ወያኔ፤ አንድም በብልሀት - አንድም በጉልበት
ይገረም አለሙ
ወያኔዎች ለትግል በረሃ ገባን የሚሉበት ግዜ የንጉሡ ሥርዓት ፈርሶ ኢትዮጵያ ወዴት እንደምትሄድ አይደለም የት ላይ እንደቆመች እንኳን በቅጡ ያልየበት ወቅት ስለነበር፤ ለብሶት ዳርጎ ወደ ጫካ የሚያስኬድ ቀርቶ ከተማ ተቀምጦ ለማኩረፍ የሚያበቃ በደል ነበር ለማለት አይቻልም። ስለሆነም ወያኔዎች በዛን ወቅት ለትግል የተነሱት የአጼ ዮሐንስን ቤተ መንግሥት ይዘው የትግራይን መንግሥት የመመስረት ህልማቸውን ለማሳካት መንግሥት አልባው ወቅት ምቹ ሆኖ ስለታያቸው ነበር። ቢዘገይም ካሰቡት በላይ ተሳክቶላቸዋል።
ወያኔዎች “ሀ” ብለው ትግል ሲጀምሩ በሰነድ ያሰፈሩት ዓላማቸውም ሆነ፤ አመሰራረታቸውን፣ እድገትና ሂደታቸውን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች የሚሰጡት ምስክርነት ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያን በጥቅል እየገዙ ነጻ አውጪ የሚለውን ስማቸውን መለወጥ አለመቻላቸውና ተግባራቸው ሁሉ ጫካ የገቡበትን ዓላማም ሆነ የረዥም ግዜ ዘላቂ ግባቸውን ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ።
ንጉሣዊው ሥርዓት ፈርሶ የመጪው ምንነትና እንዴትነት ባልለየበት ሰዓት አጋጣሚው በአጭር ግዜ ዓላማችንን ለማሳካት ያስችለናል በማለት ከከተማ ተጠራርተው በረሃ ቢወርዱም የአጭር ግዜ ዓላማቸውን ለማሳካትም ሆነ ወደ ረዥሙ ግዜ ግባቸው የሚያደርሳቸውን መንገድ ለማመቻቸት በጥልቀት አስበውና አቅደው የተነሱ ለመሆናቸው በብልሀትም በጉልበትም የፈጸሙዋቸው ተግባሮችና አሁንም ቀሪ ዓላማቸውን ለማሳካት እየሄዱበት ያለው መንገድ ይመሰክራል። ሀያ አራት ዓመት አናሳዎቹ ብዙኃኑን ረግጠው እየገዙ ለመዝለቅ መቻላቸውም በራሱ ከመነሻው በጠንካራ መሰረት ላይ መቆማቸውን የሚያሳይ ነው።
ምንም እሰጥ አገባ የማያስከትለውና እነርሱም ሊክዱት የማይችሉት አነሳሳቸው ለትግራይ መንግሥትነት ነበር። ነገር ግን አጋጣሚው ለኢትዮጵያ መንግሥትነት አበቃቸው። እነርሱ ግን መነሻ ዓላማቸውም ሆነ መድረሻ ግባቸው ይህ አይደለምና ሀያ አራት ዓመት በሥልጣን ላይ ሆነውም የኢትዮጵያ መንግሥት ለመሆን አልቻሉም። የኢትዮጵያን መንግሥትነት በመያዛቸው ምክንያት የዘገየው ግን ሊተዉት ያልቻሉትና መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን እነርሱም ርግጠኛ ያልሆኑበትን ዓላማቸውን ማመቻቸቱን ግን አንድም ቀን ችላ ብለውት አያውቁም።
ያ የደደቢት ጽንስ ዓላማቸው በአስተማማኝ ተግባራዊ እንዲሆን ሁለት አበይት ነገሮችን ይፈልጋል። አንድ ለሚመሰረተው የትግራይ መንግሥት ዘላቂነትና መረጋጋት ኢትዮጵያዊነት የሚባለው የአንድነት አስተሳሰብ መጥፋትና ኢትዮጵያ የተዳከመችና የተበታተነች ሀገር መሆን። ሁለት አዲሲቱ ሀገር በሁለንተናዊ መልኳ ራሷን እንድትችል የቆዳ ስፋቷን ማስፋት፤ መሰረተ ልማቷን ማስፋፋት የህዝቡን ሥነልቦና መለወጥ። ወያኔዎች ይህንን በብልሀትም ሆነ በጉልበት ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት ትግሉን “ሀ” ብለው ሲጀምሩ ነው።
