Prof. Getatchew Haile ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ

መግቢያ፤

መጀመሪያ ለመግቢያ ያህል፥ “ዘመድ” የሚለውን ቃል እንዴትና ለምን እንደተጠቀምኩበት ላስረዳ። “ዘመድ” ማለት “ወገን” ማለት ነው። በእንግሊዝኛ “kin, family, tribe” ማለት ነው። በየሊቃቸው የሚመሩ የተለያዩ የመላእክት ሠራዊት “ዘመድ” ወይም “ነገድ” ነው የሚባሉት”--ዘመደ መላእክት፣ ነገደ መላእክት። ሌሎች ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው መጠሪያዎች “ቤት” (ቤተ አምሐራ)፣ “ጎሳ” (የጉጂ ጎሳ)፣ “ዘር” ናቸው። ዛሬ ደግሞ “ብሔረ ሰብ” የሚለው መጠሪያ ነግሧል።

ከነዚህ ስሞች ውስጥ አንዳንዶቹን የሚጠሏቸው ሰዎች አሉ። “ዘመድ” የሚለውን መጠሪያ የመረጥሁት ዝምድና ስለሚያስተሳስብና አምላክ የሰውን ልጅ ከመላእክት ደረጃ መመደቡን ለማስታወስ ነው። ቅዱስ ዳዊትም ጌታን “የሰውን ልጅ ከመላኮችህ ብዙ አላሳነስከውም” ይለዋል። ሰው እንደ መላእክት ክቡር ነው። መላእክት የተፈጠሩት እግዚአብሔርንና ሰውን ለማገልገል ነው። ዓለም ራሷና በውስጧ ያሉት ሁሉ የተፈጠሩት የአዳምን ልጆች ለማገልገል ነው። ክርስትና እንደሚያስተምረን አምላክ ሰው ሁኖ ለስቅላት የደረሰው የሰውን ልጅ ከጥፋት ለማዳን ነው። የመላእክት ሠራዊት የተለያዩ ቢሆኑም፥ ፍጥረታቸውና ደረጃቸው እኩል ነው። የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ሠራዊት ከሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ሠራዊት አይበልጡም አያንሱም። ዘመደ መላእክት ይተባበራሉ እንጂ አይጣሉም። አንዱ ሊቅ ልብለጣችሁ ቢል ከነሠራዊቱ ተሽቆልቁሎ እንጦርጦስ ወርዷል። ዘመደ ኢትዮጵያውያንም አይበላለጡም አይተናነሱም። የሚያበላልጠን ካለ የኛም የእግዚአብሔርም ጠላት፥ የሳጥናኤል ወዳጅ ነው። የሰውን ልጅ በሚነካ ጉዳይ ላይ በዋልን ቍጥር፥ በተለየ ልግዛ የሚሉ ባለጡንቾች፣ ማንን እንደሚነኩ ያስተውሉ። የሰው ልጅ የሚያንከባክቡት እንጂ የሚደፍሩት አይደለም።

የሞኞች ወይስ የአላዋቂዎች ጥያቄ፤

“አማራ የሚባል ዘመድ አለ ወይስ የለም?” የሚለው ጥያቄ የሞኞች ነው። ሞኝ የሚባለው ዓይን እያለው፥ ሰው ሁሉ የሚያየውን ግዙፍ ነገር የማያይ፥ ሰው ሁሉ የሚያውቀው የወልና የጋራ ዕውቀት እንግዳ የሚሆንበት ነው። ሞኝ ዛሬ የተወለደ ይመስል የሚያጋጥመውን ነገር ሁሉ ሰው ሳይጠይቅ በራሱ አይደርስበትም። እውነት እንዲህ ያለ ሰው አለ? “አማራ የሚባል ዘመድ አለ ወይስ የለም?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ካለ እሱ አንዱ ነው።

