ግርማ ካሳ

Tesfaye Gebreab, ተስፋዬ ገብረአብ

አቶ ተስፋዬ ገብረአብ በአንድ ወቅት የኢሕአዴግ ባለሥልጣን የነበሩ ሰው ናቸው። ጥሩ ፀሐፊ ናቸው። ከኦሮሞ ብሔረተኞች ጋር የቅርብ ግንኙነት አላቸው። አንድ ወቅት እንደውም የኦሮሞ ተማሪዎች ማኅህበር ላይ የክብር እንግዳ ሆኖ ቀርበው ነበር። በዚያን ወቅት “በሞጋሳ እኔም ኦሮሞ ነኝ” ብለው ነበር። ሞጋሳ አንድ ሰው “ኦሮሞ” ባይሆንም የኦሮሞን ባህልንና ቋንቋን ከተቀበለ፣ በኦሮሞ “ሽማግሌዎች” ፍቃድ “ኦሮሞ” የሚሆንብት ሥርዓት ነው (naturalized ኦሮሞነት)።

አቶ ተስፋዬ “የአባይ ጸሐዬ ጦርነት” በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ አስነብበውናል። በጽሑፉ እነ አባይ ፀሐዬ አማራውን እና ኦሮሞውን በማጣላት በሥልጣን ለመቆየት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ነው የገለጹት። “ከመነሻው በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የፌደራል ሥርዓት ለመጠቀም ሲነሱ በህዝቦች መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ሥልጣናቸውን ለማቆየት እንደሚችሉ በማመን ነበር። በርግጥም ተጠቅመውበታል” ሲሉ፣ በሥልጣን ለመቆየት ሲባል ህዝብን በዘር ለመከፋፈል ከጠዋቱ ከጅምሩ የህወሓት አጀንዳ እንደነበረ ነው በጥሩ ቃላቶች የተነተኑልን።

እዚህ ላይ ከአቶ ተስፋዬ ገብረአብ ጋር በጣም እስማማለሁ። በርግጥም በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የፌዴራል ሥርዓት ዋና አላማ፣ የብሔረሰቦችን መብት ለማስጠበቅ ታስቦ ሳይሆን በሕዝብና በሕዝብ መካከል ግድግዳን በመፍጠር ከፋፍሎ ለመግዛት እንደሆነ ብዙዎቻችን ደጋግምመን ስንጽፍፍበትና ስንናገረው የነበረ ጉዳይ ነው።

በነገራችን ላይ አቶ ተስፋዬ ራሳቸው የህወሓት ባለሥልጣን በነበሩበት ጊዜ የዚህ በዘር የመከፋፈል እንቅስቃሴ አካል እንደነበሩ መረሳት የለበትም። በተለይም የቡርቃ ዝምታ በሚል ርዕስ የጻፉት፣ በፈጠራ ላይ የተመረኮዘ መጽሐፍ፣ ሆን ተብሎ በኦሮሞዎች እና በሌላው ማኅበረሰብ መካከል ትልቅ ጥላቻ እንዲኖር ያደረገ፣ በጣም መርዛማ መጽሐፍ ነበር። ታዲያ አሁን አቶ ተስፋዬ፣ ከወያኔዎች ጋር ሲጣላ፣ ዞር ብሎ ስለ ወያኔ ዘረኝነት ሲነግረን ማየት ትንሽ ያስቃል። ለምንኛውም፣ ግድ የለም፣ ምናልባት የአመለካከት ለውጥ ተፈጥሮ ሊሆን ስለሚችል፣ የቡርቃ ዝምታን ለጊዜው ትቼ ወደሌሎች ነጥቦች እሄዳለሁ።

አቶ ተስፋዬ ለመግለጽ እንደሞከሩት፣ ሕዝብን ከሕዝብ ለመለያየት ሆን ተብሎ ከመነሻው የተዘረጋው፣ በኦነግና በህወሓት ተግባራዊ የሆነውና በሕዝቡ ላይ በኃይል የተጫነው በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የፌዴራል ሥርዓት፣ አንዱ ውጤት “ኦሮሚያ” የምትባል ክልል መፈጠሯ ነው። ከዚያ በፊት ኦሮሚያ የምትባል ክፍለ ሀገር፣ ዞን፣ ወረዳ መንደር ኖራ አታውቅም። ኦነግን የመንግሥት አካል ለማድረግ ሲባል ብቻ የተፈጠረች ክልል ናት። ይች ክልል፣ ለአስተዳደር አመች ካለመሆኗ የተነሳ ለብዙ ግጭቶችና አለመስማማቶች ምክንያት ሆናለች።

