Ali Birra. ዓሊ ቢራ

ቋንቋዎቻችን የልዩነት፣ የጥላቻና የዘረኝነት ጽኑ ግምብ ሲሆኑብን!

ኒቆዲሞስ

የኃይማኖት ሊቃውንት በጥንት ዘመን ፍጥረት ሁሉ በአንድ ቋንቋ ይነጋገር እንደነበርና ቆይቶ ግን ይህ በአንድ ቋንቋ የመግባባት ጉዳይ ብዙም ሳይዘልቅ እንደተቋረጠ ያትታሉ። ምክንያቱን ሲያብራሩም ጥንታውያኑ ባቢሎናውያን ገናና ሥልጣኔያቸው ጫፍ በነካ ማግሥት ሰማይን የሚታከክና የፈጣሪን መኖሪያ፣ ክብሩንና ልዕልናውን የሚዳፈር ረጅምና ግዙፍ የሆነ ታላቅ ግምብ ለመገንባት ተነሱ።

ይህን ጊዜ ታዲያ የልባቸውን ትቢዕት፣ ክፋትና ዓመፃ አስቀድሞ ያየው ፈጣሪም እርስ በርሳቸው እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን ደበላለቀው ይሉናል እነኚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን። እናም የዚህ ሁሉ ቋንቋ መፈጠር መንሥኤው የሰው ልጅ ዓመፃ ውጤት ነው ሲሉ ያስረዳሉ። ሳይንስ ደግሞ በበኩሉ ቋንቋ የሰው ልጆች የሥራና የማኅበራዊ ኑሮ መስተጋብራቸው ድምር ውጤት ነው ሲል ይደመድማል።

በዓለም ያሉት ቋንቋዎች የኃይማኖት ሊቃውንት እንደሚሉት የሰው ልጆች የኃጢአት/የክፋት ውጤትም ይሁኑ አሊያም ደግሞ የሳይንስ ጠበብቶች እንደሚሉት የሰው ልጆች የሥራና ማኅበራዊ መስተጋብር ውጤት፣ ከፍጥረት ሁሉ የላቀው የሰው ልጅ በዚህም ቢሆን በዚያ መንገድ ይባል አሳቡንና ስሜቱን የሚገልጽበት የበርካታ ቋንቋዎች ባለቤት ለመሆን ችሏል ወይም በቅቷል።

የጽሑፌ ዐቢይ መልዕክት ስለ ቋንቋ ጅማሬ ኃይማኖትና ሳይንስ የሚያነሷቸውን የመከራከሪያ እሳቤዎች እያነሱ ለመተንተን አይደለም። ግና በአገራችን በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ቋንቋዎቻችን ‹‹እነርሱና እኛ›› በሚል የጥላቻንና የዘረኝነትን ግምብ የገነባንባቸው፣ የእርስ በርስ ልዩነቶቻችን እያሰፉ ያሉ የልዩነትና የጥላቻ መስመር ያሰመርንባቸው፣ ጽኑ የሆኑ የመለያያ ግምብን የገነባንባቸው፣ የዘረኝነትና የጥላቻን ችካል የቸከልንባቸው መረገምቶቻችን እየሆኑ እንደመጡ እያስተዋልን ነው።

ለዛሬው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ ባለፈው ሳምንት የተዋዳጁ የሙዚቃ ባለሙያ የአርቲስት ዓሊ ቢራ የኀምሳ/፶ኛ ዓመት የጥበብ ጉዞው በዓል በተከበረበት ወቅት የሆነ ክስተት ነው። ነገሩ እንዲህ ነው የዓሊ ቢራን የ፶ኛ ዓመት የሙዚቃ የስኬት ጉዞ ለማክበር ከተዘጋጁት ዝግጅቶች አንደኛው በአዳማ ከተማ በሙዚቃ ሥራዎቹ ላይ በተለያዩ ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርብበት ዝግጅት ነበር። ታዲያ የማታ ማታ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ከአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ውጭ በሌላ ቋንቋ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች በምንም መልኩ እንደማያስተናግዱና ተቀባይነት እንደሌላቸው አስታወቁ።

