ቦጋለ ካሣዬ 

"... ግንቦት-7 ሲመሰረት፤ ብዙ ሀገር ወዳድ ዜጋ 500 ዶላር ወይም ኢሮ እያዋጣ ተቀላቅሎት ነበር። ይሁን እንጂ እነአንዳርጋቸው ብራቸውን ከሰበሰቡ በኋላ፤ በመጀመሪያ ከአንድነት ኃይሎች ጋር ለመስራት ፍላጎታቸውን ማሳየት ጀመሩ። ቀስ ብለው ደግሞ ከቅንጅት መንፈስ በመንሽራተት፤ የኦነግንና ኦብነግን ማሽኮርመም ጀመሩ። የአንድነቱ ኃይል አጉረመረመ። እነአንዳርጋቸው ግን ብዙም አልተጨነቁም። ኢሳታቸው ስላለ የፕሮፓጋንዳ የበላይነት አላቸውና፤ የጎሣ ፖለቲካቸውን በታሪካዊ በደል ፈጻሚ (አማራ) እና ሰለባ (ሌለው ጎሣ) እያመካኙ፤ አሁን ኤርትራ ሽባ ሆኖ የቀረውን ከማል ገልቹን፤ እንደ የአንድነት ታጋይ በማግዘፍ ጄኔራል ከማል ገልቹ! ጄኔራል ከማል ገልቹ! እያሉ አናፉብን። ..."

 

1. የግንቦት-7ቱ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ ወያኔን በሽፍትነት ዘመኑ በአማካሪነት፤ ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ ደግሞ በሹመት አገልግሎታል። ግልጋሎቱን 'በቁጭት' መንፈስ ሲናገር፤ ... "ውስጡ ገብቶ ማስተካከል ይቻላል ከሚል የዋህና ምናልባትም ደደብነት ሊባል በሚችል" እምነቱ የተነሳ እንደነበር ከኢሳት ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋር ባዳረገው ቃለ ምልልስ ነግሮናል። ይኼን እንደ ፖለቲካ እዳ ማየት አይገባም። ዛሬ ደግሞ ጎንቦት-7 ወያኔን ማስገደድ ወይም ማስወገድ የሚል አቁዋም ያራምዳል። ይሁን እንጂ ከፍሺስትና ባርነትን አፍቃሪው ከኢሳያስ አፈወርቂ ጉያ ውስጥ በመግባት ወያኔን እንጥላለን የሚል አደገኛ የፖለቲካ ቁማር ጫወታ፤ አሳሳቢ ጉዳይ ስለሆነ በግልጽ መወያየት ያሻል። ምን? ኢሳያስን እንዴት ባሪያ ትላለህ? አዎ ኢሳያስ ባሪያ ነው። ያውም ነፃነትን የሚጠላ ባሪያና የባሮች ኮርማ። የባሪያነቱን ምክንያት ለማወቅ ከፈለክ፤ የኢታሊያንን የቅኝ ግዛት ፖለቲካ እንዴት እንደሚያፈቅር በዚህ ጽሁፍ ግርጌ ማስታወሻ ላይ የተጠቀሰውን ተመልከት። የሀገርህንም እድሜ ከየት ጀምሮ እንደሚቆጥርና፤ የቆጠረበትንም ምክንያት በተራ-ቁጥር 13 ተጽፎአልና ልብ ብለህ እንብብ።

 

2. አንዳርጋቸው ከወያኔ ጋር ለመለያየት የቆረጠበት አንዱ ምክንያት፤ የቤተመንግሥት በር ጠባቂዎች ከ'ወርቅ' ዘር ያልተወለደውን ኢትዮጵያዊ ወደ ውስጥ ለማስገባት የሚያደርጉት አድሎ አንገሽግሾት ነው። ነገሩ እንደህ ነው። የቤተ መንግሥት በር ጠባቂው፤ ትግርኛ ተናጋሪ የሆነን ሰው ካለምንም ችግር ወደ ውስጥ ያስገባል። ካልሆነ ግን ጠባቂው ደጅ ጠኚውን የትግርኛ ተናጋሪ ባለሥልጣን ተባባሪነት/ድጋፍ እንደሚያስፍልገው በዘረኝነት መንፈስ ይንቀባረርበታል። አንታ! ስማእኒ! ማንን ትግሬ ትፈልጣለካ? አይነት ጥየቃ! (ስለ ትግርኛ ችሎታዬ ይቅርታ)።

 

