ግርማ ካሣ - ቺካጎ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) ጁላይ 24, 2008

“እንደ ወንድማማቾች አብረን በሠላም መኖር መልመድ አለብን። አለበለዚያ ሁላችንም እንጠፋለን።” ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ

በቅርቡ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የተቃጠሉና በሳተላይት የተነሱ በርካታ መንደሮችን ተመልክቻለሁ። የአራት ኪሎ ባለሥልጣናት ”እኛ የለንበትም” ብለው አስተባብለዋል። የኦጋዴን ነፃነት ግንባር በበኩሉ ገዢ ፓርቲውን ይከሳል። ማን ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል አብዛኞቻችን የራሳችን ግምት ይኖረናል ብዬ አስባለሁ።

 

ስለዚህ አሁን እዚህ ላይ ብዙም ማተኮር ባልፈልግም፣ አንድ ነገር ግን ማንም የማይክደው ሐቅ አለ። መንደሮች በግፍ ተቃጥለው። ኢትዮጵያውያን ሕፃናት፣ አረጋውያን ከቀያቸው ተሰደዋል። በርካቶችም በኢትዮጵያውያን እጅ ተገድለዋል።

 

ይህ በኦጋዴን የተፈጸመው እልቂትና ጭፍጨፋ የመጀመሪያው አይደለም። ባለፉት 30 ዓመታት በአሶሳ፣ በበደኖ፣ በሃውዜን፣ በአርባ ጉጉ፣ በጋምቤላ፣ … በርካታ ኢትዮጵያውያን አልቀዋል። ይህ የሚያሳየው የሀገራችን ችግር አሁን ካለው አገዛዝ ያለፈ እንደሆነ ነው። የሀገራችን ችግር ስር የሰደደና መፍትሔው የተወሳሰበ፣ የአስተሳሰብና መንፈሣዊ ችግር ነው።

 

ልዩነቶቻችንን በጠመንጃ የመፍታት ባህል እጅግ በጣም አቆርቁዞናል።

“ምን አይነት ሰይጣን ቢቆጣጠረን ነው ይሄን ያህል እንደ አውሬ የምንተላለቀው?” እያልኩኝ ብዙ ጊዜ አስባለሁ። በቅርቡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በዋሽንግተን ዲሲ ያደረጉትን ንግግር ሲከፍቱ” ኢትዮጵያ ተቸግራለች። እኛም ተቸግረናል። እርስ በርስ እንድንፋቀር ልቦናችንን ክፈት” ብለው ፀሎት ሲያደርጉ በእንባ ድምጼን ከፍ አድርጌ ነበር “አሜን!” ያልኩት።

 

እስቲ አስቡት ስንቱ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያውያን እጅ እንደተገደለ? በኢሕአፓ፣ በሻዕቢያ፣ በጀብሃ፣ በመኢሶን፣ በሜጫና ቱለማ፣ በህወሓት፣ በኢዲዩ፣ በኦጋዴን ነፃነት ግንባር … እንዲሁም በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ አባል የነበሩ፣ የኢትዮጵያ ወታደር ሆነው ያገለገሉ … ስንቶቹ ናቸው ከኢትዮጵያውያን እጅ በተተኮሰ ጥይት የወደቁት?

 

“አኬልዳማ አኬልዳማ የደም መሬት፤

እግዚአብሔር ያስብሽ በምህረት

አኬልዳማ አኬልዳማ የደም ምድር

እግዚአብሔር ያስብሽ በርሱ ፍቅር”

 

ብሎ መጋቢ ታምራት ኃይሌ እንደዘመረው ኢትዮጵያ “አኬልዳማ” ተብላ መጠራቷ ጭራሽ አያስገርምም። በኢትዮጵያ ምድር በየገጠሩና በየከተማው ደም እንደ ጎርፍ ፈሷል። አሁንም እየፈሰሰ ነው።

 

በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወገኖቻችን በጎና የከበረ ዓላማ ኖሯቸው ለሀገራቸው ትልቅ መስዋዕትነት ከፍለው፣ ዓላማቸውን ከግብ ሳያደርሱ አልፈዋል። ዓላማቸውን ከግብ ያላደረሱበትም አንዱ ምክንያት ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ የተጠቀሙበት የትግል ዘይቤ (የትጥቅ ትግል) ጠቃሚ ዘይቤ ስላልነበረ ነው። ለምሳሌ በቀይ ሽብር ወቅት የትጥቁ ትግል በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ጾታ፣ ኃይማኖትና ዘር ሳይለይ ሲፈጅ፣ ጠመንጃ ምንጊዜም ለጨካኞችና ለገዳዮች የሚመች ስለሆነ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያምና ጓዶቹ ከዚያ ሁሉ እሳት ውስጥ አይለው ብቅ አሉ።

 

ታዋቂው የኪነት ሰው ቴዎድሮስ ካሳሁን እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ያህል በሚወሰደው፣ “ያስተሰርያል” በሚባለው ዜማው የጠቀሳቸው አንዳንድ ቃላትን ማንሳት እፈልጋለሁኝ።

 

“አቤት ስቃይ አቤት ጠኔ

ሰማይ ጨክኖ በወገኔ

ስንቱን አሳልፈናል አልቅሰን ሳናባራ ብለን “ወይኔ”

እዚህ ጋር ደግም ሌላ ትኩሳት

ወገኔ አለቀ በውስጥ እሳት

ኧረ አይበቃም ወይ ኧረ አይበቃም ወይ”

 

እያለ ነበር ያቀነቀነው። “ጦርነቱ፣ ደም መፋሰሱ፣ ለቅሶና ሰቆቃው አይበቃም ወይ?” ነው የሚለን ይኼ ወጣት።

 

ኢትዮጵያውያን በጣሊያኖች እጅ ከተገደሉት ይበልጥ እርስ በርስ የተገዳደልነው ይበልጣል። በውስጣችን የሞላው የእልህ፣ የጥላቻ፣ የቂም በቀልና የትዕቢት መንፈስ እረመጥ ውስጥ ከቶናል።

 

ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን ካለመስማማታችን የተነሳ የዓለም መሳቂያ ሆነናል፤ ተዋርደናል።

በቅርቡ በሰፊው እንደተዘገበው ኢትዮጵያ ከሰባት መቶ ሰማኒያ ሚሊዮን ዶላር በላይ ከሌሎች ሀገራት እርዳታ አግኝታለች።1 የምናያቸው ፎቅች፣ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶች ወዘተ በእኛ ገንዘብ የሠራናቸው ሳይሆኑ ፈረንጆች በሰጡን ገንዘብ የተሠሩ ናቸው። ታዲያ ጣሊያን ከሰባ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን ወሮ በነበረ ጊዜ ከገነባቸው መንገዶችና ድልድዮች አሁን የሚደረጉት ልማቶች በምን ይለያሉ? አላወቅነውም እንጂ ያኔ ጣሊያን ኢትዮጵያን ይገዛ እንደነበረው አሁንም ተረግጠን በውጭ ሀገር ዜጎች እየተገዛን ነው።

 

በቅርቡ በተለያዩ ድረ ገጾች እንደሰማነው ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ወገናችን የሚበላው ዳቦ ያስፈልገዋል። በአጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ ዳቦና ሩዝ እንለምን ነበር። በደርግ ጊዜ ዳቦና ሩዝ መለመናችንን አላቆምንም ነበር። አሁንም ዳቦና ሩዝ እየለመንን ነው። የፈረንጆችን ኮቴ እንደ “ውሻ” እየተከታተልን ፍርፋሪ መልቀም ሆኗል ሥራችን።

 

