ይገረም አለሙ

አቶ ግርማ ሠይፉ ማሩ / Girma Seifu Maru

ከ2002 ዓ.ም. እስከ እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ "ለዴሞክራሲ ሥርዓት ምን ዓይነት ፓርቲ ያስፈልገናል?" በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ጽሁፍ ለማንበብ የጓጓሁት የአንድነት ም/ሊቀመንበር ነበሩና ከተግባር ተሞክሮአቸው በመነሳት ድክመት ጥንካሬን መለስ ብለው ቃኝተው መሆን ያለበትን ያመላክታሉ በሚል ነበር።

ነገር ግን የአቶ ግርማ ጽሁፍ በአብዛኛው ያተኮረው በአንድነት ፍርስራሽ ላይ “የፎርጅድ ኮፒ” ያሉት ነጻነት የሚባል ፓርቲ መመስረቱን፣ ይሄው ፓርቲ መድረክ ውስጥ ያለውን የአማራ ክፍተት ስለሚሞላ ከመድረክ ድጋፍ እንዳለው፤ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሲኮን በተለይም አመራር ሲኮን በቀጣይ የመንግሥትን ሥልጣን ለመያዝ መዘጋጀትን እንደሚጠይቅ፤ በአሁኑ ወቅት በዚህ ልክ እራሳቸውን ያዘጋጁ የገዢው ፓርቲም ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነና ርሳቸው ም/ል ሊቀመንበር የነበሩበት አንድነት ፓርቲ ግን ለዚህ ብቃቱ እንደነበረው በመግለጽ ነው።

መግባባት ሳይሆን መነታረክ መታወቂያችን የሆነው ከማንስማማባቸው እየጀመርን ነውና፤ ከምስማማበት ልጀምር፣ ፓርቲ “… አባላትን በማብዛት ሳይሆን ምርጦች የሚሰበሰቡበት፣ ለጥቅም ሳይሆን “ለአቅመ መስጠት” የደረሱ፤ በእውቀታቸው እና ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው አልፈው ለዜጎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ የሚጨነቁ ብቻ ሳይሆን አማራጭ መፍትሔ የሚያቀርቡ፣ በየደረጃው ለፖለቲካ አመራር የሚሰባሰቡበት መሆን ይኖርበታል።” ባሉት ሃሳብ እስማማለሁ። ግን ሁለት ጥያቄዎች አሉኝ። አንደኛ - ምርጦች እነማን ናቸው? በማን ነው የሚመረጡት? መስፈርቱስ ምንድን ነው? ሁለተኛ - በፓርቲ ውስጥ መሰባሰብ ለትግል ወይንስ ለፖለቲካ አመራር? ሁሉም ታጋይ መሆን አለበት ይችላልም ሁሉም፣ አመራር ሰጪ መሆን ግን አይችልምና።

እታገልለታለሁ የሚለውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ በተግባር የሚታይ እንቅስቃሴ የማያደርግ ፓርቲም ይሁን የሙያ ማኅበር መፍረስ አለበት በሚለው የአቶ ግርማ ሃሳብም እስማማለሁ። ፓርቲዎች የጡረታ ግዜ ማሳለፊያ መሆን የለባቸውም፣ የወጣቶች ፍሬያማ ግዜ በከንቱ የሚባክንባቸው ሊሆኑ አይገባም በሚለውም ሃሳባቸው እንደዚሁ እስማማለሁ። ግን ወጣቶችንና ጡረታን በተመለከተ ጥያቄ አለኝ። አቶ ግርማ ይህ ያሉት እንዳይሆን የአንድነት ም/ሊቀመንበር በነበሩባቸው ዓመታት ምን አደረጉ? ወጣትነታቸውን በአንድነት ያሳለፉትና ታስረው መከራ ስቃይ ያዩት፤ አቶ ዳንኤል ሽበሺና አቶ ሀብታሙ አያሌው ከእስር ቤት ሲወጡ መግቢያ ላጡበት ድርጊት አቶ ግርማ የድርሻ ኃላፊነት የለባቸውም?