እንግዲህ ልብ በሉ ይህ ውሳኔ ደግሞ አስቀድሞ የተነገረ አይደለም። እንደ ውኃ ደራሽ ድንገት የሆነ ውሳኔ ነው። መቼም ዓሊ ቢራ ይህን ውሳኔ ይቀበለዋል፣ ይደግፈዋል ብዬ ለማመንና ለመቀበል እቸገራለኹ። ምክንያቱ ደግሞ ዓሊ ቢራ የሙዚቃ ሥራዎቹ በኦሮምኛ ቋንቋ ብቻ የተሰሩ አይደሉምና። ባለኝ መረጃ ዓሊ ቢራ በአማርኛ፣ በአደሪኛ፣ በዐረቢኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ዘፍኗል። እነዛ ዘመናትን የተሻገሩ የዚህ ድንቅ የጥበብ ሰው ሥራዎቹ ብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ዛሬም ድረስ ትልቅ ክብርና ሥፍራ አላቸው። ዓሊ ቢራ ስለ ነጻነት፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ጥበብ፣ ስለ አገሩ ውበትና ተፈጥሮ ያዜማቸው ዜማዎቹ እኮ ዘርና ቋንቋ ሳይለዩ የሰው ልጆችን ሁሉ ማዕከል ያደረጉ እንደሆኑ ነው የሚገባኝ።

የዚህ ዝግጅት አስተባባሪዎች የዚህን አንጋፋና ታላቅ የጥበብ ሰው ሰው ሥራዎች በምን አመክንዮ ከአፋን ኦሮሞ ውጭ ሊዳሰሱ፣ ሊተነተኑ እንደማይችሉ የደረሱበትን ውሳኔያቸውን በግልጽ ቢነግሩን መልካም ነው። እንደሚገባኝ ይህ ውሳኔያቸው ፈጽሞ ለጥበብና ለጥበብ ሰዎች የሚሆን፣ የሚስማማ አካሄድ አይደለም። ደግሞስ የጥበብ ሥራ የቋንቋ፣ የዘር ድንበር አለው እንዴ?! ይህ ውሳኔ የወሰኑ ሰዎች በፍቅርና በአክብሮት የምንግራቸው ነገር ቢኖር ይህን በማድረጋቸው የዛን ታላቅ የጥበብ ሰው፣ የዓሊ ቢራን ድንቅ የጥበብ ሥራ ያሳነሱና ያኮሰሱ መሆናቸው ሊገባቸው ይገባል።

ቢሆንልን ሁሉም በየቋንቋው የዚህ የጥበብ ሰው ሥራዎች ያላቸውን ፍቅርና አድናቆት፣ እንዲሁም ትችትና አስተያየት እንዲገልጹ ዕድል መስጠት ሲኖርብን እንዲህ ጠቦና አንሶ ከአፋን ኦሮሞ ውጭ እንዴት ተደርጎ የዓሊ ቢራ የሙዚቃ ሥራዎች ይተነተናሉ፣ ይጠናሉ፣ ይተቻሉ፣ ይሔየሳሉ ብሎ ማለት ጤነኛ አካሄድ አይደለም። እነዚህ ሰዎች አሳባቸውና ዓላማቸው የኦሮሞ ሕዝብን ቋንቋና ባህል ለማሳደግ ከሆነ የመረጡት ይህ መንገድ ትክክለኛ አይመስለኝም። ጥብብም ሆነ የጥበብ ሰው የቋንቋ ድንበር የለውምና!!