3. ስለ ወርቅ ካነሳን ... "ሴትየዋ፤ በሎቲ፣ በሃብል፣ በካቴናና በአልቦ ወርቅ ተጊጠው፤ ጥላ ተይዞላቸው ከሰርግ ቤት ውለው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። ታዲያ ልብ ብሎ አይቶ የተከተላቸው፤ ሲቪል የለበሰ የፌዴራል ፖሊስ ሌባ፤ ሌሊት ቤታቸው ገባና ወርቃቸውን አንድ ሳያስቀር ሙልጭ አድርጎ ወሰደው። አሁን ይኸን ስታነቡ እሰይ! የምትሉ አንዳንድ ምቀኞች መቼም አትጠፉም። የሆኖ ሆኖ ሴትየዋ አዝነው ሲያልቅሱ ጎረቤታቸው አላቃሽም ቆሽታቸው አሮና ደብኖ ኖሮ፤ አንቺ? ዋይ! ያን ሁሉ ወርቅ ሰረቀው? አንድም ሳያስቀር? ደረታቸውን መታ! መታ! እያደረጉ፤ ዋይ! ዋይ! ዋይ! "አማራ አሮጎሽ እኮ ነው የሄደው"!፤ "አማራ አሮጎሽ እኮ ነው የሄደው!" አሉ ይባላል። ታዲያ አንዳርጋቸው የወርቅ ዘር ዘርኝነትና ሌሎች ነገሮችም እንዲታረሙ ደጋግሞ ቢወተውትም የሚሰማው ስለጠፋ ወያኔን ለቅቄ ወጣሁ አለ።

 

4. ብዙም ሳይቆይ የቀሰተ ደመና አባል ሆነ። ምንም እንኳን እንደ ቅንጅት መሪዎች ለረዢም ጌዜ ባይታሰርም፤ በቅንጅት ድል ማግስት በተከተለው የእስርና የድብደባም ሰላባ ነበር።
ከዚያም የቅንጅት ተመራጮች በቃሊቲ በታሰሩበት ወቅት፤ በስደት ቅንጅትን ከሚመሩት አንዱ ዋና ሰው ነበር። የዶ/ር ብርሃኑን መጽሐፍ በማረም፣ በማሳተምና ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ እንዲሰራጭም ከፍተኛ ሚና ተጫውቶአል። የመጽሐፉ ውጣ ውረድም ዶ/ር ብርሃኑን ለማግዘፍና የቅንጅት ፕሬዝዳንት እንዲሆን ለማመቻቸት ስለመሆኑ፤ በውስጡ ኢንጀነር ኃይሉን ለመተካት ይደረግ የነበረውን የሥልጣን ትግል ትርካ ስናነብ እንረዳዋለን።

 

5. አንዳርጋቸው እኔ ራሴ ባለፈው ዓመት እንዳረጋገጥኩት፤ ገና በጥዋቱ ከቅንጅትን መንፈስ በፍጹም በሚቃረን መንገድ ሄዶም፤ የቅንጅት የጦር ሰራዊት ለማቁዋቁዋም ግለሰቦች መልምሎ በኬንያ በኩል ጦር ለማዝመት ሙከራ አድርጎ ነበር። የዚህ አጉል የጀብደኝነት ሰለባ የሆነው ግለሰብ ዛሬ በኡጋንዳ ይገኛል። ለምን ተሰናከለ ይኼኛው የአንዳርጋቸው ቅንጅት ጦር? ኤርትራስ ሄደው የሰለጠኑ ሰዎች አልነበሩምን? አቶ አንዳርጋቸው?

 

6. የአንዳርጋቸውን የወያኔ አማካሪነትና ደጋፊነት ፋይሉን የሚያውቁ፤ ገና ከጥዋቱ በአንዳርጋቸው ወደ ተቃውሞ ጎራ መቀላቀል ደስተኛ አልነበሩም። ይሁን እንጂ አብዛኞቻችን በቅንጅት መንፈስ ተጠምደን፤ እንዳንከፋፈል እንጠነቀቅ ነበርና፤ የሚነሳበትን ተቃውሞ ተከላከልን። ከግለሰቦች ጋር ተጣላን። ይህም አጋጣሚ ማለትም የቅንጅት መንፈስ፤ ለአንዳርጋቸው የፖለቲካ ማንሰራራት አዲስ ሌላ ምእራፍ ፈጠረ።

 

7. የቅንጅት ታሳሪዎች ተፈቱ። ወዲያውም ቅንጅት 'በውስጥ የዴሞክራሲ ችግር ምች' ይሰቃያል በሚል ድራማ በአሜሪካ በአደባባይ ተናደ። ይሁን እንጂ 'የውስጥ የዴሞክራሲ ችግር ምች' በግንቦት-7ም ተከሰተና ግንቦት-7-ዴ ደግሞ ተፈጠረ። ግንቦት-7 ከወያኔ ተጽእኖ ውጭ እየተንቀሳቀሰ እንኳን ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሳይሆን ቀረ። አንዳርጋቸው የዚህ ሁሉ ቁልፍ ተዋንያን ነው።

 

