ተስፋዬ ገብረዮሐንስ (ከጀርመን)

Ethiopian federalism map. የወያኔ የጎሣ ፌደራሊዝም ሲፈተሽ

የወያኔ አስተዳደር የማዕከላዊውን የመንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ በሀገሪቱ ተግባራዊ ያደረገው የፌደራል ሥርዓት ጎሣን መሠረት ማድረጉ የሚታወቅ ነው። እንደ ወያኔ አገላለጽ ይህ የጎሣ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ ደም መፋሰስን ያስቀረና ሀገሪቱንም ከመበታተን አደጋ የሚታደግ ነው ይላል። ይሁን እንጂ በተግባር እየተፈፀመ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት ስንፈትሽ ይህ ወያኔ-ሰራሽ የሆነው የጎሣ ፌደራሊዝም ዓላማም ሆነ እያስከተለ ያለው ውጤት ከዚህ በተቃራኒ ሆኖ እናገኘዋለን።

በመጀመሪያ ምንም እንኳን በሕገ መንግሥቱ ላይ “ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት አላቸው” ቢልም በተግባር ግን አምስት ብሔሮች ብቻ የራሳቸው ክልል እንዲኖራቸው አድርጓል። ሌሎች ከሰባ አምስት በላይ የሚሆኑ ብሔረሰቦች ወይ ባለብዙ ብሔር ክልል በመፍጠር በዚያ እንዲታቀፉ ሲያደርግ፤ አልያም በሌሎች አምስቱ ክልሎች ውስጥ ህዳጣን /Minority/ ሆነው እንዲኖሩ ተደርጓል።

ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች በሚኖሩበት ሀገር ውስጥ ጎሣን ብቻ መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝምን ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻል ነው። በመሆኑም የሚከተለውን ጥያቄ እንድናነሳ እንገደዳለን፡- ወያኔ ይህን የጎሣ ፌደራሊዝም የሙጥኝ ብሎ ሩብ ምዕተ-ዓመት ለምን መጓዝ ፈለገ? በእኔ እምነት ይህን ያደረገው በሁለት ምክንያት ይመስለኛል።

ሀ. የራሳቸው ክልል እንዲኖራቸው በተደረጉ አምስቱ ክልሎች ተቀባይነትን /Internal Legitimacy/ ለማግኘት።

ለ. የወያኔን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነትን የሚቃወም ሕብረ-ብሔራዊነቱ የተጠናከረና በአንድነት የሚቆም ማኅበረሰብ እንዳይፈጠር ለመከላከል። ለምሣሌ በተለያዩ ወቅቶች በጋምቤላ፣ በአዲስ አበባ፣ በኦሮምያና በአማራ ክልሎች ህዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ ቢሆንም በአንዱ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ ቁጣና ተቃውሞ በሌላ ክልል የሚኖረው ህዝብ በአይመለከተኝም ስሜት ጉዳዩን እንዲያየው ተደርጓል፤ እየተደረገም ነው።

በሌላ በኩል ይህ የጎሣ ፌደራሊዝም በኢትዮጵያ ህዝብና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖና እያስከተለ ያለው ችግር የሚከተለውን ይመስላል።

ሀ. ባለብዙ ብሔር በሆኑ ክልሎች ውስጥ በየጊዜው የሚያገረሽ ማንነትን መሰረት ያደረገ ግጭት መከሰት።

ለ. በነዚህ ባለብዙ ብሔር ክልሎች ውስጥ የተፈጥሮ ሀብት ክፍፍልን፣ የድንበር ወሰንን እንዲሁም በክልልና በወረዳ ምክር ቤቶች ውስጥ በሚኖር የውክልና ጥያቄን መሰረት ያደረገ ውጥረት እና ግጭት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።

ሐ. ዜጎች በሀገሪቱ በየትኛውም ክልል ተንቀሳቅሰው የመሥራት፣ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብታቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንዲገታ ተደርጓል።

መ. ዜጎች በችሎታቸው ሳይሆን በብሔር ማንነታቸው በመመዘናቸው፤ የሀገሪቱ ቢሮክራሲ የተንዛዛና መልካም አስተዳደር የጎደለው እንዲሁም ለከፍተኛ ሙስናና ምዝበራ የተጋለጠ እንዲሆን አድርጓል።

ሠ. ሀገራዊ ራዕይ ያላቸውና የወያኔን መንግሥት መገዳደር የሚችሉ ሕብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይፈጠሩ፤ ይልቁንም ብሔር ተኮር የሆኑ ድንክ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን እንዲፈሉ በማድረጉ፤ ወያኔን በሠላማዊ የፖለቲካ ትግል ማስወገድ እንዳይቻል አድርጓል።

ረ. ወያኔ ሆን ብሎ በሚያሰረጨው ታሪካዊ-ቅሰጣ /Historical Revisionism/ መሰረት በተለያዩ ክልሎች መካከል ከፍተኛ የሚባል ጥላቻ እንዲነግሥ ከማድረጉ ባሻገር፤ ነገን በደም እንዲፈላለጉ እያደረገ ይገኛል።

በአጠቃላይ ይህ የጎሣ ፌደራሊዝም ወያኔ እንደሚለው በሀገሪቱ ደም መፋሰስን የሚያስቆም ሳይሆን፤ ይልቁን እንደ ባልከን ሀገሮች ከፍተኛ ለሚባል ደም መፋሰስና መበታተን የሚዳርግ ትልቅ አደጋን ያዘለ ነው። በመሆኑም በዜጎች መካከል ግንዛቤን ከመፍጠር ጀምሮ በሀገራችንና በህዝባችን ላይ ያንዣበበውን አደጋ ከወዲሁ ለማስቀረት ወያኔን በጋራ ልናስወግደው ይገባል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!