ወ/ሮ አዜብ መስፍን Azeb Mesfinታረቀኝ ሙጬ

የአሁኑን ዘመነ መንሱት አያድርገውና በዱሮ ጊዜ ሰዎች የሚሠነዝሩት ምክር አድማጭ አገኘም አላገኘም መካሪን የሚጎዳ ነገር እንደማይከተል ለመጠቆም "አፍ ወድቆ አይሰበርም" ይባል ነበር።

 


እኔም አሁን ያን ብሂል በማስታወስ ከወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውስጥ፣ ኢትዮጵያዊነቴ ቆርቁሮኝ ከዚህ በታች በቁጭት የማወሳውን ጉዳይ የሚያዳምጠኝና መፍትሄም የሚፈልግለት ወገን አላጣም ከሚል ቅን አስተሳሰብ በመነሳት ፍሬ ነገሩን አጠር አድርጌ አቀርባለሁ። የወያኔን ዕዝነ ልቦና ይክፈትልኝ።


የወይዘሮ አዜብ የድህነት ጉዳይ ጉዳዩን በቅርበት ለሚከታተለው የሁሉም ጎራዎች ኢትዮጵያውያን ወገኖች የጦፈ የመነጋገሪያ አጀንዳ ከሆነ ዋል አደር ብሏል፤ አንዳንዶች ምናልባትም ከሴትዮዋ የቀደመና የተለመደ ስድ ጠባይ አኳያ ጉዳዩን በመናቅ ከቁም ነገር ሳይጥፉት ቢያልፉም አንዳንዶች ደግሞ የሴትዮዋ አነጋገር ሊያስከትል ከሚችለው የሀገርን ስምና ክብር ለተጨማሪ ጊዜ ከማጠልሸት አንጻር አስልተውት ሲብሰከሰኩበትና ሲቆጩበት ተስተውለዋል - እኔ ከሁለተኞቹ ውስጥ ነኝ። 

 

ከኛም ባለፈ አንዳንድ የኛን ሁኔታ በሚከታተሉ የዓለም ዜጎች ዘንድም ወይዘሮዋ ኢትዮጵያን በብቸኝነት የሚወክሉ ይመስል ኢትዮጵያውያንን ከዚህች ሴት፣ ከወ/ሮ አዜብ የተለዬ ባሕርይ በተገኘ የእብለት ፍብረካ መክሊት እዬለኩ እኛም እንደሳቸው የነጭ ውሸት አቅማዳዎች ሳንመስላቸው የምንቀር አይመስለኝም፤ "መሪዎች እንዲህ ከሆኑ ሕዝቡስ በምን ሊለይ ነው?" ብለው ቢጨነቁ እነሱም የማይኮነኑበት እኛም የምናፍርበት መጥፎ አጋጣሚ የሚፈጠር ይመስለኛል። ይህ የሚያልፍ ዘመን የማያልፍ ሁለንተናዊ ጠባሳ እያስከተለብን እንደሆነ ከተገነዘብን ብንቆይም የአሁኑ ግን ከምን ጊዜውም የባሰ ሣይሆን አይቀርም። ከዚህ የሚቆጭና የሚያንገበግብ ሀገራዊ ጉዳይ ተነስቼ ነው እንግዲህ ይህችን አነስተኛ ማስታወሻ ለመንግሥት ለመላክ የተነሣሁት። ይህን ባላደርግ ኅሊናየ ይወቅሰኛል። ከኔ ከወጣ ደግሞ ያ ብቻውን ለጊዜው በቂየ ነው።

 

ውድ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናትና ታናናሽ የሥራ ኃላፊዎች!

