በባህር ዳር ሰልፍ በአድዋና አዲስ አበባ የአድዋ ድል በዓል ዝግጅቶች ይኖራሉ
አማኑኤል ዘሰላም

የአንድነት ፓርቲ፣ በሶስት ከተሞች ታላላቅ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች፣ ለማድረግ መወሰኑን ከሚሊየነሞች ድምጽ ለነጻነት ፌስቡ ገጽ አነበብኩ። እንቅስቃሴዎቹ የሚደረጉባቸው ከተሞች፣ አድዋ፣ አዲስ አበባ እና ባህር ዳር ናቸው።

በአድዋ እና በአዲስ አበባ ከሌሎች ደርጅቶ ጋር በጋራ በመሆን (ሚአድ፣ አረና፣ ትብርር፣ መድረክ፣ ...)፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ሕዝቡ ሁሉ ኩራት የሆነውን የአድዋ ድል በማሰብ ትልቅ አከባባር ለማድረግ ነው የታቀደው። በአድዋና በአዲስ አበባ ባሉ ብዙ ህዝብ ሊይዙ በሚችሉ አደባባዮች አከባበሩ ሊደረግ እንደሚችል ግምት ቢኖርም፣ የአንድነት ፓርቲ የአከባበሩ ይዘት፣ ሰዓትና ቦታን ገና ይፋ አላደረገም።

በባህር ዳር የሚደረገው ግን ከአድዋና ከአዲስ አበባው የተለየ ነው የሚሆነው። በቅርቡ የአማራ ክልል ም/ ፕሬዚዳንት እና የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው፣ በክልሉ የሚኖረው ሕዝብ ላይ የሰነዘሩት ጸያፍና ከአንድ መሪ የማይጠበቅ አባባሎችን በመቃወም የሚደረግ ሰላማዊ ሰልፍ ነው። ጉዳዩ አንድ ሰው የተናገሩት ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ እንደዚህ አይነት ሕዝብን የናቀና ያዋረደ አስተያየት የሰጡ ባለስልጣን ከሃላፊነታቸው ወዲያውኑ እንዲነሱ አለማድረጉ፣ በሕግም አለመጠየቁ፣ ችግሩ ከግለሰብ አልፎ ድርጅታዊ መሆኑንም የሚያመላክትበትም ሁኔታም አለ።

"የአማራው ህዝብ ሰንፋጭ የሆነ ትምክተኝነት የተጠናወተው በመሆኑ በቤንሻንጉልና በሌሎችም ቦታዎች ለመሰደዱ ምክንያት ሆኖታል"፣ "አማራው በባዶ እግሩ እየሄደ የሚናገረው ንግግር ግን መርዝ ነው"፣ "የአማራው ሕዝብ የትምክህት ልጋጉን ማራገፍ አለበት" .... የመሳሰሉ አስተያየቶችን ነበር ባለስልጣኑ የሰነዘሩት።

ሰልፍ መጥራት በራሱ ለውጥ አያመጣም። በባህር ዳር፣ አድዋ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ የሚደረጉ ሰልፎችና ዝግጅቶች በማይሻማ መልኩ ፖለቲካውን እንዲያናጉት፣ የማያሻማና የሚያስተጋባ መልእክት እንዲያስተላለፉ ከተፈለገ፣ ሕዝብ በነቂስ መውጣት አለበት። ለዚህም ትልቅ ድርጅታዊና የቅስቀሳ ሥራ መስራቱ የግድ ነው። በየወረዳው፣ በየመንደሩ ፣ ቅስቀሳዎች መደረግ አለባችው። በራሪ ወረቀቶች፣ ፓምፍሌቶች በስፋት መዘጋጀትና መበተን ይኖርባቸዋል።

አንድ ነገር አንርሳ። እኛ ኢትዮጵያውያን ካልደገፍናቸው፣ ከጎናቸው ካልቆምን ፓርቲዎቹ ብቻቸውን በራሳቸው ምንም ሊያመጡ አይችሉም። ገዢው ፓርቲ የሚተማመነው በያዘው ጠመንጃ፣ ባሰማራቸው ሰላዮቹና ካድሬዎችቹ ነው። አንድነቶች ግን የሚተማመኑት በሕዝብ ጉልበት ብቻ ነው። እያንዳንዳችን የድርሻችንን ከተወጣን፣ በአዲስ አበባ፣ በአድዋና ባህር ዳር የምንኖር የሚደረጉ ሰልፎችን እና ዝግጅቶችን ከተቀላቀልን፣ ነጋሪና ቀሳቅሽ ሳንፈልግ፣ በኛው አነሳሽነት ቅስቀሳ ካደረግን፣ ተዓምር የማንሰራበት ምንም ምክንያት የለም።

በሰልፉ ለመገኘት የማንችል ደግሞ፣ በተለይም በውጭ አገር ያለን፣ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ከማሳወቁ በተጨማሪ፣ በገንዘባችን ትልቅ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