አብርሃም ያየህ

ማ ስ ታ ወ ቂ ያ

የግንቦት 7 ዋና ፀሐፊና የድርጅቱ ያመራር አባል የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ከቅርብ ቀናት በፊት ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለመጠይቅ አማካኝነት በሰነዘሯቸው የተለያዩ አብይ ሃሳቦችና፣ ከቃለ-መጠይቁ ውጭ ነገር ግን ተያያዥ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮች፣ መሰረት በማድረግ ለመወያየት ወስኛለሁ።

 

በውይይቱ ለመሳተፍ የፈለግኩበት ምክንያት፤

ያቶ አንዳርጋቸው ወቅታዊና አነጋጋሪ ቃለመጠይቅ የበርካታ ኢትዮጵያዊያኖችና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኖች ሰሞነኛ ትኩስ የመወያያ ርዕስ ሆኗል። በተለይ ትኩረት የተሰጠው የውይይት ርዕስ ደግሞ፣ አቶ አንዳርጋቸው አፅንኦት ሰጥተው ሰፊ ማብራሪያ የሰጡበት፣ ማለትም - ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት ማድረግ አስፈላጊነቱና ጠቃሚነቱ የሚመለከተው ክፍል ነው። ብዙ ሰው እንደሚያወቀው፣ እኔም የወያኔና የሻዕቢያ ግጭት በተከሰተ ማግስት (ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት መሆኑ ነው) ወደ ኤርትራ በመሄድ ከኤርትራ መንግሥትና ህዝብ ጋር መገናኘቴና መመካከሬ ይታወሳል። ከኤርትራ ጉዞየ መልስ፣ ከኤርትራ መንግሥትና ህዝብ ጋር የሚደረገው ግንኙነት ያለው ዘላቂ ፋይዳ ምን እንደሆነ በማስመልከትም "የኤርትራ ፋይል ሲከፈት" በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ሰፊ መጣጥፌ አማካኝነት ለህዝብ ይፋ አድርጌያለሁ።

ሰፊውና በተከታታይ እትሞች የተስተናገደው መጣጥፌ፣ ውጭ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያኖችና ትውልደ ኢትዮጵያዊኖች ለማድረስ በማቀድ፣ ካናዳ በሚታተመው "ሐዋርያ" በተባለ ጋዜጣ አማካኝነት አስተናግጃለሁ። ሀገር ቤት ለሚኖረው ህዝባችን ለማድረስ ደግሞ፣ አሁን የኢሳት ባልደረባ የሆነው (መልካም አጋጣሚ ሆኖ የቅርብ ጊዜውን የአቶ አንዳርጋቸው ቃለ መጠይቅም ያስተናገደው) ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ይመራውና ያኔ ሀገር ቤት ይታተም በነበረው "ኢትኦጵ" በተባለ እውቅ መጽሔት አማካኝነት አስተናግጃለሁ።

ይሁን እንጂ፣ ያገራችን መሰረታዊ ችግር ሁሌም የሊሂቆቻችንና የፖለቲከኞቻችን (በተለይ የአማራ ብሔር ኤሊቶቻችን) የማዳመጥና የመደማመጥ ባህል እጥረት ነው። በመሆኑም፣ አሁን አቶ አንዳርጋቸውን እያደነቁና እየካቡ ያሉት በርካታ ሰዎች (በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆች) ያኔ እኔን ለማዳመጥ ግን አልተጉም። ተምረናል፣ ተመራምረናል ከሚለው ከኔ ትውልድ ይልቅ፣ ከፈሪሃ እግዚአብሔር እምነታቸው በመነጨ ምክንያት ይበልጥ ጥበበኞችና ብልሆች የነበሩ ጥንታዊያን ወላጆቻችን እንዳሉት - "ቀድማ ያሸተች ማሽላ፣ አንድም ለወፍ አሊያም ለወንጭፍ ትዳረጋለች" ሆነና፣ በትክክለኛ ጊዜ ያስተላለፍኩት ትክክለኛ መልዕክት በፅሞና ለማዳመጥ አልተፈለገም። አላዳመጡም ብቻ ሳይሆን፣ ይባስ ብሎ ከወያኔ ካድሬዎችና ጋሻጃግሬዎች ባልተናነሰ መንገድ ሊሸነቁጡኝ የቃጡ ተቃዋሚ ነን ባይ ጋጠወጦችም በወቅቱ አልታጡም ነበር።