አቶ ግርማ ሲጽፉ ትናንትን መለስ ብለው ማስታወስ የሚቸግራቸው ይመስላል። ያ ባይሆን ትናንት የደገፉትን ዛሬ ሲነቅፉ፣ ትናንት የተናገሩትን ዛሬ ሲገድፉ ወዘተ ትንሽም ቢሆን የተጠያቂነት ስሜት ሊያድርባቸው በተገባ ነበር። ለይቅርታ ድፍረቱ ባይኖር ሾላ በደፈናው እንዲህ ያደረግነውን ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው ትክክል አለመሆኑን ተረድተናል ይባላል። ይህን በማስረጃ ላቅርብ፤ በተጠቀሰው ጽሁፋቸው ውስጥ በግል ለዶ/ር በየነና ለዶ/ር መረራ፣ በጥቅል ለመድረክ ጥሩ ስሜት እንደሌላቸው በግልጽ ይታያል። ይህንንም “አንድነትን ገፍትሮ ያስወጣው የፕሮፌሠር በየነ እና የዶክተር መረራ መድረክ አሁን ለነፃነት ፓርቲ ምስረታ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል” የሚለው አገላለጻቸው ይነግረናል።

መድረክንም ሆነ ሰዎቹን በቅርብ ያውቁዋቸዋልና ለምን ጠሉዋቸው ማለት አልችልም። ነገር ግን አንድነት ወደ መድረክ የሚገባው በጥቂት መሪዎች ፍላጎት ሳይሆን በሥርዓት መሆን አለበት ብለው የተቃወሙ ሰዎችን በብርቱ ካወገዙትና ከፈረጁት ሰዎች አንዱ አቶ ግርማ እንደነበሩ በወቅቱ አንብበናል፤ በመጽሐፋቸውም ገልጸውታል። ስለሆነም ዛሬ በዚህ መልኩ ስለ መድረክና መሪዎቹ በጥላቻ ሲጽፉ፤ ይሆናል ብለን ያደረግነው ሳይሆን ቀረ ብሎ ተጠያቂነትን መውሰድ ትልቅነት ነበር።

ሌላው አቶ ግርማ በየጽሁፋቸው የሚያነሱት በተጠቀሰው ጽሁፍም ላይ በቀጥታም በተዘዋዋሪም የገልጹት ርሳቸው ቆራጥና ሐቀኛ ፖለቲከኛ እንደሆኑና፤ ፓርቲያቸው አንድነትም ጠንካራ ፓርቲ እንደነበረ ነው። ይህ ደግሞ ራስን ለማየት የማያስችለው ዶ/ር መረራ “የቡዳ ፖለቲካ” የሚሉት ለዘመናት ያልተለየን በሽታ ነው። አቶ ግርማ እንደሚሉት አንድነት ርሳቸውን የመሰለ ፖለቲከኛ በም/ሊቀመንበርነት የሚመራውና በአለት ላይ የቆመ ጠንካራ ፓርቲ ከሆነ፤ እንደምን በቀላል አውሎ ነፋስ ተገረሰሰ ብሎ ጠይቆ መልሱን በስሜት ሳይሆን በእውነት ለመፈለግ ከተሞከረ፤ የሚገኘው ውጤት ተቃራኒ ነው። ለዚህም ከብዙ በጥቂቱ ከቅርብ ወደ ሩቅ ሦስት ማስረጃዎችን ላቅርብ።

አንደኛ፤ አንድነት እንዳይሆኑ ከሆነ በኋላ በወቅቱ ተ/ም/ሊቀመንበር የነበሩት (ማለትም በአቶ በላይ እና በአቶ ግርማ መካከል) አቶ ተክሌ ለአንድነት መፍረስ ሁላችንም የድርሻ ተጠያቂነት አለብን በማለት፤ ሌላው ቢቀር የአመራር ምርጫ ቃለ ጉባዔን ምርጫ ቦርድ ሳያስገቡ ሰባት ወራት መቆየት ድክመት መሆኑን ገለጹ። አቶ ግርማ ለዚህ የሰጡት ምላሽ፤ ይህ ድክመት ተብሎ ሊጠቀስ አይችልም የሚል ነበር። ታዲያ! ቃለ ጉባዔ አዘጋጅተው ከቀበና ቢሮአቸው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አጠገብ ለሚገኘው ምርጫ ቦርድ ለማድረስ ሰባት ወራት የፈጀባቸውና ይህንንም ድክመት አይደለም ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ይመሩት የነበረ ፓርቲ ጠንካራ ነበር ሲባል እንደምን ሕሊና ይቀበላል።

ሁለተኛ፤ ለአንድነት መፍረስ አብይ ምክንያት የሆነው የኢ/ር ግዛቸው ከሊቀመንበርነት መገፋት/መልቀቅ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ የመኢአድ አንድነት የውህደት ድርድር ይሳካ አይሳካ ገና ሳይታወቅ፣ የመኢኢድ ሰዎችም የውህዱ ፓርቲ መሪ የመሆን መብት እንዳላቸው ከግምት ውስጥ ሳይገባ፣ በጠቅላላ ጉባዔ መመረጡም ተዘንግቶ ፓርቲዎቹ ሲዋሀዱ መሪ የሚሆነው ግዛቸው ነው የለም በላይ ነው በሚል የተፈጠረው የተካረረ ሽኩቻ ባስከተለው ችግር ነው። በሌለ ሥልጣን ጎራ ለይተው ጦርነት በመግጠም ራሳቸውን ለጥቃት አጋልጠው አንድነትን ለመፍረስ ያበቁ ሰዎች ሀገራዊ ሥልጣን ለመያዝ ብቁም ዝግጁም ነበሩ/ነበርን ሲባል እንዴት አምኖ መቀበል ይቻላል።

