Ethiopias tear. እናት ኢትዮጵያም ስለ ልጆቿ አለቀሰች የሉምናእናት ኢትዮጵያም ስለልጆቿ አለቀሰች የሉምና!!

ዲ/ን ተረፈ ወርቁ

”... ዓይኔ በእንባ ደከመ፣ አንጀቴም ታወከ። ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ አንጀቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ። አቤቱ የሆነብንን አስብ፣ ተመልከት ስድባችንንም እይ ...።” ሰቆ. ፪፣፲፩ ፤ ፭፣፩።

ይህን ቃል የተናገረው በመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ዘንድ ”አልቃሻው፣ ባለ ሙሾው ነቢይ” በመባል የሚታወቀው አይሁዳዊው ነቢዩ ኤርምያስ ነው። ይህንን ነቢይ እንዲህ እንደ ርኁሩኋ እናት አንጀቱን ያላወሰው፣ እንባው እንደ ክረምት ጎርፍ እንዲፈስ ያደረገውና ነፍሱ ድረስ ዘልቆ ብርቱ ኀዘንና ቅጥቃጤን የፈጠረበት ምክንያቱም፡- ኢየሩሳሌም በጠላቶቿ ተማርካ፣ ሕዝቦቿም ተዋርደው፣ ከአገራቸውና ከምድረ ርስታቸው ተነቅለው፣ ያ እጅጉን ያከብሩትና ይፈሩት የነበረው መቅደሳቸው ፈርሶ፣ በግዞት ውስጥ የነበሩትን የሕዝቡን ሰቆቃና መከራ በዓይኑ በማየትና የመከራቸውም ተካፋይ መሆኑ ነበር።

ጸሎተኛውና ኀዘንተኛው ኤርምያስ ስለ ኢየሩሳሌም ኃጢአትና በደል በዚህም ስለደረሰባት ከባድ ውርደትና መከራ ዓይኔ ምነው የእንባ ምንጮች ፈሳሽ በሆኑልኝ በማለት የተመኘ፣ በብርቱ የጸለየ፣ የተማጸነና የማለደ የሀገሩ፣ የሕዝቡ ውርደትና ጭንቀት፣ መከራና አበሳ፣ ሰቆቃና ዋይታ እንቅልፍ፣ እረፍት የነሳው ብርቱ የእግዚአብሔር ነቢይ ነበር።

ከራብ የተነሳ እናቶች የአብራካቸውን ክፋይ ልጆቻቸውን የበሉበትን፣ በቅምጥልነት የኖሩ የኢየሩሳሌም ቆነጃጅትና ደናግል በጠላቶቻቸው ብርቱና ጨካኝ ክንድ ከሰውነት ክብር ተዋርደው፣ ከመፈራትና ከመወደድ የክብር ሰገነት ላይ ተሸቀንጥረው፣ ተንቀውና ተጥለው በጎዳና ያለ ምንም ተሰፋ ሲንከራተቱና የሁሉም መጫወቻና ማላገጫ ሲሆኑ፣ ሕፃናት በእናቶቻቸው ደረቅ ጡት ላይ አፋቸው ተጣብቆ በጣእረ ሞት ተይዘው ሲጨነቁ፣ አባቶችና እናቶች የጥንቱን የበረከትና የድሎት ኑሮአቸውን እያሰቡ እንባ ሲቀድማቸው፣ ከክፉ ጠኔ የተነሳ ወላዶች የማኅፀናቸውን ፍሬ እንኳን ለመብላት ያስጨከናቸውን ያን ክፉ ቀናት የታዘበ ነቢዩ ስለ ቅድስት ምድሩና ሕዝቡ ሰቆቃና መከራ እንዲህ ጸለየ።

”እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጎበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል እንባን ታፈሳለች። …” ሰቆ ፫፣፵፱፣፶። በማለት በመጮኽና በመቃተት ሰለ አገሩ ውርደት ስለ ሕዝቡ መከራ ሌት ተቀን በእንባ ባሕር እንደዋኘ ውሎ የሚያድር ኀዘንተኛና ሙሾ የሚደረድር ነቢይ ነበር አይሁዳዊው የእግዚአብሔር ሰው ኤርምያስ።