ቃል ያንድ ነገር መጠሪያ ነው። ለምሳሌ፥ “ዛፍ”፣ “ድመት”፣ “ቤት” የምንለው በነዚህ ቃላት የሚጠሩ ነገሮች ቢኖሩ ነው። ባይኖሩ ኖሮ ቃላቱም አይኖሩም ነበር። አንዳንድ ቋንቋዎች ውስጥ ያሉ ቃላት እሌላው ቋንቋ ውስጥ የማይኖሩት በእነዚያ ቃላት የሚጠሩት ነገሮች የዚያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ዘንድ ስለሌሉ ነው። ለምሳሌ bird በአማርኛ “ወፍ” ነው። ወፍ የተባለችው ፍጥረት ኢትዮጵያ ስላለች “ወፍ” የሚለው መጠሪያ ወጣላት። ለ kangaroo ግን አማርኛ የለንም። የሌለን kangaroo የሚባል ፍጥረት በሀገራችን ስለሌለ ነው። በአንጻሩ፥ መዝገበ ቃላት ውስጥ ያሉ ቃላት በሞላ ላለ እና ለታወቀ ነገር መጠሪያ የተፈጠሩ ናቸው። በመፈጠር የቅደም ተከተል ሂደት፥ የሚጠራው ነገር ይቀድማል፤ መጠሪያው ይከተላል። ውይይቱን ሰፋ ለማድረግ፥ መጽሐፋችን እንደሚለው፥ አባታችን አዳም ፍጡራኑን በዕብራይስጥ ላም፣ በሬ፣ ርግብ፣ ዋኖስ፣ ዝሆን፣ አንበሳ፣ ነምር፣ በሬ፣ ግስላ፤ ንስር፣ ወፍ ብሎ የጠራቸው ተፈጥረው ስላገኛቸው ነው።

የሌለ ነገር ስም ስለማይወጣለት መጠሪያ ስም ከሚጠራው ነገር ቀድሞ ተፈጥሮ አያውቅም። “ምናልባት አንዳንድ ነገሮች የተፈጠሩ ወይም ድንገት የተገኙ እንደሆን መጥሪያ ይሆናሉ” ተብለው የተከተቱ ቃላት ወይም ስሞች የሉም። እርግጥ አንዳንድ ሰዎች “ወንድ ልጅ የወለድኩ እንደሆነ እገሌ (አሰፋ)፣ ሴት ልጅ የመለድኩ እንደሆነ እገሊት (አልማዝ) እላታለሁ” ይሉ ይሆናል። እነዚህም ስሞች ቢሆኑ፥ ለታሰቡት ልጆች በመጠሪያነት የሚያገለግሉት መጀመሪያ ልጆቹ ከተወለዱ በኋላ ነው። ልጆቹ ካልተወለዱ ላልተወለዱት ልጆች ስሞች አይሆኑም። በአጭሩ በአንድ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ቃላት ሁሉ ላሉ ነገሮች መጠሪያ ናቸው፤ ቃል ካለ ነገር አለ።

አማራ አለ፤

እንዲህ ከሆነና “አማራ” የሚል መጠሪያ ቃል ካለ ተጠሪ አለ ማለት ነው። ተጠሪው ዘመደ አማራ ነው። “አማራ የሚባል ዘመድ የለም” ከተባለ ስሙ የተፈጠረው ማን እንዲጠራበት ነው? አማራ የሚባል ዘመድ ለመኖሩ ዋናው ማስረጃ መጠሪያ ስሙ መኖሩ ነው። አማሮች እንደ አግዓዝያን፣ እንደ ሐርላ ስማቸውን ትተውልን ሊጠፉ ይችላሉ፤ አሁን ግን አሉ።

ለአማሮች መኖር ሁለተኛው ማስረጃ፥ አማራ ነን የሚሉ ሰዎች መኖራቸው ነው። ቍጥራቸውም ቀላል አይደለም። አማራውን “አማራ ነኝ ካልክ የለህም (You do not exist)” አይሉትም። ቢሉትም ይኖራል።

