ጓድ ካፍትሌ

ጥያቄ ለአንባገነኖች፤ ዓለምን የሚገዛው ኃይል የቱ ነው?

"Whoever wishes to foresee the future must consult the past; for human events ever resemble those of preceding times. This arises from the fact that they are produced by men who ever have been, and ever shall be, animated by the same passions, and thus they necessarily have the same results." Machiavelli

የዴሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ በዓለም ላይ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት የተለያዩ የአስተዳደር ስልቶች ተግባራዊ ለማድረግ ተሞክሯል። አብዛኞቹ የአስተዳደር ስልቶች ግን ኃይልን መሠረት ያደረጉ ስለነበሩ በመሪና በተመሪዎች መካከል ከፍተኛ ቅራኔን ሲያሳድር ኖሯል።መሪዎቹ ለሚገዙት ሕዝባቸው ወፍራም ዱላ ካሳዩ ሕዝቡ ቀጥ ለጥ ብሎ ይገዛልኛል ብለው ስለገሚገምቱ የሥልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም የሚሊዮኖችን ደም በከንቱ አፍስሰዋል። የአንድ ቀን የሥልጣን ዕድሜያቸውን በአንድ ሺህ ሰዎች ደም ያቆዪታል።

እስቲ በዓለም ላይ በጭካኔያቸው ብዛት በታርክ ገጾች ላይ በቅድሚያነት የሰፈሩ ሰዎችን እንመልከት፡

1. ማኦ ዘዱንግ (ከ48-79 ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል)

የኮሜኒስት ቻይና አብዮተኛ አስገራሚ ዕቅዶችን ነድፎ በታርክ አደባባይ ላይ ብቅ አለ። ባህላዊ አብዮት (Cultural Revolution) ና ወደ ፊት መዘርጋት (Great Leap Forward) ይሉታል፣ የፕሮግራሞቹ አስገራሚ ስሞች (መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ ይሏል እንዲህ ዓይነት ነገር) ። በዕቅዶቹና በዓላማው በግራ በኩል የሚሰለፉትን ሰዎች በዘዴ እንደት እንደሚያስወግዳቸውም ያውቅበታል። ሥልጣን ከያዘ በአምስት ዓመቱ ከ4 እስኬ 6 ሚሊዮን ሰዎች የሞት ጽዋ እንድጎነጩ ፍርድ ሲያስተላልፍባቸው ግማሾቹን ከባድ ሥራ በማሰራት አስተሳሰባቸውን ለማሳደስና ከጎኑ ለማሰለፍ ጥረት አድርገ፤ይሄንን reform through labor ይሉታል። አብዛኛው የቻይና ሕዝብ ያለቀው በረሃብ ነው። ምክኒያቱም ሁሉም የሃገሪቱ ዜጋ ብረት እንድያመርት ትዕዛዝ ስለተላለፈበት ነው። ከትዕዛዙ ፍንኪች ማለት የሞትን ጽዋ ያስጎነጫል። ሰዎቹ ታዲያ የራሳቸው መመገቢያ ዕቃዎች እንኳን ሳይቀር ወደ ብረት ስለቀጠቀጡት ባዶ እጃቸውን ቀሩ፣ መጨረሻ ላይ የሚበሉትን ሲያጡ 20 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ለሞት እጃቸውን ሰጡ።

ከ1949 እስኬ 1976 ስልጣን ላይ የቆዩ ማኦ ዘዱንግ እስከ 79 ሚሊዮን ሰዎች ሞት ምክኒያት ሆኗል።

2. አዶልፍ ሂትለር (17 ሚሊዮን ሰዎች)

ከ1934 እሰኬ 1945 ጀርመን በአንባ ገነን መሪ ስር ወደቀች። አዶልፍ ሂትለር የናዚ ጀርሜን መሪ። ስለዚህ ሰውዬ ብዙ ማውራት አያስፈልግም። የበዓለም የታርክ መዝገብ ላይ ስሙን በደማቅ ቀለም አስጽፎ አልፏል። የጭካኔ ተምሳሌት። በሥልጣን ዘመኑ 6ሚሊዮን አይሁዳውያንን ጨምሮ በአጠቃላይ ለ17 ሚሊዮን ሰዎች ሞት ምክኒያት ሆኖ አልፏል።

