(የማለዳ ወግ) ነቢዩ ሲራክ
ትናንት ቅዳሜ ምሽት ላይ የማያልቅበትን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ምን አዲስ ነገር ይነግረን ይሆን? ብየ ከፈትኩት። ቀዳሚው ዜና የሳውዲ ጉዳየ ነው። ክቡር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሃኖም "በኢትዮጵያውያን ላይ የተለየ ጥቃት አልደረሰባቸውም!" ያሉት አስከፍቶኝ ካመሸው በሪያድ መጠለያ የሰማሁት እንግልትና ስቃይ ውል መቋጫ ጋር ተዳምሮ አሳዘነኝ! ዛሬም ሚኒስትራችን የመረጃ ምንጫቸው ችግር እንዳለበት ስረዳም ከፋኝ ...

 

የሳውዲ መንግስት የምህረት አዋጁ እንዳለቀ የቤት ለቤት ፍተሻ እንደማይደረግ ይፋ ቢያደርግም ህጉ ለእኛ አለመስራቱ ን ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖምን የሚነግራቸው ቢያጡ በይፋ የወጡት ጋዜጦ አላዩዋቸው አልልም። አዎ መመሪያው በእኛ ላይ ተጥሶ በመንፉሃ በቤት ለቤት ፍተሻው ኢትዮጵያውያን ተጠቅተዋል። በጥቃቱ ንብረት መዘረፋቸውን መገደላቸውን እና በሴት እህቶቻችን ላይ በህጋዊው የጸጥታ አስከባሪዎች ብቻ ሳይሆን በወጣት ጋጠወጥ አረብ ዜጎች መደፈራቸው ሃገር ያወቀው ጸሃይ የሞቀው እውነት እኮነው ዶክተር አድሃኖም! የሚነግሩዎትን ሁሉ አይመኑ! በሽህ የሚቆጠረው ተፈናቃይ በመጠለያ የሚገኘወ ህዝብ በመስሪያ ቤትዎት ባልደረቦች ድጋፍ እያገኘ ላለመሆኑ ደግሞ በቀጣይ ቀናት በተግባር እንደሚያዩት አስረግጨ እነገርዎታለሁ!

አልኩና ወደ ማለዳ ወጌ ላምራ ...

በሳውዲ ዋና ከተማ በሪያድ መንፉሃ ኢትዮጵያውያን ተለይተን ስለተፈጸመብን ወንጀል ብዙ አልሰማንም አላየንም ባይ ነኝ፣ በራሳቸው በሳውዲዎች ከወጡ መረጃዎች ብዙ ግፍ አይተናል እና አሞን መክረሙ እውነት ነው። የሆነውን፣ እየሆነ ያለውን ከባለ ጉዳዮች በቅርብ አይቻለሁ፣ እያየሁም ነው፣ እየሰማሁም ነው! ግፍ በደሉ ሰላም ነስቶ እንደቀራችሁት እኔንም በሽተኛ አድርጎኛል። ጭራሽ ሃገር በነቂስ ልቡ ተሰብሮ አዝኖ፣ በዘባተሎ ፖለቲካ የተለያየው ባንድ አብሮ፣ የወገን እንባን ለማድረቅ ደፋ ቀና በሚልበት በዚህ ወሳኝ አስተዛዛቢ የታሪክ ምዕራፍ ወቅት በሃገር ቤት ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የተወሰደውን እርምጃ ከሪያዱ በመከራ ባልተናነሰ አስከፍቶ አሳዝኖኛል።

