ይቅርታ - የወያኔ ካርታ / yekerta ye tplf kartaይገረም አለሙ

1437ኛው የኢድ አል አድኻ (አረፋ) በዓል በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲከበር ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፤ በሽብር ወንጀል ተከሰው ከተፈረደባቸው የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ችግሮች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት መካከል ስድስቱ በቅርቡ የተለቀቁት በእነርሱ ጥያቄና ጥረት እንደሆነ፤ ጥያቄአቸው ምላሽ በማግኘቱና ጥረታቸው በመሳካቱ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ለመንግሥት ምሥጋና ማቅረባቸውን የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ዘጋቢ ከስፍራው ባስተላላፈው ዘገባ አሰምቶናል። ወያኔ ግዜና ወቅት እየጠበቀ የሚጠቀምባት የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ የይቅርታ ካርድ በሌላ መንገድና መልክ ተመዘዘች ማለት ነው።

ይቅርታ መጠየቃቸው ተሰምቶ ሳይፈቱ ዓመታት ያስቆጠሩ፤ በአንጻሩ ይቅርታ መጠየቅ ቀርቶ በፍርድ ቤቱ እምነት የለንም በማለት የፍርድ ማቅለያ አስተያየት አናቀርብም ያሉ ይቅርታ ጠየቁ ተብሎ ሲፈቱ፤ እንዲሁም ወራት በፈጀ የሽምግልና ጥረት የተፈቱ ፖለቲከኞች ወያኔ የጭንቁን ግዜ ሲያልፍ ክዶ፤ ሽምግልና ብሎ ነገር የለም በሕግና በሕግ ብቻ ነው የተፈቱት፤ … ወዘተ እያለ በይቅርታ ፖለቲካ ሲቆመር አይተናል ሰምተናል።

ወያኔዎች ይህን የሚፈጽሙት የይቅርታ ሥነ ሥርዓት አዋጁ ከጠረጴዛቸው ላይ ተቀምጦ ጻፋችሁኝ እንጂ አታውቁኝም፣ አወጃችሁኝ እንጂ አትተገብሩኝም እያለ እንዳያፌዝባቸው፣ ሌላውም ሰው አውቆትና ተረድቶ እንዳይጠይቅ መሳቢያ ውስጥ ቆልፈው ነው። በመሆኑም በየደረጃው በትንሽም በትልቅም ኃላፊነት ላይ ያሉ የሚሠሩት ሕጉን አውቀው ሳይሆን በአለቆቻቸው የሚታዘዙትን ነው። ከተቀዋሚውም በአብዛኛው የሚሰማው ጩኸትም ሆነ ተቃውሞ ወያኔ ከሚሠራውና ከሚናገረው በመነሳት እንጂ አዋጁን መሰረት ባደረገ አይደለም።

ይቅርታ ምንድን ነው? ማነው የሚጠይቀው የሚጠየቀውስ? መቼና እንዴትስ ነው የሚጠየቀው? የሚሉትን ጥያቄዎች ምላሽ ማወቅ ወያኔ ይቅርታን የፖለቲካ መቆመሪያ ካርታ አድርጎ እየሠራበት መሆኑን በበቂ ማረጋገጥ ያስችላል። እናም ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ የአዋጅ ቁጥር 395/1996 አንቀጾችን ለማሳየት እሞክራለሁ።

የይቅርታ ጥያቄ ማለት፤ ይህ ዐዋጅ ትርጓሜ በሚለው ክፍሉ አንቀጽ 4 “የይቅርታ ጥያቄ ማለት አንድ ፍርድ በሙሉ ወይንም በከፊል ቀሪ እንዲሆን ወይም የቅጣቱ አፈፃፀምና አይነት በቀላል ሁኔታ እንዲፈፀም የሚቀርብ ነው” በማለት ይተረጉማል። በአንቀጽ 2(3) ደግሞ “ፍርድ ማለት በወንጀል ጉዳይ በፍ/ቤት የመጨረሻ ውሳኔ የተወሰነ ዋና ቅጣት፣ ተጨማሪ ቅጣት ወይንም የጥንቃቄና ጥበቃ ውሳኔ ነው” ይላል።

