ኤፍሬም እሸቴ

ታላቁ የክርስቲያኖች ጾም፣ ዐቢይ ጾም እነሆ የመጨረሻው "ሰሙነ ሕማማት"/ስቅለት ላይ ደረሰ። ለእምነቱ ተከታዮች የአጽዋማት ሁሉ በኩር እና ዋነኛ (ዐቢይ) እንደመሆኑ ከምንም በዓል በላይ በታላቅ መንፈሳዊ ስሜት የሚከበር ነው። የእምነቱ ተከታይ ላልሆነውም ወገን ቢሆን የሚኖረው ባህላዊ አንድምታ ከፍ ያለ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ታሪኩን በደረቅ ንባብ ለሚመለከተውም ቢሆን ከዕለት-ተዕለት ሕይወቱ ጋር ሊያስነጻጽረው የሚችለው ብዙ ቁም ነገር እንደሚያገኝበት ጥርጥር የለኝም።

 

 

ዐቢይ ጾም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም ነው። ከጾሙም ጋር የጌታን ሕማም፣ መከራ መስቀል እና ትንሣኤውን የምናስብበት ብቻ ሳይሆን በታላቅ ሁኔታ የምናከብርበት ወቅት ነው። በምግብ ደረጃ ክርስቲያኖች ከጥሉላት ምግብ (ከእንስሳት ተዋጽዖ) ተከልክለው፣ በጾም በጸሎት፣ በስግደት፣ በምጽዋትና በሌሎችም ምግባረ ሠናያት የሚያሳልፉበት ሰሞን።

 

ቅዱስ ያሬድ ሳምንታቱን የየራሳቸው ስያሜ እንዲኖራቸው ባደረገው መሠረት እያንዳንዱ ሰንበት የሚጠራበት የተለየ ስያሜ ሊኖረው ችሏል። በየሳምንታቱ ያለውም ምንባብ፣ ዝማሬ እና አጠቃላይ አገልግሎት በዚያው መንፈስ የተቃኘ ነው። ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መጻጉዕ፣ ደብረ ዘይት፣ ገብር ሔር፣ ኒቆዲሞስ፣ ሆሳዕና እና ትንሣኤ እሑዶቹ የሚውሉባቸው ዕለታት ስያሜዎች ናቸው። የጾሙ እኩሌታ "ደብረ ዘይት" እና የሰሙነ ሕማማት መግቢያ ሳምንት ላይ የሚገኘው "ሆሳዕና" በሁሉም አማኝ ዘንድ የሚታወቁ ናቸው። ሌሎቹ ስሞች አማኙ ለቤተ ክርስቲያን ትምህርት ባለው ቅርበት እና ርቀት የሚወሰኑ ናቸው።

 

በቅዱስ ያሬድ የስያሜ ተርታ መሠረት ያለፈው እሑድ "ሆሳዕና" ነበር። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ እና በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት፣ ሕዝቡ የዘንባባ ዝንጣፊ እያርገበገበ፣ ልብሱን ከመንገድ ላይ እያነጠፈ እና "ሆሳዕና" እያለ እየዘመረ ጌታውን የተቀበለበት በዓል። ኢየሩሳሌም እንዲህ ባለ ደስታና ክብር የተቀበለችውን ጌታ ከሞት ሁሉ በከፋ ሞት ያውም በመስቀል ሞት እንደምትገድል ስንረዳ ከሆሳዕና ሆታና ክብር በኋላ "መስቀል እና ስቅለት" የመከተሉን ምስጢር እንድናሰላስል ያደርገናል።

 

በርግጥ የአይሁድ ካህናት ከመጀመሪያውም ትምህርቱን አለመቀበል ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን በእጁ ተዓምራት እና በቃሉ ትምህርት መማረኩን አልወደዱትም። "ናሁ ኩሉ ዓለም ተለዎ ድኅሬሁ፤ ዓለሙ ሁሉ ተከተለው እኮ"፣ ምን ብናደርግ ይሻላል ብለው መምከራቸውም የተለመደ አጀንዳቸው ነበር። ለዚህ "ችግር" መፍትሔ ያደረጉት ደግሞ ገድሎ መገላገልን ነው። ተከራክረው ባያሸንፉት፣ በጎ ሥራ በመሥራት፣ እንደ እርሱ ሙት እያስነሱ እና ሐንካሳ እየፈወሱ የሰዉን ልብ ማግኘት ባይችሉ ያንን ያደረገውን ለማጥፋት ወሰኑ። ዛሬም ድረስ ያለ የደካሞችና የጨካኞች መፍትሔ። ማጥፋት።