እውነቱን ለመናገር ያህል፣ በደርግ ውድቀት ዋዜማ ከካርቱም ተነስቸ አዲስ አበባ የደረስኩት በግል ገንዘቤ ያውሮፕላን ትኬት ገዝቼ ነው። እንደዚሁም፣ ወያኔዎችን ለማጋለጥ ብቻ ወዳገሬ ከተመለስኩበት ጊዜ ጅምሮ ወያኔ አዲስ አበባን እስከተቆጣጠረ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ በቆየሁባቸው 15 ወራቶች (ራሴ አልፈልግም ስላልኩ) ለአንዲት ወር ቢሆን እንኳ ስሜ በመንግሥት ደመወዝ መቀበያ ሊስት (payroll) ሰፍሮ አይገኝም። ይህ አሁንም በህይወት ያሉ የቀድሞ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም የሚመሰክሩት ሐቅ ነው። በብዙ ድካምና ጥረት ወዳገሬ ተመልሸ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምን በግል ለአምስት ሰዓታት በማነጋር የመጣሁበትን ልዩ ምክንያት አስረድቼ፤ እሳቸውም ዓላማየን በሚገባ ተረድተው ሁሉም ያገሪቱ ሚድያዎች ክፍት ተደርገውልኝ በሰፊው የሰጠሁት ማስጠንቀቂያ አድማጭ አጥቶ ውሃ በልቶት መቅረቱ የሚያስቆጭ ቢሆንም፤ ብዙ አላሳዘንኝም። ምክንያቱም፣ ምንም እንኳ ጥፋቱና ብልሽቱ የወታደሮቹ ብቻ ሳይሆን፣ ከየፈረንጁ ሀገር የጎረፉት የኢትዮጵያ ሊሂቃን፣ የኤርትራን ጉዳይ ጨምሮ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ሳያገናዝቡ ሥልጣን ከወታደሮቹ ጉያ እናስጥላለን በሚል ቁማር በፈጠሩት ውዥንብር ምክንያት ጭምር፤ በደርግ ያሥራ ሰባት ዓመታት አስተዳደር አብዛኛው ህዝብ ያኮረፈና የተበሳጨ በመሆኑ፣ የኔን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ለምን በውል አላዳመጠም የሚል ቅያሜ የለኝም።

እኔን በግል የሚያስቀይመኝና የሚያስቆጣኝ ነገር ቢኖር፣ በወያኔና ሻዕቢያ ግጭት ማግስት በጽሁፍ በተለያዩ የሚዲያ ውጤቶች (በግጭቱ ማግስት የዘረጋሁት ባለ 18 ገፅ "አስቸኳይ መግለጫ" ያስታውሷል)፣ እንደዚሁም በተለያዩ ያውሮጳና ያሜሪካ ስብሰባዎች በአካል በመገኘት በቃል ያስተላለፍኩት ማስጠንቀቂያ መልዕክቱ ያለመደመጡ ነው። ምክንያቱም፣ በደርግ ጊዜ ባስተላለፍኩት ማስጠንቀቂያ መሰረት የተናገርኩት ሁሉ በተግባር የተመሰከረ ስለሆነና፣ በሻዕቢያና በወያኔ ግጭት ማግስት ግን እንደ ደርጉ ጊዜ ከሰማይ የወረድኹ ያልታወቀች ወፍ ስላልነበርኩ ነው።