ለአማሮች መኖር ሦስተኛው ማስረጃ አማራው የገዢ ዘመድ ነው እየተባለ ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም እስከ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለው የጨለማ ዘመንና የጨለማ ግዛት መጠቃቱ ነው። ይህን ጽፉፍ በማረቅበት በአሁኑ ሰዓት ሳይቀር በኢትዮጵያ መንግሥት አበረታችነት አማራው ተለይቶ እየተመታ ነው--ያለውን እንዳይኖር ለማድረግ፤ የሚያስፋፋውን ኢትዮጵያዊነት ለማቆም።

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የብዙ አዝማድ አባል ነው--የጾታ፣ የቋንቋ፣ የትውልድ። አባልነቱ በራሱ ምርጫ የመጣ ስላይደለ ሊክደውም ሊያፍርበትም አይገባም። ለምሳሌ፣ ሴት ወይም ወንድ መሆን ሊካድ አይቻልም፤ ሊታፈርበትም የማይገባው እግዚአብሔር የመረጠው ጾታ ስለሆነ ነው። ዘመድም እንደዚያ ነው። የጾታ ባሕርይ አለው፤ አማራነት፣ ጉራጌነት፣ ዶርዜነት የማይደበቅ፥ የማይካድና የማይታፈርበት ነው።

ግን ጾታና ዘመድ ትልቅ የሚለያዩበትም ባሕርይ አላቸው። ጾታ ለብዙ ከፍተኛ ጉዳይ መመዝገብ ሲኖርበት ዘመድን በተለይ በመንግሥት ደረጃ መመዝገብ ለተንኮል ነው። ጾታን ለይቶ ማሳወቅ ለጥቅም ነው፤ ለሐኪም ቤት፥ ለመጸዳጃ ቤት፣ ለጋብቻ፥ ለልብስ ሰፊ፥ ወዘተ. በመታወቂያ ወረቀት ላይ ሳይቀር በወል ሊታወቅ ያስፈልጋል። ልብስ ለመግዛት ወደልብስ ተራ ስንሄድ “የወንዶች”፣ “የሴቶች”፣“የሕፃናት” ክፍል እናገኛለን። ዘመድና ሃይማኖት ግን የግል ናቸው። በልብስ ሱቅ ውስጥ “የአማራ”፣ “የቱለማ” ፣ “የጉራጌ” . . . ክፍል አናይበትም። አንድ ኢትዮጵያዊ የየትኛው ዘመድ እንደሆነ እንኳን በመታወቂያ ወረቀት ላይ መስፈር ቀርቶ በተራ ውይይትም ቢሆን ለባህል ካልሆነ በቀር ሌላ ጥቅም የለውም። በባህል ረገድም ቢሆን፣ የአማራን ዘፈን ትግሬው ይዘፍነዋል፤ የከረዩንና የጉራጌውን ጭፈራ መንዜው ያሳምረዋል። ግን ሴት ያለ ተፈጥሮዋ ወንድ መሆን፣ አትችልም ወንዱም ሴት መሆን አይችልም።

የኢትዮጵያዊ መታወቂያ(ዎች)፤

“አማራ አለ ወይስ የለም?” ስለሚለው ጥያቄ አንድ ነገር ማወቅ ይኖርብናል። ዕውቀቱ ምናልባት ሞኙን ጠያቂ ከሞኝነት ያድነው ይሆናል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሁለት የባህል መታወቂያ (identity) ሲኖረው አማራው በተለየ መታወቂያው አንድ ብቻ ነው። ባለሁለት መታወቂያዎች አንዱ መታወቂያቸው የጎሳቸው ባህል ሲሆን ሁለተኛው መታወቂያቸው የመንግሥቱ ባህል ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በተስፋፋበት ጊዜ፥ ባህሉ (ሥርዓቱና አስተዳደሩ) በታሪክ አጋጣሚ በአስፋፊዎቹ ቋንቋ (በአማርኛ) ተገልጿል። የመንግሥቱና የተከታዮቹ መታወቂያ አማርኛ ሆኗል። የአንድ መንግሥት ባህል በአንድ ቋንቋ መገለጽ በየትኛውም ታሪካዊ ሀገር የተፈጸመ ነው። በኢትዮጵያና በሌሎችም ሀገሮች እንዴት እንዲህ እንደሆነ ታሪኩን እናውቀዋለን፤ እዚህ እንዳንተቸው ንባብ ሰልቺ ያበዛል።

