ይገረም አለሙ

People has been taken by federal police in south Ethiopia, Sumra. በደቡብ ኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሱምራ ብሔረሰብ አባላትን በገመድ አስሮ እየደበደበ አሰቃየ

ሰሞኑን በደቡብ ኢትዮጵያ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የተፈጸመን የባሪያ ፍንገላን ዘመን የሚያስታውስ ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚያሳይ ፎቶ በማኅበራዊ ድረ-ገጽ ተሰራጭቶ አጀኢብ ጉድ ብለናል። ነገሩ ትናንትን እየረሳን ዛሬ ለሚያጋጥመን ነገር አዲስ እየሆንን ጉድ ጉድ ለምንለው ለእኛ ነው እንጂ አዲስነቱ ለወያኔ ከበረሃ ጀምሮ አብሮት የኖረ ተግባሩ ነው።

አይደለም ሥልጣኑን ሊነጥቁት በተቃውሞ የተሰለፉ፣ እኩይ ድርጊቱን እያጋለጡ ማንነቱን ፀሐይ የሚያሞቁ፣ ሃሳብ ዕቅዱን እየተቃወሙ ጉዞውን የሚያደናቅፉ ቀርቶ፤ የህወሓት አባል ሆነው ስህተት የጠቆሙ፣ የዓላማቸውን መስመር መሳት የገለጹ፣ የመሪዎቹን እኩይ ተግባር የነቀፉ ወዘተ ምን እንደተፈጸመባቸው የዓይን ምስክር የሆኑ ሰዎች ሲናገሩ ሰምተናል፣ ጽፈው አንብበናል። ባዶ ምንትስ ይባሉ በነበሩት እስር ቤቶች በውልደታቸው ትግሬ፣ በድርጅታቸው ህወሓት የነበሩ ዜጎች ሳይቀሩ ምን አይነት ኢሰብዓዊ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው እነ ገብረመድህን አርኣያ ደጋግመው የነገሩን ነው። ዛሬም በተለያየ የሥልጣን ስም ተቀምጠው አረመኔያዊውን ድርጊት የሚፈጽሙ፣ የሚያስፈጽሙት እነዛ የበረሀው ሲዖል እስር ቤቶች ኃላፊዎች የነበሩቱ ናቸው።

ለሥልጣናቸው የሚያሰጋ፣ ያሰቡ ያቀዱትን ተፈጻሚ እንዳያደርጉ እንቅፋት የሚሆን፣ ማንም ሆነ ከየትም ከማጥፋት የማይመለሱት ወያኔዎች (በተለይም አቶ መለስ) ዘር ኃይማኖት ሳይለዩ አስሮ ማሰቃየቱን፣ አፍኖ መሰወሩን፣ ገድሎ መጣሉን ብሎም ርስ በርስ ማገዳደሉን አብይ ተግባራቸው አድርገው የኖሩ ለመሆናቸው ብዙ እጅግ ብዙ መረጃዎችን መዘርዘር ይቻላል።

የህወሓት ቀኝ እጅ የነበረው የደህንነቱ ሹም ክንፈ፤ የአግልግሎት ግዜው ሲያበቃ እንዴት እንዳስገደሉትና የግድያ ትዕዛዙን በፈጸመው የዋህ ታዛዥ ላይ ያደረጉትን የምናውቅ፤ በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ የሚፈጽሙት አረመኔያዊ ተግባር ለምን አዲስ እንደሚሆንብንና እንደሚገርመን ራሱ የሚገርም ነው። ለህይወታቸው መድኅን፣ ለሥልጣናቸው ዘብ ሆነው የኖሩ ሰዎቻቸውን ለማጥፋት የማይመለሱ ሰዎች፤ አንገዛም ባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽሙት ኢሰብዓዊ ድርጊት ሁሌም አዲስ የሚሆንብን እኛ ትናንትን በመርሳት በሽታ በመለከፋችን፤ አለያም ሞኝ የሰማ/ያየ ዕለት እንደሚባለው እየሆነብን እንጂ፤ ድርጊቱ ለወያኔ አዲስ አይደለም። እንደውም ትናንትን የመርሳት ችግራችን ከእባብ እንቁላል ርግብ አይጠበቅም የሚለውን አባባል አስረስቶን፤ የተቃውሞአችን እንዴትነትና የጩኸታችን ምንነት ከወያኔ የባህሪው ያልሆነ ነገር የምንጠብቅ ያስመስለናል።