ከዛም አልፎ ይህ እነዚህ ሰዎች የወሰዱት ውሳኔ ቋንቋና ዘር ሳይለይ ተዋድኖ ተጋብቶ በኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ሌላ የጥላቻና የመለያየት ግምብ መገንባት፣ የጥላቻ ክፉ ዘርን መዝራት ነው የሚሆነው። እስከማውቀው ድረስ ዓሊ ቢራ በኦሮሞነቱ፣ በቋንቋው፣ በባህሉ የሚኮራውን ያህል ኢትዮጵያዊነቱ በደሙ ያለ፣ ማንም ሊነጥቀው የማይችለው በልቡ ውስጥ በደማቅ የታተመ ክብሩና መኩሪያው እንደሆነ ነው ደግሞ ደጋግሞ ሲገልጽ የሰማነው።

በዓሊ ቢራ የጥበብ ሥራ ውስጥ ተደጋግሞ የተዘፈነለት የኦሮሚያ ምድርና የታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ የረጅም ዘመናት ታሪክና ሥልጣኔ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ አኩሪ የነጻነት ተጋድሎው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በትልቁ ያደመቀና ያስዋበ የጥበብ ሸማ ነው። ‹‹በትናንትናዋም ሆነ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ታሪክ መልክና ገጽታ ውስጥ ኦሮሞ ግንድ ነው።›› እንዲሉ የፖለቲካ ምሁሩ ፕ/ር መረራ ጉዲና። ይህ ታላቅ ሕዝብ ከአማራው፣ ከትግሬው፣ ከአፋሩ፣ ከሱማሌው፣ ከሐረሪው፣ ከጉራጌው፣ ከደቡብ ሕዝብ ጋር በጽኑ የፍቅርና አንድነት፣ የአብሮነት መሠረት ላይ የተሳሳረ፣ የተዋሐደ ታላቅ ሕዝብ ነው።

ይህ በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ነገዶች መካከል በሕዝብ ብዛቱ ተወዳዳሪ የሌለው የኦሮሞ ሕዝብ ታሪኩ፣ ቋንቋው፣ ባህሉ፣ ሙዚቃው ... ወዘተ እንዲስፋፋ፣ በአፍሪካና በመላው ዓለም ተሰሚነት እንዲኖረው ለማድረግ መጣር ሲገባ በአጉል ጥላቻና ጠባብነት ተይዞ ጥበብንና የጥበብ ሰዎችን በአንድ ቋንቋ ብቻ መወሰን፣ መገደብ ትልቅ ስህተት ነው። ይህን ውሳኔ ያደረጉ ሰዎችም ዞር ብለው ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑ፣ በዚህ ውሳኔ ውስጥም የዓሊ ቢራ እጅ ካለበት ይህ ለጥብብና ለጥበብ ሰው የማይበጅ አካሄድ፣ ጥላቻንና መለያየትን የሚያነግሥ እንደሆነ በአክብሮት ለመግለጽ እወዳለሁ።

የፍቅር፣ የተፈጥሮ፣ የውበት፣ የነጻነት፣ ውብና መገለጫ፣ የሰው ልጆች ሁሉ የመግባቢያ ረቂቅ ቋንቋ የሆነች ሙዚቃን በዚህ ደረጃ አውርዶና አዋርዶ፣ ከዘመን ፖለቲካ ጋር አጋብቶና አዋሕዶ እንዲህ አመንዝራ እንድትሆን ማድረግ የሚገባ አካሄድ ነውን?! ይህ ያደረጉ ሰዎች ምክንያታቸውን በግልጽ አብራርተው ሊነግሩን ይገባል ባይ ነኝ። ከዚህ ጋር አያይዤም የሁሉም ሕዝቦች ሀብት በሆነው የዓሊ ቢራ የጥበብ ሥራዎች ውስጥ ኦሮሞነትን ከኢትዮጵያዊነት ለይተውና ነጥለው፣ በአንድ ቋንቋ ብቻ ገድበው ለማየት፣ ለመተንተን ለሚፈልጉ ሰዎችም አንድ ገጠመኜን በማንሳት ጥቂት ነገሮችን ለማለት እወዳለሁ።

