Ato Gemoraw Kassaገሞራው ካሣ

በቅድሚያ አንድ ማሳሰቢያ አለኝ። የእኔ ዕቅድና ዓላማ በዚህ ጽሁፍ ለማስተላለፍ የፈለኩትን መልክት መምህራን፤ ተቆርቋሪ ዜጎችና የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ በቅጡ እንዲረዱልኝ ማድረግ ነው። ስለሆነም የትኛውንም ወገን በማይቆረቁር ቋንቋ መጠቀም ብችል ደስ ባለኝ ነበር። ሆኖም ከስር ከሳሽ ኢመማን ከተከሳሽ ኢመማ መለየት ካልተቻለ ብዥታን ፈጥሮ ለመግባባት ስለሚያዳግት የሚከተለውን አጭር ማሳሰቢያ መስጠት የግድ ብሎኛል።

 

ከስር ፍ/ቤት (መጀመሪያ) ከሳሽ ኢመማ የነበረው በመምህራንና በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በስፋት የሚታወቀው ተለጣፊው ኢመማ በሚል መጠሪያ ነው። ከዓለም-አቀፉ ህብረተሰብ ከፊሉ ”አዲሱ (የመንግሥት) ኢመማ - The New (government sponsored) ETA” ይሉታል። ከፊሎቹም የተመሠረተበትን ዓ. ም. ወይም የምዝገባ ቁጥሩን ለመለያ ይጠቀሙበታል። ከስር ፍ/ቤት ተከሳሽ የነበረው ኢመማ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አንጋፋው ወይም ነባሩ ኢመማ በመባል ይታወቃል። የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የመጀመሪያው (እውነተኛው) ኢመማ (original (authentic) ETA) ወይም የዓለም መምህራን አባል የሆነው ኢመማ (ETA of EI) በማለት ይጠሩታል። ስለዚህ በእኔ በኩል ከአንባቢዎቼ ጋር መግባባቱን ቀላል ለማድረግ በነዚህ ስያሜዎች ስጠቀም ለትንኮሳ ወይም ለመታበይ አለመሆኑን እንድታውቁልኝ በትህትና እጠይቃለሁ። ወደ ፍሬ ጉዳዩ ልውስዳችሁ።

 

አንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር (ኢመማ) ለምንድን ነው እስከዚህ ድረስ የመንግሥት የጥቃት ዒላማ የሆነው? እንደው ለመሆኑ ለመንግሥት ስልጣን ተቀናቃኝ የሚያፈራበትን መድብለ ፓርቲ ስርዓት እያራምድኩ ነው የሚል መንግሥት እንደምን አንድ ለአባላቱ መብትና ለሙያው መከበር የቆመና ለሲቪል ህብረተሰብ ምስረታ አይነተኛ እገዛ ማድረግ የሚችል ነፃ የሙያ ማኅበር መኖር እስከዚህ ድረስ አስፈራው? ደሞስ መንግሥት ከፈለገ በአንድ ቀን ጀምበር ድምጥማጡን ሊያጠፋው ሲችል በምን ምክንያትስ ነው እስከ ዛሬ ድረስ እንዳይሠራም እንዳይሞትም አድርጎ ሲያስታምመው የቆየው? የሚሉት ጥያቄዎች በብዙዎች ዘንድ ተደጋግመው የሚነሱ ናቸው።

 

መንግሥት ኢመማን ሳያፈርሰው እስከ ዛሬ ታገሰው ለሚለው ከግምት ያለፈ የተጨበጠ መረጃ የለኝም። ከተጨባጩ ሁኔታ ተነስቶ ምክንያታዊ ግምት መስጠት ባይናቅም የሚመስለውን ግምት የመስጠቱ እድል ለሁሉም ወገን ክፍት ስለሆነ እኔ በዚሁ ልለፈው። በዚህ ቦታ የማይታለፈውና አስፈላጊ መነጋገሪያችን መሆን ያለበት ለምን መንግሥት ኢመማን ማፍረስ ፈለገ የሚለው ነው።

 

እኔ መረዳት የቻልኩትን ያክል መንግሥት የኢመማን ነፃ ድርጅታዊ ህልውና ያልፈለገው አንደኛ፣ ከአገዛዙ የፖለቲካ ፍልስፍና አንጻር የማኅበሩ አባላት ስብጥር (የአደረጃጀቱ ህብረ-ብሔርነት) እና ከህብረተሰቡ ጋር ያላቸው ስር የሰደደ መስተጋብር፤ በኋላም ማኅበሩ በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ላይ ያለው ሚዛናዊ ትችቶች (coherent criticisms) እና የመምህራን ድርጅታዊ አንድነት ከጎለበተ አገዛዝን ባለመቀበል ለሌላውም መጥፎ አርአያ መሆን ስለሚችሉ ለኢህአዲግ የሚመቸው ማኅበር መስሎ አልታየውም። ሁለተኛ፣ መምህራንን በመሸንገል ለመቆጣጠርና ለውጭው ዓለም መስሎ ለመታየት (ኢትዮጵያ የዓለም ሥራ ድርጅትን (ILO) ቃልኪዳኖችን (conventions) ቁጥር 87 እና 98 በነፃ የመደራጀትና በጋራ የመደራደር መብቶችን ለማክበር መፈረሟን ያስቧል) የማያገለግሉ የይስሙላ ማኅበራት በአካል ብቻ እንዲኖሩ (physical existence of nominal unions) እንጂ አባላትና ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ፍላጎቱ ቆራጥነቱ፡ ብቃቱና ተአማኝነቱ ያላቸው ነፃ የሙያና ሠራተኛ ማኅበራት እንቅስቃሴዎች (independent trade union movements) በዚህ አገር እውን ከሆኑ አለጥርጥር ሲቪል ህብረተሰብ ይመሠረታል። በቪል ህብረተሰብ ውስጥ ደግሞ የመንግሥት ስልጣን ምንጩ ሕዝብ ይሆናል። በጠመንጃ ኃይል ወይም በተጭበረበረ የይስሙላ ምርጫ ተሸፋፍኖ ያለችሎታና ያለህዝብ ፈቃድ ወደሥልጣን መምጣትና የሥልጣን እድሜን ማራዘም እርም ይሆናል። ስለዚህ ኢህአዲግ ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠረው የማይችለው ምንም ነፃ የሲቪል ድርጅት (ከተቻለው የሰፈር እድርም ቢሆን) በኢትዮጵያ ምድር እንዲኖር የሚፈልግ አይመስለኝም። ይህ በምን ሰበብና እንዴት በኢመማ ላይ ተግባራዊ ሆነ የሚለውን ላቅርብ።

 