ጀግናው የተንቤኑ ራስ አሉላ አባነጋ “የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ቀይ ባህር ነው። እንኳን መሬቷ አፈሯ አይነካም” ሲሉ ፈረንጆች ጫማቸውን አራግፈው እንዲሄዱ ያደርጉ እንደነበረ በልጅነቴ ተምሪያለሁ። በአድዋና በአዱሊስ ጣሊያኖችን፣ በአፋር ቱርኮችን፣ በጉራና በጉንድተ (ኤርትራ ውስጥ) ግብጾችን፣ በመተማ ደርቡሾችን፣ በሐርርጌ ተስፋፊው የዚያድ ባሬን ጦር በሀገራችን ላይ እንዲሰለጥኑ “አንፈቅድም” ብለን በጀግንነት መክተን መልሰን ነበር። ነገር ግን አሁን ተራ ነገር ይመስል የሀገራችን ለምለም መሬት ለጎሮቤት ሀገር እንሰጣለን። በደም የራሰው የሀገራችንም አፈር ኪሎ ሜትሮችን እያቋረጠ የግብጽ ምድርንም ያለመልማል። (ኢትዮጵያ እየወደቀች ግብጽና ሱዳን እያለፈላቸው ነው ማለት ነው)

 

እንግዲህ ተመልከቱ ወገኖቼ ምን ያህል እንደተዋረድን! ተመልከቱ ምን ያህል እንደወደቅን! ይሄ ሁሉ እግዚአብሔር ያመጣብን መርገም ሳይሆን፤ እኛው እራሳችን በራሳችን ላይ ያመጣነው መርገም ነው።

 

ሀገራችን ኢትዮጵያን ማንሳት እንችላለን።

አሜሪካኖች አገራቸውን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማሻገር “እንችላለን” እያሉ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። እኛም ከእነርሱ መማር አለብን። “በኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔ እስካለ ድረስ በሠላም ለውጥ ማምጣት አይቻልም። ሀገራችን ተረግማለች። ተስፋ የላትም“ እያልን የሽንፈትና የስንፍና ንግግር ከመካከላችን ማስወገድ አለብን። “ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” እንደተባለው ደም ሳይፈስ ሀገራችንን ማንሳት እንችላለን።

 

በቀዩና በነጩ ሽብር የረገፉትን፣ በአዲስ አበባ በታጠቁ የደህንነት አባላት በቅርብ ርቀት የተገደሉትን እነ ሽብሬ ደሳለኝን እንዲሁም በጋምቤላ፣ በበደኖ፣ በሃውዜን፣ በአርባ ጉጉ፣ በአዘዞ፣ በአሶሳ፣ በናቅፋ፣ በደጋ ሃቡር፣ በአምቦና በተለያዩ የሀገራችን ግዛት … በኢትዮጵያውያን እጅ የተገደሉትን በመቶ ሺህ የሚቀጠሩ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እናስታውሳቸው። በተለያዩ ገጽታዎች የከፈሉትንም መስዋዕትነት፣ “ከአሁን በኋላ ሌላ ኢትዮጵያዊ አንገድልም” የሚል የጸና ቃል ኪዳን በመግባት እንዘክረው።

 

እነዚህ የወደቁት ወገኖቻችን፣ የተበታተነው አጥንቶቻቸው እንደገና ቢገጣጠሙ፣ የበሰበሰው ስጋቸው መልሶ አጥንታቸውን ቢያለብሰው፣ ሰውነታቸው ሙቀት ቢያገኝና ከናፍርቶቻቸው እንደገና መናገር ቢጀምሩ፤ ”እባካችሁ ሰዎች ሁኑ! እርስ በርስ መገዳደል አቁም! ችግራችሁን በውይይት ፍቱ! ጠመንጃውንና ሰይፉን አስቀምጡና ሀገር ለመገንባት ሞፈርና ቀንበር መዶሻና ማጭድ አንሱ!” ነበር የሚሉን።

 

እስከመቼ ሀገር እያለን እንሰደዳለን? እስከ መቼ ልብስ እያለን እንታረዛለን? እስከመቼ ክብር እያለን እንዋረዳለን? እስከ መቼ ምግብ እያለን እንራባለን? እስከ መቼ ወገን እያለን በብቸኝነት እንኖራለን? እስከ መቼ መስጠት ስንችል ለማኝነት ሥራችን ይሆናል? እስከ መቼ በሩጫና በረሃብ ብቻ እንታወቃለን?

