አንዱዓለም ተፈራ
Atse Tewodros. አፄ ቴዎድሮስ

እንደ እውነቱ ከሆነ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ገዥ ቡድን በእብሪት ተወጥሮ አገራችንን ሲጫወትባት፤ "እኛ የኔ ድርጅት! የለም የኔ ድርጅት!"፣ "እኔ ልምራ እናንተ ተከተሉኝ! የለም እኔ ልምራ እናንተ ተከተሉኝ!"፣ "እኔ እበልጣለሁ! የለም እኔ እበልጣለሁ!" እየተባባልን፤ በሌለ ሥልጣን ሽሚያ ልባችን ተወጥሮ፤ ዛሬ ትናንት፤ ነገ ደግሞ ዛሬ እየሆነ ዓመታትን አስቆጠርን።

ለምን? የአገር ጉዳይ እያንዳንዳችንን የሀገሯ ተወላጆች እኩል አይሸነቅጠንም? ምን እንስኪሆን ድረስ ነው የምንጠብቀው? በየድረገጹ የማነበው፣ በየፓልቶኩ ክፍል የማዳምጠው፣ በየሬዲዮኖች የሚተላለፈው፤ በአንድነት እስካልተነሳን ድረስ፤ ትግሉ አይሳካም! የነገውም ሂደት አያስተማምንም! ነው። ለምን በዚህ አውቶቡስ ሁላችን አንሳፈርም? ኧረ ተው! ታሪክ ይፋረደናል!

አሜሪካ ፈልጌውና ጓጉቼለት የመጣሁበት አገር አይደለም። የዴሞክራሲ ሥርዓቱ ናፍቆኝም አይደለም የመጣሁት። የተሰማራሁበት ትግል ሂደት ተሰናክሎ፣ ቀኑ ጨልሞብኝ፣ በሰደት ከነበርኩበት የኑሮ ዝግመት ማምለጫ ስለሆነልኝ ነበር። መጥቼ ደግሞ በአድናቆት ተውጬ ማንነቴን ረስቼ አልቧረቅሁበትም። በርግጥ ያገኘሁትን ዕድል በመጠቀም ኑሮዬን ገፍቻለሁ። ይኼው ከመጣሁ ሰላሳ ዓመታት አልፈዉኛል። የአሜሪካን የዴሞክራሲ ሥርዓት አካሄድ ስገነዘብ፤ ያላቸውን ድክመት ደግሞ በዚያው ጎን ለጎን አጢኛለሁ። ለሀገሬ ከማደርገው መሯሯጥ ጋር፤ በአሜሪካ አገር ያለሁበትን አገር የፖለቲካ ሀቅ ለማስተካከል፤ እንዲህ መሆን ሲገባው ለምን አልሆነም? እያልኩ ከማማረር አልቦዘንኩም። አሜሪካኖች የራሳቸውን የዴሞክራሲ አካሄድ "ፍጹም ወደ መሆን እያዘገምን ነው።" ብለው ነው የሚያምኑት። "ፍጹም ነው!" አይሉም። በምችለውና ባጋጠመኝ መንገድ ሁሉ፤ ይኼን ፍጹም ወደመሆን የሚጓዘውን ሂደታቸውን፤ በንቃት በመሳተፍ እየረዳሁ ነው።

አሁን በአገራችን የኑሮ ሀቅ፤ የወሃ ጥማት፣ የምግብ ማጣት፣ በሰላም የገበያ አገልግሎት፣ የመንገድ አለመሠራት፣ የትምህርትና ሕክምና አለመስፋፋት፣ የመናገርና የመጻፍ፣ የመሰባሰብና ተቃውሞን የመግለጽ፣ የአድልዕና ሙስና መንገሥ፤ መሠረታዊ የኅብረተሰቡ ጥያቄዎች፤ የፖለቲካውን መድረክ ማዕከላዊ ቦታ አልያዙም። ለዚህ ተጠያቂ የሆነውን መንግሥት በመወንጀል ባንድነት የመነሳት ግዴታችንን በውል አልጨበጥነውም። በርግጥ ከአሜሪካ ጋር የኛን አገርና የኛን ሁኔታ እያወዳደርኩ አይደለም። አዎ እንደነሱ በሀብት የበለጸግን አይደለንም። ግን ይኼ ላለንበት ሁኔታ ወሳኝነት የለውም።

