ይገረም አለሙ

ወያኔ ብአዴንና ኦህዴድ የሚባሉ አገልጋዮቸን ፈጥሮ፣ ኢትዮጵያውያንን በጎሣ አከፋፍሎና ለአገዛዙ እንዲመቸው አድርጎ አደላድሎ ለ17 ዓመታት የተዋጋለትን ዓላማውን ተግባራዊ ከማድረግ አልፎ ሃያ አራት ዓመታት በሥልጣን መቆየት በመቻሉ ሊደነቅ ይገባል። ለዴሞክራሲ እንታገላለን የሚሉ እንደ ወፍ ዘራሽ በየቦታው በቅለው ሳይለያዩ ተለያይተው፣ ሳይነጋገሩ ተጣልተው፣ የቃላት እንጂ የተግባር ሰውነት ርቆአቸው ሃያ አምስት ዓመታት ስንዝር መራመድ ባልቻሉበት ወያኔ እኩይ ዓላማውን ለማሳካት አንድነቱን አጥብቆ፣ ገመናውን ደብቆ በሌሎችም ተጠቅሞ መዝለቅ መቻሉን ማድነቅ አለመቻል የራስን ድክመት ለመቀበል አለመፍቀድ ነው።

ነገራችንን ሁሉ እንቆቅልሽ ያደረግነው እኛው መሆናችንን አምኖ አለመቀበል ደግሞ ለበሽታችን መድኃኒት ለችግራችን መፍትሄ እንዳናገኝለት አድርጎናል። ወያኔ በጎሰኛነት እየከሰስን በተቃራኒው እኛ እሱ የሚዘራውን የዘረኝነት መርዝ ወኃ እያጠጣንና እየኮተኮትን እናሳድጋለን። አንድነት የማጣታችን ምክንያቱ የመለያየታችን በሽታ ምንጩ ወያኔ ነው እያልን እኛ ግን በጎሣ መለያየቱ አልበቃ ብሎን የሚያቀራርበንን ሳይሆን የሚያለያየን በመፈለግ በተለይ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትጵያውያን ስለ ፖለቲከኞች አንድ አለመሆን እየተቆጩ፤ እነርሱ ግን የአንድ እምነት ተከታዮች ሆነው ቤተ እምነታቸውን ለያይተው ላይገናኙ አጥር አበጅተው፣ ላይደራረሱ ተማምለው ርስ በርስ ይወጋገዛሉ። ከአንዱ ደብር ሌላው ጋር ሄዶ ምኮት መፈጸምን ወንጀል አለያም ክህደት አድርገው ያያሉ። ለመሆኑ በዚህ መልክ የተገነባ ቤተ እምነት እንዲህስ እየተሆነ የሚደረግ ጸሎት ለምህረት ወይስ ለቅስፈት።

ለወያኔ አገልጋይነት ያደሩት ወገኖች ሃያ አራት ዓመት ሙሉ ሰጥ ለጥ ብለው የመገዛታቸው ምክንያትም ሆነ ተቃዋሚው ይህን ያህል ዓመት ትንሽ እንኳን ለውጥ አለማምጣቱ ሊያስመርረው ሊስያቆጨውና በእልህ ሊያነሳሳው ያለመቻሉ ነገር (ይህ የማይመለከታቸው ጥቂቶች ቢኖሩም) ለፍቺ ያስቸገረ እንቆቅልሽ ሆኗል ማለት ይቻላል። አበው ማር እንኳን ሲበዛ ይመራል ይላሉ እንኳንስ አገዛዝ። በዚህ ዘመን ግን ለወያኔ ያደሩት አገልጋዮች ሌላ ሌላው ቢቀር ንቀቱ ውርደቱ የሚሰማቸው አልሆኑም። ተቀዋሚዎቹም በህዝብ ላይ የሚፈጸመው ግድያ እስራትና ድብደባ፣ በሀገር ላይ የሚፈጸመው ታሪክን ማዛባት፣ ሉዓላዊነትን መናድና ዳር ድንበርን መሸራረፍ ብሎም ወዘተ ከማማረር ወደ ማምረር ሊያደርሳቸውና ከቃላት ተቃውሞ አውጥቶ ለተግባራዊ ትግል በአንድነት ሊያሰልፋቸው አልቻለም። በመሆኑም ዛሬም ዜጎች ይገደላሉ፣ ይታሰራሉ፣ ይሰደዳሉ አብዛኞቹ ፖለቲከኞች ግን እዛው የቃላት ጨዋታቸው ላይ ናቸው።