ሦስተኛ፤ በ2000 ዓ.ም. የአንድነት አመራሮች የታሰረችውን ሊቀመንበራቸውን ካዱ፣ በሥልጣን ባለጉ ወዘተ በማለት አንድነትን ለማስተካከል እየታገልን ነው አግዙን እያሉ፤ በየኢሜይላችን መልዕክት ይልኩ የነበሩት የያኔው ዝም አንልም መርኅ ይከበሮች ስለ አቶ ግርማ የገለጹት፤ የተማረ ወጣት በመሆኑ የአሮጌው አስተሳሰብ ምርኮኛ አይሆንም ለእውነት ይቆማል ብለን ብናማክረው “ተዉኝ እኔ የመርካቶ ልጅ ነኝ፤ ጭንቅ አልችልም” አለን በማለት ነበር። ታዲያ እኝህ ሰው ከአንድነት መፍረስ በኋላ በየምክንያቱ ብቅ እያሉ ሌላውን እየፈረጁ፣ እየዘለፉና እያናናቁ፤ ራሳቸውን እውነተኛ ታጋይ ለለውጥ የቆመ አርበኛ ወዘተ አድርገው ሲገልጹ እንዴት እንቀበላቸው።

ያለፈውን መመለስ ባይቻልም ለታሪክ ምስክርነትም ሆነ ለሌላው መማሪያነት የሚበጀው አቶ ተክሌ በገለጹት መሰረት ሁሉም የድርሻ ድርሻውን ወስዶ በእያንዳንዱ ስሜት ውስጥ የነበረውን ሳይሆን በትክክል መሬት ላይ የነበረውን አንድነትን በመግለጽ፤ ለመፍረስ ያበቁትንም ምክንያቶች በሐቅና በድፍረት መናገር/መጻፍ ነው።

ቅዱሱ መጽሐፍም እንዲህ ይላል፤ “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በአለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል፤ ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንንም ቤት ገፋው፤ በአለት ላይም ስለ ተመሰረተ አልወደቀም” (ማቲ/7/24-26-) አዎ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመብቃት በአለት ላይ የቆመ ፓርቲ ያስፈልገናል።

ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያበቃ በአለት ላይ የቆመ ፓርቲ፣

የሚመሰረተው በእምነት እንጂ በስሜት አይደለም። ለመታገያነት እንጂ ለመታወቂያነት ወይንም ለመጠቀሚያነት አይደለም። በዓላማ የሚገናኙበት፣ በቃል ኪዳን የሚተሳሰሩበት እንጂ፤ በጥቅም የሚቆራኙበት፣ በእከክልኝ ልከክልህ የሚተሻሹበትም አይሆንም።

መሪዎቹ፣ የምን-ይልክን ቤተ መንግሥት አንጋጠው እያዩ ሳይሆን ዝቅ ብለው ሕብረተሰቡን እያስተዋሉ፣ ራሳቸውን ለሥልጣን ለማብቃት ሳይሆን፤ የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመስረት፣ ከምቾት ባሻገር ለመታገል የወሰኑና ራሳቸውን ለትግሉ የሰጡ ናቸው።

አባሉ፣ ወያኔን በመጥላት ሳይሆን ሀገራዊ ለውጥ በመሻት፤ በስሜት ሳይሆን በእምነት፤ በወረት ሳይሆን በዓላማ፤ የመሪዎች ተከታይ ሳይሆን የፓርቲ አባል በመሆን የሚደራጅበት ነው፤

አሠራሩ፣ ፕሮግራሙ ተፈጻሚ የሚሆንበት፣ ደንቡ የሚከበርበት፣ ውይይት ባህል የሆነበት፣ ቃልና ተግባር የሚዛመዱበት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት፣ ወዘተ ነው። እንዲህ አይነት ፓርቲ እስካሁን አላየንም፤ ወደፊትም በእኛ ዕድሜ ማየት የምንችል አይመስለኝም። ይህም ነው ካለፈው ይበልጥ መጪውን አሳሳቢ የሚያደርገው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