የማተቤን ለመመስከር፣ እኔ ወይዘሮ አዜብ ድሃ ይሁኑ ሀብታም፣ ጤነኛ ይሁኑ በሽተኛ በቅርበት አላውቅም። እንደሕዝቡ ግን ከከባቢያዊ መረጃዎችና ከምድራዊ መንግሥት አጠቃላይ ባሕርይ በመነሣት ያለኝን ግምት መሠንዘር እችላለሁ። ስለሆነም እሳቸው እንደሚናገሩት ባለቤታቸው (የቀድሞው?) ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊና መላው ቤተሰባቸው በተጠቀሰው የአራት ሺህ ብር ገደማ ደመወዝ ልክ እንደኛው በኑሮ ውጣ ውረድ ችግር እየተጠበሱ ይኖሩ እንደነበር አላምንም ብቻ ሳይሆን ይህን እጅግ አጸያፊ ንግግር ሰምቶ ሊያምን የሚፈልግ ዜጋ ሁሉ - በዓላማ አንድነትም ይሁን በየዋህነት ወይም በሁለቱም- ከኃጢአተኝነት አያመልጥም የሚል ፅኑ እምነት አለኝ - ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ለጊዜው ትዝ በማይለኝ ምዕራፍና ቁጥር "በድሆች የሚያላግጥ ኃጢኣት አደረገ" እንዲል። በሀገር ውስጥ ያለን ዜጎች እንኳንስ እነመለስ ዜናዊና እነሱ ጃዝ ብለው የሚልኩብን በንግዱና በፖለቲካው የተሠማሩ የቀን ጅቦች እንዴት ያለ የተዘማነነ ኑሮ እንደሚኖሩ ነቃሽ ሳያስፈልገን እኛው ምሥኪኖቹ በሚገባ እናውቃለን።

 

በተጨባጭ መረጃ የተደረሰባቸው የቢሊዮኖች ዶላሮች ባለቤት መሆናቸው እንዳለ ሆኖ የመለስ ቤተሰቦች በሀገር ውስጥና በውጪው ዓለም እንዴት እንደሚኖሩ በመንጌ አገላለጽ ብታምኑም ባታምኑም ሕዝቡ በደንብ ያውቃል። በመሠረቱም መለስና ቢጤዎቹ ቅጥፈትና መሠሪነት፣ ግድያና ሙስና እንደበጎ ባህል በሚቆጠርበት የፖለቲካ ዐውድ ውስጥ እንጂ የተራድዖ ድርጅት ውስጥ በአመራር ሰጪነት እንዳልነበሩ እንረዳለን። በዛሬ ዘመን የሃይማኖት ቁንጮዎች ሣይቀሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብትና ንብረት በሚያፈሩበት ወቅት እነመለስ እንደማርያ ተሬዛና እንደአበበች ጎበና ለረድኤት የተቀደሰ ዓላማ ከድሆች ጋር ጎዳና ለጎዳና እንዲንከራተቱ አንጠብቅም(በግል አውሮፕላኑ የሚንሸራሸረውንና በግል ቤተ መንግሥታዊ ግቢው የሚዝመነመነውን ናይጄሪያዊ ሰባኬ ወንጌል እዚህ ላይ በማጣቀሻነት ያስቧል)። በዚያ ላይ መለስ ዜናዊ ሃይማኖት ያልነበረው ሰው መሆኑን በራሱ አንደበት ስለገለጸ ለየትኛው ጽድቅ ብሎ ወይም የትኛውን ኩነኔ ሊያስቀር ብሎ እንደባሕታዊ በመቁነን ሊኖር እንደሚፈልግ ጨርሶ አይገባኝም።

 

የዚህ ውሸት ዓላማ ጭራሹን የማይገባን ከነዚህ ነጥቦች አንጻር ነው። ሴትዮዋ ራሳቸው ግራ ተጋብተው ግራ እያጋቡን ናቸው። ድህነቱ ካልተጫናቸው የግል ሀኪም እንዲኖራቸው ቢያደርጉና ጤንነታቸውን ቢፈትሹ መልካም ነው። ለድሆች በነጻ የሚቆም የሥነ አእምሮ ሀኪም ካለም ከአሁኑም ሳይብስባቸው ኢሕአዴግ ራሱ ይፈልግላቸው፤ አለበለዚያም ድህነታቸውን በሚኖሩበት ቀበሌ አስመስክረው አማኑኤል ሆስፒታል እንዲቀበላቸው ቢደረግ አይከፋም። ያኔ እንዲያውም በሳቸውና በባለቤታቸው አብደው ይህን ሆስፒታል ያጥለቀለቁ ዜጎች ድነው ስለሚወጡ ለርሳቸውና ለመሰል አዲስ አባጆች ይሰፋቸዋል - "አባጆች" ከሚለው "ባ"ን ላላ አድርጓት።