እኔ በኢመማ ውስጥ በነበረኝ ቀጥተኛ ተሳትፎ ምክንያት በቅርብ መገንዘብ እንደቻልኩት ማኅበሩ የአባላቱን 20 የጋራ ጥያቄዎች በነሀሴ ወር 1984 በጽሑፍ ለመንግሥት ካቀረበ ጊዜ ጀምሮ አራት ተፈራራቂ ኩነቶች ገጠሙት። አንደኛ መምህራን ከምንጊዜውም በላይ አንድነታቸውን ጠብቀው ከሙያ ማኅበራቸው ጎን በፅናት እንዲቆሙ አደረጋቸው። ሁለተኛ ቢገፋበት ኖሮ ለሁሉም ወገን ዘላቂ ጠቀሜታ የነበረው በ20ዎቹ ጥያቄዎች ላይ ተወያይቶና ተማምኖ የሀገሪቱ አቅም በሚፈቅደው ደረጃ በሰለጠነ መንገድ ለመመለስ በመንግሥት በኩል የተደረገ ቅን አዝማሚያ ነበር። ሶስተኛ የመምህራን ወኪሎችን በመሸንገል የመምህራንን የትኩረት አቅጣጫ ማስቀየር ካልሆነም በጡንቻ ፀጥ ለማሰኘት ከተራ ሽብር እስከ ግድያ የዘለቀ ጥቃት በመንግሥት ሲፈጸም ቆየ። አራተኛ የእውነተኛው የሙያ ማኅበር ህልውና በሕግ ሽፋን እንዲያከትም አድርጎ የመንግሥትን በትረ ስልጣን በጨበጠው የፖለቲካ ፓርቲ (በኢህአዲግ/ህወሀት) አምሳል የተቀረፀ የይስሙላ ተለጣፊ ማኅበር ለመፍጠር ያልተበጠሰ ቅጠልና ያልተማሰ ስር አልነበረም።

 

ለዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ዋነኛ መነሻ ምክንያት ስለሆኑት ስለ20ዎቹ የኢትዮጵያ መምህራን ጥያቄዎች ትንሽ ገፋ አርጎ አንባቢን ማስታወሱ በኢመማና በመንግሥት መሀከል እስከዚህ ጦዞ የቆየውን ትርምስና ዛሬ የደረስንበትን ሁኔታ በቅጡ ለማጤን ይረዳል የሚል እምነት አለኝ።

 

ጥያቄዎቹ የተሰበሰቡት በመላው ሀገሪቱ ተሰማርተው ከሚያስተምሩ መምህራን በጽሁፍ ሲሆን አንገብጋቢነታቸውና የአብዛኛው አባላት የጋራ ችግር ስለመሆናቸው እንደዚሁም በሀገር ብሄራዊ ጉዳይ በተለይም በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ስለሚያሳድሩት እድምታ በስፋትና በጥልቀት መክሮባቸው ማዕከላዊ ቅርጽና ይዘት ያስያዛቸው የኢመማ ማዕከላዊ ሥራ አስፈጻሚ ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ነበር። የጥያቄዎቹ ይዘት ሲጨመቅ እንደሚከተለው በሦስት ሊመደብ ይችላል፡-

 

የመምህራን ደሞዝ፦ እንደ ማንኛውም የሌላው መንግሥት መ/ቤት የትምህርት ደረጃቸውንና የሚሰጡትን አገልግሎት የሚመጥን፤ ለመኖር የሚያስችላቸው እንዲሆንና በህብረተሰቡ ውስጥ ማኅበራዊ ቦታቸው ተከብሮ ቀና ብለው በመሄድ ቀና ብሎ የሚሄድ ዜጋ ማፍራት እንዲችሉ፤ ከመምህራን ምልመላና ስልጠና ጀምሮ ተከታታይ የሙያ ማጎልበቻና የከፍተኛ ትምህርት እድል እንዲኖራቸው፤ ፍትሀዊ አስተዳደርና ለመማር ማስተማሩ ሥራ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው፤

 

ሥርዓተ ትምህርቱ፦ የደረጃው ያሉት ማስተማሪያ መጻሕፍትና የትምርት መርጃ መሣሪያዎች በብዛትም ሆነ በጥራት የትምህርትን ሥራ የመጨረሻ ግብ ለመምታት (ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን የባህሪይ ለውጥ ለተማሪው ለማቀዳጀት) የሚያስችሉ ሆነው በቀጣይነት ተሻሽለው እንዲዘጋጁ፤

 

የሀገራችን የትምህርት ዓላማና ግብ፦ አቅጣጫና አሠራር ከኅብረተሰባችን የባህል እድገት ደረጃና ከሀገሪቱ አቅም ጋር ተመጣጥኖ፤ ሁኔታው የሚፈቅደውን ያክል የዓለም አቀፍም ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ የሚመራበት የተሻሻለ የትምህርት ፖሊሲ ብቃቱ ባላቸው ሙያተኞችና አግባብ ባላቸው አካሎች ሙሉ ተሳትፎ እንዲዘጋጅ ለዚህም ታላቅ ብሔራዊ ጉዳይ ስኬታማነት እንዲያግዝ ማለትም የእስካሁንን የትምህርት ሥራ ድክመትና ጥንካሬ በስፋትና በጥልቀት መርምሮ የወደፊቱን በጋራ ለማቀድ እንዲረዳ በቅድሚያ ሀገር አቀፍ ብሄራዊ የትምህርት ኮንፈረንስ (ሲምፖዚየም) እንዲካሄድ የሚጠይቁ ነበሩ በመንግሥት እንደ መሬት አንቀጥቅጥ መብረቅ የተፈሩት 20ዎቹ የመምህራን የጋራ ጥያቄዎች።

 

ከሁሉም በላይ በቅርብ የሚመመለከተውና በኢትዮጵያ የትምህርት ሥራ በሕግ በተሠጠው ኃላፊነትም ሆነ ከሙያ አንጻር በቀጥታ በሚያገባው የትምህርት አመራርና አስተዳደር ጉባኤ ላይ ነበር እነዚህን የኢትዮጵያ መምህራን ጥያቄዎች በኢመማ ተወካይ በንባብ ተሰምተው ጉባኤተኛው በሙሉ ድምጽ የተቀበላቸው። ይህም የትምህርት አመራርና አስተዳደር 25ኛው ጉባኤ ሲሆን የተካሄደው በነሐሴ ወር 1984 ዓ.ም. በትምህርት ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ነበር። እነዚህ ጥያቄዎች በአግባቡ ካልተመለሱ መምህራን ለሙያቸው ተገቢው ፍቅርና አክበሮት ኖሯቸው፤ ከመንግስትም ሆነ ከቅርብ አሠሪያቸው አካል ጋር መልካም ግንኙነት ፈጥረው የመማር ማስተማሩን ሂደት የተሳካ ለማድረግ ፈጽሞ የማይታሰብ መሆኑን አመነበት። ጉባኤውን በሊቀመንበርነት የመሩት በወቅቱ የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር የነበሩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የመምህራን ጥያቄ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠውና ቀና ምላሽ የሚያገኝበት ሁኔታ እንዲመቻች ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

