ሠላማዊ ወይስ ትጥቅ?

ጋቹዬ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

“የሰዎቹን ሃሳብ አልወደውም፤ የሚሉት ነገር ሁሉ ለእኔ ሕልውና አደገኛ ነው። አትናገሩ የሚላቸው አካል ሲነሳ ግን አሰላለፌ ከሰዎቹ ጋር ነው” ነው ያለው ቮልቴር?

 

ይህን ጽሑፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ”ሠላማዊ ወይስ ትጥቅ? - እንካስላንቲያዎቹ” በሚል ርዕስ ኩቺዬ የተባሉ ‘የሠላማዊ ትግል ሐዋርያ’ ሰሞኑን በተለያዩ ድረ-ገፆች ያስነበቡን ጽሑፍ ነው። የኩችዬ ጽሑፍ በአንድ በታለመ ጭብጥ ዙሪያ ያነጣጠረ ባለመሆኑ ወይም ስለትጥቅ ትግልና ስላለው ተጨባጭ ሁናቴ አስቸጋሪነት የሚያትት እየመሰለ፤ ሲፈልግ ስለግለሰቦች ተክለ-ስብዕና፤ ሲያሻው ትጥቅ ስለመረጡ ድርጅቶች ዓላማ እየነካካ በመውረዱ፤ ምላሼን ስጽፍ እንደ ኩችዬ እዚህም እዚያም መርገጥ ግድ ሊሆንብኝ ነው።

 

ሆኖም ዚቅ እንደሚዘርፍ ደብተራ፤ ከዚህም ከዚያም ዘርፈው ኩችዬ በጽሑፋቸው ካካተቱዋቸው ነገሮች ውስጥ፤ በማውቃቸው እርግጠኛ በሆንኩባቸውና መሰረታዊ ናቸው ባልኳቸው ነጥቦች ዙሪያ ትኩረቴን ማድረግ እፈልጋለሁ። እነሆ፦

 

ፀሐፊው፦ ”ዛሬ የትጥቅ ትግልን የመረጡ ሰዎች ትናንት ስለሠላማዊ ትግል ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩ ናቸው” በማለት ነው ጽሑፋቸውን የጀመሩት። ለዚህም ብዙ ማስረጃዎች መኖራቸውን ለማመላከት ይመስላል … ”ሞኝና ቪዲዮ …” የሚል ተረት አስቀምጠዋል። አዎ! በዚህ እንስማማለን። ከቅንጅት አመራሮች ውስጥ እንደዶክተር ብርሃኑ ስለሠላማዊ ትግል በቃልም፤ በተግባርም የተናገረ የለም። ይህን ዶክተር ብርሃኑም ራሳቸው በተደጋጋሚ በየመድረኩ ሲናገሩ እየሰማን ነው። እንደውም ዶክተር ብርሃኑ ቅንጅት በወረዳ 23 የጠራውን ስብሰባ፤ ከኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል ጋር ሆነው ሲመሩ የተናገሩትን እዚህ ላይ መጥቀስ ይህንኑ ሃሳባችንን ያጠነክርልናል።

 

“ባላጋራን መግጠም በማይችለው መንገድ ነው። ኢህአዴጎች ጦርነት ይችላሉ፣ ቆረጣ ይችላሉ፤ እነሱን በኃይል መግጠም በጥንካሬያቸው መግጠም ነው። ግን የማይችሉትና የማያውቁት አንድ መንገድ አለ። እርሱም ፍቅር ነው።የምናሸንፋቸው በማያውቁት የፍቅር መንገድ ስንገጥማቸው ነው። አሁን እዚህ አዳራሽ ውስጥ ያለነው በሙሉ ነጭ በነጭ ለብሰን ጧፍ እያበራንና እየዘመርን ወደ መስቀል አደባባይ ብንሄድ ድንብርብራቸው ነው የሚወጣው ...”

