የኢትዮጵያዊው ኦባማ ውልደት!!

አፍቃሬ - ኦባንግና ልጅ ተክሌ ከካናዳ

የ2009 ቋንቋችን “ኦባንግ በዲ.ሲ. ለኢትዮጵያ ያሰልፈናል” ቢሆንስ። ኦባንግ ጥቁሩ አይደለም። ኦባንግ አኝዋኩ አይደለም። ኦባንግ ወጣቱ አይደለም። ኦባንግ የኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ቁስላትና ህማማት ሊሸከም የተዘጋጀው ኦባንግ ሜቶ። ዋናው ጠላት፣ ዋናው ጅብ ኢህአዴግ ስጋችንን እየበላን፤ እርስ በርስ የምንሻኮትባትን ሳይሆን፤ ቅድሚያ ለጋራ ጠላት የምንሰጥባትን የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ያነገበውን ኦባንግን ልንከተለው ይገባል።

 

ከዚህ በፊት፤ ከዚህም አስቀድመን

 

ከዚህ በፊት እንዲህ ብለን ጽፈናል። “በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ምናልባትም የመሀል አገርና የደጋው አገር ሰዎች ያጣመምነውን፣ የደፈጠጥነውን፣ ያበሻቀጥነውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲያክም ተስፋ ከምንጥልባቸውና ከምናጫቸው ጥቂት አትዮጵያዊያን መካከል አንዱ ነው። የኛ ንትርክና ሽኩቻ አያሰለቸውም። ተስፋም አያስቆርጠውም። ነጋ ጠባ ይጽፋል። መሸ ነጋ ይናገራል። የሚሰብከውን ይኖራል። የሚኖረውንም ይሰብካል።” ይሄንን ጽፈን ነበር።

 

እነሆ ከዚህ ቀደም ድርሻዬን ልወጣ ብሎ የኢትዮጵያን መስቀል ተሸክሞ ወደ ዋሽንግተን ሲጓዝ ያገኘነው ኦባንግ ሜቶ፤ ኦባንግ መቶ፤ ሕዝበ-ኢትዮጵያን ይዞ ሊሰለፍ እየተጋ ነው። “የመቶ ሺህ ኢትዮጵያዊያን ሰልፍ በዋሽንግተን ዲ.ሲ.”። በዲያብሎስ ላይ እንደተሰለፉት እልፍ አእላፍ መላእክት መሆኑ ነው። በጥይት የሚበተነውን የህዝባችንን ሰለፍ፤ በጥይት መበተን ከሌለበት አገር በነጻነትና በድሎት የምንኖር ኢትዮጵያዊያን እንሰለፍ ነው የሚለው። በዚህ ስርአት የተከፋ፤ የተከፋም ብቻ አይደለም ጆሮ ያለውም ጭምር ኦባንግን ይስማ። መስማት ኦባንግን ነው። እንደ ኦባማ ያለ አሜሪካዊ አሜሪካንን ካሻገረ፤ እንደ ኦባንግ ያለ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያን ሊቤዥ ይገባል ማለት ነው። አሁንም ከዚህ ቀደም ከጻፍነው እንጥቀስ።

 

“በዚህ ስርአት፡ ኦነግም ተከፍቷል፤ ኦባንግም ተበድሏል፤ ኦብነግም ተገፍቷል፤ አማራው ተቃጥሏል፤ ኦጋዴንም ተደብድቧል፡ ኦሮሞውም ተሰዷል፣ ተማሪ ተገርፏል፣ ወጣት ተረሽኗል፣ ኢንጂነርም ታስረዋል፣ ብርሀኑም ተሰቃይቷል። ኤርትራም ሄዳለች። ዝርዝሩ አያበቃም። የሆነው ሁሉ ሆኖ ግን ከዚያም ባሻገር እንድንሄድ ለመነን ኦባንግ። የማያንቀላፋው ኦባንግ። ኦባንግ እንዲህ አለን “ማንም ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖረ፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነጻ ካልወጣ በስተቀር፡ ነጻ ነኝ ቢል ሀሰት ነው።” ነጻነታችንም ባርነታችንም አንድ ላይ ነው ማለቱ ነው።

 

የኦባንግ መፈክር ይመቸኛል። ሰብአዊ ብሄርተኝነት !! ኦባንግ እንዲህም አለን፤ “ከዘራችን ይልቅ፣ ከብሄራችን በፊት፣ ከጎሳችን አስቀድሞ፣ ሰብአዊነታችንን እናስቀድም።” ትክክል ነው። ከኢትዮጵያዊነታችን፣ ከአፍሪካዊነታችን፣ ከአሜሪካዊነታችን፣ ከክርስትናችን፣ ከእስልምናችንም፣ ከአኙዋክነታችንም ጭምር በፊት ሰውነታችን ይቀድማልና ሰውነታችንን እናስቀድም ማለቱ ነው። የሚቃወም አለ? የሚቃወም ካለ የመረጠውን ይሁን። ለኦባንግ የምንሆነውን መምረጥ መቻል ራሱ ሰውነት ነው። የኦሮሞ ብሄርተኛ፣ የትግሬ ብሄርተኛ፣ የአማራም ብሄርተኛ፣ የጉራጌም ብሄርተኛ ይምጣ። ግን ነገዳዊ ብሄርተኛነታችን “በሰብአዊ ብሄርተኛነት” ይጠቅለል አለ።