8. ግንቦት-7 ሲመሰረት፤ ብዙ ሀገር ወዳድ ዜጋ 500 ዶላር ወይም ኢሮ እያዋጣ ተቀላቅሎት ነበር። ይሁን እንጂ እነአንዳርጋቸው ብራቸውን ከሰበሰቡ በኋላ፤ በመጀመሪያ ከአንድነት ኃይሎች ጋር ለመስራት ፍላጎታቸውን ማሳየት ጀመሩ። ቀስ ብለው ደግሞ ከቅንጅት መንፈስ በመንሽራተት፤ የኦነግንና ኦብነግን ማሽኮርመም ጀመሩ። የአንድነቱ ኃይል አጉረመረመ። እነአንዳርጋቸው ግን ብዙም አልተጨነቁም። ኢሳታቸው ስላለ የፕሮፓጋንዳ የበላይነት አላቸውና፤ የጎሣ ፖለቲካቸውን በታሪካዊ በደል ፈጻሚ (አማራ) እና ሰለባ (ሌለው ጎሣ) እያመካኙ፤ አሁን ኤርትራ ሽባ ሆኖ የቀረውን ከማል ገልቹን፤ እንደ የአንድነት ታጋይ በማግዘፍ ጄኔራል ከማል ገልቹ! ጄኔራል ከማል ገልቹ! እያሉ አናፉብን። በደርግ ሥርዓት ብዙ ሰው ገድለው በኢትዮጵያ ባንዲራ ፍቅር ስር የተደበቁ የፓልቶክ ጀሌዎቻቸውም አብረው ከበሮ ደለቁ። ኦነግ ለሁለት ተከፈለ ተባልን! የጎሣው ቡድን አረቄ ሳይጠጣ ሰከረ። ይሁን እንጂ ከግርግሩ ውጭ፤ የጎሣው መንጋ ሾፌሮች ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና የኦነጉ ባቲ በጀርመን ተገኝተው የተናገሩትን፤ ከሚከተለው የአንድ የግንቦት-7 ደጋፊ የነበረ ግለሰብ ማስታወሻ ማየቱ፤ በመሰረቱ ኦነግ ምንም ለውጥ እንዳላደረገ ስለሚያሳይ ትዝብቱን እንዳለ አቅርቤዋለሁ፤

"በኦገስት 2012 ኑረንበርግ (ጀርመን) በግንቦት ሰባትና በኦነግ በተጠራው ስብሰባ ላይ ተሳትፌ ነበር። በወቅቱ ጥያቄም አንስቼ ባገኘሁት መልስ ስለግንቦት ሰባት የነበረኝን አመለካከት እስከወዲያኛው እንድቀይር ተገድጃለሁ። የቀዳሁትን ለመረጃነት እልክልሃለሁ። ግንቦት ሰባትን የወከሉት የግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ነበሩ።

"አንደበታቸው የተፈታ በመሆኑ ንግግራቸው ለአድማጭ ይጥማል። የንግግራቸው ይዘት ግን ተሰብሳቢውን ኢትዮጵያዊነት የሚጠቅመን አንድ አማራጭ ብቻ መሆኑን ለማሳመን የሚጥር ነበር።
ለኔ ግን ይህ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ከመነሻውም እዛ ላይ ሁላችንም የማያወላውል አመለካከት ያለን መስሎኝ ነበር።

"ለዚህም ነበር በአቅሜ ግንቦት-7ን የምረዳው። ይሁንና ነገርና ጭራ ከወደ ሁዋላ ነው እንዲሉ ጨዋታው የለየለት የአቶ ባቲ ተራ ሲደርስ ነው። በነገራችን ላይ የአቶ ባቲ ስም ሌላ ነው። ነገር ግን በአማራ ተጽእኖ የተሰጠኝ በመሆኑ ኦሮሞነቴን የሚያንጸባርቀውን ባቲ እመርጣለሁ ብለው ባለፉት ዘመናት ኦሮሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የደረሰበትን በደል ዘርዝረው ንግግራቸውን አበቁ። ያኔ ነው ለኔ ዶ/ር ብርሃኑ ወይ የቤት ስራቸውን አልሰሩም ወይም ሌላ አጀንዳ አላቸው የሚል ስሜት ያሳደረብኝ። ከዛም በመነሳት ይህንን ጥያቄ አቀረብኩ፤ ንግግራችሁን ሳዳምጥ የዶ/ር ብርሃኑ ንግግር እንደ ዘፈን ነው የሆነብኝ፤ ዘፈኑም "ኧረ ባቲ ባቲ"" የሚል ነው ካልኩ በኋላ፤ ለመሆኑ አቶ ባቲ "በኢትዮጵያ አንድነት ያምናሉ ወይ?" ስላቸው የሰጡት መልስ "ድል አድርገን ስንገባ የኦሮሞ ሕዝብ ትገነጠላለህ? ወይስ አብረህ ትኖራለህ? ተብሎ በሚሰጠው መልስ ይወሰናል። ለዚህ ጥያቄ መልስ በአሁን ሰዓት የለኝም ብለዋል። ከዚህ በመነሳት እዛ ስብሰባ ላይ ለኔ የሚጠቅም ነገር ለመስማት በመሰረተ ሃሳቡ ላይ "በኢትዮጵያ አንድነት" ላይ ስምምነት ባለመኖሩ ግንቦት ሰባት በዚህ ሃሳብ ላይ የጠራ አመለካከት እንዲኖረው አስመዝግቤ የኢትዮጵያውያን የአውሮፓ ዓመታዊ እግር ኳስ ለማየት ሄጃለሁ።"

 

9. የኦነግ የታሪክ ክህደት፣ የመገንጠል አባዜ፣ ጥላቻውንና ወንጀሉን ከግንዛቤ በማስገባት፤ ከኦሮሞ ሕብረተሰብ አብራክ የወጡት ፕሮፌሠር ፍቃዱ ደገፌ፤ የተቃዋሚ ወገን እንዳይጠነክር አንዱ ደንቃራ የሆነው ኦነግ እንደሆነ ተናግረዋል። በቅርቡ የተቋቋመው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ድርጅትም ኦነግ ከሚያራምደው መሰረታዊ የፖለቲካ አቋዋም ልዩነት እንደሌለው፤ ሊቀመንበሩ እና ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ካደረጉት ምልልስ ግንዝቤ ያገኘን ይመስለኛል። ታዲያ ግንቦት-7 ሀገር የማፍረስ ፖለቲካ ከሚያካሂዱ ድርጅቶች ጋር ለምን አጋር ይሆናል? ለምንስ ጀሌ ይሆናል?

