ይገረም አለሙ

Crooked forest and TPLF.

የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያቸው ድል ማግስት መቀሌ ተገኝተው በትግርኛ ባደረጉት የአደባባይ ንግግር፤ “እኛ ከሥልጣን ብንወርድ፤ ነፍጠኞች አንድ ቀን አያሳድሩዋችሁም” ማለታቸውን የዓይን እማኝነታቸውን የሰጡ ሰዎች በወቅቱ አስነብበውናል።

ይህ የአቶ መለስ ዘረኛ የጥላቻ ዘር አብቦ እንዲያፈራ የሚያግዝ ተግባር ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ቁጥራቸው ቀላል በማይባል ወያኔን እንቃወማለን በሚሉ ሰዎች ሲፈጸም አይተናል፤ እያየንም ነው። አንዳንዶቹ ከጽሑፋቸውና ከንግግራቸው ይዘት፤ ብሎም አጥብቀው ከሚጮኹበት ወቅት ምንነት አንጻር ድርጊቻው ሲመዘን ዓላማቸው ይሄው መሆኑን መገመት ይቻላል። ከምር ወያኔን የሚቃወሙትና በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ ከልብ የሚሹት ሰዎች ግን ይህን ለማድረግ የበቁበትን ምክንያት መገመት ቢቻልም፤ በወያኔ ቦይ እየፈሰሱ መሆናቸውን መገንዘብ ለተያያዙት ትግል እንደማይጠቅምም መረዳት እንደምን ተሳናቸው የሚያሰኝ ነው።

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ለተፈጸሙት ጥፋቶች ሁሉ ተጠያቂው አቃጁ፣ መሪው፣ ፈጻሚና አስፈጻሚው የደደቢቱ ወያኔ መሆኑ ያከራክረም። ይህ ማለት ግን እርሱ ብቻ ነው ማለት አይደለም። ሌሎች በማቀዱም ሆነ በመሪነቱና በማስፈጸሙ ላይ ይህ ነው የሚባል ድርሻ ባይኖራቸውም፤ በፈጻሚነት ተሰልፈው እንደውም አንዳንዶች ከወያኔ በላይ ወያኔ ሆነው አጥፍተዋል፣ እያጠፉም ነውና፤ ድርሻው ይለያይ ካልሆነ በስተቀር ተጠያቂው ብዙ ነው። መተባበርም፣ ጥፋትን ማስቀረት ሲቻል ዝም ማለትም ያስጠይቃል። ነገር ግን ውግዘቱ፣ ተቃውሞውም ሆነ ትግሉ በእነዚህ ላይ ሲያተኩር አይታይም።

የሥልጣንም ሆነ የቁስ ፍርፋሪ እየተጣለለት፤ “ውሻ በበላበት ይጮኻል” እንዲሉ ሆኖ ወገኖቹን መውጫ መግቢያ የሚያሳጣውን፣ የሚገድል የሚያስረውን፣ የሚዘርፍ የሚያዘርፈውን የብሔራቸውን አባል፤ ኧረ! እንደውም ወንድማቸውን አልያም የአጎት የአክስት ልጅን ምንም ሲሉ የማያሙ ትግርኛ ተናጋሪውን ወገን በጅምላ ለመወንጀል ለመውቀስ ብሎም ለመዝለፍ ያላቸው ድፍረት ይገርማል።

የደደቢቱ ወያኔዎች በሙሉ ትግሬዎች መሆናቸው እንደማያከራክር ሁሉ፤ ትግሬ ሁሉ ወያኔ አለመሆኑ እንዲሁ ሊያከራክር ባልተገባ ነበር። ወያኔን በዘረኝነት እየከሰሱ ሀገሪቱን ለአደጋ ያጋለጠውና ለችግር የዳረገው የዘር ፖለቲካ በማራመዱ ነው እያሉ እየተቃወሙ፤ እነርሱ ትግርኛ ተናጋሪውን በሙሉ ከደደቢት ወያኔዎች ጋር ደምረው ሲያወግዙና ሲያጥላሉ ራሳቸው ዘረኝነትን እያራመዱና በወያኔ ቦይ እየፈሰሱ ስለመሆኑ መረዳት እንዴት እንደሚቸግራቸው ግራ የሚያገባ ነው።

