ዓሊ ጓንጉል

“... ሃያዎቹ መጨረሻ ላይ ያለ፣ በፊቱ የተደፋ፣ እጆቹን ወደፊት ዘርግቶ፣ ... ልብሱ በደም እና አቧራ የጨቀየ ኢትዮጵያዊ ... አስከሬን መንገድ ዳር ወድቋል፣ ሰውየው ጫማ፣ ገንዘብ፣ መታወቂያ የለውም። ለአርብ ጸሎት የሚሄዱት ሰዎች በሚያዩት አዝነዋል፣ ግን የገረማቸው አይመስሉም ...” ይህ በትናንትናው ዕለት (august 31/2016) በኒውስዊክ መጽሔት ላይ ከወጣ የዜና ዘገባ የተወሰደ ነው። ርዕሱ “ጦርነትን የሸሹ የመናዊያን እና ድርቅን የሸሹ ኢትዮጵያዊያን ጅቡቲ ላይ ተገናኙ” ነው የሚለው።

የመናዊያኑ ጦርነት ሸሽተው ጅቡቲ እየመጡ ባሉበት ወቅት፣ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ወደ የመን የመግባታቸውን ሁኔታ ያየ አንድ ከየመን የጦርነት ወላፈን አምልጦ ጅቡቲ የገባ የመናዊ “ኢትዮጵያዊያን እብዶች ናቸው ...” ነበር ያለው። በዚህ ዘገባ ውስጥ ሦስት ጉዳዮች አስገረሙኝ።

1ኛ) ሟቹ “መታወቂያ የለውም”፦ ስንት ሰው በየበረሃው አለቀ? ስንት ሰው በስንቱ የደቡብ እና ምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች በረሃ የአውሬ እና የሰው አውሬዎች (በየዐረብ ሀገሩ እና በደቡብ አፍሪካ በአደባባይ የሜንጫ/ስለት) ቀለብ ሆነ? ስንት የማይታወቅ ኢትዮጵያዊ አለቀ? የህወሓት መንግሥት እንደ መንግሥት፣ በ25 ዓመት ታሪኩ ውስጥ፣ እስኪ አንድ ቀን! እንዲያው አንዲት ቀን ... “ዜጎቼ በምን ምክንያት ታሰሩ? ተገረፉ? ተገደሉ? ... የተገደለው/የሞተውስ ማን ነው?” ብሎ ጠይቆ የሚያውቅበትን አንድ ጊዜ የሚጠቅስልኝ ሰው ማን ነው? ምን መታወቂያ አለን? እንታወቃለን? በርካታ ኢትዮጵያዊያን ያኔ በደቡብ አፍሪካ በአደባባይ በእሳት ነደው እና በሜንጫ ስለት ተጨፍጭፈው በተገደሉበት ሰሞን፣ አንድ ሶማሊያዊ እንዲሁ ሞቶ ነበር። መንግሥት የሌላት የምትባለው ሀገር የሶማሊያ የወቅቱ የሽግግር መሪዎች ደቡብ አፍሪካን ስለዜጋቸው ሞት ማብራሪያ መጠየቃቸውን አስታውሳለሁ።

2ኛ) በጅቡቲ ጎዳና ለአርብ ጸሎት የሚሄዱት ሰዎች የኢትዮጵያዊውን አስከሬን እያዩ “... አልተገረሙም ...”፦ ምን ይገርማል? የኢትዮጵያዊ ስደት እና ሞት፣ በረሃብ መሞት የተለመደ አይደል እንዴ? በየሚዲያው ሁልጊዜ የሚታይ እና የሚሰማ የኢትዮጵያዊያን ሞት ዜና እንዴት ይገርማል? አንዳንዴ የማይገርም ነገርም እንዲህ ይገርማል፤ እናም እኛንም የማይገርመን መሆኑ ራሱ ገረመኝ።

3ኛ) “ኢትዮጵያዊያን እብዶች ናቸው”፦ ለየመናዊው እብደት ነው። ወደ የመን እና ሳውዲ ዐረቢያ ለመሻገር፣ አሻጋሪዎቹን እየተጠባበቀ ላለው የሰላሳ ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ገበሬ ካሊል እና የመንደሩ ልጆች ግን እብደት አይደለም። ካሊል የመናዊያን እየሸሹ ከሚወጡበት ሀገር የመን ውስጥ መግባት አደገኛ መሆኑን ሲነግሩት፤ “የተወለድኩበት መንደሬ ውስጥ ካለው ነገር የከፋ ምንም ነገር አይኖርም ...” ነበር ያለው።