በ1990ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ተማሪዎች፣ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ፊንፊኔ መሆን አለባት በሚል ለዓመታት የቆየውን ሙግት እንደገና ነፍስ እንዲዘራ በማድረግ እንደ አዲስ ለጥያቄ አቅርበውት ነበር። በወቅቱ ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት የኦሮሚያ ዋና ከተማ አዳማ እንጂ ፊንፊኔ አይደለችም ባይ ነበር። እናም ይህን አጀንዳ ማለትም የኦሮሚያ ዋና ከተማ ፊንፊኔ እንጂ አዳማ አይደለም የሚለውን አቤታታቸውን ለመንግሥት ለማሰማት የኦሮሚያ ብሔር ተወላጅ ተማሪዎች በአንድነት ተሰባስበው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ቢሮ ፊት ለፊት ከሚገኘው አስፋልት ላይ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው ነበር።

በዚህ ለግማሽ ቀን በዘለቀው የተማሪዎቹ ተቃውሞ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ከቴክኖሎጂ ፋኩልቲ፣ ከፋርማሲ ት/ቤትና ከአራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የመጡ የኦሮሞ ክልል ተወላጆችም ሰልፉን ተቀላቅለውት ነበር። ሰላማዊ የሆነ ተቃውሞአቸውን በተለያዩ መፈክሮችና መዝሙሮች ያሰሙት ተማሪዎቹ በኋላ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ቢሮ ከሚገኝበት ፊት ለፊት ካለው አስፋልት ላይ በፀጥታ ተቀምጠው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ኃላፊዎች ምላሽ ይሰጧቸው ዘንድ መጠባበቅ ያዙ።

ዘግይቶም ቢሆን በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ቫይስ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር የተማሪዎቹን አሳብና አቤቱታ ለመቀበል በርጋታ እየተራመዱ ወደእነርሱ መጥተው ተቀላቀሏቸው። ተማሪዎቹም የዩኒቨርሲቲውን ባለ ሥልጣን በአክብሮት ከተቀበሏቸው በኋላ በቢሮአቸው ፊት ለፊት ለግማሽ ቀን ያህል ለተቃውሞ እንዲሰበሰቡ ወዳደረጋቸው ወደ ዋና ጉዳያቸው በቀጥታ አመሩ።

ሰልፈኞቹ ተማሪዎችም ከመካከላቸው የሚወክላቸውን ተማሪ መርጠው ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል፣ ለጠ/ሚሩ ጽ/ቤት እንዲያቀርቡላቸው ለእኚህ ሰው በቃል አቀረቡ። በዚህ ሒደት ነበር በግሌ ያስገረመኝን አንድ ነገር የታዘብኩት። የኦሮምኛ ተናጋሪ የሆነው የተማሪዎቹ ተወካይ አማርኛ ለመናገር ባለመፈለጉ ብቻ ሳይሆን አማርኛ የነፍጠኞቹ፣ የቅኝ ገዢዎቹ የአቢሲኒያውያን ቋንቋ ነው በሚል ድምዳሜ የተነሣ እርሱ በኦሮምኛ ቋንቋ የሚያቀርበውን አቤቱታ ሌላኛው ጓደኛው በእንግሊዝኛ ለዩኒቨርሲቲው አካዳክሚክ ቫይስ ፕሬዝዳንት እያስተረጎመ መናገር ጀመረ።

ይህ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች ዙሪያ ጥምጥም አካኼድ ስለአማርኛ ቋንቋ ያላቸውን የተሳሳተ ግምትና ጥላቻ በግልጽ ያሳዩበት እጅጉን የተገረምኩበት አጋጣሚ ነበር። የአማርኛ ቋንቋ የአገሪቱ ወይም የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ነው ተብሎ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ በተቀመጠበት የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የኾኑት ተማሪዎች አማርኛ ቋንቋን ሽሽታቸው ለጊዜውም ቢሆን ግራ አጋባኝ። የሆኖ ሆኖ ግን ተማሪዎቹ በወደዱት መንገድ አቤቱታቸውን ካቀረቡ በኋላ ሰልፉ በሰላማዊ መንገድ ተጠናቆ ተበተነ።

