ይኸነው አንተሁነኝ

የዚህ ጽሁፍ መነሻ ሰሞኑን የህወሓት ደጋፊ የሆኑ ራዲዮኖች ጋዜጦች ድረ ገጾችና መወያያ ክፍሎች ከአማራው ወገናችን መፈናቀል ጋር በተያያዘ እያሉት ያለው ፍጹም ሚዛን የጎደለው ሀዘኔታ ያልዳሰሰው ከዚያም ሲከፋ ጭካኔ የተሞላበት ንግግር ነው።

 


ይህን ከመሰሉት ንግግሮች ተጠቃሚው ማሕበረሰብ የትኛው ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አስቸጋሪ ነው፤ የሚጠቀም ማሕበረሰብ ካለ ማለቴ ነው።


የራሱን መጥፎም ሆነ በጎ አሻራ ትቶ ቢያልፍም ሀገራችን ከውስጥም ሆነ ከውጭ በተቀሰቀሱ አካባቢን ከአካባቢ ጎሳን ከጎሳ አንደኛውን ሃይማኖት ከሌላኛው ሃይማኖት ሲያጋጩ የነበሩ ብዙ ፈታኝና በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ወቅቶችን አልፋለች። ቀጥሎ የመጣውም ተከታታይ ትውልድ ከነዚህ ፈታኝ ወቅቶች ተምሮባቸዋል እየተማረባቸውም ይገኛል ከህወሓትና ጭፍን ደጋፊዎቹ በቀር። ሀገራችንም አንድነቷን ጠብቃ ሕዝቦቿን በባንዲራዋ ስር አስተባብራ የዘለቀችው ሕዝቦቿና መሪዎቿ ወቅታዊ የሆኑ ችግሮችን ከሀገር አንድነትና ሉአላዊነት ነጥለው በማየታቸው ነበር።


በቀደመው ወቅት ለሀገራዊ አጀንዳ መልሱ ሀገራዊ ነበር። የአንድ አካባቢ ወይም ሕዝብ መጠቃት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቃት ወይም የሀገር መደፈር ተደርጎም ይቆጠር ነበር። በጊዜው ሊያስተባብሩን ሊያወያዩን ሊያገናኙን የሚችሉ ብዙ የጋራ የሆኑ ነገሮች ነበሩን። ከነኝህም ሀገር ባንዲራና ሃይማኖት ዋና ዋናዎቹ ነበሩ። እነኝህን ግሩም የጋራ እሴቶቻችንን ቀስ በቀስና ፍጹም በተቀናጀና በእቅድ በመመራት ህወሓት እያጠፋቸው ይገኛል። ይህንንም የህወሓት እኩይ ተግባር አእያወቁ ተባባሪ በመሆን ወይም ሳያውቁ በጭፍን ደጋፊነት ስለ ትክክለኛነቱ እየሰበኩ የሚገኙት ራዲዮኖች ጋዜጦች ድረ ገጾችና መወያያ ክፍሎች ከጆሯቸው ይልቅ አይናቸውን ማመን የሚገባቸው ወቅት ነው ዛሬ። ከሀገር አቀፍ እስከ ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች እየዘገቡት ያሉትን ህወሓት የፈጠራቸው የሕዝባችንና የሀገራችን ችግሮች አላይም ብሎ በስማ በለው የሚያኖጉበት ዘመን አይደለም ዛሬ ለህወሓት ደጋፊዎች። አንዳንዴ ትብብርን ለሚሹ ሀገራዊ ችግሮችና ለእንደዚህ አይነቱ ፈታኝ ወቅት ማሰብም አስፈላጊ ነው።


ህወሓት መራሹ አገዛዝ ሀገራችንን ከተቆጣጠረበትና ሕዝባችንንም በየምክንያቱ ከፋፍሎ በግፍ መግዛት ከጀመረበት አንስቶ በሀገራችን የተለያዩ ማሕበረሰቦች ላይ አሰቃቂና ጠላት እንኳ ሊያደርጋቸው ይችላሉ ትበለው የማይገመቱ ድርጊቶችን ሲፈጽም ቆይቷል። በምስራቅ ሀገራችንን ከጅቡቲ ከሶማሊያና ከኬኒያ በሚያወስነው አካባቢ የሚኖረው የኦጋዴን ሕዝብ ሰቃይ የኢትዮጵያ ዳርፉር እስከመባል የደረሰ ነው። የሀገርም ሆነ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች አያውቁትም፤ እርዳታ ሰጭ ሰብአዊ ድርጅቶች አይጎበኙትም፤ ሌላኛው ወገኑ ለዚህ ሕዝብ እንዳይደርስ እንኳ ከራሱ ያላነሰ ችግር በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥጥርና ወከባ ይደርስበታል፤ የአካባቢው ሕዝብ በህወሓት ፖሊሶችና ወታደሮች እንደተፈለገ ሲደረግና ኢትዮጵያዊነቱን እንደ እርግማን እንዲያስብ ሲሆን፤ አብሮ መኖር ምንም ጥቅም አላመጣልኝም እንዲልና መለያየትን እንዲመኝ በጉልበት ተጽእኖ ስር ሲወድቅ የህወሓት ደጋፊ የዜና አውታሮች የሌት ከቀን ወሬ ስለአካባቢው የማይታይ ልማት ብቻ ነበር።