እየሞተ ያለ ሰው ሞት አይፈራም። ህወሓቶች ያልገባቸው ነገር ይኼ ይመስለኛል። ከሀገር ቤትም ወጥተው ሞት እንደሚጠብቃቸው እየተገነዘቡ የሚሄዱ እንደ ካሊል ያሉ ዜጎች እየተበራከቱ በሄዱ ቁጥር፣ ... እዚህም እዚያም ሞት እንደሚጠብቃቸው የተገነዘቡ ሰዎች ሞትን አይፈሩም። ህወሓት በተፈጥሮው መቻቻልን የማያውቅ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በሀገር እና ህዝብ ላይ ያደረሰው በደል እና ግፍ መብዛት እና መግዘፍ ምክንያት ብቻ ካሁን በኋላ ተቻችሎ መሥራት የሚሉ ማደናገሪያውን ለመስማት ጆሮውን የሚሰጠው ህዝብም አያገኝም። ባጭሩ ህወሓት እና የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያየ መንገድ “no turn” መንገድ ላይ ደርሰዋል። ህወሓት አንድ ሰላማዊ ሰው በገደለ እና ባደማ ቁጥር፣ በገዛ ሠራዊቱ ውስጥ ያለው አንድ ታጣቂ ወታደር ልብ ይደማል። ... እናም ህወሓት ይወድቃል። አሳሳቢው ነገር፣ በኢሳቱ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ቋንቋ “ህወሓት እንዳይወድቅብን” ምን እናድርግ? ነው።

ምላሻቸው ምን እንደነበር ባይነግሩንም፤ “ሌላው የኢትዮጵያ ቀሪ ህዝብ የኦሮሞን ትግል የማይቀላቀለው ለምንድነው? ለወደፊቱስ ህዝቡን ለማስተባበር ምን ታስቧል?” የሚል ጥያቄ ከተሳታፊዎች እንደቀረበላቸው በኢሳት የነገሩን ፕሮፌሠር መረራ ጉዲና ናቸው። እኔ ፕሮፌሠሩን ወይም ከኦሮሞ ነገድ ልሂቃን አንዱን ብሆን ኖሮ “የኦሮሞ ህዝብ ሆይ! ህወሓት የተከለውን የጡት ቆረጣውን ሐውልት አፍርሰን እንጣለው” የሚል መመሪያ አስተላልፍ ነበር - ቢያንስ ለጊዜውም እንኳን ቢሆን ... በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሞት፣ ስደት፣ ረሃብ፣ መከራ ... ለማሳጠር፣ እሠራ ነበር።

አማራ እና ኦሮሞን በጡት ቆረጣ፣ ወላይታ እና ጋሞውን በድንበር፣ አኝዋክ እና ሱርማውን በግጦሽ፣ አፋር እና ኢሳውን በከብት ዘረፋ፣ ቅማንት እና አማራውን በማንነት፣ ትግሬውን “ህወሓት ከሌለ አንተም የለህም! ወየውልህ ...” ወዘተ እያለ እኛን ኢትዮጵያዊያንን እያቆራረጠ እና እያበጣበጠ፣ ብቻውን ማር እየቆረጠ ያለው ... ህወሓት ሲወድቅ በህዝብ ላይ እንዳይወድቅ አደርግ ነበር።

የኦሮሞ ልሂቃን፣ ህወሓት በሐውልት ጭምር እያጋነነ የሚያራግበው እና እንዲህ የዛሬ ሁለት መቶ ዓመት አካባቢ ሆነ የተባለውን የጡት ቆረጣ ለማራገብ ሞራላዊ ድፍረት ያገኙትን ያህል፣ እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ፣ አሜሪካ እምብርት ላይ ሆኖ ዛሬ በ21ኛው ክ/ዘመን “በሜንጫ አንገት” ስለመቁረጥ የፎከረውን ጃዋርን ለማውገዝ ሰብዓዊ ሞራላቸውን የሚያሳዩን መቼ ነው? በሩዋንዳው የRTLM ራድዩ ጣቢያ የጥላቻ እና መሰል መዘዞች ሳቢያ በሩዋንዳ የደረሰውን የርስ በርስ እልቂት ያስታወሰ ሰው፣ የጃዋርን የሜዲያ ኃላፊነት በቀላሉ ማየት የለበትም።

ህወሓት ሲወድቅ እንዳይወድቅብን፣ የጡት ቆረጣውን ሐውልትም ሆነ የጃዋርን የሜንጫ ፉከራ ለማውገዝ አሁንም አልዘገየም።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!