 

ይህን የዶክተሩን አባባል ስላስታዎስኩ በማንነቴ ዙሪያ ጥያቄ ከተጫረብዎ፤ በጊዜው ስብሰባውን በቦታው ተገኝቼ የተከታተልኩ ሰው መሆኔን ልጠቁምዎ እፈልጋለሁ።

 

እንግዲህ በግንቦት ሰባት አመራሮች የቀድሞ አቋም ዙሪያ የሚያለያየን ነገር የለም።ይህን ራሳቸው አመራሮቹም እያሉት ያለ ነገር ነው። በዚህ ዙሪያ ኩችዬ ያሉት ትርፍ ነገር ቢኖር፦ ”ሞኝና ቪዲዮ …” ብለው ያዘመኑት ተረት ብቻ ነው። በእርግጥም የግንቦት ሰባት መሪዎች “ሠላማዊ ትግል ያዋጣል ብለን አናውቅም” ባላሉበት፤ ይልቁንም “ወዳሁኑ አቋማችን የደረስነው ስናራምደው የነበረው የሠላማዊ ትግል ስትራቴጅ በአሁኑ ጊዜ አያዋጣም የሚል ድምዳሜ ላይ ከደረስን በኋላ ነው” እያሉ ባለበት ሁናቴ፤ ልክ “ይህን ብለን አናውቅም” ብሎ የተናገረ ሰው ያለ ይመስል “ሞኝና ቪዲዮ …” ወደሚለው ተረት መንደርደርዎ፤ ተረት ማዘመን መቻልዎን ካልሆነ በስተቀር ሌላ የሚያሳየን ነገር የለም።

 

ብዙዎቻችን እንደምናውቀው ሠሰላማዊ ትግል የነዶክተር ብርሃኑ ብቻ ሳይሆን የፓርቲያቸው የቅንጅትም ዋነኛ አማራጭ ነበር። ልብ በሉ! ዋነኛ እንጂ ብቸኛ አማራጭ አላልኩም። ይህ ማለት ቅንጅት እንደ ፓርቲም ሆነ በዙሪያው ተሰባስበው የነበሩ ሰዎች፤ ከሠላማዊ ትግል ጋር ላይፋቱ በቁርባን አልተጋቡም ማለት ነው።

 

ሆኖም እጅግ በጣም አጭር በሆነው የኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ፖለቲካዊ ምህዳር፤ በገዥው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚዎች ጎራ ዘንድ የሚታይ ትልቅ ድክመት አለ። ይህ ድክመት በአመዛኙ የፖለቲከኞቻችንን ብስለት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። እርሱም አንዴ የያዙትን ወይም የሰሙትን ቲዮሪ አለመልቀቅ ወይም በእንግሊዝኛው ‘ዳይናሚክ’ አለመሆን ነው። እንደውም አቶ/ወ/ሮ ኩችዬ ይህን “መገለባበጥ” ብለውታል። እርሳቸውም ከዚያው ኋላቀር የፖለቲካ ማኅበረሰብ የወጡ እንጂ ከሌላ ፕላኔት የመጡ እስካልሆኑ ድረስ ይህን ማለታቸው ብዙ አያስገርምም። ሌላው ቢቀር ሰባኪው “ኃይማኖት እንደ አባቶቻችን፤ ጥበብ እንደዘመናችን” ማለቱን ቢሰሙ እዚህ ግልብ ድምዳሜ ላይ ባልደረሱ ነበር።

 

ግን ... ግን ... ተገለባባጭ ማለት ምን ማለት ነው? ‘ዳይናሚክ’ ማለትስ?

 

ቃሉ ለብቻው ተነጥሎ ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር፤ ‘ተገለባባጭ’ ማለት በዚህ ጽሑፍ ጭብጥ መሰረት አንድ ግብ የሌለው ወይም ላስቀመጠው ግብ ፅናት የሌለው ማለት ሲሆን፤ ‘ዳይናሚክ’ ማለት ደግሞ፦ የዓላማ ለውጥ ሳያደርግ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት ጊዜንና ሁናቴዎችን እየተከተለ ስትራቴጂዎችን የሚቀይስ ማለት ነው። የተግባር እንጂ የቲዮሪ ችግር እስከሌለብን ድረስ፤ ይህን ትርጉም ኩችዬም ቢሆኑ ይጋሩታል ብዬ እገምታለሁ። ባይጋሩትም እውነት ነው።

 

ታዲያ ከዚህ አንፃር ተገለባባጩ ማነው? መቼም “የሠላማዊ ትግል ሜዳውን ያጠበበብኝን አፋኝ ኃይል በትጥቅ እገጥመዋለሁ” ብሎ የተነሳ አካል፤ የስትራቴጅ ለውጥ አደረገ እንጂ የዓላማ መዋዠቅ ታየበት ማለት ፈፅሞ አይቻልም። ይልቁንም አዲሱ ስትራቴጂ በትግሉ ማምረሩንና በዓላማው መጨከኑን ነው የሚያመለክተን።