 

10. እነ አንዳርጋቸውም ይኽን ሁሉ የሚያጡት አይመስለኝም። ታዲያ ለምን ወያኔን ለመጣል በሚል የጋራ አጀንዳ ብቻ አንዴ ከፈረሰ እንደገና ለመመስረት የማይቻለውን ሀገር ያህል ነገር አፍራሽና አፋራሽ ይሆናሉ? ይኽ የፖለቲካ ደደብነት ካልሆነ የኢትዮጵያ ጠላትነት ከመሆንስ ይዘላል ወይ? እንደምናውቀው ግንቦት-7 ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ስላልሆነ ብዙ ጉዳዮች በግለሰቦች ብቻ ነው የሚወሰኑት።

እነዚህ ግለሰቦች ደግሞ መላዕክቶች ሳይሆኑ፤ በጥቅም ሊገዙ፣ ሊታለሉና ሊገደዱ የሚችሉ ሰዎች ስለሆኑ የተደበቀ ዓላማ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ አያራምዱም ብሎ መገመት በፖለቲካ ዓለም የሚቻል አይደለም።

ስለዚህ ግንቦት-7 አውቆም ሆነ በድንቁርናው ለሥልጣን ጥማት ሲል፤ ከኢትዮጵያ አንድነት ጠላቶች ጋር መሰለፉ እርሱንም ከጠላት በምንም መንገድ ልዩ አያደርገውም ማለት ነው። ቀጥለን በሴፕቴምበር 5፤ ከኢሳት ሬዲዮና ቴሌቪዝን ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋር አንዳርጋቸው ጽጌ ባካሄደው ቃለ ምልልስ ላይ ተመርኩዘን፤ እንወያይ።

 

11. አንዳርጋቸው ጽጌ ስለኢሳያሳ አፈወርቂ የሰጠው 'በጎ' ምስክርነት ራሱም የማያምንበት ነው። እርሱው እንዳለው ሳይሆን፤ ዛሬ በኤርትራ ምንም አይነት ነፃነት የለም። የፖለቲካ እስረኞች ሲታሰሩ እንጂ ሲፈቱ ወይም ፍርድ ቤት ሲቀርቡ አይታይም። ኢሳያስ ስለፖለቲካ እሰረኞች ሲጠየቅ፤ "አላውቃቸውም ነው የሚለው።" የሚያደርገውም አሰቃይቶ መግደል ብቻ ነው። አለቀ። ደቀቀ።

 

12. የአንዳርጋቸው ቃለምልልስ የፈጠረው ትኩሳት ገና ሳይበርድ፤ ኢሳያስ ኢትዮጵያ የሚባል ሀገር እንደውም የተፈጠረው ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ ነው ብሎ ከች አለ። አንዳርጋቸው ይኼን ይጋራ እንደሆነ አላውቅም።

ይሁን እንጂ ኢሳያስ እንደዚህ ያለው ካለነገር አይደለም። እንደሚታወቀው ኢታሊያ ለአምስት ዓመታት ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ወያኔ ዛሬ እንዳደረገው በጎሣ ከፋፍላት ነበር። የዚህ የፖለቲካ ግብም ትናንሽ ሀገሮች እንዲፈጠሩ ያለመ ነበር። የሙሶሎኒ፤ ከሂትለር ጋር መወዳጀት የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት የኃይል አሰላለፍ ስለቀየረው የሙሶሎኒ እጣ ውድቀት ሆነ። ያ የተጀመረው የሀገር ብተና መሰናዶ ፖለቲካም በኢትዮጵያውን አርበኞች ትግልና በእንግሊዝ ቀጥሎ በአሜሪካ እርዳታ ሊቀለበስ ቻለ። ይሁን እንጂ እስካሁን ሻዕቢያ ትግራይን ከኤርትራ ጠቅልሎ እንደ ሙሶሊኒ ማስተዳደር አልጀመረም። ስዚህም ነው እንግዲህ ኢሳያስ፤ ኢትዮጵያን ሲያስብ ከሙሶሊኒ ፖለቲካ ሀ ብሎ የሚጀምረው። ኤርትራንም ሲያስብ ያው ከኢታሊያው ክርሲፒ ነው ጅማሪው። ይኼም የኢሳያስ አስተሳሰብ አዲስ አይደለም። ጉዳዩ የአፍሪካ ታሪክ የጀምረው መቼ ነው? ከሚለው ድርሰት የሚመነጭ አስተያየት ነው። ኢሳያስ ለኢትዮጵያ የሰጣት ዕድሜም ከዚሁ ድርሰት፤ ማለትም የአፍሪካን ታሪክ የፈጠረው የነጭ ቅኝ ገዢ ነው፤ በማለት የባሪያ ፈንጋይና ተፈንጋይ አቀንቃኞች የሚያራምዱት ሃሳብ ጋር የሚስማማ ነው። የዚህ ድርሰት ጭብጥ፤ አፍሪካውያን ወይም ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ታሪክ አልሰሩም። የራሳቸው ታሪክ የላቸውም የሚል ነው። በዝርዝርም፤ የዛሬዋ ኤርትራ ባሕረ ነጋሽ በሚል አትጠራም ነበር ማለት ነው። የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥቶች ባሕረ ነጋሽን አስተዳድረው አያውቁም ማለት ነው። ለአስመራ ስም ያወጡለት አሉላ አባ ነጋ አይደለም ማለት ነው። ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ቆማ አታውቅም ማለት ነው። በቃ ይኼው ነው የኢሳያስ አፈወርቂ ፖለቲካ፤ ክህደት፤ በክህደት ላይ ክደት። ለዚህም ነው ኢሳያስን ባሪያ፤ የባሪያ ፈንጋይ የታሪክ አንቀቃኝ ነው የምንለው።