 

በወቅቱ የመፍትሄ ሃሳብ በማፈላለጉ ሥራ ላይ ጉባኤተኛው ጥያቄዎቹን በሁለት መደባቸው። 1ኛ በትምህርት ሚኒስቴር መ/ቤት አቅም መስተናገድ የሚችሉና 2ኛ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ቀርበው በመንግሥት መልስ መሰጠት ያለባቸው። ለዚህም ተፈጻሚነት አንድ ግብረ ኃይል ተሰየመ። በአቶ አዋሽ ገብሩ እንዲመራ ተደርጎ በነበረው በዚሁ ግብረ-ኃይል ውስጥ እኔም ራሴ ኢመማን ወክዬ ተሳትፌያለሁ። ግብረ-ኃይሉ ሀላፊነቱን በብቃትና በተሰጠው ጊዜ ገደብ አጠናቆ ለሚመለከተው አካል ማስረከቡንም አውቃለሁ።

 

ወደ ትምህርት ሚኒስቴር የተመሩት ጥያቄዎች ቀናና የሚያበረታቱ ምላሾች እያገኙ ሲመጡ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የተላኩት ግን ነጮቹ እንደሚሉት ካሮትና በትር እየተመዘዘባቸው ተቸገርን። በአንድ በኩል የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ከኢመማ ማዕከላዊ ሥ/አስፈጻሚ ጋር በመልስ አሰጣጡ ላይ ሲመክርና በሌሎቹም በሚመለከቱን ጉዳዮች ላይ አብሮን ሲሠራ፣ በሌላ በኩል ግን በየክልሉ ያሉ ካድሬዎች መምህራንን እየሰበሰቡ 20ዎቹ ጥያቄዎችና አቅራቢዎቹ ከበስተጀርባቸው እኩይ የፖለቲካ ተልእኮ ስላሏቸው ማውገዝ አለባችሁ ብለው ማዋከቡን ተያያዙት። ለዚህ ግብ መሣሪያ ሆነው የሚያገለግሏቸው ከመምህራን መሀከል ደካሞችን የማሰባሰቡን ሸፍጥ በመላው ሀገሪቱ አጧጧፉት። መምህራን ግን እንዲህ በቀላሉ የሚበገሩላቸው አልሆኑም። በዚህ ትንቅንቅ ወቅት በመምህራን ስብሰባ ላይ ይነገሩ የነበሩ ሀሳቦችን ዛሬ ላይ ሆኖ ላጤነው እጅግ በጣም የሚያስገርሙ ነበሩ። በአካል ከተገኘሁባቸው ስብሰባዎች ላይ ከተነገሩት ሁለቱን ብቻ ልጥቀስ።

 

ቦታው በአሰላ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ቅጽር ግቢ በ1985 ዓ.ም. ነበር የአሰላ ከተማና የአካባቢው መምህራን የተሰበሰቡት። ትምህርት አቅራቢዎችና የክብር እንግዶች ሆነው በእለቱ ከተገኙት መሀከል የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የፖለቲካል ሳይንስ አስተማሪው ዶ/ር መረራ ጉዲና እና የሕግ ሙያተኛው አቶ ተሾመ ገ/ማሪያም እንደነበሩ ትዝ ይለኛል። በውይይቱ ክፍለ ጊዜ አንድ ወጣት ሴት መምህር የመናገር እድል አገኘች። ”በታዳጊ ሀገሮች” አለች መምህርቷ ”በተለይ በአፍሪካ ፖለቲካው የሚያዘው ካልጠፋ ዕቃ በፌስታል (በወረቀት ከረጢት) ነው። ወይ ተቆንጥሮ ያልቃል፤ አለያም ፌስታሉ ተቀዶ እስከነ ካቴው ደብዛው ይጠፋል። ታስታውሱ እንደሆን ወታደራዊ ደርግ አነሳሱ ላይ በሩን በርግዶ ዲሞክራሲ በድሞክራሲ አርጎን ሲያንጫጫን ቆየና ከተደላደለ በኋላ ቀፎ ሰቀለ። ማሪቱን ለማግኘት የፈለገ ሁሉ መጀመሪያ በአብዮታዊ ሰደድ ወፍጮ ተዳመጦና በኢሠፓ ወንፊት ተጣርቶ በጠባቧ ቀዳዳ ወደ ቀፎው መግባት የሚችል ንብ መሆን ነበረበት። እኔ እስከገባኝ ድረስ ኢህአዲግም የሚደግመው ይሄንኑ ታሪክ ነው። ስለዚህ ዲሞክራሲው አልቆብን ሳንታፈን 20ዎቹን ጥያቄዎቻችን ለማስመለስ ዛሬውኑ በአንድነት እንነሳ” ነበር ያለችው።

 

ሁለተኛው ስብሰባ በሳምንታት ልዩነት በዛው ዓመት ዲላ ከተማ ነበር የተካሄደው። በከተማውና በአጎራባች ወረዳዎች ካሉ ት/ቤቶች የመጡ መምህራን ነበሩ የተሰበሰቡት። ከአዋሳ ከተማ ሳይቀር ከየወረዳው የተሰባሰቡ ትኩስ ካድሬዎች እኛን ባለቤቶቹን እንዳልነበርን ቆጥረው ባልጠሩትና ባልተጋበዙበት ስብሰባ በስልጣናቸው ከመድረኩ ላይ ተሰየሙ። ”በ20ዎቹ ጥያቄዎች የተነሳ መምህራን ተከፋፍለዋል ስለተባለ ልናስማማችሁ ነው የመጣነው” አሉ። ማነው ይሄን ያላችሁ? ከሆነስ እንደምን ነው ልታስማሙን ያሰባችሁት? የሚል ጥያቄ ከቤቱ ቀረበላቸው። ለዚህ ጉዳይ አዘጋጅተዋቸው ከነበሩት መምህራን ከፊሎቹ የቤቱን የጋለ ስሜት አይተው ሀሳባቸውን የቀየሩ በሚመስል ሁኔታ ዝምታን መረጡ። ለመናገር የሞከሩትም እንዲያጠኑት የተሰጣቸው የቤት ሥራ እየጠፋባቸው ሲርበተበቱ መሳቂያና መሳለቂያ ሆኑ። በመሀከሉ አንድ አዛውንት መምህር ከመቀመጫቸው ብድግ አሉ፣ ”እናንተ መድረክ ላይ ያላችሁ ሰዎች አንድ የጌዲዮ ህብረተሰብ ተረት አስታሳችሁኝ” አሉ። ”በጌዲዎኛ ብናገረው የበለጠ ይጥም ነበር። መልዕክቱን ለማስተላለፍ ያክል ሁላችንም ልንግባባበት በምንችለው በአማርኛ ላቅርበው። ”የጦጣና የዝንጀሮ መንጊያዎች የተትረፈረፈ የሠራተኛ ጉልበት እያላቸው፤ ፈረስ ጋልቦ የማይዘልቀው ኩዳድ መሬት ሳያጡ የሰው ልጅ በሠራው ሰብል ያውም ስንት ውርጅብኝ እየወረደባቸው ለዓመታት መኖራቸው ቆጫቸው። በመረዳዳት ሠርተው ህይታቸውን መለወጥ እንዳለባቸው አመኑበት። ቀኑን ሙሉ ሲመነጥሩ፤ ሲያርሱና ሽንኩርት ሲተክሉ ውለው ወደየ ሰፈራቸው ላዳር ሄዱ። ጥቂት እንደቆዩ በጦጣ ሰፈር አንድ ያልታሰበ ሽብር ተፈጠረ።