 

እንግዲህ ጊዜው አሁን ነው። አስተሳሰባችንን የምንቀይርበት፣ በመንፈስ የምንታደስበት፣ ከራስ ወዳድነትና ከግድየለሽነት የምንላቀቅበት ጊዜው አሁን ነው። አምባገነንነትን፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣን፣ ዘረኝነትን፣ መከፋፈልን፣ ልዩነታችንን በጠመንጃ የመፍታት ባህልን፣ የሸፍጥና የውሸት ፖለቲካን፣ በገንዘብና በጥቅም ተገዝቶ የመሰሪ ስርዓት ተባባሪ መሆንን “እምቢ” የምንልበት ጊዜው አሁን ነው። ኢትዮጵያን የምናድንበት ጊዜው አሁን ነው።

 

የታጠቁ ኃይላት ከጫካ መጥተው እንዲያድኑንና መብታችንን እንዲይስከብሩልን መጠበቅ የለብንም። ለኢትዮጵያ መድኃኒትና በረከት እንድንሆን የምንፈለገው እኛው ኢትዮጵያውያን እራሳችን ነን። ኢትዮጵያ በእኛ እጅ ላይ ነው ያለችው። የኢትዮጵያ ዕድል የሚወሰነው በእኛው በኢትዮጵያውያን ብቻ ነው።

 

ታዲያ ኢትዮጵያን እንዴት እናድናታለን?

“እንዴት ነው ኢትዮጵያን የምናድነው?” የሚል አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ኢትዮጵያ ማለት ድንጋዩና አፈሩ አይደለም። ኢትዮጵያ ማለት እኛ ነን። ኢትዮጵያን ማዳን የሚጀመረው ከእኛው ነው። እያንዳንዳችን በግላችን እራሳችንን ማዳን፣ መብታችንን መጠየቅና የፍርሃትን ነገር ከውስጣችን ማውጣት ስንጀመር ያኔ ኢትዮጵያ መዳን ትጀምራለች። እኛ የአስተሳሰብና የመንፈስ ተሃድሶ ማድረግ ስንጀመር ያኔ ኢትዮጵያ መታደስ ትጀምራለች። እያንዳንዳችን እግዚአብሔር ሲፈጥረን፣ በውስጣችን ያስቀመጠው ፀጋ እንዳለ አምነን በራሳችን ስንተማመንና እግዚአብሔር ይረዳኛል ብለን በተሰጠን ችሎታና አቅም ለመሥራት ስንነሳ ያኔ ኢትዮጵያ መነሳት ትጀምራለች።

 

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የአስተሳሰብ ተሃድሶ ካላደረገ አሁን ያለውን መንግሥት መቀየር ብቻ ለሀገራችን መፍትሔ አያመጣም። ምናልባትም “ከሳት ወደ ረመጥ” እንደሚባለው የባሰ አገዛዝ ሊተካም ይችላል።

 

አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት ባለሥልጣናት፣ እየሠሩ ባሉት ማስተዋል የጎደለው ሥራ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ጥላቻን እያተረፉ እንደሆነ የታወቀ ጉዳይ ነው። በአስቸኳይ ከህዝብ ጋር ለመታረቅ የሚረዱ ተጭባጭ እርምጃዎችን ካልወሰዱ፣ አሁንም ህዝቡን “በውሸትና በሸፍጥ እንዲሁም በጠመንጃ ኃይል እየረገጥነው እንቀጥላለን” ብለው ልባቸውን ካደነደኑ አወዳደቃቸው እጅግ በጣም የከፋ እንደሚሆን መቼም እንደ ቻዎቼስኮ ያሉ አምባገነኖችን ፍጻሜ እንዴት እንደሆነ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው በቀላሉ የሚተነብየው ነው።

 

አሁን ግን በጣም ላተኩርበት የምፈልገው በአራት ኪሎ፣ በምኒልክ ቤተመንግሥት የተቀመጡት ግለሰቦች ከእኛው መካከል የወጡ የሕብረተሰባችን ውጤቶች እንደሆኑ ነው። ከሥልጣናቸው ቢወገዱ እንኳን እኛ ካልተለወጥን እንደገና አምባገነኖችን እንወልዳለን። በኢትዮጵያ ደም ማፍሰስ የተጀመረው አቶ መለስ ዜናዊ ሥልጣን ሲይዙ አይደለም። ከዚያ በፊት ሲወርድ ሲዋርድ የመጣ ስር የሰደደ ችግር ነው።