ገና ትግላቸው ሳይጠነክርና አቅማቸው ሳይደረጅ ሀገራዊ ዓላማና አደረጃጀት የነበራቸውን ድርጅቶች ዒላማ ማድረጋቸው በኢትዮጵያዊነት ላይ ላላቸው አመለካከት አንዱና ዋናው ማሳያ ነበር። ለዚህ ደግሞ በቀላሉ በኢህአፓና ኢዲዩ ላይ የፈጸሙትን ማስታወስ ይበቃል። ከዛም ከኢህአፓ በወጡ እንበለው በከዱ ወይንም ለወያኔ እጅ በሰጡ ሰዎች የተመሰረተውና የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ይባል የነበረውን ፓርቲ ዓላማና ስም አስለውጠው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) እንዲባል ሲያደርጉት ሀገራዊ አስተሳሰብ ፈጽሞ እንዲጠፋ ታጥቀው የሚሰሩ ለመሆናቸው በቂ ማረጋገጫ ነበር። ልብ ያለው ብዙም አልነበረም እንጂ።
ብሔር ብሔረሰቦች በአለፉት ሥርዓታት የተነፈጉትን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ለማጎናጸፍ በሚል ልብ አማላይ ስብከት በየደረሱበት ምርኮኛውንም ወዶ ገቡንም እየሰበሰቡ አባልም አጋርም ያሉዋቸውን የጎሣ ድርጅቶች በመመስረት፤ ለዓላማቸው ስኬት እንቅፋት ይሆናል ያሉትን ኢትዮጵያዊ አመለካከት የሚያጠፉበትን መንገድ ሲያመቻቹ፤ ዓላማቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁና የመሪዎቹን እኩይ ተግባር የተረዱ ሰዎች ሊከተል የሚችለውን ጥፋት ለማመላከት ቢሞክሩም፤ ብዙም ከቁብ የቆጠራቸው አልነበረም።
ይልቁንም በየጎሣችሁ ተደራጁና የሽግግር መንግሥቱ አካል ሁኑ የሚለውን ጥሪ ተቀብለው አያሌ ኢትዮጵያውያን በአጭር ግዜ በርካታ የብሔር ብሔረሰብ /የጎሣ ድርጅቶች በመመስረት፤ እያወቁም ይሁን ሳያውቁ የወያኔዎቹን መንገድ አመቻቹላቸው። (በደቡብ ብቻ በአንድ ግዜ ከ15 በላይ ድርጅቶች መፈጠራቸውን እናስታውሳለን።) አስገራሚ የነበረው ነገር በብሔራዊ ስሜት አቀንቃኝነት በሀገራዊ መፈክር አንጋቢነት ከዛም በላይ በዓለም አቀፋዊ አጀንዳ አራማጅነት ይታወቁ የነበሩ ትላልቅ የተባሉ ሰዎች ሳይቀሩ የጎሣ ድርጅት መስርተው የሽግግሩ ፓርላማ ውስጥ ለመታየት መብቃታቸው ነበር።
ይህ የኢትዮጵያዊነትን ቡሉኮ እየገፈፉ የየጎሣውን ነጠላ እያለበሱ የማስጨፈር መላው በብዙ መልኩ የሰመረለት፤ ወያኔ የሚዘፍኑትን ዘፈን ግጥምና ዜማ ሳይቀር እየሰጠ ሁሉንም በተናጠል ማዘፈን ቻለ። ይህም ብቻ አይደለም፤ ያለፈ ታሪክ እየመዘዘ ለእያንዳንዱ የቤት ሥራ በመስጠት የኢትዮጵያ ልጆች ርስ በርስ እንዲወጋገዙና ሆድና ጀርባ እንዲሆኑ ለማድረግ ቻለ።
ወያኔዎች ይህን በማድረግ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ መሰረታቸውን ለማጠናከር ያስቻላቸውን ኢኮኖሚያዊ እቅዳቸውንም አሳክተዋል። በድርጅት ከህወሓት በክልል ከትግራይ በስተቀር ሌሎቹ በተሰጣቸው አጀንዳ ተጠምደው በጎሣ ፖለቲካ ሰክረው እንወክለዋለን የሚሉትን አካባቢ እንኳን በንቃት ማየት ባለመቻላቸው፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የነበሩና የወያኔን ቀልብ ያማለሉ ንብረቶች ያለምንም ተቃውሞና ሀይ ባይ የተቻለው በቀን በጠራራ ፀሐይ ሌላው በለሊት መብራት እያጠፋ ተጓጓዘ።
