክርስትያን ሆኖ ያደገውን የወሎን ሕዝብ አክራሪ፣ ተስፈንጣሪና አሸባሪ ማለት ለወሬም አይመችም። ከተከሳሾቹ መካከል ሁሴን አበጋዝና አህመድ ማሞ የሚመሰክሩልን ነገር ቢኖር አባት ክርስትያን ልጅ ሙስሊም መሆኑን ነው እንደምን ሆኖ ነው እነዚህ ሰዎች የእስላም መንግስት የሚያቋቋሙት? ምናልባት አበጃችሁ የሚለው ፍርፋሪ ለቃቃሚውና ፓርላማ የድጋፍ እጁን ሲሰቅል የሚኖረው ሆዳም እንጂ ሌላው ሕዝብ አይደለም። ይህ ሲባል ደግሞ በኃይማኖት ምክንያት አክራሪ የሆኑ የሉም ለማለት አይደለም። በነርሱ በመንደርደር የመብት ጥያቄ ያነሳውን ሁሉ አሸባሪ ማለት ግን ይቅር የማይባል ወንጀል ነው። በተለይ ወያኔ የተሸበረበት ዋናው ምክንያት እስላሙና ክርስትያኑ ችግራችን ጎጠኞቹና ሁዋላ ቀሮቹ ኢትዮጵያን እየዘረፉ ያሉት አሸባሪዎች ናቸው ማለቱ አሳሳቢ ስለሆነባቸው ጥርጣሬን ለመፍጠር ብለው እንደ ቸኮለ ጅብ ቀንድ የነከሱበት ፊልም መስራታቸውን ነው።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ አሸባሪዎች ስለመኖራቸው የማይካድ እውነት አለ። አሸባሪዎቹ ግን የስልጣን መንበር ላይ ፊጥ ብለው አገር እያፈረሱ ያሉ ዘራፊዎቹ የትግራይ ተገንጣይ ቡድን አባላትና ፍርፋሪ ለቃሚዎቹ ናቸው። ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት እንደኖረችው ሁሉ በኃይማኖት የተነጣጠለ ሳይሆን በሀገር ፍቅር የተሳሰረ ሕዝብ የሚኖርባት አገር ነች። የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች የመብት ችግር የክርስትና እምነት ተከታዮችም ሸክም ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ዳኛቸው ቢያድግልኝ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!