እዚህ ላይ የኔም ሆነ የብዙዎቻችን ጥያቄ ይህን ሊሰሙት የሚቀፍፍ የውሸቶች ሁሉ የበላይ የሆነ ታላቅ የሚሌኒየም ውሸት ለምን ዓላማ አሁን በድጋሚ ማንሣት አስፈለገ? የሚለው ነው - እርግጥ ነው - ባልም ሚስትም የዚህ "ድሃ ነኝ" የማለት ልክፍት ሰለባ መሆን ዛሬ የተጀመረ አይደለም፤ አፈሩን ገለባ ያድርግለትና መለስ፣ "እዚያች መደርደሪያ ላይ ከምታያቸው መጻሕፍት በስተቀር ሌላ የኔ ነው የምለው ሀብትና ንብረት የለኝም" ሲል ያላፈረ፣ "ሰው ቀርቶ ትንኝ አልገደልኩም" በማለት በሣቅ ካንፈራፈረን ሌላው ማፈሪያ የቀድሞ መሪያችን ጋርም በውሸታምነት የሚስተካከል ብቻ ሣይሆን አልፎ የሚያስከነዳ እንደነበር እናውቃለን። መሬታችን የምታፈራው ግን ምንድነው? ሰው እየተቀበረ የእንግዴ ልጁ እያደገ ይሆን እንዴ? የዚህ ሁሉ መርገምት መንስኤው ምን ይሆን? አይጨንቃችሁም? ሀገርና ሕዝብ ስንት ጊዜ ይቀጣል? ዳዊት ለፈጣሪው "እስከማዕዜኑ ትረስኣኒ ሊተ" ያለው ለዚህ መሆን አለበት - መረሳቱ ቆጭቶት።


ሴትዮዋ ይህን የማይጨበጥና እኛን ዐዋቂዎችን ቀርቶ ጡጦ የሚጠባ ሕጻንን እንኳን ሊያሞኝ የማይችል የድህነት ወሬ ለሆነ ዓላማ ሊጠቀሙበት ቢፈልጉ እንኳ በሀገር ላይም ሆነ በሴትዮዋ በራሳቸው እንዲሁም በኢሕአዴጋውያን መንደር እስከመመለክ በደረሰው በታላቁ ባለራዕይ መሪ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን አሉታዊ ተፅእኖ የሚገነዘብ አንድ ብልህ ሰው ከኢሕአዲግ ውስጥ እንዴት ሊገኝ አልቻለም? "!ኧረ ጎበዝ ይቺ ሴት ገደል እየጨመረችን ናት!" የሚል አንድ አቅል ያለው ሰው ይጥፋ? ሁሉም ተያይዞ ደንቆሮ ይሁን? ምን ዓይነት ተፈጥሮ ነው? ኢሕአዴግ እንደኢሕአዴግነቱ በሕይወት ካለ ትልቅና ፈታኝ ጥያቄ ይመስለኛል - ይህ ድርጅቱ ሰው አልባ እየሆነ የመምጣቱ ችግር።

 

ሴትዮዋ ሊሳሳቱ ይችላሉ፤ ሀዘን ላይ ስለሆኑ፣ ላጣው እችል ይሆናል ብለው የሚጠራጠሩት አንዳች የሥልጣንና የጥቅማ ጥቅም ቦታ ሊኖር ስለሚችል፣ በሀዘን ምክንያት አእምሮኣቸውና ሥነ ልቦናቸው ተቃውሶ ሊሆን ስለሚችል፣ ቀድሞ ባላቸው አቶ ተማቹ ሳይሞት ይኖሩበት የነበረውን ጎስቋላ ግን ከአሁኑ የተሻለ የድህነት ኑሮ ስለሚያስቡና አሁን ደግሞ የባሰ ችግር ገጥሟቸው ሊሆን ስለሚችል፣ በትምህርት የገፋ ስብዕና ስለሌላቸው... በነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሣ ጤናማ አስተሳሰባቸው ተዛብቶባቸው ይህንና ከዚህም የከፋ ኅሊናን የሣተ የመዘባረቅ ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ - በዚህ ወቅት ግን ባጠገብ ሰው ሊኖር ይገባል። ኢሕአዴግ እንደድርጅትና እንደተቋም ይህን መሰሉን ጠርዝ የለቀቀና በማንኛውም መለኪያ ከዕብደት ያልተናነሰ ምናልባትም የበለጠ ድርጊት ሃይ ሊለው በተገባ ነበር። ከአንድ ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ድርጅት ሕይወት የአንዲት ተራ ተጋዳላይ ሕይወት እንዲበልጥ የተደረገበት ዕንቆቅልሽ ይሁንታዊ ይሁን የነገሮች ግጥምጥም በጭራሽ ሊገባኝ አልቻለም።