ኦሮሚያን ጨመሮ አሁን ያሉት ዘረኛው የፌዴራል አወቃቀር የወለዳቸው ክልሎች፣ አሁን እንዳለው ቋንቋን ብቻ ሳይሆን፣ የአስተዳደር አመችነትን፣ የሕዝብ አሰፋፈርን፣ ባህልን፣ የሕዝቡ ፍላጎትን፣ ኢኮኖሚን፣ ጂዮግራፊን፣ ... ባካተተ መልኩ በጥናት፣ መስተካከል እንዳለባችው የብዙዎች እምነት ነው።

አቶ ተስፋዬ ገብረአብ ግን፣ ህወሓት/ኢሕአዴግ ለከፋፍለህ ግዛ ከመነሻው የተጠቀመበት የፌዴራል ሥርዓት እንደሆነ ግሩም በሆነ ሁኔታ ባሰፈሩበት ብዕራቸው፣ ወረድ ብለው ደግሞ፣ “የአማራ ልሂቃን ቢያንስ ኦሮሚያን እንደ ክልል በማወቅ የመቀራረቡን መንገድ መክፈት ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ በኦነግና በህወሓት በኃይል በሕዝቡ ላይ የተጫነን ፌዴራሊዝም መቀበል እንደሚገባ ይነግሩናል። በቀኝ እጅ የተገነባን በግራ እጅ ማፍረስ ይሉታል ይሄ ነው።

ሌሎች ብዙ አቶ ተስፋዬ ጫር ጫር ያደረጓቸው ነጥቦች አሉ። በተለይም “አማራ” ስላሉት ማኅበረሰብ የጻፉዋቸው ትንሽ መስመር የለቀቁ አባባሎችን አንብቢያለሁ። ብዙም እዚያ ላይ አሁን ለጊዜው አላጠፋም። ግን ሳልጠቅስ የማላልፈው አንድ ነጥብ አለ።

በኦሮሚያ የተነሳውን ተቃውሞ በመደገፍ፣ በኦሮሚያ ባሉ ትላልቅ ከተሞችና በሌሎች ክልሎች ያለው ማኅበረሰብ ተነስቷል ማለት አይቻልም። ይሄም የራሱ የሆነ ምክንያቶች አሉት። ዶ/ር መሳይ ከበደ እንደጻፉት ላለፉት 25 ዓመታት በነበረው ሁኔታ ጥርጣሬ መኖሩ (ብዙዎች በኦሮሞ አክራሪዎች ጥቃት ሲፈጸምባቸው፣ ከቀያቸው ሲባረሩ ስለነበረ ...) አንድ ምክንያት ነው። ሕዝቡ አለመደራጀቱ፣ የኦሮሞ ተቃዋሚዎች ይዘውት የነበረው አጀንዳ ሀገር አቀፍ አለመሆኑ እንደ ሌሎች አበይት ምክንያቶች ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። ሆኖም አቶ ተስፋዬ ገብረአብ፣ ምክንያቶችን ከመረዳት ይልቅ፣ የኦሮሞዎችን ተቃውሞ አልደገፉም በሚል፣ ለሌላው ማኅበረሰብ ማስጠንቀቂያ ቢጤም ለመስጠት የሞከሩበት ሁኔታ ነው ያለው።

“በቅርቡ የወያኔ ነባር አባል ከሆነ የቀድሞ ወዳጄ ጋር በጽሑፍ ስናወጋ” ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ ይሄ ወዳጃቸው “የሞጋሳ ዘመዶችህ (ኦሮሞዎች ማለቱ ነው) አይሳካላቸውም። አማሮች ለታክቲክም ቢሆን ከኛ ጋር ናቸው።” እንዳላቸው ጽፈዋል። ሌላም ማኅበረሰብ ከወያኔዎች ጎን እንደቆመ ነው ሊያመላክቱን የሞከሩት። ይሄም አንድ ማኅበረሰብ ዝም አለ ማለት አገዛዙን ደገፈ ወደ ማለት ድምዳሜ እንደመድረስ ነው። በአዲስ አበባ ከ200 በላይ ዜጎች ሲረግፉ ሌሎች አልተነሱም ነበር። ያ ማለት የባህር ዳር፣ የደሴ፣ የአዳማ፣ የአዋሳ፣ የአምቦ ህዝብ ከወያኔዎች ጋር ቆሞ ነበር እንደማለት ነው።

ወረድ ብለውም አቶ ተስፋዬ “የኦሮሞ ሕዝብ አመፁን አጠናክሮ ቀጥሎ ብቻውን የወያኔን ሥርዓት ለማስወገድ ከበቃ ለሌላው ወገን ለፀፀት የሚያበቃ ታሪካዊ ስህተት ይሆንበታል። በአብሮ መኖር ሂደት ሌሎች የሚሉትን መስማት ቀዳሚ ጉዳይ ነው። የኦሮሚያን አመጽ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም እንዲሳተፉበት ሲጠየቁ፤ ለነገ አብሮነት በማሰብ እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ ብቻውን ወያኔን ማንበርከክ አይችልም ከሚል አልነበረም። ይህን አብሮ የመታገል ጥያቄ በተሳሳተ መንገድ የተገነዘቡ ወገኖች ወያኔን ሥልጣን ላይ በማቆየቱ ረገድ የማይናቅ ድርሻ እያበረከቱ ነው” ሲሉም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የኦሮሞዎችን ንቅናቄ ሌላው መደገፍ እንዳለበት ያስጠነቅቃሉ።