የይቅርታ ጥያቄ የሚቀርበው በማን ነው? ስለ ይቅርታ ጥያቄ አቀራረብ የሚገልፀው የዐዋጁ ክፍል፤ ስድስት ንዑሳን አንቀጾች ያሉት ሲሆን፣ ንዑስ አንቀጽ 1 “በወንጀል ጉዳይ በፍ/ቤት ተከሶ የመጨረሻ ፍርድ የተፈረደበት ማንኛውም ሰው፣ የተወሰነው ፍርድ በሕግ ይቅርታ የሚያስከለክል ካልሆነ በስተቀር የይቅርታ ጥያቄውን ራሱ ወይንም በባለቤቱ፣ በቅርብ ዘመዶቹ፣ በወኪሉ ወይም በጠበቃው አማካኝነት ማቅረብ ይችላል” ይላል።

ይህ አንቀጽ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮችን መያዙን ልብ ማለት ያሻል። ይሄውም አንደኛ የይቅርታ ጥያቄው መቅረብ የሚችለው ከመጨረሻ ፍርድ በኋላ መሆኑንና ሁለተኛ ጥያቄው በማን እንደሚቀርብ በግልፅ የሚያሳይ መሆኑን።

የዐዋጅ አንቀጽ 12(2) ደግሞ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ ይቅርታ ሊደረግላቸው የሚገባቸውን ሰዎች በመምረጥ የይቅርታ ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችሉ ይገልፃል።

ይቅርታ የሚጠየቀው መቼ ነው? የይቅርታ ጥያቄ መቼ እንደሚቀርብ ግልፅ የሚያደርገውና ይህንኑ ብቻ የሚገልፀው አንቀጽ 14(1) ፍርዱ ከተሰጠ በኋላ በማናቸውም ጊዜ ሊቀርብ ይችላል በማለት በማያሻማ ሁኔታ በግልፅ አስፍሯል።

የይቅርታ ጥያቄ የሚቀርበው ለማን ነው? የይቅርታ ጥያቄ የሚቀርበው የይቅርታ ቦርድ (ኮሚሽን) ተብሎ ለተሰየመው ተቋም ሲሆን፣ የሱ ተግባርም በአዋጁ አንቀጽ 4(1) የይቅርታ ጥያቄውን በመመርመር የውሳኔ ሃሳብ ለፕሬዝዳንቱ ማቅረብ እንደሆነ በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል።

ይቅርታ የሚሰጠው ማነው? ይቅርታ መስጠትም ሆነ መንሳት ብሎም የተሰጠን ይቅርታ ማንሳት በአዋጅ ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ ሥልጣን የተሰጠው ለፕሬዝዳንቱ ነው። የሕጎች ሁሉ የበላይ የሚባለው (የሚባለው ያልኩት በተግባር የሕጎች ሁሉ የበላይ መሆን ቀርቶ የባለሥልጣናትም የበላይ ለመሆን ባለመቻሉ ነው) ሕገ መንግሥት የፕሬዝዳንቱን ተግባርና ኃላፊነት በዘረዘረበት በአንቀጽ 71 በንዑስ አንጽ 7 ላይ “በሕግ መሰረት ይቅርታ ያደርጋል” በማለት ሥልጣን የሰጠው ለፕሬዝዳንቱ ብቻ ነው።

አዋጁ ይቅርታ መስጠት መከልከልና የተሰጠን ይቅርታ ማንሳትን በተመለከተ በግልጽ የደነገገ ቢሆንም ሕግን ሊገዛበት ሳይሆን ሊያስመስልበት የሚያወጣው፣ ወያኔ ይቅርታን የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ካርድ አድርጎ ሲጠቀምበት ይህ አዋጅ ከነመኖሩም የሚያስታውስ አይመስለኝም።

በርግጥ ሕገ መንግሥትን ያህል ነገር እንዳሻው የሚደፈጥጥ ቡድን አዋጅ ቢሽርና ደንብ ቢተላለፍ፤ በፍትሕ ቢያላጋጥ ብዙ ሊገርም አይችልም። ዳኞች በስልክ ትዕዛዝ በሚፈርዱበት፣ አቃቤ ሕጎች አቃቤ ወያኔ ሆነው በሐሰት በሚከሱበትና አባይ ምስክር እያሰለጠኑ በችሎት በሚጋለጡበት፤ ዜጎች ያለምክንያት ታስረው ያለምክንያት በሚፈቱበት፤ ፖሊስ፣ ዳኛ፣ የወህኒ ቤት ኃላፊዎች፣ ደህንነት፣ ማን የበላይ እንደሆነ በማይታወቅበት፤ ፍትሕ ሳይገነዝ በተቀበረበት ሥርዓት ውስጥ የሚነገር የሚፈጸመው ሁሉ አዲስ እየሆነ ሊደንቀን አይገባም። ምክንያቱም ወያኔን በሚገባ አውቀነዋልና። ከዚህ ውጪ መልካም ነገር ከሱ መጠበቅ ካቆምን ቆይተናልና። ይልቁንስ በሕግ አምላክ ሲባል እንኳን ሰው የወንዝ ውኃ ይቆማል ይባልላት የነበረችን ሀገር ጨርሶ ሕግ አልባ ከማድረጉ በፊት መገላገያውን መላ መምታት ነው የሚሻለው።

