Prof. Al Mariam ፕ/ር ዓለማየሁ ገብረማርያም ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም (ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ)
ታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች ህልም አላቸው፤ ቀሪዎቹ በቅዠት የተሞሉ ናቸው።

በቅርቡ የአፍሪካ መሪዎች ቢያንስ በአፍሪካ ህብረት ስልጣን ያላቸውና የእነርሱ ጋሻ ጃግሬዎች ስለህግ ልዕልና፣ ስለዘር ማደን (ማሳደድ) የማያቋርጡ አስደንጋጭ የቅዠት ሪፖርቶች በገፍ እያቀረቡ ነው። ቅዠታቸውም የፍትህ ጎራዴ ስያሳድዳቸው በላብ ተጠምቀው ከእንቅልፍ ይነቃሉ።

 

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንደ ታይም መጽሔት አገላለጽ "የኬንያው አንደኛ ሀብታም ሰው" ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን ለማውገዝና ከስምምነቱ ለመውጣት በተጠራው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ በመገኘት ለመሰሎቹ በግልጽ እንደተናገረው በሌሊት ቅዠቶች በመሞላት እንቅልፍ ማጣቱን አሳውቆ እንዲህ ብሏል፣

"በአሁኑ ጊዜ በተለይም አገሬ እና እኔ እንዲሁም የእኔ ምክትል እንደግለሰብ እንቅልፍ ያሳጣንን ቅዠት ለእናንተ ክቡራትና ክቡራን ማሳወቅ ያለብኝ አይመስለኝም። የተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን የፍትህ ሂደት የሚዘውሩት የምዕራብ አገራት ኃያላን ናቸው። ኃያላኑ የዓለም አቀፍ የፍርድ ሂደቱን የሚጠቀሙበት ለማታለያና በኬንያ አመራር ላይ ጫና በመፍጠር የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎችን እነርሱ በሚፈልጉት መልክ ለማድረግ ነው። ሁልጊዜ የፍርድ ሂደቱን እንደማስፈራሪያ በመጠቀም ለእነርሱ አደግዳጊ አጎብዳጅ የሆኑ መሪዎች ወደ ስልጣን እንዲመጡ በማድረግ ለእነርሱ ምቹ የሆኑ ፖሊሲዎችና መርኃ ግብሮች እንዲተገብሩላቸው ማድረግ ነው። በዚህ ሁኔታ በረቀቀ ዘዴ በአፍሪካ አገሮች የመንግስት ለውጥ እንዲመጣ ሙከራ ያደርጋሉ። ለዚህም በብዙ መልኩ ተሳክቶላቸዋል። ከሁለት ሳምንታት በፊት ብቻ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ህግ በኬንያውያን ፕሬዚዳንታዊ አስተዳደር ላይ ዴሞክራሲያዊና ህገመንግስታዊ ያልሆነ ማሻሻያ እንዲደረግ ሀሳብ አቅርቧል። እነዚህ በውስጣዊ የአገር ሉዓላዊነታችን ዘንድ የሚደረጉ ጣልቃገብነቶች ከምንታገሰው በላይ ሄደዋል፣ አነዚህ ድርጊቶች ለኬንያውያንና ለአፍሪካውይን ትልቅ ስድቦች ናቸው። የአፍሪካ ሉዓላዊነት ለተባበሩት መንግስታት የወንጀለኞች ፍርድ ቤትና ለደጋፊዎቹ ጉዳያቸው አይደለም።"

አንዳንድ ጊዜ ህይወት እንቆቅልሽና ግራ አጋቢ ይሆናል። ኡሁሩ ኬንያታ የኬንያ ፕሬዚዳንት የመሆን ህልሙን (በነገራችን ላይ አባቱ ጆሞ ኬንያታ የኬንያ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ነበሩ) ባለፈው መጋቢት ወር በተደረገው ምርጫ በጠባብ ልዩነት 50.7% ድምጽ በማግኘት አሸናፊ ሆኖ የስልጣን እርካቡን ተቆናጧል። ኬንያታ ባለፈው ጊዜ በፈጸማቸው ወንጀሎች ሳቢያ በተደጋጋሚ በሚያስፈራ ሙት መንፈስ እየተጎበኘ አሁን ደግሞ "በዘር አዳኞች" እየተፈለገ በአስቸጋሪ ሁኔታ የቅዠት ህይወትን በመግፋት ላይ ይገኛል። ኬንያታ እንዲህ ብሏል፣ "ህዝብ የአሁኑን ሁኔታ (የዓለም ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደትን) 'ዘር አደና' ብሎ ሰይሞታል፣ ድርጅቱ የያዘውን አቋም ስህተት ነው ብዬ ለማሳመን በከፍተኛ ችግር ላይ ወድቄ እገኛለሁ።" ሳይኮሎጅስቶች እንደሚሉት በህዝብ ዘንድ በጣም የተለመደው ቅዠት በስሜት በተሞላ ምዕናባዊ ጭራቅ፣ አስፈሪ መንፈስ፣ ጠንቋይና በእብድ መሳደድ ነው። በኬንያታ ቅዠት ቀንድና የመጋዝ ጥርስ ያለው ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቢዎችና ዳኞች ላብ በላብ እስኪሆን እያሳደዱት እንደሆነ ይሰማዋል።

