Ethiopian Electric Power Corporation. የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንጓድ ካፍትሌ ከአርባምንጭ

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የደርግ ሥርዓት መገርሰሱን በማስመልከት ያስተላለፉትን መልዕክት ሰምቼ ነበር። መልዕክቱ ባጭሩ እንዲህ የሚል ነበር። “የድህነት ዘበኛ የነበረው ሥርዓት ስለተወገደ ከዚህ በኋላ ጦርነታችሁ ከዘበኛው ጋር ሳይሆን ቀጥታ ከጠላቱ (ድህነት) ጋር ነው።” በእርግጥ ደርግ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ”ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!” እያለ ሕዝቡ በድህነት እንዲማቅቅ አድርጓል። ከዚህ የተነሳ የሥርዓቱ መውደቅ ብዙዎችን በደስታ አስፈንጥዟል።

ሆኖም ግን ለድህነት ዘብ የቆመ ሥርዓት የወደቀ ቢመስልም ወታደራዊውን ሥርዓት አልፈው በዴሞክራሲው ዘመን ዘውድ ጭነው የነገሡ የድህነት ዘበኞች ዛሬም ድረስ እያየናቸው ነው። ምሳሌ መጥቀስ ቢያስፈልግ “የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን” ዋንኛ የድህነት ዘበኛ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የመንግሥት መ/ቤቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን እያሳዩ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፤ ምንም እንኳ እንደ ግምገማውና እንደ ስብሰባው ብዛት ለውጡ በቂም ባይሆን።

“የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን” ግን ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ከበፊቱ እየባሰበት ሄዷል። ከዚህ በፊት በፈረቃ የሚጠፋው መብራት አሁን እንደ ልቡ ይጠፋል። ከጠፋም እስኬ ሦስት ቀን እረፍት አድርጎ ይመጣል። ይሄንን ጽሑፍ በምጽፍበት ሰዓት ብቻ ሦስት ጊዜ መብራት በመጥፋቱ ምክንያት የኮምፒዩተሬ ኦፕሬቲንግ ሲስተም (operating system) corrupt አድረጎብኝ (ተበላሽቶ) ለብዙ ሰዓታት ወደ ቦታው ለመመለስ ብርቱ ትግል አድርጌአለሁ።

መፍትሄ የለሌው ችግር፤ የመብራት ጉዳይ። ሁል ጊዜ ሪፖርቶች ሲቀርቡ የማትቀር ርዕስ አለች። “ዕቅዳችንን መቶ ፐርሰንት እንዳናሳካ ያጋጠሙን ችግሮች” ይባልና ከዝርዝሩ ውስጥ አንደኛ “የመብራት መቆራረጥ” ይባላል። ከዛሬ አስር ዓመት በፊትም ነበር ይሄ ችግር፣ ዛሬም አለ። ወደ ፊትም የሚኖር ይመስላል። “ለምን ይሆናል?” ተብሎ ሲጠየቅ፤ ሚኒስትሩ ብቅ ይልና “ልማቱ የፈጠራቸው ችግሮች” ብሎ ያርፋል። ግና የኛ ልማት ችግር መፍጠር ትቶ ችግር የሚፈታው መች ይሆን? አባይ ግድብ ይፈታው ይሆን? ግና ይሄ ችግር በእውነት የኃይል ማነስ ነው ወይስ የመልካም አስተዳደር?

ኤጭ ጠፋ ደግሞ! ሆ መጣ!! ብሎ ከመጮህ ባለፈ እስቲ መብራቱ ሲጠፋ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ አስልታችሁ ሞክሩ። የዕለት ገቢያቸውን ከመብራት ጋር በተያያዝ ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎችን አስቡ።

እስቲ ቀላል ሂሳብ እንሥራ። በአንድ ከተማ ውስጥ ያለውን የፀጉር ቤት ሥራን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።

አንድ ከተማ ውስጥ 100 የወንዶችና 100 የሴቶች ፀጉር ቤቶች አሉ እንበል። ሁለቱም ፀጉር ቤቶች በቀን 100 ብር ያገኛሉ እንበል።

የወንዶች ፀጉር ቤት = 100*100=10,000 ብር

የሴቶች ፀጉር ቤት = 100*100= 10,000 ብር

መብራት በአንድ ቀን ቢጠፋ ወደ 20,000 ብር በትንሹ ይባክናል ማለት ነው በቀን። ትላልቅ ቢዝነሶችን አስቡ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ የሚያስገቡ። በአንድ ቀን ብቻ በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ሚሊዮኖች (ቢሊዮኖች) በመብራት መቆራረጥ ምክንያት እንደሚባክኑ አስሉት። የሚቃጠሉ ዕቃዎችስ። የተጉላሉ ደንበኞች፣ ኧረ ስንቱ ተነግሮ ስንቱ ይተዋል! መብራት የለም፣ ሥራ የለም ማለት ነው!!

ታዲያ መብራት ኃይል የድህነት ዘበኛ ካልሆነ ማን ሊሆን ይችላል? ዜጎች ድህነትን ለማሸነፍ ደፋ ቀና በሚሉበት ሰዓት መብራቱ ድርግም ይልና ከድህነቱ ጎን በመሰለፍ የትግሉን ትጥቅ አስትቶ ሥራ ፈት ያደርጋል። ጠላታችን ድህነት ብቻ አይደለም። መልካም አስተዳደር እጦትም አንዱና ወንኛ ጠላታችን እየሆነ መጥቶአል።

ጓድ ካፍትሌ ከአርባምንጭ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!