 

ከዚህ አኳያ ስለግንቦት ሰባት መስራቾች፦ ፅኑዎች፣ ደፋሮች፣ በሳሎች፣ ፈጣኖች፣’ዳይናሚኮች’፣ አዲሱ ትውልድ የሚፈልጋቸው መሪዎች የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የግድ የፓለቲካ ተንታኝ መሆን አያስፈልግም። ይህ ግልፅ ሐቅ በአጭር ጊዜ ማንም ሊያዳፍነው ያልቻለ የሚሊዮኖች እውነት ሆኗል።

 

ይልቁንም ሌላው ቀርቶ ቅንጅት የተሰኘውን ስያሜ ማግኘት ባልተቻለበት፣ ብዙዎች የሞቱለት ስምና ዓርማ በኢህአዴግ ለተሠሩ ‘ተቃዋሚ’ ተብዬዎች በተሰጠበት፣ ‘ቅንጅት ስንት ካሬ ሜትር ነው?’ እየተባለ በገዥው ልሳኖች ስላቅ በተያዘበት፣ ብልጭ ብላ የነበረቸው ጨረር ከነአካቴው በተዳፈነችበት፣ “ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ ይቋቋም፣ የፍትህ አካላት ከተፅዕኖ ነፃ ይሁኑ፣ ሚዲያዎች ሚዛናዊ መረጃ ማስተላለፍ በሚችሉበት አግብብ ይዋቀሩ፣ …” ብሎ መጠየቅ ብቻ ‘ሕገ-መንግሥታዊውን ስርዓት በኃይል እንደመለወጥ’ ተቆጠሮ በአገር ክህደት በሚያስከስስበት፣ እነዚህን ጥያቄዎች ዳግም ላለማንሳት የፊርማ ዋስትና በተሰጠበት፣በጎደሎው ሕገ-መንግሥታዊ ዶሴ ሳይቀር የሠላማዊ ትግል ዓይነቶች ናቸው ተብለው የተዘረዘሩትን ማሰብ በከባድ ወንጀል እንደሚያስከስስ ልቦና በሚያውቅበት፣ የነፃነቱና የዲሞክራሲው ገደብ የኢህአዴግ ውሃ ልክ፣ ሕግና ዳኝነት አንድ ሰው በሆነበት፣ በአጠቃላይ ሀገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ በጠመንጃ አገዛዝ በታፈነችበት ሁኔታ የእነአቶ በረከትን ምርቃትና ፈቃድ እየተጠበቀ በሚደረግ እንቅስቃሴ “በሠላማዊ ትግል ለውጥ እናመጣለን” ብሎ ማሰብ፤ አንድም ራስን እንደመሸንገል፣ አንድም የኢትዮጵያን ህዝብ እንደ መደለል ይመስላል።

 

የዚህ ሁሉ ዋነኛ ምንጭ ግን ከላይ እንደጠቀስኩት የሁሉም ሳይሆን የብዙዎቹ ፖለቲከኞቻችን ‘ባዶ ግንዛቤ’ ነው። አንዴ በሰሚ ሰሚ የሰማውን የማይለቅ ሌጣ ጭንቅላት ማለቴ ነው። በእርግጥም ከነባራዊው ትንሽ ተስፋ-ሰጭ ጊዜ ጋር ተገናዝቦ፤ ስለሠላማዊ ትግል በትንሹ ከሁለት ዓመታት በፊት የሰሙትን ያንኑ መዝሙር ዛሬ ሁኔታዎች በተለወጡበት ሁኔታ፤ ምንም ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ እንዳለ (እንደወረደ) መዝፈን፤ የአቋም ፅናት ሳይሆን የአዕምሮ መሽናት ነው።መዛግ፣ መሻገት ማለቴ ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለ እነዚህ ሰዎች አገር ተረካቢውን ትውልድ የመምራት አቅሙም፣ አቋሙም አላቸው ማለት ይከብዳል። ምክንያቱም መሪነት ዕውቀትን፣ ብልሀትን፣ አስፍቶ አሳቢነትን፣ ድፍረትን፣ ፅናትን፣ ፈጣንነትን፣ ዕውነትን፣ ከአሉባልታና ከተንኮል መፅዳትን፣ መስጠትን ይጠይቃላ።