 

ለካስ የሰው ልጅ እንደዚህ የደከመበትን ሰብል ነው ከአያት ቅድማያቶቻችን ጀምሮ ለዘመናት ስንበላበትና ስናበሳጨው የኖርነው። ዛሬ እንደሚበቀለን ጥርጥር የለውም የሚል ሹክሹክታ ነበር ቀስ በቀስ ነፍስ ዘርቶና ገዝፎ የጦጦቹን ሰፈር የበጠበጠው። አስደንጋጩን ዜና የመስማትና መፍትሄ በማፈላለጉ ዝንጆሮዎችም የመሳተፍ መብት ስላላቸው መልክተኛ ተላከባቸው። ለካስ እነሱም ሰፈር ውስጥ ውስጡን እያነጋገረ የቆየ ጉዳይ ስለነበር ተስማምተው የጋራ እርምጃ ለመውሰድ አልዘገዩም። ዝንጆሮዎችና ጦጦች ቀኑን ሙሉ ደክመው የተከሉትን ሽንኩርት ማታ ላይ ነቅለው ተከፋፈሉት። የነሱም ኑሮ ሳይለወጥ ይሄው እስከዛሬ እንደነበሩ አሉት። አሁንም እናንተ (ካድሬቹን ማለታቸው ነው) ይሄን ሁሉ መምህር ዝንጀሮና ጦጣ ለማድረግ መሞከራችሁ ለሚያልፍ ቀን ትዝብት ላይ ወደቃችሁ። እግዚአብሔር ወደ ህሊናችሁ ይመልሳችሁ።

 

በእኛ በኩል ግን 20ዎቹ ጥያቄዎች ጥያቄዎቻችን ናቸው። ተቀባይነት ያለው መልስ እስኪሰጣቸው ትግላችን ይቀጥላል። ባነበብናቸው ቁጥር እንደ ራጶል (አቤቱታ) አጻፊው ሰው ለካስ ይሄ ሁሉ በደል ደርሶብናል እያልን እንደምናለቅስ ማን በነገራችሁ። እንቅጩን እወቁት፤ ጥያቄዎቹ የወጡት ከኛው ሲሆን የኢመማ መሪዎችም እኛው የመረጥናቸው ታማኝ ወኪሎቻችን ናቸው። ትናንት መርጠን ዛሬ አንሽራቸውም። ምን በደሉና!! ምንጊዜም ከጎናቸው ነው የምንቆመው። የሰማችሁትን ማመን ከተሳናችሁ እንድታዩት በጭብጨባ እዚሁ እፊታችሁ እናረጋግጥላችሁ” ሲሉ ተሰብሳቢው ሁሉ ብድግ ብሎ በሆታና በፉጨት ለረጅም ጊዜ ሲያጨበጭብ ካድሬዎቹ በመደናገጥ እየተገላመጡ ከአዳራሹ ወጥተው ሄዱ።

 

ውለው ሳያድሩ የአካባቢውን ቅርንጫፍ ማኅበር አመራርና ጉልህ ተሳትፎ የነበራቸውን መምህራን መበቀል ሥራዬ ብለው ተያያዙት። ተለጣፊውን ኢመማ በማቋቋምም የመጀመሪያዎቹ ሆኑ።

 

ከላይ በመጀመሪያው ምዕራፍ ውስጥ ከተገለጹት በአራተኛው ኹነት መሠረት የአንጋፋው ኢመማ መሪዎችና በማኅበሩ ውስጥ የጎላ ተሳትፎ ያላቸው መምህራን ላይ ሲፈጸም ከቆየው ከሕገ ወጡ በደል ጎን ለጎን በየደረጃው ባሉት የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች ቋሚ ተሟጋች ደንበኞች ሆነው ለ15 ዓመት ሲንገላቱ ከርመዋል። ሙግታቸውን ልዩ ከሚያደርጉት በርካታ ኹነቶች መካከል፡-

 

1ኛ - የከሳሽም የተከሳሽም ስም አንድ ነበር፤ ከሳሽ ኢመማ - ተከሳሽ ኢመማ

ከላይ እንደተጠቀሰው የኋለኛው (አዲሱ) ማኅበር የፊተኛውን (አንጋፋውን) ማኅበር ስም እንዲይዝ ተደርጓል። አርማውም ሳይቀር። ይህም ሊሆን የቻለው ህጋዊ ሁኔታዎች አሟልቶ በ1941 ዓ.ም. ላልተወሰነ ጊዜ በሚል ፈቃድ የተመሠረተው ነባሩ (አንጋፋው) ኢመማ በህጋዊ አካሄድ (በራሱ በውስጥ መተዳደሪያ ደንቡ ወይም በመመሥረቻው ጽሁፉ መሠረት (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 459)፤ በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 460)፤ በዳኛ ውሳኔ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 461)፤ ወይም ደግሞ በአስተዳደር ውሳኔ (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 462) መሠረት ስለመፍረሱ የቀረበ መረጃ የለም። በህጉም መሠረት ባይሆን ፈርሷል ያልተባለ ለመፍረሱም ለማኅበሩ የደረሰው ወይም ለህዝብ ይፋ የተደረገ ነገር ሳይኖር ህጋዊነቱን እንደያዘና መምህሩ ከጎኑ እያለ ሌላ ኢመማ በስምና አርማው እንዲጠቀም በመንግሥት የተፈቀደለት ”አዲሱ ኢመማ” ተመሠረተ ተባለ።

 

ይህ ድርጊት ከሕግ አግባብ ጋር ሲገናዘብ የሕግ ጥሰት የተፈጸመበት አድራጎት ነው። የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 452(1) ብንመለከት ”የማኅበሩ ስም እንደሰዎች ስም ዓይነት ልክ የሚጠበቅ ነው” የሚለው ድንጋጌ ተጥሶ የተፈጸመ ድርጊት ነው።

 