አሁን ባለፈው ወር እንኳ ኬንያታ በሞይ ኤልዶሬት ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች ምረቃ በዓል ስነስርዓት ላይ በመገኘት ባሰማው ንግግር የሚከተለውን ብሎ ነበር። "እኔ፣ ዊሊያም ሩቶና ጆሹዋ ሳንግ ነጻ ሰዎች መሆናችንን የማያውቅ ማን ነው? እያንዳንዱ ዜጋ ቢያንስ ማን መዋጋትንና በማሳደድ ብጥብጥና ሁከት በዚህች አገር ውስጥ እንዲንሰራፋ እንደሚወድ ያውቃል፣ በመሆኑም እ.ኤ.አ በ2008 የተደረገውን ሀገር አቅፍ ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሰውን የማስገደል ዕቅድ በእኛ በኩል እንዳልተደረገና እኛ አጃችን የሌለበት መሆኑን ህዝቡ ይመሰክርልናል። "ኬንያታ በተደጋጋሚና በኩራት "ጉዳዩ በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መታየት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ለእኔ ስሜን ለማደስ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርልኛል በማለት በሙሉ ልብ ለፍርድ ቤቱ ትብብሬን ሳደርግ ቆይቻለሁ። ከተመረጥኩ በኋላም ሙሉ በሙሉ ትብብር ማድረጉን ቀጥለንበታል፣ ለ5 ዓመታት የነበረውን ውጥረት በመቋቋም ሙሉ ትብብሬን ሰጥቻለሁ።" ብሏል።

አሁን ግን ኬንያታ መተባበር እንደማይችል ይናገራል። ከዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደማይኖረው ይገልጻል። እሱና (የእርሱ መሰል የአፍሪካ ህብረት ባለስልጣን ተባባሪዎቹ) እስከሚያወቁት ድረስ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ገሃነብ መሄድ ይችላል። ኬንያታ አስረግጦ እንደተናገረው በምንም ሁኔታ ቢሆን ሄግ በተቋቋመው የፍርድ ሂደት ላይ እ.ኤ.አ ህዳር 12/2013 የእኔን ጉዳይ ለማየት በተያዘው ቀጠሮ ላይ አልገኝም፣ ምን ይመጣል? አሁን ሙሉ በሙሉ ነጻ መሆኑን በእርግጠኝነት የሚናገረውና ባለፉታ አምስት ዓመታትም ለፍርድ ሂደቱ ስኬት ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሙሉ ትብብር ሲያደርግ የቆየው ኬንያታ አሁን መንቀጥቀጥ፣ ስሜቱን መቆጣጠር ለምን አንዳቃተውና በላብ መዘፈቁ እንዲሁም ቀጥ ብሎ ለመሄድ አለመቻሉና በሀሰት በተቀነባበረ ክስ በሚለው ለስሙ፣ ለዝናውና ለክብሩ ሲል አለመታገሉ አስገራሚ ነው! የሸክስፒርን አባባል በመዋስ "እኔ እንደሚመስለኝ ብዙ ከንቱ ተቃውሞ አድርጓል።"

 

ለመሆኑ የዓለም ወንጀለኞች ፍር ድ ቤት የማን ፍርድ ቤት ነው?
ኡሁሩ ኬንያታ፣ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ባሽርና ተባባሪዎቻቸው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በቀልተኛና ዘረኛ "የነጮች ፍርድ ቤት" መሆኑን አንድናምንላቸውና 70 በመቶ ያህሉን ገንዘብ የሚያገኘውም ከአውሮፓ ህብረት መሆኑን ይናገራሉ። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የዓለም የወንጀለኞች ፍርድ ቤት 99 በመቶ የሚሆኑትን ኢላማ ያደረገው በአፍሪካውያን ላይ ስለሆነ ድርጅቱ "ዘር አዳኝ" ነው በማለት አስደንጋጭ ክስ አሰምተዋል። (እ.ኤ.አ በ2010 በኢትዮጵያ በተደረገው አገር አቀፍ ፓርላሜንታዊ ምርጫ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ፓርቲ 99.6 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸናፊ ሆኗል።) እውነታዎቹ ግን በተቃራኒው ይናገራሉ። የተባበሩት መንግስታት የዓለም የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲቋቋም የሮምን ስምምነት ከፈረሙት 122 አገሮች ውስጥ 34ቱ ወይም 28 በመቶው ኬንያን ጨምሮ አፍሪካውያን ናቸው። ከድርጅቱ 18 ዳኞች 5ቱ ወይም 28 በመቶው አሁንም አፍሪካውያን ናቸው። የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሳንጂ ማሴኖኖ ሞናገን ከቦትስዋናና ፋቱአ ቤንሱዳ የዓለም የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ህግ ከጋምቢያ የታወቁና በዓለም አቀፍ ህግ ችሎታቸው ዝናን ያተረፉ አፍሪካዊ ሴቶች ናቸው።

የደቡብ አፍሪካው መንፈሳዊ ዴዝሞንድ ቱቱ ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ያልተቆጠበ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፣ እንዲህም ይላሉ "እስከ አሁን ድረስ ደካሞችን ከኃይለኞቹ ለመጠበቅ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ትልቅ እመርታ እያሳየ መሆኑን እያየሁ ስለሆነ ትልቅ ተስፋ እየሰጠን ነው። ስለሆነም የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አንዱ የተስፋችን የአክሊል ቀንዲላችን ነው" ብለዋል። እንዲሁም የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ጋናዊው ዋና ጸሀፊ ኮፊ አናን በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ የቀረበውን ስም አጥፊ ክስ በመቃወም እንዲህ ይላሉ፣ "የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጸረ አፍሪካዊ ነው የሚለውን ሀሳብ አልጋራውም። የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አፍሪካውያንን በክስ ላይ አላቆመም፣ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እየተዋጋ ያለው በሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል የተዘፈቁትንና ከተጠያቂነት ለመሸሽ የሚጥሩትን አምባገነኖች ነው። እርግጥ ነው የአውሮፓ ህብረት ትልቁን የገንዘብ ድርሻ ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሊሰጥ ይችላል፣ ነገር ግን ብዙው የድርጅቱ ቦታ በአፍሪካውያን የተያዘ መሆኑ ሊካድ አገባም"!