በወያኔ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ልብ አማላይ ስብከት ተታለውም ይሁን ከመጀመሪያው በውስጣቸው የነበረው የጎሠኝነት ስሜት አመች ግዜ ሲያገኝ ፈንቅሎአቸው ይሁን ባይታወቅም፤ ድርጅት እየመሰረቱ በወያኔ የጎሠኝነት መስመር የገቡ ሰዎች አንዳንዶቹ ብዙም ሳይቆዩ ከሰሙ፤ እስከዛሬ የዘለቁትም ቢሆኑ ለወያኔ ከመጥቀማቸው ባሻገር ይህ ነው የሚባል ያስገኙት ፋይዳ የለም።
ምንም ተባለ ምንም ተደረገ ግን ኢትዮጵያዊነት እንዲህ እንደ ዋዛ የሚጠፋ ባለመሆኑ፤ ወያኔ አጠፋሁት ብሎ እፎይ ማለት በጀመረ ማግስት መልሶ እያንሰራራ፤ ይሄው እስከ ዛሬ እንቅልፍ እንደነሳው ይገኛል። ወያኔ ከደደቢት ሲነሳ ካነገበውና ሀያ አራት ዓመታትም ለተግባራዊነቱ እየሠራ ካለው ዘላቂና የረዥም ግዜ ግቡ አንጻር፤ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ሊታረቅ የሚችል አይደለም። ኢትዮጵዊነትም በየዘመናቱ ከውስጥም ከውጪም የተቃጣበትን አደጋ ሁሉ ተቋቁሞ ለመዝለቅ የቻለ እንደመሆኑ መጠን፤ መቼም ሆነ በማንም የሚጠፋ አይደለም። ይህም ሆኖ ወያኔ በበረሃ ታጋይነቱም ሆነ፤ በከተማ መንግሥትነቱ ዘመን የፈጸማቸው ተግባራት ሁሉ ኢትጵያዊነትን ማጥፋት እንዳላስቻሉት ከራሱ ተሞክሮ ትምህርት አግኝቶ፤ ከእኩይ ተግባሩ ሊገታ አልቻለም። በመሆኑም ግዜ እየጠበቀ ለደደቢቱ ዓላማው ስኬት ሲል በብልሀትም በጉልበትም በሚፈጸመው ተግባር ህዝብ እየተጎዳ ነው። ከዚህ የማያባራ ጉዳት ለመዳን የህዝቡ ምርጫ የሌለው አማራጭ አንድ ነው። እሱም ከወያኔ አገዛዝ መገላገል፤ አለያም ወያኔ መቼም በምንም ሊያጠፋው የማይችለውን ኢትዮጵያዊነት ለማጥፋት በየግዜው በሚፈጽማቸው ኢ-ሰብአዊ ተግባራት እየታሰሩ፣ እየተደበደቡ፣ እየተገደሉ፤ በአንዱ ሲደርስ ሌላው እያለቀሰ ተራውን እየጠበቀ መኖር። ሁለተኛው የሚመረጥ አማራጭ አይመስለኝም።
ለኢትዮጵያ መንግሥትነት መብቃቱ የደደቢት ዓላማውን ሊያስተወው ያልቻለው ወያኔ፤ በኢትዮጵያ መንግሥትነት ስም የያዘውን ሥልጣን የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችለውን ምቹ ሁኔታ ለማመቻቸት መጠቀሚያ ማድረግ የጀመረው፤ ገና ወንበሩ ሳይደላደል እንደነበረ አሌ የሚባል አይደለም። ይህንንም የቻለውን በብልሀት በዚህ መንገድ ያልሆነለትን ደግሞ በጉልበት ተግባራዊ እያደረገ ከዛሬ ደርሷል። አሁንም ቀጥሏል።
