የወያኔ ሳያንስ የነፃ አውጪዎቻችን (የግንቦት 7) የግፍ ተግባር እና የመገናኛ ብዙኀን ዝምታ
ያሬድ ኃይለማርያም ከብራስልስ

ከተወሰኑ ወራቶች በፊት "ወያኔ የሚፈጽማቸውን ስህተቶችና ወንጀሎች ሌሎች ሲፈጽሙት ትክክል ወይም ሕጋዊ ሊሆን አይችልም" በሚል ርዕስ አጠር ያለ ጽሑፍ ለአንባቢያን አቅርቤ ነበር። መልዕክቱም የኢትዮጵያን ሕዝብ የመከራ ዕድሜ እናሳጥራለን፣ ...

 

ከዛሬዎቹ ጨካኞችና አፋኞች እጅ ነጻ እናወጣለን ብለው፣ ምለው እና ተገዝተው እራሳቸውን በፖለቲካ ድርጅት ዙሪያ ያደራጁ ቡድኖች የአገርንና የሕዝብን ዘላቂ ጥቅም እና ደህንነት ሲጎዱም ሆነ አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራቶችን ሲፈጽሙ እያየን ዝም ልንላቸው አይገባም፤ 'ሳይቃጠል በቅጠል' እንዲሉ ዛሬ በእንጭጩ ከጥፋትና ከሕገ ወጥ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ሕዝብ ሊገስፃቸው ይገባል የሚል ነበር። በዚሁ ርዕስ ላይ በድጋሚ እንድመለስበት ያስገደደኝ ሰሞኑን በተከታታይ ከወደ ኤርትራ የሚሰማውና እጅግ አሳዛኝም አሳፋሪም የሆነው የኢትዮጵያዊያን እሮሮና ሰሚ ያጣው የድረሱልን ጥሪያቸው ነው።

ኢትዮጵያዊያን በየተሰደዱበት አገራት ከሰው ተራ ወጥተውና ተዋርደው የሚያሳልፉትን የስደት ሕይወት፣ የሚደርስባቸውን በደልና የሰብዓዊ መብት ረገጣ በተለይም ከሳውዲ፣ ከየመን፣ ከሱዳን፣ ከቤሩትና ሌሎች የአረብና አፍሪቃ አገራት ሆነው በየቀኑ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን የሚያሰሙትን የድረሱልን ድምጽ፣ የመንግሥት ያለህ፣ የወገን ያለህ፣ የፍትህ ያለህ እያሉ የሚያቀርቡትን ጥሪ እየሰማን ነው። ለእነዚህ ወገኖቻችን በቂ የሆነ ምላሽ ሳንሰጥ በጭንቀት በተዋጥንበት በዚህ ወቅት ለኢትዮጵያ ነፃነት እንታገላለን የሚሉ ባለ ነፍጥ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ከሆነው ሻዕቢያ ጋር በማበር በኤርትራ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ላይ ተመሳሳይ በደልን እያደረሱ መሆኑ ሲሰማ ከማሳዘኑም ባሻገር ግራ የሚያጋባ ሆኗል። የበለጠ ግራ የሚያገባውም በሳውዲ፣ በሱዳን፣ በሊቢያ፣ በየመንና ሌሎች አገሮች በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን እየተከታተሉ ይዘግቡ የነበሩ በውጭ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኀን ከወደ ኤርትራ ለሚሰማው የወገን ስቃይ 'ዓይናችንን ግንባር ያድርገው' በሚል ድምፃቸውን አለማሰማታቸው ነው። ለነገሩ ይህን የመገናኛ ብዙኀን ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሰብዓዊ መብቶች እና ለሕግ የበላይነት ያላቸውን የተዛባ ምልከታ በቅርቡ 'የግንቦት ሰባት ሁለገብ ጋዜጠኞች ክሽፈት' በሚል ርዕስ አንዳንድ ማጣቀሻዎችን በማንሳት ገልጬ ነበር።