 

ታዲያ ለዚህ ስር ለሰደደ ችግር በአመለካከታችንና በጎጂ ባህላችን ላይ ያነጣጠረ ስር ነቀል የሆነ መፍትሔ ነው የሚያስፈልገው። በሀገራችን ኢትዮጵያ ዳግማዊ አብዮት ያስፈልገናል።

 

ይህ ዳግማዊ አብዮት በማርክስና ዔንግልስ መጻሕፍት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፤ በእግዚአብሔር ቃልና በአዕምሮ መታደስ ላይ የተመሰረተ ነው፤

 

ይህ ዳግማዊ አብዮት መደብን ከመደብ፣ ጉሣን ከጉሣ፣ ኃይማኖትን ከኃይማኖት ጋር በማጋጨት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፤ ከሁሉም ጉሣዎች፣ ኃይማኖቶችና መደቦች ኢትዮጵያውያንን በአንድ ላይ፣ ለአንድ ዓላማ፣ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በማምጣት ላይ የተመሰረተ ነው፤

 

ይህ ዳግማዊ አብዮት የጥቂቶችን ውስኔ በብዙኀኑ ላይ በጉልበት በመጫን ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፤ በየጓዳውና በየቤቱ ኢትዮጵያውያንን ለመልካም ሥራ ውስጥ ለውስጥ ማነሳሳቱና ማነቃቃቱ ላይ የተመሰረተ ነው፤

 

ይህ ዳግማዊ አብዮት አንዱን የሀገራችን ክፍል ወይንም አንዱን የፖለቲካ ድርጅት እንደ ጠላት በማየት ለማጥፋት በመሞከር ላይ የተመሰረተ ሳይሆን፤ በአራት ኪሎና በአስመራ ያሉትን ጨምሮ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በማፍቀር ላይ የተመሰረተ ነው መሆን ያለበት።

 

ወገኖቼ ሌሎች ከቻሉ እኛ የማንችልበት፤ ሌሎች ካደጉ እኛ የማናድግበት ምክንያት የለም። እኛ ከማንም በጭራሽ አናንስም። ኢትዮጵያ ከጋና፣ ከሲንጋፖር፣ ከታንዛኒያ፣ ከሕንድ፤ ከቻይና … በምን ታንሳለች? ኢትዮጵያውያን በስደቱ ዓለም በሕክምናው ሆነ በኢንጂነሪንጉ፣ በሕጉ ሆነ በፋይናንሱ ዘርፍ ከቻይና ሆነ ከሕንድ ተወላጆች ያላነሰ ሥራ እንደሚሠሩ ማንም የሚያውቀው ነው። ታዲይ ይሄ ከሌሎች አለማነሳችንን በግልጽ አይሳይምን?

 

አንዳንዶቻችን ”ወያኔ እስካለ ድረስ ምንም ጥሩ ነገር አይኖርም። ወያኔን ደግሞ የሚያነቃንቀው የለም” ብለን ተስፋ የቆረጥን አለን። አሁን ያለው አገዛዝ ከህዝብ በላይ ሊሆን አይችልም። የህዝብን ኃይል ለአንድ ቀን መቋቋም አይችልም። ህዝብ ከተነሳ አገዛዙ የህዝብ አካል ሆኖ ይጓዛል፤ ወይንም ስፍራውን ይለቃል እንጂ ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ አፍኖ መቀጠል አይቻለውም።

 

ህዝብ ከተባበረና ከተነሳ ይቻላል ተራራን መውጣት። ይቻላል ሸለቆን መውረድ። ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ቂም በቀል፣ ትዕቢትና ጦረኝነት ከሚባሉ ንጥረ ነገሮች የተሰራውን፣ ለዘመናት ሲመለክ የነበረውን “ጣዖት” መሰባበር ይቻላል። ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጃፓን ማደረግ ይቻላል።

 

እግዚአብሔር ሀገራችን ኢትዮጵያን ይባርካት!

ልባችንን በፍቅሩ አዕምሯችንን በጥበቡ ይሙላልን! - አሜን!!!


1 http://www.ethiopianreview.com/content/1903  

 

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!