 

ሰውነት፡ ሰው፡ የድርጅቶች ሁሉ ቁንጮ፤ ሰው

 

ከዚያ ወደ መጨረሻ ላይ ይሄንን አለን ኦባንግ፡ “ማናቸውም በማናቸውም መንገድ ኢህአዴግን ሊዋጉ የተነሱ ሀይሎች ሁሉ እርስ በርሳቸው መዋጋታቸውን ካላቆሙ ኢህአዴግን መዋጋተቸው መና ይቀራል።” ኢህአዴግ እድሜ ልክ ይነግስብናል። ይፈነጭብናል። እነዚህን መፈክሮች ሰንቆ ነው ኦባንግ ዲሲ ላይ ድርሻውን ሊወጣ ከትሞ የነበረው። ቡሽ አልሰማውም። ቡሽ ይቅር፤ እኛም የተፈለገውን ያህል አላደመጥነውም። ገሸሽ አደረግነው። አልከፋውም። ከበደል ጋር ነው እልህ የገባውና አሁንም እኛን ለኛ ጉዳይ እንድንሰለፍ ፈለገን።

 

የሚሰብከውን የሚኖር ታጋይ፤ ድርሻችንን እንወጣ አለ። ድርሻውን እየተወጣ። ድርሻችን ደግሞ ብዙና ከባድ አይደለም። ሌላው ሁሉ ቢቀር ከጎሳችን በፊት ሰውነታችንን ማስቀደም፤ ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነጻ እንደማይወጣ እንረዳ አለ። ከዚያ ርስ በርስ መቋሰላችንን ማቆም እንዴት ይሳነናል? የምንሳሳለትን ገንዘብ፤ ግድ የለም እንቋጥር። የምንቋምጥለትን ስልጣን ግድ የለም እንሟሟትለት። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ሰው መሆናችንን እናስቀድም። ኦሮሞ አትሁኑ አላለም ኦባንግ። አማራነትም አይከጅላችሁ አላለም። ወይም ወሎዬነት አይሞክራችሁ አላለም። ከዚያ ሁሉ በፊት ግን ሰው መሆናቸንን እናስቀድም። ሰውነታችንን ዘለን ሌላ መሆናችን ላይ ካተኮርን ግን ነገር ይበላሻል ነው የሚለን። ሰውነታችንን አስትቶ ብሄራችንን ካስቀደመብን ስርአት የገጠምነውን ትንቅንቅ በድል ለማጠናቀቅ መጀመሪያ ከምንም በፊት በሰውነታችን መደራጀት አለብን። ከግንቦት ሰባት፣ ከኦነግ፣ ከኦብነግ፣ ከቅንጅት፣ ከኢዴፓ፣ ከኢህአዴግ ከምንም በፊት ቀዳሚው ድርጅታችን “ሰውነት” ነው።

 

ለዚህ ነው ኦባንግን “ከብሄርህ ከብሄሬ አስቀድመህ ሰው ስላደረግከኝ ሰው ይውጣልህ። ሰውም ይብዛልህ።” ያልኩት። እነሆ ኦባንግ የሰው ያለህ ይላል። የራሳችንን ኦባማ መውለድ ካልቻልን ምን ቀኑን ሙሉ ቲቪ ላይ ብናፈጥ፤ የቲሸርት መአት ተሸክመን ብንሄድ፤ የዩቱብ ተራራ ብንሰራለት፤ ቀኑን ሙሉ ስንቀድለት ብንውል ከኦባማ ጠብ የሚል ነገር የለም። ኦባማ የነሱ እንጂ የኛ አይደለም። የራሳችንን ኦባማ የመውለድ ግዜ አሁን ነው። ልክ እንደ መዳን ግዜ። የኛ እጩ ኦባማ ደግሞ ከበር ቆሞ ከተራራው ወጥቶ ይጣራል። ኦባንግ ሜቶ።

 

ለተገፉት ካልጮህን፡ ለሞቱት ካልተሰለፍን

 