በዚሁ ሕግ ቁጥር 38 (1) በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ”ማንኛውም ልጅ የአባቱ ወይም የእናቱ ወይም ደግሞ በህይወት ካሉት እህቶቹና ወንድሞቹ የአንደኛው የግል ስም ብቻ ሊሰጠው አይችልም። ተብሎ የተደነገገው ከላይ ከተጠቀሰው ቁጥር 452(1) ድንጋጌ ጋር ሲገናዘብ ”አዲሱ ማኅበር” በአንድ ሀገር፤ በአንድ የመምህራን ስብሰባ ውስጥ አንድ የታወቀ ዓላማ አራምዳለሁ ብሎ የተቋቋመና በሕግ አግባብ ያልፈረሰን ማኅበር ስምና አርማ እኔም ልጠቀም ፍቀዱልኝ ሲል (ራሱም ጠይቆም ከሆነ ማለቴ ነው) ሕገ ወጥ ጥያቄ ማቅረቡ ሲሆን ይህን የሚፈቅድም አካል ቢኖር ሕገወጥ ድርጊት መፈጸሙ የሚያከራክር አይሆንም። በኢትዮጵያ ሀገራችን ግን ተፈጸመ።

 

ይህ በሌሎች አካላት የተፈጸመ የሕግ ጥሰት እንዳለ ሆኖ በዚህ ቦታ በጣም አስገራሚው ጉዳይ የፍትህ ሰጭ አካላት እርከን ቁንጮ ላይ በሚገኘው በጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ላይ ሳይቀር ”ከሳሽ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር - ተከሳሽ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር” እየተባለ ሲጠራ ውስጡን ለማያውቅ ታዳሚ ግራ ከማጋባቱ ባሻገር የሀገሪቱ የፍትህ አሰጣጥ ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ክስተት ይመስለኛል።

 

2ኛ - ከሳሽ (አዲሱ ኢመማ) ገና ከመነሻው ፋይል ሲከፈት በጊዜው ስያሜ በአራዳ ወረዳ ፍ/ቤት ምክንያቱን እግድ አርጎ ነው

ይህ ርዕስ ትንሽ ወደኋላ መለስ ብለን የጉዳዩን መነሻ ታሪክ እንድናስታውስ ይገፋፋናል። ነባሩ ኢመማ ከየካቲት 11 እስከ 13 ቀን 1985 ዓ. ም. 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በማኅበሩ የስብሰባ አዳራሽ በዋናው ጽቤት ቅጥር ግቢ አዲስ አበባ አካሄደ። በነ አቶ ዮሐንስ ሀጎስ የሚመሩ አምስት ሰዎች የተሰጣቸውን የቤት ሥራ ለማስፈጸም እንዲረዳቸው ለአመራር ባለመመረጣቸው አኩርፈው አፈነገጡ። ራሳቸውን የዲሞክራቶች መምህራን ጊዜያዊ አስተባባሪ ነንና ቻርተሩ ባጎናጸፈን መብት ተጠቅመን በአዲስ መልክ እስክንደራጅ የአንጋፋው ኢመማ ንብረት ይታገድልን ብለው በጊዜው አጠራር በአራዳ ወረዳ ፍ/ቤት ክስ መሠረቱ። ከቀበሌ 53 ተመራጮችና ከፖሊስ ጋር ተመሳጥረው የማኅበሩን ቢሮዎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ አሳሸጉ፣ የባንክ አካውንቱን አሳገዱ። አንድ መኪና አስወሰዱ። ሕገ ወጥ ድርጊቱን የተቃወሙ ሥራ አስፈጻሚዎችን አሳሰሩ።

 

ወደ ሙግቱ ሲገባ ከላይ እንደተጠቀሰው ”እነዚህ” ሰዎች የክሳቸው ምክንያት አድርገው (የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 222 (1) (ለ) ይመለከተቷል) የክስ ፋይል የከፈቱት እግድን ብቻ መሠረት አድርገው ማለትም እስክንደራጅ ድረስ የነባሩ ኢመማ ንብረት ይታገድልን ብለው ሲሆን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 1555 ስር እንደተደነገገው እግድ እንደ ክስ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው ተከሳሽ ከከሳሽ ጋር የገባውን ግዴታ እንዳይጥስ እየጣሰም ከሆነ እንዳይቀጥል የእግድ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ሲፈልግ ነው። በዚህ በኢመማዎች ጉዳይ ግን አንደኛው ከሌለኛው ጋር የገባው ግዴታ በሌለበት ይህን ፋይል መክፈት ህጋዊነት የሌለው አካሄድ ነበር።

 

በሕግ ላይ ብቻ ተመስርቶ ብይን ሰጠ የተባለለት የአራዳው ፍ/ቤትም እግድን የክሱ ምክንያት ያደረገ ፋይል የክስ ምክንያት የለውም ብሎ መዝገቡን ዘጋው። ክሳቸው ውድቅ ሆነ፤ በተክለሃይማኖት ፍ/ቤት የታሰሩትን በነፃ ፈቶ አሰናበተ።

 

በዛን ወቅት ከተፈጸሙብን አሳዛኝ ድርጊቶች ውስጥ ተለጣፊዎች እኛን ለመውረስ በሚያመቻቸው መልክ ክስ መስርተው ሌላ እግድ እስኪያስወጡ ድረስ ታስቦበት በሚመስል ሁኔታ ከኪሳችን እሱን አምነን ያስቀመጥነውን የማኅበሩን ገንዘብ እንዳንጠቀምበት የብሔራዊ ባንክ ያልሆነ የሆነ ሰበብ እየደረደረ ከለከለን። በጊዜው 5ኛ አሁን የወረዳ 3 ፖሊስ ጣቢያ የተባለው አግቷት የነበረውን ቶዮታ መኪና የት እንዳደራሳት እስካሁንም የሚታወቅ ነገር የለም።

 

3ኛ - የመጀመሪያዎቹ ከሳሾች (እነ ዮሐንስ ሐጎስ) ክሱን በእነ አህመድ አባቡልጉ ስም እንዲያደርጉት ሲመከሩ የከሳሽና የተከሳሽ ኢመማዎችም አፈጣጠርና ህልውና ሆን ተብሎ አንድም ሁለትም መስለው እንዲታዩ ተደርጓል፤