3. መንግሥቱ ኃይለማርያም (400 000 አስከ 1.5 ሚሊዮን)

በትረ ሥልጣናቸውን በሰዎች ደም ለማራዘም ከጣሩ ክፉ መሪዎች ዝርዝር ውስጥ የእኛው መንጌ ደረጃ አለው። አገሪቱን ከዳር እስከ ዳር በቀይ ደም ለማጥለቅለቅ ማቀዱን ለመግለጽ በአብዮት አደባባይ ደም የተሞሉ ሶስት ጠርሙሶችን በመወርወር ማስጠንቀቂያ ሰጠ። በቀይ ሽብር የብዙ ኢትዮጵያውያን ሬሳ በየመንገዱ ተጣለ። ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ለመግደል የተተኮሰውን የጥይት ዋጋ (the wasted bullet) ከከፈሉ ብቻ ሬሳው ማንሳት ይፈቀድላቸዋል። አለዚያ ጥንብ አንሳ ወይም ጅብ ያነሳላቸዋል። what a curse!!!

ሌሎቹ እነ ጆሴፍ ስታሊን፣ እነ ያኩቡ ጎዎን፣ እነ ኢድ አሚን ዳዳ፣ እነ ቭላድሚር ለኔን፣ እነ ሙአመር ጋዳፊ በአንባገኔንነታቸው የዓለም የታርክ መዝገብ የሚያውቃቸው ናቸው።

እኔዚህ ሁሉ ዓምባገኔን መሪዎች አንድ የጋራ ግንዛቤ ነበራቸው። ይሄውም ተቃዋሚዎቻቸውን በማንኛውም መንገድ አጥፍተው በሥልጣን ወንበራቸው ላይ ዝንታለም መቀመጥ ነው ሕልማቸው። ሕዝቡም ይሄንን አስፈሪ (Horror)ና አውሬአዊ ድርጊታቸውን ካየ ቀጥ ለጥ ብሎ ይገዛልኛል ብለው ስለሚያስቡ አውቀው ሆነ ብለው በሕዝብ ላይ ሽብር ይነዛሉ፤ ይገድላለሉ።

ነገር ግን ታርክ እንደሚያስተምረን ከሆነ አንድ መሪ የፈለገውን ያህል ሰይጣናዊ ማንነት ተላብሶ የሕዝቡን ግማሽ በሞት ብቀጣ የሥልጣን ዘመኑ እንደሚያስበው ሳይሆን ሁሌም አጭር እንደሆ ነው። ይዋል ይደር እንጂ ከሚወዱት የሥልጣን ወንበራቸው ተከንብለው መውደቃቸው አይቀርም።

ከዚህ የሚንማረው አንድ ነገር ቢኖር ሕዝብን በጉልበት ማሸነፍ እንደማይቻል ነው። የፈለጉትን ያህል ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቀው የፈለጉትን ያህል አስፈሪ መንግስት ቢሆኑ ሕዝብን በጉልበት ማሸነፍ አይቻልም።

ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን አውሮፓውያን አፍሪካን የወረሩበት የቅኝ ግዛት ታርክ ነው። በዚያን ጊዜ አውሮፓውያን ከአፍሪካ ይልቅ የሰለጠኑና ጉልበታሞች ነበሩ። አፍሪካን የወረሩት በዚህ በሥልጣኔያቸውና በጉልበታቸው በመተማመን ነው። አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት አንድ በአንድ በቅኝ ገዥዎቻቸው ጡጫ ስር ወደቁ። የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት ተደርጋ የሚትቆጠረው አገራችንም ለአምስት ዓመታት ያህል የሞት ሽረት ትግል ካካሄደች በኋላ ነፃነቷን ተቀዳጀች። እያንዳንዱ የአፍሪካ አገራትም ኢትዮጵያን ተከትለው ነጻነታቸውን ለማግኘት የሞት ሽረት ትግል ካካሄዱ በኋላ ሁሉም አገር አንድ በአንደ ነፃነቱን ተጎናጸፈ። እዚህ ጋር ግን አንድ ጥያቄ ልነሳ ይችላል። አውሮፓውያን ከአፍሪካ በኢኮኖሚም በሥልጣኔም የተሻሉ ከሆኑ አፍሪካውያንን ለማሳደግ የሚያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሚሆን አይጠረጠርም። በአገራችን እንኳ ስንመለከት በአምስት ዓመት ቆይታዋ ፋሺስት ጣሊያ በአገራችን ብዙ መሠረተ ልማቶችን ዘርግታለች። ሰዎቹ ታዲያ ለመን ቅኝ ገዥዎቻቸውን እሺ ብለው አልተቀበሉም?