 

ቅርጽና እውነታ፣ ኡሁሩ ኬንያታንና ግብረአበሮቹን ወደ ፍትህ ለማቅረብ በቂ ማስረጃ አለን?
የአፍሪካ መሪዎች ሀሳብን የማስቀየስ ጌቶችና የማታለል ንጉሶች ናቸው። የሚሰነዘሩባቸውን ትችቶች አቅጣጫ ለማስቀየስ እንዲሁም ከተጠያቂነትና ግልጽነት ለማምለጥ ሲሉ ሌላ ደንቃራ በማጀል የተካኑ ናቸው። በስሜቶቻችን ላይ እንደማሲንቆ ይጫወታሉ፣ የማሰብና ምክንያታዊ አቅማችንን በማሳነስ ንቀትን ያሳያሉ፣ የሞተውንና የተቀበረውን የኢምፔሪያሊዝምንና ቅኝ ገዥነትን ጭራቅነት በማንሳት ታሪካዊ ብሶታችንን ብቻ በየጊዜው እያነሳን ስሜቶቻችንን እንድናስጨንቅ ይጥራሉ። የኒዮኮሎኒያልና ኒዮሊበራል ህገወጥነትን በስሜቶቻቸን ላይ በማጀል እንድንፈራ ጥረት ያደርጋሉ። ህሊናችን በሀሰት በተፈበረኩ የዘረኝነት ውርደት ስሜት እንዲጠመድ በማድረግ "ትልቁ ነጭ ዘር አዳኝ" በአፍሪካ ላይ እያንዣበበ እንደሆነ ለማስረዳት ይፍጨረጨራሉ፣ ተፈጥሯዊ አዛኝነታችንንና ፍቅራችንን በመጠቀም እራሳቸውን ምንም ድጋፍ የሌላቸው በማስመሰልና በደል ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ በማድረግ ላይ ያለውን ድርጅት እንደ ጭራቅ እንዲቆጠር ይሞክራሉ። የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እያንዳንዱን የአፍሪካ ዜጋ ለመከታተል እየመጣ እንደሆነ አድርገው ሊያሳምኑን ይሞክራሉ። በአጭሩ ከቁንጫ የበለጠ ዕውቀት እንደሌለን አድርገው ይቆጥራሉ።

የኬንያታን የክስ ሁኔታ በአንክሮ ላልተመለከተና በቀረበው ስሜታዊነት ላይ በመመስረት ግንዛቤ የሚያደርግ ሰው ካለ ወደተሳሳተ አቅጣጫ ሊሄድ ይችላል። በተጨባጭ ያለው መረጃ እንደሚያሳያው ግን በኬንያታ ላይ የቀረበው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ በማይረባና ሰውን ለመወንጀል ሲባል ሆን ተብሎና በሀሰት በተፈበረኩ መረጃዎች የተሞላ አይደለም።

ኬንያታ የተከሰሰው በአስደንጋጭና በመረጃ በተደገፉ ሰነዶች በተረጋገጡ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀሎች ነው። ብዙዎቹ ማስረጃዎች በነጻ አካል የተረጋገጡና በአግባቡ የተዘጋጁ ናቸው።

የተራጋገጡ ውንጀላዎች በጣም ውስን ናቸው። ለምሳሌ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርደ ቤት ቅድመ ክስ ቻምበር (የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ህግ ጉዳዩ ለፍትህ እንዲቀርብ ያጸደቀው) እንደወሰነው እ.ኤ.አ ጥር 3/2008 በናይሮቢ ክለብ በመገኘት ሚስተር ኬንያታ ከሙንኪጊ አባላት አንዳንድ ጊዜም "የኬንያ ማፍያ" እየተባሉ ከሚጠሩት ጋር በመዶለት ክስ የተመሰረተበትን ወንጀል እንዲፈጽሙ አዟቸዋል። የቀረበው መረጃ እንደሚያሳየው ኬንያታና ግብረአበሮቹ የተገኘወን አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም የቀድሞው የኪባኪ ናሽናል ዩኒቲ ፓርቲ አባላት በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ድርጅታዊ ፖሊሲ በመንደፍ እና ፖሊስ የወንጀል ድርጊቱን ሳይቀር አንዳያስቆመው በማድረግ ከባድ ወንጀል ፈጽመዋል። መረጃው እንደሚያሳየው ኬንያታና ግብረ አበሮቹ በብርቱካናማው ዴሞክራቲክ ንቅናቄ (ኦዲኤም) ደጋፊዎች ላይ ሰፊና የተቀነባበረ ጥቃት ለማድረስ የጋራ ስትራቴጅ በመንደፍ 1ኛ) የብቀላ ጥቃት እንዲፈጸምባቸው አድርጓል፣ 2ኛ) ሆን ተብሎ የብቀላ ጥቃቱ እንዳይቆም እርምጃ እንዳይወሰድ አድርጓል። አሁንም መረጃው እንደሚያሳየው ኬንያታ በናሽናል ዩኒቲ ፓርቲ (ፒኤንዩ) እና በሙንጊኪ የወንጀለኞች ድርጅት መካከል በመሆን የአስታራቂነት ሚና በመጫወት ከኖቬምበር 2007 ጀምሮ የፒኤንዩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ፖለቲከኞች፣ የቢዝነስ ሰዎች እና የሙንጊኪ አመራሮች እ.ኤ.አ በዴሴምበር 2007 ለሚደረገው ምርጫ መንግስትን በመደገፍ የሙንጊኪ እርዳታ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። በድህረ ምርጫው ማግስት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኬንያታና ሌሎች በኦዲኤም ደጋፊዎች ላይ በስምጥ ሸለቆ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ከሙንጊኪ ጋር ስብሰባዎችን በማካሄድ ከፕሬዚዳንቱ ቃለመሀላ በኋላ የፒኤንዩን ስልጣን በማጠናከር እገዛ አድርገዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኬንያታና ሌሎች የጋራ ዕቅድ በመንደፍና ተግባራዊ እንዲሆን በማገዝ የኬንያ ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ጥቃቱን እንዳያስቆመውና ዋናዎቹ የጥቃቱ ተዋንያኖች ለህግ እንዳይቀርቡ አድርገዋል።