የሀብት ጉዳይ ከተነሳ፤ በሀብት ያልበለጸግን መሆናችን አዲስ አይደለም። ከሕዝቡ ጥቅምና ከአገሪቱ ዕድገት ይልቅ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ቅድሚያ የሠጡ ገዥዎች በነበሩበት ዘመን፤ አጠቃላይ የአገሪቱን እውነታ ፈትሸው፤ ለረጅሙ የወደፊት ብልጽግና በማቀድ እርምጃ ስላልወሰዱ፤ ድኅነቱ አብሮን ኖሯል። እዚህ ላይ አንዳንዶቹ ያደረጉትን የልብ አስተዋፅዖ በምንም መንገድ ልስት አልችልም። ከነዚህ መካከል ባገኘሁት ዕድል ሁሉ፤ መጽሐፍትን በማገላበጥ ለማወቅ ጥረት ከማደርጋቸው መሪዎች መካከል፤ አፄ ዘርዓ ያዕቆብንና አፄ ቴዎድሮስን እጠቅሳለሁ። በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ምን ነበር? ያሁኑስ ዘመን ከዚያ ዘመን በምን ይለያል?

ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የአሁኑ ዘመን የሚለየው፤ ያኔ ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ፤ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ትልቅ ክብር የነበራቸው ሲሆን፤ አፈሩ እንኳ ሳይቀር የተከበረበት ዘመን ነበር። አፄ ቴዎድሮስ፤ ከሕዝቡ በመጠቀ ደረጃ፤ ከራሳቸው የወቅቱ ክብር ይልቅ፤ የሀገራቸው እድገትና በአካባቢያቸው የተኮለኮሉት የውጭ ጠላቶች እንቅስቃሴ፤ የዕለት ተዕለት ጭንቀታቸው ነበር። የተበታተነች ኢትዮጵያን ለመመለስና የቀድሞ ቦታዋን ለማስያዝ የሕይወታቸው ዋና ማዕከላዊ ትርጉም አድርገው ጣሩ። ለራሳቸው የስም ማስጠሪያ ግንብ ወይንም ቤተክርስትያን ከማሠራት ይልቅ፤ ለሀገራቸው መጠበቂያ የጦር መሣሪያ እንዲያበጁላቸው ነበር የውጭ አገር ሰዎችን የጠየቋቸው። ምንም እንኳ አሁን ምሁር ነን ባዮች፤ የአፄ ቴዎድሮስ ጠላቶች በውጭም ሆነ በውስጥ የነበሩት የጻፉትንና ያሉትን ተሸክመው ቢያጥላሏቸውም፤ እኒህ መሪ በተወለዱበት ዘመንና በቦታው የነበራቸውን የፖለቲካ ድርሻ አጢነው ቢመረምሩ፤ ከማንም መሪ የበለጠ ሊያደንቋቸው በተገባ ነበር።

የበዕደ ማርያም መምህሬ ዶክተር ገብሩ አስራት ለቀረበላቸው ጥያቄ የሠጡት መልስ እጅግ በጣም አርክቶኛል። ከነበሩት መሪዎች ሁሉ አንደኛ አድርገው የሚያደንቁትን ቃለ መጠይቅ አቅራቢዋ እንድትነግራቸው ስትጠይቃቸው፤ ያለምንም ማመናታት "አፄ ቴዎድሮስ ናቸው!" በማለት በኩራት አስቀምጠውላታል። ልክ ድሮ ሲያስተምሩኝ እንዳደነቅኋቸው ሁሉ፤ አሁንም መምሬ ሆነው አገኘኋቸው። ከመሬት ተነስተው፤ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ሀገራዊ ሕልውና፤ የመሠረቱን ደንጋይ ያስቀመጡ አፄ ቴዎድሮስ ናቸው። ከግለሰብ ማንነታቸው ይልቅ፤ የሀገራቸው መሪነታቸው ነበር ልባቸውን የሞላው። ያኔ በሕዝቡም መካከል፤ ከግለሰብ ምንነታችን ይልቅ የስብስብ ማንነታችን ማዕከላዊ ቦታውን የያዘ ነበር። ዛሬ በኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያዊነት አፈር የተንከባለለበት፤ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ኢትዮጵያዊ አለመሆን የተወደደበት፣ ከኢትዮጵያዊያን ስም ይልቅ የውጪ አገር ስሞች የተመረጡበት፣ ከራሳችን ቋንቋ ይልቅ የውጪ ቋንቋ፣ ከራሳችን እምነት ይልቅ የውጪ እምነት፣ ከራሳችን ምግብ ይልቅ የውጪ፤ ባጠቃላይም ከራሳችን ማንነት ይልቅ የውጪውን መቅዳትና መስሎ መገኘት የጎላበት ክስተት፤ ሀቅ ሆኖ ይታያል። ለምን? ዋናውን ማዕከላዊ ቦታ ይዞ በተጠያቂነት የቆመው ያለው ገዥ ቡድን ነው። ዋና ሥራዬ ብሎ የያዘው፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት ነው። ይኼንንም በትውልድ ማንነት ተክቶታል። እናም ከራሱ የገማን አሣ ... እንደሚባለው ቆርጦ መጣል ያለበት ገዥው ክፍል ነው።