ሌላው በጣም ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይም፤ ኢሳያስ ኢትዮጵያ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረች ነች የሚለው ቅጥፈቱ፤ ትግራይ ትግሪኝ ከሚለው እቅዱ ጋር በጣም ተስማሚ መሆኑን ነው። ምክንያቱም ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው ኢታሊያ ትግራይና የዛሬዋን ኤርትራ አንድ ላይ ቀላቅሎአቸው ስለነበር የሙስሎኒ ውርስ ይገባኛል ባይ ነውና። ትግራይን ገና ያልጠቀለለች ኤርትራም በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ስላገኘች፤ ኦሮሚያ፣ ኦጋዴንና ሌሎችም ከተፈጠሩና እውቅና ካገኙ፤ ለትግራይ ትግሪኝ መፈጠር በተዘዋዋሪ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ኢሳያስ በከዘራው መሬት እየቆፈረ ያስላስላል።

ወያኔን አከርካሪውን ሰብሮ ትግራይን ከኤርትራ መቀላቀል የሚያልመውን የኢሳያስ ፖለቲካ ዛሬ ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በሚያካሄደው ግፍ በተንገፈገፉ ወገኖች፤ እንደግልግል እንደሚያዩት ይሰማኛል። ይኸ ማለት ግን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር አትኖርም ማለት ነው። ለዚህ ነው በሠላም ወይም በአመጽ የምናደርገው ትግል ከተጽዕኖ ውጭ በሀገራችን ውስጥ ይጠናከር የምንለው። ወያኔን በተሻለ ሥርዓት መተካት የሚቻለው፤ ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ብቻ የሚቆጣጠሩትና የሚመሩት ጠንካራ ድርጅት መስርተው ሲታገሉ ነው። ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ደመኛ ጠላት ነውና በጎዋን አይመኝም። በባርነት ደዌ የታመመና ኢትዮጵያን የሚጠላ ኢሳያስ እንዴት ብሎ የኢትዮጵያ የነፃነት አጋር ይሆናል ብሎ ግንቦት-7ና አንዳርጋቸው እንደሚያምኑ በጣም ያስደንቃል። ለኔ ይኸ ከደደብነት ውጭ፤ ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ እንዳለው የማይካድ ነው።

ቀጥለን በእኛም ሆነ በሌላው ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ፖለቲካን ከታጠቀ የኃይል ሚዛን ውጭ ለይቶ ማየት እንደማይቻል የአሰብን ጉዳይ አንስተን እንመልከት። ግራና ቀኙን መለየት የተሳነው፤ አንዳርጋቸው በኢሳት ቃለመጠይቁ እንዳድበሰበሰው አይደለም የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ጉዳይ።

 

13. ስለግጭት አፈታት፤ ፕሮፌሠር ሕዝቂያስ አሰፋ ሲይስተምሩ፤ በምሳሌነት ይነሳ የነበረው፤ ስለኢትዮጵያ ምንም እውቀት ይሁን መብት የሌለው አንድ ዝቅተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን (አንዳርጋቸው 'ያን የሚያህል ሰው' በሚል አምልኮቱን በተዘዋዋሪነት በቃለምልልሱ ላይ ያንጸባርቃል)፤ ኸርማን ኮኸን ለአካባቢው ሠላም ጠንቅ ሊሆን የሚችል የፖለቲካ ውሳኔ የሰጠበት ምክንያት የራሳችንን ጉዳይ አሳልፈን ስለሰጠን ነው በማለት፤ ቅራኔን ለመፍታት ስለቅራኔው የጠለቀ እውቀትና የተደበቀ አጀንዳ የሌላቸው ገለልተኛ አስታራቂዎች እንደሚያስፈልጉ ያስተምራሉ።

 