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ዋናው ፍሬ ነገር የእነዚህን የመገናኛና ብዙኀን መድረኮችን ትኩረት ሊያገኝ ስላልቻለውና በኤርትራ ውስጥና ከኤርትራ መንግሥት ጥቃት ሸሽተው በሱዳን ስላሉት ወገኖች የድረሱልን ጥሪ ድምጽ ነው። በቅርቡ እራሱን ከግንቦት 7 ድርጅት በመነጠል 'የግንቦት 7 ዲሞክራቲክ' በሚል የተቋቋመው ቡድን በተከታታይ በድርጅቱ ድህረ-ገጽ (http://www.ginbot7d.org/) በድምጽና በምስል አስደግፎ ያወጣቸውን የተበዳዮች እሮሮ የሚመለከት ነው። ጉዳዩን በአጭሩ እንዲህ ነው። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ጊዜያት በዶ/ር ብርሃኑ እና በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሚመራው ግንቦት 7 የቀረበላቸውን የትግል ጥሪ በመቀበል እና በድርጅቱና በአመራሮቹ ላይም እምነት ያደረባቸውና አገራቸው ነፃ እንድትወጣ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ፣ ከተለያዩ የአፍሪቃ አገራትና ከአውሮፓ ተመልምለው በኢሳያስ አፎርቄ መንግሥት ትብብር ወደ ኤርትራ ከተወሰዱ በኋላ ለከፋ የሰብዓዊ መብት እረገጣ የተዳረጉ መሆኑን ተበዳዮቹ በአንደበታቸ የደረሰባቸውን ስቃይና እንግልት እያነቡ ገልጸዋል። እነኚህ ግለሰቦች ወደ ኤርትራ ከመጓዛቸው በፊት በግንቦት 7 አመራር አባላት ተደጋግሞ በኤርትራ ስላለው ሁኔታ እና ስለድርጅቱ አቋም ብዙ ነገር እንደተነገራቸው፤ ይሁንና የተነገራቸ ነገር ሁሉ ሥፍራው ላይ ሲደርሱ ሃሰት ሆኖ ማግኘታቸው፤ እንዲሁም የድርጅቱን ዝርክርክ አሰራርና ብልሹ አመራር አስመልክተው ጥያቄዎች በማንሳታቸው የተነሳ በግንቦት 7 አመራሮች ከተፈጸመባቸ በደል ባሻገር በቅጣት መልክ ተላልፈው ለኤርትራ የፀጥታ ኃይል መሰጠታቸውን ገልጸዋል። በኤርትራ መንግሥት ቁጥጥር ስር ሆነውም እጅግ ለከፋ የእስር ሁኔታ፣ ለድብደባና የማሰቃየት ተግባር፣ ለበሽታና ለርሃብ የተዳረጉ መሆኑን፤ እንዲሁም ከመካከላቸው የተገደሉ ሰዎች መኖራቸውን ነው ዝርዝር ማስረጃቾችን በመጥቀስ ገልጸዋል። በአሁን ወቅት በእስር ላይ ከሚገኙትም መካከል የአ.አ. ዩንቨርሲቲ ምሩቅ የሆነው አቶ ትእግስቱ ብርሃኑ እና አብረውት የሚገኙ ሌሎች እስረኞች በማናቸውም ጊዜ በኤርትራ መንግሥት ሊገደሉ እንደሚችሉ የወጡት ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