ምክኒያቱ አንድና አንድ ነው፤ ሰው በእንጀራ ብቻ የሚኖር እንስሳ አለመሆኑ ነው። ሰው ነጻነትን ይፈልጋል። ሰውን ለመግዛትም ሆነ ለማስተዳደር የሰውዬውን ነጻ ፈቃድ ማግኘት ግድ ነው። ጉልበት ማንንም አይገዛም። ጊዜው የተሸነፈ መስሎ ዝም ብል ምቹ ጊዜ እየጠበቀ እንጂ በሃይል መገዛቱ ስለተመቸው አይደለም።

እስቲ በሌላ በኩል ደግሞ በመልካም አመራራቸው ዓለምን ያስደመሙ በምን ዓይነት መስፈርት ሚሊዮኖችን ከኋላቸው ማስለፍ እንደቻሉ፣ ለሚሊዮኖች ሞት ምክኒያት በመሆን ሳይሆን ለሚሊዮኖች ሕይወት መለወጥ ምክኒያት የሆኑ ሰዎችን እንመልከት።

1. ማሃታማ ጋንዲ

ባፑ፣ የሕዝብ አባት (the Father of the Nation): ከተራ ቤተሰብ የተወለደ በታላላቆች ተርታ የተሰለፈ የሕንዶች የነፃነት ታጋይ፣ የዓለም ተምሳሌት። የአንድም ሰው ነፍስ ሳትጠፋ ከጨቋኝ የብሪትሽ ቅኝ አገዛዝ ስር ህንድን ነጻ ያወጣ ጀግና፣ መሃታማ ጋንዲ። ያለ ደም መፋሰስ ለነፃነት መታገል እንደሚቻል ዓለምን ያስተማሪ ጀግና ነው ጋንዲ።

2. ማርቲን ሉተር ኪንግ

“I still have a dream, a dream deeply rooted in the American dream – one day this nation will rise up and live up to its creed, "We hold these truths to be self evident: that all men are created equal." I have a dream ...”

መልካም መሪዎች በሰው ልጆች እኩልነት የሚያምኑ፣ ራዕያቸውና ሕልማቸው የራሳቸውን የስልጣን ዘመን በጡንቻ ማራዘም ሳይሆ ይሄንን የሰው ልጅ እኩልነት ማስከበር ነው። ማርቲን ሉተር ኪንግ በዚህ ሰብዕና ከታደሉት ጥቂት የዓለማችን ሰዎች መካከል አንዱ ነው። “ሕልም አለኝ” የሚለው ትንቢታዊ መልዕክቱ ዛሬ በአሜሪካ ውስጥ ለሚታዬው የዜጎች እኩልነት መሠረት ነው (እሱ ከሞተ በኋላ ብዙ የኪንግ ትንቢቶች ተፈፃሚነት እንዳገኙ ይነገራል)። የማርቲን ሉተርን የልደት ቀን መላው ዓለም ያከብረዋል። እሱን የማያደንቅ ሰው ማግኘት በጣም ከባድ ነው። ዓለምን ከኋላው ያስከተለው ኪንግ ያለምንም ዱላ በብዕርና በወርቀት ብቻ ነው። ደም ሳይፈስ ለብዙዎች ነፃነት የታገለ፣ ነፍሱንም ለሌሎች ጥቅም አሳልፎ የሰጠ ጀግና ነው ማርቲን ሉተር ኪንግ ትንሹ::