ለዘመናት በኢትዮጵያ አንድነት ኮርቶ የኖረውና ከጅቡና ከኤርትራ የሚዋሰነው የአፋር ሕዝብ ከኖረበትና ካለማው ቦታው በልማት ሰበብ ተፈናቅሎ የትም ሲበተን እያዩ የህወሓት ደጋፊዎችና የዜና አውታሮች ግን የአስረሽ ምችው ዘፈን ላይ ነበሩ። ከዚህም በከፋ መልኩ የተወሰኑ የአፋር ክልል አካባቢዎች የኛ እንጅ የእናንተ አይደለም በሚል ሰበብ አፋሮች ተገፍተው ክልሉ በሕወሃቶች ሲወረርና ሲከለል የህወሓት ደጋፊዎችም ሆኑ የዜና አውታሮቻቸው ለነሱ ደስ የሚል ሌላ የልማት ቅዠት ላይ ነበሩ።


ሀገራችንን ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያዋስነው ጋምቤላ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ለሽያጭ ሲቀርብ፣ ኗሪው ሕዝብ ያላግባብ ሲዋከብና የዘር ማጥራት ሲፈጸምበት የወያኔ ደጋፊዎች ምንም አላሉም። አማራውን ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲያሳድዱት ሐወሃትና ደጋፊዎቹ ደን ስለጨፈጨፉ ነው ማለታቸው ሲታወስ ደግሞ ንግግሩን አንደሬት የሚመር ያደርገዋል ምክንያቱም ዓለም ከተፈጠረች አግር ያላረፈበትንና አስፈሪና አስደማሚ ደን ያለበትን የጋምቤላ ክልል ነውና እንደፈለጉ እንዲያደርጉት ለአረብና ለህንድ ነጋዴዎች አሳልፈው የሰጡት።


በደቡብ ከደቡብ ሱዳን እና ከኬኒያ ጋር በሚያዋስኑን ክልሎች አካባቢ የሚኖረው ሕዝባችንም ለስሙ በስኳር ፋብሪካና በመብራት ሃይል ግንባታ ስበብ የከፋ ጉስቁልናና መሳደድ ሲደርስበትና ኢትዮጵያዊነቱን እንዲጠላ ሲገፋ የህወሓት ደጋፊዎችና የዜና አውታሮች ትንሽ እንኳ ለእውነት የሚቀርብ ነገር ለመናገር አልደፈሩም። ይልቅስ ህወሓት ሽህ ዓመት ንገስ እያሉ በረከተ ዜማ ከማውረድና ይደልዎ እያሉ የማይገጣጠም ቅኔ ዘረፉ እንጅ ወደ ህሊናቸው ተመልሰው ከጆሯቸው ይልቅ እየሆነ ያለውን የሚያይ ዓይናቸውን ለማመን አልሞከሩም።


በምእረብ ከደቡብ ሱዳንና ሱዳን የምንዋሰንበት የቤኒሻንጉል ክልል ሕዝብ በተለመደው ልማት ሰበብ ከሚደርስበት የራሱ መከራ በተጨማሪ ከሌሎች አጎራባች አትዮጵያዊያን ሕዝቦች ጋር በሰላምና በትብብር እንዳይኖር ህወሓት እየሰራ ይገኛል። ይህንንም ተከትሎ ሰሞኑን ህወሓት አማራውን ከዚህ ክልል ውጣ አገርህ አይደለም ብሎ በማባረር የቤኒሻንጉልን ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ከሌላው ወገኑ ጋር በማጋጨት አንድ እንዳይሆን በርትቶ እየሰራ መሆኑን እያየን ነው። የህወሓት ደጋፊዎችና የዜና አውታሮቻቸው ግን ይህንንም ድርጊት እንደለመዱት ትክክል እንደሆነና ሁሉም ወደ መጣበት መመለስ እንዳለበት እየወተወቱን ይገኛሉ። ከዚያም ሲያልፍ ከአህጉራችን አልፎ በዓለም ፊት ማፈሪያ ሆነውን የህወሓት አገዛዝ በአፍሪካ የሚቀናበትና አንቱ የሚባል እያሉ ያንቆለጳጵሱታል እኒሁ ደጋፊዎች።


