ሄኖክ የሺጥላ

የሀገራችን ፖለቲካ፣ ትችት እና ዘለፋ እንደ ርችት እያብረቀረቀ የሚዘንብበት የነገር ሸራተን ነው። ትናንት ወዳጅህ የነበረ፣ ዛሬ እንደ አማዞን እባብ ቆዳውን ሸልቅቆ ሙልጭ አድርጎ ሊሰድብህ ይችላል፤ ሃሳብህን ሳይሆን ሱሪህን ሊያወልቅ ይፈልጋል። እሱ ራሱ የወጣለት ጠንጋራ ብሔርተኛ ሆኖ፣ ዓይኑን በጨው አጥቦ «ለምን ስለ አንድነት አትሰብክም» ይልሃል፤ የሌሎችን ቁመና ሲያፍረጠርጥ ከርሞ፣ የሱ ቁመና ሲነካ፣ አደለም ቁመናዬን እዳሪዬን እንኳ መተቸት (መንካት) መብትህ አይደለም ሲል አያፍርም።

ዲሞክራሲ አቅም የሚኖረው እና ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው እሱ ለሚፈልገው ዓላማ ሲውል ብቻ ነው፤ ኢ-ፍትሃዊነት ትርጉም የሚኖረው እሱ ሲናገረው ብቻ ነው፤ የነፃነት ጥያቄ በሱ ልሳን ካልሆነ በሌሎች ሰዎች ልሳን መነገር የማይችል የመለኮት ቃል አስመስሎ ይቀርፅልሃል። ሃሳቡን፣ አካሄዱን፣ መንገዱን እና መድረሻውን እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ «ይህ እንዳይሆን እንዲህ ይሁን» ብለህ ስታመለክት፣ ከግንዛቤህ ከመማር፣ የተሳሳትከውን በጨዋ መንገድ ከማረም እና ከማስተማር ይልቅ ከየፓልቶኩ እና መሰል ቦታዎች በጋራዥ ሴል (በብላሽ ይለዋል ጉራጌ) የተገዙ የሳይበር ወታደሮቹን ጥቃት እንዲፈጥሙ መረጃ ይሰጣል።

እርግጥ ይህ አካሄድ እነዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያትን ከሜዳ አስወጥቶ ሊሆን ይችላል፣ እነ ሣይንቲስት ጥላሁን ይልማን አስደንግጦ (ወይም ተስፋ አስቆርጦ) ይሆናል፤ ግን ለሁሉም ይሠራል ማለት አይደለም። ፖለቲካው ምህዋሩን በማይረቡ ሰዎች ዙሪያ ሲቀልስ እና ሲሽከረከር ስናይ፤ ዛሬ አዲስ አይደለም፤ ትናንት አዲስ አልነበረም፤ ነገም አዲስ አይሆንም። እነአባ መላ በአንድ ጊዜ የግሎባል አሊያንስ እና መሰል ድርጅቶች ወግ ከዋኒ ሆነው ወደፊት የመጡት በእውቀታቸው ሳይሆን ባላቸው ገደብ አልባ የመባለግ ብቃታቸው ነበር። ከነሱ የብልግና እውቀት መጠቀም የሚሻ፣ በደካሞች መሃል ትልቅ ሆኖ መታየት የሚሻ ትንኞችን እየመረጠ የደረቀ ባሊ ላይ ማሰማራቱ የምንነቱ መገለጫ ነው። እርግጥ እንደዚህ አይነት ሰዎችን ከላይ እንደገለጥኩት «በርካሽ ከጋራጅ ሴል ላይ» ልታገኛቸው ትችላለህ፤ ግን እንደዚህ አይነት ደካማ፣ ነውረኛ እና አሳፋሪ ሰዎችን ወደፊት በማምጣት ለውጥ ማምጣት እንችላለን የሚል ተቋም ይሁን አቋቋም ለምን ተተቸሁ ብሎ አካኪ ዘራፍ ሲል ብትሰማው፤ «ማነው ልክ» ብለህ ራስህን ትጠይቅ ይሆናል እንጂ፤ አካኪ ዘራፉ የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እውነት ኖሮት ያንተን የእምነት ተራራ በፍርሃት ጨረሩ ሊገፋ አያስችለውም።

የኛ ፖለቲካ ከሞላ ጎደል እውነትን በመፍራት እና የተናገረንን በማስፈራራት ላይ የተመሰረተ ነው። ለራሱ ክብር የሌለው ሰው ሁለቱንም ሲያደርግ ልታየው ትችላለህ፤ ከዚህ ለራሱ ክብር ከሌለው ሰው ያነሰው ሰው ደሞ በዚህ ክብረ ነክ የሚደርስበትን ዘለፋ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በመፍራት እንደ ቀንድ አውጣ ብርድልብሱ ውስጥ ተደብቆ «ፖለቲካ ለምኔ» ሲል ልታገኘው (ልታየው) ትችላለህ። በዚህ የመፍራት እና የማስፈራራት ትብታብ የተጠመዱት፣ የወደቁት እና መነሳት ያቃታቸው፤ በግሩፕ ዘለፋ፣ በህዝባዊ ዛቻ እና በግብረ ኃይል ጥላቻ ከሜዳ እንዲወጡ የተደረጉት እና እጅ ሰጥተው የወጡት (የወደቁት)፤ በኔ ዕይታ የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና ምን እንደሆነ የማያውቁ ናቸው። በኔ ግንዛቤ «ተሳዳቢው» ከኔ በኢትዮጵያዊነት ይበልጣል ብለው ያመኑ ናቸው፤ ተቀጣሪው ወይም አቃጣሪው የተሻለ የሰውነት አቅም አለው ብለው ሽንፈትን የተቀበሉ ደካሞች ናቸው። ይህ ግን ልክ አይደለም።