በሌላ አቅጣጫ ሳስበው ሁኔታው ባሏን የጎዳች መስሏት የገዛ አካሏን በጋሬጣ እንደወጋችሁ ቂል ሴት ይመስለኛል። ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ያዋረደ መስሎት ይህ የሴትዮዋ ንግግር ሲሰራጭ በሞኝነት ዝምብሎ ተመልክቶ ከሆነ የተጎዳው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሣይሆን ራሱ እንደሆነ ሊረዳው ይገባል። በበኩሌ ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ተሠርቷል - ታሪክ አለ ብሎ ለሚያምን ወገን ማለቴ ነው።


ይህ መጥፎ ክስተት - በጥሞና ለተመለከተው ወገን - ኢትዮጵያን አያዋርድም፤ ኢትዮጵያውያንን በጭራሽ አያሣጣም። ይህ መረን የለቀቀ የጅልነትም ይሁን የብልጣብልጥነት ሥራ በብቸኝነት የሚናገረው የኢሕአዲግን ተፈጥሮ ነው። የተዋረደው እርሱ ራሱ ነው። ለእኛ እንዲያውም በእርግማን የተሸፈነ ምርቃት ነው - ፈረንጆቹ "Mixed blessing" ወይም " Blessing in disguise" እንደሚሉት። መነሻ የሴትዮዋ ዓላማ ምንም ይሁን ምን - ዕብደትም ይሁን ቅዠት - ለእኛ ግን "ኢትዮጵያውያንን የሚመሩ እነዚህ ሰዎች ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው ? ለካንስ ይህን ያህል የዘቀጠ ስብዕና ያላቸው ናቸው?" በሚል ሌሎች የዓለም ዜጎች ችግራችንን እንዲረዱልኝ የሚያደረግ ፈልገን የማናገኘው አጋጣሚ ነው - መረዳት ለሚፈልግ። በውነቱ እንደነዚህ ያሉ ሰዎችን እንኳን በመሪነት በተመሪነት ደረጃ ማግኘት ራሱ የሀገርን ሁለንተናዊ መራቆት የሚያመለክት የክስረት ምልክት ነው። (ወዴት እየሄድን ይሆን? አያሣፍርም?)


ኢሕአዲጋውያን ሳይቀሩ በሀፍረት የተሸማቀቁበትና በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት እርስ በርስ እየተፈራሩ አንዳችም አስተያየት እንኳን ለመስጠት ያልደፈሩበት፣ የእርምት እርምጃ እንዲደረግበት ባለመፈለግም ለሣቅና ሥላቅ የተጋለጡበት ይህ ታሪካዊ ህፀፅ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ታላቅ ስህተት ነው - ዋጋ ስል በአፍሪካዊ የዋጋ ትመና በዱላ ብቻ አታስሉት። የሆነው ይሁንና የችግሩ ወገብ አገዳ ይህ ከፍ ሲል የተገለጸው ሆኖ ቀጣይ ዳፋም እንዳለው ቀጥለን እንመለከት።

 