ከሰሞኑን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እንደ አይሁዳዊው ነቢይ ኤርምያስ አንገታችንን የሚያስደፋና በኸፍረት የሚያሸማቅቅ፣ ጆሮን ጭው የሚደርግ፣ የዋላድ እናቶችን አንጀት የሚያላውስና በእንባ ጎርፍ እንዲታጠቡ የሚያደርግ ሌላ የሞት፣ ሌላ የውርደት፣ ማብቂያ የሌለው የሚመስል መሪር የሆነ የመርዶ፣ ሰቅጣጭና ክፉ ዜና ለእናት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ምድር፣ ከሊቢያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሀገረ የመን ተሰምቷል።

በእርግጥ የኢትዮጵያ አገራችንና የሕዝባችን፣ የወገናችን የውርደትና የመከራ ዘመናት ገና ዛሬ የጀመረ ነገር አይደለም። በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል። ዓለምን ሁሉ እግዚኦ ካሰኘ ድርቅ፣ የራብ/የጠኔ እልቂት እስከ የወንድማማቾች የእርስ በርስ ደም መፋሰስ ዘግናኝ ጦርነትና ፍጅት ድረስ የሕዝባችን ስደት፣ መከራና ውርደት የአገራችን ዋንኛ መለያ ሆኖ አብሮን ለዓመታት ዘልቋል። በዓለም ሁሉ ፊት ኢትዮጵያዊነት ብዙዎችን እንዲሳቀቁና እንዲያፍሩ ያደረጋቸው አሳፋሪ ማንነት የሆነበትን ጥቁር ታሪካችን ዛሬም ገና በቅጡ ልንላቀቀው እንዳልቻልን እያየን፣ እያስተዋልን ነው።

ስደትና ውርደት፣ መከራና ሞት የሕዝባችን ዕጣ ፈንታ እንዲሆን የተፈረደበት ይመስል ዛሬም ምስኪን ሕዝባችን በሚሰቀጥጥ ሁኔታ የአውሬ፣ የበረሃና የባሕር ሲሳይ እየሆነ ነው። በለስ ቀንቶት ወደ ባዕድ ምድር የገባው ሕዝባችንም ከእንሰሳ በወረደ ሁኔታ ሰብአዊ ክብሩ ተደፍሮና ተዋርዶ የሞት ሞት እንዲሞት የተደረገበትን አጋጣሚዎችንም ደግመን ደጋግመን ታዝበናል። በሳውዲ ዐረቢያ ሊያውም በአገራችን ኤምባሲ ፊት ለፊት አስክሬኗ በመኪና መሬት ለመሬት እንዲጎተት የተደረገበትን ያን አንገታችንን ያስደፋንን የሕዝባችንን፣ የወገናችንን ውርደት መርሳት እንዴት ይቻለናል?!

በመካከለኛው ምሥራቅ ከፎቅ ላይ የሚወረወሩ፣ የፈላ ውኃ የሚደፋባቸውን፣ አሰቃቂ የሆነ ግፍና ውርደት የሚፈጸምባቸው የእህቶቻችን ሰቆቃና መከራ ዛሬም በቅጡ ማብቂያ የተገኘለት አይመስልም። በኬንያ፣ በታንዛንያ፣ በማላዊና በሞዛምቢክ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ሕገ ወጥ ናችሁ በሚል ሰበብ በእስር ቤት ታጉረው ፍዳ መከራቸውን እየቆጠሩና እባካችሁ ወገን ያለህ ደረሱልን እያሉ ያሉ ወገኖቻችንን ቁጥርም ቀላል አይደለም።