በሀገራችንም ሆነ ከሀገራችን ውጭ፤ ሀገራችንን በተመለከተ የሚደረግ ማንኛቸውም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባችንን የመሰንዘርም ሆነ ቢሆን ጥሩ ነው ብለን የምናስበውን ነገር የመናገር መብት አለን። ይህንን መብት መለስ ዜናዊ አልሰጠኝ፣ አያስጠብቅልኝም፣ ይህንን መብት ብርሃኑ ነጋ አልሰጠኝም፣ ታግሎም አያጎናፅፈኝም!! ይህንን መብት ከማንም ሳይሆን እንደ ሰው ከእግዚያብሔር ያገኘሁት ምንነት ነው፣ ማንነት ነው። ብርሃኑ ቢሳካለት ምናልባት ለተፈጥሮ መብቴ እውቅና ይሰጥ ይሆናል፤ ባይሰጥ ግን እሱ እነ መለስን እንደተቃወመው እኔ ደሞ በተራዬ እሱን እቃወመዋለሁ። ያንን ያህልም ተራ የምጠብቅ አይመስለኝም እንደውም!

ለሀገራቸው በየበረሃው መስዕዋት እየከፈሉ የሚገኙ ታጋዮች በመጀመሪያ ነፃ የሚያወጡት ራሳቸውን ነው ብዬ ነው የማስበው። የወያኔም ትልቁ ክሽፈት ራሱ ነፃ ሳይወጣ ሌሎችን ነፃ ለማውጣት መታገሉ ላይ ይመስለኛል። የሃሳብ ነፃነትም ሆነ የመሰብሰብ መብት በድህረ ወያኔ ሥርዓት የተነፈግነው፣ እኛ ሳንሆን ወያኔ ራሱ ነፃ ስላልሆነ ነው። እኛማ ነፃ ነን፣ ነፃም ስለሆንን ነው የነፃ ሰው ባህሪ ያሳየነው። የመናገርም ሆነ የመፃፍ ነፃነት የነፃ ሰው ባህሪ ነው። ያንን ማድረግ አትችልም የሚልህ አካል ግን፤ ያንን ነፃነት የማያውቅ እስረኛ ስለሆነ ነው። ለዚህም ይመስለኛል ካርል ማርክስ የዘመናዊ ሰው መነጠል (The Alienation of Modern Man) በተባለው መጥሐፉ፣ “The Germans toured us, used a poison gas to massacre us and even put us in a furnace, it is only because we are free” ያለው።

የምንታሰረው፣ ስንጥፍ የምንነቀፈው፣ ስንናገር የምንፎተተው፣ ስንደፍር «ኩም» አድራጊው የበዛብን፤ እኛ ነፃ ስለሆንን ነው። ለምን፣ እንዴት፣ እንዲህ ባይሆንስ፣ ይሄ ቢሆንስ የሚል ሁል ጊዜም በእንቅልፍ ልቡ የሚኖር ስላለመሆኑ ማሳያ ነው። ስለዚህ ሰድባችሁ የምታቆሙት፣ አብራችሁ የምታስበረግጉት፣ አሲራችሁ የምትጥሉት፣ ወጥናችሁ የምታሰናክሉት ማንነት ትከሻችን አይሸከምም። የተወሰነ ደረጃ መሄድ ትችሉ ይሆናል፤ አራት ወይም አስር ሰዎችን አሳፍሮ ከጫወታ ውጭ ማድረግ ይቻል ይሆናል፤ ሁሉንም ግን በአንድ አይነት መንገድ ማሸነፍ አይቻልም። እንዲህ ያለውን ሰው ለማሸነፍ ብቸኛ መንገዱ ግን መብቱን ማክበር ብቻ ነው።

መልዕክቴ ከወንዚያ ወዲህ ማዶም ወዲያ ማዶም ላላችሁት ነው። መፃፍ፣ ማጋለጥ፣ ማስተማር፣ ክርክር መፍጠር፣ ጠያቂ እና መርማሪ ትውልድ እንዲፈጠር የአቅማችንን ማድረግ እንቀጥላለን። ከዚያ እኩል ተንኮሉ፣ ሴራው፣ ደባው እንደሚኖርም እናውቃለን። ያፈቀሩን ለምን ጠሉን ብለን አይደለም የምንታገለው፤ ወይም እንደ አንዳንድ ግብዞች በግሩፕ ፍቅር ሰክሮ፣ በጋርድ እና በከበባ ለመሄድም አይደለም። አላደግንበትም። ከሊስትሮ ጋ ኳስ ተጫውተን፣ ከቆሎ አዟሪ ጋ ተጋፍተን ነው ያደግነው። የህዝብ ልጆች ነን! አስተዳደጋችን አድር ባይነትን አይፈቅድም! ማስመሰልን ደባል አድርጎ መኖር አይችልም። ለድሃ መቆምህን ለማሳየት ስለድሃ አታውራ፤ ከድሃ ጋ ኑር! ከድሃ ጋ ተዋለድ፣ ከድሃ ጋ ብላ፣ ከድሃ ጋ ጠጣ። ስለ ነፃነት መቆምህን ለማሳየት ጥቅስ አትጥቀስ፣ አንተን ጠቅሰው፣ ስህተትህን ነቅሰው የሚናገሩትን የማድመጥ ልምድ ይኑርህ። ሐቀኝነትህን በምታገኘው ላይክ እና በያዝከው ማይክ ልክ አትለካው፤ ሐቀኝነትህን ሌሎችን ለማዳመጥ ባለህ ቅንነት ልክ ለካው! ይሄ ከማላቆመው መልዕክቶቼ ውስጥ አንዱ ነው!

ቸር እንሰንብት!

ሄኖክ የሺጥላ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