ሄኖክ የሺጥላ

ስደት

ወዳጄ እና ጓደኛዬ በቅርቡ በሱዳን አሳብሮ፣ በሊቢያ በረሃ አቋርጦ፣ በባህር አሳልጦ ጣሊያን፣ ከጣሊያን ደሞ ጀርመን እንደደረሰ አጫወተኝ። እርግጥ የተጓዘው መንገድ፣ ያየው መከራ፣ የቀመሰው ችግር እንዲህ በሁለት መስመር በሱዳን አድርጎ በሊቢያ አቋርጦ ጣሊያን ደረሰ ብሎ እንደማለት ቀላል አይደለም።

ወዳጄ በጉዞ ላይ ሳሉ ስለገጠማቸው ችግር፣ በሊቢያ የአሸዋ ሙቀት በሰዓት 160 ኪ. ሜትር የሚጓዝ መኪና፣ ይህንን ሙቀት መቋቋም አቅቶት መንገድ ላይ ጎማው የፈነዳ እና አሸዋ ውስጥ ሰምጦ የቀረ መኪና፣ ቁጭ እንዳሉ የሞቱ፣ ተንበርክከው የሞቱ። የጫናቸው መኪና ስር ከጠኃይ ለመሸሽ ሲሉ የሚደርስላቸው አጥተው የሞቱ። ሞት በየመንገዱ፣ በየአሸዋው ላይ፣ ዋይ የሚል በሌለበት በበረሃ ንዳድ ዋይ የጥንብ አንሳ ራት የሆኑ ወገኖቻችን ምን እንደሚመስሉ ተረከልኝ። እያንዳንዱ የታሪኩ መስመር፣ የትዝታው እና የሁኔታው ትውስታ፣ እንባዬን ጨርሼ በደሜ እንዳነባ አደረገኝ።

ለምሳሌ ወዳጄ አዲሱ ያካፈለኝን ሁለት ታሪኮችን ላካፍላችሁ፤

አዲሱ ታሪኩን እንዲህ ነበር ያወጋኝ

ሱዳንን እቋርጠን ወደ ሊቢያ ስንገሰግስ፣ አይሲስ አለ የሚባልበት አካባቢ እንደደረስን ሰማን። ክርስቲያኖቹ በፍጥነት አንገታችን ላይ ያለውን መስቀል በጥሰን እንድንጥል ተነገረን። እኔና ጓደኞቼ ይህንን መልዕክት ላስተላለፈው ሰው ”እጃችን ላይ ብናስረውስ ብለን ጠየቅነው”። ሰውየው ያ በፍጡም እንደማይሆን ነገረን። በዚህን ጊዜ ”ለምን በጥሰን ካልሲያችን ውስጥ እንደብቀው” አልን። እሱንም አደረግን። ይኽንን ባደረግን ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አይሲሶች ወደተጫንንበት መኪና የጦር መኪናዎቻቸውን እየጋለቡ መጡ። ሁላችንም ከተጫንበት መኪና ላይ እንድንወርድ አዘዙን። የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ”ሙስሊም ናችሁ ወይ” የሚል ነበር። ሰውነቴ ብርክ ብርክ አለው፣ እግሬ ራደ፣ በይበልጥ ደሞ አይሲሶቹ ከኛ ቀደም ብለው የያዟቸውን ክርስቲያን ኢትዮጵያዊያኖች የኋሊዮሽ የፊጥኝ አስረዋቸው በክፍት ኦራል ላይ ጥቅጥቅ አድርገው ጭነዋቸው ይታዩ ነበር። ልጆቹ ከታሰሩበት መኪና ላይ ሆነው፣ እያነቡ ”ሙስሊም ነን በሉ፣ ሙስሊም ነን በሉ!!” እያሉ ይጮኻሉ። ልጆቹ የሚሉትን ስሰማ በለሆሳስ ”ኦሮማይ!!” አልኩ።

የመጨረሻ የስንብት ቃሌን ለአምላኬ አቀረብኩ። ገብርኤልን ተዓምራቱን ያሳየኝ ዘንድ ተማጠንኩት። የአይሲሱ ዋርድያ መኪናችን እንዲቆም ምልክት ሰጠ። ዘመናዊ መሣሪያው፣ የለበሰው ጥቁር የወታደራዊ ልብሱ፣ ፊቱን የሸፈነበት መልኩ ሁሉ ከዚህ በፊት አይሲስ ተብለው ስላየኋቸው ሰዎች በድረ ገጥ ላይ ከተለቀቀው ጋ ፍጡም አንድ አይነት ነው። ጭካኔ ፊቱ ላይ ይነበባል። ሁለት ወይም ሦስት ጓደኞቹ መኪና ላይ የኋሊት ታስረው የተጫኑትን ኢትዮጵያዊያኖች ባይናቸው ይቆጣጠራሉ። ከመኪናው እንድንወርድ በመሣሪያው አፈሙዝ አዘዘን። ከዚያም ”ሙስሊም ናችሁ?” ብሎ ሲጠይቅ፣ ከዚህ ቀደም በሳዑዲ ዐረቢያ የኖረ አንድ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊ ቀደም ብሎ በዐረብኛ ”አይዋ! ”አዎ!” ሙስሊሞች ነን” አለው።