ዛሬም ስደትን አማራጭ ያደረጉ ወገኖቻችን በደቡብ አፍሪካ ምድር በቁማቸው በእሳት እንዲጋዩ፣ በቆንጨራና በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ተፈረደባቸው። ጥረው ግረው፣ ለፍተውና ደክመው ያከማቹት ሀብት ንብረታቸውም የዘራፊዎች ሲሳይ ሆነ። በዚሁ ከሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን በእሳት እየጋዩ፣ በቆንጨራና በጦር መሣሪያ እየተጨፈጨፉ ያሉበትን አሳዛኝ ክስተት ምክንያት የደረሰብንን ኀዘናችን በቅጡ ሳንወጣ ዳግመኛ ልባችንን በኀዘን ጦር የወጋ፣ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ክፉ ወሬን ከወደ ሊቢያ ምድር ሰማን። 28 የሚሆኑ ወገኖቻችን በሊቢያ በረሃ ዘግናኝ በሆነ አኳኋን በግፍ ታርደው ሰማዕትነትን መቀበላቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አረዱን።

በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን ለተፈጁት 14 ሺ አይሁዳውያን ሕፃናት ምክንያት ነቢዩ ኤርምያስ፡- ”የጩኸት፣ የጣርና ሰቆቃ ድምፅ በራማ ተሰማ፣ ራሄል ስለ ልጆቿ አለቀሰች የሉምና።” እንዳለው ዛሬም ከመካለኛው ምሥራቅ፣ ከየመን፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከሊቢያ ምድር የልጆቿን ጩኸት፣ ሰቆቃና ዋይታ የሰማች እማማ ኢትዮጵያም ማቅ ለብሳ፣ ትቢያ ነስንሳ ሙሾን እያወረደች ነው። የልጆቿ ኀዘን፣ ሰቆቃና ዋይታ ገና በቅጡ ያልታበሰላት ምድር ዛሬም ዕጣ ፈንታዋ ዕንባና ደም፣ ሰቆቃና ዋይታ ሆኗል።

ሕዳሴዋ በደጅ ነው፣ ልማቷና ዕድገቷም እየተፋጠነ ነው ያልንላት አገራችን ኢትዮጵያችን ዛሬም ለበርካታ ልጆቿ ጥላና ከለላ ለመሆን የቻለች አይመስልም። ስደትን አስቆማለሁ፣ በርካታ የሥራ ዕድሎችን እናመቻቻለን፣ በዚሁ በአገራችሁ ሠርታችሁ ራሳችሁንም ቤተሰዎቻችሁንም መለወጥ ትችላላችሁ እያለ ሲምል ሲገዘት የነበረው መንግሥታችንም በስንት እግዚኦታና ተማጽኖ ከመካለኛው ምሥራቅ ወደ እናት አገራቸው እንዲመለሱ ያደረጋቸው እህቶቻችንም ከዚህስ ኑሮ ብንሞትም ብንደንም እዛው አረብ አገር ይሻለናል በሚል ተስፋ ቆርጠው ዳግመኛ በመጡበት እግራቸው ሲመለሱ ታዘበናል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ለብዙ ዘመናት አንገታችንን የደፋን ሕዝቦች ነን። ሺ ዘመናትን በሚያስከነዳው ዥንጉርጉር ታሪካችን ከምንኮራበት ሥልጣኔያችንና ጀግንነታችን ይልቅ የምናፍርበት ጉስቁልናችን፣ ስብራታችንና ኸፍረታችን አይሎብን በእጅጉ ተሸማቀናል፣ በሀገራችን ትናንትና በሆነው ዛሬም እየሆነ ባለው፣ በምናየውና በምንሰማው ነገር ሁሉ አንገተ ሰባራ ሕዝቦች ሆነናል። መቼ ነው ይህ ታሪካችን ተለውጦ፣ ስማችን ታድሶ ቀና ብለን የምንሄደው ብለን በብዙ ተስፋ አድርገናል፣ ታግለናል።

