ቴዎድሮስ ጌታቸው Tewodros Getachewቴዎድሮስ ጌታቸው (ከኦስሎ - ኖርዌይ)
በዓለም የወንዞች ታሪክ እንደ አባይ የተዘፈነለት፤ የተዘመረለት ወንዝ ያለ መቸም አይመስለኝም በዓለም በረዥምነቱ የሚስተካከለው የሌለው አባይ በትውልድ ሃገሩ ከዘፈን ግጥምና ከእንጉርጉሮ አድማቂነት ያለፈ ጥቅም ሳይሰጥ ለዘመናት ያለማቋረጥ መፍሰሱ እርግጥ ነው። ከወቀሳ እስከ ሙገሳ ከቁጭት እስከ ብስጭት ብዙ ብዙ ተብሎለታል ለአባይ ያልዘፈነ ዘፋኝ፣ ያልገጠመ ገጣሚ፣ ያልተቀኘ ባለቅኔ ማግኝት ይከብዳል፤ እናም አባይ ለቁጥር የሚታክቱ የሥነጥበብ ጉዳዮችን አስተናግዷል።

"አባይ ... አባይ ... አባይ ... አባይ
የአገር አድባር ያገር ኩራት ... የአገር ሲሳይ ..." ተብሎ ተዘምሮለታል።

"አባይ ስም ነው'ጂ ምን ሰርቷል ላገሩ
ትርፉ ለሌላ ነው ሄዶ መገበሩ ..." ተብሎም ተዚሞለታል።
ባለ ቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን እሳት ወይ አበባ በተሰኘው የግጥም መድብላቸው ስለ አባይ በፃፉት ስንኝ ደግሞ እንደዚህ ተቀኝለውታል፤
አባይ Abbay, Nile"... አባይ የምድረ ዓለም ሲሳይ
የቅድመ-ጠቢባን አዋይ
አባይ የጥቁር ዘር ብስራት
የኢትዮጵያ ደም የኩሽ እናት
የዓለም ሥልጣኔ ምስማክ
ከጣና በር እስከ ካርናክ
በእቅፍሽ ውስጥ እንዲላክ
መመለክ በመመስገን
ጽላትሽ ከዘመን ዘመን
በአዝዕርትሽ አበቅቴሽ ሲታጠን
አቤት አባይ ላንቺ መገን ...


አድርጎሽ ቅድመ ገናና
ዛሬ ወራቱ ራቀና
ምድረ-ዓለም ያንችን አድናቆት
ፈለጉን መሻት ተስኖት
እንዲህ ባንቺ መንከራተት
ታሪክ ወሮታሽ ጠፍቶበት
ትላንት በባዕድ ጩኸት
ዛሬም ባላዋቂ ኹከት
ቋንቋ ለቋንቋ ቢራራቅ
የቅድሚያሽ ንድፍ ላይፋቅ
እዚህ ደማም እዚያ ተማም
መባልሽ ብቻ ባይበቃም
የቅርስሽ ጭብጥ ይዞታ
ሆሄታሽ እስካልተፈታ ..."

እንደዚህና እንደዛ እየተባለለት በሀገሩ ከኪነጥበብ ፋይዳነት ብዙም ፈቀቅ ያላለ ጥቅም ሳይሰጥ የኖረው አባይ፤ ለባዕድ ሀገራት ግን የሕይወት ምንጫቸው በመሆን በሁሉም ረገድ ሲያገለግላቸው ከመኖሩ የተነሳ መነሻውም መድረሻውም የነሱና የነሱ ብቻ እስኪመስላቸው ድረስ በምድራቸው ያለማንም ከልካይ ለዘመናት ፈሷል።
አባይ Abbay, Nile

ከጥንታዊያን የኢትዮጵያ ነገሥታት ጀምሮ አባይን የመጠቀም ፍላጐትና ሙከራዎች ቢኖሩም የተሳኩ ግን አልነበሩም። ላለመሳካቱም በአብዛኛው የእነዚሁ የባዕዳን እጆች ትልቁን ሚና ይይዛል። ይሁንና ከውጪው ኃይሎች ተጽዕኖ በተጨማሪም ሀገሪቷ ከውስጥም ከውጪም በሚነሱ ያላቋረጡ ጦርነቶች መዘፈቋ ላለመሳካቱ በምክንያትነት ይነሳሉ።