የጎሳ ወይም የዘመድ ባህል ከቤተ ሰብ ይወረሳል፤ የመንግሥት ባህል ከቤተ መንግሥት ይወጣል። ሁለቱንም የሚጐናጸፉ ኢትዮጵያውያን ባለሁለት መታወቂያዎች ናቸው። የመንግሥቱ ባህል መገለጫ ወይም መታወቂያ አማርኛ ነው ብያለሁ። የጎሳን (የዘመድን) ቋንቋና የመንግሥቱን ቋንቋ (አማርኛን) የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን/ት ባለሁለት መታወቂያዎች ናቸው (ጉራግኛ-አማርኛ፤ ትግርኛ-አማርኛ፤ ሱማልኛ-አማርኛ፤ ወዘተ.)። የመንግሥቱን ባህል ብቻ ይዘው የሚጓዙ መታወቂያቸው አንድ ብቻ ሆኗል (አማርኛ ተናጋሪዎች)። የታሪካችንን ሂደት ለተመለከተው አማርኛ ተናገሪዎች ሁለት ዓይነት ናቸው፤ (ሀ) “xxx-አማርኛ”፤ (ለ) “አማርኛ-አማርኛ” ልንላቸው እንችላለን። (ሀ) “xx-አማርኛ” የምላቸው አማራነታቸው “ከጉራግኛ-አማርኛ”፣ ወይም “ከትግርኛ-አማርኛ”፣ ወይም “ከወላይታኛ-አማርኛ” ወዘተ. የሆኑትን ነው። ጥንቱ ግንዳቸው ጉራግኛ፥ ትግርኛ፥ ወላይትኛ፥ ወዘተ. ነበር፤ አሁን ግን አማሮች ሆነዋል ለማለት ነው። (ለ) “አማርኛ-አማርኛ” የምላቸው ጥንቱን በግንዳቸው አማሮች የነበሩትንና መንግሥቱን ለመከተል አዲስ ቋንቋ ማወቅ ያላስፈለጋቸውን ነው። ዛሬ እነዚህ ሁሉም (ሀ እና ለ) እኩል አማሮች ይባላሉ፤ (ሀ) የቤተ ሰብ ቋንቋ ያልወረሱ አማሮችና (ለ) የወረሱ አማሮች ።

በይበልጥ ለማብራራት፥ ዛሬ አማርኛ ብቻ የሚናገሩ ባለአንድ መታወቂያዎች ናቸው። ከእነሱ ውስጥ ብዙዎቹ እንደ ሌሎቹ ሁሉ ባለሁለት መታወቂያዎች ነበሩ (ሀ)። በታሪክ ሂደትና በዘመን ብዛት የጎሳቸውን መታወቂያ እየተዉ የመንግሥቱን መታወቂያ ብቻ ይዘው ቀሩ፤ ከባለአንድ መታወቂያዎች ጋር አንድ ሆኑ። መንግሥት አማርኛን መታወቂያው ከማድረጉ በፊት የጎሳ መታወቂያቸው አማርኛ የነበረ ኢትዮጵያውያን ነበሩ (ለ)። እነዚህ ኢትዮጵያውያን አማርኛ የመንግሥቱ መታወቂያ ስለሆነ በጎሳ መታወቂያቸው ላይ የመንግሥት መያወቂያ ባህል አልተጨመረባቸውም። ቍጥራቸውም ቀላል አልነበረም። መጀመሪያውኑ ባህላቸውን የመንግሥቱ ባህል ያደረገው የቍጥራቸው ትልቅነት ነው። ባለሁለት መታወቂያዎች የነበሩም የጎሳ መታወቂያቸውን እየተዉ የመንግሥቱን ባህል መታወቂያቸው ያደረጉም (ሀ) ጥቂቶች አይደሉም። እነዚህ በታሪክ ሂደት የመንግሥቱን ባህል መታወቂያቸው ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ዘመዶቻቸው ባለሁለት መታወቂያ የነበረ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