 

ይህ ክርስቶስን በመስቀል ሞት የመግደል ተንኮል ተጠንስሶ፣ ተቀምሞ እና ተዘጋጅቶ የቀረበው ሕዝቡን በዕውቀት፣ በሃይማኖት፣ በመንፈስ ልዕልና የበላይነት ይመራሉ ተብለው በሚታመኑት በአዋቂዎቹ ነው። ሌላው ሕዝብ ተከታይና ጀሌ እንጂ አድራጊና ፈጣሪዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው።

 

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ክርስቶስን ይከተል ነበር። ትምህርቱን ይሰማሉ፣ ጥቂቱን እንጀራና ጥቂቱን አሳ በተዓምራት አብዝቶ ሲመግባቸው ራባቸውን ያስታግሳሉ፣ ሕመምተኞቻቸውን ይፈውስላቸዋል። በአንድ ወቅት እንዲያውም "ለምን አናነግሠውም" ብለው አስበውም ነበር። ከረሃብና ጥም ከታደጋቸው፣ ከበሽታ ከፈወሳቸው ሌላ ምን ይፈልጋሉ። እንዲህ የሚያደርግ ንጉሥ ማን ይጠላል። የእርሱ አመጣጥ ምድራዊውን ንግሥና ለመሻት አይደለም እንጂ።

 

ታዲያ እንዲህ ሊያነግሠው የፈለገ ሕዝብ በጥቂቶቹ ነገር-ሠሪዎች ተንኮል ለመስቀል ሞት ሲያበቁት "ይህማ አይሆንም፣ ተርበን አብልቶናል፤ ታመን ፈውሶናል፣ ሙታንን ሲያስነሣ፣ እውር ሲያበራ፣ ሽባ ሲተረትር/ሲያረታ ተመልክተናል" ብለው ጥብቅና አልቆሙለትም። ("ጥብቅና የሚቆምለት የሚሻ" ባይሆንም)። እንዲያውም በፍርድ አደባባይ "ይህንን ሁሉ ካደረገላችሁ ከኢየሱስ እና በወንጀል ከታሠረው ከበርባን ማን እንዲፈታ ትፈልጋላችሁ" ሲባሉ "በርባን ይፈታልን" ማለታቸውን እናነባለን። ኢየሱስንስ? ቢባሉ "ስቅሎ! ስቅሎ!" ማለት "ስቀለው! ስቀለው!" አሉ። ሆሳዕና ብለው እንዳልዘመሩለት፣ ልብሳቸውን እንዳላነጠፉለት፤ ጥቂት ቆይተው "ይሰቀል! ይሰቀል" ብለው ጮኹበት።

 

በክርስቶስ ላይ የተዋለው ግፍ ብዙ ነው። ከመጀመሪያም እንኳን ለሞት - ለወቀሳ የሚያበቃ ጥፋት አላገኙበትም። ትዕግስተኛው ጻድቁ ኢዮብ እንደተናገረው "በእውነተኛ ሚዛን" ሳይመዘን፣ መበደል አለመበደሉ ሳይታወቅ (ሎቱ ስብሐት፣ በደል የሚስማማው አምላክ አይደለም) በፍርደ ገምድልነት እና በነገር ሠሪነት ለመስቀል ሞት አብቅተውታል።

 

በትክክለኛ አዕምሮ ካስተዋልነው ከረሃባቸው የሚታደጋቸው፣ በሽታቸውን የሚያርቅላቸው፣ ሙታኖቻቸውን የሚያስነሳላቸውን ሊጠሉት አይገባም። ነገር ግን ሆነ። ትክክለኛ አዕምሮ በምን ይሸነፋል ከተባለ ነገር መሥራት በሚችሉ ምላሶች ብሎ መመለስ ይቻላል። አገር በምን ይደነቁራል ከተባለ በክፉ አስተሳሰቦች እንደማለት ነው።

 

እንደ ሥርዓታቸው ከሆነ የሚሰቀል ሰው አይገረፍም፣ የሚገረፍ ሰውም አይሰቀልም። ክርስቶስን ግን ገርፈውትም ለመስቀል ሞት አብቅተውታል። ፍርደ ገምድልነት እና ግፍ ጽዋዋ ሲሞላ አይሆንም የተባለ ነገር በሙሉ ይሆናል። በጤነኛ አዕምሮ የማይታሰብ ነገር በሙሉ ይፈጸማል።

 