በተለይም የቀዳማዊ ኃይለስላሴ መንግሥት አባይን ለመገደብ ሰፊ እቅድ ይዞ እቅስቃሴ ማድረጉን የሚገልጹ መረጃዎች በብዛት አሉ። እስከ አሁንም ድረስ የሚያገለግሉት ወንዙ በሚመለከት የተደረጉ ጥናቶች በዛን ዘመን የተደረጉ መሆኑ ይነገራል። ይሁንና በአባይ ወንዝ ዙሪያ እ.አ.አ. ከ1929 ጀምሮ የተለያዩ ስምምነቶችና ድርድሮች ሲካሄዱ ቢቆዩም፤ ሁሉም ስምምነቶችና ድርድሮች አብዛኛውን የውሃ መጠን የምታበረክተው ኢትዮጵያን ያላሳተፉና ከግምት ውስጥ ያላስገቡ ነበሩ። በዚህም ሰበብ ኢትዮጵያ አባይን ለመጠቀም በምትሞክርበት ወቅት ሁሌ ተቃውሞ ሲገጥማት ቆይቷል። ስለሆነም ቀደም ያሉ ስምምነቶች የግብጽ እና የሱዳንን ጥቅም የሚያረጋግጡ ሆነው በመቆየታቸው ኢትዮጵያ አባይን በእንጉርጉሮ ለመሸኘት ለዘመናት ተገዳለች።

በ1929 እና 1959 የተፈጠሩት የቅኝ ግዛት ስምምነቶች በመሆናቸው እንዲሁም የተፋሰሱ የላይኛው ሀገራትን ያገለሉ፤ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የሌላቸውና ሊኖራቸውም የማይችሉ በመሆናቸው በወቅቱ ከቀኝ ግዛት ነፃ የነበረችው ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ይህንኑ ጉዳይ ለማሳሰብ ሞክራለች። አፄ ኃይለስላሴ በ1957 ለሱዳንና ለግብፅ ይህንኑ በሚመለከት የፃፉት ደብዳቤ በተፋሰሱ የላይኛው ሀገራት ያለው ፖሊሲ ብቻችንን እንልማ የሚል ሳይሆን በአባይ አጠቃቀም ላይ ያላት አቋም "በጋራ እንጠቀም" የሚል እንደነበረ ተነግሮዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በወቅቱም የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ይጠቀምበት የነበረው የ50 ብር ኖት ላይ የነበረው ምስል የአባይ ግድብ ዲዛይን እንደሆነ በብዙዎች ይታመናል። ይኽም ወንዙን ለመገደብ በወቅቱ የነበረውን ትልቅ ፍላጎትና ሙከራዎች ያሳያል።

የወቅቱ የአባይ ወንዝ ግድብ ንድፍ በ1953 ዓ.ም በቀ.ኃ.ሥላሴ የ50 ብር ኖት ላይ
የወቅቱ የአባይ ወንዝ ግድብ ንድፍ በ1953 ዓ.ም በቀ.ኃ.ሥላሴ የ50 ብር ኖት ላይ

ይህንን የመሳሰሉ ጥረቶች በየግዜው በነበሩ መንግሥታት ቢደረጉም የተሳኩ ግን አልነበሩም። ከዛን ግዜም በኋላ ሀገሪቷ የነበረችበት ያላቋረጠ የእርስ በእርስ ጦርነት እና የገባችበት አስከፊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር አባይን ለመገደብ የማይቻል ብቻ ሳይሆን የማይታሰብ እንዲመስል አድርገውት ቆይተዋል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የተጀመረው የአባይ ግድብም ከመነሻው ትልቅ ውዝግብ ያስነሳ እና አሁንም እያስነሳ እንዳለ የታወቀ ነው። አባይ በመገደቡ ላይ ልዩነት ባይኖርም፤ ገዥው መንግሥት ግድቡን ለተለመደውና የፕሮፓጋንዳው ዘመቻ ፍጆታው ለማዋል መራወጡ ብዙኋኑን ያላስማማ ብቻ ሳይሆን፤ ለተቃውሞ ያነሳሳ ሆኗል። ኢትዮጵያውያንን በጠቅላላ ሊመለከትና ሊያገባ የሚገባው ፕሮጀክት እዳው የሁሉም ጥቅሙ የጥቂቶች መሆኑ ኢትዮጵያውያንን አንድ ከማድረግ ይልቅ ለመከፋፈል በቅቶአል።

በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የፓርቲና የመንግሥት ልዩነት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሥልጣን ላይ ቆይቶ እንኳን መለየት ያልቻለ ሲሆን፤ ሀገሪትዋ ውስጥ የሚካሄደው ጉዳዮች በጠቅላላ ለርካሽ የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ማዋሉና ለብሔራዊ መግባባት ምንም አይነት እድል ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ፤ ኢትዮጵያዊያን ከአገዛዙ ጋር ለመተባበር ያላቸውን ፍላጐት ያጠፋ ክስተት ሆናል።