ወያኔ የደደቢት ውጥኑን ለማሳካት ከተጠቀመባቸው ብልሀቶች አንዱና ዋናው በማር የተለወሰ መርዝ የሆነው ፌዴራላዊ አወቃቀር ነው። የፌዴራል የመንግሥት ሥርዓትም ሆነ የመሬት አከላለል የአሀዳዊ ሥርዓት ደጋፊ ከሆኑ ሰዎች በስተቀር በአብዛኛው ሰው የሚደገፍ በመሆኑ፤ ወያኔ ከላይ ሲታይ ለሀገርና ለህዝብ በማሰብ የመረጠው በሚመስል ሁኔታ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲሆን በሕገ መንግሥት እንዲሰፍር ያደረገው ብዙም ተቃውሞ ሳይገጥመው ነበር። ፌዴራል አወቃቀርን የፈለገው የተነሳበትን ዓላማ ገቢራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟያነት፤ ብሎም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በማለም እንጂ ለሀገርና ለህዝብ አስቦ ባለመሆኑ፤ አከላለሉ በቋንቋንና በብሔረሰብ/በጎሣ ላይ ብቻ ተመስርቶ የሚከናወን እንዲሆን የሚያደርግ ሕገ መንግሥት አጸደቀ። ይህ አዋቃቀር የወያኔን ፍላጎት የሚያሳካ እንጂ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የማይሆን ለመሆኑ የደቡብ ክልል የሚባለውን ማየት ብቻ ይበቃል። ፌዴራላዊ መንግሥትነትን ደግፈው ቋንቋና ብሔርን መስፈርት ያደረገውን አወቃቀር የተቃወሙ የመኖራቸውን ያህል፤ ደጋፊዎችም ስላልታጡ የፌዴራል አወቃቀሩን በሕገ መንግሥት ለማስፈርም ሆነ ተግባራዊ ለማድረግ ወያኔ ብዙ አልተቸገረም።
በመሆኑም በፋኖነት ዘመኑ የትግራይን የቆዳ ስፋት ለማስፋት በኃይል የያዛቸውን የጎንደርና የወሎ ቦታዎች በዚህ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ መሰረት ከማጽናቱ በተጨማሪ፤ ሲጎመዥባቸው የነበሩ ለም መሬቶችን በሙሉ የትግራይ ክልል ብሎ ወደሰየመው ለመጠቅለል ቻለ። እንዲህ በብልሀት በሕገ መንግሥት ሽፋን ወደ ትግራይ የተከለሉ ዜጎች፤ እኛ ጎንደሬ/አማራ እንጂ ትግሬ አይደለንም ብለው፤ ትግሬ ናችሁ ለመባላቸው የተጠቀሰባቸውን ሕገ መንግሥት ራሱኑ ለመከራከሪያነት ጠቅሰው፤ ይህን መሰል ጉዳይ የማየት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ለተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤት እስከ ማለት ቢደርሱም፤ ጩኸታቸው በተኩላ አደባባይ የበግ አቤቱታ እንዲሉ ሆኗል። ሕገ መንግሥቱ ወያኔ ሲጠቀምበትና ህዝብ ጥያቄ ሲያነሳ አፈጻጸሙ የተለያየ በመሆኑ፤ ሕግ አለ ብለው በሕግ ተማምነው ከጎንደር አዲስ አበባ ዘልቀው አቤት ላሉ ወገኖች ለጥያቄአቸው መልስ ሊያስገኝላቸው ቀርቶ ከጥቃት ሊታደጋቸው ባለመቻሉ፤ ዓላማና ፍላጎቱን በብልሀት ካልሆነም በጉልበት ተግባራዊ በሚያደርገው ወያኔ እየታደኑ ነው። ሕገ መንግሥቱ በተግባር የተጻፈበትን ወረቀትና ቀለም ያህል እንኳን ዋጋ የለውም የተባለውም እንዲህ በመሆኑ ነው።
ወያኔ ዓላማውን ተፈጻሚ ለማድረግ አስቀድሞ በብልሀት፤ ብልሀቱ ካላዋጣ በጉልበት፤ ይሄ አልሆን ካለ ደግሞ በሕግ መሣሪያነት ጉልበት ከሥርዓት ይሉት ዘዴ የሚጠቀም በመሆኑ ከመነሻው ነገሮችን ለዚሁ ያመቻቻል። በመሆኑም ወደ ትግራይ ሊጠቀልላቸው ያሰባቸውን ቦታዎች አስመልክቶ በብልሀትም በጉልበትም ምን ማድረግ እንዳለበት ገና ደደቢት ሳለ ነው ያሰበው ያቀደውና የተዘጋጀው። ይህ እቅዱንም ነው በፋኖነት ዘመኑም ሆነ በመንግሥትነት ግዜው ተግባራዊ ያደረገውና አሁንም እያደረገ ያለው።