ከነዚህም በተጨማሪ በመላው ኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በሲዳማ እንዲሁም በሌሎች የደቡብ ክልሎች ላለፉት የህወሓት አገዛዝ ዘመናት ሳይቋረጥ የቀጠለው አንዱ ከሌላው እንዳይቀራረብና እንዳይተባበር የማድረጉ እንቅስቃሴ የነበረንን የመተሳሰብ መንፈስ ጎድቶታል። ለወጥሮው በአንድነት ሊያቆሙን ይችሉ የነበሩት ሀገራዊ ስሜት ላንዲት ባንዲራ በጽናት የመቆምና የመታገል ፍላጎት እና ሃይማኖቶቻችን ቀስ በቀስ እኛን አንድ አድረገው ስብስበው እንዳይዙ እየተደረጉ ነው። ባሁኑ ሰአት ያን የድሮውን ወኔ ቀስቅሶ ለትብብር የሚያጓጓ ነገር አልተወልንም ህወሓት። ይህም ቢሆን ግን ለህወሓት ደጋፊዎችና የዜና አውታሮቻቸው የጥንካሬያችን ያንድነታችን መለኪያ መታወቂያ ምልክት ነው።


ይህ ሁሉ ሲጠቃለል እንግዲህ ሀገራችን ከጎረቤት ሀገሮች በምትዋሰንባቸው አካባቢዎች የሚኖረው ወገናችን ባንዱ ወይም በሌላ ምክንያት ከመሃል ሀገር ወገናችን ጋር እንዲቋሰል ተደርጓል። አንደኛው ክልል እራሱን የቻለና በምንም መልኩ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ እንዲሰማው በብዙ ተደክሟል። በድንበር አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ እየኖረበት ያለው ክልልና በውስጡ የሚገኘው ሃብት የራሱ እንጅ የሌላው ኢትዮጵያዊም እንዳልሆነ እንዲያስብ ህወሓት ባለፉት አገዛዝ ዘመኑ ሁሉ በርትቶ ሰርቷል። ከሌላው የዓለም አካባቢ ለመጡት የሚሰጠው የመስራትና አብሮ የመኖር ፈቃድ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ለምን እንዳልተሰጠ ወይም እንዳልተፈቀደ በዚህ አካባቢ ያለው ሕዝብ እንዳያስተውል ቢያስተውል እንኳ በሕወሃቶች ዝም እንዲል ተደርጓል። ይህና የህን የመሳሰለው ነገር ለህወሓት ደጋፊዎችና የዜና አውታሮቻቸው ያሳሰባቸው አይመስልም "በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ" እንደሚባለው መሆኑ ነው።


ስለሆነም ፈጠሪ ክፉን ያርቅ እንጅ ሀገርን የሚዳፈር አንድ ወራሪ ሃይል ቢመጣ ህወሓት በየምክንያቱ ያቋሰለውን ይህን ሕዝባችንን አንድ አድርጎ የሚያስነሳው ቅመም ምን ይሆን? እምቢ ለሀገሬ አምቢ ለድንበሬ ብሎ በመነሳት ያስተባብር የነበረውን የየአካባቢውን የጎበዝ አለቃ አንድ ያደርጉት የነበሩት ሀገር ባንዲራና ሃይማኖት ባግባቡ እንዳይሰሩ ተኮላሽተዋል። ህወሓት ከሀገር ይልቅ በብሄር ብቤረሰብና አካባቢ ላይ በማተኮሩ አንድነታችን ቋጠሮው የተፈታ ያህል ላልቷል። መተሳሰባችንና መተባበራችንም የዚያኑ ያህል ተጎድቷል። አንደኛው የህዝባችን ክፍል ሲጎዳ ለምን በማለት ለእርዳታ በመነሳት ፋንታ የሩቅ ተመልካች መሆን ከጀመርን ቆይተናል። ለዚህም ይመስላል በጣም በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ በተለይ ላለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አማርኛ ተናጋሪው ብቻ እየተለየ ሲገረፍ ሲገደልና ሀብቱ እየተወረሰ ሲባረር የሌላው አካባቢ ኢትዮጵያዊ ምንም አለማለቱ።


ህወሓት የራሱን ፍላጎት ለማሳካት እኛን እነዲህ ከፋፍሎ እንዳንተባበር የቻለውን ሁሉ ሲሞክር እኛስ ወደፊት ሀገራዊ አንድነትንና አብሮ መቆምን ለሚሹ ወቅቶች አናስብምን? በክፉ ዘመን ከጎን የሚቆምን ወዳጅ በሰላም ወቅት ማስቀየምና ማባረርስ እስከመቼ ይቀጥላል? የህወሓት ደጋፊዎችና የዜና አውታሮቻቸውም መለያየትንና ቂም በቀልን ከምትሰብኩ ይልቅ አንድነትን ለሚሹ ወቅቶች መሰረት ለመጣልና እና ከሕዝብ ጎን ለመቆም ከዚህ የተሻለ ጊዜ የላችሁም። የምታዩትን ብቻ በመናገርና በመጻፍ ወገንተኝነታችሁን አስመስክሩ ከህሊናም ሆነ ከሕዝብ ፍርድ የምትድኑት በዚህ መንገድ ነውና።


ይኸነው አንተሁነኝ
ሚያዚያ 16 ቀን 2013 እ.ኤ.አ.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