ኦህዴድና ብአዴን ብየ ጀምሬ የነገሮች ተያያዥነት እየጎተተ እዛና እዚህ አስረገጠኝ እንጂ በዚህች አስተያየቴ ለማንሳት የፈለግሁት በጠቅላይ ምኒስትሩ ዙሪያ የሁለቱ ድርጅቶች ሰዎች አለመኖር ለአገልጋይነት እንጂ ለቤተ መንግሥት የማይፈለጉ ወይንስ የማይመጥኑ ሆነው በሚል ስሜቴ ያጫረብኝን ጥያቄ ነው። በሟቹ ጠቅላይ ምኒስትር ዘመን ያልነበሩ የሥልጣን ቦታዎች እየተፈጠሩ የህወሓት ሰዎች በተለያየ የማዕረግ ስም ወደ ቤተመንግሥት እየገቡ አቶ ኃለማሪያምን ሲከቡ ከሁለቱ ድርጅቶች አንድም ሰው ወደዛ ቦታ ድርሽ እንዲል አልተደረገም።

ብዙ አሳይቶንና አሰምቶን ባለፈውና በታሪክ ውስጥ ልዩ ምዕራፍ በያዘው ምርጫ 97 ከተካሄዱ የክርክር መድረኮች በአንዱ ኦህዴድ እወክለዋሁ እንደሚለው የቆዳ ስፋትና የህዝብ ብዛት ተገቢ የሥልጣን ቦታ አልያዘም። ለኦሮሞ የሚገባው ምንም ሥልጣን የሌለው የፕሬዝዳንትነት ቦታ ሳይሆን የጠቅላይ ምኒስትርነቱ ቦታ ነበር የሚል ጥያቄ ተነስቶ፤ ጠቅላይ ምኒስትርነቱ የተያዘው በእውቀት በችሎታና በብቃት እንደሆነ የሚገልጽ ምላሽ ነበር የተሰጠው። ይህ ማለት በጠባቡ ሲታይ ከኦህዴድ በሰፊው ከታየ ደግሞ ከኦሮሞ ለጠቅላይ ምኒስትርነት የሚያበቃ እውቀት ችሎታና ብቃት ያለው የለም የሚል መልዕክት ያለው ነው።

መልዕክቱ በዚህ ብቻ አይወሰንም፤ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆነ በአጠቃላይ ከኢትጵያውያን መካከል መለስን የሚተካከል ለጠቅላይ ምኒስትርነት የሚያበቃ እውቀትም ሆነ ችሎታና ብቃት ያለው የለም፤ እኛ በትግላችን ደርግን ደምስሰን ያመጣንላችሁን እያጣጣማችሁ አርፋችሁ ተገዙ፤ የማይገባችሁን አትጠያቁ፣ የማይመጥናችሁን አትከጅሉ፣ የማይሆን ነገር አታንሱ ወዘተ ማለት ነው። ያ ጥያቄ ከአስር ዓመት በኋላ ዛሬ ቢነሳ የመላሾቹ መልስ ተመሳሳይ ይሆናል ተብሎ መገመት ይቸግራል። ህወሓት የፈቀደው ምንም ይሁን ማ ጠቅላይ ምኒስትር መሆን ይችላል ሊሉ ይችሉ ይሆናል ብሎ መገመት ግን ይቻላል። ጥያቄው ቢነሳና ምላሹ የገመትነው ቢሆን ደግሞ ብአዴንና ኦህዴድ በህወሓት የሚፈለጉት ለአገልጋይነት እንጂ ለወሳኝ ቦታ ሹመት አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ይሆናል። በተግባር የሚታየውም ይኸው ነው። ታዲያ ሎሌነትም ልክ አለውና ይህን ለምን ብሎ መጠየቅ የእነርሱ እንጂ የእኛ ድርሻ ሊሆን አይችልም።

በተደጋጋሚ ግዜ ስለ ወታደራዊ ከፍተኛ መኮንኖችም ጥያቄ ተነስቷል። በተለይ ጀነራሎቹ ህወሓት መሆናቸው መቼም የማይቆም ጥያቄ ነው። ታግለን ነው ለሥልጣን የበቃነው የሚሉትን፤ ብዙ ሚሊዮን ብሮች ከህዘብ ጉሮሮ እየነጠቁ የምስረታ በዓል እያሉ የሚያከብሩት፤ አንባገነኑን የደርግ ሥርዓት ደምስሰን እያሉ የሚያቅራሩት ብአዴንና ኦህዴድ ግን የጀነራልነቱ ቦታ እንደማይገባቸው አውቀው አቅማቸውን አውቀው የተቀመጡ ነው የሚመስለው። ከፕሮፓጋንዳው በስተጀርባ ያለውን ለዚህ ሰጥ ለጥ ብሎ መገዛት ያበቃቸው ምክንያት በመጠኑ የሚታወቅ ቢሆን ሃያ አራት ዓመት ሙሉ ያለምንም ኮሽታ ለማገልገላቸው፤ ይልቁንም በአደባባይ በግልጽ የሚነሱ ጥያቄዎች (ምሳሌ የጀነራልነቱ) የማይሞቅ የማይበርደው የሆነበትን ምክንያት የሚያውቁት እነርሱ ናቸው። ይህ ደግሞ ይዘገይ ይሆናል እንጂ ከእነርሱው አንደበት መስማታችን አይቀርም።