3. ኒልሰን ማንዴላ

Rolihlahla አባቱ የሰጠው ስም ሲሆን ስተረጎም “አሸብር” የሚል የአማርኛ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። በኢንግሊዝኛ the troublemaker የሚል ትርጉም አለው። የመጀመሪያ ክፍል ነጭ አስተማሪ ኒልሰን ብላ ሰየመችው። ችግር የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው። ነጮች የበላይነታቸውን ለማሳየት የብዙ አፍሪካውያን ስም እንደ ልባቸው የሚቀይሩበት ጊዜ ነበር። ማንዴላ እያደገ ሲሄድ በሃገሪቱ ያሉ ሁሉም ዜጎች እኩል እንዳልሆነ ተገነዘበ። ለዚህም የዕድሜውን 40 ዓመት (ከዚያ ውስጥ 27 ዓመት በእስራት) ለሕዝቦች እኩልነት መሰዋዕት አደረገ። መጨረሻ ላይ የተመኘው ተሳካለት። የአበርታይድ ሥርዓት ሲፈረካከስ ማንደላ የጥቁሮች ፕረዚደንት ለመሆን በቃ። ዓለም ሁሉ አንድ ነገርን በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። ማንዴላ ሥልጣን ሲይዝ 27 ዓመት ሙሉ በእስር ያንገላቱትን ከሁሉም በላይ ደግሞ በገፍ አገዛዝ አገራቸውን ያስጨነቁትን ይበቀላቸዋል ሲባል በይቅርታ አለፋቸው። ሁሉም በአንድነት በሰላም መኖር እንድችሉ አወጀ። የይቅርታን ኃያልነት ከማንዴላ በላይ የተረዳ የዓለም መሪ ማን ይሁን? ይህ አስገራሚ ሰው ዓለም ላይ የማያደንቀውና የማያከብረው ሰው ማግኘት ከባድ ይሆናል።

(ማንዴላ ነጮችን ይቅር ማለት ከቻለ፣ እኛ መንግስቱ ኃይለማሪያምን ጨምሮ ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችን የሆኑት የደርግ አመራሮችን ይቅር ብንላቸው ምን ይጎድልብናል?)

ሌሎችም እነ አብርሃም ሊንከን፣ እነ ጂዎርች ዋሽንግተን፣ እነ ናፖሊዮን ቦናፓርት፣እነ አሌክሳንደር ዘ ግረት፣ እነ ዌስቲን ቸርቺል እና እነ ቼ ጉቬራን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ሰዎች ለብዙዎች ሕይወት መለወጥ ምክኒያት የሆኑ ታርካቸውን በሰው ልብ ውስጥ በደማቅ ቀለም የፃፉ ድንቅ የዓለማችን ሰብዕናዎች ናቸው። ከሌሎች የሚለያቸው የብዙዎችን ደም ማፍሰስ ሳይሆን ለብዙዎች ደማቸውን ያፈሰሱ ድንቅ ሰዎች ናቸው።

ስለዚህ ከታርክ የሚንማረው ነገር ዓለምን ከኋላ አስከትሎ ለመምራት የተራቀቁ የጦር መሣሪያዎች ጋጋታና የፈረጠመ ጡንቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ እኩልነት ክብር ዋጋ በመስጠት ነው። ወርቀት ይዞ ለተቃውሞ አደባባይ የወጣው ሕዝብ ላይ ጥይት መተኮስ የአንድ ሌሊት መፍትሄ ሊሆን ይችላል። ጥያቄውን ግን ከሰው አእምሮ ልደመስስ ወይም ልመልስ ስለማይችል ነገ ተመልሰው መውጣታቸው አይቀርም። በእስርና በግድያ ተቃዋሚዎችን ማጥፋት አይቻልም። አንድ ተቃዋሚ ስታሰር አስር ይወለዳሉ። አንድ ተቃዋሚ ሲገደል መቶ ተቃዋሚዎች ይወለዳሉ። ስለዚህ ሕዝብን የመምራት ዕድል ያገኙም ሆነ ወደፊት ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ታርክን ጠንቅቀው ሊያውቁ ይገባል። ዓለምን የሚገዛው ኃይል ፍቅር እንጂ ጉልበት አይደለም።

በየትኛውም ዓለም ታርክ ውስጥ ጠብመንጃ ችግር አባብሶ አንጅ ፈትቶ አያውቅም!!!!

"Those who do not learn history are doomed to repeat it." George Santayana

ጓድ ካፍትሌ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!