የቁጣየ መሰረት ደግሞ፣ ያለምንም የህዝብ ውክልና፣ ለኤርትራ ከኤርትራዊያን በላይ የሚጣበቅና ኤርትራን በጠራራ ፀኃይ ከሕግ ውጭ በሆነ መንገድ ያስረከበን ሥርዓት ባዲስ አበባ ቤተመንግሥት አስቀምጠው፣ ባገር ድንበርና ሉዓላዊነት ሽፋን ከወያኔ ሥርዓት ጎን በመሰለፍ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የድሃ ልጆች በጦርነት ተማግደው እንዲያልቁ ያደረጉት ወያኔዎች ብቻ ሳይሆኑ ተቃዋሚ ነን የሚሉት የኢትዮጵያ ሊሂቃን ጭምር በመሆናቸው ነው። እነዚህ ነገር የማይገባቸው ሊሂቃን ከወያኔ ሥርዓት ወግነው ያስጨረሱብን ልጆቻችንን ብቻ ሳይሆን፣ ያንን ተደፈረ ያሉት መሬትና በመሬቱ ላይ ያለው ህዝባችንም (በተለይ ታላቁ የኢሮብ ህዝባችን) በማስወሰድ ጭምር ነው። ይኽ የማያስቆጨው የለም። እጅግ አሳሳቢውና ገና ያልተዘጋው የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝብ የውዝግብ ፋይል በእንጥልጥል ላይ እያለ፣ የወያኔ ሥርዓት ከሰማይ መና ያወርድልኛል ብሎ የሚያምን ሰው ካለ በቁሙ የሞተና የበከተ ወይም ለግል ጥቅሙ ሲል ከዲያብሎስ ጋር ቢሆንም በሽርክና ለመነገድ የተዘጋጀ አሳፋሪ ፍጡር ብቻ መሆን አለበት።

ከዚህ ጭብጥ በመነሳትና፣ ወደፊት በተከታታይ በሚቀርቡ መጣጥፎቼ በሚገለፁ ሌሎች ምክንያቶች፣ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በቅርቡ ያደረጉት ወቅታዊ ቃለመጠይቅ ከማንም ይበልጥ እኔን ለውውይት የሚጋብዝ ነው። ስለሆነም፣ እኔም በዚህ ውይይት በመሳተፍ በቅንነትና በግልፅነት ውይይቱን ለማስፋት ወስኘ ተዘጋጅቻለሁ።

ይህ ዛሬ የምወያይበት አብይ ጉዳይ በተመለከተ፣ ወዳጆቼ፣ ዘመዶቼ፣ ደጋፊዎቼና ሌሎች በርካታ ዜጎች በተለያዩ ጊዜያቶች፣ ወደ ኤርትራ ለምን ሄድክ? በዚያ በኩልስ ፋይዳ ያለው ሥራ ማከናወን ይቻላል ወይ? ያኔ ወደ ኤርትራ ያስኬደኽ ጉዳይስ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ወዘተ ... የሚሉ ጥያቄዎች እያቀረቡልኝ በሚገባ ሳስረዳቸውና ሳሳምናቸው ቆይቻለሁ። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ መወያየትም ሆነ መግባባት የማይቻለው ከወያኔ ደጋፊዎችና ጋሻጃግሬዎች ጋር ብቻ ነው። ምክንያቱም ግልፅ ነው፤ በዋናው መጣጥፎቼ ላይ እመለስበታለሁ።