ሲጀምርም በዚያ ምክንያት ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን አኝዋኮች በኢህአዴግ ወታደሮች ተሰየፉ። ረገፉ። አለቀሰ። አዘነም። ሰልፍም ወጣ። በአኝዋክ አልተወሰነም። ከምርጫ 2005 እስከ ኦጋዴን ጭፍጨፋ፤ ከቴዲ አፍሮ እስራት እስከ ብርቱካን ስቃይ፤ ከኦሮሞዎች አፈና እስከ … አላባራም። ድንበር ተቆረሰ ኦባንግ እዚያ ነው። ለሀይሉ አልቆመም፣ ለብርሀኑም አልሰገደም። ለኢትዮጵያ እንጂ። ኦባንግ ለኔ ሀሳብና ታሪክ፣ ሽግግርና ዘመንን፣ መጪውንና ያለፈውን የሚወክል ምስል ነው። ኦባንግ የተገፉትንና የሚከሰሱትን እንደሱ የጠቆሩትንና እንደኛ የጠየምነውን የሚያስታርቅ ምስል ነው። ኦባማም ከዚያ የላቀ ምንም አላደረገም። ኦባንግ የሁሉም ቁስል የሚሰማው፡ አስታራቂ ሰው ነው። በኦሮሞ ተገንጣዮችና በአማራ ብሄርተኞች፤ በኦጋዴን ነጻ አውጪዎችና በአኝዋክ ምስኪኖች መካከል የቆመ ሰውን በብሄሩና በመልኩ ሳይሆን በሰውነቱና በምግባሩ የሚመዝን ሚዛናዊ ሰው ነው። ልንከተለው ይገባል።

 

የጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሀይሎች አባላትን እያበሰለና እያነቃ በእውቀትና በአገር ፍቅር እያጠመቀ የሚሄድ አጋዥ ድርጅት እንጂ እንደ ጠላት ሊታይ የማይገባው ድርጅት ነው። “መጪው 2009 ዓ.ም. ለኢትዮጵያዊያን ከአምባገነኖች የሚገላገሉበት የኢትዮጵያዊያን አመት ይሆን” ወይስ ልክ እናዳለፉት አስራምናምን አመታት ለኢህአዴግ ይሆን ብሎ ጠየቀ፤ ኦባንግ በቅርቡ በጋራ ንቅናቄ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ስም በወጣው የትንቢትና የተግሳጽ ድርሳን ላይ። ከአሜሪካው ህግ አውጪና የኢትዮጵያዊያን ሰብአዊ መብት ጉዳይ አጋርም ጠቀሰ። ህግ አውጪው ክሪስ ስሚዝ እንዲህ አለ፤ “ሰብአዊ መብት ለብቻ የሚጋፈጡት ፈተና አይደለም። የሁሉንም ህዝቦች አጋርነት ይጠይቃል። ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ቆመው በሁላቸውም ላይ የተቃጣውን የሰብአዊ መብት ገፈፋ ሊጋፈጡት ይገባል። ኢትዮጵያዊያን አሁን ካላቸው መንግስት በብዙ እጥፍ የተሻለ ይገባቸዋል። ግን ኢትዮጵያዊያን ባንድ ድምጽ ሊናገሩ ይገባል። ያኔ ነው እኛም ልንረዳቸው የምንችለው።” ይገርማል። አሜሪካዊው ክሪስ ስሚዝም ገብቶታል፡ የኛ ነገር። የባቢሎንን ህዝብ ሆናችኋል አይነት ነገር ነው። አሜሪካ ከኦባማ የተሻለ ነጻ አውጪና አዳኝ ካላገኘች፤ ኢትዮጵያም ከኦባንግ የተሻለ ሰብሳቢና ፊታውራሪ ልታገኝ አትችልም።

 

የ2009 ቋንቋችን “ኦባንግ በዲ.ሲ. ለኢትዮጵያ ያሰልፈናል” ቢሆንስ። ኦባንግ ጥቁሩ አይደለም። ኦባንግ አኝዋኩ አይደለም። ኦባንግ ወጣቱ አይደለም። ኦባንግ የኢትዮጵያዊያንን ሁሉ ቁስላትና ህማማት ሊሸከም የተዘጋጀው ኦባንግ ሜቶ። ዋናው ጠላት፣ ዋናው ጅብ ኢህአዴግ ስጋችንን እየበላን፤ እርስ በርስ የምንሻኮትባትን ሳይሆን፤ ቅድሚያ ለጋራ ጠላት የምንሰጥባትን የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ያነገበውን ኦባንግን ልንከተለው ይገባል። ኦባንግ በዚህ ዓመት አጋማሽ፤ በመጪው መስከረም መቶ ሺህ ኢትዮጵያዊያንን በአሜሪካን ዋና ከተማ፤ በዋሽንግተን ዲ.ሲ. ሊያሰልፍ ይለፋል። ብንሰለፍ እናተርፋለን። ባንሰለፍ ግን ኦባንግ አይጎዳም። እኛም አንጎዳ ይሆናል። እነዚያ የኛን ሰልፍ፣ የኛን ጡጫ በጠላት ላይ አርፎ ማየት የሚሹ ወገኖቻችን ግን መከራቸው አንድ ተጨማሪ ዘመን ይኖራል። ተጻፈ፡ ብርቱ ካህናችን በታሰረች፡ በ30ኛው ቀን።

  

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!