14. በበኩሉ ኸርማን ኮኸን የሚነሳበትን ክስ ደግሞ ሲከላከል፤ ወያኔና ሻዕቢያ በጦር የበላይነት ስለነበራቸው አሜሪካኖች የሚሉትን ሊቀበሉ አይችሉም ነበር፤ የአሜሪካም ሚና ተጨባጩን ሁኔታ አይቶ የተደረገ ዳኛነት እንደነበር ግንዛቤ መወሰድ ያስፈልጋል ይለናል። ይሁን እንጂ ወያኔንም ሆነ ሻዕቢያን አሜሪካ ምን ያኽል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ትርዳ እንደነበርና በተቃራኒው ደርግን በተለይም የኢትዮጵያን ሠራዊት ለማፍረስ የተጫወተችውን ሚና አያነሳም። ይኽም ብቻ አይደለም፤ ኸርማን መለስ ዜናዊን የአሰብን ጉዳይ አንስቼበት አያገባኝም ብሏል በሚል፤ ለኢትዮጵያም አሳቢ እንደነበር አንጀታችንን ለመብላት ይዳዳዋል። ይሁን እንጂ ኸርማን ያልነገረን ወይም ያልገባው ነገር ቢኖር፤ አሜሪካ ወያኔና ሻዕቢያ እንዲሁም ደርግን በገለልተኝነት/ካላድሎ ማደራደር ያቃታት የደርግ መዳከም ወይም የነወያኔ ጥንካሬ ከሆነ፤ መለስ ዜናዊስ ቢሆን ገና ያልጠና ሥልጣኑ አደጋ ላይ እንዳይወድቅበት፤ በአሰብ ጉዳይ አያገባኝም ያለው ወደብ ጠልቶ ሳይሆን የሻዕቢያን ኃይል ፈርቶ ላለመሆኑ ማረጋገጫው ምንድን ነው? የሚለውን ነው። እንደውም ከዊኪሊክስ እንዳነበብነው፤ ኢሳያስ ወደ ኬንያ እረፍት በሄደበት ግዜ መለስ አውሮፕላን አዞላት አዲስ አበባ ከአስመጣው በኋላ፤ ወደ አስመራ በሚመለስበት ጊዜ በአውሮፕላኑ ላይ አደጋ አድርሶ ከኢሳያስ ለመገላገል ያደረገው የመጀመሪያው የከሽፈ ሙከራ፤ መለስ የሚፈራውን ተቀናቃኝ ለማስወገድ አንድ እርምጃ መሄዱን ያሳያል።

ይሁን እንጂ በኤርትራና በኢትዮጵያ ጦርነት ጊዜ የኢትዮጵያ ጦር ኢሳያስ ከአንድ ሆቴል ሆኖ ትዕዛዝ መስጠቱን ደርሶበት፤ ኢሳያስን ለመግደል ፍቃድ ጠይቆ ይሁንታ ቢያገኝም ኢሳያስ ቀደም ሲል መረጃ አግኝቶ እንደወጣ እየሩሳሌም ኣርአያ ባደረገው ቃለምልልስ መናገሩ ትዝ ይለኛል። እንደ እየሩሳሌም ከሆነ አቶ ስዬ አብርሃ ይሄን ለሕዝብ ባለመናገራቸው ሊወቀሱ ይገባል ባይ ነው። የሆኖ ሆኖ ኢሳያስ እንዳይገደሉ ያከሸፈው መለስ ቢሆንም፤ ከጦርነቱ በኋላ ግን የድንበሩን አወሳሰን ጉዳይ አልቀበልም ያለውም መለስ ነበር።

አሁን ደግሞ በቅርብ በዊኪሊክስ እንደተጋለጠው፤ መለስ የልብ ልብ ስለተሰማው፤ 'የድንበሩን' ችግር ለመወሰን፤ የወያኔ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ተዳርሶት እንዲኖራት መፈለጉን እንማራለን። ይኽንንም ደግሞ እውን ለማድረግ ወያኔ እንደ ማካካሻ ለኤርትራ መሬት ለመስጠት እንደሚፈልግና ይኽ ሳይደረግ ግን በድንበሩ ክለላ ስምምነት ላይ ለመድረስ አለመፈለጉን ሰነዱ አጋልጦአል።

ለነገሩ የዚህን ፍንጭ የዛሬው የይስሙላ ጠ/ሚርም ምክትል በነበሩበት ጊዜ ስለአሰብ ተጠይቀው፤ ኢህአዴጋቸው 'ወደብ ቢያገኝ እንደማይጠላና'፤ የአሰብን ጉዳይ በሚመለከት ግን ስለጥያቄው አንስቶ እንደማውቅ ነገርውናል።

አንድ ጊዜ መለስ ዜናዊም የኤርትራና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፤ የጥባቴነት (parasitic) ጠባይ ያለው ነው ማለቱ አይዘነጋም።

ስለዚህ የጅቡቲው ወደብ ክፍያ እየናረ ስለመጣ፤ ለኢፈርት ኢኮኖሚም ቢሆን መለስ የራሱ ወደብ ያስፈልገኛል ብሎ የተነሳው፤ የወታደራዊ ኃይሉ፤ በማንኛውም ወቅት ቢሆን ኤርትራን አፈር መሬት ያስግጣል ብሎ ካመነ በኋላ ነው። መለስ ለሱዳን መሬትም የሰጠውም በዚያ በኩል ክፉኛ ተቃዋሚ እንዳይመጣበት ለመከላከል ነው። መለስ ዜናዊ ሥልጣኑን ለመያዝ የማይወስደው እርምጃ አልነበረም። ሥላሴ ባይጠራልን ኖሮ ምናልባት ሌላ 20 ዓመታት ሊገዛን ይችል ነበር።