ከመነሻው ተከሳሽ የነበረው አንጋፋው ኢመማ የተቋቋመው በ1941 ዓ.ም የምዝገባ ሰርተፊኬት ቁጥሩ 25፤ የተሰጠው በ1961 ዓ.ም. የሚያገለግለው ላልተወሰነ ጊዜ ሲሆን ከሳሽ የነበረው ተለጣፊው ኢመማ ደግሞ የመጀመሪያ ስብሰባውን ያካሄደው በ1985 ዓ.ም. በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት አዳራሽ፤ የምዝገባ ሰርተፊኬት ቁጥሩ 161 የተሰጠው በ1986 ዓ. ም.፤ የሚያገለግለው በየዓመቱ ከታደሰ ነው። ይህን እውነታ ማለትም ሁለት የመምህራን ማኅበራት በኢትዮጵያ ስለመኖራቸው 1ኛ የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በራሳቸው አንደበት ደጋግመው በአደባባይ ተናግረውታል፤ 2ኛ ከዓለም ሥራ ድርጅት (ILO) ጋር የቀድሞዋ የትምህርት ሚኒስቴር ወ/ሮ ገነት ዘውዴና የኢትዮጵያ መንግሥት በጄኔቭ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ፍሰሀ ይመር በተለያየ ወቅት ኦፊሻል የሆነ የጽሁፍ ደብዳቤ ሲለዋወጡ ይህንኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቃል በመድገም ሁለት ማኅበር መኖሩን አረጋግጠዋል፤ እንደዚሁ ከዓለም መምህራን ማኅበር (EI) ሹማንቶች ጋር እነ አቶ ብሩክ በቤልጄም ከኢትዮጵያ ኢምባሲ የኢትዮጵያን መንግስት ወክለው በተደጋጋሚ ባካሄዱት ውይይት (ሁለት ማኅበር እንዳለ) አልካዱም። አሁን ያሉት የትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ስንታየሁም ቢሆኑ በግንቦት ወር 1998 ዓ. ም. ከዓለም ሠራተኞች ፌደሬሽን፤ ከዓለም መምህራን ማኅበርና ከዓለም አቀፉ የነፃ ጋዜጠኞች ማኅበር የተውጣጣ ልኡክ በቢሯቸው ተቀብለው ሲያነጋግሩ ”አዲሱ” ማኅበር ብዙ ተከታይ እንዳለው፤ የአንጋፋው ግን ውስን መሆናቸውን መስክረው ያም ሆኖ ቢሯቸውን ለሁለቱም ማኅበራት ክፍት እንደሚያደርጉና ከሁለቱም ጋር አብረው ለመሥራት ፍቃደኛ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።

 

እንግዲህ ይህ ሁሉ የባለስልጣናቱ ምስክርነት ለዲፕሎማሲው ፍጆታ ሲባል ለትልልቆቹ ሰዎች የቀረበ እንጂ ለእኛ ለስኪን ዜጎች ፍ/ቤት መረጃ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም ቢባል እንኳን የሁለቱ ማኅበራት (እውነተኛውና ተለጣፊው) የመመስረቻ ዓመትና የሰርተፊኬት ቁጥር የተለያየ መሆኑን የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤትና የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት መቀበል ተስኗቸው በመዝገብ ቁጥር 161 የተመዘገበው ”አዲሱ” ኢመማና በመዝገብ ቁጥር 25 የተመዘገበው ነባሩም ኢመማ አንድ ማኅበር ነው ሲሉ፤ ሰበር ሰሚውም ይሄንኑ ሲያጸድቀው የፍትህ ሥርዓታችን ምን ያክል አደጋ ላይ እንደወደቀ የሚያረጋግጥ ይመስለኛል። ውሳኔው የፖለቲካ ትዕዛዝ እንጂ የሕግ አተረጓጎም ጉዳይ አይደለም የምለውም ለዚህ ነው።

 

4ኛ - በስር ፍ/ቤት ተከሳሽ ላይ ምንም አይነት መሸፈኛና ይልኙታ የሌለው የመንግሥት ተደጋጋሚ አድልዎና የፖለቲካ በደል ተፈጽሞብናል፤

ከወረዳ ፍ/ቤት እስከ ፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የዘለቀው የ15 ዓመት ክርክር ሲካሄድ ማንኛውም የማኅበሩ ንብረት እንዳይንቀሳቀስ በፍ/ቤት ትዕዛዝ ታግዶ ነበር። ለምሳሌ ቢሮዎች ታሽገዋል፤ የባንክ ሂሳብ ተዘግቷል፤ ተሸከርካሪዎች ቆመዋል። ይሄ እግድ ተጀምሮ እስኪጨረስ ተፈጻሚ የሆነባቸው ግን ከስር ፍ/ቤት ተከሳሽ የነበሩት ማለትም በመዝገብ ቁጥር 25 የታቀፉት የነባሩ ኢመማዎች አባላት ብቻ ናቸው። የተለጣፊው ማኅበር ግን የኪራይ ቤቶች ቢሮ እንዲሰጣቸው ተደርጓል። በየክልሉ ያሉ የማኅበሩ ቢሮዎች ተፈቅደውላቸዋል። የባንክ ሂሳብ እንዲያንቀሳቅሱ በውስጥ ሰርኩላር ሁሉም የመንግስት አካል እንዲተባበራቸው ታዞላቸው ሲጠቀሙ ቆይተዋል።

 

እኛ ግን በልመና ያገኘነው ንብረት (ኮምፒውተሮች፤ እስካነርና ፋክስ፤ መጻሕፍት፤ የጥናትና ምርምር ሥራዎችና ጠቃሚ ሰነዶች) ሳይቀር በማይመለከተን ጉዳይ ሁሉ ለምርመራ እየተባለ በፖሊስ ተወስዶብናል። የህትመት ሥራዎቻችን እንዲቋረጡብን ተደርጓል። ንፁሀን መምህራን በደህንነት ሠራተኞች የቁም ስቅላቸውን እንዲያዩ ተደርገዋል። ልዩ ክትትል ይደረግባቸዋል። ይህ ዓይነቱ ከሕግ በላይ የሆነ ሕገ ወጥ የአድልዎ ተግባር እንዲታረም በየደረጃው ላሉት ፍ/ቤቶችና የመንግሥት ባለስልጣናት አመልክተን ሰሚ አላገኘንም። በመንግስት ትዕዛዝ ለተለጣፊዎች ያልሆነላቸው ወሳኝ ነገር ቢኖር የመምህራንን ልብ ማግኘት ወይም ማሸነፍ አለመቻላቸው ብቻ ነው።

 

5ኛ - የስር ፍ/ቤት የስምና አርማ (የማንነት መለያ) እና የምዝገባ ቁጥር ቅደም ተከተል ልዩነትን ግምት ውስጥ ባለማስገባቱ ያስከተለውን የሕግ ግድፈት የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለማየትና ለማቃናት አልቻለም ወይም አልፈለገም፤

ለዓመታት በዘለቀው የፍ/ቤት ውሎ የደረሰብን እንግልት ምን ይመስል እንደነበር ግንዛቤ ያህል ከአራት ዓመት ወዲህ የሆነውን ብቻ ቀንጨብ አድርጌ ለቅርብ።

 