ቀጣዩ ዳፋ በከተማችን እየተወራ ያለው ነገር እውነት ከሆነና እኚሁ ሴት "ከነድህነታቸው" የአዲስ አበባ ከንቲባ ከሆኑ ነው። ወይዘሮ አዜብ መስፍን ወይም በአያታቸው በደጃች ጎላና በበረሃ የሥራ ጠባያቸው ምክንያት አምሣ በግ ፈጅ የጎላ ድስት ብቻ ለብቻ ከማገላበጣቸው አንጻር በተደረበላቸው ስም ሲጠሩ አዜብ ጎላ በሕዝብ ከመሾማቸው በኢሕአዲግ የተሻሩትን በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ የሕዝብ ተመራጭ ከንቲባ ዶክተር ብርሃኑ ነጋን ተክተው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቱ ከንቲባ ሲሆኑ ይታያችሁ። "እስመ አልቦ ነገር ዘይሰዓኖ ለእግዚአብሔር" የሚለው ለኢሕአዲግ ተገልብጦ ብዙ ጉድ እየታዘብን ስለሆነ የአዲስ አበባ ሕዝብ 99.9 በመቶ ወይዘሮ አዜብ ካልመሩኝ ብሎ አሻፈረኝ እንደሚልና በካርዱ "እንደሚመርጣቸው" ሰሞኑን እናይ ይሆናል - እግዚአብሔር ጥላውን ጥሎልን ይህን ህልም ወደ ቅዠት ካልለውጠልን ዕዳችን ገና ተከፍሎ የማያልቅ ሊሆን ነው።(የቬንዞላው ኒኮላስ ማዱሮ በጠባብ ውጤትም ቢሆን በማሸነፉ እንኳን ደስ አለው፤ የሥልጣን ነገር መድሓኒት የሌለው መጥፎ በሽታ በመሆኑና ተገቢና ትክክለኛ ቢሆንም እንኳን ሽንፈትን መቀበል ለብዙዎች የማይዋጥ መራር ክኒን በመሆኑ ይህን ውጤት ለመቀበል እያንገራገረ የሚገኘው ካፕሪሌም መጽናኛውን እንዲልክለት በዚሁ አጋጣሚ እጸልይለታለሁ፤ "ምን አገባህ" አይባልም- ነውር ነው - የሰው ልጆች ሰላም የሁላችንም ሰላም ነውና።)

 

ውድ ኢሕአዲጋውያን! በምታምኑበት ይሁንባችሁ - ሰይጣንም ይሁን ግዴለኝም - በርሱው ይሁንባችሁና እባካችሁን የዛሬን ይህችን ምክር አድምጠሩኝ። ከሕዝቡ አንዳችም ተቃውሞ አትጠብቁ - እስካሁንም እንደማትጠብቁ ሁሉ። የምታደርጉት ሁሉ ለሕዝቡ አይሞቀውም አይበርደውም፤ እኛና እናንተ በተለያዬ ምህዋር እንደምንኖር ታውቃላችሁ ብዬ እገምታለሁ። ሌላው ቀርቶ አነስተኛና ቀጫጭን -ማነው - ጥቃቅን የምትሏቸውና ብቻችሁን ሮጣችሁ ራሳችሁ ከራሳችሁ ጋር ለምትወዳደሩበት ምርጫ የምትጠቀሙባቸው የራሳችን ናቸው የምትሏቸው ልጆች እንኳን የሚጠጓችሁ ለጥቅም እንጂ ወደዋችሁ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ምድባችሁ "Power comes out of the barrel of a gun." ብለው ከሚያምኑ አፄ በጉልበቱዎች መሆኑን እናንተም ሆናችሁ እኛ እናውቃለን። ግን ግን አንዳንዴ ታዲያን ግፍ ሲሠራ እየተስተዋለ ቢሆን ክፍያው ተመጣጣኝ እንዲሆን ለማድረግ እንዲቻል የወደፊት ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩም በላይ የጥፋቶች ውጤት ተካካይ የአጸፋ ክፍያ እንዲኖራቸው ያደርጋልና የዕዳ ቁልል ላለማሰቀመጥ በኔ ይሁንባችሁ ይቺን ምክሬን ስሙኝ።


እናም ይህን አጠቃላይ እውነት በመገንዘብ እኚህ የተከበሩ የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት እንደተከበሩ እንዲኖሩና የ(ቀድሞ) ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ስም ከመቃብር እያወጡ በክፉ እንዳያስጠሩ ከዚህ ሺሞት - ማለትም ሹመት - ነጻ አድርጓቸው፤ ይረፉበት - ይበቃቸዋል። ችሎታና ሙያ ሊኖራቸው ይችላል። ነገር ግን የሰሞኑን ያገጠጠ የሴትዮዋን ኑዛዜ መሰል ሀፍረተቢስ የፈጠራ ወሬ ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሕዝብ እንደማይመርጣቸው እየታወቀ የዓለም መሣቂያ በሆነ አላዲናዊ ምርጫ ሕዝብ እንደመረጣቸው በማስመሰል የአዲስ አበባን ከንቲባነት ብትሰጧቸው ሕዝቡ ስለታፈነ አማራጭ ባይኖረውና ወድዶ ሣይሆን እንደሁልጊዜው ሁሉ በዝምታው የተቀበለ ቢመስልም የኢትዮጵያ አምላክ የሚለቃችሁ እንዳይመስላችሁ። ዕዳችሁን አታብዙ፤ የእስካሁኑ ንቀትና ትዕቢት ይብቃችሁ። አሁን በዚህች እንኳን ካሱን።(F. Marshal Dr. Pro. Hajji Aladin is the major character of the comedy film entitled 'the dictator', please miss it not, and watch it now!"