 

15. የሆኖ ሆኖ ዛሬ ኸርማን ኮኽን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያላቸው አስተያየት በጣም ተቀይሮአል። ደሞ እንዴት? ማለት ጥሩ ነው። ባለፈው በጋ ወር በአሜሪካ በተደረገው የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት አመሰራረት ጉባዔ ላይ ምሁራን፣ ምርጥና ምላጭ ጭንቅላት ያላቸው ዲፕሎማቶችና የቀድሞ ባለሥልጣናት ተሳትፈው ነበር። ከጉባዔው እንደተረዳነው ኸርማን ኮኽን፤ ትናንት ኢትዮጵያ አሰብን አጣች ብለው የአዞ እንባ ቢያልቅሱም፤ ዛሬ ግን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ማየት አቁመዋል። ከዶ/ር ካሳ ከበደ የንግግር ጭብጥ እንደምንረዳው፤ ኮኽን 'ኢትዮጵያዊነትን በማይፈልጉ' ቡድኖች (ኦነግና ኦብነግን ማለታቸው ለመሆኑ ጥርጥር የለውም) ላይ በግድ መጫን አያስፈልግም የሚል አቁዋም ይዘዋል። ክፉ አትበሉኝና፤ እንግዲህ የዛሬውን የኮኽን አቁዋምና በኢሳት ላይ ደግሞ አንዳርጋቸው የለገሳቸውን ሙገሳ ስናጤን፤ አንዳርጋቸው/ግንቦት-7፣ ኮኽንና ኢሳይስ አፈወርቂ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ በአንድ መስመር ላይ እንደተሰለፉ ለማረጋገጥ ጠንቋይ መቀለብ ይሻን ይሆን? ፈዛዛ ጭንቅላት የሌለው ሰው ካልሆነ ይህን አደጋ ማየት የሚከብድ አይመስለኝም። በነገራችን ላይ በጉባዔው ላይ ግንቦት-7ን ወክሎ የነበረው፤ ነዓምን ዘለቀ፤ የኢሳት ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው። ኢሳት የግንቦት-7 አይደለም ይባል የነበረውን ማደንቆሪያ ለማጋለጥ ከዚህ የበለጠ መረጃ የለም።

 

16. በተጨማሪም አቶ አንዳርጋቸው አሰብ በመሄዱ በቃለምልልሱ ላይ ቢቆጭም፤ ስለአሰብ ያነሳነው ግን ከላይ የጠቀስነውን የኃይል ሚዛን ያላገናዘበ ነው። ደግሞም አሰብ ከሄደ በኋላ 2 ዓመታት ወያኔን በማገልገሉ ብቻ በኤርትራ መገንጠልም ሆነ በአሰብ መሄድ ማንንም የመክሰስ የሞራል ብቃት የለውም። ስለዚህ አቶ አንዳርጋቸው ሊገነዘበው የሚገባው አላህ የተጠራልንን መለስ ሺህ ጊዜ ማውገዝ ፋይዳ የሌለው ከመሆኑ ሌላ፤ ጀሌዎችን እንጂ ሌላውን አድማጭ መሸንገል የማይቻል መሆኑን ነው።

 

17. ለነገሩ ኢሳያስ በቅርቡ እንደተናገረው ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛትና በአሰብ ጉዳይ ላይም ውይይት መጀመሩን አልደበቀም። የሚደንቀው ግን አንዳርጋቸው 'ጫካ ለጫካ ሲንከራተት' ኢሳያስ እንኳን ስለአሰብ የተዋዋለውን ውል አለመስማቱ ነው። ጫካ ያደድባል ይል ነበር፤ አብርሃም ያየህ!!

ደግሞም እኛ ነፃነት አፍቃሪና በታሪካችን የምንመካ ኢትዮጵያውያን አሰብ! አሰብ! የምንለው 1.5 ቢሊዮን ዶላር ለመቆጠብ ብቻ ሳይሆን፤ በሠላማዊ መንገድ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ግንኙነቶች በማጠናከር የቅኝ ግዛትን መርዝ፤ ቀስ በቀስ አምክነን፤ የመረብ ምላሴ ትውልድም (የዛሬዋ የባርነት አሻራ ኤርትራ ተፍቃ፤ በባሕረ-ነጋሽ ተተክታ ማለት ነው) ሆነ የተቀረው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ታላቋን ኢትዮጵያ ገንብቶ፤ በታሪኩ ኮርቶ በሠላምና በዲሞክራሲ ሥርዓት በልጽጎ የማየት የነበረውን የቅድመ አያቶቻችንና አያቶቻችን ራዕይ ስለምንጋራና ለአዲሱ ትውልድ እንዲተላለፍ የማድረግም ኃላፊነት ስላለብን ነው። ለሚያልፍ ዓለም የማያልፍ ስምና ሥራ ተክቶ ማለፍ የተማርነው ከአያቶቻችን ነውና።

 