ቀደም ሲል በተካሄደው ሙግት የነበረው የመርታትና የመረታት ሂደት እንዳለ ሆኖ የፌደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት (የኮም/ቁጥር 11985) በህዳር 18 ቀን 1996 ዓ. ም. ባስዋለው ችሎት ”የአዲሱ” ኢመማ አመራሮች ቀድሞ ነገር የመክሰስም ህጋዊ መብት እንደሌላቸው አረጋግጦ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 33/2/ መሠረት ክሳቸውን ውድቅ አደረገው። እነሱ ለጠቅላይ ፍ/ቤት (የፍ/ብ/ይ/መ/ቁ. 13828) ይግባኝ ብለው በየካቲት 15 ቀን 1996 ዓ. ም. ባስዋለው ችሎት ጠቅላይ ፍ/ቤቱ በፍትህ ሚኒስቴር ስለተመዘገቡ ህጋዊ ናቸውና መክሰስ ይችላሉ። አከራክረህ ፍርድ ስጥ ብሎ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 341/1/ መሠረት ወደ ከፍተኛው ፍ/ቤት መለሰው።

 

ከፍተኛው ፍ/ቤትም የተወሰነ ወራት በቀጠሮ ካመላለሰን በኋላ ጠቅላይ ፍ/ቤቱ ህጋዊ ናቸው ያለውን ጠቅሶ በዚሁ መሠረት የኢመማን ንብረት ለተለጣፊዎች እንድናስረክብ ፈረደብን። እኛም በተራችን ይግባኝ አልንና ባልቀረበለትና ባላየው ጉዳይ ጠቅላይ ፍ/ቤቱ መጠቀሱ አላግባብ መሆኑ ተተችቶና ፍርዱ ተገልብጦ እንደገና ወደ ከፍተኛው ፍ/ቤት ተመለስን።

 

የፌደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት እንደገና ፈረደብንና ለሦስተኛ ጊዜ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ አልን። ጠቅላይ ፍ/ቤቱም ከተወሰኑ ቀናት ቀጠሮዎች በኋላ ፍርዱን አጸናብን። ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቀረብን። በቀጠሮ ስንመላለስ ቆይተን ሰኔ 4 ቀን ስንቀርብ እንደገና ለሐምሌ 23 ቀን 2000 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቶን ተመለስን።

 

በመካከሉ የከፍተኛው ፍ/ቤት በወሰነው መሠረት የኢመማን ንብረት ሰኔ 19 ቀን 2000 ዓ. ም. ለተለጣፊዎች እንድናስረክብ ከፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ደረሰን። እግድ እንዲታዘዝልን ቃለ መሀላ አስገባን። ፋይላችን የትኛው ክፍል እንደተመደበ ከሬጅስትራር ቢሮ በተነገረን መሠረት ስንጠባበቅ ቆየን። ተጠርተን ስንገባ ዳኛው አቶ ሐጎስ ወልዱ ”በእናንተ ጉዳይ ሁለት ጠጉር አበቀልኩ፤ እዚህ ቤት ካአለ እናንተ ጉዳይ ሌላ የማይሠራ መሰላችሁ!! የእናንተን ጉዳይ አላይም” ብለው ተቆጡን። እጅግ አዝነን ወጣን። ዳኛው ለምን እንደዛ እንደተበሳጩ ገረመን እንጂ ፋይሉን አለማየታቸው የሕግ መሠረት አላቸው። ምክንያቱም አንድ ዳኛ አንድን ጉዳይ ደግሞ ማየት የለበትም። አቶ ሀጎስ ደግሞ በከፍተኛው ፍ/ቤት ዳኛና ፕሬዝዳንት ሆነው፤ ወደ ጠቅላይ ፍ/ቤት ከተዛወሩም በኃላ በአስተዳደር መልክም ሆነ በዳኝነት የኢመማ ጉዳይ ከሳቸው እይታ ውጭ የሆነበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም።

 

ከሳቸው ቢሮ በዚህ መልክ ከተሰናበትን ጊዜ ጀምሮ በተከታታይ ቀናት የተለያዩ ሦስት ዳኞች ዘንድ ፋይላችን ቀርቦ አንዳቸውም ሊያዩት ፍቃደኛ አልሆኑም። እንደሚመስለኝ ”ማን ያቦካውን ማን ይጋግራል” በሚል ሳያድሙ አልቀረም። በነገራችን ላይ በዚህ በፍ/ቤት ደንበኝነታችን ያፈራናቸው በርካታ ሙያተኞችና ባለጉዳዮች ”እናንተ ሁሉንም ማኖ እናስነካቸው ብላችሁ ካልሆነ በስተቀር ሙግታችሁ ከመንግሥት ጋር መሆኑን እያወቃችሁት ይፈረድልናል ብላችሁ ነው የምትደክሙት᐀” እያሉ በተዋዛ አማርኛ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ይነግሩን ነበር። ትንቢታቸው ተፈጸመ።

 

ከብዙ አቤቱታ በኃላ ሰኔ 18 ቀን ወደ 11 ሰዓት ገደማ ለበነጋው ሰኔ 19 ቀን ጧት ተመለሱ ተብልን ተቀጠርን። በታዘዝነው መሠረት ቀረብን። ያለወትሮው ስድስት ዳኞች ተሰይመዋል። የሕግ ግድፈት ተፈጽሞብናል ያልነውን እንድናስረዳ ለሦስት ደቂቃ ያክል ጥያቄና መልስ ከተደረገልን በኋላ ”ውጭ ቆዩ” ተባልን። ከሁለት ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ እንደገና እንድንገባ ታዘዝን። እኛ ቢያንስ እስከመጪው ቀጠሮ (ሐምሌ 23 ድረስ) እግድ ይታዘዝልናል ብለን ስንጠብቅ ምናልባት የመሀል ዳኛ ሳይሆኑ አይቀሩም የምላቸው አቶ አብዱልቃዲር ሙሀመድ በቃል የገለጹልን፡-

 

የስር ከሳሾች (ተለጣፊዎችን ማለታቸው ነው) የስር ፍ/ቤት ባዘዘው መሠረት ጠቅላላ ጉባኤ አካሂደዋል፤ አመራር መርጠዋል፣ የስር ከሳሾችን የፍትህ ሚኒስቴር ማኅበራት ምዝገባ ክፍል ህጋዊነታቸውን ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሰጥቶ መዝግቧቸዋል፤ በየጊዜውም አድሶላቸዋል፤ እናንተ (በስር ፍ/ቤት ተከሳሽ አሁን አቤት ባይ) ግን የምዝገባ ሰርተፊኬታችሁ አልታደሰም፤ ጠቅላላ ጉባኤም አልጠራችሁም ማኅበሩም ሁለት ሳይሆን አንድ ነው፤ ”ስለዚህ የስር ፍ/ቤት በሰጠው ፍርድ ምንም የሕግ ግድፈት ስላላገኘንበት እንዳለ ተፈጻሚ እንዲሆን አጽንተነዋልአ” የሚል ነበር።

 