እነዚህን የጎሳ መታወቂያቸውን ትተው የመንግሥቱን ባህል ብቻ መታወቂያቸው ያደረጉትን ኢትዮጵያውያን በዘመድ፣ በቤት፣ በብሔር ረገድ ማን እንበላቸው? ከጥንት ተነሥተን አማሮች እንዳንላቸው ጥንታቸው አማራ አይደለም። “አማራ የለም” የሚሉ ሰዎች ዋናው ምክንያታቸው ይህ ነው። የአማርኛ መስፋፋትና የመንግሥቱ ጥንካሬ አማራ ያደረጋቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው። መንግሥቱን በማቀፍ አማራ ያልነበረው ሕዝብ አማራ ሆነ። ዛሬ በትውልድ ከአማራው ቤተሰብ በመጡ አማሮችና ከሌላ ቤተሰብ በመጡ አማሮች መካክል ምንም ልዩነት የለም። ማን ከየትኛው ጥንት (origin) እንደመጣ እንኳን አይታወቅም። ሁሉም ከየመጡበት መጥተው የመንግሥቱን መታወቂያ እኩል መታወቂያቸው አድርገዋል።

ዘመድ መለወጥ ወደ አማራነት መዛወር ብቻ አይደለም፤ ከረዩ ያልነበሩ ብዙ ኢቱዎች ከረዩ ሆነዋል። አግዓዝያንና ሐርላዎች ጠፍተዋል፤ ጠፉ የምንለው ስለጠፉ ሳይሆን አጠገባቸው ወዳለው ጎሳ ስለተዛወሩ ነው። ግን በሁለቱ የለውጥ ዓይነቶች መካከል ያለው ልዩነት ትልቅ ነው። አንዱ ለውጥ የኢትዮጵያ መንግሥት (የአገር-አቀፍ) አባል ለመሆን ሲሆን፥ ሁለተኛው ለውጥ የጎሳ (የአካባቢ-አቀፍ) አባል ለመሆን ነው። የመንግሥቱ መታወቂያ አማርኛ የሆነው የአፄ ይኩኖ አምላክ ቤተ ሰብ የመንግሥቱን ሥልጣን በትልቁ ሕዝብ (ቋንቋው አማርኛ በሆነው) ላይ ስለመሠረተ ነው።

የወያኔ መንግሥት የመንግሥቱ ቋንቋ እንዳይስፋፋ ብዙ ጥረት ሲያደርግ ይታያል። የቋንቋ አገልግሎት መግባቢያ ከሆነና አማርኛ ያንን አገልግሎት ለአፍሪቃ ቀንድ ሲሰጥ ዘመናት ከአለፉ በኋላ ዛሬ አገልግሎቱን መግታት ምን ጥቅም ለማግኘት ነው? በአማሮቹ ቀንተው እንደሆነ፥ የቋንቋ ባለቤት ተናጋሪው ግለሰብ ነው፤ ባለቤቱ ጎሳው መሆኑ ከቀረ ዘመናት አልፈዋል። ማለት፥ የአማርኛ ባለቤት የጥንቶቹ አማሮች ብቻ ከሆኑ ታሪክ ሆኖ ከቀረ ዘመናት አልፈዋል። አማሮች አሉ፤ ግን አማራ የሚባል የአማርኛ ባለቤት ከግንዱ ወጥቶ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ጥንታዊ ጎሳ ግን የለም። ያለው የመንግሥትን ባህል (ኢትዮጵያዊነትን) ብቻ ባህሉ ያደረገ “አማራ” የተባለ ዘመድ ነው።