የብዙዎች ወገኖቻችን እንባና ደምም ለለውጥና ለአዲስ ተስፋ በሀገራችን ተራሮችና ሸንተረሮች እንደ ውኃ ፈሷል። በለውጥና በዕድገት ስምም የአንድ ማኅፀን አብራክ ክፋዮች እርስ በርሳቸው ተራርደዋል፣ ተላልቀዋል። ብዙዎቻችንም ነፍሳችን እስክትዝል ለሀገራችን ለውጥ በብዙ አንብተናል፣ ወጥተናል ወርደናል። የለውጥ ያለህ በሚል ከልብ በሆነ ናፍቆትም ነደናል፣ ተቃጥለናልም። ዛሬም በናፍቆት እንደተቃጠልን፣ እንደ ሽንብራ እንደተረገበገብን በናፍቆት ነፍሳችን እንደዛለች መሽቶ ይነጋል።

ይህችን በለውጥ ናፍቆት፣ የተስፋ ጭላንጭል ያለህ በሚል የዛለች ነፍሳችንን አይዞሽ የሚላት፣ የውስጣችንን ጩኽት የሚመልሱ፣ ስብራታችንን የሚጠግኑልን፣ ታሪካችንን፣ ስማችንን የሚያድሱልንና ለነገ ብሩህ ተስፋ ሊያሳዩን የሚችሉ ደጋግ፣ ሁሉን በፍቅር ዓይን የሚያዩ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የኃይማኖት መሪዎችና መንፈሳዊ አባቶች እንዲኖሩን ደጋግመን ተመኝተናል። ግና እምብዛም አልተሳካልንም። እናም ዛሬም ለምድራችን ወገገው ያለው ብሩሕ ንጋት ገና የመጣ፣ የወጣ አይመስልም። ተስፋችን ያዝነው ስንለው እያመለጠን፣ ጉልበታችን ዝሎ ከዚሁ የዘመናት እንቆቅልሾቻችን፣ ያለ ቅጥ ከረዘመው የጨለማው ዘመን ዥንጉርጉር ታሪካችን፣ ጉስቁልናና ውርደት ከተሞላው አስከፊ ገጽታችን ጋር አብረን እየተጓዝን እዚህ ደርሰናል።

በዚህ ሁሉ ጭንቀት፣ መከራና ውርደት ገብቶ ነፍሱ ላዘነችበት ሕዝባችንና አገራችን መንግሥትና ባለ ሥልጣኖቻችን፣ የኃይማኖት አባቶችና መንፈሳዊ መሪዎቻችን ቢያንስ በተግባር ቢዘገዩ እንኳን ሕዝባችን ከኀዘኑ የሚጽናናበትን፣ ስብራቱ የሚጠገንበትንና ቁስሉ የሚሽርበትን፣ ፍቅርን፣ ተስፋንና ርኅራኄን የተሞላ የማጽናኛ መልእክትን እንኳን በጊዜውና በቅጡ ሊያደርሱት ሲያዳግታቸው ታዝበናል። በደቡብ አፍሪካ፣ በየመንና በሊቢያ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ ለደረሰው ግፍ መንግሥትም ሆነ ቤተ ክህነቱ የሰጡት ምላሹ የዘገየና ግራ የሚያጋባ ነው።

መንግሥቱም ሆነ ቤተ ክህነቱ በግፍ የታረዱት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ገና አላረጋገጥንም በሚል ነበር ዜናውን ቸል ለማለት የሞከሩት። የሚገርመው ነገር የሟች ቤተሰቦች ኀዘን ተቀምጠው እንባቸውን እያጎረፉ፣ በኀዘን ተቆራምደው ባሉበት የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥንና ኤፍ ኤም ሬዲዮኖቻችን ቀኑን ሙሉ ሊባል በሚችል የአስረሸ ምቺው ዘፈናቸውንና በማስታወቂያ መልእክታቸው ልባችን ሲያደሙት፣ ጆሮአችንን ሲያመግሉት ነበር የዋሉት።