ሁለተኛው የቅድመ ፍትህ ቻምበር ኬንያታና ግብረአበሮቹ የተባለውን ወንጀል መፈጸማቸውን በበቂ መረጃ በማረጋገጥ ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው ወሰነ። የፈለገ በ155 ገጽ በዝርዝር የቀረበውን እና የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በአንቀጽ 61 (7) (a) እና (b) በኬንያታና በግብረ አበሮቹ ላይ የቀረበው ውንጀላ ለክስ የሚበያቃ መሆን አለመሆኑን በእልህ አስጨራሽና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ በዓለም አቀፉ የወንጅል ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ህግና በቅድመ ፍትህ ቻምበሩ የኬንያታን ፍትህ የማግኘት መብት ለመጠበቅ የተዘጋጀውን ማንበብ ብቻ በቂ ነው። በመሆኑም በአፍሪካ ስሜታዊ እራስ ወዳድ የእባብ ዘይት ሻጮች ለተሰነዘረው ክስ ማጎብደድ የለብንም።

 

እንቅልፍ ማጣት በአፍሪካ፣
ሁልጊዜ ሌሊት የፍትህንና እረዳቷን ቅዠት የሚፈራውና እንቅልፍ አልባ የሆነው ኬንያታ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች ጭምር ናቸው። የአፍሪካ መሪዎች "በአይሲሲ የሌሊት ቅዠት" (በሌሊት በላብ ተዘፍቀው የሚነቁ፣ ጥርሳቸውን የሚነክሱ፣ እራሳቸውን የሚያኩና ምንጣፋቸውን እያዩ ስለ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ህግ ለማሰብ ልምድ ላላቸው የአፍሪካ መሪዎችን ለመግለጽ ያዘጋጀሁት) በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያው የይስሙላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ላለፈው አንድ ዓመት የሟቹን ባለራዕይ ጠቅላይ ሚኒስትር ራዕይ እንደሚያሳካ ሲነግረን ቆይቷል። አሁን ደግሞ በእርግጥ ራዕዩ "ትልቁ ነጭ አዳኝ" የሌሊት "የዘር አደን" ቅዠት ውስጥ ተዘፍቆ እናገኘዋለን። የሩዋንዳው ፓውል ካጋሜ "ኢምፔሪያሊስቶቸና ቅኝ ገዥዎች" በስውር እንደ ዳኛና አቃቤ ህግ ሆነው የአፍሪካ መሪዎችን ለመያዝና ለማሰር ወደ አፍሪካ በመመለሳቸው ቅዠት ውስጥ ገብቷል። የሱዳኑ ኦማር አልባሽር በቤተመንግስቱ ውስጥ መሽጎ የአይሲሲ ጭራቆች ሊይዙት እያንዣበቡበት መሆኑን አያየ ይቃዣል። የደቡብ አፍሪካው ታቦ ኢምቤኪ የምዕራቡ ዓለም አታላዮች፣ እምነተ ቢሶች በድብቅ በአፍሪካ ጨለማ እየተጓዙ ስለመጡ እያዘገመ የመጣውን ንቀታቸውን ለመከላከል አብረውት እንዲታገሉ ለአፍሪካ ምሁራን ጥሪ አስተላልፏል። የኡጋንዳው ዮሪ ሙሴቬኒ በ2003 ከልብ በመነጨ መልኩ በበጥባጭነቱ የሚታወቀውን ጆሴፍ ኮኒን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለማስረከብ ተስማምቶ በ2013 ግን አይሲሲ መሰል ጓደኞቹን እየመረመረ መያዝ ሲጀምር በግልብና በእብሪት ቅዠት ውስጥ መዋኘት ጀመረ።