ወያኔዎች በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ጉዳያቸውን የሚያስፈጽሙትና ዓላማቸውን የሚያሳኩት ከኋላ ሆነው ከፊት በተቀመጡት የአካባቢው ሰዎች አማካኝነት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ግድያው፣ እስራቱ፣ ድብደባው፣ የመሬት ቅርምቱ፣ የሀብት ዘረፋው፣ ማፈናቀሉ … ወዘተ ሁሉ የሚፈጸመው በየአካባቢው ሥልጣን ላይ ባሉ ሰዎች ቀዳሚ ተዋናይነት መሆኑ እንዲህ እየታወቀ፤ በዚህ ድርጊት ትግርኛ ተናጋሪውን በሙሉ መወንጀል ከሕሊና ዳኝነት ይልቅ ስሜታዊነት ያየለበት ተግባር ነውና ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም።

ከስሜታዊነት ወደ ሕሊና ዳኝነት በመሸጋገር ሁለት ነገሮችን ማድረግ ቢቻል ለዛሬው ትግል ውጤታማነት ለነገውም ኢትዮጵያዊ አንድነት ይበጃል። የመጀመሪው ትግርኛ ተናጋሪውን በሙሉ ከደደቢቱ ወያኔ ጋር ደምሮ በጅምላ ማውገዙን፣ መክሰሱንና መዝለፉን ማቆም፤ ሁለተኛው የቃል ውንጀላና ውግዘታችንንም ሆነ የተግባር ትግላችንን ከጉያችን መጀመር። እየገደሉን የሚሾሙትን፤ እየዘረፉ የሚያዘርፉትን፤ ጃስ እየተባሉ የሚነክሱንን፤ ከጉያችን አስቀምጠን፤ “ወያኔ” … “ወያኔ” … ማለቱ የትም አላደረሰንም፤ ወደፊትም የትም አያደርሰንም። ጠብደል ውሻ በግቢው ያለን ባላንጣ ከቤቱ ገብቶ ለማነጋገርም ሆነ ርምጃ ለመውሰድ፤ መጀመሪያ ውሻውን ማለፍ ግድ ነው። ውሻው የሚበላበት ሥራው ነውና አላስገባ ብሎ ይከላከላል፤ ከቻለም ይነክሳል፤ ባለቤቱንም ያነቃል። ስለሆነም ባለቤቱን ለማግኘት ሲታቀድ ውሻው ይህን ተግባሩን እንዳያከናውን ማድረግ የሚቻልበት ብልሃት ካልታሰበ የተፈለገው አለመሳካት ብቻ ሳይሆን መቀደምም ይከተላል።

ፕ/ር አሥራት ወልደየስ በሕክምና ሙያቸው ዘር፣ ቋንቋ፣ ኃይማኖት ሳይለዩ የአያሌ የሰው ልጆችን ሕይወት ከሞት ታግለው ያስጣሉ እውቅ ቀዳጅ ሐኪም ነበሩ። ሕይወታቸው በወያኔ ባይቀጭ ኖሮም በርካታ የሰው ልጆችን ሕይወት በታደጉ ነበር። በወቅቱ የፖለቲካ ስካር ለአደጋ የተዳረገውን አማራ ለመታደግ ሙያቸውን ቀይረው የመአህድ (የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት) ፕሬዝዳንት በመሆን የፖለቲካ ትግሉን የጀመሩት ፕ/ር አሥራት ወልደየስ፤ ከሁለት ዓመት ያለፈ በትግሉ አልቆዩም። ከጅምሩ ያገኙት የህዝብ ድጋፍና የፓርቲው እንቅስቃሴ ያስፈራው ወያኔ እስከ ዛሬም ድረስ መታወቂያው የሆነውን የሐሰት ክስ መስርቶ ወህኒ አወረዳቸው። ፕ/ር የታሰሩት ዛሬ ለአፍሪካ ሕብረት ተሰጥቶ ቻይና ፎቅ በፎቅ ባደረገችው ቦታ ላይ በነበረው የአዲስ አበባ ወህኒ ቤት ነበር። ርሳቸውን ለመጠየቅ ከምዝገባ እስከ ፍተሻ የነበረው ሂደት አናዳጅም እልህ አስያዥም የነበረ ሲሆን፣ በተለይ ጫማ እስከማስወለቅ የሚደርሰው ፍተሻ ለሴቶች በጣም ፈታኝ ነበር። ፈተናው ሲገባ ብቻ አልነበረም፣ የሚወጣውም ተሰልፎ፣ ተፈትሾ፣ መታወቂያ ተቀብሎ ነበርና፤ በወቅቱ አንተ/ቺ ከፕሮፌሠሩ ጋር ምንድን ነው ያወራኸው/ሽው፣ በምልክት ተነጋግራችኋል … ወዘተ በሚል መታገት ያጋጥም ነበር።