ከእነዚህ ሥራዎች አንዱና ዋናው ከላይ የተጠቀሰው ቋንቋና ብሔርን መሰረት ያደረገው የፌዴራል አዋቃቀር ሲሆን፤ ሌላው ተቀናሽ ያላቸውን ታጋይ ተጋዳላዮች ቦታው ላይ ማስፈር ነው። እነዚህ እነ መለስን ቤተመንግሥት በማድረስ ተልዕኮአቸው የተጠናቀቀና ከታጋይነት ወደ ቀደሞ አራሽነታቸው እንዲመለሱ የተደረጉ ዜጎች በቦታው የሰፈሩት ከነጠመንጃቸው በመሆኑ፤ የተሰጣቸውን ለም መሬት አርሰው ከሚያገኙት ጥቅም በላይ ለወያኔ የሚሰጡት ጥቅም ብዙ ነው። ወሰናችን ተከዜ ነው በማለት የሚያስቸግሩትን እያስፈራሩ ጸጥ ማሰኘት፤ በፍራቻ ለማይበገሩት ደግሞ ጠመንጃቸውን ሥራ ላይ ማዋል። ይህን ደግሞ ሰሞኑን በተካሄደ ሰልፍ ላይ የተሰሙት ታውቁናላችሁ እናሳያችኋላን ወዘተ መፈክሮች በቂ ገላጮች ናቸው። ሌላው የወያኔ ርምጃ ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ሰዎችን በመውሰድ በወረራ በተያዘው መሬት ላይ ማስፈሩ ነው። ተቃውሞ በርትቶ ትግሉ ገፍቶ በብልሀትም በጉልበትም የማይገታ ከሆነና ወያኔ በመጠባቢቂያነት ወደሚያስበውና አስቀድሞ የተዘጋጀበት ወደሚመስለው ህዝበ ውሳኔ ቢያመራ፤ የተጋዳላዮቹም ሆነ የሰፋሪዎቹ ውሳኔ ምን እንደሚሆን የአደባባይ ምስጢር ነው።
ከሀገር ጥቅም አንጻር ሳይሆን ከራሱ ዓላማ ስኬት አንጻር አርቆ የሚያስበውና የሚሠራው ወያኔ፤ ልብ አማላዩን የፌዴራል ሥርዓት ለራሱ ዓላማ ማመቻቻ የተጠቀመበት በመሬት አከላል ብቻም አይደለም። አንድ ቀን መንግሥት ሊሆንባት የሚያዘጋጃትን ክልል በቀሪው የኢትዮጵያ ሀብት በሁለንተናዊ መልክ ለማሳደግም ተጠቅሞበታል። የፌዴራል ሥርዓት በሚፈቅደውና በሕገ መንግሥቱም ውስጥ በተጻፈው መሰረት ክልሎች ሙሉ ነጻነት ቢኖራቸው እቅዱን ገቢራዊ ማድረግ እንደማይችል ቀድሞውንም የተረዳውና የዘየደው ወያኔ በአደባባይ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን የማስተዳደር መብት እስከ መገንጠል ሕገ መንግሥታዊ እውቅና እንዳገኘ እየለፈፈ በተግባር ግን የየክልሎቹ ሹማምንት ስሙንና ወንበሩን ከመያዝ የለፈ ሥልጣንም ነጻነትም እንዳይኖራቸው አድርጎ፤ ያልተጻፈ አሀዳዊ ሥርዓት እያራመደ የሁሉም ጠቅላይ ገዥ ራሱን አድርጎ ይሾማል፣ ይሽራል፣ ሀብት ይዘርፋል።
ወያኔ ፍላጎቱን በብልሀት ለመፈጸም እንዲያስችለው በማር የተለወሰ መርዝ ሲያቀርብልን መርዙን ባለማየት ለእኩይ ዓላማው ስኬት ብዙዎች ተባባሪ ሆነዋል፤ ብዙችም በዝምታ ተመልክተዋል። ነገሮች ካለፉ በኋላ መርዙን በማየት የሚሰሙ ጩኸቶችም ሆኑ የሚደረጉ ትግሎች በብልሀት ያሳካውን በጉልበት ለማስጠበቅ በሚወስደው ርምጃ መስዋዕትነት እንጂ ድል ሊያስገኙ አልቻሉም።