የግፍ ጽዋ ሲሞላ ሰዎች ግፍ መሥራትን፣ ደም ማፍሰስንና ንጹሐንን መስቀልን ይለማመዳሉ። ደም የሚያፈሱት ብዙ ጠበቃና ደጋፊ ያገኛሉ፣ ደማቸው ደመ ከልብ የሚሆነው ንጹሐን ደግሞ ብቸኞች ሆነው ይገኛሉ። በደስታቸው ጊዜ ዘንባባ ያውለበለበላቸውና ልብሱን ያነጠፈላቸው ሰው፣ ሲቸገሩና ቀን ፊቷን ስታዞርባቸው ዞር ብሎ ሳያያቸው ይቀራል።

 

ልብ ብለን ካስተዋልነው፣ ድምጽ የሌላቸው ብዙዎች ድምጻቸው ሊሆን የሚችል ብዙ ሰው ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም። ችግሩ ከተገፉት ጋር መቆም ከገፊዎች ጋር የሚያጣላ በመሆኑ - ከመስጋት እንጂ። በክርስቶስ የመስቀል ጉዞ ውስጥ ተዋናይ የሆኑትን ሰዎችና አቋማቸውን ስንመለከት ዛሬም የመከራ መስቀል በሚሸከሙ ሰዎች ሕይወት ውስጥ የምንይዘውን አቋም እንድንፈትሽ የሚያስገድድ ብዙ ትምህርት እናገኝበታለን።

 

ክርስቶስ በመስቀል ላይ በዋለ ጊዜ ተከታዮቹ በሙሉ ተበትነዋል። እንኳን በሕይወቱ፣ ቅድስት ነፍሱ ከቅዱስ ሥጋው ከተለየች በኋላም ቢሆን "የክርስቶስ ወዳጅ" ላለመባል ሁሉም የአቅሙን ሞክሯል። መግረፍ የሚችለው ገርፏል፣ ማንጓጠጥ የሚችለው አንጓጧል፣ መቸንከር የሚችለው ቸንክሯል። በጦር መውጋት የሚችለው ወግቷል።

 

በዚህ ሁሉ መካከል ደግሞ ከራሳቸው ከሰቃልያኑ ከሊቃውንቱ መካከል የሆነና እውነትን ለመመርመርና ከእውነት ጋር ለመቆም ያልፈራ ኒቆዲሞስ የሚባል ሊቅ ሰው ተገኝቷል። ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ጌታ እየሄደ ይማር የነበረና ቅዱስ ያሬድም ከዐቢይ ጾም ሳምንታት አንዱን በስሙ የሰየመለት ሰው ነው። ይህ ሰው ከወገኖቹ ሊመጣበት የሚችለውን ችግርና መከራ ሳይፈራ የክርስቶስን ሥጋ ለመቅበር የጠየቀ እና ተሳክቶለትም በክብር የቀበረ አንደኛው ሰው ነበር።

 

ምንም እንኳን የግፍ ጽዋ ቢሞላም አዕምሯቸውን የጠበቁ፣ እውነታቸውን ሙሉ ለሐሰት ያላስረከቡ ሰዎች ከመካከል ይገኛሉ። የሰው ልጅ የመንፈስ ልዕልና በየዘመናቱ የሚተርፈው እንደዚህ ባሉ ሰዎች ብርታት ነው። ከአይሁድ ሸንጎ መካከል ተቀምጦ ነገር ግን ክርስቶስን ለመደገፍ መነሣት እንዴት ከባድ ውሳኔ ኖሯል? እንዲህ ያለ ሰው ከየት ይገኛል? ሕዝቡ ሁሉ "ይሰቀል ይሰቀል" የሚለውን ሰው "እውነተኛ ነው፣ ለምን ይሰቀላል?" የሚል አንደበት ምን ያህል ያስደንቃል?

 

በርግጥ ክርስቶስ ሰው የሆነው በሞቱ የዓለምን ኃጢአት ለማስተስረይ ነውና በመስቀል ሞት ለመሞት ፈቅዷል። በፈቃዱ እንደሞተ ከሦስት ቀን በኋላ መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ሙስና-መቃብር (በመቃብር መበስበስን) አጥፍቶ ተነሥቷል። የሰቀሉት ቀብረው ሊያስቀሩት አልተቻላቸውም። ከሆሳዕና ሆሆታ በኋላ የቀራንዮ መስቀል፣ ከዕለተ አርብ መስቀል በኋላ ደግሞ ትንሣኤ አይቀርም። ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ እግዚአብሔር በሰላም።

ይቆየን - ያቆየን!!


ኤፍሬም እሸቴ

(ይህ ጽሑፍ አዲስ አበባ በሚታተመው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው።)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!