በዚህ የኀዘን ቀን ”የምን ኀዘን ነው የምን ትካዜ፣ ሁሉም ያልፋል በጊዜው” የሚል እንዲህ ዓይነት ኢ-ሞራላዊና ሰብአዊነት የጎደላቸው ዘፈኖችን በማሰራጫ ጣቢያዎቻቸው የለቀቁ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎቻችን በእውን ለሰው ልጆች ሰብአዊነትና ርኅራኄ አላቸው ብሎ ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያዊነት እንዲህ ወርዷል ማለት ነው፣ መተዛዘንና መተሳሰብስ በኢትዮጵያችን ምድር እንዲህ በጠራራ ፀሐይ እንዲህ ውኃ በልቶታል ማለት ነው። በዚህች ምስኪን አገርስ ሃይ ባይ መሪ፣ መካሪና ዘካሪ የኃይማኖት አባትና የአገር ሽማግሌ የለም፣ የለንም ማለት ነውን?! በእጅጉን ያሳዝናል፣ ልብንም ይሰብራል!!

በደቡብ አፍሪካ፣ በየመንና በሊቢያ ያለቁ፣ በግፍ የታረዱ ያሉ ወገኖቻችን አይደሉም እንዴ! ምንም ዓይነት ኢሰብአዊነትና ጭካኔ ነው?! በየቤቱ በስደት ከጉያቸው የወጡ ልጆቻቸውን ዕጣ ፍንታ በማሰብ በኀዘን ተኮራምተው፣ በዋይታና በሰቆቃ ውስጥ ለገቡ ምሰኪን እናቶችስ እውን የመገናኛ ብዙኃኖቻችን ስትለቁት በነበረው አስረሽ ምቺው ዘፈኖቻችሁና የንግድ ማስታወቂያዎቻችሁ ምን መልእክት ነው ልታስተላልፉላቸው የፈለጋችሁት?!

በአገራችን ኢትዮጵያ የምትገኙ የኃይማኖት አባቶችስ በዚህ እማማ ኢትዮጵያ የኀዘን ከል ልብሳ፣ በዋይታና በልቅሶ ተጨንቃ ባለችበት ሰዓት ተዉ፣ ይህ አግባብ አይደለም የሚለውን ድምፃችሁን ካልሰማነው መቼ ይሆን ድምፃችሁ የሚሰማው?! መቼ ነው ለሰው ልጆች ሁሉ ያላችሁን ፍቅር፣ ርኅራኄና ክብር በተግባር የምታሳዩን። እናንተ የመገናኛ ብዙኃኖቻችን እባካችሁ ከሁሉምና ከምንም በፊት ለሰው ልጅ ሁሉ ፍቅር፣ ሰብአዊነትን፣ ርኅራኄንና ታማኝነትን የክቡር ሙያችሁ መለያና መታወቂያ አድርጉት።

በእውነት ይህች የሰው ልጅ ገናና ሥልጣኔ ምንጭ፣ የሰው ልጆች የነጻነት ተጋድሎ ክቡር ተምሳሌትና አጋር የሆነች፣ ለዓለማችን ታላላቅ ለሆኑ ለክርስትና ለእስልምና ኃይማኖት በሰላም ያሰተናገደች፣ እንግዳ አክባሪና ተቀባይ የሆነች አገር እንዳልሆነች ሁሉ ከሊቢያ እስከ ደቡብ አፍሪካ፣ አውሮፓ፣ የመንና መካከለኛው ምሥራቅ ድረስ ኢትዮጵያዊነት የውርደት፣ የመከራ፣ የዋይታና የሰቆቃ መገለጫ የሆኑ ያህል ተቆጥሯል። እናም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሁላችን በእፍረት ተሸማቀን፣ በኀዘን ደቀንና ተኮራምተን አለን። አቤቱ እባክህ የሆነብንን አስብ፣ ተመልከት ስድባችንንም እይ ...።”

ሰላም! ሻሎም!

ዲ/ን ተረፈ ወርቁ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!