ከኤርትራ መንግሥትና ህዝብ ጋር ተቀራርቦ መነጋገር ያለውን ፋይዳ ያስረዳኋቸውና ሃሳቡን ያመኑበት ብዙ ሰዎች (በተለይ የትግራይ ተወላጆች) በተደጋጋሚ የሚሰጡኝ ግብረ-መልስና የሚለግሱኝ ምክር፣ ሚዲያውን ተጠቅመህ ይህንን ጉዳይ ባጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ በተለይ ደግሞ ለትግራይ ህዝብ፣ ይፋ ማድረግ አለብህ የሚል ነው። እኔም ሃሳባቸውና ምክራቸው በአክብሮት የምቀበለውና የማምንበት ቢሆንም፣ ሁሌም የምከተለው የአሠራር ስልት ወቅትንና ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ በመሆኑ፣ ይህንኑ እያስረዳሁ ትዕግስታቸውን እንዲለግሱኝ ስማጠን ቆይቻለሁ። አሁን ያ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ስጠብቀውና ስመውኘውም የነበረ ወቅት ደርሷል። ምስጋናየ፣ ባጠቃላይ ለግንቦት 7 መሪዎች በተለይ ደግሞ ምንም ሳይፈራና ሳይደባብቅ ሃሳቡን በይፋ ግልፅ በማድረግ ይህንን ጠቃሚ ውይይት እንዲጀመር አጋጣሚውን ለፈጠሩልኝ ላቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ይሁንልኝ።

የውይይት መጣጥፎቼ ይዘትና ትኩረት

ይህንን ወቅታዊና ልዩ ውይይት ለመጀመር፣ ምንም እንኳ አጋጣሚውን የፈጠረልኝ ያቶ አንዳርጋቸው ቃለ-መጠይቅ ቢሆንም፣ የውይይቱ ይዘት ዋና ትኩረት ግን ባቶ አንዳርጋቸው ቃለ-መጠይቅ ዙሪያ ብቻ የሚያጠነጥን አይደለም። ያቶ አንዳርጋቸው ቃለመጠይቅ የራሴን የውይይት መድረክ እንድከፍት ሰበብ ከመሆኑ በቀር፣ የመጣጥፎቼ ይዘት ብቸኛ ወይም ዋነኛ አካል አይደለም። የኔ በዚህ ውውይት መሳተፍ፣ ምናልባትም ያቶ አንዳርጋቸውን ቃለ- መጠይቅ በማብራራትና በማዳበር አመኬላውንና ሸውራራ አመለካከቶችን አፅድቶ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ከሰመጡበት ማጥ በማስወጣት አዎንታዊ አስተዋፅዖ ይኖረዋል የሚል ተስፋ አለኝ።

በተለያዩ ርዕሰ-ነገሮች ተከፋፍለው የሚቀርቡት የመጣጥፎቼ ፍሬ-ሃሳቦች በዋነኛነት የሚያወያዩትና የሚያጠነጥኑት፤ ብዙ ውዝግብ፣ ክፍፍል፣ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ፣ የትግል ስልቶች ለውጥና፣ ፀረ-ትግራይና የትግራይ ህዝብ (እኔን ጨምሮ) የተከሰተበት ማለትም ከኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ጀምሮ እስከ አወዛጋቢው ምርጫ-97 ደረስ ባለው የጊዜ እርከን በተከናወኑ ጉዳዮች ላይ በማነጣጠር ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ መጣጥፎቼ፣ በምከተለው ወቅትን ግምት ያስገባ ስልታዊ አሠራር ምክንያት፣ ካሁን በፊት ለህዝብ ይፋ ያላደረግኳቸው ከበድ ያሉ ምስጢራዊ ጉዳዮች ጭምር ያካተቱ ናቸው። በዚሁ መሰረት፣ አጠቃላዩ የመጣጥፎቼ ይዘት ከዚኽ በታች በተመለከቱ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የተመሰረቱ ይሆናሉ፤

1. መግቢያ፣

2. ከኤርትራ መንግሥትና ህዝብ ጋር የሚደረግ ግንኙነትና ትብብር ለምን?

3. የኔና የነአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ (የግንቦት ሰባቶች) ወደ ኤርትራ ሄዶ ከኤርትራ መንግሥት ጋር መነጋገር ሲነፃፀር፣

4. በወያኔና-ሻዕቢያ ግጭት ማግስት፣ ከሻዕቢያ ጋር በተደረገ ግንኙነትና ምክክር መሰረት፣ የኢትዮጵያ የሽማግሌዎች ምክር ቤት ለመመስረት ስለማስፈለጉ፤ ይህንኑ ለማሳካት የተደረገው አድካሚ ጥረትና ያልተሳካበት ምክንያት። የኢትዮጵያ ሽማግሌዎች ምክር ቤት መመስረት ለምን አስፈለገ?