ሰልፉ ህጋዊ ህገ ወጥ ወደሚለው ተራ ሙግት በተለይ በዚህ ጉዳይ አልገባም ... ህግና ስርአት ሽፋን ሆኖ ነገር ግን በሳውዲን ኢትዮጵያ መካከል ሁለትዮሽ የጋራ ሰራተኛን የማቅረብና የማቀበል ውል በሌለበት መንገድ ልጃቸውን ሳውዲ ልከው መዳረሻቸውን ያጡ እናቶችን የትየለሌ ናቸው፣ በኮንትራት ስራ መጥተው እና በመብት ማስጠበቁ የተጉ ዲፕሎማቶች ስለሌሉን ግፍ በደል ተፈጽሞባቸው፣ እንቅልፍ አጥተው የሰሩበትን የላብ ዋጋ ተነጥቀው፣ ተደብድበው፣ ከፎቅ ተጥለው፣ በውስጥ ደዌ በሽታ ተለክፈው፣ ነሁልለው ፈዘው፣ አዕምሯቸውን ስተው በየመንገዱ ተጥለው ለስደቱ መከራ የተዳረጉት በመቶዎች ሳይሆን በሽዎች የሚቆጠሩ ናቸው።

እንደኔ እንደኔ እንኳንስ በጠራራ ጸሃይና በድቅድቅ ጨለማ ሽፋን ህግ አስከባሪ ሳይሆን ህገ ወጥ ጋጠዎጥ ወጣቶች ዜጎቻችን እየዘረፉ፣ እየደበደቡ፣ ሴቶቻችን እየደፈሩና እየገደሉና ለተሰራብን የመንፉሃው በደል እንኳንስ ፈቃድ ጠይቀው ሳይጠይቁ ቁጭት በደላቸውን ለመንግስትና ህዝብ ቢያሰሙ ክፋቱ ምኑ ላይ እንደሆነ አልገባኝም። ስርአት ተጥሶብን አይደለም እንዴ ግፉ የተፈጸመብን!? ሃዘን ገብቶት ዋይታውን በአደባባይ ማሰማቱ ቢቀር በሳውዲ ኢንባሲ በር ሰላማዊ ሰልፍ ያደረገ ዜጋን ከፖለቲካው ጋር እያላተሙ በስርአት አልበኛነት መፈረጅ ምን ማለት ነው? ልጆቹን በግፍ ያጣው ወገን እንደ መሆናችን ሃዘን ጉዳታችን ባለ ጥቁር ጥልፍ ነጠላ ዘቅዝቀን ለብሰን፣ ጥቁር ከረባት፣ መሃረብና ቆብ ደፍተን በሰላማዊ መንገድ ድምጽን የማሰማት ሽብርተኝነት ከቶ በምን ሂሳብ እንደሚያስወግዝ እና ዘብጥያ እንደሚያወርድ እንኳንም አልገባኝ!! የበደለንን የሳውዲ መንግስት ተወካይ ኢንባሲውን አይደለም ለዚህ መከራ ዳረጉን የምንላቸውን የመንግስት ተቋማት የመቃወሙ ሃጢያት አልገባኝም፣ እንዲገባኝም አልፈልግም!