ሌሎች ብዙ የአፍሪካ መሪዎች ተስፋ በመቆረጥ መልኩ የአይሲሲ ሙትምስል በፈረስ ላይ ሆኖ ገና ከአድማስ ጫፍ ሲመለከቱት በሰሩት የሰብአዊ መብት ረገጣ አንድ ቀን ተይዘው እንደሚጠየቁ በማሰብ በፍርሀት መራድ ጀመሩ። ከ60 የነጻነት ዓመታት በኋላ እንደ ኔልሰን ማንዴላ የመሳሰሉት የአፍሪካ መሪዎች ሰለአፍሪካ ያላቸውን ራዕይ ነበር ግዴታቸው: "በውስጧ ሰላሟ የተጠበቀ አፍሪካን እመኛለሁ።" ሰብአዊ መብት ረጋጮች ከፈጸሙት የሰብአዊ መብት ረገጣና ከተጠያቂነት ቅዠት ለማምለጥ የሚያደርጉት መፍጨርጨር በጣም የሚያስገርም ነገር ነው። ሆኖም ግን እውነተኛው ቅዠት - ህይወት ያለው ቅዠት - በአፍሪካውያን ህዝቦች ላይ ውጤት እያመጣ ነው። ከ2003 ጀምሮ አልባሽር በሱዳን በዳርፉር ክልል የማያቋርጥ የዘር ፍጅት በመፈጸሙ በተባበሩት መንግስታት መረጃ ግምት መሰረት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያለቀበትና ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ደግሞ የተፈናቀለበት ፖሊሲ በመንደፍ እልቂቱን አስፈጽሟል። በ2005 በኢትዮጵያ በመንግስት የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት መሰረት ድህረ ምርጫውን ተከትሎ 193 መሳሪያ ያልያዙ ሰላማዊ ተቃዋሚ ዜጎች ተገድለዋል፣ 763 ሰላማዊ ዜጎች በጥይት ተደብድበው ቁስለኞች ሆነዋል (ይህም በትንሹ የታየው ነው)፣ ቀደም ባለው ዓመት በጋምቤላ ክልል ከ400 በላይ ነዋሪዎች ተገድለዋል። በ2008 በኦጋዴን አካባቢ በታጣቂዎች በተከፈተ የእሩምታ ተኩስ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ አካለ ጎደሎ፣ የሞቱና መፈናቀል የደረሰባቸው ሆነዋል።

በ2007-2008 በተባበሩት መንግስታት ግምት መሰረት በኬንያ ለሳምንታት ለቀጠለውና በዴሴንበር 2007 እና ፌብሯሪ 2008 መካከል በተካሄደው ብጥብጥ ወደ 1200 የሚሆኑ ሰዎች ሲሞቱ፣ 600 000 የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ተፈናቅለዋል። በዚያ ብጥብጥ ኬንያታ ከደሙ ንጹህ ነኝ ምንም ጥፋት የለብኝም ሲል ቆይቶ ነበር በኋላ የአይሲሲ ዋና አቃቤ ህግ ያለምንም ጥርጣሬ ኬንያታ ድርጊቱን መፈጸሙን አስከሚያረጋግጥ ድረስ።

በ2010 የኮትዲቯሩ ሎሬንት ባግቦ በመለያ ምርጫው በተቀናቃኙ ተሸነፎ ስልጣን አላስረክብም አለ። በአሁኑ ጊዜ ባግቦ በሄግ በተሰየመው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፍርዱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። (የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባግቦ ወደ ሄግ እንዲሄድ በተደረገው ጥረት የአፍሪካ መሪዎች ምንም ጆሮ አልሰጡም ነበር)። በተባበሩት መንግስታት ግምት መሰረት የድህረ ምርጫውን ብጥብጥ ተከትሎ በተቀሰቀሰው ሁከት 3000 ሰዎች ኮትዲቯር ተገድለዋል።

በ2011 በሊቢያ የመጀመሪያዎቹ የአመጽ ቀናት ሞአማር ጋዳፊ በተቃወሙት በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ በቁጥጥር ስር የማዋል፣ የእስራትና የሞት ትዕዛዝ በማዘዝ አስፈጸመ። በ2012 ተገንጣይ የማሊን ሰሜናዊ ክፍል የተቆጣጠሩት አማጺያንና ሚሊሻዎች ለመግለጽ በሚያስቸግር መልኩ የሰበአዊ መብት ረገጣና የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል። በ2013 በሩዋንዳ ኤም23 በሚደገፉት አማጺያንና በዴሞክራቲክ ኮንጎ ተፋላሚዎች መካከል በተካሄደ ጦርነት በምስራቅ ዴሞክራቲክ ኮንጎ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አካለ ጎደሎ ሆነዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ተገድለዋል። ይህ ከብዙ በጥቂቱ የአፍሪካ መሪዎች ቅዠት ነው።

 

የአፍሪካ መሪዎች አይሲሲን በዓለም ህዝብ ሕሊና ፍርድ ቤት በማቅረብ የሌሊት ቅዠታቸውን ለማስወገድ ይፈልጋሉ፣
የአፍሪካ ህብረት አመራር አይሲሲን በዓለም ህዝብ ፊት ለፍርድ በማቅረብ የብልጣብልጥነት ታክቲክ በመጠቀም ቅዠታቸውን ለማስወገድ ይሞክራሉ። እስቲ ይታያችሁ በወንጀል የተዘፈቁት እነዚህ የሰብአዊ መብት ረጋጮች አቃቤ ህጉንና ዳኛውን በወንጀል ሊያስቀጡ ሲሞክሩ! የአፍሪካ ህብረት የህዝብ ግንኙነት ስትራቴጂ አይሲሲ ከአሜሪካው Seal Team 6 ወይም ከእንግሊዙ Special Air Service ከሚባሉት በድብቅ ከጠላት አገር ገብተው የተለየ አላማን ለማሳካት ከሚያከናውኑ ኃይሎች ጋር እኩል አስመስሎ ለማሳየት ነው። ለዚህም ነው ኬንያታ የምዕራቡ ኃያላን የአይሲሲ ሂደት ቁልፍ ዘዋሪዎች ናቸው ያለው። የህግ ሂደትን እንደማታለያ በመጠቀም የኬንያን አመራር በማስፈራራት የተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች በሌላ እንዲያዙ ጥረት ያደርጋሉ። አይሲሲ በኬንያ ላይ የሚያንቀሳቅሰው "የጨለማው ኃይሎች" ክስ ምንም ትርጉም አይኖረውም። ኬንያ ለምዕራቡ ዓለም ሽብርተኝነትን ወይም በህንድ ውቅያኖስ የባህር ላይ ዘራፊዎችን በመዋጋት ዋና እረዳት እና ለደህንታቸው ማዕከል ናት። በ2013 ለአሜሪካ ኮንግረስ ተጠንቶ በቀረበው መረጃ መሰረት አሜሪካ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየዓመቱ ለኬንያ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እርዳታ የምትሰጥ ሲሆን ይህም ከአሜሪካ እርዳታ ተቀባይነቷ ከዓለም በ10ኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል። በ2011 የበጀት ዓመት አሜሪካ ለኬንያ የሰጠችው እርዳታ 200 ሚሊዮን የምግብና ሌሎች ሰብአዊ እርዳታዎችን ጨምሮ 900 ሚሊዮን ደርሷል። በ2012 የበጀት ዓመት ኬንያ ከ700 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ እርዳታ ያገኘች ሲሆን 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደግሞ በሁለትዮሽ/በባይላተራል ስምምነት እንዲሁም 8 ሚሊዮን ዶላር የውጭ መጠባበቂያ ፈንድና ወደ 200 ሚሊዮን የሚጠጋ የሰብአዊ እርዳታ በተጨማሪም ለአሚሶን ወታደሮች ድጋፍ አድርጋለች። ለ2014 የበጀት ዓመት የአሜሪካ መንግስት መምሪያ ለኬንያ 564 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አስቸኳይ ላልሆነ እርዳታ እንዲያዝላት ጠይቋል። ይህም ለምግብ እርዳታ ወይም የተለዩ ለደህንነት የተያዘውን አያካትትም።