የጀነራልነቱ ሥልጣን በአብዛኛው በህወሓት ስለመያዙ ምክንያት ምላሽ ሲሰጥ የሚሰማው ከህወሓት ሰፈር ሲሆን በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከፍተኛ ድርሻ የነበረው ህወሓት በመሆኑ የሚል ነው። ይህ አባባል ብዙ ነገሮች ያሳያል። እንደው በትንሹ ቀንጭበን ብናየው የታገልነው ለሥልጣን ነው፤ እናንተንም ለዚህ ያበቃናችሁ እኛ ስለሆንን የሰጠናችሁን መቀበል ነው ያለባቸሁ፤ የህወሓቶች ወታደራዊ አመራር ችሎታና ብቃት በተግባር የተረጋገጠ ሲሆን ሌሎቻችሁ ለዚህ ደረጃ የሚያበቃ በተግባር የተፈተነ ብቃቱ የላችሁም፤ ወዘተ የሚል ነው። ራቁቱን ለተወለደ ልጅ ጥብቆ መች አነሰው እንደሚባለው፤ በህወሓት ትግል በተገኘ ድል በተመሰረተ መንግሥት ውስጥ በችሮታችን የሰጠናችሁ ቢበዛባችሁ እንጂ አያንሳችሁም ነው መልዕክቱ። ሃያ አራት ዓመት ሙሉ ማመጣጠን ያልተቻለውም በተግባር ተፈትኖ የተረጋገጠ ብቃትን በጦር ትምህርት ቤት የሚገኝ እውቀት ሚዛን ደፍቶ ሊገዳደር ስለማይበቃ ነው። የብአዴንና የኦህዴድ ሰዎችም ይህንኑ ተቀብለው የህሊናቸው ጉዳይ ባይታወቅም ቁሳዊ ፍላጎታቸውን አርክተው ሆዳቸውን ሞልተው እየኖሩ ነው።

ታዲያ ምን አዲስ ነገር ኖሮ ነው ይህ ጉዳይ እንደ አዲስ መነሳቱ የሚል ጥያቄ ቢቀርብ ተገቢ ነው። ምክንያት ሆኖኝ ይህን ያነሳሁት ብአዴንና ኦህዴድ ለጠቅላይ ምኒስትርነትም ሆነ ለሌሎች ወሳኝ የሥልጣን ቦታዎች፣ እንዲሁም ለጀነራልት የሚበቃ ሰውም ሆነ ለዚህ እንዲታጩ የሚያበቃቸው ድርጅታዊ ቁመና ባይኖራቸውምና ይህንኑ አምነው ቢቀበሉም ለጠቅላይ ምኒስትሩ አማካሪ የሚሆን ከእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ሰው እንኳን መጥፋቱ አስገርሞኝ፤ የወያኔ የንቀት ደረጃ ጥያቄ ሆኖብኝ ነው።

በአቶ መለስ መልካም ፈቃድ ወደ ቤተመንግሥት የተሳቡትና በህወሓት ፍላጎት ጠቅላይ ምኒስትር የሆኑት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፤ ከህወሓት ፍላጎትና ፈቃድ ውጪ አንዲት ጋት እንዳይራመዱ ለማድረግና አገዛዙ በአቶ ኃይለማሪያም ስም ሽፋን በህወሓት መከናወኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በተለያየ የሥልጣን ስም የህወሓት ሰዎች ወደ ቤተመንግሥት በመግባት አቶ ኃይለማሪያምን ከበዋቸዋል። ይህን ተከትሎ ብአዴንና ኦህዴድ እንዴት ለዚህ ቦታ እንኳን የሚሆን ሰው የላቸውም? ለምንስ ይሆን ህወሓት ይህን ቦታ እንኳን ሊፈቅድላቸው ያልፈለገው፣ ሎሌነታቸው እስከምን ደረጃ ቢሆን ነው፣ እነርሱስ ይህን ሁሉ አሜን ብለው መቀበላቸው ለምን፣ ወዘተ የሚል ጥያቄ ማንሳት አግባብነት ይኖረዋል።