በኢትዮጵያ የፍትሕ አስተዳደር የሚታዩ ችግሮችና የፖሊስ ነጥቦች፣ የውይይት መነሻ ሃሳቦች በጥላሁን ተሾመ ተባባሪ ፕሮፌሠርና ዲን ሕግ ፋክልቲ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚል በቀረበ 11 ገጽ ጽሑፍ (ቀንና ዓመተ ምህረት የለውም)፤ ወያኔ ምክር አይሰማም እንጂ የጽሑፉ አቅራቢ በማጠቃላያቸው ላይ እንዲህ የሚል ምክር አቅርበው ነበር።

“የፕሮፓጋንዳ ፍላጎታችንን ለማርካት ብለን ሳይሆን፣ የግል ወይንም የቡድን ዓላማዎቻችንን ለማራመድ ብለን ሳይሆን፣ ከሌሎች የሕግ ሥርዓቶች ለመፎካከርና እንዲህ ነን ለማለትም ሳይሆን፤ ታግለንለታል እየታገልንለትም ነው ለምንለው ሕዝባችን መብትና ነጻነት ብለን የፍትሕ ሥርዓታችንን እንደገና የምንፈትሽበት ጊዜ አሁን ነው። ጀንበሯ ልትጠልቅብን ሩብ ሰዓት ብቻ ቀርቷታልና።”

ስለ ይቅርታ ከተነሳ አይቀር ወያኔዎች ጠዋት ማታ ከሚምሉለትና ከሚገዘቱለት፤ ነገር ግን ከማያውቁትና ከማይገዙበት ሕገ መንግሥት አንድ አንቀጽ ላስታውሳቸው። የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28/1፤ “ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕጎች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች፤ የሰው ዘር የማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር፣ ወይም ኢሰብዓዊ የድብደባ ደርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም፤ በሕግ አውጪው ክፍልም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት ውሳኔዎች በምህረት ወይንም በይቅርታ አይታለፉም።” ይላል። ወያኔዎች ይህን አንቀጽ ሲጽፉ የደርግ ባለሥልጣን በማለት ያሰሩዋቸውን ሰዎች እያሰቡ ይመስላል። እስቲ የራሳቸውን ድርጊት ከዚህ አንቀጽ ጋር ለአፍታ ያገናዝቡት።

ለመሰናበቻ ከላይ ከገለጽኩት ከፕ/ር ጥላሁን ጽሁፍ አንድ አንቀጽ ልጥቀስ።

“ሕዝብ ከመንግሥት የሚጠብቀው ዋንኛ አገልግሎትም ፍትሕ ማስፈንን ነው። በተረፈ ገበሬው አርሶ፣ ነጋዴውም ሸቅሎ፣ ሠራተኛውም ለፍቶ ነው ሕይወቱን የሚመራው። የተለየ ችግር ካላጋጠመ በስተቀር ሕዝብ መንግሥትን አብላኝ አጠጣኝ ወይንም አኑረኝ አይለውም። ይልቁንም አስተማማኝ የፍትሕ ሥርዓት በመኖሩ ሕዝቡ ራሱ መጠቀሙ ብቻ ሳይሆን መንግሥትንም ይጠቅመዋል። ፍትሕ ሲኖር ሀገር ይለማል፣ ሀገር ሲለማም መንግሥት ይጠነክራል። ፍትሕ ሲኖር ሰላም ይሰፍናል፣ ሰላም ሲሰፍን ሕዝብ በመንግሥት ላይ አመኔታ ይኖረዋል። ፍትሕ ሲኖር ሕዝብ ይሠራል፣ ገቢም ያገኛል።ከዚህ ሂደትም መንግሥት በልዩ ልዩ መንገዶች ይጠቀማል። ሕብረተሰቡም ከሕገ-ወጦች ከሁሉም በላይ ደግሞ መረን ከለቀቀና ከጨቋኝ መንግሥታዊ አስተዳደር ይጠበቃሉ።”

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!