ባይታሰብበትና ክፋት ስለሌለበት ነው እንጂ የዛሬዎቹ አማሮች “አማራ” መባልም አልነበረባቸውም። ባይገርመን ጎጃም፥ ጎንደር፥ ሸዋ፥ ወሎ በከፊል በመሠረቱ አማራ አይባሉም ነበር። “አማራ” (አምሐራ) እንደ ጎጃም፥ እንደ ጎንደር፥ እንደ ሼዋ የክፍለ ሀገር ስም ነበር። የነዚህ ክፍለ ሀገር ነዋሪዎች ሁሉ እንዴት አማራ እንደተባሉ የሚገመት እንጂ በማስረጃ የተደገፈ ዕውቀት የለንም።

ዛሬ ሁሉም ማኵረፊያ (ሌላ መታወቂያ) ሲኖራቸው፥ አማሮች ሁሉን ትተው ከተከተሉት ከመንግሥቱ (ከኢትዮጵያዊነት) በቀር ሌላ መታወቂያ የላቸውም። ወያኔዎች አንድ ቦታ ከለሏቸው እንጂ የነሱ ክልል የኢትዮጵያ መንግሥት የተዘረጋበት ነው። ኢትዮጵያ እንዳትበታተን የሚፈልጉት ክልላቸውና መታወቂያቸው ስለሆነች፥ ራሳቸውንና አባቶቻቸው የመሠረቷትን ኢትዮጵያ ከመጥፋት ለማዳን ነው። መታወቂያቸው መላዋ ኢትዮጵያ ብቻ ስለሆነች፥ በክልል መወሰንን ባለሁለት መታወቂያ ኢትዮጵያውያን ሲቀበሉት አማሮች አይቀበሉትም። የወያኔ መንግሥት የዛሬዎቹን አማሮች የሚያጠቃው ኢትዮጵያን በጎሳ ለመበታተን የሚያደርገውን ጥረት አንቀበልም በማለት እንቅፋት ስለሆኑበት ነው። የአማራው ቍጥር እንዲቀነስ፥ የተረፈው ለሀገር አንድነት ድርና ማግ መሆኑ እንዲያቆም ከየቦታው እያሶጡ አንድ ቦታ እንዲታጎር፥ ሙሉ ዘመቻ ዘምተውበታል።

የወያኔ የሐሰት ክስ፤

ወያኔዎች አማሮችን፥ “ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያዊነት የምትሉት የመንግሥቱ ባህል የናንተን ባህል ስለያዘ ነው” ይሏቸዋል። የዚህ ወቀሳ ምንጩ ታሪክ ከአለማወቅ የመጣ ወይም አንገት ለማስደፋት የታቀደ ተንኮል ነው። የሆነው ግን ወያኔዎቹ እንደሚሉት ብቻ ሳይሆን፣የተገላቢጦሽ ሂደትም አለበት። አማሮች (ሀ) ናቸው የመንግሥቱን ባህል ወስደው አማራ የሆኑ እንጂ የጥንቱ መንግሥት ባህል የአማሮች ባህል አልነበረም። መንግሥቱ ሲቋቋም የራሱ ባህል ነበረው፤ ቋንቋውም ግዕዝ ሳይሆን አይቀርም። ከላይ እንደገለጥኩት መንግሥት አማርኛን ቋንቋው ያደረገው የአማርኛ ተናጋሪው ቍጥር ትልቅ ስለነበረ ነው። እርግጥ መንግሥቱ አማርኛን ቋንቋው ማድረጉ ለአማርኛ መስፋፋት ረድቷል፤ ግን አማርኛ የተስፋፋው የመንግሥት ቋንቋ በመሆኑ ብቻ አይደለም። የመንግሥቱ እጅ እማይደርስበት ቦታ ሁሉ አማርኛ ይነገርበት ነበር። ደግሞስ መንግሥት ያቋቋሙት አማሮች ከሆኑ ያስከብራቸዋል እንጂ አያስወቅሳቸውም። እማን ላይ ቆመው በአማራው ያማርራሉ!