ሌላ ሰው ያጣችሁ ያህል እሳቸውን ከንቲባ ብታደርጉ እኔም በበኩሌ እረግማችኋለሁ። አንጀትን ለማራራትና ልመናን እንዲሰማ ለማድረግ እርግማንን በቅድመ ሁኔታነት ማስቀመጥ ያልተለመደና ፍሬያማነቱ ላይም አሉታዊ ድባብ እንደሚጥል ብገነዘብም ሌላ የተሻለ አማራጭ አጣሁና ያንኑ መቀጠሌ ነው፡- ወይዘሮ አዜብን ከንቲባ ብታደርጉ በእሳቸው ውስጥ ያለው የመርገምት ደዌ በእናንተም ላይ ይደር - ዱሮውንም ሠፍሮባችሁ ከሆነ ደግሞ ተፋፍሞ ይቀጥልና እርሱም በበኩሉ ትንሣኤ ኢትዮጵያን ያፋጥን። ምክሬን ባትሰሙ ጥቁር ውሻ ውለዱ። መቀመጫው ላይ ቁስል ያለበት ውሻ እንደልቡ አይጮኽም እንዲሉ በሀገርና በሕዝብ ላይ በሠራችሁት ወንጀልና የግፍ ሥራ ምክንያት ብዙዎቻችሁ እንደተሸነፈ ውሻ ምናባዊ ጅራታችሁን ወደ ጭኖቻችሁ ጣብቂያ ወትፋችሁና በፍርሀት ካባ ተጀቡናችሁ ይህን ትልቅ በደል ሀገርና ሕዝብ ላይ ብትፈጽሙ በቁማችሁ የሥጋና የመንፈስ ተንከራታች ሁኑ፤ ስትሞቱም ምድር አትቀበላቸሁ - መቀመቅ ውረዱ - የሰማያት በሮችም በተንከራታቿ ነፍሳችሁ ላይ ይከርቸሙ። ይህ የኔ የግል እርግማን ነው። ይህችን ሃሳብ በዚህ መልክ ለመግለጽ አማራጭ በማግኘቴ፣ ፍላጎት፣ ጊዜና መንገድም ስላገኘሁ በዚህ ሁኔታ የራሴን እርግማንና ከዚያ በፊትም ምክርና ተግሣጽ ቢጤ ለገስኩ እንጂ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠረው "ወገናችሁ" በየቤቱ ሰማይና ምድር ተደፍተውበት በችጋር አለንጋ እየተሸነቆጠ፣ በርሀብና ጠኔ እየተቆራመደ አንጋጥጦ ወደፈጣሪው በመጸለይ ለመንበረ ፀባዖት የማይቀር የመጨረሻ ፍርድ አጋልጦ እየሰጣችሁ ነው።

 

ዛሬ ምንም ስላልሆናችሁ ሁልጊዜ እንደዚህ እንደሆናችሁ ትቀራላችሁ ማለት እንዳልሆነ ተገንዘቡና ያደቆነ ሰይጣን ሳያስቀብር ባይለቅም ከተቻላችሁ አሁኑኑ ፖለቲካዊ ንስሃ ግቡ። ደግሞም ምንም አልሆንም ብላችሁ አታስቡ። አትሞኙ፤ እናውቃለን - ማወቃችንንም ታውቃላችሁ፤ እንተዋወቃለን። ምንም ያልሆናችሁ እንዳልሆናችሁ ልብሳችሁና አኗኗራችሁ የሚያሳብቁት ነገር እምብዝም ባይኖርም - ልብስ ሲሰፋና ሲንዘለዘል ማስጠበብ ወይም አዲስ መግዛት ስለሚቻል - ከሀኪም ቤት ጋር ያላችሁ የዘወትር ቁርኝትና የኅሊና ወቀሣን ለጊዜው ለመሸሽ በየምሽት ክበባቱና የእርቃን ዳንስ ቤቶች ውስጥ መሽጋችሁ በዝጉብኝ የምታሳልፉት የአሥረሽ ምቺው ቅብዝብዝ ሕይወታችሁ አፍ አውጥተው ይናገራሉ። አጭር መልእክቴ ይህችው ናት። የምለያችሁ በጸሎት ነው። ፈቃደኞች የሆናችሁ ቀጣዩዋን ጸሎት አብረን እንጸልያት። መጸለይ ትርፍ የለውም ተብሎ ቢታሰብም እንኳን ኪሣራ ሊኖረው እንደማይችል ግን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ - ኪሣራ የሌለውን ነገር ደግሞ መሞከሩ አይከፋም። እንደእውነቱ ጸሎታችን ልባዊ ከሆነ ደግሞ ጸሎት ትርፍ እንጂ ኪሣራ ኖሮት እንደማያውቅ የልብ ጸሎተኞችን ጠይቆ መረዳት ይቻላል። ዋናው እምነት ነው - የክርስቶስን ቃል ልዋስና የሰናፍጭ ቅንጣት ታህልም ብትሆን እምነት ካለን ፈጣሪ መሻታችንን እውን ያደርግልናል። ችግራችን ...። አሄሄ ... አሁንማ ምን የሌለን ችግር አለ? ብቻ ሆድ ይፍጀው ነው።