5. እኔ የመሥራቹ አመራር አባል የሆንኩለት "የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ" (ትህዴን) መቼና ለምን ተመሰረተ? እድገቱና አሁን የሚገኝበት ሁኔታ ምን ይመስላል። ትህዴን በትግራይ ህዝብ ዘንድ እንዴት ይታያል?

6. በምርጫ-97 ዋዜማ "የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት - "Union of Ethiopian Democratic Forces" (ኢዴኃህ/UEDF) አዋላጅ የነበረው "የሁሉም ፓርቲዎች ኮንፈረንስ" - "All Parties Conference" (ሁፓኮ/APC) ሂደትና በኢዴኃህ/UPDF ምስረታ ትህዴንና የትግራይ ህዝብ ለማግለል የተፈፀመው አሳፋሪ ደባ፤ በዚህ አፍራሽ ደባ ምክንያት በ"ህብረቱ" (በኢዴኃህ) ላይ የደረሰው አጠቃላይ ኪሳራ። የ"ኢዴኃህ" አክሳሪ ደባ ለቅንጅት የሰጠው ጥቅም።

7. ምርጫ-97 እና በምርጫ-97 ዙሪያ የመአህድ/መኢአድ (የውጭ ክንፍ) የምርጫ "እቅድ-ሀ" (Plan-A)። የምርጫ-97 አንፀባራቂ ውጤትና የቅንጅት ስኬት ኢዴኃህን፣ ሻዕቢያን፣ ኦነግንና፣ ኦብነግን ስለማስደንገጡ፤ በተለይ ኦነግና ኦብነግ ስለወሰዱት ፈጣን እርምጃና፣ በዚህ እርምጃ የኔ ተሳትፎ።

8. የቅንጅት አመራሮች ተጠራርገው ወደ ቃሊቲ እንደወረዱ፣ በምርጫው ውጤት እጅግ ተደናግጠው ከነበሩት ኃይሎች መካከል፤ ሻዕቢያ፣ ኦነግና፣ ኦብነግ የወሰዱት ፈጣን እርምጃ። ከዚህ የሦስትዮሽ እርምጃ ጋር ተያይዞ የመአህድ/መኢአድ "እቅድ-ለ" (Plan-B) ስለመተግበሩ።

9. አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ውስጥ በመርሆ ደረጃ የምስማማባቸውና፣ በአፈፃፀምና በወቅታዊነት ምክንያት የምለይባቸው አንዳንድ ነጥቦች።

10. የአማራ ሊሂቃን (ኤሊቶች) የዕይታና የአደረጃጀት ችግር፤ ስልት የጎደለውና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ፖለቲካዊ አመለካከታቸው፤ ከእውነታው እጅግ የራቁና የተሳሳቱ ቅስቀሳዎቻቸው አደገኛነት፤ በሊሂቃን/በኤሊቶች ልጆቹ ያልታደለው የመላው አማራ ህዝብ ዕጣ ፈንታ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሲገመገም።

11. ምን መደረግ አለበት? የኔ የመፍትሔ ሃሳብ።

ስለዚህ፣ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች በቅደም ተከተልና፣ በተለያዩ የቀናት ልዩነት ስለማስተናግድ የሚመለከታቸው ሁሉ በጥሞና እንዲከታተሉኝ እጋብዛለሁ። የነገ ሰው ይበለን!

የአቶ አንዳርጋቸው ቃለ-መጠይቅ ያልተከታተሉ ሰዎች ይህንን የኢሳት ድረ-ገፅ (ሊንክ) በመጎብኘት ሊያዳምጡ ይችላሉ።
http://ethsat.com/video/esat-yesamintu-engida-ato-andargachew-tsege-sep-2013-ethiopia/ 


አብርሃም ያየህ
መስከረም 15 ቀን 2006 ዓ.ም. (September 25, 2013)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!