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የተለየ የሚመስል ነገር ይታያል። ወያኔ በማስተር ፕላን ስም በብልሀት ያሰበው የመሬት ወረራ የገጠመውን ተቃውሞ፤ በጉልበት ሰጥ ለማድረግ ኢሰብዓዊ ተግባር ፈጽሞ አልሳካ ሲለው፤ የለመደውን በሕግ ሽፋን ጉልበት ከሥርዓት የመጠቀም አካሄድም ሞክሮ ውጤት ባለማግኘቱ፤ ማስተር ፕላኑን ሰርዣለሁ ብሏል። ይህን ብሎ ግን በባልሥልጣኖች አንደበት የሚነገረውም ሆነ በነብሰ ገዳዮቻቸው የሚፈጸመው ድርጊት እንዲሁም ኦህዴድን በወያኔ ታማኞች ለማጠናከር የተያዘው ርምጃ፤ ወያኔዎች እንዴት ያሰብነውን ማሳካት ያቅተናል በሚል እልህ ውስጥ ያሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ታክሲ አሽከርካሪዎች ባካሄዱት የአንድ ቀን ሥራ ማቆም አድማ፤ መንገድ ትራንስፖርት ያወጣውን ደንብ ለሦስት ወር አዘግይተነዋል የሚል ምላሽ ተሰምቷል።
ጫካ ሆኖም ሆነ ቤተመንግሥት ተቀምጦ የደደቢት ህልሙን በብልሀትም በጉልበትም ተግባራዊ ሲያደርግ ለኖረው ወያኔ፤ ማስተር ፕላኑን ሰርዣለሁ ማለቱ፣ የመንገድ ሥነ ሥርዓት ደንቡንም ተግባራዊነት ለሦስት ወር አራዝሜአለሁ ማለቱ የህዝብ ትግል ውጤት መሆኑ ባይካድም፤ ወያኔ የባህርይ ለውጥ አምጥቶ ነው ማለት ግን አይቻልም። እንዲህ በማሰብ መዘናጋት ከተፈጠረ ይህን ውጤት ያስገኘውን ትግል ማክሸፍ፣ ታጋዮችንም ማስበላት ይሆናል።
ወያኔ ከዓላማው ፍንክች ያለበት ግዜ የለም። ቅንጅቶችን ከፀሐይ በታች ባለ ማናቸውም ጉዳይ ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ ብሎ ትጥቃቸውን (የህዝብ ኃይል) ካስፈታ በኋላ፤ እኔ በመረጥኩት አጀንዳና በምለው መንገድ ብቻ ነው መነጋገር የሚቻለው ማለቱ የሚዘነጋ አይመስለኝም። ስለሆነም በብልሀትም በጉልበትም ያሰበውን ከማሳካት ወደ ኋላ የማይለው ወያኔ ሸብረክ ያለ የሚመስለው ግዜ ለመግዛት፣ ሁኔታዎችን ለማመቻቸትና ወጥመዱን ለማጥበቅ እንደሆነ በመረዳት፤ በማስመሰያ ድርጊቶች ሳይታለሉና ሳይዘናጉ ለተጨባጭ ለውጥ መታገል ያስፈልጋል።
ወያኔ የደደቢት ህልሙን ለማሳካት ብልሀትን ከጉልበትን፣ ጉልበት ከሥርዓትን እንደ ሁኔታው እያማረጠም እያደባለቀም እንደሚጠቀመው ሁሉ፤ በለውጥ ኃይሉ በኩል ለትግሉ ከግብ መድረስ አንድና አንድ መንገድና አማራጭ ብቻ የሚጠቀም ሳይሆን፤ መስዋዕትነቱን ቀላል ድሉን ቅርብ ሊያደርጉ የሚችሉ ግንባር ቀደም ታጋይ አታጋዮችን፣ ከአደጋ የሚከልሉ፣ ወያኔ ጉያ ውስጥ እሳት ማቀጣጠል የሚያስችሉ አማራጭ ስልቶችንና ተግባራዊ የማድረጊያ መንገዶችን መተለም ያስፈልጋል። በወያኔ ብልሀት መበለጥ፤ በጉልበት ለሚያደርገው መንበርከክ፤ በሕግ ሽፋን በሚፈጽመው ውንብድና መታለል እንግዲህ ያበቃ ይመስላል። ቢሆንም ግን ወያኔ እስካሁን ካጠፋው ይልቅ ወደፊት ሊያጠፋው የሚችለው ለበለጠ ተጠያቂነት እንደሚዳርገው ተረድቶ፤ እርቅ የሚፈልግ፣ አድራጎቴን ህዝብ አልወደደውም ብሎ ከደደቢት ህልሙ የሚላቀቅ ሳይሆን፤ ሸብረክ ያለ እየመሰለ፣ የህዝብን ጥያቄ ተቀብያለሁ እያለ በብልሀትም በጉልበትም ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ከጥፋት የማይመለስ በመሆኑ፤ ከነጻነት ወዲህ ማዶ የሚኖር መዘናጋት ተራ በተራ መበላትን ያስከትላል።