ወያኔዎችና አማሮች አይግባቡም፤

ወያኔዎችና አማሮች ከማይግባቡባቸው ጉዳዮች ዋናው፥ ወያኔዎች “በጎሳ ተከፋፈሉ” (አገሪቷ ትበታተን) ሲል አማሮች “አሻፈረን” ማለታቸው ነው። ከጎሳዎች ውስጥ አንዳንዶች መከፋፈሉን ይደግፋሉ። አማሮች የኢትዮጵያን በጎሳ መከፋፈል የሚቃወሙት የጎሳዎች መብት መከበርን ለመቃወም ይመስላቸዋል። ግን ሁለቱ ግንኙነት የላቸውም። እርግጥ የጎሳ ቋንቋዎች መጻፊያ እንዳይሆኑ መንግሥት የከለከለበት ጊዜ ነበረ። አንደኛ፥ ለዚያ ተጠያቂው አማሮች አይደሉም፤ ሁለተኛ፥ የጎሳዎች መብት ባይከበር አማሮች ምንም የሚያገኙት ጥቅም የለም። ጥቅም ካላገኙበት ለምን ይቃወማሉ? ሦስተኛ፥ አሁን ያ ከአለፉት ጋር አብሮ አልፏል፤ አራተኛ፥ አማርኛ ተናጋሪዎች “ባህል ይጨቆን” አይሉም፤ “የሚሉት ባህልን ማስከበር የሚቻለው ሰላምንና የሀገርን ጥንካሬ በሚያመጣ ስልት እንጂ የግድ መለያየትን፣ መበታተንን፥ በሚያስከትል መንገድ መሆን የለበትም” ነው።

አራተኛውን ነጥብ ለማብራራት፥ የጎሳውን ቋንቋና የአካባቢውን ታሪክ ከኢትዮጵያ ታሪክና ከብሔራዊ ቋንቋ ጋር ጎን ለጎን ማስተማር አማራጭ ሊኖረው የማይገባ ዘዴ ነው። መንግሥት የሚቋቋመው የሀገር ዳር ድምበር ለማስከበር፥ የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ፣ ሕዝቡ ኢኮኖሚውን እንዲያዳብር መንገዱን ለመጥረግ፣ ክፍትና ሰላማዊ ለማድረግ ነው። ወያኔዎች የመጡት ግን ይህን ሁሉ ለመቃረን ስለሆነ ይኸን አማራጭ ዞር ብለው እንደማያዩት በሥራ አሳይተውናል። አንድነትን ጠብቀን በምርጫ ጊዜ ለኢኮኖሚው እድገት የጎሳየ ሰው ይጠቅመኛል የሚል እሱን መምረጥ ይችላል።

የሀገርን ኢኮኖሚ ከማዳበር የተለየ የፖለቲካ ዓላማ ያለው ዜጋ ካለ ሌላው ሞኝ ነው። ደንቆሮም ክፉም ልንለው እንችላለን። የሀገር ኢኮኖሚ ሊዳብር የሚችለው ሕዝብ የሚቆጣጠረው መንግሥት ሲኖር ብቻ ነው። በተገላቢጦሽ እንደወያኔ የሕዝብን ሕይወት የሚቆጣጠርና ዳር ድምበር የማያስከብር መንግሥት ለኢኮኖሚው መዳበርና ለሀገሪቱ ጥቅም ማሰብ አይችልም፤ ዘበት ነው። ይህ ነቀፌታ ከብዙዎች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሊቃውንት በተነሣ ቍጥር የወያኔዎችና የደጋፊዎቻቸው መልስ፥ “በሀገራችን የምንገነባውን አታዩም ወይ? ኢትዮጵያን ለውጠናታል” የሚል ነው። ኢኮኖሚስቶች እንደሚነግሩን መጀመሪያ መገንቢያው ገንዘብ አገር በቀል አይደለም፤ ከውጪ የመጣ ነው። እርግጥ ከውጪ ገንዘብ ማምጣት መንግሥታት ሁሉ የሚመኙት ነው። ግን ገለልተኛ ተቆጣጣሪ ከሌለ ገንዘቡ ለታሰበው ሥራ መዋሉ በምን ይታወቃል? ፎቅ ቤቶች የሚያሳዩን ከውጪ የመጣውን ገንዘብ ሁሉንም አልጠጣንበትም፥ ሁሉንም የግል ግምብ ቤት አልሠራንበትም፥ ሁሉንም የግል ንግድ አላቋቋምንበትም፥ ሁሉንም እውጭ አገር ባንክ በየስማችን አልሸሸግነውም ለማለት አይደለም?