በግንቦት 7 እና በኤርትራ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጥቃት ሰለባ የሆኑት አብዛኛዎቹ ግለሰቦች በቅርቡ 'የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል' በሚል ለአንድ አመት ያህል በበርካታ ድረ-ገጾች፤ በተለይም የኢሳት ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ 'ሁለገብ' ጋዜጠኞች አማካኝነት በርካታ ፕሮግራሞችን እየተዘጋጁ ያስተዋውቁን የነበረው ቡድን አባላት ናቸው። እንደውም አንዳንዶቹ በነዚህ የመገናኛ ብዙኀን በስልክ እንዲቀርቡ እየተደረገ የወሬ ዘመቻውን ነጋሪት ጎሣሚዎች ነበሩ። ዛሬ እነዚህ ወገኖች ህይወታቸው በአደጋ ላይ ሲወድቅ እና 'የከፋ የመብት እረገጣ ተፈጽሞብናል፣ ተሰቃይተናል፣ ነፍሳችንን አድኑን፣ ግንቦት 7 ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመሆን የሚፈጽመውን ሕገ ወጥ ተግባራትና በገዛ አባላቱ ላይ የሚያደርሰውን አፈናና ወከባ ሕዝብ ይወቅልን፣ ሌሎች ወገኖቻችንም እውነተኛ ትግል ያለ መስሏቸው ተታለው ወደ ኤርትራ ምድር እንዳይሄዱና እኛን የገጠመን አይነት መከራ እንዳይደርስባቸው ታደጉዋቸው' በሚል ጥሪ ሲያቀርቡ የሰማቸ ያለ አይመስለኝም። እርግጥ ነው የግንቦት 7 ልሳን የሆነው 'ኢሳት' እንዲህ ያሉ የሕዝብ ብሶቶችን በካድሬ መነጽር ስለሆነ የሚመነዝረው ምንም እንኳን ጉዳዩ ኢትዮጵያዊያንን እና ኢትዮጵያን የሚመለከት ቢሆንም የግንቦት 7ን አካሄድ የሚያደናቀፍ ወይም የሚገታ መስሎ የታየውን ማንኛውንም ጉዳይ ለማስተናገድ ተፈጥሮው ስለማይፈቅድለት በድርጅት ልሳንነቱ ልንተወው እንችላለን። ይሁንና በውስጡ የሚሰሩት 'ጋዜጠኞች' ለእንዲህ አይነቱ ጉዳይ የሚራራ ልቦና እና እውነቱን ለሕዝብ እንዲታወቅ ለማድረግ የሚያስችል መንፈሳዊ ብርታት ማጣታቸው ግን ትንሽ ያስገርማል። ይህ አይነቱ ክሽፈት በኢሳትና በኢሳት ጋዜጠኞች ብቻ ሳይሆን በሌሎች በእዚሁ ሙያ የተሰማሩ የሕዝብ የመረጃ ምንጭ ለመሆን ለራሳቸው ቃል ገብተው የተለያዩ የመገናኛ መድረኮችን የተቆጣጠሩ ባለሙያዎች ተመሳሳይ ግርዶሽ ውስጥ መሆናቸው ከማስገረም አልፎ የሚያሳስብ ነው።

ግንቦት 7ን በተመለከተ እና በተለይም የድርጅቱ አመራ አባላት ከላይ የተጠቀሱትን ንጹሐን ዜጎችን 'በነፃነት ትግል' ስም ወደ ኤርትራ እየወሰዱ እያደረሱባቸው ስላለው በደል እና ግፍ ወደፊት በዝርዝር እመለስበታለሁ። በዝርዝር ስል የተበዳዮችን ማንነት፣ የደረሰባቸን የመብት እረገጣ፣ በማን እና እንዴት፣ የግንቦት 7 አመራሮች ያላቸውን ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ተሳትፎ፣ ስንት ሰዎች በእስር እንደተጉላሉ፣ ስንቶች ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ ስንቶች ከኬንያ ተመልምለው ወደ ኤርትራ ከተወሰዱ በኋላ ይህ ነው ያማይባል ስቃይና መከራ አይተው በድጋሚ ከኤርትራ ተወስደው በኡጋንዳና በኬንያ ከተሞች እንደተበተኑ እና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችን ወደፊት ሁኔታው እንዳመቸ ለሕዝብ ይፋ አደርጋለሁ። ለነገሩ ይህ አይነቱ በዜጎች ሕይወትና ተስፋ የመቀለዱ ተግባር የተጀመረው ዛሬ ሳይሆን ገና ግንቦት 7ን ለማቋቋም ሸርጉድ ከሚባልበት ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ ታሪኩ ብዙ ነው። የብዙ ወጣት ኢትዮጵያዊያኖችም ሕይወት በዚህ መያዣና መጨበጫ በሌለው የግንቦት 7 ቅዥት ተደናቅፏል፣ በርካቶችም ለወያኔ የደህንነት ኃይሎች ሲሳይ ሆነውና በሽብርተኝነት ተወንጅለው በሃሰት የበርካታ አመታት እሥራትን ተከናንበው በየማጎሪያ ቤቱ ፍዳቸውን እይቆጠሩ ይገኛሉ፤ ከታሳሪዎቹ መካከል የተወሰኑት ቤተሰቦቻቸውም ተበትነዋል።