ይህ በወቅቱ የታዘብኩት ነገር ዛሬ ደግሞ የዓሊ ቢራን የጥበብ ሥራዎቹን ከአፋን ኦሮሞ ውጭ እንዴት ሲባል ጥናት ይደረግበታል የሚሉ ሰዎችን አካሄድ ጋር ተዳምሮ እጅጉን ግራ አጋባኝ። ለመሆኑ አማርኛ የአገሪቱ ወይም ፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ አይደለም እንዴ ስል ለመጠየቅ ተገደድኩ። የኦሮሚያ ተወላጅ የሆኑት ተማሪዎች ነገረ ሥራቸው በወሬ እሰማው የነበርኩትን ‹‹የአማርኛ ቋንቋ የአቢሲኒያውያን የቅኝ ገዢዎች ቋንቋ ነው።›› በሚል የፈረጁበት የተሳሳተ ታሪካዊ ድምዳሜና ትርክት እውነታውን በተግባር በአደባባይ አይቼና ሰምቼ በማረጋገጤ መገረምና ግራ መጋባትን ሞላኝ። ቆየት ብዬ ደግሞ ድንጋጤና አንዳንች የፍርሃት መንፈስ ውስጤን ሲያርደው ተሰማኝና ሽምቅቅ አልኩኝ።

እናም በወቅቱ ለመሆኑ ወዴየት እየሔድን ነው፣ በዚህ የተሳሳተ የታሪክ ትንታኔና ሚዛናዊ ያልሆነ ትርክት ድምዳሜ ዕጣ ፈንታችን ምን ይሆን፣ ይህ የእርስ በርስ ጥላቻና ንቅት ወዴየትኛው ጎዳና ያደርሰን ይሆን በሚል ጥያቄ ውስጤ ተወጥሮ ነበር። እንደው የሆነስ ሆነና የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑ አንዳንድ ምሁራንና የኦሮሞ ሕዝብ ነጻ አውጪ ታጋዮች ነን ባዮችና ኦሮሚያ በአቢሲኒያ በቅኝ ግዛት ሥር የኖረ ነው የሚለውን አሳብ አቀንቃኞች እንደሚሉት፣ አቢሲኒያ በቅኝ ገዝታቸው ቢሆንስ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ይልቅ የትኛው ቋንቋ ነው የሚቀርባቸው፣ የሚቀላቸውስ አልኩኝ ለራሴ።

እነዚህ የኦሮሚያ ተወላጅ ተማሪዎች አማርኛን ቋንቋን ላለመናገር የሔዱበት የዙሪያ ጥምጥም መንገድ ፍርሃትን አጫረብኝ። አቢሲኒያ በቅኝ ገዝታናለች በሚል ሰበብም የቅኝ ገዢዎቻችን ወይም የነፍጠኞች/የአማሮች ቋንቋ ከልባችንም ከአንደበታችንም ፈጽሞ ይራቅ፣ ውጉዝ ይሁን ያሉበት ጥላቻ የወለደው አካኼዳቸው በውስጤ ሌላ ልጋፈጠው የሚገባ የታሪክ ጥያቄንና ሙግትን ፈጠረብኝ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታችን የአፍሪካን ኮሎኒያልና የነጻነት ትግል ታሪክ ያስተማሩን እጅጉን የምናከብራቸውና የምንወዳቸው፣ ምስጉንና ምሁራዊ ጨዋነትን በእጅጉ የተላበሱ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የኾኑ የታሪክ ፕሮፌሰር ናቸው። የአፍሪካ የቅኝ ግዛት ታሪክ ጥናታችን አውሮፓውያን አፍሪካውያን ሕዝቦች ከታሪካቸው ተነቅለው፣ ቋንቋቸው ተረግጦ፣ ቅርሳቸውና ማንነታቸው ተዋርዶ፣ የእንሰሳ ያህል እንኳን ክብር ተነፍጓቸው፣ ወደ አውሮፓ ተጓጉዘው በዛ በሚገኙ ታላላቅ ቤተ መዘክሮች/ሙዚየም ውስጥ ፍጹም ኢሰብአዊ በሆነ መልኩ እንደ ዱር አራዊት በብረት አጥር ተከልለው ለትዕይንት እንዲቀርቡ የተደረጉበትን አስከፊ፣ አሳፋሪ የባርነትና የቅኝ ግዛት ዘመናትን እንዳሳለፉ ነበር የተማርነው።