አይሲሱ ቀጥሎም ”በቀን ስንት ግዜ ይሰገዳል?” አለው፣ ልጁ መለሰለት። ”ቂብላ ወዴት ነው አለው?” አሁንም መለሰለት። ከዚያ ”ሁላችሁም በአፈር ”ኡዱ አድርጉ አለን” ደግነቱ የሁላችንንም እንቅስቃሴ ማየት አልቻለም፣ ያም ቢሆን የጠየቀውን አደረግንለት፣ ከዚያ ”ማሽ ኣላህ” አለ፣ ሙስሊም መሆናችንን ባረጋገጠ መንፈስ። እናም ወደምንሄድበት እንድንሄድ ለቀቁን።

ከበስተጀርባዬ፣ በአይሲስ መኪና ላይ የፊጥኝ የኋሊዮሽ ታስረው የሚያለቅሱት ኢትዮጵያዊያኖች ድምፅ ይሰማኛል። መኪናችን ወደፊት መገስገስ ጀመረ፣ የልጆቹ የጣር ድምጥ በአሸዋ ውስጥ ተውጦ ሲቀር ልቤን አንዳች ነገር ተሰማው። የነዚህ ልጆች እናት እና አባት ልጆቻቸው አንገት ላይ ካራ ሲወደር ምን ይሰማቸው ይሆን አልኩ። የእናታቸው አንጀት እንዴት ይማታ ይሆን? ወይ ሰው መሆን። በአፈር ላይ ዑዱ ሕይወቴን አትርፌ ወደ ባህር ዳርቻው መገስገስ ቀጠልን።

ወደ አመሻሹ ላይ ከመርከብ አገናኞቹ ጋ ተገናኘን። 1900 የአሜሪካን ዶላር ወደ ጣሊያን ለምናደርገው ጉዞ ቀድመን ለኢትዮጵያዊያን ደላሎች ከፍለን ነበር። ከኢትዮጵያ የሱዳንን በረሃ አልፎ የሊቢያ ጠረፍ ለመድረስ ደሞ 1200 ዶላር ከፍለናል። ኢትዮጵያዊው ደላላ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋ ትስስር ያለው ሰው ነው። አንደበቱም ያንን ነው የሚያንጠባርቀው። ሊቢያ ስንደርስ ስለሚገጥመን መርከብ ሲነግረን ”መርከቡ በቃ ታይታኒክን በለው!” ነበር ያለን። ወደ መርከብ መጫኛችን ደርሰን መርከቡ የተባለውን ነገር ስናየው፣ ከእንጨት የተሠራ፣ ከቆሻሻ ገንዳ ምናልባት በአንድ ሜትር የሚበልጥ ጠባብ ታንኳ ነበር። በዚች እጅግ ጠባብ በሆነች የውሃ ታንኳ ውስጥ 1500 ሰው ከመርከቡ የላይና የታችኛ ክፍል ታጭቆ ጉዞ ወደ ጣሊያን ጀመርን።

ወደ ጣሊያን ጉዞ በጀመርን ምናልባት በ20 ወይም ሰላሳ ሰዓታት ውስጥ ”የመርከቡ” የታችኛው ክፍል ውሃ ማስገባት ጀመረ። ውሃው የተለያዩ ዝቃጮች ይራገፉበት የነበረ (የሆነ) ስለሆነ፣ ሰውነትህን ሲነካው የመለብለብ ስሜት ይሰማኻል። ከመርከቡ የታችኛው ክፍል ያሉት ልጆች ውሃውን በባሊ እየቀዱ ለኛ ይሰጡናል፣ እኛ ደሞ እንደፋለን። ይኽ ለሰዓታት ቀጠለ። አንድ የማነ የሚባል ልጅ ውሃው ሰውነቱን ሸፍኖት ስለነበር እየተዳከመ መጣ። አብሮ ሰደድ እንደመሆናችን ከመርከቡ ላይኛው ክፍል ላይ ጮክ ብዬ ”አይዞን የማነ” እለዋለሁ። የሚሰማኝ ግን አይመስለኝም። መርከቡ ውስጥ የሚገባው የውሃ መጠን ከጫናቸው 1500 ሰዎች ጋ ተዳምሮ፣ ቀስ እያለ ማዘቅዘቅ ጀመረ። ይኽ የመጨረሻችን እንደሆነ ገመትኩ። ትንፋሼን ሰብስቤ ተስፋ በቆረጠ አንደበት ጠሎት ማድረስ ጀመርኩ። እንዳንዶች ”እናቴ አንቺን ልረዳ ብዬ እንደወጣሁ ቀረሁ” እያሉ ያለቅሳሉ፣ አንዳንዱ በተደራረበው መከራ በድን ኹኖ፣ በዝምታ ተውጧል፣ አንዳንዱ በሕይወት ዘመኑ ጠርቶት የማያውቀውን ሁሉ ታቦት ይጠራል፣ አንዳንዱ ”ምነው እግሬን በቆረጠው” እያለ ሰፊ ባህር ላይ፣ ለመስጠም ያዘቀዘቀ መርከብ ላይም ሆኖ ይጠጠታል።