መቅረጸ ድምጽም ሆነ ምስል ያልደረሰባቸው፣ የዓይን ምስክርም ተገኝቶ ይፋ ያላደረጋቸው ብዙ እጅግ ብዙ ዘግናኝ አረመኔያዊ ድርጊቶች በወያኔ ለመፈጸማቸው በመረጃ ከተረጋገጡት ድርጊቶቹ ተነስቶ መገመት ይቻላል። እነዚህ ሰዎች ለሥልጣን የበቁት የመረጃ ማስተላለፊያው ጥበብ እንዲህ ባለልተስፋፋበትና ባልተራቀቀበት ዘመን ቢሆን፤ ምን ያደርጉ ነበር ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ። የሚሠሩት ብቻ ሳይሆን በር ዘግተው በምስጢር የሚነጋገሩት ድምጽ ከምስል እየሾለከ ለዓለም ህዝብ ዓይንና ጆሮ ሲበቃ የማያስደነግጣቸው፣ የማያሳፍራቸውና የማያስፈራቸው (ለነገሩ ማንን ሰው ብለው) ወያኔዎች በድብቅ የሚሠሩት ሁሉ ተደብቆ የሚቀር ቢሆን፤ የአረመኔነታቸው መጠን፣ የክፋታቸው ደረጃ፣ የአገዛዛቸው ግዞት እስከምን ይደርስ እንደነበር መገመት አይገድም።

ጎምቱ ጋዜጠኞች ውሻ ሰው ነከሰ ዜና አይሆንም፤ ሰው ውሻ ቢነክስ ግን ትልቅ ዜና ነው ይላሉ። የአባባሉ ምንነት ግልጽ ነው። ውሻ ሰው መንከሱ የተፈጥሮው፣ የባህሪው፣ የሚጠበቅበት ተግባሩም ስለሆነ ነው ዜና የማይሆነው። ሰው ግን ውሻ ቢነክስ ያልተለመደ ብቻ ሳይሆን የማይጠበቅና የማይገመት አዲስ አስገራሚ ክስተት በመሆኑ ነው ትልቅ ዜና የሚሆነው።

ወያኔም ማሰሩ፣ መግደሉ፣ ማሰቃየቱ፣ መዋሸቱ፣ ማታለሉ፣ ሰው በሀሰት መወንጀሉ ወዘተ ለሥልጣን የበቃበትና ሀያ አራት ዓመታትም ለመግዛት የቻለበት የተፈጥሮ ባህሪይው እና ተግባሩ በመሆኑ፤ በዚህ መልክ የሚፈጽማቸው ድርጊቶች ለጋዜጠኞች ዜና ሊሆኑ ቢችሉ እንኳን፤ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ክስተት የሆኑ ያህል ሊያስገርሙን፣ ሊያስደንቁንም ሆነ ሊያስደነግጡን አይገባም ነበር። ምነው ቢሉ እየረሳናቸው ካልሆነ በቀር አብረውን ያሉ ናቸውና።

ይልቁንስ ከወያኔ አንጻር ለመገናኝ ብዙኀን ትልቅ ዜና ሊሆን ከኢትዮጵያውያን አልፎ የኢትዮጵያን ጉዳይ (ለራሳቸውም ዓላማም ሆነ ለህዝቡ ጥቅም ሲሉ) በቅርብ ለሚከታተሉ ዓለም አቀፍ ግለሰቦች ቡድኖችና መንግሥትታ አስገራሚ ክስተት ሊሆን የሚችለው።