በአገራችንም በኢትዮጵያ ለአምስት ዓመታት የቆዩት ኢጣሊያውያኑ ቅኝ ገዢዎች ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ነጭና ጥቁር በሚል የዘረኝነት መርዝ ስብከታቸውና የነጭ የበላይነት ባሰፈነው በከፋፍለህ ግዛው ስልታቸው ለጥቂት ዓመታትም ቢሆን ሕዝባችንን ለመከራ እንደዳረጉት ነው ታሪክ የሚነግረን። ኢትዮጵያውያን ከዐራተኛ ክፍል በላይ እንዳይማሩ፣ ኢጣሊያውያኑ በሚዝናኑበት፣ በሚኖሩበትና በሚንቀሳቀሱበት በማንኛውም ቦታ ለጉልበት ሥራ ብቻ ካልሆነ በቀር ሐበሻ ዝር እንዳይል በሚደነግገው ሕጋቸው ሕዝባችን የቅኝ አገዛዝን አስከፊ ገጽታውን በመጠኑም ቢሆን ለመረዳት ችሎ ነበር።

እንግዲህ በአጭሩም ቢሆን የቅኝ አገዛዝ ገጽታውና መልኩ ይህ ነበር። ይህን የታሪክ እውነታ ይዘን የኦሮሞ ተወላጅ ወንድሞቻችንን አቢሲኒያ በቅኝ፣ በኃይልና በነፍጥ ገዝታናለች ትርክትን ወይም ታሪካዊ ሙግትን ስንገመግም አንዳንድ የተሳሰቱ ነገሮች እንዳሉ ይታዩናል። ለመሆኑ ቅኝ መገዛት ማለት ምን ማለት ነው? በእርግጥስ በአገራችን ታሪክ ነገሥታቱና ገዢዎች በገብር አልገብርም፣ የግዛት ማስፋፋትና የኢኮኖሚ የበላይነትን ለማስጠበቅ የተደረጉ ዘመቻዎችና ወረራዎች የቅኝ አገዛዝ ባሕርያትና ገጽታዎች ነበሩት ወይ ብለን በእርጋታ መጠየቅ ያለብንም ይመስለኛል።

መቼም በአቢሲኒያ/በኢትዮጵያ ታሪክ ኦሮሞ በመሆኑ በሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችን እንደሆነው አስከፊ የሆነ የዘር መድሎ የደረሰበት፣ እስከ ዐራተኛ ክፍል ብቻ እንዲማር የተገደደ፣ አቢሲኒያውያን በሚሔዱበት ጋሪ፣ አውቶቡስ አሊያም ባቡር እንዳይሔድ የተከለከለ፣ አቢሲኒያውያን በሚገቡበት ሆቴል እንዳይገባ፣ በሚማሩበት ትምህርት ቤት እንዳይማር፣ በሚዝናኑበት መዝናኛ ቦታዎች ፈጽሞ እንዳይገኝ የተደረገ የኦሮሞ ተወላጅ እንዳለ አንድም የታሪክ ሐቅ ማቅረብ እንደማይችሉ ራሳቸው አቢሲኒያ ቅኝ ገዝታናለች አቀንቃኝ የሆኑ የኦሮሞ ምሁራን ሳይቀሩ ልባቸው በሚገባ ያውቀዋል።