የብአዴንም ሆነ የኦህዴድ ሰዎች በወያኔ የሚደርስባቸውን ንቀቱን ችለው፣ ውርደቱን ተቀብለው፤ አገልጋይነቱ አሜን ብለው፣ የመኖራቸው ምክንያት ከመነሻው ህወሓት ሠራሽ መሆናቸው ነው ሊባል ይችላል። እነዚህ የራሳቸው ህልውና የሌላቸው በወያኔ ፈቃድ የሚኖሩና በትዕዛዝ የሚሠሩና የሚናገሩ ሰዎች የሚመሩዋቸውን ድርጅቶች እንደ ድርጅት ተቀብለው በአባልነት አለያም በደጋፊነት ተሰልፈው በተዋረድ ውርደትን አሜን ብለው ንቀትን ተቀብለው እየኖሩ ያሉ ሰዎች ምክንያትም አጠያያቂ ነው። የሰው ልጅ ቁሳዊ ፍላጎቱን ለማርካት እስከዚህ ይደርሳል። አበው ሆዱን የወደደ ማዕረጉን ይጥላል የሚሉት እንዲህ አይነቱን አይደል።

ለሁሉም ግዜ አለው እንደሚባለው፤ የእነዚህ ሁለት ድርጅቶች ሰዎች የተሰጣቸውን እየተቀበሉ፣ የታዘዙትን እየፈጸሙ፣ በሉ የሚባሉትንም እየተናገሩ ሃያ አራት ዓመታት ቢዘልቁም አሁን ጊዜ ትልቅ ፈተና ጋርጦባቸዋል። ህወሓት በተካነበት ብልሀትም ጉልበትም እንደስከዛሬው ነገሮችን ዝም ጭጭ ማሰኘት አለመቻሉ ደግሞ የእነርሱን ፈተና አክብዶታል። ህወሓት በሚያሳያቸው መንገድ እየተጓዙ የህወሓትንም ምክር ይሁን ትዕዛዝ እየተቀበሉ ፈተናውን ሊያልፉት፣ አደጋውን ሊወጡት እንደማይችሉ የተገነዘቡ ሰዎች (ከብአዴንም ከኦህዴድም) ፈተናውን የማለፊያ መንገድ እየፈለጉ እንደሆነ እየተሰማ ነው።

የሚባለው እውነት ከሆነ ለሁሉም ልክ አለው ብለው የተጫነባቸውን ቀንበር አውልቀው ለመጣል የሚታገሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ ሎሌነት ወይንም ሞት ብለው በመጡበት መንገድ መቀጠልን የሚመርጡ ሌላ የርስ በርስ ትግል ይጀምራሉ። ይህ ጠርቶና ነጥሮ ከወጣ ሎሌነት በቃን ያሉት በህዝብ ሲደገፉ፤ በሎሌነት መቀጠል ምርጫቸው የሆነው የወያኔ ድጋፍ አይለያቸውም። ማን እንደሚያሸንፍ ደግሞ ለሦስት ወራት ያላባራውና ወያኔን ያንበረከከው በኦሮምያ እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ይነግረናል።

ሲሆን ሲሆን ብአዴንም ሆነ ኦህዴድ እንደ ድርጅት ሎሌነት በቃን፣ ነጻነት እንሻለን ቢሉ፤ ለየግል ጥቅማችን ስንል እንወክለዋለን የምንለውን ህዝብ ማስጠቃቱና ማስናቁ ይበቃል፤ ከእንግዲህ የህወሓትን የሞግዚት አስተዳደር አንሻም፣ በሕገ መንግሥት ያሰፈርነው የክልሎች ነጻነት ተግባራዊ ይሁን ወዘተ ብለው ቢወስኑ ለኃጢአታቸው ስርየትን፣ ለበደላቸው ይቅርታን ሊያስገኝላቸው ይችላል።

ይህም ካልሆነ በየግል ውሳኔ በቃን ብለው ነጻነታቸውን በመሻት የሚታገሉትንና ታሪክ ለክብር ያጫቸውን፤ በአንጻሩም ሎሌነቱ ተመችቶኛል የማይገባኝን ያገኘሁት በህወሓት ነው ብለው በአገልጋይነታቸው በመቀጠል ከውርደት አትውጡ ያላቸውን ለማየት እንበቃ ይሆናል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!