ወያኔዎችና አማሮች ከማይግባቡባቸው ሌላው ዋና ጉዳይ የዲሞክራሲና የነፃነት ነገር ነው። ወያኔዎች ለዲሞክራሲ ዋጋ እንደማይሰጡት አስመስክረዋል። በዚህም ትልቋን ኢትዮጵያ አዋርደዋታል። ውርደቱን አለመቀበላችንን በቃል ሳይሆን በሥራ ማሳየት ይኖርብናል። የአንድ ሀገር ዜጋ ለዲሞክራሲ አስተዳደር ቅድሚያ ካልሰጠ ኋላ ቀር ደንቆሮ ነው። ለዲሞክራሲ አስተዳደር በመታገል ፈንታ መገዛትን ከተቀበለ፥ ደረጃውና ክፍሉ ከመላእክት ደረጃ ወርዶ ከእንስሳት ጋር ይሆናል፤ ይነዳል፤ እንደ አጋሰስ ጭነት ያጓጕዛል። በዚያው አንጻር የሕዝብን የዲሞክራሲ ጥያቄ የሚጨቁን ገዢ የዲያብሎስ መልክተኛ ነው።

መደምደሚያ፤

ድርሰቴን በተነሣሁበት ለማጠቃለል፥ በዘር ሲታይ የአማራ ጎሳ የለም። በመንግሥት ባህል ሲታይ አለ። ወያኔዎች ስለኢትዮጵያ አንድነት የሚቆረቆረውን ሁሉ ሲያጠፉ አማራውን ለምን ተቀዳሚ ዓላማቸው እንዳደረጉት ሊገባንና በግላጭ ልንቋቋመው ይገባናል። ዓላማቸው “የኢትዮጵያ አንድነት የለም” ለማለት ነው። በሥራ “እምቢ አሻፈረኝ” እንበል። የሚገርመው አማራው የሚመታው የኢትዮጵያን አንድነት ያነገበና የአንድነት ባንዲራ የሚያውለበልብ መሆኑ እየታወቀ፥ “ኢትዮጵያ አንድ ናት” ከሚለው ወገን ውስጥ የደረሰለት ቍጥሩ ኢምንት ነው። ይኸ ብቻ አይደለም፤ አማራው ራሱ “ለአማራው ብቆረቆር ጎሰኛ እሆናለሁ/እባላለሁ፤ ለአማራው እየተቆረቆርኩ ለጎሳው የሚቆረቆረውን እንዴት እነቅፋለሁ?” በማለት ጭጭ ብሎ ራሱን ደፍቶ መርዶውን ያዳምጣል። በሞኝነት ከወያኔ ወጥመድ ገብቷል። “ኢትዮጵያ አንድ ነች፤ አትከፋፈልም” በማለቱ ለሚያጠቁት የአንድነት ወገን መድረስ ኢትዮጵያዊነት እንጂ ጎሰኝነት አይደለም። ወያኔዎች አማራውን የሚመቱት የአንድነት ኃይልን ለማዛል መሆኑ የገባቸው በቍጥር ናቸው። ግን የአማራውን ሕዝብ መሠረት ያላደረገ የአንድነትና የነፃነት ትግል አለት ድንጋይ እያለለት ቤቱን አሸዋ ላይ እንደመሠረተ ሞኝ ሰው፥ ወይም መድፉን ከካዝና ቈልፎበት በሽጉጥ እንደዘመተ ሠራዊት ይቈጠራል ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!