ኬንያ ከአሜሪካ መንግስት መምሪያ በማያከራክር ሁኔታ ትልቁን የጸረ ሽብር አርዳታ በጸረ ሽብር ስልጠና፣ በወታደራዊ መሳሪያና በደህንነት ጥበቃ ቴክኖሎጂ በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር እርዳታ ተጠቃሚ ናት። አሜሪካና ኬንያ በጋራ ጸረ ሽብር ግብረ ኃይልና በጋራ የስለላ ልውውጥ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ። እውነት ለመናገር አሜሪካ ለኬንያ ለጸረ ሽብር እርዳታ በገፍ እየሰጠች ለሰብአዊ መብት ረገጣው ግን አይታ እንዳላየች፣ ሰምታ እንዳልሰማች፣ መናገር እየቻለች እንዳልተናገረች ተደርጎ ከፍተኛ ትችት ይሰነዘርባታል።

የአውሮፓ ህብረት ጸረ ሙስና ላይ ትኩረት በማድረግ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን ለማሻሻል፣ የፍትህ ስርዓቱ ተደራሽ እንዲሆን፣ ለምርጫና ለሲቪክ ኢዱኬሽን፣ ለአካባቢያዊ አስተዳደር፣ ለህግ ማሻሻያ፣ የሰብአዊ መብትን ለማስፋፋትና ለመጠበቅ፣ የፐብሊክ ሴክተሩን ለማሻሻል፣ ለተቋማዊና አቅም ግንባታ በርካታ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለኬንያ እርዳታ ሲሰጥ ቆይቷል። ናይሮቢ በአፍሪካ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የልብ ትርታ በመሆን ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች አግልግሎት በመስጠት ላይ ትገኛለች። በናይሮቢ ከተማ ጊጊሪ በተባለው ቦታ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤት ከኒዮርክና ከጀኔቫ በመቀጠል በዓለም ትልቁ አህጉራዊ የተባበሩት መንግስታት ማዕከል ነው ይባልለታል።

እንዴት ኬንያታ ፊት ለፊት "የምዕራቡ ዓለም ኃያላን የፍትህ ሂደቱን እንደማታለያና በሚፈልጉት የኃላፊነት ቦታ ላይ እነርሱ የሚፈልጉተን ለማስቀመጥ ነው" ብሎ ይናገራል? እስቲ እውነት እንነጋገር ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ያለምዕራቡ ዓለም ምጽዋት መኖር ይችላሉን? ካለጭራቁ የዓለም ባንክና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ብድርና እርዳታ መቆየት ይችላሉን? ታላቁ የአሜሪካ የስራ ሰው ፈላስፋ ኤሪክ ሆፈር እንዲህ ብሏል። "የሚመግቧቸውን እጆች የሚነክሱ ሰዎች ሁልጊዜ የሚረግጣቸውን ጫማ ይልሳሉ።"

 

ቅዠቶች በየቦታው፣
በእርግጥ ማንም በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ ከተናገሩት መሪዎች ውስጥ ስለረዳት የለሾች፣ ስለአቅመቢሶች፣ ስለተከላካይ የለሽ የዳርፉር ነዋሪዎች በአሁኑ ጊዜ በጃንጃዊድ (በፈረስ ጀርባ ላይ ያሉ ጭራቆች ማለት ነው) ሚሊሻዎች እየተሳደዱ ለመሀናቸው አውነተኛ ቅዠት የተናገረ የለም። በኢትዮጵያ በኦጋዴንና በጋምቤላ አካባቢዎች ህዝብን ፈጅተው የሰብአዊ መብት ረግጠው በቅዠት በሚኖሩ የሰብአዊ መብት ረጋጮች ላይ ማንም በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ የተናገረ መሪ አልነበረም። በአሁኑ ጊዜ በዴሞክራቲክ ኮንጎ ላይ እየተካሄደ ስላለው የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል ማንም ትንፍሽ ያለ መሪ አልታየም። በጥባጩን ጨፍጫፊ የኡጋንዳውን ጆሴፍ ኮኔ ለመያዝና ለፍርድ ለማቅረብ የተደረገ ጥረት ሪፖርት ማንም መሪ በስብሰባው ላይ አላቀረበም። በግድያ፣ በማሰቃይት፣ አካለጎደሎ በማድረግ፣ በአስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋና ቅሚያ በመፈጸም በየቀኑ በመቃዠት ላይ ስላሉት ወንጀለኞች አንድም የአፍሪካ መሪ በስብሰባው ላይ ሲያልፍ እንኳን አልተናገረም።