ማጠቃለያ፤

18. ከላይ ዘርዝር አድርገን እንዳየነው፤ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ በወያኔ አገልግሎት፣ በቅንጅት ምስረታ፣ ቅንጅት ውስጥ ደግሞ ብዙም ባልገፋ 'የሚደቅሳ' ፖለቲካ ጫወታ፣ በቅንጅት መንፈስ የተላበሰ መሳይ ግንቦት-7 ምስረታ፣ ከጎሣ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሳሳብና ዛሬ ደግሞ በአደባባይ እንደሚነግረን በኤርትራ የተሰበሰቡትን የኢሳያስ የጎሣ ጦሮች፤ በሻዕቢያ ፍቃድ፤ 'ፖለቲካ' እያስተማረ ይገኛል። እንግዲህ ቀንቶት ለሁለተኛ ጊዜ የጎሣ ጦር አጅቦ አዲስ አበባ ከገባ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ትቀጥል? ወይም ትፍረስ? የሚለውን የኦነግን ሪፈረንደም ወደደም ጠላም ለማስፈጸም ይገደዳል ማለት ነው። አንዳርጋቸው በቃለምልልሱ ላይ እንደ ፈጣሪ ለማየት የዳዳው ኸርማን ኮኽንም፤ አስታራቂ ይሆንና ኦጋዴንም እንዲሁ እንደ ኦሮሚያ ልገንጠል? ወይስ ከኢትዮጵያ ጋር ልኑር? የሚል ምርጫ እንዲያካሂድ አጋጣሚው ይመቻቻል ማለት ነው። ባይ! ባይ! ደህና ሁኝ ሀገሬ! ይሉኻል ይኼ ነው!

እንግዲህ ግንቦት-7 አስቸጋሪ ለሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አስተማማኝ አቅጣጫ ለማመላከት አልቻለም። እንደውም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ወደ ተሸረበው ሁለተኛው ዙር ታላቁ ሴራ ዘው በማለት ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ከኢሳያስ ጉያ ውስጥ ገብቶአል። ግንቦት-7 የማይታረቁ ጉዳዮችን፤ ጎሣና የግለሰብ ነፃነትን በማምታታትና በመቀላቀል ከጠላት ጋር ወግኖ ነፃነትን ለማምጣት በመቃዠትና እንደ ኢሳት ያሉ የመረጃ አገልግሎቶችን እንኳን ነፃነት በመንፈግ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ የጭቆና ዘመን ማሳጠር ሲገባው እያራዘመው ይገኛል።

ዶ/ር ብርሃኑ ግንቦት-7ን ሲመሰርት፤ "እኛ እንጀምራለን። ካቃተን ግን እናቆማለን ብሎ ነበር።" አሁን ከእልህ ወጥቶ ቆም ብሎ የማሰቡ ጊዜ የደረሰ ይመስለኛል። በግል አንዳርጋቸውም ሆነ ዶ/ር ብርሃኑ በወያኔ ተጠቅመዋል። ግፍም ደርሶባቸዋል። ይሁን እንጂ ከኢሳያስ ጉያ ገብቶ በሀገር ጉዳይ ቁማር መጫወት አደገኛ እንደሆነ ሌላ ተልዕኮ ከሌላቸው ቁጭ ብለው ሊያስቡበትና፤ ትግሉ በመሃል ሀገር ብቻ እንዲጠናከር ሊሠሩ ይገባል። ኢሳትም እንደልቡ እንዲሠራ ድርጅታዊ ጭቆናቸውን ቢያቆሙ ይበጃቸዋል።

 

19. ደፋሩ የእነ አበበ ገላው ትውልድም ዳር ቆሞ ከሚያይ፤ የሠላማዊ ትግሉ በሀገር ቤት እንዳይዳፈን ተጨባጭ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል።

በ1995 የኢታሊያው ፕሬዝዳንት፤ ሊዊጂ እስካልፋሮ በኢትዮጵያና በኤርትራ የስራ ጉብኝት አድርጎ ነበር። ታዲያ ለዘመን መለወጫ የእንኩዋን ደስ ያላችሁ መልእክቱን ለኢታሊያውያን ሲያስተላልፍ፤ ኢሳያስ የነገረውንም አካፍሎ ነበር። "የኢትዮጵያው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፤ የለም የኤርትራው ማለቴ... የነገረኝ ልቤን ነካው። እንዲህ አለኝ። የቅኝ ግዛት ፖለቲካ ገዳይና አዋራጅ ነው። የኢታሊያ የቅኝ ግዛት ፖለቲካ ግን የተቀደሰ ነው። ለዚህም ነው ክቡር ፕሬዝዳንት የእኛ ፍቅር ሁል ጊዜ እንደጋለ(ሳይቀዝቅዝ) የቀጠለው።" ኢሳያስ እንግዲህ ይኼን ያለው፤ የገንዘብ እርዳታ ፈልጎ ወይም ከልቡ ሊሆን ይችላል። ለገንዘብ ሲል ምንም የማያደርገው ነገር የለም። ኢሳያስ አፈወርቂ የነፃነት መንፈስ የማያውቀው የፍሽት ባሪያ ነው የምንለው ለዚህ ነው።


ቦጋለ ካሣዬ (አምስተርዳም፤ 19/9/2013)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!