ወገን ለወገን ደራሽ ነው

ሜሮን አድማሱ ከኖርዌይ
በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵዊያን በሚኖሩባት ሳውዲ ዐረቢያ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን ላይ እያደረገችው ያለችው ኢሰብዓዊ ድርጊት ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ሲሆን፣ ከአንድ ኃይማኖት አለን ከሚል ሀገር የማይጠበቅ አሳፋሪ ተግባር ነው። በታሪክ እንደሰማነው የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ሲሠደዱ ኢትዮጵያ በጊዜው ተቀብላ መኖሪያና ማምለኪያ ቦታ እንዳልሰጠቻቸው ሁሉ፤ ዛሬ ግን በኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ላይ እያደረሰችባቸው ያለው ስቃይና እንግልት ውለታ በይነቷን ያሳያል።

በ21ኛ ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን እንደ 13ኛ እና 14ኛ ክፍለ ዘመን የሚያስቡት ኋላ ቀሮቹና ጭንቅላታቸው በብር የተደፈነው ሳውዲ ዐረቢያን እህቶቻችንን እየደፈሩ፣ ነፍሰጡር እናቶችን እያሰቃዩ፣ ወንዶቹን እንደ እንስሳ ቆዳቸውን እየገፈፉና እያረዱ ነው ያሉት።

አረመኔውና ጨካኙ የወያኔ መንግሥት ህዝቡን በተለያየ መንገድ እንዲሠደድ ከማድረጉ በተጨማሪም ከዓመት በፊት ከሳውዲ ዐረቢያ መንግሥት ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት በየወሩ 40ሺ ኢትዮጵዊያን እህቶቻችንን ለቤት ሠራተኝነት ሲልክ እንዳልሰነበተ፤ አሁን ኢትዮጵያዊያን እንደ እንስሳ ሰውነታቸው ሲተለተልና ሲገደሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት መምረጡ እንደ አንድ ሀገር አስተዳዳሪ ለዜጎቹ ተጠሪነት ያለበት ሳይሆን እንደ ማፍያ ቡድን የሳውዲ ዐረቢያን ጭካኔ የተሞላበትና አረመኔያዊ ተግባር ሲደግፍ ይታያል።

የሳውዲ ዐረቢያ አራጋቢና ተባባሪ የሆኑት የወያኔ ባለሥልጣኖች "በሕገ ወጥነት የሚኖሩ ለቀው እንዲወጡ የአንድ ወር ጊዜ ተሰጥቷቸው ነበር" በማለት ወገኖቻችንን ጥፋተኛ አድርገው ከመሳለቃቸውም በተጨማሪም ከሞት የተረፉትን እንኳን አልቀበልም በማለት ዜጎቻችን በተለያዩ ካምፖች ውስጥ ካለምግብ እና መጠጥ ታጉረው እየተሰቃዩ ይገኛሉ።

ኧረ! ለማን አቤት ይባላል፤ ማፍያ በሆነ መንግሥት በግምት እየተመራን፣ በሀገራችን እንኳን መተንፈስ አቃተን እኮ! ... በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ደሞ በአዲስ አበባ ሠማያዊ ፓርቲ በሳውዲ ዐረቢያ ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን አረመኔያዊ ተግባር ለመቃወም ሊያደርጉት የነበረውን ሠላማዊ ሠልፍ ወያኔ በመቃወሙ በሠልፈኞቹ ላይ የፈፀመው ግፍ፣ ጭፍጨፋና ጭካኔ ለሳውዲ ዐረቢያ ያለውን ድጋፍ አጉልቶ አሳይቷል።


ወገን ለወገን ደራሽ ነው

በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን አረመኔያዊ ተግባር እንደ ህዝብ ጥቃታችንና ውርደታችን ከመቼውም በላይ እየባሠበት ስለሆነ ይህን አሠቃቂ ተግባር ለማስቆም ሁላችንም ዘር፣ ኃይማኖት ሳንል ባለንበት ቦታ ሁሉ ተቃውሞ ማድረግ የኢትዮጵያዊያነት ግዴታችን ነው።

ወገን ለወገን ደራሽ ነው!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!