እዚህ ሳውዲ አረቢያ ብዙዎች ለህሊናችን እንደር ብለንና ስለ ኢትዮጵያ ብለን በአደጋ ተከበን በመስራት ላይ ነን፣ የመንግስታችን ተወካዮች ዲፕሎማቶቻች ግን እኛን ወክለው በተከቀመጡባት ወንበር ከስጋትና ከአደጋ ተከልለው ለቆሙለት የመብት ማስከበር የተጉ አይደሉም! ባሳለፍናቸው ጥቂት ቀናት ብቻ በመላ ሳውዲ አረቢያ ከ50 ሽህ በላይ ስደተኛ መጠለያ፣ ማቆያ የሚል ስም በተሰጠው ጊዜያዊ እስር ቤት ላይ ናቸው። ህጻናትን ጨምሮ አቅመ ደካማ ሴት እህቶች የሚገኙባቸው ቁጥራቸው 30 ሽህ ሊደርስ የተቃረበ ዜጎቻችን በሪያድ መጠለያዎች አልተመቻቸውም ብየ ብቻ ልለፈው ... ስቃይ በደል ጩኸታቸውን የሚሰማ የሚጎበኟቸው ግን ዲፕሎማቶቻችን አይደሉም ... ዲፕሎማቶች የታሉ ብለን ስናፈላልግ "በስብሰባ ላይ፣ በስራ ውጥረት ላይ ናቸው!" ይሉናል ... ይህ ሲባል ግን ለማን እንደሚሰሩ ግራ ግብት የሚለኝ እኔን ብቻ ቢሆን መልካም ነበር፣ መጠለያ የከተመ ወገንን ብሶት ስንነግራቸው አይሰሙንም "... አደጋው ከፍ ያለ ሔዷል፣ ህዝብ ጥሩ ይምከር ይዝከር። እንምከር እንዝከር!" እንላቸዋለን! መስሚያቸው ተደፍኗል! የወገኖቻችን ሮሮ መስማት፣ ደገፉ ተብለው አልደገፉም፣ ስሙ ሲባሉ አልሰሙምና የመብት ጥበቃ አጥቶ የተደፈረ፣ የተዘረፈ፣ የተገደለውን ዜጋስ ሃዘን ደርሰው ሃዘን የገባውን ወገን ማጽናናት ማረጋጋት አልቻሉም! እውነቱ ይህ ሆነና ስው በመንግስት ሃላፊዎች ተስፋ ቆርጧል። በደል በዝቶበት ተስፋ ቆርጦ በውስጡ አመጻን አርግዞ ውሎ ለማደር ተገድዷል! እኛም ይህንን እውነታ ስንነግራቸው እንደኖርነው ባይሰሙም የማህበረሰቡን ችግሮችን እንዲፈቱልን ብቻ ሳይሆን ተባብረን እንድነፈታ እንነግራቸዋለን! በማህበረሰቡ ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ ይፈለጉ ዘንድ እናግዛችሁ ስንላቸው በደገፍናቸው ያገሉናል፣ ወደ ዚያች መከረኛ ሃገር እንደማንገባ በገደምዳሜም ቢሆን እያስነገሩ ሊያስፈራሩን ይፈልጋሉ። በዚህም ሃሞታች ያፈሱታል እና ዝም ብለን ግፍ ተጭኖብን ለሆዳችን አድረን እንኖራለን!

በዚህም በሉት በዚያ እንዲህ አይነት አስነዋሪ ስራዎች ይሰራሉ። ይህን መሰል ሰራዎች ደግሞ የመንግስት ሃላፊዎች እየሰሩት ያለው ታላቅ ስህተት እኔም እንደቀሩት ተስፋ ቆራጮች " ሃገር እና መንግስት አለን ወይ! ?" እንድል ተገድጃለሁ! ቁጭ ብሎ ለታዘበው የኢትዮጵያ መንግስት አስተዳደር ትልቅ ጎደሎ አለበት፣ እኔ በማውቀው የ16 አመት የአረብ ሃገር ስደት ህይዎት የመንግስት ተወካዮች በተጨባጭ መረጃዎች ስገመግመው ሃላፊዎች የዜጎችን መብት መደፍጠጥን ተከትሎ መብት በማስከበሩ ረገድ በቦታው የሉም ማለት ይቀለኝ ይሆናል። ከዚህ አልፎ ተርፎ መንግስትና ሃላፊዎች ብሔራዊ ክብርን የሚነኩት ተደጋጋሚ ስህተቶች ከመስራት አልታረሙም።