ይህን ስል ግን በተለያዩ ዘመናት በኦሮሞም ይሁን በሌሎች በአገራችን በሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ላይ ጭቆና፣ የመብት ረገጣ አልደረሰም፣ በቋንቋቸው እንዲያፍሩ፣ ታሪካቸው እንዲደበዝዝ፣ ባህላቸውና ቅርሳቸው እንዲናቅ፣ ከማንነታቸው እንዲነቀሉ ወይም እንዲሰደዱ አልተደረገም ማለት ግን አይደለም። ይህ ግን ዛሬ አንዳንዶች እንደሚሉት ዓይነት አንድ ሕዝብ የሌላውን ሕዝብ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ቅርስንና ባህልን ሆን ብሎ ለመጥፋት የተደረገና አንዳንዶችን ደፍረው እንደሚሉት የዘር ማጥፋት ዘመቻ ዓይነት መልክ አልነበረውም። አሊያም ደግሞ ዛሬ ዛሬ በድፍረት እንደሚባለውም የቅኝ ግዛትና የአፓርታይድ ዓይነት መልክ ወይም ገጽታ በጭራሽ አልነበረውም።

እንዲህ ዓይነቶቹ እውነተኛ መሠረት የሌላቸው የታሪክ ትንታኔዎችና አተያየቶች በኢትዮጵያ ሕዝቦች መከካል ልዩነትንና ጥላቻን በማራገብ፣ ተዋዶና ተፈቅሮ የኖረውን ሕዝብ በጥርጣሬና በጥላቻ ዓይን እንዲተያይ እያደረጉ ያሉ አጋጣሚዎችን በተለያዩ ጊዜያት እያየን ነው። ባሳለፍነው ሳምንት በአዳማ ከተማ በዓሊ ቢራ የሙዚቃ ሥራዎች ላይ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ለማቅረብ በተገኙ ምሁራን ላይ ከኦሮምኛ ቋንቋ ውጭ ያሉ ጥናታዊ ጽሑፎችን የአንቀበልም ውሳኔም ከላይ ካነሳሁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገጠመኜና ከዚሁ ከአዳማው ክስተት ጋር ተያይዞ አንድ የሚነግረን ሐቅ አለ።

ይኸውም በአገራችን በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ቋንቋዎቻችን ‹‹እነርሱና እኛ›› በሚል የጥላቻንና የዘረኝነትን ግምብ የገነባንባቸው፣ የእርስ በርስ ልዩነቶቻችን እያሰፉ ያሉ የልዩነትና የጥላቻ መስመር ያሰመርንባቸው፣ ጽኑ የሆኑ የልዩነትን ግምብ የገነባንባቸው፣ የዘረኝነትና የጥላቻን ችካል የቸከልንባቸው መረገምቶቻችን እየሆኑ እንደመጡ እንዳለን በተግባር ያረጋገጠልን ያለ እውነታ ነው።

ለመሆኑ ዓሊ ቢራ ከኦሮምኛ ውጭ በአማርኛ፣ በአደሪኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በዐረቢኛ ቋንቋዎች አልዘፈነም እንዴ?! የዓሊ ቢራ የጥበብ ሥራዎች የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ሀብት ብቻ ናቸው ያለውስ ማን ነው?! ሙዚቃ የቋንቋና የዘር ድንበር የሌላት ሰው ልጆች ሁሉ ሀብትና መግባቢያ ረቂቅ ቋንቋ እንደሆነች አይደለም እንዴ ዓለም ሁሉ በአንድ ድምፅ የተስማማው?! እናስ የዚህን ታላቅ የጥበብ ሰው ሥራዎች ከኦሮምኛ ቋንቋ ውጭ ሊታዩ፣ ሊጠኑ፣ ሊገመገሙ አይገባም ማለትን ምን አመጣው?!

በመጨረሻም ተዋዳጁን አርቲስት ዓሊን ቢራን ዘመን ለማይሽራቸው ድንቅ ለሆኑ የጥበብ ሥራዎችህ ፶ኛ ዓመት እንኳን በሰላምና በጤና አደረሰህ በማለት ልሰናበት።

ሰላም!

ኒቆዲሞስ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