 

ፈጣሪ ሆይ፣ ለኢሕአዴግ ልብ ስጠውና - ይዋል ይደር እንጂ - ከምንሰማውና ፈጽሞውንም እንደማይቀር ከምንጠብቀው የሦርያን መሰል ምድራዊ መከራና ስቃይ ታደገን!!


አንድ ኔልሰን ማንዴላና አንድ ኤፍ ደብሊው ደክለርክ በአንድ አዳር ፈጥረህ ካለደም መፋሰስ ነጻነታችንን አጎናጽፈን! ሁሉንም እንደምትችል እናምናለንና።


እስካሁን ድረስ ከትዕዛዛትህ ውጪ በተጻራሪ ጎራዎች እየቆምን በተለይ እኛው በኛው ላይ ያወረድነው መቅሰፍት ከበቂ በላይ ነውና እባክህን አባት ሆይ ያዞርክብንን ፊት መልስልንና ከአሁን በኋላ በቃችሁ በለን፤ ከስደትና ከፍልሰት፣ ከቂም በቀል አዙሪትና በዘርና በጎሣ እየተቧደኑ ከመጠፋፋት፣ ከእሥራትና ከህገወጥ የመንግሥት ግድያና ጭፍጨፋ ነጻ አውጣን። እኛም ሕዝብህ ነንና አትተወን፤ ከኛ ወገን መልካም ሥራ ባይኖር በልጅነታችንና በአባትነትህ ብቻ በምሕረት ዐይኖችህ ተመልከተን።


እንደጨው ዘር በመላዋ ዓለም የተበተኑ ኢትዮጵያውያን ልጆችህን በያሉበት ጠብቅ፤ ከሀገር ቤቱ ወያኔያዊ በቋንቋና በነገድ የመከፋፈል በሽታን አላቅቃቸው፤ ራሳቸውን ተቅመው ሀገርና ወገናቸውን እንዲጠቅሙ ባርካቸው - ቀድሳቸውም። በዕውቀትና በጥበብ ገንብተህ ሀገራቸውን በአዲስ መሠረት እንዲያንጹ ለዳግመኛ ጊዜም ገናናዋ ኢትዮጵያ እንደቀድሞው ኃያልነቷና ሥልጣኔዋ እንድታንሠራራ ያደርጉ ዘንድ ዕድሉን ስጣቸው። እኛን በሀገር ቤት የምንገኘውንም ከተዋራጅነትና ከደቀቀ ሥነ ልቦናዊ ሕይወት አውጥተህ አዲስና ለመብቱ የሚሟገት ሰውነት አላብሰን። አሁን ያለንበት አሣፋሪ ሁኔታ ተወግዶ የገባንበት የራስ ወዳድነት ክርታስም ተቀዳዶ አንገታችንን ቀና የምናደርግበት የሁላችንም የሚሆን ዘመን እንዲብት በአዲስ መንፈስ ሙላን፤ ልዩነቶቻችን ጌጦቻችን እንጂ የጦርነት ዐውድማ እንዳይሆኑና እንደ እስካሁኑ እንዳያጨራርሱን ወይም የጎሪጥ እንድንተያይ እንዳያደርጉን ፈቃድህ ይሁንልን። አሜን።


ታረቀኝ ሙጬ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