እነዚህ እንደ ፍርድ መስጫ ምክንያት የቀረቡትን ሀሳቦች የሕግ አግባብ እንደሌላቸውና ከእውነታው ጋር የሚጋጩ ስለመሆናቸው ከላይ በየጋጣሚው ያብራራኋቸው ስለሆነ የተባለ ሀሳብ ላለመደጋገም አልመለስባቸውም። በቀደምት ገጾች ያልተነሱት ጠቅላላ ጉባኤ መጥራትና የሰርተፊኬት እድሳት የተባሉት ይመስለኛል።

 

በመሠረቱ ኢመማ የስብሰባ ሥነሥርዓትና የውክልና ምርጫ ደንብ አለው። እኛ በዚህ ስነሥርዓትና ደንብ ተመርተን የጠራነው ጠቅላላ ጉባኤና ያካሄድነው የአመራር ምርጫ ወደጎን ተብሎ ከማኅበሩ ደንብና ሥርዓት ውጭ በካድሬዎች ትዕዛዝ ከየመንገዱ የተሰባሰበው የተለጣፊዎቹ ጠቅላላ ጉባኤ በምን መስፈርት እንደ አንድ የፍርድ ምችችት ነጥብ ሊመዘግብላቸው እንደቻለ እጅግ የሚያሳዝን ነው። በምንም መስፈርት የሕግ አግባብ ያለው አሠራር ሊሆን አይችልም። ሌላው ስለ ሰርተፌኬት እድሳት ካነሳን በመጀመሪያ ሰርቲፊኬትን አለማሳደስ በራሱ ህጋዊ ህልውናን የሚያሳጣ ምንም የሕግ መሠረት የለውም። ሌላው ነጥብ የአንጋፋው ኢመማ ሰርቲፊኬት የሚያገለግለው ላልተወሰነ ጊዜ ነው። እንድናሳድስ ስልጣን ባለው አካል ታዘን ያልፈጸምንበት ሁኔታ የለም። ይልቁንም በኛው ተነሳሽነት እንዲታደስልን አመልክተን የእናንተ ጉዳይ በፍ/ቤት ስለተያዘ አንድ ውሳኔ እስኪሰጥ ጠብቁ ነበር የተባልነው። የተለጣፊዎቹ ሰርቲፊኬት እየታደሰላቸው የመሆኑን ሚስጢር ያወቅነው ከችሎቱ ነው።

 

ማጠቃለያ፡-

በዚህ ውሳኔ መሠረት 59 ዓመት ያስቆጠረው፤ እንደ ወርቅ በእሳት የተፈተነው፤ በዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና ያተረፈውና ለኢትዮጵያ መምህራን ብቸኛ ነፃ የሙያ ማኅበር የነበረው አንጋፋው ኢመማ ለጊዜውም ቢሆን ህልውናውን አጥቷል። ከዚህ በደል ለመታደግ አመራሩና አባላቱ ይህ ቀረው የማይባል መሪር መስዋዕትነት (ህይወታቸውን ጭምር) ከፍለውለታል። የዓለም መምህራን ማኅበር (EI – Education International) እና በ160 ሀገሮች ያሉት አባላቱና ደጋፊ ድርጅቶች፤ ለመምህርነት ሙያ ክብር ያለው የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ሁሉ ኢመማን ከዚህ አደጋ ለማዳን ያላደረጉት ጥረት አልነበረም። የኢትዮጵያ መንግሥትና የቀድሞ የፍትህ ሚኒስትሩ ”ወርቃማው የፍትህ ዘመን” ያሉትን ተቋም የሚያንቀሳቅሱት አካሎች ግን በሰለጠነው መንገድ ችግርን ለመፍታት ገና ስላልተዘጋጁ ለጊዜው አልሰሟቸውም።

 

በእርግጥ በአንድ በኩል ሂደቱና ውጤቱ ምንም ሆነ ምንም በሀገሪቱ በየደረጃው ባለው የፍትህ እርከን (ወረዳ፤ ከፍተኛ፤ ጠቅላይ) ፍ/ቤቶች ብሎም በጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ድረስ ጉዳያችንን የማድረስ መብታችን መከበሩ አንድ መልካም ነገር ነው። እኛም የአንጋፋው ኢመማ ተጠሪዎች የወከለንን መምህር አደራ ጠብቀንና በፍላጎቱ ተመርተን ጉዳዩን እዚህ ደረጃ ማድረሳችን ቢያንስ ከታሪክ ተወቃሽነት የፀዳ ህሊና አትርፈናል። በሂደቱም ተፈትነን ብዙ ትምህርት ቀስመናል።

 

በሌላ በኩል ደግሞ መምህራን አንድ ላይ በጽናት ቆመን ድርጅታዊ አቅማችንን ባለማጎልበታችን፤ የኛም የአመራሩ አካል የልምድ እጥረት ተዳምሮበት ለዚህ ጥቃት መጋለጣችን እንዳለ ሆኖ ሁላችንንም (እኛንም፤ ተለጣፊዎችንም ሆነ የመንግሥት ባለስልጣናትን) ሊያሳፍረንና ለታሪክ ትዝብት የሚጥለን ኩነት ገጥሞናል። በዚህ ሁሉንም (ብሔራዊ ክብራችንን ጭምር) ለውርደትና ለሽንፈት በዳረገው የገመድ ጉተታ የባከነውን ጊዜ፤ እውቀት፤ ጉልበትና ገንዘብ ለሀገርና ለወገን በሚጠቅም ተግባር ላይ ለማዋል አለመቻላችን የባህሪይ ለውጥ አምጥተን የተሻለ ህይወት ለመምራት ገና ብዙ እንደሚቀረን አመልካች ነው።

 

መጠኑና አጠቃቀሙ በከፍተኛ ደረጃ ተጠንቶ ቀለል ያለውን በሽታ ተከትቦ ከባዱን ወይም ገዳዩን በሽታ መከላከል ተችሏል። ጥላቻን በጥላቻ፤ ቂምን በብቀላ፤ ችግርን በችግር፤ ቀውስን በቀውስ፤ በደልን በበደል ለማስቆም መሞከር ግን ቀን ይገፋ እንደሁ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ሲያመጣ አልታየም። ጊዜ ጠብቆ መፈንዳቱ የማይቀር ነው።

 

እስከዛው መንግሥትና መምህራን እየተራራቁ፤ መምህራን እየተከፋፈሉ፤ ሥራው እየተበደለ የአገርና የወገን ብሔራዊ ጥቅም ላይ ቀላል የማይባል አሉታዊ እድምታ እንደሚኖረው እሙን ነው። የኢመማ ጉዳይ የሆነው ይሄው ነው። መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት ሦስት ጊዜ ሊያስብበት ይገባል። የኢትዮጵያ ህዝብና ለማስተማር ሙያ ክብር ያለው ወገን ሁሉ ለችግሩ መቃለል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በመምህራን፤ በሙያ ባልደረቦቼና በራሴ ስም አሳስባለሁ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!