ፕ/ር አሥራት በመደበኛ የመጠየቂያ ቦታቸው ሆነው የሚመጣውን ሁሉ በየተራ የሚያነጋግሩት ሙሉ ወታደራዊ ትጥቅ ታጥቆ ጠብ-መንጃ በወደሩ ታጋዮች እየተጠበቁ ሲሆን፣ ሲቪል ለባሾች ደግሞ ከጠያቂው ጋር ተመሳስለው የሚነገረውን ብቻ አይደለም የሰውነት እንቅስቃሴን ሁሉ ይከታተላሉ። ይህን የተላመዱት ፕ/ር ብዙ ግዜ የሚፈልጉትን ነገር የሚነግሩን በምሳሌ ነበር። ታዲያ ከዛ ስንወጣ እንዲህ ያሉት ይህን ለማለት ነው በሚል እንከራከራለን፤ የማንተማመንበትም ግዜ ነበር።

“ነገርን ነገር ያነሳዋል” እንዲሉ፤ በዚህ መልኩ ካጫወቱንና ከማልረሳቸው አንዱ፤ ከላይ የገለጽኩትን ጉዳይ የሚያጠናክር ስለመሰለኝ ልጠቅሰው ፈለጌ ነው ስለወህኒ ቤቱ ያነሳሁት። በተለይ የፕ/ር አሥራትን ስም እየጠሩ ፈለጋቸውን ተከታይ ነንም እያሉ ለአማራ እንደሚታገሉም እየተናገሩ ትግርኛ ተናጋሪውን ኢትዮጵያዊ በመሉ በደደቢቱ ወያኔ ቅርጫት ውስጥ ከትተው ለሚያወግዙ፤ ሲያልፍም ለሚዘልፉ፤ ሲብስም ጠላት ለሚሉ ጠቃሚ ምክር ይመስለኛል።

ወቅቱ ልክ እንደ አሁኑ ከወያኔ አልፎ ትግርኛ ተናጋሪውን በሙሉ በወያኔነት ፈርጆ፣ መወንጀል፣ ማውገዙ የበረታበት ነበር። እናም ከፕ/ር ጋር በወህኒ ቤት ስናወራ ጉዳዩ ተነስቶ በምሳሌ ከነገሩን በአጭሩ ልግለጽ። ጣሊያን ተሸንፎ ከሀገር በወጣ ግዜ በርካታ ጣሊያኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ቀርተው ነበር። ከእነዚህ አንዱ በሚኖርበት ሠፈር ሲወጣ ሲገባ ዘመዶችህ ወገኖቻችን በመርዝ ጋዝ ጨርሰው፣ በአካፋና ዶማ ጨፍጭፈው፣ … እያለ ሰዉ ይነዘንዘው ነበር፤ ታዲያ አንድ ቀን ምርር ብሎት ምን እኔ ላይ ጣታችሁን ትቀስራላችሁ፤ እኔን መውጫ መግቢያ ታሳጡኛላችሁ፤ ከእኛ ወታደሮች እየቀደሙ ሲተኩሱ፣ ሲገሉ፣ ቤት ሲያቃጥሉ የነበሩት፤ የአርበኞችን ምሽግ እየጠቆሙ ሲያሲዙ የነበሩት የእናንተው ወገኖች አልነበሩም ወይ? አላቸው በማለት አስረዱን።

አዎ! ዛሬም ከየቤታችን አንስቶ እስከ ቤተ መንግሥቱ ድረስ የወያኔ መሣሪያ ሆነው ዜጎችን የሚበድሉ፣ ሀገሪቱንም እየገደሉ ያሉ፤ ከሁሉም ብሔር ያሉ ናቸው። ታዲያ በየጉያችን ያሉ አጥፊዎች ላይ ተቃውሞ ማሰማትም ሆነ ጣት መቀሰር ሳንችል፤ በደም ይገናኛሉ፣ በቋንቋ ይግባባሉ በሚል፤ ትግርኛ ተናጋሪውን ሁሉ ወያኔ ብሎ መፈረጅ፤ ከዛም አልፎ በአጥፊነት መወንጀል፤ ለወያኔ ፍላጎት መሳካትና መርዳት ካልሆነ በስተቀር ተገቢና ትክክል የሚሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም።