በሀገሪቷ ሀብትና ንብረት የሚታቀዱና የሚሰሩ ሥራዎች የአገዛዙና የደጋፊዎቹ ግኝት ተደርገው መወሰዳቸው ሀገር ውስጥ የተንሰራፋው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፤ በየእስር ቤቱ ታጉረው ያሉት ዜጎች ጋዜጠኞችና፤ ፖለቲከኞች እንዲሁም አገዛዙ የሚከተለው የከፋፍለህ ግዛው ውጤቶች የሆኑት በብሔሮችና በኃይማኖት ዙሪያ የተፈጠሩ ውጥረቶችና ልዩነቶች፤ ስር የሰደደውን የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር እጦት፤ ከተቃዋሚው ኃይል ጋር በመግባባትና በመቻቻል ችግሮችን ለመፍታት ምንም አይነት ፍላጐት አለመኖር፤ ዜጐች ተገደው እና ፈርተው ካልሆነ በፍቃደኝነት ከአገዛዙ ጋር ለመተባበር እንደማይፈልጉ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

በአንጻሩ የግብፅ መንግሥት በአባይ ጉዳይ ላይ ከተቃዋሚዎቹ ጋር ተሰብስቦ በየግዜው በመወያየት በሀገራቸው ጉዳይ ሁሉም ግብፃዊያን እኩል የሚያገባቸውና የሚመለከታቸው መሆናቸውን አሳይቷል። በርግጥ ይሄ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው አገዛዝ ትልቅ ትምህርት ሊሆን ይገባ ነበር። የሆነው ሆኖ በአንድ ሀገር ጉዳይ ላይ አንዱ ብቻ አዛዥና ናዛዥ ሆኖ እስከ መጨረሻው መቀጠል እንደማይቻል የሩቁ ብቻ ሳይሆን በጣም የቅርብ ታሪኮች ደግመው ደጋግመው አሳይተዋል። ለማንኛውም ግብፃውያንን አንድ ያደረገው የአባይ ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው አገዛዝ በሚያሳየው ግብዝነት የልዩነት ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል። ለዚህም ማሳያው በየውጪ ሀገራቱ ለአባይ ግድብ ቦንድ ማሰባሰቢያ የተካሄዱት ዝግጅቶች አንዳቸውም እንኳን አለመሳካታቸው በቂ ማሳያ ነው። ለዚህ ደግሞ አገዛዙ ተጠያቂ መሆኑ እርግጥ ነው።

አባይ የሚገነባው በኢትዮጵያውያን ገንዘብ፣ ጉልበትና ሀብት ነው፤ በተጨማሪም በኢትዮጵያውያን ስም በሚበደሩት ገንዘብ ነው። ስለዚህ ጉዳዩ የህዝብ በመሆኑም የአገዛዙና የደጋፊዎቹ የግል ጉዳይ መሆኑ አብቅቶ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በሂደቱ መሳተፍ ይኖርባቸዋል።

ከዚህ በተረፈ አባይን ለመገደብ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው መንግሥት እግረ መንገዱንም የሰብዓዊ መብት ጥሰትንም፤ ሞልቶ የፈሰሰውን የህዝብ ብሶት አብሮ መገደብ ይኖርበታል። አገዛዙ በግለሰብ ነፃነት፤ በኃይማኖት ጉዳዮች ውስጥ፤ ሃሳብን በመግለጽና፤ በመምረጥና መመረጥ መብት ውስጥ ጣልቃ ገብቶ የሚያደናቅፈውን ሕገወጥ ተግባራት አብሮ ለመገደብ መነሳት ይገባዋል። ኢትዮጵያ ሊገደቡ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች የታጨቁባት ሀገር ነች። ስደትና የስደት መንስኤዎቹ ሊገደቡ ግድ ይላል። የኑሮ ውድነቱ፤ ዘረኝነትና ሙስናው ሊገደብ ይገባዋል። ቦንድ የማያስፈልጋቸው የቻይና ብድር የግብፅ እሰጥ አገባ የማይኖራቸው ብዙ ግድቦች ያስፈልጋሉ። ያለበለዚያ አባይ ቢገደብ ለብቻው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ እንዲሁም መፍቻና መፍትሄ ባለመሆኑ አገዛዙ የፕሮፓጋንዳ እረፍት አድርጐ ወደራሱ ቢመለከት ለሁሉም ይበጃል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ፀሐፊውን ለማግኘት፣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!