 • • ሀያ አራት ዓመት የተጓዝንበት መንገድ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እየወሰደን እንዳልሆነ ስለተገነዘብን መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል ቢባል፤
  • ለዘመናት አብረውን የዘለቁ ሀገራዊ ችግሮችን እየቆፈሩ አዳዲስ ልዩነቶችን መፍጠር የዛሬ መንገዳችንንም ሆነ የነገ ግባችንን ከማሰናከሉም በላይ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማቆየት አስጋቸሪ የሚያደርጉ በመሆናቸው በእርቅ እልባት ሰጥቶ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበናል ቢባል፤
  • የገደለ ያስገደለ፣ የሰረቀ የተባበረ፣ በህዝብ ሀብት የከበረ፣ ከሕግ በላይ ያደረ፣ ወዘተ ለፍትህ ቀርቦ የሕግ የበላይነትን በተግባር ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ርምጃዎች መታየት ቢጀመሩ፣
  • የመገናኛ ብዙኀን ሠራተኞች አፋሽ አጎንባሽ መሆናቸው ቀርቶ እውነትን አነፍናፊ፣ የባለሥልጣናትን ፊት እያዩና ትንፋሽ እያዳመጡ የሚሠሩ ሳይሆን የሙያቸውን ነጻነት አክብረው ለህሊናቸው ታማኝ ሆነው መሥራት የሚችሉበትን አሠራር ተግባራዊ የማድረግ ጅምር ቢታይ፤
  • ክልሎች በሕገመንግሥቱ የሰፈረው ሙሉ ነጻነታቸው ተጠብቆ ከህወሓት የሞግዚት አስተዳደር ተላቀው ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን በተግባር የሚያረጋግጥ ጅማሮ ቢታይ፤
  • አባልም ሆነ አጋር የሚባሉት በህወሓት ተፈጥረው በህወሓት የሚዘወሩት ድርጅቶች የአገልጋይነት ዘመናቸውን ፈጽመዋል ተብሎ፤ በራሳቸው መቆም የሚያስችላቸው እንቅስቃሴ ቢጀመር።
  • በድርጅት ታጥሮ በታማኝነት ተወስኖ ሀገር መምራት እንደማይቻል የሀያ አራት ዓመት ልምዳችን አስተምሮናል፣ ስለሆነም ከዚህ በኋላ ሀገር መምራት በእውቀትና ሁሉን አሳታፊ በማድረግ መሆን እንዳለበት ተገንዝበናል ተብሎ፤ ይህንኑ ገቢራዊ ማድረግ የሚያስችል ተግባራዊ ርምጃ ቢታይ። ሌላም ሌላም ተመሳሳይ ነገር ከወያኔ ሰፈር ቢታይ ቢሰማ ትልቅ አስገራሚና ማራኪ ድንቅ ዜና ይሆናል። ከዚህ ውጪ መልካም አስተዳደር የፍትህ መጓደል እያሉ ማላዘንም ሆነ ይቅርታ እንጠይቃለን ማለት ሸብረክ ያሉ መስሎ ግዜ መግዣ የወያኔ የባህሪው ተግባር ነውና ሊደንቀን አይገባም።

ነገር ግን ወያኔ ያልፈጠረበትን በምክርም በመከራም ሊቀበለው ያልቻለውን ይህን ቅዱስ ተግባር በምን ተዓምር ፈጽሞት ይህ እውነት ሆኖ ለመስማት እንበቃለን! አይታሰብም። ወያኔዎች ይህን ለማድረግ እንደገና መፈጠር ይኖርባቸዋል። እኛስ ትናንትን እየረሳን በየግዜው የሚገጥሙንን የወያኔን የባህርይ ድርጊቶች እንደ አዲስ ከማየት ለመላቀቅ እና ትግሉን በምሬትና በወኔ ለማጥበቅ እንደገና መፈጠር ይጠይቀን ይሆን?

ትናትን እየረሱ የዕለት የዕለቱን አዲስ እያደረጉ መጮኹ፤ በትግሉ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ያለው ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም። የበደል ሸክሙ የሚከብደን፣ የጥቃቱ ምሬት የሚመረን፣አንባገነናዊ አገዛዙ የሚያንገሸግሸን እስከ አሁን ያለውን ስናስታውስ ነው። የዛሬው ሲያስለቅሰን ሲያስቆጣን ብቻ ሳይሆን የትናንቱም ሲቆጠቁጠን ነው። የትናንቱን እየረሳን ለዛሬው አንድ ሣምንት እየጮኸን፤ ከዛም ሌላ አዲስ ነገር እስኪመጣ ይህን እየረሳን እኩል መብሰል ባለመቻላችን (ጥሬ ብስልና የአረረ) ነው ሀያ አራት ዓመት ሙሉ ትግል እንጂ ለውጥ ማስመዝገብ ቀርቶ አዳዲስ ጥቃቶችን ማስቀረት፤ ተጨማሪ ጥፋት እንዳይፈጸም ማስቆም ወያኔን ከደደቢት ህልሙ ስንዝር መግታት ያልቻልነው። እውቁ የጽሁፍ ሰው አቶ ከበደ ሚካኤል ልጆች ሆነን ባነበብነው አንድ ጽሁፋቸው፤

ያለፈው ሲረሳኝ መጪውን ሳላውቀው
እኔ መቼ ይሆን የምጠነቀቀው፤

ብለው የነበረው ከላይ ለተገለጸው ለእኛ እኛነት በቂ ገላጭ አይሆንም ትላላችሁ?

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!