የአንዳንዶች መከራከሪያ ወያኔ ነግሦ ትግሬዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፤ ሌላው ቢቀር ሲቃወሙ አይሰሙም የሚል ነው። ነገር ግን ማስተዋል ከተቻለ በወያኔ ንግሥና ተጠቃሚ የሆነው ትግርኛ ተናጋሪው ብቻ አይደለም፤ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ለወያኔ ያደረ፣ አብልቶ መብላቱን የተካነ፣ የአባትህ ቤት ሲበዘበዝ አብረህ በዝብዝ የሚለውን ብሂል የተከተለ ተጠቃሚ ሆኗል፤ ወደፊትም እስከጠቀመ ድረስ ይጠቀማል። ታዲያ የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ተለይቶ ጎልቶ ለውግዘት የሚያበቃው ለምንድን ነው? ወያኔዎች ትግራይን የክፉ ቀን ምሽጋቸው ለማድረግ ካላቸው ዓላማ አንጻር፤ ትግርኛ ተናጋሪው ወገን በሌሎች ኢትዮጵያውያን እንዲጠላና ሞቴን ከወያኔ ጋር ያድርገው የሚል ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሠርተዋል፣ እየሠሩም ነው። ለዚህ ዓላማቸው መሳካት ከፈጸሙዋቸው እኩይ ተግባራት አንዱና ዋናው ትግራይን በተለየ ሁኔታ ማልማትና ትግሬዎችን በተለያየ መንገድ እያሰባሰቡ በአንድ ጀንበር ከበርቴ እንዲሆኑ በማስቻል፤ ሌላው ኢትዮጵያዊ ከጥላቻም አልፎ የጠላትነት ስሜት እንዲያድርበት ማድረግ ነው። ትግሬ ሁሉ ወያኔ ነው የሚሉ ሰዎች እንግዲህ ይህን የወያኔን ዓላማ ነው እያሳኩ ያሉት። ከመነሻው የተገለጸው የአቶ መለስ ዘረኛ ስብከት በትግርኛ ተናጋሪው እንዲታመን ነው የሚያግዙት።

ትግርኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን በወያኔነት የሚፈረጁበትና የሚኮነኑበት ድርጊት ሁሉ በሌሎች ኢትዮጵያውያን የተፈጸሙና የሚፈጸሙ ናቸው። ታዲያ ኦሮሞ በሙሉ ኦህዴድ፣ አማራ በሙሉ ብአዴን ደቡብ በሙሉ ደኢህዴግ … ወዘተ ሳይባሉ፤ ትግሬዎችን ብቻ ጠቅልሎ ወያኔ ማለትና ማውገዝ፤ ሲከፋም መጥላት ከወያኔ ያልተናነሰ ዘረኛ መሆንና አውቆ በድፍረት፣ ሳያውቁ በስሜት የወያኔን ዓላማ ማሳካት ነው።

ብዙ ግዜ የሚጠቀሰው የዛፎች ምሳሌም በዚህ ጽሑፍ ለተነሳው ሃሳብ በቂ ገላጭ ይመስለኛል። ምሳሌው በአጭሩ፤ ዛፎች መጥረቢያ ጨረሰን ብለው መከሩ፣ ሊከሱትም ተወካይ መርጠው ወደ ችሎት ላኩ፤ ተወካዮቹ በመንገድ ላይ ሳሉ አንዱ ምስጢሩ ተገለጠለት፤ ለመጥረቢያ ዛቢያ ሆነው የሚያገለገግሉት ከመካከላችን የሚበቅሉ ጠማማ እንጨቶች ናቸው፤ እነርሱ ባይኖሩ መጥረቢያ ዛፍ ለመቁረጥ አቅም አይኖረውም፤ ስለሆነም መጥረቢያን ከመክሰስ የራሳችንን ጠማሞች ከመካከላችን እናስወገድ አለ። ሁሉም ነገሩን አመኑበት፤ ተስማሙ፤ ክሱን ትተው ጠማማዎችን የማስወገድ ሥራ ላይ ተሰማሩ።

እህ! … እኛስ ምስጢሩ የሚገለጥልን መቼ ይሆን?!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!