እንግዲህ ነፃነትን የማያውቁት ገዢዎቻችን ብቻ ሳይሆኑ 'ነፃ አውጪዎቻችንም' ጭምር እንደሆኑ ልብ ልንል የገባል። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመጽሐፋቸው ርዕስ 'ነፃነትን የማያውቁ ነፃ አውጪዎች' በሚል የገለጹት የገዢው መንግሥት ባህሪ እርሳቸውንና ድርጅታቸውንም የተጠናወተው መሆኑ ልብ ሊሉ ይገባል። ለዚህም እርቀን መሄድ ሳያሻ በቅርቡ ከወደ አስመራ ብቅ ብለው የራሱን ሕዝብ በማፈን፣ በማሰቃየት፣ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን በማዋከብ፣ በመግደልና ለአመታት አስሮ በማሰቃየት፤ በጥቅሉ ሰብዓዊ መብቶችን በከፋ ሁኔታ በመጣስ አለም ያወቀውን አንባገነናዊ የአቶ ኢሳያስን አስተዳደር ሲያሞካሹና ዲሞክራት አድርገ ሲያቀርቡ ሰምተናል። ለዚህ ምስክርነታቸው ከበርካታ ኤርትራዊያን እና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ከቆሙ ኢትዮጵያዊያን በቂ ምላሽ ስለተሰጣቸው በዚህ ጉዳይ ብዙ ከማለት እቆጥባለው። ነገር ግን እሳቸውንም ሆነ ድርጅታቸውን ለማሳሰብ የምወደው የኤርትራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ባለው ግፍ እና መከር በዚ መልኩ መሳለቅ፤ እንዲሁም የአቶ ኢሳያስ መንግሥት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን ላይ እየፈጸመ ያለውን ደባና የመብት እረገጣ ችላ በማለት አብሮ መቆም ወደፊት በታሪክም ሆነ በሕግ እሳቸውን፣ ድርጅታቸውን እና የአመራር አባላቱን የሚያሰጠይቃቸው መሆኑን ነው። ለነገሩ ይህ ሂደት ባጭሩ ታሪክ እራሱን እየደገመ እንደሆነ ነው የሚያሳየው። የአንባገነኑን የደርግን ሥፍራ ወያኔ ከነ ጎሰኝነት መርዙ፣ የወያኔን በሻዕቢያ ጉያ ስር ተወሽቆ ኢትዮጵያን የማተራመሱን ተግባር የዛሬው ታጣቂ ግንቦት 7፣ ሻዕቢያ ያንኑ ቦታውን ሳይለቅ ገዢም፣ ነጻ አውጭም፣ ተባባሪው ሻዕቢያም አንድም ሦስትም ሆነው ቀጥለዋል። ሰብዓዊ መብቶችን፣ ዲሞክራሲን፣ ፍትሕንና የሕግ የበላይነትን በተመለከተ በነዚህ አካላት መካከል ምንም አይነት ልዩነት አይታይም። አንድ አይነት ባህሪይ ነው የሚታይባቸው። ልዩነታቸው የሚገኙበት ሥርፍራና ድርጅታው ተልኳቸው ነው። ተልኳቸም የሚያስፈጽሙበት መንገድ ግን ከሞላ ጎደል አንድ ነው።