ይህ አይነት አቀራረብ በጣም አደገኛ አቀራርብ ነው። የኦሮሞ ብሔረተኞች አቶ ተስፋዬ እንዳሉት፣ የኦሮሚያ ትላልቅ ከተሞችን ሳያቅፉ፣ ሌላውን ማኅበረሰብ አግልለው ለብቻው የሚያመጡት ውጤት ይኖራል ብዬ አላስብም። ላለፉት ሁለት ወራት የተደረጉት እንቅስቃሴዎች ለውጥ ካላመጡ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ነው ለውጥ የሚያመጣው? መቼም የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እንዲሰረዝ ተደርጓል የሚል መልስ አይቀርብም። ማስተር ፕላኑ በሌላ መልኩ መተግበሩ ስለማይቀር።

ይህ የተጀመረውና በጣም መቀዛቀዝ እየታየበት የመጣው የኦሮሞዎች እንቅስቃሴ በቶሎ ሌሎችን ባቀፈ መልኩ እንዲሰፋ ካልተደረገ፣ በዚህ ረገድ የኦሮሞ ልሂቃን መሰረታዊ የሆነ የአካሄድ ለውጦችን ካላሳዩ፣ በጣም ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው የሚሠራው። ሌሎችን ማስጠንቀቅና በሌሎች ላይ መዛት ሳይሆን፣ የሌሎች ጥያቄ ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ሌላው ማኅበረሰብ እኮ ላለፉት 25 ዓመታት በኦሮሚያ ውስጥ ሲፈናቀል፣ ሲገደል፣ ኦሮሞ አይደለህም ተብሎ ከሥራ ሲባረር፣ ... የነበረ ማኅበረሰብ ነው። ብዙ ግፍ የተፈጸመበት ነው። ይህ ማኅብረሰብ ቢፈራና ቢጠራጠር በጭራሽ ሊወቀስ አይገባውም።

የኦሮሞ ልሂቃን “ኦሮሚያ፣ ኦሮሚያ፣ ...” የሚሉትን አቁመው፣ ጥያቄው የመብት፣ የፍትህ ጥያቄ ነው በሚል ለምን በኢትዮጵያ የዜጎችን ጥያቄ የሚያከብር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ አይነሱም? የኦሮሞ መሬት ተወሰደ ከሚሉ (መሬቱ የሌሎች ያልሆነ ይመስል) ለምን ገበሬው የመሬት ባለቤት ይሁን አይሉም? ለምን መሬት ላራሹን በይፋ አይደግፉም? የዴሞክራሲ ሥርዓት ከተገነባ፣ ሕዝቡ ከፈለገ በአጼ ኃይለስላሴ ጊዜ የነበረው አወቃቀር፣ ከፈለገ አሁን ያለው አወቃቀር፣ ከተፈለገም ደግሞ ሌላ አዲስ የመንግሥት አወቃቀር ጠረጴዛ ላይ ቀርቦ በስምምነትና ሰጥቶ በመቀበል፣ ሕዝብ እንዲወያይበት ተደርጎ ለምን አይወሰነም? ለምን ኦሮሚያ ወይንም ሞት የሚል አቋም ይያዛል? ኦሮሚያ መኖር አለበት ካሉ በኦሮሚያ ውስጥ መሆን የማይፈልገውስ ማኅበረሰብ? 75% የሚሆነው የአዳማ ህዝብ፣ 90% የሚሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ፣ 60% የሚሆነው የጂማ ህዝብ፣ ከ80% በላይ የሚሆኑት የቢሾፍቱና የሻሸመኔ ነዋሪዎች ...?

ይልቅ የሚያዋጣው ግትርነት ሳይሆን ነገሮችን በርጋታ ተመልክቶ፣ የሁሉንም መሰረታዊ ጥያቄ በመለሰ መልኩ መግባባቶች እንዲኖሩ ማድረግ ነው። ለዚህም በዋናነት ቁልፍ ሥራ መሥራት ያለባቸው የኦሮሞ ልሂቃን ናቸው። ሌላው ማኅበረሰብ በኦሮሞ አክራሪዎች ላለፉት 25 ዓመታት ሲገፋ የነበረ ነው። ይሄንን ሕዝብ ማቀፍ የግድ ያስፈልጋል። ሌላው ይቅር በኦሮሚያ ያሉትን ትላልቅ ከተሞች ማቀፍ ያስፈልጋል። በኦሮሚያ ያሉ ትላልቅ ከተሞች ደግሞ multi-ethnic ናቸው።

ግርማ ካሳ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!