እውነት ለመናገር ቅዠቶች ለአፍሪካ መሪዎች፣ ለተጠቂዎች፣ ከጥቃት ለተረፉት ብቻ በሞኖፖል የተሰጡ አይደሉም፣ ሁላችንም ብንሆን ቅዠቶችን ለማየት ዕድሉን ላላገኘንና ምስክርነት ለመስጠት ባንችልም የነዚያ ጭራቅ ቅዠቶች እኛም ቅዠቶች አርጎናል። ምክንያቱም የአፍሪካ የፖለቲካና አማጺያን መሪዎች እንደዚያ ያለ አስቀያሚና አስደንጋጭ የሰብአዊ መብት ይረግጣሉ ብለን እራሳችንን ለማሳመን ስለምንቸገር ነው። ሁላችንም በውል ባልታወቀ ቅዠት ውስጥ ተተብትበን እንገኛለን። ከእልቂት የተረፈው ኤሊ ዌይሴል "ጨለማ" በሚለው መጽሀፉ እንዲህ ይላል፣ "ከእኛ ብዙም ሳይርቅ ከጉድጓዱ የእሳት ነበልባል ይንቀለቀላል ... ህጻናት! አዎ በአይኔ በብረቱ አየሁት... ፊቴን ቧጠጥኩ፣ ግን አሁንም በህይወት አለሁ? ነቅቸ ነበርን? ማመን አልችልም፣ አነርሱ እንዴት ሰውን፣ ህጻናትን ሊያቃጥሉ ቻሉ? እና ዓለምስ እንዴት ዝም አላቸው? አንዱም ቢሆን ይህ እውነት ሊሆን አይችልም፣ ቅዠት ነበር ..."

በጥቂት ወራት ውስጥ እንዴት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሩዋንዳውያን በዘር ማጥፋት ፍጅት ያልቃሉ? ዓለምስ እንዴት ጆሮ ዳባ ልበስ አለ? ወይም ግማሽ ሚሊዮን ዳርፉራውያን ሲያልቁና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሲፈናቀሉ እንዴት ዓለም ዝም አለ? ከ200 ሺህ በላይ ሴራሊዮናውያን እና ላይቤሪያውያን ሲጋደሉና ሲተራረዱ አሁንም ዓለም ዝም? ከ50 ሺህ በላይ ኢኳቶሪያል ጊኒያውያን ሲዋረዱ፣ሲያልቁ አሁንም ዓለም ዝም? በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ማሰቃየት ሲፈጸምባቸው (በዚህ ባለፈው ሳምንት ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ባለ 70 ገጽ ሪፖርት መሰረት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች፣ ህገወጥ የአጠያየቅ ዘዴዎች፣ ማዕከላዊ እየተባለ በሚጠራው እስር ቤት የታየው ደካማ የእስር ቤት አያያዝ እና ግድያ) ዓለም ዝም ማለቱ?

ኤሊስ ዌይልሴ የሚያስተምረን "ኢፍትሃዊነትን ለማስቆም አቅመቢስ የምንሆንበት ጊዜ ይኖራል፣ ነገር ግን ለማመጽ ጊዜ ልናጣ በፍጹ አንችልም" ለዚህም ነው ድምጻችንን ከፍ አድርገን መናገር ያለብን፣ ማመጽ፣ መጮህና መቃወም። የኢፍትሀዊነት ሰለባ ለሆኑና ፍትህን ለሚፈልጉ ሁሉ ፍትህን ከመጠየቅ ወደ ኋላ ማፈግፈግ የለብንም።

 

የአይሲሲን የፍርድ ሂደት ማዘግየት ቅዠቱን አያቆመውም፣ እንዲያውም እንዲራዘምና ጠንካራ እንዲሆን ያደርገዋል፣
ኬንያታ የአይሲሲን ሙዚቃ መጋፈጥ አልፈለገም። የፍርድ ሂደቱን በማዘግየት እሱና የእርሱ ምክትል ሩቶ የመንግስታዊ ስራቸውን ማከናወን ይፈልጋሉ። የአፍሪካ ህብረት መሪዎችና የኬንያታ የህግ ጠበቆች የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በሮም ስምምነት አንቀጽ 16ን መሰረት አድርጎ የኬንያታ ጉዳይ ለ12 ወራት እንዲራዘምና በቀጣይም እንዲራዘም የሚያሳስብ ነው። ማዘግየት የሚለው ማቆየት ለሚለው የገባ ቃል ሲሆን እንደ ወንጀልን መከላከል ህግ ከሆነ ማዘግየት የጥንቱ የማታለያ ዘዴ ነው። ጊዜ ባለፈ ቁጥር ለተከሳሹ ጠቃሚ ነው። ማዘግየት ሁልጊዜ ለወንጀለኛው የአሸናፊነትን ዕድል ይሰጣል። የወንጀል መከላከል የህግ ባለሙያዎቸ በሶስት የ'መ' ኮዶች ይመራሉ፣ እነርሱም "ማዘግየት፣ መካድ፣ መከላከል" ናቸው። አንድ የክስ ጉዳይ ከዘገየ ብዙ ነገሮች ሊከተሉ ይችላሉ፣ ምስክሮች ቦታ ሊቀይሩ ይችላሉ፣ ወይም ሊሞቱ ይችላሉ፣ ወይም ቀደም ሊመሰክር የነበረውን ይቀይራል፣ ወይም የሀሰት ምስክርነት ይሰጣል፣ ወይም ደግሞ ምስክሩ በጊዜ ሂደት ዝርዝር ሁኔታውን ማስታወስ ይሳነዋል፣ በትልልቅ ጉዳዮች ላይ የህዝብ ሀሳብ ሊሰረቅና ህዝብም ዝምተኛ ሊሆን ይችላል፣ ወይም በፖለቲካና በዘር ላይ ያነጣጠረ ክስ አስመስሎ ለህዝብ በማቅረብ ድጋፍ አግኝቶ ለማምለጥ ይሞከራል። ጠንካራ አቃቤ ህግ በደካማና በግዴሌሽ፣ ፍትህ መስጠትን ወደ ጎን ትቶ ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት ወይም ክሱን ለመሰረዝ በሚሞክር አቃቤ ህግ ሊተካ ይችላል።