አሁንም ያኔም ኢትዮጵያዊነት፤ ኢትዮጵያዊነት ነው። አሁን ግንዛቤያችን ፈሩን ለቋል። የብሔር ብሔረሰብ ጥያቄ የፖለቲካውን ማኅደር አጥለቅልቆታል። ምኑም ሆነ ምኑ የአገራችን ሀቅ፤ ከዚህና ከዚህ ብቻ እንዲታይ ተደርጓል። ይህ ደግሞ በገዥው ክፍል ብቻ ሳይሆን በታጋዩም ወገን ያለ እውነታ ነው። በዚህ ተለጉመን፤ መሠረታዊ የመኖርና ያለመኖር የሕልውና አምዶች፤ ቦታ ተነፍገዋል። የፍትኅ መጓደል፣ የትምህርት ጥራትና ዕድገት ወደ ታች ማሽቆልቆል፣ የሕክምና አለመሟላት፣ የምግብ እጥረትና ረሃብን የመቋቋም ዕቅዶች አለመኖር፣ የሴቶችን እኩልነት አለመቀበልና ተሳትፏቸውን አለማሳደግ፣ አድልዕና ሙስና፤ እነዚህ መሠረታዊ የሕልውና ጥያቄ ናቸው። መስመሩ የተዘጋበት የውሃ ፈሰስ፤ ዙሪያውን ይዳስሳል። የተገደበበትን መዝጊያ መጋፋቱን፤ በጎን መፋሰሻ ከመፈለግ ጋር በእኩል ይዳስሳል። ተገድቤያለሁ ብሎ ተስፋ በመቁረጥ አይረጋም። ከግድቡ ጋር ብቻም አይታገልም። ዙሪያውን በሙሉ ነው ጥረት የሚያደርገው። በግድቡ አናት፣ በግድቡ ሥር፣ ከታቆረበት ዙሪያ ይውዘገዘጋል። የታፈነ በመሆኑ ቦርቅቆ ለመውጣት ይፍጨረጨራል።

ወገኖቻችን በየበረሃው መንገላታታቸው፣ እህቶቻችን በአረብ ሀገሮች መጎሳቆላቸው፣ በገዛ ሀገራቸው ወገኖቻችን መፈናቀላቸው፣ በገዛ ሀገራቸው ወንድምና እህቶቻችን በረሃብ ተጠምደው ለማኝና አገሪቱ በሞላ የውጭ አገር ምጽዋተኛ መሆናቸው፤ አእምሯችንን በማስጨነቅ የፖለቲካ ምኅዳሩን ሊያናጉት ይገባል። በርግጥ በአሁኑ ሰዓት የፖለቲካ ውይይቱ ተጧጡፏል። ይህ በምን ዓይነት ውጥረት ላይ መሆናችንን አመልካች ነው። ነገር ግን መፍትሔ አፈላለጉ ላይ ለየብቻ እየሮጥን ነው። ለየብቻ ሮጦ የግብ መሰመሩ ላይ ለየብቻ ነው የሚደረሰው። ታዲያ ምን ዋጋ አለው? ግቡ የማንም ግለሰብ ወይንም ቡድን የግል መኖሪያ አይደለም። የሁላችንም ነው። ባንድ ላይ መሯሯጥ አለብን። የተጎተቱ ካሉ፤ አብረን መሳብና መሳሳብ እንጂ፤ እኔ ቀድሜ ሄጄ እሸለማለሁ ወይንም ሌሎችን እጎትታለሁ የሚባልበት አይደለም። አብረን ስንነሳ፤ ቀዳሚ ሆነው የቆሙት ሲመሩ፤ የተጎተቱት ደግሞ ሲከተሉ፤ ባንድነት ከግባችን እንደርሳለን። ታሪክ ደግሞ ከኛ ጋር አብሮ ይኖራል። ተወቃሽ አያደርገንም። ከታሪክ ተወቃሽነት መዳን አለብን። በሕይወት እስካለን ድረስ፤ ሆዳችን መሙላቱን ሳይሆን፤ በሕይወት የኖርንበትን ወቅት ትርጉም መሥጠቱ ላይ ማተኮር አለብን። ቆመን እንቆጠር። አብረን እንሰለፍ።

አንዱዓለም ተፈራ - የእስከመቼ አዘጋጅ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ቅዳሜ፤ መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፯ ዓመተ ምህረት - 04/04/2015

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!