ጽሑፌን በሦስት መልዕክቶች ላጠቃልል፦

• በውጭ የምትገኙ የመረጃ መድረኮች፣ ድረ-ገጾች፣ የዜና ማሰራጫ ጣቢያዎች (ኢሳትም ቢሆን)፣ የመገናኛ ብዙኀን (ጀርመን ድምጽና ቬኦኤንም ጨምሮ)፤ በእርግጥም ለሰብዓዊ መብቶች፣ ለፍትሕ እና ለዲሞክራሲ እኩል ከልባችሁ ትወግኑና ትቆሙ እንደሆነ እና ሙያዊ የሥነ-ምግባር ግዴታችሁ በአግባቡ ትወጡ እንደሆነ የኢትዮጵያዊያን (የሰው ልጆች በጠቅላላ ማለት ይቻላል) መብት በማንም ይሁን በየትም ሥፍራ ሲጣስ ድምጻችሁን በማሰማት ሕዝቡ ማወቅ የሚገባውን መረጃ አድርሱ። በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዙሪያ መደራደርም ሆነ የአንዱ ገበና እየከለሉ የሌላው እያሳጡ መቀጠል ሙያው የሚፈቅደው ተግባር አይመስለኝም። የተበዳዮችን ድምጽና የናተን ዘገባ ዛሬ የሚሰማ ሥልጣን ያለው አካል ባይኖር እና አፋጣኝ መፍትሔ ባይገኝም እንኳን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተግባሮች በወንጀልም ሊያስጠይቁ የሚችሉ ሰለሆነ ጊዜና ሁኔታዎች ሲፈቅዱ በደል አድራሾቹ ከፍርድ አደባባይ ይቆማሉ። የእናንተም ዘገባዎችና ማስረጃዎች በአስረጅነት ይጠቅማሉ።
• ለኢትዮጵያ ወጣቶች በሙሉ እርግጥ ነው ፍትሕና ነፃነት ዋጋ የሚያስከፍሉ ነገሮች ናቸው። በፍርሃት፣ በስደትና በሽሽት ነፃነት አትገኝም። ይሁንና እራስህን ነፃ ለማውጣት የምትመርጠውን መንገድ 'ሀ' ብለህ ከመጀመርህ በፊት አቅምህ የቻልውን ያህል የመንገድህን አዝላቂነት፣ ካሰብከውና ከተመኘኸው የነፃነት ድንበር ማድረስ አለማድረሱን በጽኑ መርምር። እንደኔ እንደኔ ከፍ ያለ መንፈሳዊ ወኔን የሚጠይቀውም ሆነ ከፍ ወዳላ የነጻነት ማማ የሚያዘልቀው ፍጹም ሰላማዊ የሆነው የፖለቲካ ትግል ነውና የአገርህን ድንበር ሳትለቅ በአገር ውስጥ ለፍትሕ፣ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ከሚታገሉት የፖለቲካ ኃይሎች ጎን በመቆም እራስህንም ሆነ አገርህን ከወያኔ አንባገነናዊ ሥርዓት መንጋጋ ለማውጣት ታገል። ለነጻነት ትግል ብለው ኤርትራና ሌሎች ጎረቤት አገሮች ገብተው የሥልጣን ጥመኝነትና ቂም ባረገዙ ቡድኖችና የኢትዮጵያ ጠላቶች ከሆኑት እንደ ሻዕቢያ ያሉ ኃይሎች መንጋጋ ውስጥ ገብተው በየሜዳው ከቀሩና ከስቃይ ተርፈው ምስክርነት እየሰጡ ካሉ ወንድምና እህቶችህ ተማር።
• የመጨረሻው መልዕክቴ በተለያዩ ጊዜያት በግንቦት 7ም ሆነ በሌሎች ድርጅቶች ጉትጎታ ኤርትራና ሌሎች ጎረቤት አገሮች በመሄድ በቀቢጠ ተስፋ በተደገሱ የነፃነት ትግል ድርጅቶች በደል የደረሰባችው፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባችሁ ወገኖች ሌሎች ወንድሞቻችሁ እና እህቶቻችሁ ከእናንተ እንዲማሩና በሰላማዊ ትግል ላይ ጊዜና ሕይወታቸን እንዲያጥፉ በአደባባይ ወጥታችሁ ምስክርነታሁን ስጡ።

እንግዲህ የወያኔ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና አፈና አንገፍግፎን እያሰማን ያለነው ጩኸት ሳያበቃ ዛሬ ደግሞ 'ነፃ አውጪዎቻችንንም' በዚሁ እረድፍ ተሰልፈው ስናይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደ ለመሆኑ አንድ ምልክት ሊሆነን ይችላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ አምባገነን ገዢም ሆነ የመብቱ እረጋጭችን በታሪኩ አጥቶ አያውቅምና ነገንም ልታጨልሙብን እንቅልፍ አጥታቸው ከሻዕቢያም ሆነ ከወያኔ የአፈና ልምድ እየቀሰማችሁ ያላቸሁ 'ነፃ አውጪዎቻችን' ከዚህ እኩይ ተግባራችው ትታቀቡ ዘንድ እንደ አንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እማፀናለሁ። የአለም መሳቂያም አታድርጉን። እንኳን ገዢዎቻቸው ነጻ አወጪዎቻቸውን መኑኑም ስያዙት አንባገነኖችና የሰብዓዊ መብት እረጋጮች ናቸው አታስብሉን። ምድራችሁም ሆነ የሕዝባቸው ባህል ዲሞክራሲ፣ የሕግ ለዕልና እና ፍትሕ የማያበቅል፣ ቢያበቅልም ፍሬ ሳያፈራ የሚያክስም በርሃ ነው ለሚለው የምዕራቡ ዓለም ትችት ማጠናከሪያ አትሁኑ።
'ሁሉም ሰብዓዊ መብቶች ለሁሉም'
በቸር እንሰንብት
ያሬድ ኃይለማርያም ከብራስልስ
ጥር 29 ቀን 2006 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!