 

ከዚህ አኳያ አንዳንድ ‘ፖለቲከኞችንን’ እንመዝናቸው ከተባለ፤ ቦታቸው የት ላይ እንደሚሆን ግልፅ ነው። እደግመዋለሁ ለዚህ የመሪነት ቅባት አይመጥኑም። እነሱ ‘ዲዘርቭ’ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር “የሞኝ ዘፈን ሁል ጊዜ አበባየሆሽ፤ በፋሲካ የተገዛች ባሪያ ሁልጊዜ ፋሲካ ይመስላታል” ለሚለው የአበው ብሂል ብቻ ነው።

 

ሌላው ከኩችዬ ሃሳብ የምስማማበት ነገር ቢኖር ”እንዲመራኝ የምመኘው ሰው፤ይልቁንም ደግሞ ድጋፌን የሚሻ ፖለቲከኛ፤ በራዕይ ጥራት፣ በሐቀኝነት፣ በመልካም ስነ-ምግባር እና በታማኝነት ባህርዮች የታነፀ እንዲሆን እፈልጋለሁ” ያሉት ነው። ትክክል ብለዋል ኩችዬ።

 

ሆኖም በቅንጅት ዙሪያ ከተሰባሰቡ ሰዎች ኩችዬ ያቀረቧቸውን መስፈርቶች የሚያሟሉት እነማን ናቸው? ብለን ብንጠይቅ፤ ከ1 ተነስተን 10 ሳንደርስ 9 ላይ ልንቆም እንችላለን ብል አንባቢን ማስደንገጥ ይሆንብኝ ይሆን? ከነዚህ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ምናልባትም ዋነኛው “ዶክተር ብርሃኑ ናቸው” ብዬ ብመሰክርስ፤ የቃሊቲ ጓዶቼ ዋሸህ ይሉኝ ይሆን? በፍፁም!!!

 

ሐዋርያው “ያየነውን እንናገራለን፣ የሰማነውን እንመሰክራለን” አይደል ያለው?

 

አዎ! ከቅንጅት መሪዎች ጋር ለሁለት ዓመታት አብረን በልተናል፣ ጠጥተናል፣ አውርተናል፣ ተጫውተናል፣ ውለናል፣ አድረናል፣ ተዋውቀናል።

 

ከዕውቀታቸው፣ ከአንደበተ-ርዕቱነታቸውና ከበሳል ፖለቲከኝነታቸው ባሻገር በሰው አክባሪነታቸው፣ በእውነታቸው፣ በጨዋነታቸው፣ በስነሥርዓታቸው፣ በጥንካሬያቸው፣ በደፋርነታቸው፣ ታሳሪዎችን በፍቅር በማሰባሰባቸውና በሌሎችም መሰል ባህሪያቸው ከጠበቅናቸው በላይ ሆነው ካገኘናቸው አንዱ እርሳቸው ናቸው - ዶክተር ብርሃኑ።እዚህ ላይ ጨዋነትን፣ ደግነትንና ለአገርና ለሰው ልጅ ተቆርቋሪነትን በተመለከተ ለእነ ኢንጅነር ኃይሉ እና ለእነ ዶክተር ኃይሉ አርኣያ፤ ከዶክተር ብርሃኑ ባልተናነሰ ሁናቴ ምስክርነቴን ባልሰጥ ውሸታም እሆናለሁ። ሌሎችም ያልጠቀስኳቸው መልካምና ብቁ ሰዎች አሉ። በተገላቢጦሽ ብዙ ጠብቀን ምንም ያላየንባቸው፤ ‘ቢከፍቱት ተልባዎች’ አጋጥመውናል። ሊቁ “ዝናም የሌላቸው ደመናዎች” ያላቸው ዓይነቶች ማለት ነው። የሃሳብና የማስረዳት ችግራቸው ወደማሸሞርና በነገር ወደመዋጋት የሚያንደረድራቸው ፍሬ አልባ ዛፎች።

 