ከቅርብ ወራት ከተሰሩት ስህተቶች መካከል አሞኝ ያለፈው የፋሽሽቱ የግራዚያኒን ሃውልት በጣሊያን ሃገር የማቆም እቅድ የተቃወሙ ዜጎች በአዲስ አበባ በቁጭት ተቃውሟቸውን በአደባባይ ሲገልጹ የታሰሩበት አጋጣሚ ለእኔ ውርደትም ነበር። መንግስት መስራት ያለበትን ስራ የሰሩ ሃገር ወዳድ ዜጎች የታሰሩ እና የተደበደቡበት አጋጣሚ አዙሮ ላስተዋለው ያማል! "ነገ መልካም ቀን ይመጣል!" አጓጉል በሚል አጓጉል ተስፋ ያም እንደ ነገሩ አለፈ! ትናንት ረፋዱ ላይ ደግሞ ሌላው አሳፋሪ ስራ በመዲናችን ተፈጸመ! ሳውዲዎችን ስትቃዎሙ ያለፈቃድ ነው በሚል ሰልፍ የወጡት ተደበደቡ ታሰሩ! ግፍ ተፈጸመ ... አዘንኩ! ሃገርና መንግስት አለን ወይ ስል ራሴን ጠየቅኩ! መልስ አገኘሁ! ሃገር ያለን፣ የዜጎቹና ለሃገር ብሔራዊ ከብር የሚቆረቆር መንግስት የሌለን መሆኑ ቢገባኝ ከከበደው፣ ከተጫነኝ የወገን መከራ በላይ አሳዘነኝ ...!

የሳውዲ አረቢያ ረጅም አመት ቆይታየን እና በረጅሙ ቆይታየ የሆነውን ሁሉ አውጥቸ አወረድኩት ... ትውስታየን የጀመርኩት በቅርቡ በሪያድ መንፉሃ ከተፈጠረው አደጋ ነበር ... ችግሩ በተከሰተበት ቅጽበት መረጃው ደርሷቸው በቦታው ደርሰው ነዋሪው ማረጋጋት ሳይችሉ የቀሩትን የመንግስት ተወካዮች አሰብኩና በሆነው ሁሉ በገንኩ ... አሁንም ያ ስህተት አልታረመም፣ ከዜጎች ጋር አይመካከሩም፣ መረጃ አይለዋወጡም፣ ድረሱልን የሚለውን ድምጽ መስማት አይፈልጉም ... እናም ምሬቴ ብዙ አላስኬደኝም! ሁሉንም በአንድ ሳሰላው የበደሉን አረቦች አይደሉም ስል ደመደምኩ! አዎ የጎዱ የበደሉን የኢትዮጵያ መንግስት ሃላፊዎች ትናንትም ሆነ ዛሬ አረቦች አልበደሉንም! እውነቱን ንገረኝ ካላችሁ እዚህም እዚያም አረቦች የእኛን መንግስት ያህል አልበደሉንም!

ጥፋትን አውቆ ራስን ማረም ደግሞ የወግ ነው! ዛሬም አልመሸም! ከሁሉም በላይ በ አለም ያሉ ኢትዮጵያውያን የወገኖቻቸው በደል እሟቸው እርዳታ ሊያደርጉ ቢፈልጉ እንኳ ችግሩ ያለው ሳውዲ አረቢያ ነውና መንገዱ የከበደ እና የተዘጋጋ ነው። ይህ በመሆኑ የመንግስት ሃላፊዎች ወደ 60 እና 80 ሽህ የሚገመተውን ህገወጥ የተባለ ዜጋ ልትታደጉትና ወደ ሃገር ቤት በአስቸኳይ ዘመቻ ስለ እውነት ልትሰሩ ይገባል! ቂም በቀል ሊያስቋጥር የሚችል ስህተት እንዳይደገም ያለፈውን ስህተት አርማችሁ ዜጎቻችን ከገቡበት ማጥ ታወጧቸው ዘንድ እንማጸናችኋለን!

እርግጥ ነው እየሆነ ያለው ተስፋ ያስቆርጣል፣ እኛ ተስፋ ከቆረጥን በእኛ ተስፋ ያለቸው ብዙሃን ይጎዳሉ፣ እናም ሁሉም ይሁን ... ግን ተስፋ አንቁረጥ!

አሁንስ አምላክ ይርዳን!


ነቢዩ ሲራክ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!