መርከባችን መንቋቋት ጀመረች። ያ ከሱዳን ገንዘባችንን ተቀብሎ መርከቡን ”ታይታኒክ ማለት ነው” ያለን (ኢትዮጵያዊ ማለት ቢቀፈኝም) ኢትዮጵያዊ የመርከብ ደላላ የተናገረው እውነት እንደሆነ አሁን ገባኝ። ኣዎ! ይህ መርከብ ታይታኒክ ነው። ሊያደርስ ሳይሆን ሊሰጥም የተሠራ መርከብ። ማዕበል እያወዛወዝን፣ ጭንቀት እንዳፈዘዘን ሞታችንን እንጠባበቅ ጀመር። ስንሰምጥ እንዴት እንደምንወራጭ፣ ውሃው ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰውነታችንን እንዴት እንደሚለበልበው፣ በባህሩ ውስጥ በሐበሻ ስጋ የደለቡት ሻርኮች እንደ እርዙ ወደ ባህሩ በራሱ ጊዜ በሚደፋላቸው የኢትዮጵያዊ ስጋ በደስታ ሲሳከሩ፣ በክንፎቻቸው እየሞሸለቁ፣ በተሳለ ጥርሶቻቸው ሲቆርጡን ታየኝ። ምግብ ከበላሁ ቀናት ያለፈኝ ቢሆንም፣ ሆዴን አቅለሸለሸኝ። የራብተኛ ትውከት ሃሞት ነውና፣ ሃሞት ወደላይ ተንደርድሮ መጥቶ ላንቃዬን አስከፈተኝ። የጭንቀት እንባ አለቀስኩ። ተናደድኩ። አዎ! በሀገሬ ተናደድኩ፣ ህዝቦቹን መመገብ ሳይችል ፎቅ በሚሠራው መንግሥት ላይ ጥርሴን ነከስኩ፣ በየአሸዋው ላይ ዜጎቹ ተበትነው ስለ እድገት በሚያወራው ሥርዓት የምሬን ተበሳጨኹ። ምን ዋጋ አለው ታዲያ፣ ቁጣዬ ላይቀጣጠል፣ ንዴቴ ላይሰማ፣ ወደ ባህር ሊሰምጥ፣ ውሃ መሃል ቁልቁል እየተሳበ ከቆመ መርከብ ላይ ሆኘ ነውና የተቆጣሁት፣ ቁጣዬን እንባ ሲቀማኝ፣ ተስፋ ቢስነት ሲነጥቀኝ ይሰማኛል።

ታዲያ በዚህ የተስፋ መቁረጥ ሰዓት፣ ከየት መጣ ሳይባል ከፊት ለፊታችን አንድ ትልቅ መርከብ ቆሞ መብራት አበራ። ሰው ቀኑ ካልደረሰ እንደማይሞት ለመጀመሪያ ጊዜ በፍጡም ልቤ አመንኩ። መርከቡ፣ የምንጓዝበት መርከብ እንደተቀደደ (ውሃ እያስገባ እንደሆነ) አስረዳነው። የኛን መርከብ ከነሱ መርከብ ጋ አሰሩት። እየጎተቱ ወደ መርከቡ አስጠጉን፣ በቀስታ አንድ በአንድ ወደ መርከቡ ጫኑን። የማነ በጣም ተዳክሞ ስለነበር፣ በጓደኞቹ ድጋፍ በሸክም ወደ መርከቡ ላይ ወጣን፣ በግምት ወደ ሁለት ቀን ተኩል ከተጓዝን በኋላ ጣሊያን ደረስን።

”እንባ እንባ ይለኛል
ይተናነቀኛል
ግን እንባ እንኳን የት አባቱ
ደርቋል ከረጢቱ
ሳቅ ሳቅም ይለኛል
ስቆ ላይስቅ ጥርሴ
ስቃ እያለቀሰች መከረኛ ነብሴ”

ነው ያለው ጠሐፊው?

(ይቀጥላል)


የግርጌ ማስታወሻ፤

በዚህ ጥሑፍ ላይ ያለውን ፎቶ ወዳጄ አዲሱ ነው የላከልኝ። የተለጠፈውም በሱ ፍቃድ ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!