ነጸ መሆኑንና ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ለአይሲሲ መረጃ በመስጠት እገዛ ሲያደርግና በኩራትና በጩኸት ሲናገር የቆየው ኬንያታ እንዴት ፈጣን የፍርድ ሂደትን ሊጠላ እንደቻለ፣ እንዴት ማዘግየት እንደፈለገ ሲታሰብ አስገራሚ ነው። የዘገየ ፍትህ እንደታካደ መቆጠር ብቻ ሳይሆን ኢፍትሀዊነትን ማራዘም ጭምርም ነው። ሆኖም ግን በመከላከል ህግ እንደማውቀው ሁሉ የዘገየ ፍትህ እንደማምለጥ ወይም እንደማስወገድ ይቆጠራል።

 

የኢፍትሀዊነት ቅዠትን ለማምለጥ ፍትሀዊነትን ማለም፣
የኬንያታን፣ የሩቶንና የአልባሽርን ሰለባዎች ቅዠት ከዚሁ ጎን ለጎን ሳያካትቱ የአምባገነኖቹን ቅዠት መቋጨት ተገቢ አይሆንም። ሰለባዎቻቸው ቅዠታቸው በፍትህ አደባባይ በግልጽ የ2007 ድህረ ምርጫ ማስረጃዎችና እውነታዎች ወጥተው ፍትህን አንዲያገኙ ያልማሉ። የተጎጂዎቹ የእውነት ነጸብራቅ በአሰቃቂ የእልቂት ወንጀሎች ላይ ሲፈነጥቅ ቅዠቶቻቸው ይጠፋሉ።

 

ፕሬዚዳንት ኬንያታ፣ የአንተ ዝና፣ ጌታው! የአንተ ዝና ምንድን ነው?
በሮም ስምምነት አንንቀጽ 25 (3) (a) መሰረት ፕሬዚዳንት ኬንያታ በተዘዋዋሪ የወንጀል አስፈጻሚ ሆኖ የተገኘ ስለሆነ በሚከተሉት ወንጀሎች ተጠያቂ ነው። 1ኛ) ግድያ፣ አንቀጽ 7(1) (a) 2ኛ) ማጋዝ ወይም በኃይል ማፈናቀል፣ አንቀጽ 7(1) (d) 3ኛ) አስገድዶ መድፈር፣ አንቀጽ 7(1) (g) 4ኛ) ማሰቃየት፣ አንቀጽ 7(1) (h) 5ኛ) ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶች፣ አንቀጽ 7(1) (k)

እነዚህ ክሶቹ በሙሉ አስደንጋጭ ሰለሆኑ ቶሎ ወደ ፍትህ አደባባይ ቀርበው ቶሎ ብይን ሊሰጥባቸው ይገባል።

ፕሬዚዳንት ኬንያታ በኩራት ሲናገር "ገና ከጅምሩ ጉዳዮች መታየት ሲጀምሩ ስሜን ለማደስ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርልኛል ስል ሙሉ በሙሉ ለፍርድ ቤት ተባባሪነቴን አሳያቻለሁ።" በአሁኑ ጊዜ ፕሬዚዳንት ኬንያታ በሸክስፒር ኦቴሎ ለተጠቀሰው አፍሪካዊ ጀኔራል አሳዛኝ ታሪክ የወጣቱ ካሲዮ ቃላትን እንድናስብ ያደርጋል። ካሲዮ ታማኝና ጥሩ ወታደር በመሆን ያለውን ጥሩ ስም ተከትሎ ትልቅ እንቆቅልሸ ውስጥ በመግባት ሰው ካለ ጥሩ ስም አውሬ ነው የሚል ጥያቄ አነሳ። "ስሜን ስሜን ስሜን ኦ! ስሜን አጥቻለሁ! የማይሞተውን እኔነቴን አጥቻለሁ! የቀረኝ አውሬነት ነው። የእኔ ስም! ኢያጎ ስሜ!" አለ ካሲዮ።

ሚስተር ኬንያታ ስሙ ለጠፋ ለጎደፈ ሰው ፕሬዚዳንት መሆን ምን ትርፍ ያስገኝለታል...! የማይሞተው እሱነቱ -- ህያው ነፍሱ -- በስሙ ፈንታ የብዙሃን ገዳይ፣ የብዙሃን አፈናቃይ፣ የብዙሃን አስገድዶ ደፋሪ: የብዙሀሃን አሰቃይ: ብሎ መታወቅ አያሳፍርም አይዘገነንም?! ሚስተር ፕሬዚዳንት! እንዲህ ስብዕና አልባ ለሆነ ሰው እንግዲህ ምን ቀረው!?

ከሉዓላዊነት በፊት ሰብአዊነት!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!