ስለነዚህ ሰዎች ማንነት መናገር ብዙም አያስፈልገኝም። ምክንያቱም ብዙዎች ሐቁን እየደረሱበት ነው - ከኩችዬ በስተቀር። ስለዚህ ለኩችዬ በድጋሚ ላስረግጥላቸው የምፈልገው፤ ግንቦት ሰባትን እየመሩ ያሉት የእርስዎን የመሪነት መስፈርት ያሟሉ ዋነኞቹ ሰዎች መሆናቸውን ነው - እርስዎ እንዳሉት አንድና ሁለት ሆነው ሳይሆን፤ እጅግ ብዙ ሆነንና እልፎችን አስተባብረን። ኩችዬ! ደፈርከኝ አይበሉኝና ሳያውቁ መናገር ልምድዎ ስለሆነ ይሆን ግንቦት ሰባትን የጥቂት ሰዎች ያደረጉት? እባክዎ! እርስዎ የመሪነት መስፈርት እያወጡ፤ በማያውቁት ነገር ላይ በድፍረት የመናገር ልምድዎን ይተው። እኛ ግን ‘ያየነውን እንናገራለን! የሰማነውን እንመሰክራለን!

 

ሌላው ሠላማዊ ትግል በዚህ ጊዜ አዋጭ አይደለም ለማለት ባስቀመጡት ምሁራዊ ይሁን ኢህአዴጋዊ ድምዳሜዎ ዙሪያ፤ አቶ ፅናት ፍቅሩ የተባሉ ፀሐፊ በመጠኑም ቢሆን መልስ የሰጡዎት ይመስለኛል።

 

ኢህአዴግ ካሰራቸው የቅንጅት አመራሮች ጋር እንዲደራደር ዓለማቀፋዊ ግፊቱ በጠነከረበት ወቅት አቶ መለስ በተደጋጋሚ “ከነውጠኞች ጋር ድርድር ብሎ ነገር የለም” ማለታቸውና ጉዳዩን እርሳቸውና ፓርቲያቸው በሚፈልጉት መንገድ ብቻ መጨረሳቸው ለሁላችንም ግልፅ ነው። ሆኖም በዚያው ተመሳሳይ ወቅት የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱትን ኦ.ነ.ግንና ኦ.ብ.ነ.ግን ለድርድር ሲለማመጡ እንደነበር ከራሳቸው አንደበት ሰምተናል። ለምን ከእነኦነግ ጋር መደራደርን መረጡ? መልሱን ለኩችዬ እተወዋለሁ።

 

ልክ በኢትዮጵያ እንደተደረገው በኬንያም የምዋይ ኪባኪ ፓርቲ የምርጫውን ውጤት አጭበረበረ። ሆኖም ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ኦ.ዲ.ኤም (ኦሬንጅ ዲሞክራቲክ ሙቭመንት) በኅቡዕ ቀላል የማይባል ኃይል አዘጋጅቶ ስለነበር፤ፍጥጫውና ትግሉ እንደ ኢትዮጵያ በሁለትና በሦስት ቀናት ጥይት ሊቆም አልቻለም። ከ1500 በላይ ኬንያውያን መስዋዕት ሆነውም ትግሉና አመፁ ሊበርድ አልቻለም። የተደራጀው ኃይል ማስተባበሩን ቀጠለ። በመጨረሻ ፕሬዝዳንት ኪባኪ ከተቃዋሚው መሪ ከራይላ ኦዲንጋ ጋር ለመደራደር እጃቸውን ሰጡ። ተደራደሩ፤ ተስማሙ። የኢትዮጵያው ቅንጅት የኬንያው ኦ.ዲ.ኤም ያገኘውን ያህል ስኬት ለምን አላገኘም? መልሱን ለኩችዬ እተወዋለሁ።

 

እባክዎ ኩችዬ! በአንድ ወቅትና አጋጣሚ ያወቁት የፖለቲካ እውቀት ሁሌ እንደቀኖና የማይለቀቅ እንዳልሆነ አድርገው አይውሰዱ። በስተመጨረሻ ያነሱት ትልቅ ነጥብ ቢኖር ግንቦት ሰባት ከእነኦነግና ኦብነግ ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ያሉት ነገር ነው። እዚህ ላይ ተገቢና ትልቅ ነጥብ አንስተዋል። በቀጣይ በስፋት እመለስበታለሁ።

 

አክባሪዎ

 

ጋቹዬ

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!